EOTC Holy Synod

  • የሰላም እና አንድነት ኮሚቴው፣ የድርድሩን ቦታና ጊዜ ለይቶ በቅርቡ ያሳውቃል፤
  • ኹሉም ወገኖች፣ ከጸሎት ጀምሮ አስፈላጊውን ድጋፍና እገዛ እንዲያደርጉ ጠየቀ፤
  • የሀገር ውስጡ በብፁዕ አቡነ ቀውስጦስ፣ የውጩ በብፁዕ አቡነ ኤልያስ ይመራል፤

†††

በውጭ ሀገር በስደት ከሚኖሩት አባቶች ጋራ ለተጀመረው የዕርቀ ሰላም ንግግር፣ የሀገር ቤቱን ቅዱስ ሲኖዶስ በመወከል እንዲነጋገሩ የተመደቡትን ብፁዓን አባቶች ምርጫ ምልአተ ጉባኤው ያጸደቀ ሲኾን፤ የዕርቀ ሰላሙ ሒደት እንዲቀጥል ይኹንታ መስጠቱን የሚገልጽ ደብዳቤ ለሰላምና አንድነት ኮሚቴው እንዲጻፍም ትእዛዝ ሰጠ፡፡

የርክበ ካህናት ምልአተ ጉባኤው፣ በዛሬ ዓርብ፣ ሚያዝያ 26 ቀን 2010 ዓ.ም. ሦስተኛ ቀን የቀትር በኋላ ውሎው፣ “ከውጭ አባቶች ጋራ ስላለው ዕርቀ ሰላም” በሚል በተያዘው አጀንዳ ላይ ስለሚቀበላቸው መርሖዎችና ጥንቃቄ ስለሚያስፈልጋቸው ጉዳዮች ከተወያየ በኋላ፣ ባለፈው የካቲት ወር፣ ቅዱስ ሲኖዶሱን በመወከል የሚደራደሩትን ልኡካን ምርጫ በማጽደቅ ለተልእኮ ሠይሟል፡፡

ልኡካኑ፦ የሰሜን ምዕራብ ሸዋ – ሰላሌ ሀ/ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ቀውስጦስ፣ የምሥራቅ ሸዋ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ጎርጎርዮስ እና የባሕር ዳር ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ አብርሃም ሲኾኑ፣ በብፁዕ አቡነ ቀውስጦስ እንደሚመራ ተገልጿል፡፡

የዕርቀ ሰላሙ አስፈላጊነት የታመነበት እንደኾነና ለስኬቱም እንደሚሠራ ይኹንታውን የሚገልጽ ደብዳቤ ለተሠየሙት ልኡካን እንዲደርሳቸው ምልአተ ጉባኤው ያዘዘ ሲኾን፣ ከቀድሞው በተሻለ አያያዝ ተነሣሽነቱን በመውሰድ ለሚያደራድሩትና ለሚያነጋግሩት፣ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ሁለተኛ ዙር የሰላም እና አንድነት የአዲስ አበባ ቅርንጫፍ ኮሚቴ አባላትም ተመሳሳዩ እንዲደረግ መመሪያ ሰጥቷል፡፡

ከኮሚቴው አባላት ስድስቱ(ልዑል ራስ መንገሻ ሥዩም፣ ዶ/ር ንጉሡ መለሰ፣ አቶ ግርማ ዋቄ፣ ዶ/ር አብርሃም፣ ቀሲስ ዶ/ር መዝገቡ ካሳ እና አቶ ብርሃን ተድላ)፣ ትላንት ከቀትር በኋላ በምልአተ ጉባኤው ፊት ቀርበው፣ ይኹንታ ከሰጠበት ከጥቅምቱ ምልአተ ጉባኤ ወዲህ ከቋሚ ሲኖዶስ ጋራ ሲያደርጉ ስለቆዩት ግንኙነት በማስረዳት ሒደቱ ስለሚፋጠንበት ኹኔታ ጠይቀዋል፡፡ “ጥሩ ነገር ነው የሰማነው፤ ቅዱስ ሲኖዶሱ የተመደቡትን ልኡካን አባቶች አጽድቆ የዕርቀ ሰላም ድርድሩን እንዲያደርጉ መመሪያ ሰጥቷል፤” ብለዋል ስለዛሬው ውሳኔ የተጠየቁ የሰላምና አንድነት ኮሚቴው አባል፡፡

ኮሚቴው፣ የሚጠበቀውን ይኹንታና ውሳኔ ማግኘቱን የተናገሩት እኚሁ የኮሚቴው አባል፣ የዕርቀ ሰላሙ ልኡካን አባቶች የሚገናኙበትንና ድርድሩ የሚካሔድበትን ቦታና ጊዜ በቅርቡ ለኹለቱም ወገኖች እንደሚያሳውቅ ጠቁመዋል፡፡ ጥንታዊትና ሐዋርያዊት ለኾነችው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ሃይማኖታዊና አስተዳደራዊ አንድነት መጠበቅ የሚጨነቁ ወገኖች ሁሉ፣ ከጾምና ጸሎት ጀምሮ አስፈላጊውን ድጋፍና እገዛ እንዲያደርጉም ጥሪያቸውን አስተላልፈዋል፡፡

በብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሬዎስ የሚመራው ቅዱስ ሲኖዶስ፣ ከጥቅምት 22 እስከ 24 ቀን 2010 ዓ.ም. በኮለምበስ ኦሃዮ ባደረገው ጉባኤ፣ በሁለት የሰላም እና አንድነት ኮሚቴው አባላት የደረሰውን የዕርቀ ሰላም መልእክት በስፋት ከተወያየበት በኋላ፣ በብፁዕ አቡነ ኤልያስ ሊቀ ጳጳስ የሚመራ ሦስት አባላት ያሉት ተደራዳሪ ልኡክ ሠይሟል፡፡ ለስኬቱም ከኮሚቴው ጎን እንደሚቆም ገልጾ፣ “እግዚአብሔር ይጨመርበት፤ አምላከ አበው ሥራችሁን የተቃና ያድርግላችሁ፤” በማለት ቡራኬውን መስጠቱን በጻፈው ደብዳቤ አስፍሯል፡፡