ተሾመ ተስፋዬ (የሕግ ባለሙያ)

ዕውቁ የሰላማዊ ትግል አባት ማሕተመ ጋንዲ “ምድር ለሁላችንም የሚያስፈልገንን ለማሟላት የምትበቃ ቢሆንም የእያንዳንዳችንን ስግብግነት ግን ማሟላት አትችልም፡፡” በማለት ዘመን ተሻጋሪ መልዕክት አስተላልፎልናል፤ ሰሚ ከተገኘ፡፡ በአገራችን ተንሰራፍቶ ለሚገኘው ስግብግብነትና ሙስና በጊዜ መላ ካልተበጀለት እንደ አገር የመቀጠላችን ዕድል ጭምር አደጋ ላይ ሊወድቅ የሚችል መሆኑን ለማስረዳት አቅም ያለው ይመስለኛል፤ ሰሚ ከተገኘ፡፡ በአገራችን ያለው ሙስና አስጊ ሁኔታ ላይ የደረሰውና መፍትሔ ያላገኘው ገዢው ፓርቲ ሥልጣን ከያዘበት ጊዜ አንስቶ ሥልጣኑን ለማደላደል ሲፈጽማቸው ከነበሩ ፖለቲካዊ ሙስናዎች ጋር የተቆራኙ በመሆናቸው ነው፡፡ ሙስና የሚፈጸመው በባለሥልጣናቱ ብቻ ሳይሆኑ ገዢው ፓርቲ እራሱ ሥልጣኑን ያደላደለው የተለያዩ ፖለቲካዊ ሙስናዎችን በመፈጸም ነው በማለት ብዙዎች ይከራከራሉ፡፡

ኢሕአዴግ ሥልጣን በያዘ ማግስት በወቅቱ በነበረው ዓለም ዐቀፍ ሁኔታዎች ግፊት እና የምዕራባዊያንን ድጋፍ ለማግኘት በማሰብ የታገለለትን የአብዮታዊ ዴሞክራሲ ርዕዮት ለጊዜው መሳቢያ ውስጥ በመክተት በሊብራሊዝም አስተሳሰብ የተቃኘ የነጻ ኢኮኖሚ ሥርዓት ለመገንባት ቃል ገብቶ የነበረ መሆኑ ይታወቃል፡፡ በዚሁ መሠረት የፖሊሲና የሕግ ማሻሻያዎችን ያደረገ ቢሆንም ሂደቱ ፖለቲካዊ ሙስና የተፈፀመበት ነበር በማለት በርካቶች ይተቻሉ፡፡ ለምሳሌ አቶ ጉደታ ከበደ በጥናታዊ ጽሑፋቸው ላይ ሌሎች የውጭና የአገር ውስጥ ጥናቶችን ዋቢ በማድረግ ኢሕአዴግ በወቅቱ የነበረውን የሥልጣን የበላይነት በመጠቀም ግልጽነት በጎደለውና አድልዎ በሰፈነበት አሠራር የመንግሥትና የሕዝብን ንብረት ከፓርቲው ጋር ለተጣቡ የኢንዶውመንት የንግድ ድርጅቶችና ደጋፊ ግለሰብ ነጋዴዎች በማዛወር ፖለቲካዊ ሙስና ፈጽሟል በማለት ይሞግታሉ፡፡

መንግሥት በበኩሉ ድርጅቶቹ ለሕዝብ ጥቅም የተቋቋሙ እንጂ የፓርቲ ንብረት አይደሉም፤ የተፈፀመ አድልዎም የለም በማለት ከመከራከር ቦዝኖ አያውቅም፡፡ ተቺዎቹ ግን ድርጅቶቹ ኢንዶውመንት የሚለውን ስም ከመያዝ ባለፈ በአገሪቱ ኢንዶውመንት ሕግ መሠረት የማይተዳደሩ፣ በፓርቲውና በመንግሥት ከፍተኛ ባለሥልጣናት የሚመሩና ልዩ ድጋፍ የሚደረግላቸው፣ ለሕዝብ ጥቅም ሳይሆን ፓርቲው አጠቃላይ ኢኮኖሚውን በመቆጣጠር ሥልጣኑን ለማደላደል የተጠቀመባቸው መሆኑን ይገልጻሉ፡፡ ጉዳዩ እስካሁንም መቋጫ ያልተበጀለት ቢሆንም ተጨባጭ እውነታው ሲታይ የተቺዎቹ ሐሳብ ሚዛን የሚደፋ መሆኑ ላይ ብዙዎች ይስማማሉ፡፡

