ዳግማዊ ጉዱ ካሣ

ኢትዮጵያን መልሶ ለማነጽና ቢያንስ ወደ ቀደመው ታሪካዊ ሥፍራዋ ለመመለስ የሚያስፈልገውን ግብኣት ቁጭ ብዬ ሳስበው ዙሪያው ገደል ይሆንብኛል፡፡ ይህችን በግፈኞች መዳፍ ሥር ወድቃ በጣር ላይ የምትገኝ  ሀገራችንን እንደገና ለመሥራት ቀና ደፋ የሚሉ ጥቂት ሃቀኛ ዜጎችን ስታዘብ ደግሞ ያሳዝኑኛል – የሚያሳዝኑኝ ዋናው ምክንያት እነሱ ሲገነቡ የዋሉትን የሚያፈርሱ ቁጥር ሥፍር የሌላቸው የእንግዴ ልጆች በውስጥም በውጪም እንደጉንዳን የሚርመሰመሱ መሆናቸውን ስለምረዳ ነው፡፡ እነዚህን መሰል ጥቂት ዜጎች ሀብታቸውን፣ ጊዜያቸውን፣ ህልማቸውን፣ ትምህርታቸውን፣ ቤተሰባቸውን፣ ሕይወታቸውን፣ የግል ዕድገት ብልጽግናቸውን ወዘተ. ዕርግፍ አድርገው ትተው በሀገር ቤትም ሆነ በውጭ፣ በበረሃም ሆነ በከተማ፣ በፖለቲካው ዙሪያም ሆነ በኢኮኖሚውና በማኅበራዊው ዘርፍ ሲማስኑ ሳይ በተቃራኒው ደግሞ እነሱንና ሀገራችንን ለማፍረስ ሌት ከቀን የሚባዝኑትን የለየላቸውን ወያኔን መሰል ጠላቶቻችንንና አስመሳዮችን ስታዘብ ሁሉም ነገር ድብልቅልቅ ይልብኝና ተስፋ እቆርጣለሁ፡፡ አንዳንዴና ሰሞኑን ደግሞ ምንም አዲስ ነገር እንደማላገኝበት በመገመት ከራቅሁት በተለይ የሀገር ውስጥ ሚዲያ ጥሩ ጥሩ ንግግሮችን ስሰማ በማመንና ባለማመን ውስጥ ሆኜ እከታተልና “ይሄ ነገር እውን ይሆን እንዴ?” በማለት እገረማለሁ፡፡ ሀገራችን የትንግርቶችና የንግርቶች መናኸሪያ ሆነችና የምንጨብጠውንና የምንለቀውን አጣን፡፡ ቀስ በቀስ በሁሉም ረገድ ባዶ እየሆነች የመሄዷ ምሥጢር ደግሞ ዕንቅልፍ ይነሣል፡፡ እንግዲህ አልኣዛርን በአራተኛው ቀን ከሞትና ከምሥጦች ዋሻ አስነስቶ ወደ ሕይወት ያመጣው አንድዬ ይታደገን እንጂ በአሁኑ ወቅት ሀገራችንና እኛ “አልሞትንም” ብለን እንደማንዋሽ አምናለሁ፡፡…

ወያኔ ታድሻለሁ አለ፡፡ የኢትዮጵያን ችግሮች የሚፈታ ጠ/ሚ ከድርጅቴ እንዲሾም ፈቅጃለሁ አለ፡፡ ማዕከላዊ እሥር ቤትን ዘግቻለሁ አለ፡፡ ዴሞክራሲን አስፈኛለሁ አለ፡፡ የዜጎችን መብት አከብራለሁ አለ፤ ከእንግዲህ እመኑኝ በጥልቀት ታድሻለሁ አለ፡፡ ብዙ ብዙ አለ፡፡ እኛም ሰማን፤ እዚሁም ስላለን ሁሉን አየን፡፡ የሚባለውና እየሆነ ያለው ግን ምንም ነገር ያልተለወጠ መሆኑን ይጠቁማል፡፡

