ጌታቸው ረዳ
(Ethiopian Semay)
ለወንድም የውብሸት። “የወሎ ሙስሊምና ክርስቲያኖች ግንኙነት በዐጼ ዮሐንስ የማክፈር ዘመቻ ጊዜ” (29/04/2018) በሚል ርዕስ ቅድመ አያትህን ማስረጃ አስደግፎ ያቀረብከውን ንጉሡ በእስላሙ ብቻ ያነጣጠረ ለክርስትያኑ የወገኑ አስመስለህ ያቀረብከው፤ ወይንም አማራ እስላም ብቻ (አማራ በመሆኑ ብቻ) ማጥቃታቸውን አስገራሚ ውንጀላህ በበርካታ ድረገጾች የተለጠፈውን እንዲሁም የኔ ጽሑፍ በሚስተናገድበት Ethiopanorama ድረገጽ ላይ የተለጠፈውን ተመለክቼዋለሁ።
ትችትህ ተደርጓል አልተደረገም በሚል ሳይሆን የምከራከርህ- ትችትህ ወገናዊነት የተንተራሰ ነው። “ማከፈር” የሚለው “ዘረኞቹ” ዓረቦች የሚጠቀሙበት “ሃይማኖተ ቢስ፤ በፈጣሪ የማያምን/አረመኔ፤እርኩስ….እንዳንዴም ካፊር (ሰላይ) ወዘተ… በሚል ይተረጎማል”። አረመኔ ማለት ደግሞ ሰውን እስከ ማረድ የሚደርስ ማለት ነው። ማከፈር የሚለው ትርጉም እስላሞቹ ሊነግሩን ይችላሉ፤ በርዕስህ ላይ መሸንቀርህ ግን አልተስማማኝም። ይህ “ማከፈር” “ኩፋር” ወዘተ የሚሉ ቃላቶች (‘ታጊ-ንግ’ ይሉታል የሰብኣዊ መብት ተሟጋቾች) ኦሮሞ ወንድሞቻችን እና ወያኔዎች አማራን ‘ነፍጠኛ’ እንደሚሉት ‘ታጊግንግ’ መለያ። አማርኛ አጥተሃል እንዳልል “ያውም ወሎየ ነኝ” እያልከን- ለምን ዓረባዊው የዘለፋ ስም እንደተጠቀምክበት ላንተ ብተወውም ከርዕስህ ጋር ሳገናዝበው ለጤና እንዳልሆነ የሚያሳየው ይህ ዓረባዊ የስድብ ቃል መሸንቆርህ አመጣጥህ አልገባኝም። አሁን ወደ ነጥብህ እንግባ።
“ ከሰሞኑ የማኅበራዊ ሚዲያ አጀንዳዎች መካከል በአክሱም የሚኖሩ ሙስሊሞችና
በዐጼ ዮሐንስ ዘመን በወሎ ሙስሊም አማሮች ላይ የተፈጸመው ግፍ ይገኙበታል፡፡”
ይህ ዜና አንብቤዋለሁ። ዜናውን ያስነበበን ‘አክሱም’ ከተማ ድረስ ሄዶ የእስላሞችን ሁኔታ ተመለክቶ የታዘበው በቅርቡ ከእስር የወጣው “አህመዲን ጀበል” ነው። አህመዲን ስለ እስላሞች ትግል መታገሉ ባይከፋም እንደ ምሁርነቱ (ያውም ማስተርስ ዲግሪ ያለው ወጣት) ስላለፈው እስላም እና ክርስትያን ጦርነት አንስቶ የነፃነት ታጋይ በሚል ባሽሞነሞነው የሽብር ጌታ “ግራኝ አህመድን” (ያውም ሶማሌ መቃዲሾ ምድር ሃውልት እና አገር ውስጥ አዲስ አበባም ቤተ ፀሎትን በስሙ የተሰየመለት “የእስላሞቹ ቅዱስ” ሼኽ/ኢማም/ አሕመድ (ካልተሳሳትኩ) እንዲሁም ወጣቱ ምሁር አህመዲን ጀበል የጥንቶቹ ነገሥታት የኢትዮጵያ ሰንደቃላማ ከክረስትና አያይዘው የተረጎሙትን መነሻ በማድረግ እስላሞች እንደማይቀበሉት በመጽሐፉ (ኢትዮጵያውያን ሙስሊሞች- ከ615-1700 