ይግዛው አጥናፉ ቸኮል

ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት ማግስት ጀምሮ፣ በምራቡና ምስራቁ የዓለማችን ንፍቀ–ክበብ መካከል የነበረው ቀዝቃዛ ጦርነት፣ በካፒታሊስት የፖለቲካ ኢኮኖሚ ድል አድራጊነት መጠናቀቅን ተከትሎ፣ በተለያዩ የዓለም ሀገራት ልዩ ልዩ የአስተዳድር መንፈስ ማቆጥቆጥ ጀመረ። ጀርመን ተቀዳሚ የለውጡ ተቋዳሽ መሆኗን ለማብሰር፣ ግፈኛውን የበርሊን ግንብ ላይመለስ መንግላ፣ ዜጎቿን በደስታ እንባ አራጨች። ዓለም በምዕራቡ ስናር በቅሎ መሞሸር፣ በጥሩንባውም ማሸብረቅ አለያም መደንቆር ግድ ሆነባት። በአልባኒያን ኮሚንዝም/Albanian communism/ አምልኮት ተጠርንፈው፣ ያዙኝ ለቁኝ ሲሉ የነበሩትም፣ የፖለቲካን ከይሲነት ተገንዝበው ራሳቸውን ከአዲሱ አስተምህሮት ጋር ማላመድ ያዙ። ሳዳም “የኩየትን ደም ማፍሰስ ጽድቅ ነው” ብሎ ሲዝት፣ ሞስኮ ላይ ያለው ጎርባቾቭ ክፉኛ ተዘርሮ ታላቁን የህብረት ክንድ አጣ። ፈርጣማው የሶሻሊዝም አብዮት፣ ነጭ ውሸት ሆኖ ብቅ አለ። ያ ወቅት ብዙ ምስቅልቅል፣ እድልም ይዞ እንደ ሰደድ እሳት ተቀጣጠለ። የተጽኖውም ሰደድ አይሎ ኖሮ፣ ውቅያኖሶች ሳይገድቡት፣ የባህር ሰላጤውን ሰነጥቆ ምስራቅ አፍሪካን ነካካ። ተመሳሳይ የፖለቲካ ፍልስፍና ሰልፉም እንዲጀመር ወቅቱ አስገደደ።

ባለመለዮው ሰራተኞች ፓርቲም፣ “እናት ሀገር ወይን ሞት” ብሎ የዘመረለት ባለኮከቡ የሶብየት አብዮት፣ በርካቶችን በቀይ ሽብር መትረጌስ ሲያጸዳ ባጅቶ እጅጉን ተዳከመ። ቅይጥ ኢኮኖሚውም ጉልበት ሳይሆን ቀርቶ፣ ገፍቶ የመጣውን የምዓራብ ዓለም ጫና መሸከም ተሳነው። ይባስ ብሎም፣ መርዕድ ንጉሴንና ፋንታ በላይን፣ አበራ አበበንና ደምሴ ቡልቶን፣ ታሪኩ ላይኔን እና መሰል የሀገሪቱ ጦር የበላይና ቀደምት ስልጡን መኮንኖችን አጠናቀቀ። በርግጥም አብዮት ልጇን በላች። ትልቁ ሞተርም ተበላሸ–የሰፊው ህዝብ እምቢተኝነት ቀስፎ ያዘው። እናም ሊቀመንበሩ የሚወራጩበት፣ የደርግ መዋቅር ብቻውን መቆም፣ ብቻውንም ከማውራት ጥግ ላይ ደረሰ። ትልቅ አጣብቂኝ ያንገዳግደው ገባ። የወቅቱ የዓለም ፖለቲካ ሙቀት ብርታት፣ ደርግ ውስጥ ከሚመነጭ የአመራር ዝንፈት ጋር ተዳምሮ፣ የዛሬዎቹ አለቆቻችሁ በተለይም በሲ አይ ኤ እየተመሩ፣ ታላቁን የህዝብ ወንበር በቀላሉ እንዲቆናጠጡ፣ እነሆ የገነትን በር ከፈተላቸው። ወርሃ ግንቦት፣ 1983 ዓ/ም።

