ጠ/ሚ/ሩን እንዴት እንመናቸው?
እውነቱ በለጠ – ኮንሶ
Team ለማ በተሰኘ ቡድን ተጠርንፈው በኦሮሚያ ክልል በጀመሩት የለውጥ እንቅስቃሴና በአንደበቴ ርቱዕ ንግግራቸው በመላው ኢትዮጵያ ተቀባይነትን በማግኘት በብዙ እልህ አስጨራሽ የጠረጴዛ ዙሪያ ትግልና በኢትዮጵያ ወጣቶች ግፊት ለጠ/ሚ/ርነት ሥልጣን የበቁት ዶ.ር አብይ አህመድ በትረ ሥልጣናቸውን ከቆናጠጡ አንድ ወር አለፋቸው ።
የኢትዮጵያ ህዝብ የሥርዐት ለውጥ እንደሚፈልግና እሳቸው ወደዚያ ለውጥ ህዝቡን ይመራሉ ተብሎ በህዝብም ሆነ በአንዳንድ ተፎካካሪ የፖለቲካ ድርጅት መሪዎች ሳይቀር ተስፋ ተጥሎባቸውና ህዝቡም እሳቸውን በማግኘቱ ጮቤ ቢረግጥም ከቃለ መሀላው በኋላ ተዓምር ይሠራሉ የተባለላቸው ጠ/ሚ/ር በቢሯቸው የሚባላ ጅብ ፣ በወንበራቸው የሚዋጋ እሾህ ያለ ይመስል በየሠፈርና በየጎረቤት ሲሽከረከሩ ውለው እያደሩ ነው ። የማን እንደሆኑ ሁሉ የማይታወቀው ካቢኔያቸውን ለማቋቋም የፈጀባቸው ጊዜ የዓለምን ሪከርድ ሳይሰብር አልቀረም ። ይህን ካቢኔ ከማቋቋም ጀምሮ በማግሥቱ በጥቂት ቀናት ውስጥ ህዝብ የጠበቃቸው ወሳኝ ነገሮች እንኳንስ ያነ እስከ ዛሬ አልተጀመሩም ። ለአብነት ያህል ፦
1. ሕዝብ ተፈርዶባቸው እንዲታሠሩ የሚጠብቃቸው እነ ሽፈራው ሽጉጤ ፣ ሲራጅ ፈርጌሳ ፣ አሰፋ አብዬ ፣ ዓለምነው መኮንን ፣ አባዱላ ገመዳና የመሳሰሉትን ካቢኔያቸውና አማካሪዎቻቸው አድርገው በዙርያቸው ማሰባሰባቸው ብቻ ሳይሆን “ ሠራዊቱ እርምጃ እንዲወስድ አዘናል “ ብለው ህዝብ ያስጨፈጨፉትን ኃይለማርያ ደሳለኝን የክብር ተሸላሚና ተሞጋሽ ማድረጋቸው ፣
2. የኦሮሚያ አመራር በነበሩበት ጊዜ እሳቸውና ከሳቸው ጋር የነበሩ አመራሮች በክልሉ ህዝብ ስም ያልተቀበሉትን ፣ ተጭበርብሮ ሲጸድቅም ከእሳቸው ጋር የነበሩ የተወካዮች ም/ቤት አባላት ላለማስጸደቅ በብርቱ የታገሉትን እንዲሁም መላው የኢትዮጵያ ህዝብ በብርቱ የተቃወመውን ገዳይና አፋኝ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በተመረጡ ማግሥት ወይም
በዓለስመታቸውን በፈጸሙ በቀናት ልዩነት ያነሳሉ ተብሎ በጉጉት ሲጠበቅ እንኳንስ ሊያነሱ በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ደንብ መሠረት እሳቸው መሪ ፣ በእሳቸው የተሾሙት የመከላከያ ሚኒስቴሩ የኮማንድ ፖስት ኃላፊ ሆነው መቀጠላቸውና ስለማንሳት አለማንሳት ትንፍሽ አለማለታቸው ፣
3. ልክ እንደ አስቸኳይ ጊዜ አዋጁ በተመረጡ ወይም በዓለስመታቸውን በፈጸሙ በቀናት ልዩነት በመላው ኢትዮጵያ ያሉ የፖለቲና የህሊና እሥረኞች ያለምንም ቅድመ ሁኔታ ሙሉ በሙሉ ያስለቅቃሉ ተብሎ ሲጠበቅ ከመመረጣቸው በፊት የተፈቱት እሥረኞች ብዛት ከተመረጡ በኋላ ከተፈቱት ጋር ሲነጻጸር በእሳቸው ጊዜ እሥረኞች አልተፈቱም ወደሚል ድምዳሜ የሚያደርስ መሆኑ ፣
4. የኢትዮጵያን ህዝብ ያስጨፈጨፈ ፣ ያሰቃየውና ዛሬም እያስጨነቀ ያለው የመከላከያና የደህንነት መዋቅሩ እስካሁን በአሰቃዮች እጅ መሆኑና ከእጃቸው ለመንጠቅ የሚደረግ ሙከራ ስለመኖሩ እንኳ አለመታወቁ ፣
5. ዛሬም ንጹሀን ሰዎች በየቦታው ይገደላሉ ፣ ይደበደባሉ ፣ ይታሠራሉ ፣ ዩኒቨርስቲዎች ሠላማዊና ምቹ የመማሪያ ሥፍራ ሳይሆኑ የመከላከያ ሠራዊት መፈንጭያ ፣ ተማሪዎች የሚደበደቡበት ፣ ሴቶች የሚደፈሩበት ፣ ዕውቀት መቅሰሚያ ሳይሆን ፍርሀት ፣ ስጋትና ጭንቀት ማትረፊያ ሆነው እያሉ የእሳቸው ዝምታ መምረጥ ፣
6. የጦር መሣሪያ ሳይቀር የሀገሪቱ ሀብትና ንብረት ቀን ከሌሊት ወደ አንድ አካባቢ እየተጋዘ ነው የሚለው ወሬ ብቻ ሳይሆን አንዳንዴም እጅ ከፍንጅ እየተያያዘ የሚታይበት ሁኔታ እያለ እንደ ሀገር መሪ የማስቆም እርምጃ ከመውሰድ ዝምታ መምረጥና የመሳሰሉትን ሲንታዝብ ከንግግራቸው የተደመጠውና የኢትዮጵያ ህዝብ ከእሳቸው የሚጠብቀው ነገር መሬት ወርዶ አለመታየቱ ያሳደርንባቸውን እምነት እየሸረሸረ ይገኛል ።
የዚህ መልእክት ጸሐፊ ጠ/ሚ/ሩ በሀገር ውስጥም ሆነ በውጭ የሚያደርጉትን ጉብኝት የሚቃወም ሳይሆን የጉብኝቶቹ መብዛትና ተከታታይነት ፣ ህዝብ በየደረጃው ከእሳቸው የሚጠብቀው ምላሽ መዘገየትና ፍንጭ እንኳ ማየት አለመቻል “ እንዴት እንመናቸው? “ የሚል ጥያቄ የጫረባቸው መሆኑን አንባቢያን እንዲያውቁለት ይፈልጋል ።
አይቀሬው ድል የሰፊው ህዝብ ነው !!!