በአንድ ራስ ሁለት ምላስ ያለው ወያኔ አንድ ነገር እዚህ ሲናገር የንግግሩን ተቃራኒ ነገር እዚያው አጠገብ ያደርጋል፡፡ እጅግ ብዙ ምሣሌ ማቅረብ ቢቻልም በጣም ጥቂቶቹን ላስታውስ፡፡ አዲሱ ጠ/ሚ የሀገራቸውን ዴሞክራሲያዊነትና የመንግሥታቸውን ለሕዝብ  ተቆርቋሪነት በገዛ ምድራቸው እየዞሩ ሲመሰክሩና “ችግራችሁን ከናንተው ትብብር ጋር የዶግ አመድ አደርጋለሁ” በሚሉበት ቅጽበት ወያኔ በደቡብ አፍሪካ ገዛኸኝ ነብሮ የተባለ የሰብኣዊ መብት ተሟጋች በቅጥር ነፍሰ ገዳይ አስገደለና የመለወጣቸውን “ብሥራት በአንጸባራቂ ድል አበሠሩን”፡፡ እኛም ጉድ አልን፡፡ እሥረኞችን እንለቃለን ባሉ ምሽት አንድ ተራ ግን ግሩም ድንቅ ዜጋ – እስክንድር ነጋ – ተጋብዞ ወደ ውጭ ሀገር  ሊሄድ ቦሌ ሲደርስ ሰነዱን ቀምተው ለተወሰነ ጊዜ አገቱትና ቆይተው ለቀቁት፡፡ ይህ የዱርዬ ሥራ እንጂ … የአንድ  ነፍስ ያላወቀ ሕጻን ሊያውም የአእምሮ ታማሚ ሕጻን ተግባር እንጂ …አንድ መንግሥት ነኝ ባይ እንዲህ ያለ የወረደ ቅሌት ውስጥ አይገባም – ሊያውም አዲስ ጠ/ሚ “በተመረጠ” ማግሥት፡፡ በነገራችን ላይ እነዚህ ጉደኛ ወያኔዎች የመንግሥትንና የግለሰብን፣ የድርጅትንና የሀገርን፣ የፖለቲካ ፓርቲነትንና የመንግሥትነትን፣ የስሜትንና የአመክንዮን ወዘተ. ልዩነቶች ሳያውቁ በድንቁርና ተፀንሰው፣ በድንቁርና ተወልደው፣ በድንቁርና ኖረው፣ በድንቁርና አርጅተው፣ በዘረኝነት ልምሻ እንደተሰቃዩና በዱሮ በሬ እንዳረሱ ይህችን ዓለም ሊሰናበቱ መቃረባቸው እንደሰው ያሳዝኑኛል፡፡ ሰዎች አላወቁላቸውም እንጂ ይህ ዓይነት ዕጣ እኮ ትልቅ መረገም ነው – ሥልጣናቸውንና መብላት መጠጣታቸውን ተውት – ከነሱው ጋር የሚያልፍ ነውና፤ ሺህ ሙክት ቢጎሰጉሱ – ሺህ ጠርሙስ ዊስኪ ቢጨልጡ –  ከሺዎች ሴቶች ጋር ቢማግጡ ይህ ሁሉ እንስሳዊ ጠባይና ሰብኣዊ ምግባር ከመቃብር በላይ ዘሩም አይገኝም – ከነርሱ ቀድሞ አፈርና ውኃ ይሆናል፡፡ ሰው ላልሆነ ሰው የሰውነት መለኪያው መሾም መሸለምና መብላት መጠጣት ይመስለዋል፡፡ የዓለም ከንቱነት በወያኔዎች የዱባ ጥጋብና የታሪክ ጉሽ ጠላ ስካር በሚገባ ይገለጣል፡፡ ለከሸፈ ሰውነት አብነቱ ማለትም ምሣሌው የወያኔን አስተሳሰቦችና ድርጊቶች ማየት ብቻ በቂ ነው፡፡

ቅሌት ቀለቡ ወያኔ ታዲያን እንዲህ ይዘቅጣል፡፡ የሀገርን ሀብት እኩል ስለመጠቀምና ሙስናን ስለማጥፋት ጠ/ሚንስትሩ እየሰበኩ ባሉበት ቅጽበት ወያኔዎች ከፍርስራሽ ድልድይ የወጣ የብረት ስብርባሪ ወደ ትግራይ ሲያጓጉዙ ተደርሶባቸው በሕዝብ ትግል መለሱ፡፡ ዕንቆቅልሽ! ከ43 ዓመታትም በኋላ የማይሰክን የእጅ ዐመል! ከ27 ዓመታት የመንግሥትነት ጊዜም በኋላ የማይበርድ የስርቆትና የዘረፋ ሱስ! መጪዋ ትግራይ እንዴቱን ያህል ታፍርባቸው? የነገዋ ኢትዮጵያ በነዚህ ማፈሪያዎች (black sheep) ምን ያህል ትሸማቀቅ?!