ደርግ ለኩሶ፣ ምጎ ሳይጨርስ ያስቀመጠውን ሲጃራም፣ እኒሁ ግራዘመምነት ያባዘናቸው ጌቶቻችሁ፣ መማግ ጀመሩ። የወያኔው ሀርነት በአምሳሉ ጨፍልቆ የፈጠረው አብዮታዊ ግንባርም፣ ጦርነት ያቆረቆዘው ህዝብና የወረደ ኢኮኖሚው ስጋት ሆኖት፣ መወቅራዊ ለውጦች ላይ አብዝቶ ከማተኮር ይልቅ፣ ያለችዋን እየቆረጠመ አውራ ህዝቦችን መቆርጠምን አስቀደመ። ለወትሮው “አማራ በላኝ” ብሎ የሚለፈልፍ የማሌሊት መዥገር፣ ይህ ወቅት ሰርግና ምላሽ ሆነለት። የሆነው ሆኖ፣ ዛሬ አኖሌ ሀውልት የቆመበትን ጨምሮ፣ በአብዛኛው አርሲ አስተዳድር የሚገኙ አማሮች፣ በአሰቃቂ የአወጋግድ ስልት ተወገዱ። አካባቢውም ወደ ጅምላ የአማራ መቃብር/Mass Grave/ተለወጠ። ይህንም፣ አብዮታዊ ግንባሩ በአንድ በኩል ሲረሽን፣ በሌላ በኩል የራሱ ካሜራ ቀርጾት ኖሮ፣ ‘የኦነግ ሴራ’ በሚለው የተቆራረጠ ዶኪዩሜንትሪው በራሱ ቴሌቪዥን ካሳየ ውሎ አድሯል። የተባበረው ህወሐትና ኦነግ ጦር፣ ድንቅ ብቃቱን አሳየበት። እርስ በእርሳቸውም፣ እናኳን ደስ ያላችሁ፣ ተባባሉ። ሸጋ ነው¡¡

ዛሬ እናንተን ያሰባሰበው ብአዴን ወላጅ አባት፣ የያኔው ኢህዴንም በእነ አቶ በረከት፣ አቶ አዲሱ፣ ፖስተር ታምራትና በመሳሰሉት በኩል፣ የዘር ማጥፋት መሪ ትዛዝ እንዲሰጥ፣ የጋራ ፊርማ ስነስርዓት አጣጥመዋል። ኢህዴን በኦፊሴላዊ ደረጃ “ተስፋፊ ነፍጠኛ” ብሎ የሰየመው ያህ ዝብም፣ ከአርሲ ማዶ ይሙት በቃ ይታደን ጀመር። ኦሮሚያን አልፎ፣ በተለያዩ የሀገሪቱ ክልሎች፣ ከደቡብ እስከ ጋምቤላ፣ ከሀረሪ እስከ ጉሙዝ፣ በሶማሊም ጭምር፣ አማራ በስፋት ሚገኝባቸው ከተማና ገጠራማ አስተዳድር በመብራት እየተፈለጉ፣ የአማራ ጭፍጨፋ/Amhara Holocaust / ቀጠለ። በርግጥም “የትግራይ ተራሮች የአማራ መቀበሪያ” ይሆናሉ የሚለው፣ የወያኔ ቀደምት የትግረኛ መፈክር ወይንም “ጎቦታት ትግራዋዩ መቃብሪ ናይ አምሀራ ክኾንዮም”፣ በመላ ሀገሪቱ እየሰራ መጣ። “ሲከፋኝ፣ አክሱም ጽዮን ሄጅ እጠለላለሁ” ብሎ ይገዘት የነበረው፣ ግዙፋ የአማራ ህዝብ ባይታወርነት ተሰማው። እርሱን በማይወክል የታሪክ ስሌት፣ እሳት በቁሙ ተለቀቀበት። መሰል ድርብርብ ግፍም፣ ለዘመናት እያስተናገደ፣ ዛሬ ላይ ደርሷል።

