ከተስፋሁን አረጋይ

ባለፈው ሳምንት የኢሳቱ ጋዜተኛ አቶ ምናላቸው “ በላ ልበልሃ” በሚባለውን ፕሮግራሙ የኢድህን(የኢህአዴጉ ብአዴን) መስራች እና አመራር የነበሩትን አቶ ያሬድ ጥበቡን ይዞልን ቀርቦ ነበር፤ ይህን ፕሮግራም ከተከታተልኩ ቦኋላ በፕሮግራሙ አቀራረብም ሆነ ግለሰቡ በሰጣቸው መረጃዎች እና አስተያየቶች ላይ ያለኝን ትችት እና ገንቢ አስተያየት ለማቅረብ ብፈልግም ከራሴ ጋር ብዙ መታገል ነበረብኝ። ብዙውን ጊዜ የግለሰቦችን ስራ መተቸት እንደበጎ በማይታይ ማህበረሰብ ውስጥ ሆኖ እንደዚህ አይነት ስራ ውስጥ መግባት በራስ ሰላም ላይ ዋጋ የሚያስከፍል ቢሆንም ለፕሮግራሙ ካለኝ በጎ አመለካከት አንጻር ይችን ጽሁፍ በማቅረብ የህሊና ሰላም ለማግኘት ወሰንኩ።

ከመሰረቱ ይህ ፕሮግራም ከተሰጠው አርእስት ጋር የማይሄድ አቀራረብ ያለው በመሆኑ መሰረታዊ ችግር አለበት፤ “በላ ልበልሃ” የሚለው አባባል ድሮ አባቶቻችን( በተለይ በሰሜኑ ክፍል)) ይጠቀሙበት ከነበረው የክርክር እና የመረጃ ልውውጥ ዜዴ(ልምድ) የተወስደ ቢሆንም አቅራቢው በቃለመጠይቅ መልክ የጀመረው ፕሮግራም ከስሙ ጋር የሚሄድ አይደለም። አዘጋጁ እንደሚያውቁት ይህ ፕሮግራም መካሄድ የሚገባው በአንድ ወይም በበርካታ ጉዳዩች ላይ የተለያዩ አቁዋሞች(አመለካከት ወይም ጥቅም) ያላቸውን ከአንድ የበለጡ(ሁለት) ግለሰቦች ወይም የቡድን ተወካዬች በማቅረብ በሚነሱት ነጥቦች ላይ ሁለቱም ክፍሎች አለኝ የሚሉትን ማስረጃ(ሃቅ) እያቀረቡ እንዲከራከሩ ሲደረግ ከማህል ያሉት ዳኞች(ታዛቢዎች) በክርክሩ ወቅት እውነቱን አጥርተው ለማግኘት እድል የሚሰጥ ስልት ነው። በዚህ ወቅት አቶ ምናላቸው እንደሚያቀርቡት አይነት ጥያቄዎች ክርክሩን የበለጠ የሚያዳብር ዜዴ ሊሆን ይችላል። ሆኖም ግን አንድን ሰው ብቻ በመጠየቅ የሚፈለገውን ውጤት ማግኘት አይቻልም።

