የዘር ማጥፋት ወንጀል አሁንም በጠራራ ጸሃይ

በቤንሻንጉል ክልል በሚኖሩ አርሶ አደሮች ላይ ዘራቸው ተመርጦ ህጻን፣ ሽማግሌ፣ ሴት ወንድ ሳይባል እንደጠላት እየታደኑ እንዲገደሉ እና ቤት ንብረታቸው እንዲቃጠል ተደርጓል፡፡ የሞቱት ሞተው የተረፉት ደግሞ ነፍሳቸውን ለማትረፍ እንዲሁም ህግን በመሻት ካለ ማንም ተከላካይነት አሁን ለስድስተኛ ግዜ ተፈናቅለዋል፡፡ ይህ ግፍ እና በደል ተደጋግሞ የደረሰባቸው ሲሆን ከጥቂት ወራት በፊት ጀምሮ ግን እየተባባሰ እና ወደ ጅምላ ግድያ ተለውጦ የብዙ ወገኖችን ህይወት እና ንብረት አጥፍቷል፡፡ አጋዥ እና አለሁ ባይ በመንግስትም በኩል ይሁን ክልሉን በሚያስተዳድረው አካል በማጣታቸው እንደምንም ብለው ወደ ፍኖተ-ሰላም ሄደው በመጠነኛ እርዳታ ለተወሰነ ግዜ ቆይተዋል፡፡ ነገር ግን ሲደረግላቸው የነበረው ትንሹም እርዳታ ተቋርጦ ወደ አማራ ክልል ዋና መስሪያ ቤት ሂዱ እና ጠይቁ ተብለው ባህር-ዳር ለጥቂት ቀናት ከቆዩ በኋላ የአማራ ክልል መንግስት አይናችሁን ላፈር ከማለቱም በላይ ከተጠለሉበት ቤተክርስቲያን በኮማንድ ፖስት እየተደበደቡ እና እንደ ከብት እየተጫኑ በየቦታው በመበተን መኖራቸውን ለመካድ እና ድራሻቸውን ለማጥፋት ጥረት መደረጉ እጅጉን ያሳዝናል፡፡

የኤርትራን እና የሱዳንን ስደተኞች በእንክብካቤ እይዛለሁ እያለ የውጭ ምንዛሬ የሚሰበስበው የወያኔ መንግስት የራሱ የሆኑ እነዚህን ዜጎች ባገራቸው ላይ ስደተኛ አድርጓቸዋል፡፡ ህጻናት በረሃብ እና በእርዛት እንዲቆሉ ሆን ተብሎ የተቀነባበረ ኢ-ሰብዓዊ ወንጀል እየተፈጸመባቸው እንደሆነ እያየን ነው፡፡ ገዳዮቹ እና ንብረት ያወደሙ ግለሰቦች በሕግ ሳይጠየቁ እስከ አሁን ድረስ አሉ፡፡ እነዚህን በጭንቅ ላይ የሚገኙ ወገኖቻችንን ባህር ዳር ላይ የለው የአማራ ተወካይ ነኝ የሚለው ብአዴን እንኳንስ ሊረዳቸው ይቅር እና እሮሯቸውን እንኳ በቅጡ ለማዳመጥ አልፈለገም፤ ጭራሹኑም እንዲዋከቡ እና እንዲታሰሩ አደረጋቸው እንጅ፡፡ ቤተክርስቲያኖች እንኳ እንዳያስጠጓቸው ተነግሯቸው ማደሪያ እና መሄጃ አጥተው አስፋልት ለአስፋልት ሲባክኑ አይተናል፡፡

ለነዚህ ወገኖቻችን ባስቸኳይ ፍትህ እንዲሰጥ እና የሚያስፈልገው እርዳታ ሁሉ እንዲደረግላቸው እንፈልጋለን፡፡ ለጠፋው ህይወት፣ ለወደመው ንብረት ወንጀለኞች ለህግ ይቅረቡ፡፡ ለነዚህ ምስኪን ወገኖቻችን የምትቆጩ ሁሉ ዝም ብላችሁ አትዩ፤ በደላቸው እንዲሰማ፣ መብታቸው እንዲከበር መረባረብ የያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ ግዴታ ነው፡፡