እናንት ሹመኞች
የፖለቲካ ታሪካችሁ ሁሌ እንደምትሉት ቅዱስ አደለም። ይልቅስ አብዮታዊ ዲሞክራሲ መጽሄትና የግንባሩ ልሳን አዲስ ራዕይ ከሚሸነግሉት ጀርባ እንጅ። ከዘመን መጽሄትና አዲስ ዘመን ለፈፋም፣ በእጅጉ ተለይቶ ኖሮ፣ ጉዳያችሁ ወዲህ ነው። ብቻ ፋይሉ ተሰናድቶ ያችን ቀን ይናፍቃል። ያከመሆኑ በፊት ግን ጩኸቴን እንዲህ በይፋ ቀጠልኩ። የክልሉ ህዝብ ውስን አንጡራ ሀብት፣ አፈሩ ሳይቀር ወደ ክልል አንድ ተጋዘ። የጤና ጣቢያና መዘጋጃ ቤት ጀኒሬተሮች ሳይቀሩ፣ ከትውልድ ቦታየ ከታላቁ ዳሞት አውራጃ ጭምር፣ አይኖቼ እያዩ ተለቀሙ። ተለቅመውም የወያኔ ፋኑስ ሆነው፣ በተለያዩ ትግራይ ከተሞች ተተከሉ። ያወቅት ደግሞ፣ በሀገሪቱ ላይ ከፍተኛ የመብራት ሀይል እጥረት የነበረበት ሆኖ፣ የክልላችነን ህዝብ ከልብ ጎዳው። ወራሪ ሙሶሎኒን ያርበደበዱ፣ የቀደምት አያቶቻችን ባህላዊ ጠመንጃዎች ቤትለቤት ተዘርፈው ሽሬ እንዳ ስላሴ ተከዘኑ።

ይህም አልበቃ ብሎ፥ የእናንተ አቻ የትግራይ አመራር ለእያንዳንዱ ከተሜና ገበሬ፣ ብዛት ያለው ዘመናዊ የጦር መሳሪያ ከበቂ ጥይት ጋር “ምን ጎደለ” እያለ ሲያድል ይውላል። በርግጥም “አማራ ሊወጋህ ነውና ተዘጋጅ” የሚል፣ የዘመቻ ዝግጅትና ማንቂያ ማኗል አዘጋጅቶ፣ የትግራይን ህዝብ ሲያነቃንቅ ይታያል። በዚህ በኩል ደግሞ፣ የወያኔውን አገዛዝ ያሰጋሉ የተባሉ፣ የክልላችን ስመጥር ጀግና ልጆች፣ ውስጥ ውስጡን በደርግ ናፋቂና በፊውዳል አምላኪ ሰበብ፣ ከላይ–ከላይ ግን ሽፍታን ማውደም በሚል ዘመቻ ጸዱ። በአደባባይ ተረሸኑ። የተረፋትም ዓለም-በቃኝ እስርቤት ታጎሩ። በመሬት ስምሪት ሰበብ፣ መሬቱ እየተቆራረሰ የእርስ በእርስ ግጭት ምንጭ መሆኑ፣ አገዛዙን እያስደሰተው መጣ። በርግጥም ፍትሃዊ የተፈጥሮ ሃብት ክፍፍል ባልከፋ ነበር። በግሌም የምደግፈው አቋሜ ነው። አሻጥሩ ግን ሌላ ነው። ወያኔን የማይደግፍ አርሶዓደር መሬት እየተቆራረሰ፥ ለደጋፊ ጎረቤቱ መምራት ግድ ሆነ። ምነው በዚህ ባበቃ ነበር! ግፉ እንዲህ ቀጥሏል!

ከማንም በተለየ፣ የክልላችን አርሶ አደርና ነጋዴ፣ ምሁርና ተማሪ፣ ቤተክርስቲያናችንና መነኮሳቱ እስከነ ገዳሞቻቸው ጭምር፣ ልዩ የጥፋት ራዳር ውስጥ ገቡ። የክልሉ ግብር አስተዳድር፣ ከነጋዴው ካፒታል አቅም ጋር የማይጣጣም የንግድ ግብር ስርዓት ዘርግቶ፣ ወገኖቻችነን አንዲያጎሳቁል አይነተኛ ምክንያት ሆኗል። የሚሰበሰበው ፍርደ ገምድል ግብርም እስካሁን ለሩብ ምዕት ዓመት፣ ለአካባቢው ልማት ሲውል አይታይም። እንዲያም ሲል፣ ለከተሜውም ሆነ ለገጠሬው ወጣት፣ የስራ እድል ሊፈጥር የሚችል፣ የምዋለነዋይ ፍሰት ከቀንቀን እየቆረቆዘ መጣ። የጧት ሞትና በሽታ፣ ረሃብና መሀይምነት፣ ስደትና ስራ አጥነት የክልሉ ቀደምት መገለጫወች ሆነዋል። ዛሬ የአማራ ክልል ገዠ መደብ ት/ት ስርዓት፣ የአስረኛና የአስራ ሁለተኛ ክፍል ውጤት እድገቱ ቁልቁል እንደ ካሮት እየወረደበት ይገኛል። የአማራው አመራር ግን ለምን ብሎ ራሱንና አለቆቹን አይጠይቅም። በዛ ላይ፣ የአራት ኪሎው ‘የፈተናዎች ሀገር አቀፍ ድርጅትም’ እርማት ላይ “ርካሽ ሴራ” እንደሚሰራ፣ አያውቅም። ወይንም እያወቀ አድር ባይነቱን ቀጥሎበታል።