የ“ዝንቦቹ” ወረራ
***

መልካም አስተዳደርን ማስፈንና ሙስናን መከላከል የሚቻለው ከፖለቲካ ገለልተኛ ሆኖ በሙያዊ ብቃት የሚመራ የሲቪል ሰርቪስ ተቋም ሲኖር እንደሆነ አያከራክርም፡፡ ይህን ተግባራዊ ለማድረግ ደግሞ የመንግሥት ሠራተኞች ቅጥርና የዕድገት አሰጣጥ ሥርዓት ብቃትንና የሥራ ውጤት ምዘናን መሠረት ያደረገ ሊሆን ይገባል፡፡ የዓለም ባንክ እ.ኤ.አ. በ1997 ባወጣው ሪፖርት ላይ እንደተመለከተው መንግሥት ሙስናንን ለመዋጋትና መልካም አስተዳደርን ለማስፈን የሲቪል ሰርቪስ ማሻሻያ ፕሮግራም ለማድረግ ቃል ገብቶ ነበር፡፡ ማሻሻያውን ተግባራዊ ለማድረግም በርካታ የፖሊሲ፣ የሕግ እና የመዋቅር ለውጦች ተደርገው ነበር፡፡ ሆኖም ፕሮግራሙ የተተገበረበት መንገድ እና ውጤቱ ሲታይ ሲቪል ሰርቪሱ ገለልተኛ ሆኖ መልካም አስተዳደርን ከማስፈን ይልቅ በገዢው ፓርቲ ፖለቲካዊ ቁጥጥሩ ሥር እንዲውል ተደርጓል ማለት ይቻላል፡፡ መንግሥት በተለይም ከፍተኛና መካከለኛ የመንግሥት ሠራተኞችን ለመሾምና ለመመደብ የተከተለው ፖሊሲ ለጉዳዩ ከፍተኛ አስተዋጽዖ አለው፡፡ መንግሥት ከትምህርትና ብቃት ይልቅ የፖለቲካ ታማኝነትንና የብሔር ተዋጽዖን እንደዋና መስፈር እንደሚጠቀም ተደጋግሞ የተገለጸ ጉዳይ ነው፡፡ አቶ መለስ እራሳቸው አንድ ሰው የኢሕአዴግ ፖሊሲን እስከተቀበለና ለድርጅቱ ታማኝ እስከሆነ ድረስ ትምህርት ባይኖረውም ሚኒስትርም ሆኖ ሊሾም እንደሚችል በአደባባይ መናገራቸው አይዘነጋም፡፡

በ1993 የሕወሓት ክፍፍልን ተከትሎ በተካሄደ የማዕከላዊ ኮሚቴ ጉባኤ ላይ አቶ መለስ በትግርኛ ጽፈው ባቀረቡት የመወያያ ሰነድ ላይ “…. ሥልጣን የያዝን በመሆኑ ወደ እኛ የተጠጋ የተለያዩ ጥቅሞችን ማግኘቱ አይቀርም፡፡ ማር ባለበት አስቀድሞ የሚያንዣብበው ዝንብ ነው፤ ሥልጣን ባለበት ደግሞ አስቀድሞ የሚያንዣብበው ከዚሁ ተጠቃሚ መሆን የሚፈልግ ነው፡፡ ዝንብን ከንብ የምትለይበት ተጨባጭ መስፈርት እስከሌለ ድረስ የሚካሄደው ምልመላ አጋጣሚ ብቻ ሳይሆን፣ ንብና ዝንብ ተደባልቀው ለመለየት የሚያስቸግሩበትና በርካታ ዝንቦች የሚያንዣብቡበት ይሆናል፡፡” የሚል ትርጉም ያለው ሐሳብ ማስፈራቸውን አቶ ገብሩ አሥራት “ሉዓላዊነትና ዴሞክራሲ በኢትዮጵያ” በሚለው መጽሐፋቸው ላይ ገልጸዋል፡፡ መንግሥት የተሿሚውን ፖለቲካዊ ድጋፍ የሚያገኝ ሲሆን ተሿሚው ደግሞ ኢኮኖሚያዊና ተዛማች ጥቅሞችን ያገኛል፡፡ በተለይም ከምርጫ 97 በኋላ ኢሕአዴግ አባላትን ለማብዛት ባደረገው ሰፊ እንቅስቃሴ የተነሳ ዝቅተኛ ሥራ ለማግኘት እንኳን የፓርቲ አባልነት የሚጠየቅበት ደረጃ ላይ መደረሱ የአደባባይ ሚስጢር ነው፡፡ ኢሕአዴግ ሲመጻደቅበት የነበረው የ6 ሚሊዮን አባላት አለኝ ጉራም የጥቅም ትስስር ላይ የተመሠረተ ነው ለማለት ይቻላል፡፡ የብሔር ተዋጽዖን ለማመጣጠን መሞከር አገሪቱ ከምትከተለው የብሔር ፌደራሊዝም መርሆ አንጻር ተቀባይነት ያለው ቢሆንም የፖለቲካ ታማኝነትን እንደዋና መስፈርት መውሰዱ ግን ፖለቲካዊ ሙስና ነው፡፡