ይህን አይነት የክርክር ጥበብ ገና ድሮ በነፕሉቶ እና አርስቶትል ዘመን በመጀመሩ ለሳይንሳው ግኝቶች መስፋፋት እና ለሰው ልጆች የዕውቀት እድገት ከፍተኛ አስተዋጽዖ ያደረገ ቢሆንም በሃራችን በአንዳንድ አካባቢዎች ትክክለኛውን ፍርድ ለመስጠት ይጠቀሙበት የነበረ ጥበብ በመሆኑ ጥቅሙ ከፍተኛ ነበር። ታዲያ በዚህ የኢሳት ፕሮግራም ላይ አቅራቢው ይዞ የሚመጣው አንድን ግለሰብ በመሆኑ ፕሮግራሙ ከፍተኛ ጉድለት አለው፤ አቅራቢው ጥያቄዎችን እየነቀሰ አውጥቶ ለማነጋገርያነት ማቅረቡ ጥሩ ሆኖ ሳለ የሚጠየቀው እና የሚመልሰው አንድ ግለሰብ ብቻ በመሆኑ ተጠያቂው ከሚሰጠው መልስ የተለየ ሃቅ አለኝ የሚለውን ክፍል ማድመጥ አይቻልም፤ ጠያቂው ተጠያቂውን ለመወጠር(chalenge ለማድረግ) ቢሞክርም በነገሮቹ ላይ ያለው ግንዛቤ እና መረጃ ውስን በመሆኑ ተጠያቂው እንደልቡ አማትቶ እና ሸውዶ እንዲሾልክ እድል የሚከፍት ከመሆኑም በላይ ሊነገር የሚገባው ሃቅ ተዳፍኖ እንዲቀር ያደርግዋል፤ እንዲያውም ከዚህ አልፎ የተዛባ መረጃ የሚረጭበት መድረክ ሆኖ ፕሮግራሙንም ኢሳትንም የሚጎዳ ይሆናል።

ስለዚህ የፕሮግራሙ ጽንሰሃሳብ በጣም ጠቃሚ በመሆኑ ለውይይት(ለክርክር) በሚቀርቡ ጉዳዮች (issues) ላይ የተለያየ አቁዋም እና ልምድ ያላቸውን ግለሰቦች(ሃይሎች) በማቅረብ እውነቱ ፈርጦ እንዲወጣ ቢደረግ ፕሮግራሙን ይበልጥ ተወዳጅ ያደርገዋል። በተለይ ደግሞ (ኢሳት በተደጋጋሚ ቢጠየቅም ተግባራዊ አላደረገውም) የተለያዩ ድርጅት መሪዎችን በማቅረብ በሚያደርጉት ክርክር የድርጅቶቹን ልዩነት እና አንድነት እንድናውቅ ሊረዳን ይችላል።

ወደ ውይይቱ ስንገባ ደግሞ የአቶ ያሬድን መልሶች መሰረት አድርጎ ብዙ ነገሮችን ማንሳት ይቻል ነበር ሆኖም በዚህ ጽሁፌ በጣም መሰረታዊይ እና አከራካሪ በሆኑት ጉዳዬች ላይ ባተኩር ደስ ይለኛል። አቶ ያሬድ ውይይቱ ተጀምሮ እስኪጨረስ በኢሕአፓ ዙሪያ አንዳንድ ጥያቄዎችን ሲጠየቅ በወቅቱ የነበረውን የኢሕአፓን አቁዋም ከማብራራት ይልቅ ድርጅቱን ለመክሰስና ለማጣጣል ይጠቀምበት ነበር፤ ለምሳሌ በኢሕአፓ አመለካከት ደርግ አምባገነናዊ ባህሬ ያለው በመሆኑ አደገኛ ነው ስለዚህ ሁሉንም የህብረተሰብ ክፍል የሚያቅፍ “ጊዚያዊ ህዝባዊ መንግስት” ይቌቌም የሚል አቁዋም በመያዙ ደርግ ማሰርና መግደል ሲጀምር መኢሶን ግድያውን ከመቃወም ፋንታ ለደርግ “ሂሳዊ ድጋፍ” መስጠት ይገባል በማለት ከደርግ ጎን በመሰለፍ የዚያ ሁል ጭፍጨፋ ተባባሪ መሆኑን ከማንሳት ይልቅ “ኢሕአፓ ባንዳ ብሎ ስማቸውን አጠፋው” ብሎ ነገሮችን በመጠቅለል ዋናውን የፖለቲካ ጥያቄ ሳይተነትነው አለፈ። አቶ ያሬድ በዚያን ወቅት “የጊዚያዊ ሕዝባዊ መንግስት” ጥያቄ ምን ያህል ተቀባይነት እንደነበረው ህሊናው ያውቀዋል የሱ ችግር ግን ምን እንደሆነ ባላውቅም ወደ ተራ ነገሮች በማተኮር ኢሕአፓን ለማዋደቅ ሞከረ።