ወያኔዎች ጠ/ሚንስትሩን “ውሸታም!” ለማስባል እሳቸው ከሚናገሩት በተቃራኒ የጥንቱን ዕኩይ ተግባራቸውን – የራሳቸውን የወያኔዎችን ማለቴ ነው –  አባብሰው መቀጠላቸውን አልተውም፡፡ ይህንንም የሚያደርጉት ሆን ብለውና በይሁንታ ነው፡፡  We can clearly understand that what they’re doing now is perfectly and purposely planned just to belie the words of the PM, and thereby, to show off their, presumably declining, might within the new cabinet which is believed to be the old wine in the new bottle. And, most of all, their Supreme masters are behind this entire abracadabra and these crooked Woyannes never do anything without the permission, or at least, the consent, of these crooked children of … ኤዲያ እንግሊዝኛውም እንደ እጀ ጠባቤ አጠረኝሳ በል… “ወዳገሬ መልሽኝ” አለ አሉ አንዱ እንደኔ ቢጨንቀው … ለማንቻውም  ማዕከላዊ ቢዘጋ የእያንዳንዱ ሰላይና ወያኔን ደጋፊ ትግሬ ቤት እሥር ቤትና ማሰቃያ ሥፍራ ነው – ወገኖቼ አንሞኝ ወያኔ ካልተወገደ የወያኔ ዕኩይ ተግባራት በመፈክርና በጉልቻ መለዋወጥ አይጠፉም፡፡ በወያኔ አስተሳሰብና እምነት The current Ethiopia is synonymous with Tigre/Tigray. ስለዚህ እንደነዚህ ደነዞች እምነት የእያንዳንዱ ትግሬ ቤት በንግድ ስም ካለቀረጥ የገባና ከዜጎች የተቀማ/የተመዘበረ የኢትዮጵያ ዕቃ ማጎሪያ ብቻ ሣይሆን የንጹሓን ሰዎች መገረፊያና መሰቃያም ነው፡፡ ይህ እውነታ በብዙ የስቃዩ ሰለባዎች የተመሰከረና በመዝገብ የተያዘ ስለሆነ ጊዜው ሲደርስ እነማን የወያኔ ቀኝ እጆች እንደነበሩና በዘረኝነት ልጓም ተቀፍደው ስንቶችን ለሞትና ለስቃይ እንደዳረጉ ወደፊት የሚገለጥ ይሆናል፡፡ ያኔ ታሪክ ፊቱን ሲያዞር …

አሁን ዝናብና ፀሐይ በኢትዮጵያ ሰማይ በአንዴ እየታዩ ነው – አለወጉ! እንዲህ ሲያጋጥም ዱሮ በልጅነት “ጅብ ወለደች” እንል ነበር፡፡  የሚገርማችሁ አንዴ ወደ መተከል ብቅ ብዬ ከኃይለኛ ዝናብ በላስቲክ ተጠልለን ሳለ አናታችንን የሚሰነጥቅ ፀሐይ ደግሞ ነበረ፡፡ አያዎ ነው፡፡ የማይታመን የፀሐይና የዝናብ መገጣጠም፡፡ ማለት የፈለግሁት የዶር. አቢይና የወያኔ የብርሃንና የጨለማ ኅብረት እስከምን ሊጓዝ እንደሚችል ያለኝን አግራሞት ለመግለጽ ነው፡፡ አቢይ ወያኔንም የኢትዮጵያን ሕዝብም በአንዴ ልታስደስት የፈለገች ይመስላል፡፡ በቅርብ ርቀት ግን በአንደኛቸው መርበብ ውስጥ ትገባለች የሚል ሥጋት አለኝ – ስታሳዝን! አዎ፣ አቢይ እንደታናሽ ወንድምና እንደዜጋ በጣም ያሳዝነኛል፡፡ እንደ ጠ/ሚ ደግሞ በጣም ያሳዝኑኛል፡፡ አያዎ ማለት እንዲህም ነዋ! ሁለት ተቃራኒ ነገሮችን ለማስደሰት እንደመሞከር  ክፉ ነገር ደግሞ የለም፡፡ አሥራ ሦስት ደቂቃ በትግርኛ ከተናገሩ 13 ደቂቃ በቤንሻንጉልኛና በሌሎችም ቋንቋዎች መናገር ነበረባቸው – ይህ የሀገርና የፖለቲካ ጉዳይ እንጂ ቋንቋ አጥርቶም ሆነ አጎላድፎ የመናገር ጉዳይ አይደለምና፤ በዚያ ላይ ደግሞ… ወደይዘት ስንመጣ … ግን ባልተነሳሁበት ጉዳይ ላይ አሁን ምን ጥልቅ አደረገኝ? ግን አቢይን የሚያማክሩ ብልኅ ሰዎች ከጎኑ መኖር ነበረባቸው፡፡

…. ኢትዮጵያ እንደገና ካልተሠራች አሁን ባለችበት ሁኔታ እንደሀገርም እንደሕዝብም ለመቆጠር አትችልም፡፡ ጥቂት አብቶነችን ላሳይ፡፡