የጭቆና እና የትግል ታሪክ 4ኛ እትም) የጻፈ ደራሲ አህመዲን ጀበል ነው ዜናውን የዘገበው። እስላሙ ከዘመናዊ ትምህርት እስላም ስለሆነ ብቻ ታግዷል ብሎ የሚል ወጣት ምሁር ነው። መጽሐፉ ብዙ ጥናቶችን ያከታተ ሆነ እና ግሩም ተመራማሪ ሆኖ እያለ፤ የማይለጠፈውን ልጠፋ አልፎ አልፎ መለጠፉ አልተቀበልኩትም። ብቻ ያ ሌላ ርዕስ ስለሆነ እተወዋለሁ።
ወዳንተው ልመለስ እና “መቼም ዐጼ ዮሐንስ በወሎ ሙስሊም አማራዎች ላይ እንደፈጸሙት በደል ማንም ላይ አልፈጸሙም።” ብለሃል።
የወያኔ ቀብር ፈጣሪ ቶሎ ያበስረን እንጂ ወያኔ በወሰደው ዘረኛ መመሪያ እና የምኒልክን ስም ለማጉደፍ ሲሞክር እናንተም ዮሐንስን በተገቢው መልስ ከመስጠት ይልቅ ጭራሽኑ እንደ ሌሎቹ ነገሥታት ሁሉ መጥፎም ደግም ጎን እንደነበራቸው እያወቃችሁ፤ ያንን ጎናቸው ወደ ቆሻሻ መጣያ በመጣል፤ የንጉሡን መጥፎ ጎን ብቻ እያነሳችሁ “ታሪካቸው ውሻ እንደማይበላው” አድርጋችሁ እየዘገባችሁ ነው። ለዚህ ነው ወያኔን ተው የኛ ንጉሥ የነዚያ ንጉሥ እያላችሁ ነገሥታትን እና ሕዝብን አታባሉ ያልንበትም ምክንያት የተዛባ ውንጀላ እያመጡ በንጉሡ ላይ የውንጀላ እና የስም ማጥፋት ዶፍ ማጉረፍ ከተጀመረ ቆይቷል። አሁን ወደ ዘርም ወደ ሃይማኖትም እያደገ መጥቷል።
ይህ ውንጀላ በሳቸው ብቻ አልተወሰነም፤ አማርኛ ቋንቋም የደብተራዎች ቋንቋ (የክርስትያኖች ፊደል) ስለሆነ ኦሮሞዎችም ሆኑ እስላሞች አንፈልገውም ተብሎ አማርኛን እና የግዕዝ ፊደል ለማጥፋት ያልተደረገ ሙከራ አልነበረም። ያው ላቲንም ዓረብኛም የመረጡ ወገኖቻችን አሉ።
የሆኖ ሆኖ የወሎ “አማራ እስላሞች” ተለይተው በንጉሡ መከራ ደርሶባቸዋል ነው እያልክ ያለሁ። ንጉሡ በኔ አረፍተነገር “ በ ወሎ እስላሞች
(ኦሮሞም ይሁን አማራ እስላሞችን ) ባንተ “አማራ እስላሞች ብቻ” እንደበደሉ እና በወቅቱ ንጉሡ እስለሞቹን ወደ ክርስትና እንዲመለሱ/እንዲጠመቁ ሲያደርጉ ቅድመ አያትህ እስላሞቹን በዘዴ እንዴት እንደረድዋቸው ነግረኸናል። ይኼ የኢትዮጵያውያን ባሕል አብሮነት ያዳበርንበት ግሩም ባሕል ስለሆነ አልደነቀኝም (ዛሬ መረሳቱ ነው ያሳዘነኝ)። እኔም በዓይኔ ያየሁት ልንገርህ።
የወሎ እስላም (አማራም ኦሮሞም….) ወያኔን እና የኤርትራ ተዋጊዎችን ለመዋጋት ወደ ትግራይ ራዛ ዘመቻ ዘምቶ ፤ “ስልጠና ያልተሰጠው የገበሬ ዘማች” ስለነበር በወንበዴዎቹ ተማርኮ መሳሪያዎቻቸውን ነጥቀው ወያኔዎች ወሎዮዎቹን በሰላም ወደ አገራቸው እንዲመለሱ ሲያደርጉ፤ ያ ሁሉ በረሃ በትግራይ ሸለቆ ሲጓዙ የትግራይ ሕዝብ በየገጠሩ ሲያርፉ ውሃ፤ቡና፤ጠላ እንጀራ ወተት….