May 2, 2018
የኢትዮጵያ ህዝብ በታሪኩ እንደዚህ ዘመን ክብሩን የጣለበት ጊዜ መኖሩን እጠራጠራለሁ እርግጥ ነው ኢትዮጵያ በአንባገነን አገዛዝ ስር ስትወድቅ ይህ የመጀመሪያዋ አይደለም እስከዛሬ የነበሩትም ዴሞክራሲያዊ መንግሥት አልነበሩም በንጽጽር እንያቸው ከተባለ ግን የዛሬው አገዛዝ ካለፉት መንግስታት የበለጠ አስከፊ ይመስለኛል እንደሌሎቹ በታሪክ ብቻ ሳይሆን ሁሉንም የአንባገነኑን መንግሥት ትሩፋት ቀምሼ ስላየሁት በደንብ መመስከር እችላለሁ ፡፡
የኢትዮጵያ ህዝብ በትግሉ ይህንን አገዛዝ የጊዜ ጉዳይ ነው እንጂ አሽቀንጥሮ መጣሉ አይቀርም ግን በሀገራችን ይህም የመጨረሻው አንባገነን አገዛዝ አይመሥለንኝ አታሟርትብን ከዚህ በኋላ በኢትዮጵያ ምድር አንባገነን አገዛዝ አይኖርም የሚል አንባቢ አይጠፋም እኔ ግን ይኖራል ብየ ነው የማስበው ፡፡
ምነው እኛ ዴሞክራሲ አይወድልንም ወይስ ለዴሞክራሲ አንመጥንም ወይ ? ለሚለው ጥያቄ መልስ ይሆናል ያልኩት ዝቅ ብየ አስቀምጣለሁ ፡፡
ቆይ እዚች ጋ በቆረጣ ትንሽ ልበል
እኛ በአንባገነን አገዛዝ ስር የምንማቅቅ ዜጎች ትግላችን በመርህ የማይመራ እና የምንታገልለት አላማ በቅጡ ያልገባን የምንታገላቸውን የማናውቅ አንዱ አንባገነን በሌላ አንባገነን ሲተካ እስኪ ጊዜ እንስጠው ብለን ትግል እርግፍ አድርገን የምንቀመጥ አብረን እንሰራለን እያልን የምንዘምር የተነሳንበትን እና የምንደርስበትን ያላወቅን በጠላቶቻችን መንደር የሚደረግ ሽም ሽር ሁሉ የሚያስፈነድቀን በረባ ባረባው መግለጫ የምናወጣ አድሮ
ቃሪዎች ሆነን ለዴሞክራሲ እንመጥናለን ወይ ? አዎ ካልን ከባድ ችግር ውስጥ እንዳለን ይሰማኛል ለነፃነት እየከፈልን ያለነው ዋጋ እና የነፃነት ጥማታችንን ሲለካ ገና ባርነት ያልሰለቸን ዜጎች መሆናችን የትግል አያያዛችን ያስታውቃል ፡፡
ያለፈውን እንተውና ለወደፊቱ አንባገነን መንግሥት በኢትዮጵያ ይኖራል አይኖርም የሚለውን ለጊዜ የምንሰጠው ቢሆንም አሁን ባለን የአስተሳሰብ ደረጃ ና ለትግል የሰጠነው ዋጋ ሲለካ ገና ሌሎች ጮሌ አንባገነኖች የሚገዙን ይመስለኛል ዝርዝሩን ለዛሬ እንለፈው፡፡
ወደ ጊዜው ችግራችን ስንመለስ አሁን ያለው አገዛዝ ለምንድነው 27 ዓመት ቀጥቅጦ የገዛን ?