ጠያቂው ኢሕአፓ በበርሃ ውስጥ በትግል ላይ በነበረበት ወቅት የነበሩበትን የውስጥ ችግሮች አስመልክቶ በተለይም ከኢሕአፓ ተገንጥለው የሄዱት የኢድህን መስራቾችን እንቅስቃሴ አስመልክቶ ሲጠይቀው አቶ ያሬድ “ ኢሕአፓ ውስጥ የቆየ የዴሞክራሲ ጥያቄ ስለነበር _____”እያለ ነገሮችን ለማምታታት ከሞከረ ቦኌላ የኢሕአፓን አመራር “የፓርቲ ጉባኤ ለመጥራት ፈቃደኛ ያልሆነ አመራር ነበር” ብሎ ይከስና ጸለምት ውስጥ ስልጥን እንዲለቁ የተጠየቁት ሁለት የኢሕአፓ የአመራር አባላት ድርጅቱን ወክለው የስልጣን ሽግግር እንዲደረግ እነ ያሬድን እንዳስመረጡዋቸው ይናገራል(ይሄም በጣም አከራካሪ ነው) ከዚያም ቦሁዋላ በለሳ ድረስ ሂዶ እንደነበር ይናገራል፤ እንግዲህ ችግሩ እዚህ ላይ ነው ከመሰረቱ በድርጅቱ ውስጥ ለእድገት እና የተሻለ ውጤት የተለያዩ እንቅስቃሴዎች እንደነበሩ ይታወቃል በለሳ ውስጥ ግን ውስጥ ለውስጥ የራሱን መረብ የዘረጋ ስር የሰደደ የብተና ስራ የሚሰሩ ሃይሎች የተደራጁበት ቦታ ነበር፤ የሚወጡትም ጽሁፎች በሙሉ ድርጅቱን የበለጠ ዴሞክራሲያዊ ለማድረግና ለማጠናከር ሳይሆን የታጋዩን ሞራል የሚገድል ተስፋ አስቆራጭ እና የበሬ ወለደ መረጃዎችን የሚያሰራጭ ከዚህም አልፎ በታጋዬቹ ማህል ከፍተኛ መጠራጠርን እና መፈራራትን የሚፈጥር ቅስቀሳ ነበር፤ ለዚህም እራሱ አቶ ያሬድ እንደተናገረው አመራሮ ቹ የELF(የኤርትራ) ሃይሎችን ወደ ጸለምት አስመጥተው ሊያፍኑን ነው ሊመቱን ነው የሚለው የሃሰት ቅስቀሳ በታጋዩ ውስጥ ከፍተኛ መደናገጥን ፈጥሮ ለብዙ ጊዜ ሲሰሩበት የነበረውን ብተናቸውን ለማሳካት ችለዋል ። በዚህ ላይ መጠቀስ ያለበት በጣም አሳዛኙ ነገር እነዚህ ሃይሎች ጓዶቻቸው ወልቃይት ውስጥ ከወያኔ ጋር ከፍተኛ ውጊያ በማድረግ ከፍተኛ መስዋእትነት በሚከፍሉበት ወቅት እነሱ በጀርባ ከወያኔ ጋር በመደራደር ለወያኔ የሞራል ድጋፍ ይሰጡ ነበር(ምናልባት ሌላም መረጃ ሰጠው ሊሆን ይችላል)። ይህ ብቻ አይደለም እንዲያውም ድርጅቱን ለማጠናከር በተለይም የበለሳውን ችግር ለመፍታት የሄዱትን ሁለት የአመራር ጓዶች ከመንገድ ላይ አድፍጠው በመግደል በድርጅቱ ውስጥ ከፍተኛ ትርምስ ለመፍጠር ሞክረው እንደከሸፈባቸው አቶ ያሬድ የሚያውቀው ቢሆንም ሳይናገረው አልፎአል።

