ለውይይቱ መነሻ ሐሳቦችን ያቀረቡት አቶ ሙሉጌታ ውለታውና አብረሃም ተከስተ (ዶ/ር
ፖለቲካ
2 May 2018
ነአምን አሸናፊ
ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ወደ ሥልጣን ከመጡ ወዲህ በሚያደርጓቸው ንግግሮች የተነሳ፣ አብዛኞቹ የንግግራቸው ይዘት እስካሁን ከተለመደው ኢሕአዴጋዊ የአነጋገር ያፈነገጠና አዲስ አስተሳሰቦችን ያዘለ እንደሆነ ይገልጻል፡፡
ከዚህ በተጨማሪ እስካሁን ከኢሕአዴግ ባለሥልጣናት ባልተለመደ መንገድ ለአገር አንድነትና ለግለሰቦች መብት መጠበቅ፣ መከበርና መጠናከር አስመልክቶ የሚሰነዝራቸው ሐሳቦች ፓርቲያቸው ከሚታወቅበት የአብዮታዊ ዴሞክራሲ ርዕዮተ ዓለም አስተሳሰብ ወጣ ያሉ እንደሆኑ፣ ወደ ሊብራል ርዕዮተ ዓለም አስተሳሰብ የሚያዘነብሉ ናቸው በማለት የሚገልጿቸውም በርካታ ናቸው፡፡
ምንም እንኳን ፓርቲያቸው ከኢሕአዴግ የአብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ አቅጣጫ የሚከተል ቢሆንም፣ እርሳቸው ግን ከዴሞክራሲያዊ ማዕከላዊነት ወጣ በማለት በአብዛኛው በሊብራል ርዕዮት ዓለም እንደ ምሰሶ የሚያገለግሉ እሴቶችን አጉልተው በማውጣት በሚያደርጉት ንግግር ማንፀባረቅ ችለዋል፡፡ በዚህም ምክንያት በአብዛኛው በሚያስብል ደረጃ በንግግራቸው ይዘት፣ አብዛኛውን የኅብረተሰብ ክፍል ከጎናቸው ማሠለፍ የቻሉ ይመስላል፡፡
የሚያደርጉት ንግግር ከአብዛኛው ኅብረተሰብ ባለፈም ከተቃዋሚ ፓርቲ አመራሮችም ሆነ መንግሥትን በፅኑ ከሚተቹ ግለሰቦች ሳይቀር ይሁንታን ያስገኘላቸው ሲሆን፣ ጥያቄው የተናገሩትን ንግግር ወደ ተግባር እንዲቀይሩት መወትወትና ማሳሰብ ላይ ያተኮሩ እንጂ እንደ ከዚህ ቀደሙ የሚያነሱትን ሐሳብ የሚተች እምብዛም የለም፡፡ እየተነሱ ያሉ ሐሳቦች ግን የተናገሩትን ወደ ተግባር ይለውጡታል ወይ? ንግግራቸውን ወደ ተግባር ለመቀየር በሚያደርጉት ጥረት የፓርቲያቸው ባህልና ርዕዮተ ዓለም እንዴት ይቀበላቸዋል? የሚሉና ተያያዥ ጉዳዮች ናቸው፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ የሊብራል የአስተሳሰብ እሴቶችን ማንፀባረቃቸው፣ ቅዳሜ ሚያዝያ 20 ቀን 2010 ዓ.ም. በሸራተን አዲስ ሆቴል ‹‹ፌዴራሊዝምና መልካም አስተዳደር በኢትዮጵያ›› በሚል ርዕስ በተካሄደ ኮንፍረንስ ላይም በከፍተኛ ሁኔታ ተንፀባርቆ ነበር፡፡