ሙስና የትም ሀገር አለ፤ የኛ ግን ለየት ይላል፡፡

የሰማሁት ነው፡፡ ትክክለኛ ታሪክ ስለመሆኑ ጥርጥር የለኝም፡፡ በአንድ ጫካ ውስጥ ሁለት አይሱዙዎች ዕቃ ይቀባበላሉ፡፡ አንድ ገበሬ ያያል፡፡ ለፖሊስ ይጠቁማል፡፡ ፖሊሶች ደርሰው ይፈትሻሉ፡፡ የሚቀባበሉት ነገር ጊዜው ያለፈበትን መድሓኒት ወደገጠሪቱ የወያኔ ኢትዮጵያ ለመውሰድ ነው፡፡ ሹፌሩና የመድሓኒቱ ጌታ ከኤግዚቢቱ ጋር  ይያዛሉ፡፡ ጉዳዩ ትልቅ ሀገራዊ ክስተት እንደመሆኑ ወደፍርድ ቤት ያመራል፡፡ የሙስናውን ሰንሰለት በጣም ባጭሩ ልግለጽ፡፡ ተከሳሹ ክሱ እንዲቋረጥለት ከሚመለከታቸው “የሕዝብ አደራ ጠባቂዎች” ጋር ድርድር ይጀምራል፡፡ በሺዎች የሚገመት ሕዝብ ለመግደል በአይሱዙ ሠይፍና ጎራዴ የጫነ ጀግና ዕድሜ ለገንዘቡ የያዙትንና ለምርመራ የተመደቡትን ፖሊሶች በሶልዲው አንበረከካቸው፡፡ “ምሥክሩን ገበሬ በገንዘብ ካልያዝከው አደጋ አለው” ይሉታል፡፡ የጠቆመውን ገበሬ በአሥር ሺህ ብር ሊደራደረው ይሞክራል፡፡ ገበሬው ግን የተያዘው ነገር ሕዝብን የሚገድል መጥፎ ነገር መሆኑን ስለሰማ አይሆንም ይላል፡፡ ፖሊሶቹ በተዛዋሪ “ምን ችግር አለው፤ ነገርዬው ተወግዷል፤ ሰውየውም ሦስት ወር ስለታሰረ ግፋ ቢል ስድስት ወር ቢፈረድበት ነው ያንንም ይጨርሰዋል፡፡ ይልቁንስ ይጠቅምሃልና አሥራ ሁለት ሺህ ብር ውሰድ” ይሉታል – እነሱ የበሉትን በልተዋልና፡፡ “ገንዘብ የተጫነች አህያ የማትደረምሰው ምሽግ የለም” ይባላልና … ገበሬውን በፍርድ ቤት ውስጥ “ችሎት” ላይ ቃላት እንዲለውጥ አደረጉት – ክሱም በአንዴ ተቀየረ (ትክክለኛ ችሎት በጠፋባት ሀገር “ችሎት” ስል ዝግንን እንደሚለኝ ብጠቁም ደስ ይለኛል)፡፡ ዳኞች ሰምተው ነበርና አንዳች ነገር ሸተታቸው፡፡ “የኛስ ድርሻ?” ከሚል ግልጽ መነሻ አንገራገሩ፡፡ ባለቤቱ ከሦስቱ ዳኞች ለሁለቱ 60 ሺህ ብር ‹አስጨበጣቸው›፡፡ አንደኛው/ዋ ዳኛ ጨረቃ ላይ ቀረ/ች፡፡ በዳኝነት ሂደቱ ፍርዱ ተለሳልሶ ወንጀለኛው በነጻ እንዲለቀቅ ሲወሰን ያልበላው/ችዋ ዳኛ ጮኸ/ች፡፡ ግን ዋጋ የለውም፡፡ የበላ በለጣትና በድምጽ ብልጫ ተሸነፈ/ች (በሬና በግ ጉቦ የሰጡ ከሳሽ-ተከሳሾች ነበሩ አሉ – ዱሮ፤ ባለበጉ ተፈረደበትና “የበጌ ነገር እንዴት ሆነች?” ብሎ ዳኛውን ከችሎት በኋላ ቢጠይቀው “አይ፣ ያንተን በግ ኮርማ በሬ ረግጦ ገደላት!” አለው ይባላል)፡፡ ኢትዮጵያ እንዲህ ናት፡፡ ሕዝበ አዳም እያየህ በአደባባይ ሰው ግደል – ገንዘብ ካለህ ዝምብህን እሽ የሚለው የለም፡፡ በመንደር ውስጥ አፈር እየለነቀጥክ ቅቤ ወይም ማር ነው ብለህ ሽጥ – ገንዘብ ካለህ ማንም አይነካህም፡፡ የሽምብራ ዱቄት ከህንድና ቻይና በምታስመጣው የመድሓኒት ካብሱል እየጠቀጠቅህ አምፒሲሊነ፣ ቴትራሳይክሊንና አሞክሳሲሊን የሚባሉ “መድሓኒቶች”ን በቤትህ ውስጥ አምርተህ ስትሸጥ ብትገኝ ገንዘብ ካለህ ምን ተዳህ! እየሆነ ያለውን ነው የምነግርህ (በልብስና በጫማው፣ … በማይበሉና በማይጠጡ ዕቃዎች የሚሠራውን “ፊንታ”ና ማጭበርበር ተወው፤ እሱ እሱ ለክፉ ስለማይሰጥ በግዴለም እንለፈው)፡፡ ጀሶን ከግድግዳ ማሳመሪያነት አውጥተህ በእንጀራ መልክ የዜጎችን የሆድ ግድግዳ ብታደርቅበትና ወደሞት ብትነዳ ገንዘብ እስካለህ ጠያቂ የለህም፡፡ ሰው በመኪና ገጭተህ ዝምብለህ ሂድ- በኔ ይሁንብህ- ገንዘብህ ቀድሞ ከፖሊስና ከፍርድ ቤት ውጣ ውረድ ናጻ ያወጣሃል – ነፃ፡፡ የፈለግኸውን ዕቃ በመርከብም ይሁን በባቡር ወይም በሮቢላ ከውጭ አስገባ – የገዢው መደብ አባልና የወያኔ ቡችላ ከሆንክ ማን ነክቶህ! ካለቫትና ካለቤት ኪራይ በ“መነገድ” በመጀመሪያ በርካሽ ዋጋ ህጋዊ ነጋዴዎችን አስመርረህ ከጨዋታ ውጪ ታደርግና ኋላ ላይ በውድ ዋጋ ያመጣኸውን ዕቃ አለተቀናቃኝ ከቢጤዎችህ ጋር ሆነህ ትቸበችባለህ፡፡ የአሁኒቱን ኢትዮጵያ ጓዳ ጎድጓዳ የማያውቁ ወይም ሆን ብለው ለማወቅ የማይፈልጉ እኮ ናቸው በሕንጻዎቻቸውና በመንገዶቻችን ምክንያት “ኢትዮጵያ እያደገች ናት” የሚሉን፤ እንጂ ውስጡን ለቄስ፡፡