አሠራሩ ከገዢው ፓርቲ የተለየ የፖለቲካ አስተሳሰብ ያላቸውንና ገለልተኛ ሆነው ለመሥራት የሚፈልጉ ዜጎች እንዲገለሉ አድርጓል፡፡ በፖለቲካና በመንግሥት ሥራ መካከል ግልጽ ድንበር ባለመበጀቱም ሲቪል ሰርቪሱ በገዢው ፓርቲ አባላት፣ ደጋፊዎችና ጥቅም ፈላጊ አስመሳዮች እንዲሞላ ሆኗል፡፡ ለብልሹ አስተዳደርና ሥር ለሰደደ ሙስና እንዲጋለጥ በማድረግ አገር ላይ ኪሳራ አድርሷል፡፡

ሙስናን በግለ ሂስ የማለፍ ፖለቲካዊ አካሄድ እና የሕግ የበላይነት
***

ሕወሓት በትጥቅ ትግል ወቅት ጥብቅ የግምገማ ባሕል እንደነበረው ይታወቃል፡፡ ሂደቱ ከዴሞክራሲያዊነትና ከሰብአዊ መብት አንጻር ጥያቄ ሊቀርብበት ቢችልም በርካታ የዲሲፕሊንና ሌሎች ግድፈቶች በማረም በኩል ጉልህ ሚና እንደነበረው ብዙዎች ይመሰክራሉ፡፡ የዛሬን አያድርገውና አንድ ታጋይ የገበሬ ሚስት አሽኮርምመሃል በሚል እንኳን እርምጃ ይወሰድበት እንደነበር ይጠቀሳል፡፡ ይህ ጥብቅ የአባላት ዲሲፕሊን ትግሉ በሚካሄድበት አከባቢ ያሉትን ሕዝቦች ሰፊ ድጋፍ በማስገኘት ድርጅቱ ለድል እንዲበቃ የጎላ አስተዋጽዖ እንደነበረው ነው የሚነገረው፡፡ ሆኖም ድርጅቱ መንግሥት ከሆነ በኋላ የሚያደርጋቸው ግምገማዎች ሕግን የሚጥሱበት አጋጣሚዎች ስላሉ በብዙዎች ይተቻል፡፡ ኢሕአዴግ ደጋፊዎቹንና አባላቱን ሙስና ፈጽመው ሲገኙ በሕጉ መሠረት ጉዳያቸው ለሚመለከተው የፍትሕ አካል ቀርቦ እንዲታይ ከማድረግ ይልቅ በግለ ሂስ እንዲታለፉ ወይም የዲሲፕሊን እርምጃ በመውሰድ ብቻ እንዲታለፉ የሚያደርግባቸው አጋጣሚዎች በርካታ ናቸው፡፡ እንደሚታወቀው ድርጅቱ የፓርቲ ሥራውን በከፍተኛ ሚስጥራዊነት የሚሠራ ቢሆንም በአንዳንድ አጋጣሚዎች ሁኔታው ፍንትው ብሎ ታይቷል፡፡ አቶ ገብሩ አሥራት ከላይ በተጠቀሰው መጽሐፋቸው ላይ ሕወሓት ሥልጣን በያዘ ማግስት ከፍተኛ አመራሮቹ ከተለመደው ሶሻሊስታዊ የአኗኗር ዘይቤ በተለየ የተንደላቀቀ ኑሮ በመጀመራቸውና ሙስናም እየተለመደ መምጣቱን ተከትሎ ዝቅተኛው ካድሬ ቅሬታ በማቅረቡ፣ ጉዳዩ በ1985 ዓ.ም. ለሕወሓት ማዕከላዊ ኮሚቴ በቀረበበት ወቅት ችግሩ በተወሰነ ደረጃም ቢሆን መኖሩ የታመነ ቢሆንም ድርጅቱ አደጋ ላይ ይወድቃል በሚል ምክንያት በከፍተኛ አመራሩ ላይ እርምጃ እንዳልተወሰደ፣ ይልቁንም የታችኛው ካድሬ ላቀረበው ቅሬታ ፖለቲካዊ ትርጉም በመስጠት እርምጃ የተወሰደባቸው መሆኑን በጸጸት እንደሚያስታውሱት ገልጸዋል፡፡

