አብዲሌና ህወሓት (ብርሐኑ ተክለያሬድ )
ይህን ሰው በዚህ ትምህርት ቤት ተማረ እዚህ ሲማር አውቀዋለሁ የሚል አንድም ሰው አይገኝም እርግጥ ነው ብዙዎች መብራት ሰራተኛ ሆኖ ሽርፍራፊ ሳንቲም ካልሰጣችሁኝ በማለት ገመድ እየቆረጠ ደባ ሲሰራባቸውና በአካባቢው ባህልና በእስልምና ሀይማኖት ያልተፈቀደ ነውረኛ ተግባር ሲፈፅም አስካሪ መጠጥ ጠጥቶ ሴቶችን ሲጎነትልና ሽማግሌዎችን ሲያንጓጥጥ ያስታውሱታል ።
እድሜ ለወሮበላው ህወሓትና ለጎሳ ፌዴራሊዝሙ ይሁንና ይህ ሰው ከጥቂት ጊዜ በኋላ ህወሓት ከወለዳቸው የዛር ውላጅ ድርጅቶች የአንዱ አጋር ድርጅት አባል ሆነ የህወሓት የስልጣን መውጫ መስፈርቶች የሆኑትን የተበላሸ ስብዕና ባለቤትነትንና ጥልቅ አድር ባይነትን አጣምሮ የያዘ ሰው ነበርና በአጭር ጊዜ ውስጥ የክልል ፀጥታ ቢሮ ኃላፊ ሆኖ ተገኘ ።
መለስ መራሹ ህወሓት ከክልሉ መሪዎች ጋር በየጊዜው በሚፈጠረው አለመግባባት የክልሉን መሪዎች ገሚሱን ለእስር ገሚሱን ለስደት ሲዳርግ የህን ሰው ኳርተር የሚል ቅፅል ስም በተሰጠው የወያኔ ጄነራል ሞግዚትነት የክልሉ ፕሬዝዳንት አድርጎ ሾመው ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ክልሉ የዚህ ሰውና የህወሓት የግል ይዞታ የክልሉ ነዋሪዎችም የክፉው እሳት ማገዶ ሆነዋል ሰውየው የሶማሌ ክልል ፕሬዝዳንት አብዲ ኢሌ ነው ።ይህ ግለሰብ በስልጣን ዘመኑ በዜጎች ለይ የፈፀማቸው ግፎች ተሰፍረው የማያልቁ ቢሆኑም እነሱን ለታሪክ ትተን በእስር ቤት የሚገኙ የግፉ ሰለባዎች ካጫወቱኝና እኔም ከተመለከትኩት አሰቃቂና አስገራሚ ድርጊቶቹ ጥቂት እንጨልፍ
አሀዱ
በአብዲ ክልል ዳኛ ፍርድ ቤት ህግ ወዘተ የሚባል ነገር የለም ህግም ፍርድ ቤትም ዳኛም ራሱ ብቻ ነው ኦብነግ ገባ ብሎ አንድ መንደር አሰከብቦ ያቃጥላል ሲመሽ ጄል ኦጋዴን ሔዶ ራሱ እስረኛ ሲደበድብና ሲያስደበድብ ያድራል ራሱ እስረኞች ላይ ፍርድ ይሰጣል(አንድም ቀን ፍርድ ቤት ሳይቀርቡ የሞት ፍርድ እንደተፈረደባቸው በሬድዮ የሠሙ ወጣቶች አሁንም ዝዋይ ማረሚያ ቤት ናቸው) በክልሉ ከእርሱ ጋር ባለ ስልጣን የነበሩ ሁሉ መጨረቸው ስደት አልያም እስር ቤት ነው 54 የክልሉ የፓሊስ ባለስልጣናት(2 ኮሚሽነሮችን ጨምሮ) አሰቃቂው ጄል ኦጋዴን ገብተዋል በአጠቃላይ ክልሉ የሱ የግል ንብረት ሆኗል
ክልኤቱ
