ደጃዝማች ባልቻ ሳፎ (በፈረስ ስማቸው አባ ነፍሶ)
በአገምጃ ሶዶ(ወሊሶ) በሚባል ቦታ በነሀሴ ወር ፲፰፻፶፬ ዓ.ም ተወለዱ። የዓድዋው ጦርነት ሥመ ጥር ጀግና ባልቻ አባ ነፍሶ ፋሽስት ጣልያን ኢትዮጵያ በድጋሚ ስትወር ከቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ጋራ ፀብ ስለነበራቸው ባልቻ ከጣልያን ጎን ይሰለፋሉ ብለው ጣልያኖች አሰቡ። ደጃዝማች ባልቻ በንጉሱ ላይ ቅሬታ ቢኖራቸውም በአገር ጉዳይ ላይ ሌላ ድርድር መግባት አልፈለጉም ስለሆነም ጦራቸውን ማሰባሰብ ጀመሩ እናም ከነ ደጃዝማች ኃይለማርያም ማሞ፣ አበበ አረጋይ፣ በላይ ዘለቀና አቡነ ጴጥሮስ ጋራ ስለ ጦርነቱ የሚስጥር ደብዳቤ መለዋወጥ ጀመሩ። ደጃዝማች ባልቻ አምስት ሺ ጦራቸውን ይዘው በ፸፱ ዓመታቸው ለዘመቻ ተነሡ። የባልቻ ሰላይ የነበሩት በባንዳ ተይዘው ሲገደሉ ጣሊያን በአውሮፕላን ሆኖ የደጃዝማች ባልቻ ጦርን እየተከተለ በጣም ብዙ ሰው ፈጀባቸው። በህይወት ዘመናቸው ጣልያንን ሁለት ጊዜ የተዋጉት ብዙ ሺ ወታደር የነበራቸው ደጃዝማች ባልቻ አባ ነፍሶ ብቻቸውን ቀሩ። ባልቻ ሁለት ወንድሞች ነበሯቸው ፊታውራሪ ገብረ መድህን እና ፊታውራሪ ሳህለሚካሄል ሁለቱም በጦርነት ተማርከውና ተገለዋል። በዚህም ጊዜ ደጃች ባልቻ እንዲህ አሉ
ጦር መጣ ይላሉ እኔ ምን ቸገረኝ
እናቴም ልጅ የላት ለእኔም ወንድም የለኝ።
የጠላት ጦር ደጃዝማች ባልቻ ወደሚኖሩበት በቾ አበቤ የተባለ ቦታ ድረስ አባጆቢር በተባለ ባንዳ እየተመራ በመዝለቅ በእሳቸው ላይ ዘመተባቸው ህዝቡም ከዳቸው ወታደሮቹም ለህይወታቸው ሲሉ ሸሿቸው ደጃዝማች ባልቻ እና ሁለቱ አሽከሮቻቸው ከእሳቸው ጋራ ሦስት ሰው ብቻ ቀረ ብዛት ያለው የጣልያን ጦር ከበባቸው ወዴትም መሄድ አልቻሉም ። በመጨረሻም “እጅህን ስጥ መሳሪያህን ጣል” ብሎ ጣልያኑ ሲያዛቸው ደጃዝማች ባልቻ “እኔ እጄን የምሰጥ ሰው አይደለሁም ትጥቄን አልፈታም” ብለው ነጩን ጣልያን ገድለው በራሳቸው ጥይት የራሳቸውን ህይወት አጠፉ። እጃቸውን እንኳን ለጠላት ሳይሰጡ በራሳቸው ሽጉጥ ጥቅምት ፳፯ ቀን ፲፱፻፳፱ ዓ.ም ተሰው።
ክብር ይህቺን ውድ ሃገር በደማቸው ላቆዩልን ጀግኖች አባቶቻችን