ኮንፍረንሱን ያዘጋጀው ፎረም ኦፍ ፌዴሬሽን የተሰኘ በፌዴራሊዚም ላይ የተለያዩ ጥናቶችን የሚያከናውን ተቋም ነው፡፡ በዕለቱም በርካታ የመንግሥት ባለሥልጣናት፣ በፌዴራሊዚም ላይ ጥናት የሚያደርጉና የሚያስተምሩ ምሁራን፣ እንዲሁም የተቃዋሚ ፓርቲ አመራሮች ተገናኝተው በአገሪቱ የፌዴራሊዝም ሥርዓተ መንግሥት ግንባታ ሒደት ላይ ያሉ መልካም ተሞክሮዎችና ተግዳሮቶች ላይ ውይይት አድርገዋል፡፡
በተለይም አገሪቱ ካለፉት ሦስት ዓመታት ወዲህ የገጠሟትን በርካታ ፈተናዎች ለመቅረፍና የነበረውን ሰላምና መረጋጋት መልሶ ተግባራዊ ለማድረግ፣ የፌዴራሊዝም ሥርዓተ መንግሥቱ ድርሻ ምን ነበር? ምን መሆን ነበረበት? የሚሉ ጥያቄዎች ለውይይት መነሻ ሐሳቦች ቀርበውም ሞቅ ያለ ውይይትና ክርክር ተደርጎባቸው ነበር፡፡
በዕለቱ ኢሕአዴግን በመወከል የገንዘብና ኢኮኖሚ ልማት ትብብር ሚኒስትር አብርሃም ተከስተ (ዶ/ር) የመንግሥት የፋይናንስ ክፍፍልና ለአሳታፊ ልማት ባለው ትርጉም ላይ መነሻ የውይይት ሐሳብ ያቀረቡ ሲሆን፣ የፌዴራልና የአርብቶ ጉዳዮች ሚኒስቴር ዴኤታ አቶ ሙሉጌታ ውለታው ደግሞ የፌዴራሊዝም ሥርዓት በኢትዮጵያ የፈጠረውን ዕድልና ያጋጠመውን ፈተና መሠረት ያደረገ የመነሻ የውይይት ሐሳብ አቅርበዋል፡፡
ከዚህ በተጨማሪም ከተቃዋሚ ፖለቲካ ፓርቲዎች ወገን ደግሞ መረራ ጉዲና (ዶ/ር) ኢትዮጵያ መስቀለኛ መንገድ ላይ በሚል ርዕስ እንዲሁ የመነሻ የውይይት ሐሳብ ያቀረቡ ሲሆን፣ አቶ ልደቱ አያሌውም አሁን አገሪቱ ለገጠማት ችግር መንስዔዎችና መፍትሔዎች ላይ ያተኮረ የመነሻ የመወያያ ሐሳብ አቅርበዋል፡፡
ምንም እንኳን እነዚህ ጽሑፍ አቅራቢዎች የፌዴራሊዝም ሥርዓተ መንግሥት ለአገሪቱ መፃኢ ዕጣ ፈንታ ያለውን አጠቃላይ ጠቀሜታ፣ እንዲሁም ከዚህ አንፃር የገጠሙትን ፈተናዎች በተለመደው መንገድ በማቅረብ የሐሳብ መንሸራሸር እንዲኖር አስችለው የነበረ ቢሆንም፣ በዕለቱ በአብዛኛው ተሳታፊዎች ዘንድ ከፌዴራሊዚም ሥርዓተ መንግሥት አንፃር አዲስ አቅጣጫ እየመጣ እንደሆነ የጠየቀው የፕሮፌሰር አንድርያስ እሸቴ የመክፈቻ ንግግር የብዙዎችን ቀልብ የሳበ ነበር፡፡
ፕሮፌሰር አንድርያስ በንግግራቸው ላይ ‹‹በቅርቡ በኢሕአዴግ ቁልጭ ብሎ ጉልህ ሆኖ ባይወጣም ወደ ሊብራል ዴሞክራሲ የመሸጋገር አዝማሚያ ምልክቶች ይታያሉ፤›› በማለት፣ በተለይ ከጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ መመረጥ በኋላ የታየውን የኢሕአዴግ የርዕዮተ ዓለም አቅጣጫ ላይ አስተያየታቸውን ሰንዝረዋል፡፡
