ቢትወደድ አዳነ መኮነን

አባታችን አቶ አዳነ መኮነን በወልቃይት-ጠገዴ ልዩ ስሙ ዓዴት በምትባል ቦታ ከአባታቸው ከልጅ መኮነን መንገሻ እና ከእናታቸው ከወ/ሮ ብዙነሽ አበበ በሚያዝያ ወር በ1888 ዓ.ም ተወለዱ፡፡ ቢትወደድ አዳነ መኮነን በልጅነት ዕድሜያቸው በአደን የታወቁና ፈጣን አነጣጥረው ተኳሽ በመሆናቸው የተነሳ በአከባቢው (በወልቃይት-ጠገዴ) ባህል መሰረት ዝናና ታዋቂነት አትርፎላቸዋል፡፡ አባታችን አቶ አዳነ መኮነን በ1918 ዓ.ም የአውራጃችን (የበጌ ምድር) ገዥ የነበሩት የራስ ጉግሳ ወሌ ወታደር በመሆን በደብረ-ታቦር መኖር ጀመሩ፡፡ በ1923 ዓ.ም በአንቺም ጦርነት ተካፍለው ከራስ ጉግሳ ሞት በኃላ በአዲሱ የበጌምድር ገዥ በደጃዝማች ወንድወሰን ካሣ ኣዳነ መኮንን የቀኛዝማችነት መአርግ ተሰጧቸው የአርማጭሆ÷ የጃኒፈንቀ÷ የያይራ አስተዳዳሪ ሆኖው ተሹመዋል፡፡
.
በ1928 ዓ.ም ኢጣሊያ አገራችንን በወረረችበት ጊዜ ቀኛዝማች አዳነ መኮነን ከፊታውራሪ ኃይሉ ፋሪስ÷ ከቀኛዝማች ዓባይ ወ/ማርያም÷ ከቀኛዝማች መስፍን ረዳና÷ ቀኛዝማች ገብሩ ገ/መስቀል ጋር በመሆን የወልቃይት-ጠገዴ ህዝብ በማስተባበርና በመምራት የሠቲት ሁመራና የመተማን በር እንዲጠብቁ በደጃዝማች ወንደወሰን ካሳ ታዘዙ፡፡ ይህ የመከላከል ተግባር በማድረግ ላይ እያሉ ጠላት በዘመናዊ ጦር መሳሪያና በግዙፍ ሰራዊት በመታገዝ በጀነራል አቼሌ ስትራቴጂ የሚመራ የአርበኞቹ ምሽግ ሁመራን ጥሶ ጎንደር ከተማ ገባ፡፡
.
ጣልያኖች ጎንደር ከገቡ በኃላ ጀግናው የወልቃይት-ጠገዴው ተወላጅ ኢትዮጵያዊ አርበኛ ቀኛዝማች አዳነ መኮነን ከወንድሞቻቸውና ከጓደኞቻቸው ሆነው በረኻ ገቡ፡፡ ጣልያን ጎንደርን ከአስመራ ጋር ለማገናኘት በአርማጭሆ÷ በሠሮቃ÷ በዳንሻ÷ በወይናት÷ በበኻከር÷ በሁመራ÷ በኦም-ሓጀር÷ ወ.ዘ.ተ አድርጎ የመኪና መንገድ በመጥረግ የጦር ካምፑ በዓዲ-ረመጥ÷ በቃብትያ÷ በመሠፌንቶና በስፍራ-ጣልያን በሚባሉ ቦታዎች አቋቋመ፡፡ ቀኛዝማች አዳነ መኮነን የወራሪውን ጦር ለመመከት የወልቃይት-ጠገዴ አርበኞችን በማሰባሰብ የሽምቅ ጦር በማቋቋም የዕብሪተኛውን የኢጣሊያን ጦር መቅዘፍት ሆነበት፡፡ በዚህም መሠረት በ23/08/1928 ዓ.ም በቀኛዝማች አዳነ መኮነን የሚመራው ጦር ደብዛ በሚባል ቦታ በደፈጣ ውጊያ በማድረግ በኢጣሊያን ጦር ላይ ከፍተኛ ጉዳት በማድረስ ከፍተኛ የሆነ ጠብመንጃና ጥይት ማርከዋል፡፡
.