መንጃ ፈቃድ ለማውጣት ገንዘብ ካለህ መቸገር አይኖርብህም – እቤትህ ድረስ ይመጣልሃል፡፡ በደምብ የተሠራው – ፎርጅድ ያልሆነው ህጋዊው መንጃ ፈቃድ ይደርስሃል – ከፈለግህም ተቀጥተውበት ያመጡልሃል፤ ምን ማለት መሰለህ – መንጃ ፈቃዱ ትራፊክ ፖሊስ ቅጣት እንዲጽፍበት ይደረግና በዚያ መንጃ ፈቃድ – ምዝግብ በመሆኑ – ለጠፋው ጥፋት የተመደበው የቅጣት ገንዘብ ተከፍሎበት ቤትህ ድረስ በተላላኪ ይመጣልሃል ማለት ነው፡፡ አስተማማኝነቱ የተረጋገጠ ነው – ሰው እንድትጨርስበት፡፡ የመንደር ፎርጅድ ሳይሆን መንግሥታዊ ‹ህጋዊ ፎርጅድ› መሆኑ ነው፡፡ “ጠፍተናል” የሚለው ቃል አይገልጸንም – ከአናት እስከ ግርጌ በስብሰናል፤ ባኮረፉ የወያኔ የቀድሞ ጄኔራሎች አገላለጽ ወያኔ አምበሳብሶናል፡፡ ጥሩ ኢትዮጵያዊ ለማግኘት ዓመቱን ሙሉ ብትኳትን የምትፈልገውን  ዓይነት ሰው ለማግኘት ያለህ የመቶኛ ስሌት በዜሮና በአንድ መካከል የሚዋልል ነው፡፡ ግን ግን ይህ ዘመን ያልፍ ይሆን? እንዴት ያስፈራል!