የምርጫ ቦርድ ሊቀመንበር የነበሩት አቶ አሰፋ ብሩ በሙስና ተጠርጥረው ከተያዙ በኋላ ግለ ሂስ አውርደዋል በሚል በፖለቲካዊ ድርድር የተለቀቁበት አጋጣሚ በይፋ የተከወነ ነው፡፡ በ2001 ዓ.ም. ኢሕአዴግ ባደረገው ግምገማ ላይ በርካታ ባለሥልጣናት አላግባብ መሬትና ሌሎች ንብረቶችን መውሰዳቸውን አምነው በሕግ ሳይጠየቁ በድርጅታዊ እርምጃ ብቻ መታለፋቸው ይታወሳል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም በቅርቡ ከንግዱ ማኅበረሰብ ጋር ባደረጉት ስብሰባ ላይ “ወደ እስር ቤት የሚያስገባ” ተግባር የፈፀሙ የሪል እስቴት አልሚዎች ቢኖሩም “እስር ቤቱን ላለማጣበብ” ተደራድረው ያለፉበት ሁኔታ መኖሩን ጠቅሰዋል፡፡ የሥርዓቱ መሠረታዊ ችግር የፀረ ሙስና ትግሉን እንኳን የፓርቲ ጉዳይ አድርጎ መመልከቱ ነው፡፡ የሚዘረፈው ሀብት የሕዝብ እንጂ የፓርቲው አይደለም፡፡ የሕዝብ ሀብት የዘረፈ ደግሞ የሚጠየቅበት የሕግ ሥርዓት ዘርግተናል ተብሏል፡፡ ታድያ አንዱን ተራ ሰበብ እየፈለጉ ማሰር እና ሌላውን እሹሩሩ ከማለት የባሰ በዜጎች መካከል ልዩነት ማድረግና የሕግ የበላይነትን መናድ አለ?

በቅርቡ የታሰሩት የገንዘብና ኢኮኖሚ ትብብር ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ዓለማየሁ ጉጆ “ጉዳዩ በፖለቲካዊ መግባባት ቢፈታ ጥሩ ነው” በማለት በፍርድ ቤት የተናገሩትም ይህንኑ የመንግሥት የአሠራር ባሕል ታሳቢ ያደረገ ነው ለማለት ይቻላል፡፡ ኢሕአዴግ የሚመራው መንግሥት የፖለቲካ ባሕል ሲቪል ሰርቪሱ የመልካም አስተዳደር ጉድለትና የሙስና መፈልፈያ እንዲሆን አድርጓል፡፡ መንግሥት ሕጋዊነትን በአደባባይ በመጣስ የሕግ የበላይነትን ንዷል፡፡ የፀረ ሙስና ትግሉ እንዲዳከም አድርጓል፡፡ በዜጎች መካከል በተለይም የድርጅት አባል በሆኑና ባልሆኑ መካከል ልዩነት እንዲፈጠርም አድርጓል፡፡ የሥርዓቱ አራማጆና ደጋፊዎች ሳይቀር ኢሕአዴግ በጥቅም ፈላጊዎችና አስመሳዮች በመሞላቱ የውደቀቱ ዋነኛ ጠንቅም ከዚህ ጋር እንደሚያያዝ ይገልጻሉ፡፡

“ትላልቅ ሙሰኞች” እና “የፀረ ሙስና ትግሉ” ፈተናዎች
***

ሙስና አቶ መለስ ለጥቅም ተጠጉን ያሏቸው “ዝንቦች” ብቻ ሳይሆን የብርቱ ታጋዮችም ጉልበት የተፈተነበት ጉዳይ ነው፡፡ የደርግ ወታደር መሣርያ አፈሙዝ ያልበገረውን የታጋዮች ልብ አፍረክርኮ በጓደኞቻቸው መስዋዕትነትና አደራ ላይ ተረማምደው ከዚህ ደሃ ሕዝብ በተዘረፈ ገንዘብ የአሜሪካና አውሮፓ ቱጃሮችን ጭምር የሚያስቀና ኑሮ ለመኖር ያስቻላቸው መሆኑ የአደባባይ ሚስጥር ነዉ፡፡ በኢትዮጵያ የሙስና ሁኔታ ላይ የተለያዩ ተቋማት በተለያየ ጊዜ ጥናት በማድረግ ውጤቱን ይፋ አድርገዋል፡፡ ጠቅለል ተደርጎ ሲታይም ሪፖርቶቹ በአገሪቱ ያለው ሙስና ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መምጣቱን፣ ከሌሎች አገሮች ጋር ሲነጻጸርም ከፍተኛ ሊባል የሚችል መሆኑን እና ሕዝቡ ለተለያዩ የመንግሥት ተቋማት ያለው አመለካከት ጥሩ እንዳልሆነ ያሳያሉ፡፡ መንግሥትም ሪፖርቶቹ የተጋነኑና እየተመዘገበ ያለውን ለማጠልሸት የቀረቡ መሆናቸውን በመጥቀስ የሚሞግት ቢሆንም ሙስናና ኪራይ ሰብሳቢነት መስፋፋቱንና በጊዜው ካልተቀጨ ልማቱን ሊቀለብስ የሚችል መሆኑን በተደጋጋሚ ከመግለጽ ተቆጥቦ አያውቅም፡፡ አቶ መለስ በሕይወት በነበሩበት ወቅት መንግሥት በሙስና አንድ እጁ የታሰረ መሆኑን እስከመግለጽ ደርሰው ነበር፡፡ ኢሕአዴግ በ2008 ዓ.ም. በባሕር ዳር ባደረገው ድርጅታዊ ጉባኤ ላይ ከፍተኛ አመራሩ ሙስናና ኪራይ ሰብሳቢነት ውስጥ እጁ ያለበት መሆኑ ተገልጿል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ ከከፍተኛ ባለሥልጣናት ጋር ባደረጉት አንድ የውይይት መድረክ ላይ አንዳንድ ከፍተኛ ባለሥልጣናት የሙስና ኔትዎርክ ውስጥ እንዳሉበት መናገራቸውም ይታወሳል፡፡

