
የኢትዮጵያና የኤርትራ ጦርነት የተጀመረበት ሃያኛ ዓመት የፊታችን እሁድ ሚያዝያ 28 ቀን 2010 ዓ.ም ነው። የሁለቱ ሃገራት ጦርነት ሲታሰብ ጦርነቱ እንዴት ተጀመረና ተደመደመ ከሚለው ባሻገር ሌሎች በርካታ ነገሮች ይነሳሉ።
የጦርነቱ መንስኤና ጦርነቱ ያስከተለው የሰው ህይወት ጥፋት ፣ ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ወታደራዊ ኪሳራን የሚመለከቱ ጥያቄዎችም አሉ። ይህ ደግሞ ዛሬ አገራቱ ካሉበት እውነታ ጋር በብዙ መልኩ ይገናኛል።
አዲሱ የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ለኤርትራ ያቀረቡት የሰላም ጥሪን ጨምሮ የአገራቱ የዛሬ ሁለንተናዊ ግንኙነት ከጦርነቱ ጋር ይገናኛል።
አስመራን በትዝታ
ማቲዎስ ገብረ ህይወት የአስራ ሁለት ዓመት ልጅ ሳለ ነው የኢትዮጵያና ኤርትራ ግጭትን ተከትሎ ኢትዮጵያዊያን ከኤርትራ እንዲወጡ ሲደረግ ቤተሰቦቹ ወደ ኢትዮጵያ የተሰደዱት።
ወላጆቹ አስመራ ውስጥ ለሰላሳ ዓመታት ኖረዋል። እሱን ጨምሮ ስድስቱ ልጆቻቸውም ተወልደው ያደጉት አስመራ ካምፖቦሎ የሚባል ሰፈር ነበር።
የደረሰው ማህበራዊ ቀውስ ሲነሳ የእናት ከልጇ፣ የባል ከሚስቱ፣ በአጠቃላይ አስከፊ የቤተሰብ መለያየት ይታወሳል። ኑሯችን ህይወታችን ኤርትራ ነው ያሉ ኢትዮጵያዊን ለዘመናት ረግጠው ወደ ማያውቋት ኢትዮጵያ እንዲሄዱ ሲደረግ የእኔ ካሉት ነገር የመነቀል ያህል ስለነበር ህይወትን እንደገና ከዜሮ ለመጀመር ተገድደዋል።
በተመሳሳይ ኑሯችን ቤታችን ኢትዮጵያ ብለው ለነበረ ኤርትራዊያንም መፈናቀል ተመሳሳይ አስከፊ የህይወት ፅዋን እንዲጋቱ ግድ ብሏል።
ቤተሰብ ተበትኗል፣ ያፈሩት ሃብት ንብረት ወደ ኋላ ቀርቷል። ለዘመናት የገነቡት ማህበራዊ ህይወት ፈርሷል። በእነማቲዎስ ቤተሰብም የሆነው ይኸው ነው።
ታላቅ ወንድማቸው ቀድሞ ሲመጣ እንደ እድል ሆኖ እሱና ቀሪ የቤተሰቡ አባል በ30ኛ ዙር ወደ ኢትዮጵያ መጥተዋል። ያረፉት አዲግራት ከሚገኙ አክስታቸው ጋር የነበረ ሲሆን ለወራት እዚያ እንደቆዩ ማቲዎስ ያስታውሳል።

“ሁሉም ነገር ከባድ ነበር። ጦርነቱም ወደ መጠናቀቁ ነበር። ትምህርታችንን ቀድመን ነው ያቋረጥነው። የተወሰነ ንብረታችንን ለመሸጥ ሞከርን። ኑሮ እንደ አዲስ ነው የጀመርነው። ሁሉም ነገር አዲስ ነበር አዲግራት ውስጥ ይነገር የነበረው ትግርኛ በተወሰነ መልኩ የተለየ ስለሆነ ቋንቋ እንኳ ችግር ሆኖብን ነበር” ይላል።
የዛሬውን የኢትዮጵያና የኤርትራ እውነታ እንዲሁም በብዙ መልኩ የተሳሰረው የሁለቱ ሃገራት ህዝብ መለያየትን ሲያስብ እንደሚበሰጭ፤ ስለ ጉዳዩ ማውራት እንኳ እንደሚከብደው ማቲዎስ ይናገራል።
አስመራ አብረውት ካደጉና ዛሬ የተለያየ አገር ከሚገኙ ኤርትራዊ ጓደኞቹ ጋር በማህበራዊ ድረ-ገፅ ሲገናኙም ስሜታቸውን የሚረብሽ አንዳች ነገር እንዳለ ይገልፃል።
