ቤተ-እስራኤላውያን ለምዕተ-ዓመታት በኢትዮጵያ በተለይም በጎንደር፣ ጣና ሀይቅ አካባቢ ከኢትዮጵያውያን ጋር ኖረዋል አሁንም እየኖሩ ነው።
ስለ ቤተ-እስራኤላውያን አመጣጥ ታሪክ ብዙ ይላል።
ንግሥት ሳባ ንጉስ ሰለሞንን ጠይቃ ስትመለስ አብረዋት አጅበው እንደመጡ ታሪካቸውን የሚመዙ አሉ።
የእስራኤል ምኩራብ በባቢሎናውያን ከመፍረሱ ጋር ተያይዞ ወደ ግብፅ የተሰደዱ፤ ከዚያም ክሊዎፓትራ ስልጣን እስከያዘችበት ድረስ ቆይተው በአውግስተስ ቄሳር በመሸነፏ ምክንያት ወደ ተለያዩ አገሮች እንደተሰደዱም ይነገራል።
ንጉስ ካሌብ ግዛቱን ከማስፋፋቱ ጋር ተያይዞ የመንን በወረረበት ወቅት እንደመጡም ይነገራል።
በ20ኛው ክፍለ-ዘመን መጨረሻ የእስራኤል ባለስልጣናት ሕገ-መንግሥታዊ ውይይት ካደረጉ በኋላ ቤተ-እስራኤላውያንን ወደ እስራኤል የመመለስ ዘመቻዎች በ1970ዎቹ ተጀመሩ።
በ1980ዎቹም ነዋሪነታቸውን በሱዳን ያደረጉትን እንዲሁም ከአዲስ አበባ በሙሴ፣ እያሱ እንዲሁም በሰለሞን ዘመቻዎች በእስራኤል ፀጥታ ኃይሎች በመታጀብም በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ተወስደዋል።
ከነዚህ ዘመቻዎች በኋላ ቤተ-እስራኤላውያንን የመውሰድ ሁኔታ እንደተጓተተ ቤተ-እስራኤላውያን ይናገራሉ።
በብዙ ሺ የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን አሁንም የእስራኤል መንግሥት ከቤተሰቦቻችን ጋር በቀላሉ እንድንገናኝ ፈጣን ምላሽ አልሰጠንም በማለት እያማረሩ ነው።
በኢትዮጵያ ለሶስት ቀናት ለስራ ጉብኝት በማድረግ ላይ ለሚገኙት የእስራኤሉ ፕሬዚዳንት ሩቨን ሪቭሊንም ከቤተ-እስራኤላውያን ዘንድ የቀረበላቸው ጥያቄ ይሄው ነበር።
የቤተ-እስራኤላውያን ተወካዮች ለእስራኤሉ ፕሬዚዳንት ያላቸውን ቅሬታ ያቀረቡ ሲሆን ከሰላሳ ዓመታት በፊት የተለዩዋቸውንም ቤተሰቦቻቸውን ማግኘት ከሰማይ እንደራቀባቸው ተናግረዋል።
እስራኤል ለመሄድም መውጫ ያጡ ወደ ስምንት ሺ ቤተ-እስራኤላውያንም እንዳሉ ተወካዮቹ ይናገራሉ።
ፕሬዚዳንቱ ጋር ተገናኝተው ከተወያዩት ቤተ-እስራኤላውያን ተወካዮች አንዱ ባየ ተስፋየ ነው። ብዙዎች ከገጠሪቷ ኢትዮጵያ ክፍል እንደመጡና ወደ እስራኤልም እንሄዳለን በሚል ተስፋ ለዓመታት በአዲስ አበባ እንደሚቀመጡና አስቸጋሪ ሁኔታ ላይ እንዳሉ ይናገራል።
“በአንድ ድርጅት ውስጥ ተጠልለን እንኖር ነበር፤ ትምህርትም የተከታተልነው እዛው ሳለን ነው። ነገር ግን ድርጅቱ ሲዘጋ በርካታ ወጣቶች ትምህርት ለማቋረጥ ተገደዱ። የሚረዳቸው በማጣታቸው ወደጎዳናም ዘለቁ ብዙዎችን ነበሩ” ይላል ባየ።
በቅርብ ወራትም በኢትዮጵያ ውስጥ ለሚገኙ በሺዎች ለሚቆጠሩ ቤተ-እስራኤላውያን ፈጣን ምላሽ ሊሰጣቸው ይገባል በሚል አንዳንድ የፓርላማ አባላት ተቃውሟቸውን በማሰማት እንዲሁም ፓርላማው ላይ ላለመሳተፍ ጥለው እንደወጡም ተነግሯል።
በተቃራኒው በእስራኤል ህገወጥ ናቸው የሚሏቸውን አፍሪካውያን ስደተኞች ወደ ሀገራቸው ወይም ወደ ሶስተኛ ሀገር እንዲሄዱ የሚሉ ግፊቶችም አሉ።
የእስራኤል ፓርላማ አባል የሆኑት ዶክተር አቭራም ንጉሴ በእንግሊዝ ነዋሪነታቸውን ያደረጉ ቤተ-እስራኤላዊ ሲሆኑ ባለው ሁኔታ ደስተኛ እንዳልሆኑም ይናገራሉ።
“ከቤተሰቦቻቸው ጋር ለመገናኘት ለዓመታት ቢጠብቁም ሊሳካ አልቻለም፤ በዚህም ደስተኛ አይደለሁም፤ ይበቃል ልንል ይገባል። ከሚወዷቸው ቤተሰቦቻቸው ጋር በእስራኤል እስከሚገናኙ ተስፋ አንቆርጥም፤ ድካምም አናሳይም። ጠንክረን እንሰራለን፤ የፓርላማውንም ሆነ የተለያዩ የእስራኤል ባለስልጣናትን ድጋፍ እንድናገኝ እየሰራሁ ነው። እርግጠኛ ነኝ የእስራኤል መንግሥት ላይ ተፅዕኖ መፍጠር የሚያስችለኝ የፕሬዚዳንቱ ድጋፍ አለኝ” ይላሉ።
በአሁኑ ወቅት ወደ 140 ሺ የሚሆኑ ቤተ-እስራኤላውያን በእስራኤል ነዋሪነታቸውን አድርገዋል።
Source – BBC/AMHARIC