እየጋበዙ ነበር። የሚሰግዱበትም ውሃ እያቀበሉ ምንጣፍ እየሰጡ።፡ ወደ ከተማ ሲገቡም ሲጋራ እና ተገቢውን ምግብ ያስተናገዳቸው ሕዝቡ ነበር።ስለዚህ እስላም ክርስትያን ሳይባባል የነበረ ባሕላችን ስለነበረ ቅድመ አያትህ ምስጋና ይግባቸው እና የትግራይ ሕዝብም ያንኑ ደግሞታል። እያሱም እስላም እንደሆኑ ይነገርላቸዋል። የትግራይ ሕዝብ ግን ከንጉሡ ሰይፍ ደበቆአቸው ነበር። እስላም በሚል ቢሆን ኖሮ የዮሐንስ የልጅል ልጅ እያሱን መጠለያ ባልሰጥዋቸው ነበር።
እኔ የገረመኝ “አማራ እስላሞች” ተለይተው በንጉሡ ሲጠቁ አማራ ስለሆኑ ነው ወይስ እስልምናን ስለተከተሉ? ንጉሡ አማራ ላይ ጥላቻ ነበራቸው የሚሉ ሰዎች የዛሬ በሽተኞች
እንጂ ጤነኛ ሰው ዮሐንስ አማራን ይጠሉ ነበር ብሎ ማለት በእውነት “ዕብደት ነው”፡ ያውም ንጉሡ በአማርኛ እየጻፉ እና እየተነጋገሩበት። ንጉሡ ተራ ዜጎች ብቻ ሳይሆን ኦሮሞ ናቸው የሚባሉት ‘ንጉሥ ሚካኤልም’ (ይማም መሐመድ ዓሊ) ወደ ክርስትና አስመልሰው ልጃቸውን ድረውላቸዋል። ሌሎቹም እንዲሁ ያደርጉ ነበር። ንጉሥ ሚካልን የመረጡበት ምክንያት ‘አማራ’ ስላልነበሩ ነው? እጅግ የደነቀኝ ደግሞ እንዲህ የምትለውን ጽሑፍን ነው፡
“የወሎ ሙስሊም አማራ ላይ የፈጸሙትን ግፍ ሙስሊም ትግራዋዮች ወይም አፋሮች ላይ አልፈጸሙም፡፡ ከዚህ አንጻር የተፈጸመውን ግፍ ረጋ ብሎ ላጤነ ሰው ስለምን ሙስሊም አማሮችን ብቻ ለማክፈር ፈለጉ ማለት አይቀርም።” ብለሃል።
እንግዲህ ለምን አማራዎች ብቻ የምትሉት እንተ እና መሰል ሰዎች ናችሁ እንጂ ጤነኛ ሰው ንጉሥ ዮሐንስ አማራን ይጠሉ ነበር፤ ክርስትያን ይወዱ ነበር ብሎ የሚል ሰው ትክክል አይደለም።
ንጉሡ ከአፋሮች ጋር ያደረጉት ተደጋጋሚ ውግያ አድርገዋል። ዮሐንስ ከአፋሮች ጋር ሲዋጉ እስላሞች ይሁኑ እንጂ ‘የትግራይ ሕዝብ አካል’ ስለሆኑ ብለው አልተውዋቸውመ።
እንዳውም ባይገርምህ ንጉሡ ብዙ የትግሬ እስላሞች አሁን ኤርትራ ምድር ከመንደፈራ እስከ ምዕራባዊ እና ማአከላዊ ኤርትራ (አስመራ) ያሉት “ጀበርቲ” የሚሏቸው ትግርኛ ተናጋሪ እስላም ወንድሞቻችን አንተ እንደምትለው (አማራ እስላም ዘንድ ተፈጸመ እንደምትለው ዓይነት) ተመሳሳይ ድርጊት ስለተፈጸሙባቸው ወደ ኤርትራ ተሰድደው ጣሊያን ጋር በሰላም መኖር መርጠው እንደተሰደዱ አንዳንዶቹ ይናገራሉ። ስለዚህ ያንተ ውንጀላ መሰረተ ቢስ ነው። ኦሮሞ እስላም እየተው ‘አማራ’ እስላም ብቻ ለይተው ወሎ ውስጥ አላጠቁም። ስንወነጅልመጠን ይኑረን! አማራ አማራ የሚለው ጉዳይ የትም እየተሰነቀረ ትርጉምን እና ትግሉን እንዳናጣምመው መጠንቀቅ አለብን።