ቤተ ክርስቲያን ግባ፡፡ ከዚህ የባሰ ነው፡፡ የካህናቱን በየ….ቤት የሚወሳልቱትንና የልጆቻችንን ማንነት እስክንጠራጠር ድረስ የሰየጠኑበትን የብልግና ሥራ ለጊዜው እንተወውና በገንዘብ ሙስና ረገድ የሚታየው ጉድ፣ በዘረኝነቱ መስመር የሚሰተዋለው ቅጥ ያጣ ነውረኝነት የእክህደከ ክርስቶስን ሰይጣናዊ ጸሎት ያስመርጣል – ብዙ ሰው ሃይማኖቱን እየተወ ኢ-አማኒ የሚሆነው ወይም ወደማያውቀው ጎራ የሚቀላቀለው ለምን ይመስልሃል? ካለጉቦ አንድም ነገር አይሳካልህም፡፡ ከአንድ ድሃ አጥቢያ ወደ ሀብታም ደብር ለመዛወር በመቶ ሺዎች ሆኗል ጉቦው፡፡ የቀብር ቦታ ለማግኘት፣ ቅስና ለመውሰድ፣ ድቁና ለመቀበል፣ በክህነትም ሆነ በድብትርና ለመቀጠር ፣ አንድን ጉዳይ ለማስፈጸም…. ለኃላፊዎችና ለጳጳሳት ከምናውቃት ስም-አይጠሬ የዓይነት ጉቦ ጀምሮ እስከገንዘብ ድረስ ካልተሰጠና ካልተከፈለ ምንም ነገር አይገኝም፡፡ ኢትዮጵያ እስከዚህን ጠፍታለች፡፡ “አይ! መጥፋት እንዲህ አይደለም” ካልህ የራስህ ጉዳይ፡፡ በትምህርቱ ዘርፍም ብትሄድ ዋናው የዕውቀት አምባ ዋና የድንቁርና ዋሻ ነው፡፡ አድልዖና ዘረኝነት እዚያ ይፈልቃሉና፡፡ ሀገራችንን እስከፒኤችዲ “የተማሩ” ማይማን ዜጎች ወረዋታል፡፡ ከፒኤችዲው ማግሥት የሚኮፈሱና “ዶክ! ዶክዬ፣ ዶክነት…” ብለህ ካልጠራሃቸው በሰዎችም ፊት ካላንቆለጳጰስካቸው አፍንጫቸውን የሚነፉ ብዙ የምሁር ማይማን የሚገኙት ኢትዮጵያ ውስጥ ይመስለኛል፤ (“ኮምፕሌክሴ” ተንጫጫብኝ ይሆን እንዴ ጎበዝ!) ግን ምን ላድርግ? የታዘብኩትን ነው፡፡ እንዲያውም በይሉኝታ ሆን ብዬ ትቼው እንጂ በዚህ ዙሪያ ብዙ ማለት በቻልኩ፡፡ ለነገሩ እንደ ደርግ የመጨረሻ ዘመን ወታደራዊ የማዕረግ ሹመት በ“ከዚህ መልስ ዶክተር፣ ከዚህ መልስ ማስተርስ…” በሚል ዓይት የጅምላ ምረቃ ገዋን ከሚለብሱ የመርገምት ፍሬዎች ብዙም አልጠብቅም፡፡ በዚያ ላይ ትምህርትን ድባቅ ለመምታት ወያኔ ቆርጦ መነሣቱ የታወቀ ነው፡፡ አይ!  ያደለው ይችን ዘመን ተኝቶ በሰመመን ነበር ማሳለፍ! …

“ቀበሌ ግባ – በገንዘብ የፈለግኸውን ታደርጋለህ፡፡ (ካለ ቀበሌህ) መታወቂያ ለማውጣት ጥቂት መቶ ብሮችን፣ ለመንጃ ፈቃድም ሆነ ለሌላ ጉዳይ ዕድሜህን ቀንሰህ ወይም ጨምረህ መታወቂያ ለማሣተም ጥቂት መቶ ብሮችን፣ ፋይል ለመክፈት ወይም የተከፈተን የጠላትህን ፋይል ለማስጠፋት ወይም መረጃ ለመለዋወጥ ጥቂት ሺህ ብሮችን፣ አጥር ለማጠር፣ ቤት ለማደስ፣ ቤት ለመሥራት (የውሻ ቤት ሳይቀር!)…. ጥቂት ሺህ ብሮችን፣ … ካልከፈልክ በዜግነትህና በሰውነትህ ብቻ የምታገኘው መብት ፀሐይን ከመሞቅና  አየርን ከመሳብ የዘለለ  አይደለም – ለዚህ ዕድል የምትበቃውም በትልቁ እሥር ቤት ውስጥ ካለህ ብቻ ነው፤ በዞን ዘጠኝ፡፡