መንግሥት በቅርቡ ከ50 የሚበልጡ ባለሥልጣናትን፣ ነጋዴዎችንና ደላሎችን በሙስና ወንጀል በቁጥጥር ሥር ማዋሉን ለሕዝብ ይፋ ካደረገበት ጊዜ አንስቶ በጥናት ላይ የተመሠረተ መጠነ ሰፊ የፀረ ሙስና ዘመቻ በማድረግ ሙስናን ለመዋጋት ቆርጦ መነሳቱን እየገለጸ ይገኛል፡፡ ከእንግዲህ በየትኛውም የሥልጣን ደረጃ የሚገኝ ባለሥልጣን ሙስና ለመፈፀሙ ማስረጃ ከተገኘበት ተጠያቂ የሚሆን መሆኑንንም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ገልጸዋል፡፡ ሆኖም በአገራችን ያለው የሙስና ሁኔታ ከሥርዓቱ የፖለቲካ ህልውና ጋር የተሳሰረና ሥር የሰደደ ችግር በመሆኑ መሠረታዊ ፖለቲካዊ ለውጥ በማምጣት እንጂ በዘመቻ የተወሰኑ ባለሥልጣናትን በማሰር ይፈታል ማለት አይቻልም፡፡ መንግሥት የወሰደውን የእስር እርምጃ ዋነኛ ሙሰኛ የሆኑ ትላልቅ የመንግሥት ባለሥልጣናትን ያልነካ በመሆኑ የሕዝቡን ተቃውሞ ለማርገብና ትኩረት ለማስቀየር የተደረገ የተለመደ ድራማ ነው እየተባለ ከየአቅጣጫው ትችት እንደሚቀርብ ይታወቃል፡፡

እርምጃውን አስመልክቶ ጠቅላይ አቃቤ ሕጉ አቶ ጌታቸው አምባዬ ሐምሌ 22 ቀን 2009 ዓ.ም. ላይ መግለጫ በሰጡበት ወቅት ከፍተኛ አመራሩ ለምን በሕግ ተጠያቂ እንደማይሆን ማብራሪያ እንዲሰጡ ተጠይቀው መልስ በሰጡበት ወቅት “የመንግሥት ኃላፊነት ደረጃ ላይ ከፍተኛ የመወሰን ድርሻ ያለው በዳይሬክተርነት ደረጃ ያለው ኃይል ነው፡፡”፤ “የመንግሥት ሀብትና ገንዘብ በስፋት የማንቀሳቀስና የማሰማራት ኃላፊነት የተሰጠው ኃይል በዳይሬክተርነት ደረጃ ያለው ኃይል ነው፡፡ ጉዳዮችን የሚያመቻቸውና የሚፈጽመው ይኼ ኃይል ነው፡፡ ይህ ኃይል በሚያቀርባቸው የውሳኔ ሐሳቦችና ሙያዊ አስተያየቶች ላይ ተመሥርቶ ሚኒስትሩ ወይም ሚኒስትር ዴኤታው ሊወስን ይችላል፡፡” በማለት ያነሷቸው ሐሳቦች በብዙዎች ዘንድ አልተወደደላቸውም፡፡ የመንግሥት ደጋፊዎች ጭምር የሕግና ሌሎች ጥያቄዎች ያነሱበት ሲሆን ያስከፋ ሲሆን መንግሥት ትላልቅ ባለሥልጣናትን ለመያዝ ፍላጎት የሌለው ለመሆኑ ማሳያ ተደርጎ ተወስዷል፡፡