‹‹ሊብራላዊ ዴሞክራሲ አዝማሚያው ትክክክል ከሆነ ወይም ህያው ከሆነ ላይሆንም ይችላል፡፡ በአገራችን ተግባራዊ ከተደረገ ለፖለቲካ ሕይወታችን እጅግ እንግዳ አቅጣጫ ነው፤›› በማለት፣ የሊብራል ዴሞክራሲን መከተል የሚጀመር ከሆነ እንግዳ አቅጣጫ ከመሆኑ አንፃር አሁን ካለው የፌዴራል ሥርዓት አወቃቀር ጋር እንዴት እጅ ለእጅ ተያይዞ ሊሄድ እንደሚችል አስተያየት ሰንዝረዋል፡፡
ምንም እንኳን አሁን ኢሕአዴግ የሊብራል ዴሞክራሲ አዝማሚያዎች ይታዩበታል ቢሉም፣ ከኢሕአዴግ ውጪ ሌሎች ኃይሎች ሊብራል ዴሞክራሲን የሚሹ ቀደም ሲሉ እንደነበር ጠቅሰዋል፡፡ በተለይም በምርጫ 97 ወቅት ይኼን መሰል አመለካከት የነበራቸው ተፎካካሪዎች መታየታቸውን በማስታወስ፣ ከዚህ በተጨማሪም በሽግግሩ ወቅት ለሊብራል ዴሞክራሲ የተሟገቱ ወገኖች እንደነበሩ አውስተዋል፡፡ ለአብነትም የሕገ መንግሥቱ አርቃቂ ከነበሩት አንዱን አቶ ክፍሌ ወዳጆን አንስተዋል፡፡
ኢሕአዴግም ቢሆን አብዮታዊ ዴሞክራሲ ለሊበራል ዴሞራሲ የሚያበቃ መንገድ ቀይሶ፣ እዚያ ላይ ሲደርስ ራሱንና አመለካከቱን የሚያገል ኃይል ነኝ ባይ እንደነበር ፕሮፌሰሩ አውስተዋል፡፡
ለዚህም ሽግግር መሳካት የኢንዱስትሪያዊ ኢኮኖሚ መስፋፋት፣ በዚያውም የመካከለኛ ገቢ ባለቤትና የኢንዱስትሪ ሠራተኛ መደብ ማደግና መደራጀት መለኪያዎች ተብለው እንደነበር ጠቁመዋል፡፡
በእነዚህ መለኪያዎች መሠረት አሁን እየታየ ያለውን ወደ ሊብራል ዴሞክራሲ የማዘንበል አዝማሚያን ምን አፋጠነው ብሎ መጠየቅን ወደ ጎን አድርገው፣ ከዚህ በፊት የነበረውንና የዘንድሮውን የሊብራል ዴሞክራሲ አዝማሚያ በምን እንደሚለያይ ለማሳየት ሞክረዋል፡፡
‹‹የቀድሞው ምንጩ አዲስ አበባና ከተሜው የነበረ ሲሆን፣ የዘንድሮው ግን ወደ አዲስ አበባ ያመራው ከክልል ተነስቶ በገጠሬው ተደግፎ ነው፡፡ በተጨማሪም የቀድሞው በተለይ በሽግግሩ ወቅት ሊብራል ዴሞክራሲ በዓለም ድል አድራጊ ኃይል ሆኖ የቀረበበት ሲሆን፣ ዘንድሮ ግን በምዕራብም ሆነ በሌላው የዓለም ክፍል በሊብራል ዴሞክራሲ መተማመን የቀዘቀዘበት ጊዜ ነው፤›› በማለት ሊብራል ዴሞክራሲ ለመገንባት የሚታየው አዝማሚያ የነበሩትን ልዩነቶች አሳይተዋል፡፡
በዚህ ሁኔታ የሊብራል ዴሞክራሲ በአገሪቱ ውስጥ የበላይነት ካገኘ አጠቃላዩ የፖለቲካ ሁኔታ በተለይ በፌዴራላዊ ሥርዓተ መንግሥት ላይ ምን ሊያስከትል ይችላል የሚለውን ጥያቄ አንስተዋል፡፡