“ያሳደገችኝ አያቴ የምትኖረው ኤርትራ ነበር። በቅርቡ የሞተቸውም እዚያው ነው። እኛ እዚህ ነን። መለያየት ምን ያህል አስከፊ እንደሆነ በዚህ ማየት ይቻላል”ይላል በሃዘን።
የአዲስ አበባ ናፍቆት
ኤርትራዊ በመሆናቸው ከነቤተሰቡ ከኢትዮጵያ እንዲወጡ የተደረገውና የማቲዎስ እጣ የደረሰው ወጣት ስሙ እንዲገለፅ አልፈለገም።
በአሁኑ ወቅት የሚገኘው በስደት እንግሊዝ ሃገር ሲሆን እሱም ሆነ መላ ቤተሰቡ በብዙ ፈታና ውስጥ ማለፋቸውን ይናገራል።
ከኢትዮጵያ የወጡት የአስራ ስድስት ዓመት ታዳጊ ሳለ ነበር።
“በተለያየ ጊዜ ነው የወጣነው። ግማሹ ቤተሰብ ታሰረ፤ ግማሹ በመጀመሪያ ዙር ሄደ። መጨረሻ ላይ እኔና ታናሽ እህቴ ቀረን” በማለት ወደ ኤርትራ እንዲሄዱ የተደረገበት መንገድ ከባድ እንደነበር ያስታውሳል።
እሱ እንደሚለው አንዳንድ ፖሊሶች ቀና አመለካከት የነበራቸው ቢሆንም የጥላቻ ስሜት የነበራቸውም ነበሩ። በዚህ ምክንያትም ተደብድቧል።
እሱና ታናሽ እህቱ በእድሜ ትንሽ ስለነበሩ የቤተሰቦቻቸውን ንብረት መሸጥ ወይም ሌሎች ኤርትራዊያን እንዳደረጉት ውክልና ወይም አደራ በመስጠት ነገሩን መልክ ማስያዝ አልቻሉም ነበር።
“ከባድና አስቸጋሪ ጊዜ ነበር። ቀላል አይደለም ጠባሳው በህይወታችን እስከዛሬ አለ” ቢልም ዛሬም ኢትዮጵያን እንዲሁም የልጅነት ጓደኞቹን ይናፍቃል።
“ተወልጄ ያደግኩበት አገር ስለሆነ ለኢትዮጵያዊያንና ለኤርትራዊያን የሚሰማኝ አንድ አይነት ነገር ነው። የልጅነት ጓደኖቼን እናፍቃለው።ሁሌም በማህበራዊ ሚዲያ ተገናኝተን ስናወራ ሰላም ተፈጥሮ የምንገናኝበት ቀን ቢመጣ ብዬ አስባለሁ” በማለት የመለየትን ከባድነት ይገልፃል።

ኤርትራና ኢትዮጵያ በጦርነቱ ዋዜማ
የኤርትራን ነፃነት ተከትሎ በሁለቱ ሕዝቦች መካከል ጥሩ ግንኙነት ይኖራል የሚል ግምት በመንግሥት በኩል እንደነበርና ይህን ታሳቢ ያደረጉ ነገሮችም ይከናወኑ እንደነበር በጦርነቱ ወቅት የኢትዮጵያ አየር ኃይል አዣዥ የነበሩት ሜ/ጀነራል አበበ ተክለሃይማኖት ያስታውሳሉ።
እሳቤው ይህ ስለነበርም ድንበር ላይ የነበረው የኢትዮጵያ ወታደር ቁጥር በጣም ትንሽና ድንበር ላይ ጦር አለ በሚያስብል ደረጃ እንዳልነበርም ያስታውሳሉ።
“ጥሩ የፖለቲካ፣ ኢኮኖሚያዊና ወታደራዊ ትብብር ይኖረናል ብለን አስበን ነበር። ነገር ግን የኤርትራ መንግሥት የድንበር ጉዳይን ምክንያት በማድረግ ኢትዮጵያን ወረረ። የድንበር ጉዳይን ለማስፈፀም ኮሚሽን ተቋቁሞ ነበር” የሚሉት ጀነራል አበበ እውነተኛው ምክንያት ኢኮኖሚያዊ ነበር ይላሉ።
እሳቸው እንደሚሉት የኤርትራ መንግሥት የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ላይ ጥገኛ የመሆን ፍላጎትና አቀራረብ የነበረው ሲሆን የኢትዮጵያ መንግሥት ደግሞ ይህ እንዲሆን አልፈቀደም።
በተለይም ኤርትራ የራሷን ገንዘብ ናቅፋ ማተሟን ተከትሎ ከኢትዮጵያ ጋር የሚደረግ ግብይት በዶላር እንዲሆን መወሰኗ፤ በኤርትራ በኩል ኢትዮጵያ ኤርትራ ላይ እንዳደረሰቸው ትልቅ የኢኮኖሚ ኪሳራ መታየቱም ቁልፍ ነገር ነው ይላሉ ጀነራሉ።