በአንድ ወቅት የእርማት ክፍሉ ጊዜያዊ የክረምት ሰራተኛ የነበሩ ጓደኞች የሚሰራውን “ቆሻሻ አሻጥር” እየቆዘሙም ቢሆን አውግተውኛል። ወደ ርማት ማሽኑ ከመግባቱ በፊት፣ የእያንዳንዱን ክልል ተፈታኝ መልስ ወረቀት፣ ማንኛቸውም እንደ ፈለጉ፣ የተፈታኙን ስም ሳይቀር፣ በላፒስና እርሳስ የሚቀያይሩበት አግባብ መኖሩን ተረድቻለሁ። ትልቁ ውጤት ወደ ታች የሚጎተትበት አግባብ ያሳዝናል። ይህን አገር–ዓቀፉ የፈተናወች ተቋም፣ በበላይነት የሚመሩት ደግሞ፣ ጽንፈኛ ወያኔዎች ሆነው ኖሮ፣ የእነርሱ ሀገር ማለት ህወሐት፣ ከፍ ሲልም ዋና መናህሪያቸው የትግራይን ራስ-ገዝ አስተዳድር ሆኗል። ያም ማለት፣ ያይኑ ቀለም ያላማራቸውን ክልል ተፈታኝ ውጤት እንደፈለጉ፣ ይዘበራርቁታል ወይንም ሊዘበራርቁ የሚችሉበት እድል በእጅጉ ሰፍቶ ይስተዋላል። ይህም ሌላ መቅሰፍት ነው!! በርግጥም፣ የሰውን ልጅ ቤት ዘግቶ፣ በላዩ ላይ እሳት የሚለኩስ፣ የወረደ ስብዕና ያለው ወያኔ፣ ይህን ቢያደርግ ልዩ ታእምር አይሆንም። አይደንቅምም።

እናንት አመራሮች
በተለይም የተዋህዶ ቤተክርስቲያን፣ የአማራ ፖለቲካ ልማት ፓኬጅ ምንጭ መሆኑን፣ የወያኔው ሀርነት መስራችና አፈቀላጼ አቶ ስብሀት ነጋ ሁሌ መለፍለፍ የማይሰለቸው ትልቅ ጉዳዩ ነው። መለፍለፍ ብቻ ሳይሆን፣ የዋልድባን አካባቢ ዶጋመድ አስደርጎ አሳይቶናል። መች በዚህ አበቃና! በየትኛውም የከፍተኛ ትምህርትና በሌሎችም የስቪል ተቋማት፣ የአማራ ምሁራን ከአስተዳድር፣ ከተራ መምህርነትና ሰራተኝነት ጭምር በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች እየተወገዱ ይገኛሉ። እነርሱ መወገዳቼው አደለም ጭንቄ፥ ከፋፋይና ዘረኛ አገዛዛችሁ ሀገርን እያፈረሰ መምጣቱ እንጅ። ክልሉ ላይ ያሉትም ቢሆኑ፣ በብአዴን ጸበል የግድ ተጠምቀው፣ ራሱን ብአዴንን አበ–ነፍስ ያደረጉ ናቸው። የምሁር ነጻነት እነሱ ጋ አይሰራም! አርሶ አደሩ ሌላ እንዳያስብ፣ በኖርዎዩ ያራ ማዳበሪያ ውዝፍ እዳ ተነክሮ፣ እንዲህ እየባዘነ ይኖራል። የወጣቱ ስራ ፈጠራ በህልና የሞራል ተነሳሽነት ከታመመ ሰንብቷል።