ከዚህም በመቀጠል በህዳር ወር 1929 ዓ.ም ስፍራ-ጣልያን የነበረ የጠላት የጦር ሠፈር ሳይታሰብ በማጥቃት ብዙ የኢጣሊያን መኮንኖችና ወታደሮችን በመግደል ወደ ፊት ለሚያደርጉት ጦርነት አጋዥ የሚሆን ጠብመንጃና ጥይት ማርኳል፡፡ በዚህ ሁኔታ እንዳለ ጣልያኖች ትጥቅ ለማስፈታት በሚያደርጉት ጭፍጨፋ ህዝቡ እየተማረረ በረኻ በመግባት ያርበኞቹን የነቀኛዝማች አዳነ መኮነን ጦር ያጠናክር ጀመረ፡፡ በኢጣሊያን የወልቃይት-ጠገዴ ገዥ ካርዴሌ የአርበኞች አመፅ ለማጥፋትና ለመደምሰስ ብዙ የባንዳ ጦር በማሰማራት ላይ እንዳለ 05/02/1930 ዓ.ም በቀኛዝማች አዳነ መኮነን የሚመራው የወልቃይት-ጠገዴ የአርበኞች ጦር ቡራዩ በሚባል ወንዝ ፈጣን የሆነ የደፈጣ ጥቃት አድርሶ ብዙ የኢጣሊያን ወታደሮችን ደምስሷል፡፡ በዚሁ የተነሳ ቁጭት ካርዴሌ 22/02/1930 ዓ.ም ከፍተኛ ጦር አሰባስቦ ዓዴት አባ ድንጋይ ላይ ከአርበኛውን ጦር ገጥሞ ያርበኛውን ጦር ቀደም ብሎ በማረከው የጦር መሳሪያ ስለተዘጋጀና የወልቃይት-ጠገዴ ህዝብ ድጋፍም ስላገኘ ድል ተጎናጸፈ፡፡ ቁጭት የተሞላው የፋሽስት ጦር እንደገና ለሶስተኛ ጊዜ 21/03/1930 ዓ.ም ስፍራ-አለቃ በሚባል ቦታ ከአርበኞቹ ገጥሞ የተለመደውን ሽንፈት ተከናነበ፡፡
.
ከዚህም ቀደም ብለው በተደረጉ ጦርነቶች ያልተሳካለት የጠላት ጦር እጅግ ስላስቆጣው ከግዜ ግዜ እየተጠናከረ የመጣው የአርበኞች እንቅስቃሴ ለመደምሰስ በሁለት አቅጣጫ ማለትም በዓዲ-ረመጥ በኩልና በወገራ በኩል ካርዴሌ ወደ አርበኞቹ መናኸሪያ ወደነበረችው ዓዴት ዘለቀ፡፡ በዚህም ማይገና በሚባል ጦርነት ተካሂዶ በሁለቱም በኩል ከፍተኛ እልቂት ቢደርስም ምን ግዜም ድሉ የአርበኞቹ ሆነ። ይህ ድል በቀኛዝማች አዳነ መኮነን የሚመራውን የአርበኞቹ ግንባር ትልቅ ዝናና ክብር ሰጠው የአርበኞቹ ቁጥር እጅግ ከፍ አድርገው በዚው ግዜ ነው የጠላት ጦር ሽንፈቱን አውቆ ዓዴት÷ ማይገና÷ ቀራቅር÷ ጨጓርኩዶ እና ሌሎች አከባቢዎች ለቆ የወጣው፡፡ በጀግናው ቀኛዝማች አዳነ መኮነን የሚመራው ጦር በዚህ አላቆመም ትግሉን በመቀጠል በጥር ወር 1930 ዓ.ም ጠለሎ ላይ መሽጎ የነበረውን የጠላት ጦር በአከባቢው ተወላጅ የሆነው በደጃዝማች ደስታ ማሩ መሪነትና አስተባባሪነት እንዲደመሰስ አደረጉ፡፡
.