ሙስናን ለመዋጋት ከሚያግዙ አሠራሮች አንዱ የተሿሚዎችን ሀብትና ንበረት መዝግቦ መያዝና ለሕዝብ ይፋ ማድረግ፣ ከሀብትና ገቢያቸው ጋር ያልተመጣጠነ ንብረት እንዳለቸው ሲታወቅ ተጠያቂ የሚደረጉበትን የሕግ ማዕቀፍና አሠራር መዘርጋት ነው፡፡ ለዚህ እንዲረዳም ተሻሽሎ በወጣው የወንጀል ሕግ ምንጩ ያልታወቀን ሀብት ይዞ መገኘት በሙስና ወንጀል የሚያስጠይቅ ተግባር ሆኗል፡፡ የባለሥልጣናትና ቤተሰቦቻቸውን ንብረት መዝግቦ በማጣራት ውጤቱን ለሕዝብ ይፋ ለማድረግ የሚያስችል ሕግም ወጥቷል፡፡ ሆኖም ተመዘገበ የተባለው የባለሥልጣናትና የመንግሥት ሠራተኞች ሀብት ቃል በተገባው መሠረት ለሕዝብ ክፍት/ይፋ አልሆነም፡፡ መንግሥት በተደጋጋሚ ሕዝቡ ማስረጃ እንዲያቀርብ፣ የትኛውም ባለሥልጣን ሙስና ውስጥ መኖሩ ከተረጋገጠ ተጠያቂ አደርጋለሁ እያለ ነው፡፡ ሕዝቡ ደግሞ ባለሥልጣናቱ በራሳቸውና በቤተሰቦቻቸው፣ ካስፈለገም በቅምጦቻቸው ስም ያላቸውን ንብረት ስለማውቅ፣ ያስመዘገቡት ንብረት ግልጽ ይደረግና ልዩነቱ ይታወቃል እያለ ነው፡፡ መንግሥት ግን የተለያዩ ሰንካላ ምክንያቶችን በማቅረብ በእምቢታው ቀጥሎበታል፡፡ መንግሥት ሙስናን ለመታገል ቆርጬ ተነስቻለው እያለ በነበረበት በቅርቡ እንኳን ለኮሚሽኑ የኮሚኒኬሽን ጉዳዮች ቡድን አስተባባሪ አቶ ብሩክ ነጋሽ አዲስ ዘመን ጋዜጣ ስለጉዳዩ ጥያቄ አቅርቦላቸው “መረጃውን በጽሑፍ ለሚጠይቅ እየተሰጠ ነው፡፡ በዘንድሮው ዓመት ብቻ 78 መረጃዎች ጠቅላይ አቃቤ ሕግ፣ ፖሊስና ሌሎች አካላት ጠይቀው ወስደዋል፡፡ ይፋ መደረግ አለበት የሚለውን ግን ኮሚሽነሮቹ በተደጋጋሚ ከሰጡት መግለጫ የተለወጠ ነገር ስለሌለ ያንን መጠቀም ትችላላችሁ፡፡” ማለታቸውን ጠቅሶ ጽፏል፡፡ ይህም ጉዳዩን ይፋ ለማድረግ መንግሥት ፍላጎት የሌለው መሆኑን ያሳያል፡፡ ከዚህም በመነሳት ሕዝቡ ትላልቅ ባለሥልጣናት ተጠያነትን ለመከላከል ያደረጉት ነው የሚል ድምዳሜ ላይ እንዲደርስና መንግሥት እያደረገ ያለው የፀረ ሙስና ትግል ላይ ጥርጣሬ እንዲያድርበት አድርጓል ለማለት ይቻላል፡፡

ትላልቅ ባለሥልጣናት ተጠያቂነትን ለማስቀረት የፀረ ሙስና መታገያ የፍትሕ ተቋማትን የማሽመድመድ እና በሙስና ያገኙትን ሀብት የአገሪቱ ሕግ የማይደርስበት የውጭ ባንኮች የማስቀመጥ ድርጊት ውስጥ እንደሚገቡ ጥናቶች ያሳያሉ፡፡ ለመስማት የሚዘገንን የገንዘብ መጠን ከዚህ ደሃ ሕዝብ ተዘርፎ ወደውጭ እንደተሰደደ በበርካታ ሪፖርቶች ይፋ መሆኑ ይታወቃል፡፡ በዚህም የተነሳ የፀረ ሙስና ትግሉ የተወሳሰበና ዓለም አቀፍ ገጽታን የተላበሰ እንዲሆን አድርጓል፡፡ የሌሎች አገሮችና ዓለም አቀፍ ተቋማት ድጋፍ ታክሎበት ሰፊ ሕዝባዊ ንቅናቄ ካልተደረገ በስተቀር የተዘረፈን ንብረት ለማስመለስ አስቸጋሪ ይሆናል፡፡ የሥነ ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን ኮሚሽነር የነበሩት አቶ አሊ ሱለይማን የተለያዩ ተቋማት ይፋ ያደረጓቸው አለአግባብ ወደውጭ የወጡ ገንዘቦችን በተመለከት ስለተወሰደ እርምጃ ከአንዴም ሁለቴ ተጠይቀው እሱን ነገር አታንሱት ውስብስብ ነው የሚል ከእርሳቸው የማይጠበቅ ምላሽ መስጠታው ይታወሳል፡፡ በርካቶችም መልሳቸውን ትላልቅ ባለሥልጣናትን ተጠያቂ ለማድረግ ኮሚሽኑ ፍራቻ ያለው ለመሆኑ በማሳያነት ያቀርቡታል፡፡ ኮሚሽኑ በሕግ ደረጀ ነጻ ነው ቢባልም የሙስና ወንጀልን ከመመርመር ከመክሰስ ጋር በተያያዘ ከጣልቃ ገብነት ነጻ አለመሆኑን በርካታ ጥናቶች ያረጋግጣሉ፡፡ የምርመራና የክስ ሂደቶችን በአንድ ተቋም ሥር ለማሰባሰብ በሚል ሰበብ የሙስና ወንጀል የምርመራና የክስ ሥራ ከኮሚሽኑ ተነጥቆ ለጠቅላይ አቃቤ ሕግ እና ለፖሊስ መሰጠቱና በቅርቡም ኮሚሽነሩ በአምባሳደርነት ስም ገለል እንዲሉ መደረጉም የፀረ ሙስና ትግሉን የበለጠ ለማዳከም የተወሰደ እርምጃ አድርገው የሚቆጥሩ አሉ፡፡