ተመልከት – የአውሮፓ ታሳሪ ሽንት ቤት ጠበበኝ፣ የክፍሌ ቀለም አስጠላኝ፣ የምግቡ ዓይነት ቀነሰብኝ፣ የብርድ ልብሴ ሞዴል ስድስት ወር አለፈው…. በሚል አሳሪዎቹን እንደማያሽቆጠቁጥ – ሊያውም እኮ 70 ምናምን ሰው ገድሎ የገባ የተፈረደበት ወንጀለኛ – እኛ ሀገር ግን ገና ለገና ወያኔን ለመጥላት ታስባለህ በሚል የወደፊት “ታሳቢ ወንጀል” ወይም አንድ ሰው ወዶና ፈቅዶ ባልተፈጠረበት ነገዱ ምክንያት “የዐይኑ ቀለም” አስጠልቷቸው ታስሮ ጨለማ ቤት ውስጥ ይዘጋበታል፤ መቆምም ሆነ መቀመጥ በማያስችል ጠባብ ክፍል ከብዙዎች ታሳሪዎች ጋር ይታጎራል፤ መግረፍና ማሰቃየት በሚያስደስታቸው እርጉማን የሥርዓቱ ሰዎች አጥንቱ እስኪላጥ ይገረፋል፡፡ በርሃብ ይጠበሳል፤ እንደሰው ቀርቶ እንደ ቅማል እንኳን አይቆጠርም፡፡ በዚህ ላይ አንዱ ዘር ከሌላው ተለይቶ እንደመልኣክ ስለሚቆጠርና ሌሎቹም የዚሁ ዘር አሽከርና ገረድ እንደሆኑ በመንግሥት ሥርዓት ሳይቀር ተቀባይነት ያለው አካሄድ በመሆኑ ጥላቻና ማይምነት የተቀላቀሉበት የበቀል ብትር በብዙኃን ዜጎች ላይ እያረፈ ነው – ዕንቆቅልሹ ደግሞ አዲሱ ጠ/ሚ አገር ላገር እየተንከራተተና የሚችላቸውን የሀገሪቱን ቋንቋዎች ቃላትና ሀረጋት አምጦና አሟጦ በመጠቀም እያባከነ ባለበት በዚህ “የለውጥና የዴሞክራሲ ግንባታ” ወቅትም ይሄው የወያኔ “በረከት” ጋብ ሊል አለመቻሉ ነው –  ያዳቆነ ሰይጣን መች ሳያቀስ ይተውና! ገልቱዎቹ እኛ ነን! ንግግርን ከተግባር፣ ተስፋን ከምኞት መለየት ያቃተንና ግራ ተጋብተን በነፈሰው የምንነፍስ እኛ እንጂ ወያኔ መቼ ምን እንደሚያደርግ ዕድሜ ለአማካሪዎቹ ጠንቅቆ ያውቃል፡፡ እንግዲህ ይህችን ሀገር ሀገር ካላችሁ፣ ይህ ሁሉ ግፍና በደል እየተፈጸመበት ምርጫ ከማጣትም ይሁን ሰቆቃውን ከመለማመድ አኳያ ዝም ብሎ የሚኖር ሕዝብ፣ ሕዝብ ካላችሁ ፍርዱን ለእናንተው ለራሳችሁ መተው ነው የሚሻለው፡፡ ምክንያት መደርደር ደግሞ አይሠራም፤ የምክንያት ጊዜም ያልቃል፡፡ ለምክንያት ለምክንያትማ “የእናቴ መቀነት አሰናከለኝ” ያለችው ጦጢትም የሰጠችው ምክንያት አጥጋቢ ሆኖ ከቅጣቱ ባተረፋት ነበር፡፡ “በበቀደሙ ግጥሚያ የተሸነፍነው ሣሩ እያዳለጠን በመቸገራችን ነው!” – ያኛውስ ቡድን ያሸነፈው ሣሩ አዳልጦት ወይም ሳያዳልጠው ቀርቶ ይሆን?

ይህን ሁሉ የተዘበራረቀ ሀገራዊ ስዕል ለማስተካከል ምን ዓይት ደፋር አናጺ፣ ምን ዓይነት ደፋር ግምበኛ፣ … እንደሚያስፈልግ በመገረም ከመነሻየ ራሴን የጠየቅሁት በዚህን መሰሉ ቅጥ አምባሩ የጠፋበት ወያኔ ሥሪት ሀገራዊ አረንቋ ስለምኖር ነው፡፡ ያለው ነባራዊ ሁኔታ ከምናገረውም በላይ ነው፡፡ ሀገራችን የገባችበት ማጥ እንኳንስ በሁለትና ሦስት ገጽ በሺዎች ገፆችም ተጽፎ አያልቅም፡፡ በአእምሮው የሚጠቀም ዜጋን ለመፍጠር፣ ኅሊናውን ለገንዘብ ያልሸጠ ንጹሕ ዜጋን ለማፍራት የሚወስደውን ጊዜና ቁርጠኝነት ሲያስቡት በርግጥም ተስፋን ይነጥቃል፡፡ በግልጽ ለመናር – ካለሙስና ምንም ነገር አይከናወንም፡፡ ሙስና ሁሉንም ያዳረሰ ወረርሽኝ ሆኗል፡፡ ችግሩ ገንዘብ ክፈል እንጂ የማይሳካልህ ነገር አለመኖሩ ነው፡፡ የዱሮ ሙስና ኅሊናን የሚስት አልነበረም፡፡ አሁን ግን ሕዝብን በአንዴ ለመጨረስ ሞክረህ ብትያዝ በገንዘብ ነፃ ትወጣለህ፡፡ ይህ አደገኛ የሀገር ጥፋት ነው፤ የዜግነት መጥፋት ነው፤ የሰብኣዊነት መጥፋት ነው፡፡ የአህያ ሥጋ ያበላ፣ በርበሬ የደበቀ፣ … በስቅላት በተቀጣባት ሀገር የጀሶ እንጀራ ያበላ ዜጋ ተመርቆ በነፃ ይሸኛል፡፡ ጉድ በሉ እንግዲህ!!