ከዚህ አንፃር የፌዴራል ሥርዓት ግንባታውን ሒደት በአጭሩ በመዳሰስ፣ ከወታደራዊው ወደ አሁኑ ሥርዓት ሽግግር በተደረገበት ወቅት የመከፋፈልና የመለያየት አደጋዎች በአገር ውስጥም በውጭም በሚንቀሳቀሱ ኃይሎች አንዣቦ እንደነበር አስታውሰዋል፡፡
ከብሔር ስብጥርና ጭቆና በላይ በረሃብና ሥር ሰደድ ድህነት የተገረፈ አገር ለተማከለ ሥርዓት ምቹ እንዳልነበር አስታውሰው፣ ይኼን ችግር ለመፍታትና ‹‹የአገሪቱን አንድነት በአዲስ መሠረት መገንባት በእጅጉ አስቸኳይ ጉዳይ ነበር፤›› በማለት፣ የፌዴራል ሥርዓቱ የግንባታ ሒደትን ወደ ኋላ መለስ ብለው ቃኝተዋል፡፡
ኢሕአዴግ ለፈጠረው ግንባር ዋነኛው መሣሪያ አብዮታዊ ዴሞክራሲ ነው በማለት የመንግሥትን ርዕዮተ ዓለም የገለጹት ሲሆን፣ የአብዮታዊ ዴሞክራሲም ዋነኛ ተልዕኮ እጀግ የደኸየውንና በታሪክ የተበደለውን ገጠሬውን ያስቀደመ ፈጣን ልማት ማምጣት ነው ብለዋል፡፡
በጠቅላላው በዚህ አካሄድ ኢሕአዴግ የልማት ትኩረቱና ውጤቱ በብዙኃን ተጠቃሚነት ከሞላ ጎደል ድጋፍ ለማግኘት አብቅቶታል፡፡ ‹‹ይህም ያለ ፌዴራልና ክልላዊ መንግሥት ጥብቅ ትስስር አንድ ወጥ አካሄድ ዘበት ነው፤›› በማለት፣ ኢሕአዴግ ለሚከተለው አብዮታዊ ዴሞክራሲ ፌዴራላዊ ሥርዓት ዋነኛ ማጠንጠኛ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡
ከዚህ አንፃር በቅርቡ የፈለቁት ችግሮች የዴሞክራሲያዊ ማዕከላዊነት በከፊልም ቢሆን የመዳከም ምልክቶች ሊሆኑ ይችላሉ በማለት አብራርተዋል፡፡ ‹‹የሆነ ሆኖ የነበረውን አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ማዕከላዊነትን ትተን ወደ ሊብራላዊ ዴሞክራሲ ካዘነበልን አዲሱ ዴሞክራሲ ከፌዴራላዊ ሥርዓቱ ጋር እንዴት ይጣጣማል?›› በማለት ትኩረት የሚሻውን ጥያቄ ሰንዝረዋል፡፡
የዚህም ጥያቄ ማጠንጠኛ፣ ‹‹ከፌዴራላዊ ሥርዓቱ በቅርቡና በቀላሉ መላቀቅ አይቻልም፡፡ ፌዴራላዊ ሥርዓቱ ማንነት፣ ብሔራዊ ራዝ ገዝነት ሥር ሰዶ በአደባባይ የራሱን ሕይወት አግኝቶ ባደገበት ይኼን ላስወገድ ወይም እጅግ በተለየ መንገድ መልሼ ልቀይስ ቢባል ቀላል አይሆንም ከሚል እምነት የተነሳ ነው፤›› በማለት ጥያቄውን አጠናክረው አቅርበውታል፡፡