የወጣቱ ወኔና የድል ብስራት
አዲስ አበባን ጨምሮ ከተለያዩ ከተሞችና ክልሎች የአገርን ዳር ድንበር ለማስከበር ወጣቱ በወኔ ሆ ብሎ ነበር የዘመተው።
ለምሳሌ በአዲስ አበባ በየአካባቢው በየሰፈሩ ወጣቶች ወደ ጦርነት ወደ እሳት ሳይሆን ወደ የደስታ ቦታ የሚሄዱ በሚመስል መልኩ መዝመታቸው ከብዙ ሰዎች የሚያስታውሱት ነው።
ግንባር ላይም ወጣቱ በወኔ የተጠመደ ፈንጂ ላይ መስዋዕት እየሆነ ለሌላው መንገድ ይከፍት እንደነበር በተለያዩ የጦር ግንባሮች ለአምስት ወራት የቆየው ጋዜጠኛ መንግሥቱ አበበ ይናገራል።
“ለመዝመት በወሰንኩበት ወቅት 18 ዓመት ቢሆነኝ ነው። በአይደር ት/ቤት ላይ የቦንብ ድብደባ የተጎዱ ህፃናትን የሚመለከት ዝግጅት ይቀርብ ነበር። ያንን ስመለከት በተሰማኝ ስሜት ነው ለመዝመት የወሰንኩት” ይላል በ19ኛ ሜካናይዝድ ክፍለ ጦር ዘምቶ የነበረው ኤፍራታ።
አስራ ሁለተኛ ክፍል ትምህርቱን እንዳጠናቀቀ መከላከያን ተቀላቅሎ ከዚያም በኋላ በጦርነቱ የኢትዮጵያ ሠራዊት አባል ሆኖ የዘመተ ጓደኛው ታሪክ የሁለቱ ሃገራት ጦርነት ምን ያህል አስከፊ እንደሆነ ከሚያስታውሱት ነገሮች አንዱ ነው።
“ጦርነቱ ከመጀመሩ ሦስት ወይም አራት ወራት በፊት ነው መከላከያ ሠራዊትን የተቀላቀለው (ቤተሰቦቹ ኤርትራዊያን ነበሩ)፣ ከጊዜያት በኋላ ጦርነቱ ተጀምሮ እሱ ዛላምበሳ ተመደበ። ከወራት በኋላ ጦርነቱ ተጀምሮ ኤርትራዊያን ወደ ሀገራቸው ሲባረሩ የእኔ ጓደኛ ግዳጅ ላይ ሆኖ ዛላምበሳ ላይ አገኛቸው። መላ ቤተሰቡን በዚያ ሁኔታ አግኝቶ ሲላቀስ ከዚያ በኋላ ባሉት ጊዜያት ደግሞ ከኢትዮጵያ ጦር በኩል በጥርጣሬ ሲታይ የደረሰበትን ጭንቀት እያሰብኩ በጣም አዝን ነበር” በማለት ጓደኛው የነበረበትን ሁኔታ ያስታውሳል።
ዛሬ ላይ ቆሞ ወደ ኋላ ሲመለከት ጦርነቱ ለሱ ትርጉም አልባ ነው።
“በጣም ይቆጨኛል። ለእኔ አላስፈላጊ እና ምንም ውጤት ያልመጣበት ጦርነት ነው” ይላል።
«ባድመን መጀመሪያ ከያዝን በኋላ ልቀቁ ተብሎ ስንለቅ፤ እኔ ለሁለተኛ ጊዜ ተመትቼ ሆስፒታል ውስጥ ነበርኩ። በሆስፒታሉ የነበሩ ቁስለኞች ይሄን ሁሉ መስዋዕትነት ለምን አስፈለገ? በሚል ቅሬታ ያሰሙ ነበር። የኋላ ኋላ አመራሮቻቸውን እየላኩ አረጋጉት እንጂ ወታደሩ የሞቱ ጓዶቹን እያሰበ ያለቅስ ነበር።”

ጋዜጠኞች በጦር ግንባር
አንጋፋው ጋዜጠኛ መንግሥቱ አበበ ጦርነቱን ለመዘገብ የጦር ግንባሮች ላይ ከተገኙ ጋዜጠኞች አንዱ ነበር። የጦርነት ዘጋቢ የመሆን ፍላጎት የነበረው ቢሆንም በወቅቱ ይሰራበት በነበረው ፕሬስ ድርጅት በየሁለት ወር እየተቀያየሩ ወደ ግንባር ለዘገባ መሄድ ግዴታ እንደነበርና እሱም በዚህ መልኩ እንደሄደ ይናገራል።
ለሁለት ወር ተብሎ ቢሄድም አምስት ወር ቆይቷል። ነገር ግን እሱን ጨምሮ ግንባር ላይ የተገኙ ጋዜጠኞች ሁሉ ስለ ጦርነቱ እንዲዘግቡ እንዳልተፈቀደላቸው መንግሥቱ ያስታውሳል።