ጥይት እና ስኳር
***

ጠንካራ የሲቪል መንግሥት በሌለበት ሁኔታ መከላከያው በሰፊው ወደ ኢኮኖሚው መግባቱ የፀረ ሙስና ትግሉን ከባድ የሚያደርገው መሆኑ አከራካሪ አይደለም፡፡ የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ መለስ ዜናዊ አገሪቱን ወደልማታዊ መንግሥት የዕድገት አቅጣጫ ከመሯት በኋላ የትራንስፎርሜሽን ዕቅዱን ለማሳካት ተስፋ የተጣለባቸው ትላልቅ የመንግሥት የልማት ድርጅቶች በብድር በተገኘ ገንዘብ ጭምር ግዙፍ ካፒታል ተመድቦላቸው መቋቋማቸው ይታወቃል፡፡ መከላከያውም ወደኢኮኖሚው ውስጥ በሰፊው እንዲገባ የተደረገ ሲሆን ግዙፍ ፕሮጀክቶችን የሚያንቀሳቅስ መሆኑ ይታወቃል፡፡ የአገር መከላከያ ሠራዊት በቴክኖሎጂ እና በአቅም መጠናከሩ የሚደገፍ ቢሆንም የግል የንግድ ተቋማት ሊሠሩት በሚችሉት የሲቪል ሥራዎች ላይ በስፋት መሰማራቱ ግን በሂደት ችግር ሊፈጥር የሚችል በመሆኑ በርካታ ሰዎች አስተያየታቸውን ሲሰጡበት ቆይተዋል፡፡ ለምሳሌ የዚህ መጽሔት አምደኛ እና የሕግ ጠበቃ የሆኑት አቶ ሄኖክ አክሊሉ ዕንቁ መጽሔት ላይ “ጥይት ከስኳር ይለይ!” በሚል ርዕስ በጻፉት መጣጥፍ ላይ መከላከያው በሂደት በኢኮኖሚው ውስጥ ገኖ ከወጣ የከፍተኛ ወታደራዊ ኦፊሰሮች የግል ተጠቃሚነትንና ጥቅምን ለማስጠበቅ የሚደረግ ትግልን ከመፍጠር አልፎ፣ ከሲቪል አስተዳደሩ ቁጥጥር ሥር በመውጣት በአገሪቱ ላይ የከፋ ችግር ሊያደርስ የሚችል መሆኑን የሌሎች አገሮችን ተሞክሮ በማሳያነት በማቅብ ስጋታቸውን ገልጸዋል፡፡