ፌዴራላዊ ሥርዓተ መንግሥቱ የሚወስንበት ከሆነና ሊብራላዊ ዴሞክራሲ ዕውን ከሆነ ሁለቱ አብሮ መጓዝ ይችላሉ? እጅግ ኋላ ቀርና ደሃ አገር ውስጥ የመንግሥት ቀዳማይ ተግባር ድህነትን ማጥፋትና ልማትን ማረጋገጥ ነውና ይኼንን ከፍተኛ ኃላፊነት ሊብራላዊ ዴሞክራሲ በፌዴራላዊ ኢትዮጵያን እንዴት ይወጣዋል? በመንግሥት የሚመራ ረዥምና ቀጣይ የፖሊሲ ዕቅድ፣ እንዲሁም በሰፊና የተቀናጀ የሕዝብ ተሳትፎ የተደገፈ ልማታዊ አስተዳደር ሊኖር ይችላል? በማለት ዋነኛ መሠረታዊ ጥያቄዎችን ሰንዝረዋል፡፡
ከዚህ በተጨማሪም በሊብራል ዴሞክራሲ ሊጠቀሱ የሚችሉ ሊብራላዊ ግቦችን ለምሳሌም ራስን የመግለጽና የሚዲያ ነፃነትን ማክበርና ማስከበር፣ ነፃ፣ ገልተኛና ፍትሐዊ የምርጫ ሥርዓት መዘርጋት፣ መንግሥታዊ ላልሆኑ ማኅበራት በነፃ መደራጀትና መነቃነቅ ዋስትና መስጠት፣ የሰብዓዊ መብትና የሕግ የበላይት ማረጋገጥ እንዴት ማካተት እንደሚቻል ሊታሰብበት እንደሚገባ አውስተዋል፡፡
ሆኖም ሊብራላዊ አጀንዳው እንዲሳካ ከተፈለገ ፌዴራላዊ መንግሥቱም ሁሉም ክልላዊ መንግሥታት እንዲያከብሩትና እንዲያስከብሩት ማድረግ እንደሚኖርበት አሳስበዋል፡፡ ይኼ ደግሞ በክልል መንግሥታት አንድ የሥልጣን ሥጋት ካሳደረ ወይም ደግሞ በሌላ ምክንያት ተቀባይነትና ትብብር ካላገኘ ፌዴራል መንግሥት ምን ማድረግ ይችላል? በሃይማኖት ወይም በሌላ መነሻ የግል ወይም የጋራ መብቶችን የሚደፍሩ ክልላዊ ኃይሎች ቢነሱ የፌዴራል መንግሥት የተበደሉትን ለመከላከልስ ምን ሰላማዊ መሣሪያ ይኖረዋል? ከፍተኛ የተፈጥሮ ሀብት ያገኘ ክልል ሀብቱን በተመጣጣኝ ለሌሎች አላካፍልም ቢል ፌዴራል መንግሥት እንዴት በሰላም ያግባባዋል? ፌዴራል መንግሥት እነዚህን ችግሮች በኃይል ለመወጣት ቢከጅልና የእርስ በርስ ግጭት ቢስፋፋ ሊብራል አጀንዳው እንደሚቀጭ በመጥቀስ፣ አሁን እየተሄደበት ያለው ወደ ሊበራል ዴሞክራሲ የማዝመም አዝማሚያ በቅጡ ሊጤን እንሚገባው አፅንኦት ሰጥተዋል፡፡
በዕለቱ የመወያያ ሐሳብ ካቀረቡት መካል አብርሃም ተከስተ (ዶ/ር) አንዱ ሲሆኑ፣ እርሳቸውም በፌዴራላዊ ሥርዓተ መንግሥት አወቃቀር ውስጥ የአገሪቱን ዜጎች በፍተሐዊነት ከልማቱ ተጠቃሚና ተሳታፊ ከማድረግ አንፃር መንግሥት የሠራቸውን ሥራዎች አውስተዋል፡፡
በዚህም መሠረት ከሽግግር መንግሥቱ ምሥረታ ጀምሮ መንግሥት ፍትሐዊነትን ለማስፈን የተከተላቸውን ስትራቴጂዎች፣ ፖሊሲዎችና አቅጣጫዎች በዝርዝር በማቅረብ ምን ምን እንዳካተቱና ሕዝቡን የልማቱ ተጠቃሚ ከማድረግ አንፃር የተሠሩ ሥራዎችና ስኬቶች ላይ ያተኮረ ገለጻ አድርገዋል፡፡