የዚህ ሁሉ መንስዔ፣ የእናንተ –ተላላኪ የአማራ ገዥዎች– ሆድ፣ እንደ ፊኛ መለጠጥና ህሊናችሁም ጠቦ መወጣጠሩ ጭምር ነው። የሀገር ልማት ማለት፣ የእናንተ፣ የልጆቻችሁና የሚስቶቻችሁ፣ እንዲሁም በዙሪያችሁ የተኮለኮሉ ዘመድ ወዳጆቻችሁ የመልማት ጉዳይ ብቻ ይመስላችሗል። ከግል ፍላጎት በሚመነጭ ስሜት ሳይሆን በሀገር ፍቅር ስሌት ብታስቡ ግን ይህን ትገለብጡት ነበር። ሀገርን እየበላችሁ፣ ሀገር የምታበለጽጉ አመራር ብትሆኑ ኖሮ ባልከፋ ነበር። እናንተ ግን ሆዳችሁንና ቤተሰዎቻችሁን ብቻ አረሸረሻችሁበት። ለዚህም፣ ወያኔ በቀላሉ ያጣጥፋችሗል። የክልላችሁን ዘርፈ ብዙ ፖሊሲ ወለድ ሸፍጥ፣ በጥልቅ ማደናገሪያ ስልቱም፣ “የፖለቲካ ኢኮኖሚው ዕርዮተ–ዓለም ዝቅጠት ሳይሆን፣ የክልሉ አመራር የአፈጻጽም ብልሽት ነው” ብሎ በየድርጅታዊ መድረኩ በሂስና ግለሂስ እንድታምኑ ያባዝናችሗል። እውነት ይመስል፣ ሳይገባችሁ ታጨበጭባላችሁ። ወያኔ በተሰባበረ አማርኛውም፣ እናንተንና መሰል ሰነፍ ረኞችን ያጃጅላል።

አዎ! ያለጎጃም ህዝብ ፍላጎት፣ የመተከል አውራጃ ወረዳዎች ተዘርፈው የወያኔ ጉሙዝ ፈጠሩ። ዛሬ በክልሉ ላይ ተጠቃሚው ግን፣ በድህነት ራቁት የሚማቅቀው የጉሙዝ ህዝብ ሳይሆን፣ የአገዛዙ የጡት ልጆች ሆኑ። እናም የአካባቢውን ተወላጅ ሎሌ አድርገውና በትግርኛ ከበሮ ምት ታጅበው የተንደላቀቀ ኑሮ ይኖሩበታል። ቦታው ላይ የነበረው ቀደምት አማራ ግን እንዲገደል፥ እንዲታሰር፥ እንዲደበደብና በፍርሃት እንዲሰደድ ሆኗል። የክልል አንድ አጎራባች፣ የወሎና የጎንደር ክፍለ–ሀገራት አውራጃዎች፣ ህዝቡና ለም መሬቱ እስከነ ባህሉ በሃይል እንደ ተወረረ ይገኛል። በቋንቋው እንዳይጠቀምና ማንነቱ እንዲመክን ተበይኖበት ይዳክራል/Sentenced to Assimilation of Identity/። የአካባቢው ባህል መዛባት ሰለባ የሆነው የእድሜ ክልል/Victim Age Group of Cultural Dislocation/ በተለይም ወያኔ ከወረረን ወዲህ የተፈጠረው ወጣት ሆኖ ተስተውሏል። ህዝብን ለዘመናት እንዲህ የሚነቅል፣ መሰል የወያኔ ሴራ፣ ቅንጣት የማይዘገንናችሁ እናንተ ሹመኞች፣ ይህን ሁሉ ትታችሁ የወልቃይትን የቅርብ ጉዳይ አዳፍናችሁ፣ ስለቅማንት መገንጠል ታዜማለችሁ።