የጎጃም ዓለምአቀፍ ትብብር የወገኖቹን እሮሮ ገና ከመጀመሪያው ቀን ጀምሮ በመካፈል ካሉበት ቦታ ማለትም በካማሽ፣ በለው ደዴሳ ላይ ገና ሳይበታተኑ የ $3000 እርዳታ አድርጓል፡፡ ይሄንንም ተከፋፍለው በግዜው ይፈልጉት የነበረውን አንገብጋቢ የምግብ እና የአልባሳት ወጭ ሸፍነውበታል፡፡ ከዛም በኋላ ነገሮችን በመከታተል ያላሰለሰ ጥረት ስናደርግ ቆይተን ከሆነ ግዜ በኋላ ከኛ ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት የነበራቸው ሰዎች ተሰወሩብን፡፡ እኛም ምንአልባት ለደህንነታቸው ሰግተው ይሆናል ብለን ግንኙነቱን አቁመን እስካሁን ቆይተን ነበር፡፡ አሁን ግን ችግሩ ከመድበስበስ አፈትልኮ ወጥቶ እዛው የእናንተ ተወካይ ነኝ ወደሚለው የብአዴኑ ጽህፈት ቤት አፍንጫ ላይ ደርሷል፡፡ አሁንም ብአዴን የመፍትሄ አካል ከመሆን ይልቅ ነገሩን ለማድበስበስ እየሄደ ያለበት መንገድ በእጅጉ ያማል፡፡ ይበል በሎ የተዋቀሩ የኮሜቴ አባሎችንም ለእስር እንደዳረጋቸው ሰምተናል፡፡

እነዚህ ወገኖች አሁንም ቢሆን የወገንን ጥሪ ከምንግዜውም በላይ ይሻሉ፡፡ አለንላችሁ ልንላቸው እና ይህ መሰረታዊ የሆነ ችግርም ዘለቄታዊ መፍትሄ ያገኝ ዘንድ ሁላችንም በአንድነት መረባረብ ይኖርብናል፡፡ አሁንም ደግመን ደጋግመን እንደምንለው ችግር ሲፈጠር ብቻ ራስን ለማንቃት ከመሞከር በሰከነ መንገድ ወደ ውይይት እና የመፍትሄ ሃሳብ ህዝባችን የሚመጣበትን መንገድ መፈለግ ይኖርበታል፡፡ የጎጃም ብሎም የአማራው ችግር ተዘርዝሮ የሚያልቅ እንዳልሆነ ሁላችንም እናውቃለን፤ ምን አይነት ሴራ እንደተሰራብን አሁንም እየተሰራብን እንደሆነ የማናውቅ እና ያልነቃን ካለን በጅጉ ዘግይተናል እና ካሁኑ የድርጅታችን አባል ሆነው በምናደርገው የተቀደሰ ወገንን የመርዳት ተልዕኮ ተሳታፊ ይሁኑ፡፡
በባህር ዳር አብያተ ቤተክርስቲያኖች ተጠልለው ለሚኖሩ ወገኖች ለምግብ እና ለአንዳንድ ነገር ይሆናቸው ዘንድ የጎጃም ዓለምአቀፍ ትብብር መጀመሪያ ካደረገው እርዳታ ሌላ አሁንም የሚገባውን ልኳል፡፡ በተጨማሪም የ ጎ ፈንድ ሚ ከፍቶ ገንዘብ ለነዚሁ ወገኖች እየሰበሰበ ይገኛል እና የቻሉትን፣ ያቅመዎትን ይርዱ፡፡

በአማራ ላይ ለዘመናት እየደረሰ ያለው ይህ የዘር ማጥፋት ወንጀልን የጎጃም ዓለምአቀፍ ትብብር በጽኑ ይቃወማል፡፡