ከዚህ አንፃር በተለያዩ ወቅቶች በመንግሥት የተረቀቁ ፖሊሲዎችንና ስትራቴጂዎችን ለማሳካት ዋነኛው መንገድ ግብርና መሆኑን፣ ከግብርናም የአነስተኛ አርሶ አደሮች ግብርና መሆኑን በከፍተኛ ሁኔታ በማመን መንቀሳቀሱን አውስተዋል፡፡
በተመሳሳይ አቶ ሙሉጌታ ውለታው የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ሥርዓትን በተመለከተ ማብራርያ የሰጡ ሲሆን፣ በማብራርያቸውም የፌዴራል ሥርዓቱን ትሩፋቶችና ፈተናዎች ላይ ያተኮረ ገላጻ አድርገዋል፡፡
‹‹ባለፉት ሦስት ዓመታት የሕግ የበላይነት በእጅጉ ተጎድቷል፣ ሰዎችና ቡድኖች ከሕግ በላይ ነበሩ፡፡ መንግሥትን እያስፈራሩ፣ እያስጨነቁና ንብረት እያወደሙ ጥያቄያቸውን ለማስመለስ የሄዱበት ሁኔታ ተፈጥሮ ነበር፤›› በማለት፣ ፌዴራላዊ ሥርዓቱ ያጋጠመውን ፈተና አብራርተዋል፡፡
‹‹እነዚህን ችግሮች ለመፍታትና ፌዴራላዊ ሥርዓቱን ለማስቀጠል በዋነኛነትና በቀዳሚነት ሰላምና መረጋጋትን መፍጠር አለብን፤›› ብለው፣ ‹‹እነሱን ተከትለን የለየናቸውን ችግሮች እንፍታ፡፡ ብሔራዊ መግባባትን እናጎልብት፡፡ ከተቃዋሚ ፓርቲዎች ጋር ተቀራርበን እንሥራ፡፡ የዴሞክራሲ ምኅዳሩን እናስፋ፤›› በማለት ፌዴራላዊ ሥርዓቱን ከማስቀጠልና ሰላምና ደኅንነትን ከማረጋገጥ አንፃር ሊሠሩ ስለሚገባቸው ሥራዎች አፅንኦት ሰጥተው ሐሳባቸውን ሰንዝረዋል፡፡
ኢሕአዴግ ወደ ሊብራል ዴሞራሲ እያዘነበለ ነው? ወይስ በቀደመው መስመሩ እየተጓዘ ነው? የሚለው ውይይት እንዳለ ሆኖ፣ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ ያደረጓቸው ንግግሮች የሊብራል ዴሞክራሲን እሴቶች የሚያስተጋቡ መሆናቸው ቢወሳም፣ ለውይይት አልታደለም፡፡
ፕሮፌሰር አንድርያስ እሸቴ ላቀረቧቸው ጥያቄዎችና አስተያየቶች መልካም ምላሽና ውይይት ቢደረግ ደስ እንደሚሰኙ ገልጸዋል፡፡ ከላይ የተዘረዘሩትን አስተያየቶች ችላ ማለት እንደሚከብድም ጠቁመዋል፡፡
‹‹ይሁንና ብንቀበላቸውም ባንቀበላቸውም ከሊብራል ዴሞክራሲና ከፌዴራል ሥርዓት ከመምረጥ ወይም ማስታረቂያ ዘዴ ከመፈለግ አይከለክሉንም፡፡ በትግልም ሆነ በምርምር ለኢትዮጵያ ደጉን የሚሹ ሁሉ የቀረበውን ጥያቄ ቢያብላሉ ለአገሪቱ መልካም ይመስለኛል፡፡ እኔንም ያስደስኛል፤›› በማለት ሐሳባቸውን ቋጭተዋል፡፡
ፕሮፌሰሩ ይኼንን መነሻ ሐሳብ ይዘው ምላሽ ቢጠብቁም፣ ውይይቱ ያተኮረው ግን በቀረቡት ሌሎች ጽሑፎች ላይ ነበር፡፡