ሌላው አብይ ነጥቤ አቶ ያሬድ የኢሕአፓ አመራር ጉባኤ ለመጥራት ፍቅደኝነት እንደሌለው አድርጎ ያቀርባል፤ ሃቁ ግን እንደዚያ አይደለም የድርጅቱ ማእክላዊ ኮሚቴ 4ኛ ፕሌኒየም ባደረገው ስብሰባ እስከ 1971 ዓም መጨረሻ ድረስ ድርጅቱ ባካሄደው ትግል የሰራቸውን ጠንካራና ደካማ ጎኖቹን ገምግሞ በሂደቱ በሰራቸው ስህተቶች ላይ እያንዳንዱን ነጥብ ዘርዝሮ በማስቀመጥ በጣም ግልጽ የሆነ ግለሂስ በማድረግ አንድ ዶክመንት አዘጋጅቶ አባላት እንዲያውቁት እና እንዲወያዩበት በመዋቅር ማስተላለፉን እኛም እነአቶ ያሬድም እናውቃለን። በዚህም ዶክመንት ውስጥ በአስቸኴይ ጉባኤ እንዲጠራ የሚገልጽ አቌም የተካተተበት ስለነበር “ጉባኤ ለመጥራት ፈቃደኛ አይደሉም” ብሎ የአመራር አካሉን መወንጀሉ አግባብ የለውም። እንዲያውም በ1972 ዓም አጋማሽ ላይ ይህ ዶክመንት ወደ አካላት እና አባላት ወርዶ ሰፊ ውይይት በሚደረግበት ወቅት በታኙ የበለሳው ቡድን ይህን አጋጣሚ በመጠቀም ድርጅቱ ምንም ህልውና እንደሌለው አድርጎ ሰፊ የተቀናበረ ስራ በመስራት ጉባኤውን አደናቅፎ የብተና ዓላማውን ከሞላ ጎደል አሳክቷል። ይህም በመሆኑ ሆን ብለው የጉባኤውን ዝግጅት ያደናቀፉት በታኞቹ እንጂ አመራሩ አልነበረም። ታዲያ የዚህ እንቅስቃሴ ደጋፊ(አንዳንዶች አቀናባሪ ይሉታል) የነበረው አቶ ያሬድ ከኢሕአፓ ጋር በሚነሱ ጉዳዬች ላይ እውነተኛውን ታሪክ ይናገራል የሚል ተስፋ ተይዞ ከሆነ ያራዳውን ልጅ ባህሬ ጠያቂው ያወቀ አይመስለኝም፤ በዚህ መልክ አቶ ያሬድ እድል ባገኘበት አጋጣሚ ሁሉ በሚናገራቸው እና በሚጽፍባቸው መድረኮች ኢሕአፓን ወንጅሎ እና አሳንሶ የሚያልፍ በመሆኑ ብዙ ሰወች ቅሬታ አላቸው ሆኖም ወቅቱ ከዚህ የበለጡ ጉዳዬችን የምንወያይበት በመሆኑ ችላ እየተባል ቢታለፍም አንዳንዴ ታሪክን ማስተካከል ግድ ይላል።