የተጫነባችሁ የባንዳ አገዛዝ፣ በአስቸኳይ አዋጅ ሰበብ፣ የነበረቻችሁን አስተዳድርነክ ሃላፊነታችሁንም ክዷችሗል/Denial of Very Fragmented Administrative Authorities Vested/። ዛሬ የምትወስኑበት የፖለቲካና ደህንነት፣ የአስተዳድርና ጸጥታ ጉዳይ ከእጃችሁ ወጥቶ፣ እንደ በቀቀን የፕሮቶኮል ሾመኞች ብቻ መሆናችሁ፣ ስንቶቻችሁ ገብቷችሁ ይሆን!? የፌደራሉን ተውትና የክልላችሁን ህገመንግስት፣ መርሃ ግብሮችና የስልጣን ክፍፍላችሁን መች ይሆን የምታዝዙበት!? ፖለቲከኛ ማለትኮ ከተንጣለለው ቢሮ ውሎ መግባት አደለም። መወሰን የሚያስችል አቅምና መሪ የፖለቲካ አመራርነት ሚና፣ እስከነ ሙሉ ክብሩ ከሌላችሁ፣ የቢሯችሁን ጥበቃ ስራ ከሚሰሩ ዘበኞች፣ በምን ትለያላችሁ!? ልዩነቱ፣ እናንተ ቢሮ ውስጥ፣ ዘበኞቹ ደግሞ ጥበቃ ቤት/Guard House/ ውለው የመግባት ጉዳይ ነው። በተጨባጭ፣ “መወሰን የሚያስችል ስልጣን ያለው፣ ከእናንተ መካከል እስኪ እጁን ያውጣ” ሲባል፣ የጅልና ሆዳም ውርደት እንደ ተዋረዳችሁ ይሰማኛል።

ይህ ነው እንግዲህ የታላቁ መሪያችሁ ትውፊት/Legacy of World Class Mind/። ከተሜው የቤት መስሪያ ቦታ የለም እየተባለ፣ አርሶ–ዓደሩ የእንስሳት ግጦሽ መሬትን እየናፈቀ፣ ባለበት በዚህ ወቅት፣ እናንተ ግን “የታላቁ መሪ ፓርክ” በሄክታር ትከልላላችሁ። የፓርኩ ስያሜ፣ ታላቅ መሪ ከምትሉት ሰው ውለታ ጋር የተገናዘበ ቢሆን ኖሮ፣ ዳሞት–ደንገልስ ላይ፣ አባቴ ለጎጆ መውጫ ሰቶኝ የነበረው፣ ቁራሽ መሬት ጭምር በእርሱ ስም ፓርክ ሆኖ ባስደሰተኝ ነበር። ዜናው ግን ወዲህ ነው! ሀበሻዊ ስሜትን የገደለ፣ በህዝቦች መካከል ጥላቻን ያስተማረ–የክፋት ነብይ። ግና ከጅምሩ፣ በጅምላና በችርቻሮ ሀገርን ለሽያጭ ያቀረበ። የበርካታ ወገኖቻችንን እልቂት ለዘመናት የመራ። የአኖሌን ሀውልት መሰረትም ጥሎ ያለፈ ገዠ። ከሁሉም በላይ ሀገር የማፍረስ ራዕዩን ለመሰል ጓዶቹ ሰንዶና አስተምሮ ያለፈ የምንጊዜም ባንዳ! ይህ ዘመናዊ የጌታና ሎሌ ስርዓትን ያቀነቀነ ራስ ወዳድ ኮሚኒስት፣ በየአድባራቱ ሳይቀር ፎቶው እንዲሰቀል ያደረጋችሁት፣ የእናንተና የአሜሪካዊቷ ስድ ቁማርተኛ–ሱዛን ራይዝ–የታላቁ መሪ ትውፊት አልታይህ ብሎኝ፣ እንዲህ ሞገትኳቸችሁ።

እናንት ጥቅመኞች፥ በርግጥም ደካሞች!
ይልቅስ ለሰፊው ህዝብ ነጻነትና ጥቅም በሚደረግ ትግል፣ ውስንም ቢሆን መሽቶብናል ብላችሁ ሳትዘናጉ የበኩላችሁን አስተዋጾ ብታደርጉ፣ ብኩኑ ታሪካችሁ ተገልብጦ በደማቅ እንዲጻፍ ይሆናል። የሚያዋጣችሁ የወለዳችሁ ህዝብ እንጅ፥ የአብይ አህመድ የይምሰል ኢትዮጵያዊነት አደለም! ስለሆነም፥ የትግራይን ነፃ-ዓውጭ ጠ/ሚ የአብይን ኢትዮጵያዊነት ጭምብል አውልቃችሁ፥ ”የግለሰብ አስተሳሰብ ፎቶ ቅጅ ወይንም የማንም የጎማ ማህተም” መሆናችሁ ማብቃቱን ታሳዩ ዘንድ፥ እንዲህ ጥሪው ይድረሳችሁ! ትግል ለፍትሃዊ ኢትዮጵያዊነት!!