ይህን የአርበኝነት ትግል የመሰረተ÷የጦር አመራር ችሎታና ብቃት ያለው መሪ÷ አርበኛውን ድል በድል ያጎናፀፈ መሆኑን የወልቃይት-ጠገዴ ህዝብ አምኖበት በጥር 21 ቀን 1930ዓ.ም በአንድ ድምፅ ጨጓርኩዶ ማርያም በተደረገው የህዝብ ስብሰባ የወልቃይት-ጠገዴ ህዝብ ለክቡር አዳነ መኮነን “በቅጠል” የደጃዝማች ማዕረግና የወልቃይት-ጠገዴ የአርበኞች መሪ አድርጎ ሽሞት ሰጥቷቸዋል፡፡ ክቡር አዳነ መኮነን ይህንኑ አደራ ካሳደጋቸው የወልቃይት-ጠገዴ ህዝብ በመቀበል ለብዙ ተከታታይ አመታት ለአርበኞች ማዕረግ በመስጠት አርበኛውን አጠናከሩት፡፡ ጠላት በኢ/ያ ምድር በቆየበት አምስት አመታት ውስጥ ደጃዝማች አዳነ መኮነን 56 ግዜ ጦርነት በመግጠም በዓዴት÷ በማይገና÷ በቀራቅር÷ በጨጓርኩዶ÷ በጠለሎ÷ በደጀና÷ በዓዲ-ረመጥ÷ በቤተ-ሙሉ÷ በአርማጭሆ÷ በጃኖራ÷ በአጅሬ÷ በጭልጋና በወገራ ከፋሽስት ጋር ግብግብ በመግጠም ለመጨረሻ ድል በቅተዋል፡፡ ፋሽስት ኢጣሊያ ድል እንደሆነ ከተሸነፈ በኃላ 1934 ዓ.ም ደጃዝማች አዳነ መኮነን ከሰሜን ባምብሎ እስከ ተከዜ ጦር አዝማችና አበጋዝ ተብለው በአዋጅ ሹመት ተሰጡ፡፡
.
በ1938 ዓ.ም በንጉሠ ነገሥቱ ፈቃድ የወገራ አውራጃ ሁነው ተሹመዋል፡፡በ1939 ዓ.ም የማዕረግ ስማቸው ወይም በህዝብ የተሠጣቸውን የደጃዝማችነት ማዕረግ በንጉሠ ነገሥቱ ፀደቀላቸው፡፡ በ1944 ዓ.ም ከወገራ አውራጃ አስተዳዳሪነት ወደ ጭልጋ አውራጃ ተዛውረው አስተዳድረዋል፡፡ እንደገናም በ1945 ዓ.ም ወደ ወገራ ተመልሰው እስከ 1966 ዓ.ም ሲያስተዳድሩ ቆይተዋል፡፡በ1959 ዓ.ም በቀዳማዊ በንጉሠ ነገሥቱ ፈቃድ የቢትወደድ ማዕረግ ተሰጥቷቸዋል፡፡ ክቡር ቢትወደድ አዳነ መኮነን ያገራቸውን ልማት ለማፋጠን ባደረጉት ልባዊ ጥረት ከሰቲት ሁመራ ወደ ጎንደር የተዘረጋውን መንገድና የአከባቢው ልማት ህዝቡን በማሰባሰብና በማበረታታት ልማቱን መርተዋል።
.
~ የአምስት ዓመት አገለግሎት የአርበኝነት መዳሊያ
~ የቅዱስ ጊዮርጊስ የጀብዱ መዳሊያ
~ የአፍሪካ ስታር (ኮከብ) የወርቅ መዳሊያ ከታላቋ ብርታንያ(እንግሊዝ )
~ የቅ/ጊዮርጊስ ንሻን የፈረሰኛ ደረጃ ያንገት ኮርዶ
~ የዳግማዊ ምኒልክ የክብር ኮከብ የወርቅ መዳሊያ
~ የሠለሞን የክብር ኮከብ ባለ አምበል
~ የቀዳማዊ ሃ/ስላሴ የክብር ኮከብ ወርቅ መዳሊያ
~ የኢ/ያ የክብር ኮከብ የወርቅ መዳሊያ
.
(መ/ር ታማኝ መብራቱ የወልቃይት ጠገዴ ህዝብ ታሪክና ማንነት ፩ኛ ዕትም)

#የአርበኞች_ቀን_77ኛ_ዓመት!

#ልሳነ_ዐማራ