በ2006 አም አንድ የክልሉ አመራር የነበረ ሰው ከአብዲ ጋር ባለመስማማቱ ወደ አዲስ አበባ ይመጣል የፌዴራል መንግስትም ሰውየውን ተቀብሎና ጠባቂዎች ሰጥቶ እዚሁ እንዲኖር ያደርገዋል በዚህ የተናደደው አብዲም ሰውየውን አፍነው እንዲያመጡለት ጎይቶም በሚባል የህወሓት ደህንነት የሚመራ ቡድን ወደ አዲስ አበባ ይልካል አፋኞቹም ሰውየውን ሲከተሉ ውለው አንድ ሱፐር ማርኬ በር ላይ ከጠባቂዎቹ መንትፈውት ጉዞ ወደ ጅጅጋ ይጀምራሉ ነገር ግን ጠባቂዎቹ ሪፓርት አድርገው ኖሮ አዋሽ ላይ መንገድ ተዘግቶ ይቆያቸዋል ከዚያም ጠላፊዎቹ ተጠልፈው ማዕከላዊ ይገባሉ በምርመራ ወቅትም ጎይቶም የተባለው ግለሰብ ከዚህ በፊት ከአዲስ አበባ በአብዲ ትእዛዝ 26 ሰዎችን አፍኖ መውሰዱ ይደረስበታል ሲጠየቅም ኮራ ብሎ አዎ ወስጃለሁ ለአብዲ ሰጥቼዋለሁ አሁን የት እንዳሉ አላውቅም ብሎ ይመልሳል ሌላው ግብረ አበሩም አዲስ አበባ ቀበና አካባቢ ግቢ ተከራይተው ሰዎችን እንደሚያስሩ እንደሚደበድቡ የሰው ህይወትም እንዳለፈባቸው ይህም በአብዲ ትዕዛዝ እንደሆነ ይናዘዛል ይሁንና ጊዜው መግደል የሚያሸልምበት ነውና እንኳን አብዲ ሊከሰስ ቀርቶ ተላላኪዎቹም በዋስ እንዲወጡ ተደረጉ
ሠለስቱ
ጉሌድ ይባላል አብዲ ክልሉን ሲመራ እርሱ ደግሞ የፀጥታ ቢሮ ሀላፊ ሆኖ ተሾመ በመሀልም ለማስተርስ ዲግሪ ትምህርት ወደ እንግሊዝ ተጓዘ ከዚያ ሲመለስም የጠበቀው የድሮው ሹመት ነበር በስራ ላይ ሳለ ከእለታት በአንዲቱ ጎዶሎ ቀን ከአብዲ ጋር ተቀምጦ በመቃም ለይ ሳለ አብዲ እንደ ቀልድ ”ጉሌድ እኔ አንተን በሚስቴ እጠረጥርሀለው” አለ ነገር ተበላሸ ጉሌድ ግራ ገባው ግን ሰውየውን በመፍራት ምንም አልተናገረም በማግስቱ የአብዲ ቅናት መልኳን ቀይራ ኦብነግ የሚባል ካርድ መዛ መጣች እናም ጉሌድ በተራ ቅናት የተነሳ አሸባሪ ተብሎ ጄል ኦጋዴን ገባ ከሁለት ቀናት የጊዜ ቀጠሮ ፍርድ ቤት መቅረብ በኋላ በራሱ በአብዲ 13 አመት ተፈርዶበት ዝዋይ ማረሚያ ቤት ይገኛል
ስልብ አሽከር…..
ይህ ነፍሰ ገዳይ እርሱን የሚያሳስበው የአለቆቹ የህወሓቶች ትእዛዝ እንጂ የህዝቡ ብሶት አይደለም ስልብ አሽከር በጌታው እቃ ይኮራል እንዲሉ ህወሓትን የሚነካ ነገር በመጣ ቁጥር ከፊት ይገኛል ከጎንደር ተፈናቀሉ ለተባሉ የትግራይ ተወላጆች በቅፅበት 10 ሚሊየን ብር መቀሌ ድረስ ሔዶ መስጠቱ በወቅቱም እነሱ ከተነኩ አንቀፅ 39ን ጠቅሰን እንገነጠላለን የሚል መግለጫ መስጠቱ ከትግራይ ጄነራሎች ጋር በሐሆን በቅርቡ በኦሮሚያ ክልል የፈፀመው ግፍ ጥቂቶቹ ማሳያዎች ናቸው ሰውየው አሁንም ሌላ እልቂት ለመፈፀም እየተቁነጠነጠ ነው ማን ሃይ ይበለው?አይ መለስ ነፍስህን አይማረው!!!!