ብዙውን ጊዜ አቶ ያሬድን ከህዝብ ጋር የሚያወዛግበው በኢህአዴግ በተለይ በ ብአዴን (የሱው ኢድህን) ዙሪያ የሚያቀርባቸው ሃሳቦች ነው፤ በዚህ ውይይት ኢድህን ገና ሲመሰረት ብቃት እና ጥራት የሌለው ሃይል መሆኑን በመገንዘብ ወደ ሱዳን አንድ ላዑክ በመላክ ከቀረው የኢሕአፓ አካል ጋር ለመገናኘት ሞክረው ኢሕአፓ ስላልተቀበላቸው አልሳካላቸው ሲል ሉኡካኑም በዚያው መቅረታቸውን ይናገራል፤ ወደ ሁዋላ ደግሞ አዲሱ እና በረከት ወደ ሱዳን ሄደው አዲሱ በዚያው ለመቅረት ሲያስብ በረከት ደግሞ ከኢሕአፓ ጋር ለመገናኘት ሲሞክር አቶ ያሬድ ሁለቱንም አግባብቶ ሃሳባቸውን በማክሸፍ ወደ ወያኔ የመለሳቸው መሆኑን በኩራት ይነግረናል፤ አቶ ያሬድ ኢድህን ውስጥ በነበረበት ወቅት ዋናው ችግሩ አድርጎ የሚያቀርበው የወያኔ ሀርነት መሪዎች እሱን በውጭ ኮሚቴ ውስጥ እንዳይመደብ የሚያደርጉትን ግፊት ነው፤ አወን ኤርትራን በተመለከተ እነ በረከት እና ታምራት በአቶ መለስ በተሰጣቸው ትምህርት ሰልጥነው “የቅኝ ግዛት ጥያቄ” ብለው መቀበል ቢጀምሩም አቶ ያሬድ ግን ከኢሕአፓ የወሰደውን አቁዋም(ግን የራሴ ጥናት ይለናል) እንደያዘ መቀጠሉን ገልጾልናል፤ እንግዲህ እንደነዚህ አይነቶቹን የኢድህን መሪዎች ነው ለምን የወያኔ መሳሪያ ተባሉ ብሎ ህዝብን የሚወቅሰው። ኢድህን ወደ ብአዴንነት ተለውጦ የአማራው ወኪል ነኝ ካለ ቦሁዋላ ደግሞ የብአዴን መሪዎቹ በአማራው ተጨቆኑ የተባሉት ብሄረሰቦች ተወላጆች በመሆናቸው ያለውን ተቃርኖ ሲጠየቅ “ለሰዎች ፍትህ ለመቆም ብሄርተኛ መሆን የለብህም “ እያለ “ተናፋቂው” አቶ በረከት ለአማራው ልዪ ተልዕኮ እንዳለው ሊያሳምነን ይሞክራል፤ ጠያቂውም ጥያቄውን በጣም ጠበብ አድርጎ “እነ አዲሱ እና በረከት አድርባዬች ናቸው ወይ ?“ ብሎ ሲጠይቀው “አድርባዬች ናቸው ብዬ ማመን አልፈልግም “ ከሚለው በላይ “የራሳቸው የሆነ ግንዛቤ አላቸው “ ይላል። ከዚህም አልፎ እነዚህ በሚያውቀው “ስብእናቸው” የሚጨነቅላቸውን ጔደኞቹ “ተጨባጩን ሁኔታ አመዛዝነው (በሱ አባባል በመሬት ላይ ባለው) ከወያኔ ኢህአዴግ ጋር የተሰለፉ መሆናቸውን በማረጋገጥ “ለህሊናቸው አቤቱታ እያቀረብን ብንደግፋቸው ኖሮ ክፍተኛ ደረጃ ይደርሱ ነበር” በማለት ኢድህንን(ብአዴንን) ባለመደገፋችን ተቃዋሚውን ይወቅሳል። አቶ ያሬድ እስኪ አስበው ገና ከስልጣን ከወጡባት ቀን ጀምሮ ከኢትዬጵያ ህዝብ ጋር ቅራኔ ውስጥ የገቡትን ሃይሎች፤ ገና በጥዋቱን እነ ፀጋዬን የገደሉ እነ ፕሮፌሰር አስራትን ያሰሩ ሰዎች ምን ብለን እንድንደግፍ ነው የጠበከው ?? በጣም ለረዡም ጊዜ የሰላም እና እርቅ ጥያቄ በማቅረብ የተማጸናቸውን ገዢዎቻችን ሲገሉ ጥይት ሲያስሩ ሰንሰለት ማቀበል ነበረብን ወይ? የሚገርመው አቶ ያሬድን የሚቆጨው በየቦታው የተገደሉት በየእስር ቤቱ የተሰቃዩት በስደት በየሃገሩ የሚንገላቱት ወገኖቻችን ህይወት አይደለም አሁንም እሱን የሚቆ ጨው “የወያኔ መጠቀሚያ” እየተባሉ የተሰደቡት ጔደኞቹ ጉዳይ ነው። በጣም አያሳዝንም አቶ ያሬድ? እስኪ አንተው ወደ ህሊናህ ተመለስ እና እራስህ ፍረድ።