የመከላከያው ግዙፍ ኩባንያዎች በተቋቋሙበት ወቅት በአቶ መለስ ብርቱ ክንድ ሥር ስለነበሩ ያን ያህል ስጋት አልነበረም ለማለት ይቻላል፡፡ አቶ መለስ ሙስናን እንደፖለቲካ መሣርያ ይጠቀሙ የነበረ መሆኑ ባይካድም በባለሥልጣናቱና በወታደሩ ዘንድ ለአምልኮ የተጠጋ ተፈሪነት ስላላቸው እንዳሁኑ ተጠያቂነት የሌለበት ዝርፊያ ላይካሄድ ይችል ነበር ለማለት ይቻላል፡፡ እርሳቸውን የተኩት አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ የፖለቲካ ብቃታቸውና ተሰሚነታቸው ላይ በርካቶች ጥርጣሬ የነበራቸው ቢሆንም ከሙስና የጸዱ ናቸው ተብሎ ስለሚታመን በሂደት ኃይል አሰባስበው ሙስናን ይዋጋሉ በሚል ተስፋ ጥለውባቸው ነበር፡፡ ሆኖም ሁኔታዎች እንደሚያሳዩት ሰውየው ከሥልጣናቸው ጋር የሚመጣጠን ተፈሪነት የላቸውም፡፡ ከአቶ መለስ የተጠጋጋ ተፈሪነት ያለው ሌላ የሲቪል ኃይል አለ ለማለትም አይቻልም፡፡ ይህም የስጋቱን እውነትነት ሳያፋጥነው አልቀረም፡፡ መከላከያው ከሚገነባቸው ፕሮጀክቶቹ መጓተት ጋር በተያያዘ በነበሩ ውዝግቦች የስኳር ኮርፖሬሽኑ ባለሥልጣናት ከመከላከያው ጋር የነበረው የሥራ ግንኙነት በውል መሠረት እንደማይገዛና ጫና እንደሚያሳድርባቸው ማሳወቃቸው በመገናኛ ብዙሃን ይፋ መሆኑ ይታወሳል፡፡ በተቋሙ ውስጥ ለሙስና በር የሚከፍቱ የአሠራር ግድፈቶች እንዳሉ በዋና ኦዲተር ሪፖርቶች በተደጋጋሚ ሲገለጽና የማስተካከያ ምክር ሐሳብ ሲሰጥ ቢቆይም እስካሁን እርምጃ ለመውሰድ የደፈረ አካል አለመኖሩም ይህንኑ ይጠቁማል፡፡ ይህም መንግሥት እያደረኩ ነው በሚለው የፀረ ሙስና ትግል ስኬትና ተቀባይነት ላይ የጎላ ተጽዕኖ አለው ለማለት ይቻላል፡፡

ሕዝብን ያገለለ “የፀረ ሙስና ትግል” የት ያደርሳል?
***

መንግሥት በተለያየ ጊዜ ለፀረ ሙስና ትግሉ ወሳኝ መሆኑን በመግለጽ ሕዝቡ እንዲሳተፍ ጥሪ ከማቅረብ ቦዝኖ አያውቅም፡፡ ነገር ግን ጉዳዩን በትኩረት የሚከታተሉ አካላት ጥሪው አፋዊ ከመሆን ባለፈ ሕዝቡን ለማሳተፍ የሚያስችል ምቹ ሁኔታ መንግሥት አልፈጠረም በማለት ይተቻሉ፡፡ ተቺዎቹ ሲያስረዱ ሕዝቡ ተገቢውን ተሳትፎ ለማደረግ የሚችለው ነጻ የሲቪክና የሚዲያ ተቋማት ሊኖሩ ይገባል፡፡ አገሪቱ ባፀደቀቻቸው ዓለም አቀፍ እና አሕጉር አቀፍ ኮኒቬንሽኖች ላይ መንግሥት በሙስና ትግሉ ሂደት እነዚህን ተቋማት ለማሳተፍ ቃል ቢገባም በተጨባጭ ያለው እውነታ ሲታይ ግን ኮሚሽኑ ተቋማቱ ገለልተኛ አይደሉም፤ ፖለቲካዊ ተልዕኮ አለው የሚሉ ተገቢነት የሌላቸው ምክንያቶችን በመደርደር በርካቶችን ከተሳትፎ ሲያገል የነበረ ሲሆን፣ ምርጫ ዘጠና ሰባትን ተከትሎ በወጡ አፋኝ ሕጎችና አሠራሮች ጭራሽ ህልውናቸው እንዲከስም ተደርጓል በማለት ይሞግታሉ፡፡

መንግሥት በተለያዩ አጋጣሚዎች በሚያደርጋቸው ስብሰባዎች ላይም ዜጎች በመንግሥት አሠራር ላይ የሚያቀርቡት ተቃውሞ በቀናነት ተቀብሎ በምክንያትና ማስረጃ የተደገፈ መልስ ከመስጠት ይልቅ ልዩ “አጀንዳ አለህ”፤ “ፀረ ልማት ነህ” የሚሉና ሌሎች ውንጀላዎችን በመጠቀም ለመሸማቀቅ ጥረት ሲደረግ ማየት የተለመደ ነው፡፡ ታች ያሉ የቀበሌ አመራሮች ሳይቀር ሙስናን ለመሸፈንና ሕዝብን ለማግለል የተጠቀሙበት መሆኑን ሁኔታዎች ያሳያሉ፡፡ ከላይ እንደተገለጸው የባለሥልጣናት ሀብት ምዝገባ ይፋ አለመሆን ሲደመርበት ሕዝቡ በሙስና ትግሉ ላይ ጥርጣሬ እንዲያድርበትና መንግሥት ሙሰኛ ባለሥልጣናትን እየተከላከለ ነው የሚል ግንዛቤ እንዲይዝ ሆኗል፡፡ የፖለቲካ ሥርዓቱ ተቀባይነት ላይም ጥያቄ የሚያስነሳ ነው ለማለት ይቻላል፡፡