ህዝብን ገዥዎች /አንባገነኖች / ማሸነፍ ይችላሉ ወይ የሚለውን ስንመለከት ከዚህ በታች ባሉት ምክንያቶች ህዝብ ተሸንፎ ሊገዛ ይችላል ፡፡
1ኛ. ህዝብ አንድነት ሲያጣ ይህ በሀገራችን በደንብ የታየ ነው ቀደም ሲል የነበረው የሀገር አንድነት ዛሬ ላይ የተከፋፈለና የጋራ የሆነ ግብ የሌለው ሁሉም ነገር በዘር መነጽር የሚታይበት ሀገር በመሆኑ የህዝብ አንድነት አለ ለማለት በፍፁም አይቻል ይህ ለመሸነፋችን አንደኛውና ዋናው ምክንያት ሲሆን
2ኛ. አሁን ሀገራችን ካለችበት አስከፊ ሁኔታ ለማውጣት ህዝቡን በአንድ መሥመር መምራትና ወደ ግብ ሊያደርስ የሚችል ሠው ስለሌለን
3ኛ.አሁን ያለው ትውልድ የራሱን ሀገር ከአንባገነን ገዝዎች ታግሎ ነፃና ለትውልዱ ምቹ ሀገር ከመፍጠር ይልቅ ወደ ሌሎች ሀገራት ሽሽት የሚቀናው ትውድ በመፈጠሩ
4ኛ.በሀገሩና በባህሉ (በማንነቱ የማይኮራ )ነጭ አምላኪ ትውልድ በመፈጠሩ ከሀገሩ ጉዳይ ይልቅ የአውሮፓ እግር ኳስ ቀልቡን የገዛው /የወሰደበት ማለት ይሻላል / አካሉ ኢትዮጵያ ውስጥ ተኝቶ አሜራካ አውሮፓ የሚያልም በሀገራችን አባባል ዳሃ በህልሙ ቅቤ …..ልቡ
5ኛ.ለጀግኖቹ ወይም ውለታ ለዋሉለት ክብር የማይሰጥ ትውልድ በመፈጠሩ እና ተተኪ መሪዎች እንዳይፈጠሩ ስለሚያደርግ
6ኛ . በሀገሩ ጉዳይ ያገባኛል የማይል እራሱን ለሌሎች አሳልፎ የሰጠ እሱ የለውጡ አምጭ ዋና ተዋናይ አድርጎ ከመቁጠር ይልቅ በሌሎች የሚተማመን ለምሳሌ የውጭን ሀገር መንግስታት ጫና አድርገው ነፃ ያወጡናል የሚል ጥገኛ አመለካከት ያለው ወጣት መፈጠሩ
7ኛ .ከኢትዮጵያ ውጭ የተመሠረቱ የፓለቲካ ድርጅቶችን ተስፋ በማድረግ ከነሱ ነፃነት እንደ ገፀበረከት በስጦታ የሚጠብቅ ትውልድ መፈጠሩ
8ኛ . በሀገር ውስጥ የሚደረገውን የፓለቲካ ትግል በእውቀት ፣ በገንዘብ ፣ በጉልበት …. ከማገዝ ይልቅ በርቀት መተቸት
9ኛ.በሀገሩ ጉዳይ ላይ አኩራፊ መሆን
10ኛ . በአንድ መሥመር ተሰልፎ እየተጓዝ ለጠላት መረጃ መስጠት /ባንዳነት /
11ኛ .ቁርጠኝነት ማጣት
12ኛ.የአላማ ጽናት አለመኖር በትንሽ ነገር ተስፋ መቁረጥ
13. የራሱን ሀገር ከሌሎች የሀገር ጠላቶች ጋር በመሠለፍ መዝረፍ / የበዛ ገንዘብ አምላኪነት / ወዘተ ከብዙ ችግሮቻችን መካከል የሚጠቀሱ ይመስለኛል እነዚህን በመሣሠሉት ችግሮች የፊጥኝ በመታሰራችን ካለንበት አስከፊ ሁኔታ ለመውጣት የተቸገርን ይመስለኛል ፡፡
መፍትሔ የሚመስለኝ
_____________
በእኔ እይታ ከላይ በምሳሌነት የተመለከትናቸውንና ሌሎች ችግሮቻችንን ጊዜ ሰጥተን እውነት ችግር አለብን ወይ ?
የሚለውን ጥያቄ እራሳችንን በመጠየቅ በጥልቀት እራሳችንን በመፈተሽ ችግራቾንን በሚገባ ፈትሽን ካገኘነው በኋላ መፍትሔው አይጠፋንም ብየ አምናለሁ ለውጥ ከራስ ይጀምራል ያረጀውንና ደካማውን ማንነታችንን ታግለን በማሸነፍ በደካማው አስተሳሰባቻችን ጥበብ ፣ ማስተዋል ፅናት ታክሎበት ድልን መቀዳጀት ያስችለናል ብየ አምናለሁ ፡፡