አቶ ያሬድ የኢትዪጵያ ህዝብ ከኢህአዴግ ጋር ያደረገውን ትግል ሲወቅስ በተደጋጋሚ “ምን ያህል ነው መጉረስ የምንችል ምን ያህል ነው ማላመጥ የምንችል “ የሚሉ ስንኞችን በመጠቀም የተደረገውን ትግል ከአቅማችሁ በላይ ሞከራችሁ በማለት ለማጣጣል ከሞከረ ቦኋላ ጭራሽ “አገሪቱ ዜጋ የሌላት አገር ናት” በማለት ባዶአችን ካስቀረን ቦኋላ ተመልሶ ደግሞ “ለሰላማዊ ትግል የማይመች አገር ነው ያለን “ ይልና “ህዝባችን ጭቆናን ለመቀበል ጫንቃው የደነደነ ነው “ እያለ በከፍተኛ ንቀት ያገራችን ህዝብ በትእግስት ያደረገውን ትግልና የከፈለውን መስዋዕነት ትቢያ ላይ ይጥለዋል። አቶ ያሬድ ስለ ራሱ ሲናገር ግን “የሚችለውን አርጎ ደክሞ የወጣ ሰው ከዚያ ወዲህ ደግሞ የፖለቲካ ቦታ ለማግኘት ከባድ የሆነበት” እያለ ከተመጻደቀ ቦኌላ እራሱን በጣም ከፍ በማድረግ “በውስጤ ያለኝን እምቅ ችሎታ ለመጠቀም ፈቃደኛ የሆነ የሰው ሃይል የሌለበት የተጨማለቀ የዲያስፖራ ፖለቲካ ውስጥ የሚኖር” መሆኑን በመግለጽ ህዝብንና በሃገራችን ለውጥ እንዲመጣ ጊዚያቸውንና ገንዘባቸውን ከዚያም አልፎ ህይወታቸውን መስዋዕት የሚከፍሉትን ወገኖች በድፍረት ይሸነቁጣል።

አቶ ያሬድ ከተናገራቸው ተነስቶ ብዙ ብዙ መጻፍ እንደሚቻል ይገባኛል፤ ግን ለምን እንደዚህ አይነት አወዛጋቢ ነገሮችን እየቆሰቆሰ እራሱን አጀንዳ ለማድረግ እንደሚፈልግ አይገባኝም፤ ከነኢንጅነር ሃይሉ ጋር በአንድ የክስ መዝገብ እንዲገባ የተደረገው ወያኔን ለማዳከም በተደረገው ትግሉ ባደረገው አስተዋጽዖ ነው የሚል አንድም ሰው እንደማይኖር እርግጠኛ ነኝ፤ ከድሮም ምንም ሳይበድላቸው ከእነአቶ መለስ ጋር ኮከቡ አልገጥም ብሎ ችግር እንደነበረበት ነግሮናል፤ ከዚያ ውጭ ለወያኔ/ኢህአዴግ እንደ ስጦታ የሰጣቸው እንደ ፈረስ በገመድ ታስረው እየተጎተቱ የኢትዪጵያን ህዝብ ሲረግጡት የነበሩት የሱ “ተናፍቃቸዎች” የኢድህን መሪዎች ቀኑ እየጨለመባቸው በመሆኑ ለእርሱም ሆነ ለእነሱ የሚያዋጣው የኢትዮጵያን ህዝብ ማክበር ነው፤ የሚያዋጣው ለሰሩት ስህተት ህዝብን ይቅርታ እየጠየቁ ከህዝብ ጎን መቆም ነው። አቶ ያሬድ ህዝብን መናቅ ግን በጣም ነውር ነው!!!

/**/