በመጨረሻም ናቲማን የተባለ ድምጻዊ በቅርቡ ያቀነቀነውንና እንቅልፍ ካላታለለኝና በሥራ  ካልተያዝኩ በስተቀር እየደጋገምኩ በፍቅር የማዳምጠውን ዘፈን ልጋብዛችሁ ወደድኩ፡፡ ግጥሞቹን በሽማግሌ አንደበቴ ማነው ጆሮየ አድምጬ ከትቤያቸዋለሁና ተመልከቷቸው፡፡ በነገራችን ላይ እርስ በርስ ከሚጎሻመጡ ዓላማቢስ የፖለቲካ ተቃዋሚዎች ይልቅ እነቴዲ አፍሮን የመሰሉ ከያኒያን የሞቀ ኑሯቸውን አርዶና ዘልዝሎ የማይጠግበው የወያኔ ቄራ ደጃፍ ላይ አስቀምጠው ለሀገራቸው አስተዋፅዖ የሚያደርጉ በመሆናቸው ሊወደሱና ሊዘከሩ ይገባቸዋል፡፡  (ስለተናደድኩ እንዲህ ጻፍኩ፤ በኔ ጽሑፍ የሚናደድና እኔን በጨለምተኝነት የሚፈርጅ መኖሩ ግልጽ ነው፡፡ በጽሑፍ እንነጋገር፤ ሸሚዝ ለመሰብሰብ አንቀዳደም፡፡ ጉልበትን እንግራና ወደሃሳብ ፍጭት እንግባ፡፡ እኛ ኢትዮጵውያን የምንታማባቸው ብዙ ነገሮች መኖራቸው ይነገራልና እየቀነስናቸው እንሂድ፡፡ ደግሞም እንችላለን፡፡ ma74085@gmail.com)

 

እመነኝ……

እስኪ ና ቁጭ በል “እህ” በል አድምጠኝ የሆዴን፤

አረፍ በል ከጥላው ከዋርካው፤

ላንተ የኔ ኑሮ …. ሚዛኑ… መጠኑ… ምን ይሆን መለኪያው?

እስኪ ና ዝቅ በል ውረድ ወደ መሬት (2) አይተኽ ብትረዳው

ዐይንህ ቢመለከት የኛን ኑሮ የኛን ሕይወት እ…

የናንተ ቁም ነገር የናንተ ክርክር ጥማድ ለኔ [በሬ?] አይገዛ አያድስም ሞፈር፤

ይታይ ሚናፈሰው በየሞገዱ ላይ ቅንጣት ደስታን እንጂ የኛን ችግር አያይ ….

እመነኝ …..

እስኪ ና ዝቅ በል ግልጽ እንነጋገር የእውነት፣

በል እንወቃቀስ ስለፍቅር

ስንት አለ በሆዴ “እህ” ብዬ ፍርዱን ለርሱ ትቼ ያለፍኩት… ሳልናገር…

እስኪ ና ዝቅ በል ውረድ ወደ መሬት (2)

አይተህ ብትረዳው ዐይንህ ቢመለከት የኛን ኑሮ የኛን ሕይወት  እ…

የናንተ ቁም ነገር የናንተ ክርክር

ጥማድ ለኔ [በሬ?] አይገዛ አያድስም ሞፈር

ቢታይ ሚናፈሰው በየሞገዱ ላይ ቅንጣት ደስታን እንጂ የኛን ችግር አያይ፤

እመነኝ….

እፍኝ ሳይዘራ…. ግፍ[ን]ም ሳይፈራ ስንት አለ ያጨደ የሞላ ጎተራ…

አንተም ጥበበኛው…. አንተ ባለዝው

በባህሌ ደምቀህ በባህሌ ኮርተህ

በባህሌ ደምቀህ አጊጠህ በዜማው … የውስጤን ትኩሳት ምነው ማታወራው….

ካንድ እናት ተፈጥረን ሆነን በአንድ ላይ …

ኑሯችን ለዬቅል ምድርና ሰማይ …. ምድርና ሰማይ … እፍኝ ሳይዘራ … ግፍ[ን]ም ሳይፈራ…

እመነኝ….