ይልቁንም ይዘግቡ የነበረው ሕዝቡ ለሠራዊቱ ስለሚያደርገው የስንቅና ሌሎች ድጋፎች ነበር።
“እኛ ጦርነቱን የማንዘግበው ጦርነቱን የሚመለከቱ መረጃዎች የሚወጡት በመንግሥት ቃል አቀባይ ቢሮ በኩል ነበር” ይላል መንግሥቱ።
ምንም እንኳ የጦርነት ዘጋቢ የመሆን ፍላጎት የነበረው ቢሆንም ግምቱ ቦታው ላይ ሆኖ ካገኘው ጋር በመለያየቱ እንዲሁም ጦርነቱ በተጀመረ እለት አብረውት የነበሩ ሦስት ጋዜጠኞች ህልፈት ፍርሃት እንዳሳደረበት ይናገራል።
ከሟች ጋዜጠኞች አንደኛው ከወራት በኋላ ሊያገባ እንደነበር መንግሥቱ በሃዘን ያስታውሳል።
ባድመን ጨምሮ በተለያዩ ጦር ግንባሮች ላይ የነበረው መንግሥቱ ስምንት ጋዜጠኞች በፈንጂ ፍንጣሪ ሲቆስሉ ሦስት ጋዜጠኞች መሞታቸውን ያስታውሳል።
“ስህተቶች”
ከ20 ዓመት በኋላ ጦርነቱን ወደ ኋላ ሄደው ሲመለከቱት እንዲህ ወይም እንደዚያ ባይሆን የሚሉት ነገር እንዳለ የተጠየቁት ሜ/ጀነራል አበበ ሲመልሱ “አንድ ጎረቤትህ ልጅና ሚስትህን ሊነጥቅ ሲመጣ ራስን መከላከል የግድ ነው።
ከዚህ አንፃር የኢትዮጵያ መንግሥት ወራሪን መከላከል ግዴታና ሃላፊነቱም ነበር። በጦርነቱ አካሄድ በተለይም መጨረሻው ትክክል አልነበረም ብዬ አምናለው” የሚል መልስ ሰጥተዋል።
እሳቸው እንደሚሉት ጦርነቱ የኤርትራ መንግሥት ለኢትዮጵያ ህዝብ ሰላም ለኢትዮጵያ ድንበር ስጋት እንደማይሆን በሚያረጋግጥ መልኩ መደምደም ነበረበት። መጀመሪያም የነበረው እቅድ ይኸው ነበር።
ጦርነቱ በታቀደው መልኩ ተደምድሞ ቢሆን ኖሮ ሁለቱ አገራት የዛሬው ሰላምም ጦርነትም የሌለበት አስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ አይወድቁም ነበር ይላሉ።
ከጦርነቱ በኋላ ሁለቱ አገራት አልጀርስ ላይ ያደረጉት ስምምነት ለእሳቸው ሁለተኛው ስህተት ነው። ”ምክንያቱም የአልጀርስ ስምምነት የኢትዮጵያን ፍላጎት አሳልፎ የሰጠ፤ ኢትዮጵያ ጦርነቱን አሸንፋ ነገር ግን የተሸናፊ ሚና ይዛ ያደረገችው ስምምነት ነው” በማለት ይጠቅሳሉ።
የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ እንዲሁም ኃይለማሪያም ደሳለኝ ከኤርትራ ጋር ሰላም ለማውረድ ፍላጎት እንዳላቸው አሳይተው ነበር። አቶ ኃይለማሪያም በሁለቱ አገራት መካከል ሰላም ለማስፈን ሲሉ አስመራ ድረስ ሊሄዱ ዝግጁ መሆናቸውን መናገራቸውም ይታወሳል።
ይህ የኢትዮጵያ መሪዎች የሰላም ጥሪ ተገቢ እንደሆነ ሜ/ጀነራል አበበ ይናገራሉ። የኤርትራ ህዝብ የመረጠውን ነፃነት ማክበር እንዲሁም የኤርትራ መንግሥት ኢትዮጵያን እስካልነካ ድረስ የሰላም ስምምነት ማድረጉም አስፈላጊ ነው ይላሉ።
የሰላም ጥሪው እንዳለ ጎን ለጎን ግን ጥንቃቄ የሚያሻው ነገር አለ ይላሉ። እንደ እሳቸው እምነት የኤርትራ መንግሥት አሁን እያደረገ ያለውንና ፍላጎቱን በጥንቃቄ ሳይመለከቱ ሰላም መፈለግ ብቻውን የሚያዋጣ አይደለም ይላሉ።
Source – BBC/AMHARIC