ንጉሡ አንተ እንደምትወነጅላቸው አማራውን ለይተው ክርስትያን አላደረጉትም። አጼ ቴዎድሮስ ቄሱን እንዲሁም የፀጋ ተከታዮችንም አጥፍተዋል። እነኚህ ሁሉ አልፈጁትም አልተገፉም እንዴ? የክርስትያን ነገሥታትም እኮ በእስላሙ ብቻ ሳይሆን በክርስትያኑም ጥቃት ፈጽመዋል። ያውም የሐንስ ቦሩ ሜዳ በምትለው ላይ አፄ ዮሐንስ በተገኙበት የዳኝነት ክርክር ፀጋ እና ካራ በተባሉ (ሁለቱም ክርስትያን ክፍል) አማኞች ክርክር ገጥመው፤ በፀጋዎች ላይ የአካል ጉዳት ፈጽመውባቸዋል።
በዚህ የተነሳ ከዚያ ከ1870 ጀምሮ ቅባቶችም እስላሞችም ወደ ክርስትና አንዲመለሱ ማዘዛቸው ተዘግቧል። በዚህ የተነሳ እስላሞች ብቻ ሳይሆኑ ከተዋህዶ ውጭ ያለ ሁሉ ወደ ተዋህዶ እንዲመለስ ተደርጓል። ትግራይም እንደዚያ ተደርጓል (ትግራይ ውስጥ በቅባቶች ላይ
ምን እንደተደረገ ሌላ ጊዜ እግልጸዋለሁ)። በወሎ እስላሞች ብቻ ሳይሆን ክርስትያንም ይሁን እስላም ማንኛውም ዜጋ “ትምባሆ” ሲቅምም ሆነ ሲያጨስ የተገኘ ሁሉ ”አፍንጫው እና ምላሱ” ይቆረጥ ነበር። አይደለም እንዴ? ይህ እየታወቀ ‘በአማራ አስላም ብቻ’ ተደረገ እየተባለ የሐንስ አማራን ይጠላሉ ለማት የማትፈነቅሉት ድንጋይ የለም። አደብ አድርጉ! ትዕግስት! መጠን!
ፀሓፊዎች በጻፉት አነበብን እንጂ እሳቸው ደግሞ የጻፉት የተቃራኒው ነው። ለንግሥት ቪክቶርያ የጻፉትን ደብዳቤ እንደሚገልጸው፡ “
“ሸዋ ዘምቼ ሳለሁ እኛ በኛ ክርስትያኖቹ በሃይማኖት ተከራክረን እረተን በእስክንድርያ ሃይማኖት አገባናቸው (ጸጋዎቹን) እስላም ሁሉ ይህንን አይቶ ሰምቶ ‘ለካ ለኛስ አባት የለንምን’ ብሎ ያጥምቁነ ክርስትና ያስሰነሡነ’ ብሎ ለመነኝ፤ እሺ ብየ ከፈቀድክስ ከወደድክስ ክርስትና ግባ ብዬው የኢትዮጵያ እስላም ሁሉ ወደ በፈቃዱ ክርስትና ግባ። አንድ ነገር በሃይል ያደረግሁት የለኝም፤ ወዶ በፈቃዱ ነው እንጂ የገባ። በወንጌልም ጌታ ሲጽፍ በሃይል አድርጉ አላለም አላዘዘም። በሃይል የተደረገ የለም።”
ብለው የጻፉት ደብዳቤ ይገልጻል። አደረጉ አላደረጉም ሳይሆን ክርክሩ እሳቸውም ያንተን ውንጀላ “አማራ እስላም” ብቻ እየለዩ የሚለውን ለማሳየት ነው የተጠቀምኩበት፡ እሳቸው “እስላም ሁሉ” ነው ያሉት እንጂ “አማራ እስላም” የሚል እንዳልተጠቀሙ እና ንጉሥ የሐንስ አማራ ጥላቻ ነበራው የሚለው “የቀወሱ ሰዎች ውንጀላ” ለማሳየት ነው። ስለዚህ ንጉሡ ‘አማራ እስላም’ እየለዩ በአማራነቱ እየለዩ ጥቃት አላደረሱም። ጎጃምም ያደረሱት ጥፋት ‘አማራ’ ስለሆነ አማራ ስለሚጠሉ እያሉ የጻፉ ሰዎች አሉ። ሁሉም መጠን ይኑረው! አመሰግናለሁ !
ጌታቸው ረዳ
(Ethiopian Semay