“አማራ አህያ፤ ምን ታረጋላችሁ?” እያለ ሁሌ ይሳደበል።
ከባድ መሳሪያዎች የጫኑ ከ40 ያላነሱ ወታደሮች ናቸው መጥተው የያዙኝ። ደብድበውኛል በጣም አሰቃይተውኛል። የሰው ልጅ ላይ ሊፈፀም በማይገባ መልኩ “የት ነው ያለሁበት ቦታ” ስል ማዕከላዊ መሆኑ በሰው ነው የተነገረኝ እንጂ እንዴት ወደ አዲስ አበባ እንዳመጡኝ እንኳ አላውቅም፤ በዱላ ብዛት ራሴን ስቼ ነበር።
የ21ኛው ክፍለ ዘመን ፋሽስቶች ናቸው። ዘሬ እየተጠቀሰ “አንተ አህያ” እየተባልኩ ነው የሚገርፉኝ፤ ያቺ ሰአት የጣዕረ ሞትና የስቃይ ሰአት ናት። ከህዝብ ጋር ዳግም እንገናኛለን፣ ከእናንተም ጋር ቁጭ ብዬ እንዲህ አወራለሁ ብዬ አላሰብኩም ነበር። ግን እውነተኛው አምላክ ይሄን አድርጓል፡ እኔንም አባንም “እነዚህ መነኩሴ አይደሉም” እያሉ እየተቀባበሉ ነው የሚቀጠቅጡን።
ከትልልቅ ባለስልጣናት ከአነ አቶ ገዱ አንዳርጋቸው ጋር ትገናኛላችሁ፤ እያሉ ነው በየቀኑ ለወራት ያለማቋረጥ ማታ ማታ እየጠሩ የሚገርፉን፤ የሚደበድቡን። ስቃይና መከራው ከባድ ነው፤ አሁን ሰውነቴን ገልጨ አላሳያችሁም እንጂ ሰውነቴ ሸቶ ሰው ለመቅረብ ይሳቀቅ ነበር ለምፁ አሁንም ገላዬ ላይ አለ። መንታ አለንጋ አለ፣ የኤሌክትሪክ ሽቦ አለ፤ በእዛ ነው ያለ ርህራሔ ራቁታችንን አድርገው የሚገርፉን።
በቅርቡ ከእስር የተፈቱት የዋልድባ መነኮሳት ከመታሰራቸው በፊት የነበረውን ሁኔታ እና በእስር ቤት በፋሽሽት ትግሬ ወያኔዎች የደረሰባቸው ዘግኛ ግፍ ሰቆቃ ከግዮን ቁጥር 05 ዕትም ሚያዝያ 2010 ዓ.ም ጋር ባደርጉት ቃለመጠየቅ በሰፊው አብራርተዋል። ሙሉ ቃለ መጠየቁን ከዚህ በታች ያንብቡት
(ቃለ መጠየቁን በPDF ለማንበብ ከዚህ ላይ ይጫኑ)
“ህወሓት አሠረን የኢትዮጵያ ሕዝብ አስፈታን” አባ ገብረየሱስ ኪዳነ ማሪያምና አባ ገብረስላሴ ወልደኃይማኖት
አባ ገብረየሱስ ኪዳነ ማሪያምና አባ ገብረስላሴ ወልደኃይማኖት ገብረመድህን የዋልድባ ገዳም መነኮሳቶች ናቸው። በአካባቢው መንግስት “ልማት ለማካሄድ” በሚል ሰበብ የጀመረውን እንቅስቃሴ መላው መነኮሳት ሲቃወሙ አብረው ነበሩ።
የቅዱሳኑ አፅም ሲታረስ ያወጉዙት መነኮሳት በፀጥታ ሃይሎች ተይዘው አንድ አመት ከሶስት ወራት በእስር አሳልፈዋል። በእስር ጊዜያቸው ለበርካታ ቀናት በውድቅት ለሊት እየተጠሩ በአሰቃቂ ሁኔታ ተገርፈዋል። በእስረኞች ፊት ተደብድበዋል፣ ተሰድበዋል። መነኮሳቱ “ይህ ገዳም የህዝበ ክርስቲያኑ መገልገያ ነው፤ የምትቆፍሩት ቦታም የቅዱሳን አፅም ያረፈበት ስለሆነ የቤተ ክርስትያን ህግና መብት ሊከበር ይገባል” በማለታቸው ይህንን ሁሉ ግፍና መከራ ሲቀበሉ ጉዳዩ የሚመለከታት ቤተ ክርስቲያን ዝምታን መምረጧ ለምን ይሆን?… በህዝብ ግፊት ክሳቸው ተቀርጦ እንዲፈቱ የተደረጉት ሁለቱ መነኮሳት በተቀዳደደ የመነኩሴ ልብስ ከአመት በላይ የቆዩበት የእስር ህይወት ምን ይመስላል? በሚሉና ሌሎች ተዛማጅ ጉዳዮች ዙሪያ የግዮን ጋዜጠኞች ፍቃዱ ማ/ወርቅና ሮቤል ምትኩ እንዲህ ባለ መልኩ አነጋግረዋቸዋል።
ግዮን፡- እናንተን ለእስር የዳረጋችሁ የዋልድባ ጉዳይ መነሻ ውዘግቡ ምን እንደነበር ወደኋላ መለስ ብለው ቢያጫውቱን?
አባ ገብረየሱስ፡- እንግዲህ የወልቃይት ስኳር ፕሮጀክት በሚል ሰበብ የዋልድባ ገዳም ቦታን ለልማት እናውላለን በሚሉ ሰአት ማህበረ መነኮሳት ደግሞ የአባቶች አፅመ ቅዱሳን ያረፈበት፣ ስብሃተ እግዚአብሄር የሚፈፀምበት ስለሆነ ይህ ቦታ ለልማት መዋል አይችልም የሚል ነው መነሻው።
ይህንን ተቃውሞ ወደ ሚመለከተው አካል ለማቅረብ ከሶስቱ ገዳማት የተውጣጡና የተወከልን መነኮሳት በሰአቱ ለነበሩት ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ በስማቸው የተፃፈ ደብዳቤ ለማቅረብ በምንቀሳቀስበት ወቅት ነው ውዝግቡ የተካረረው። ከዛ በፊት ግንቦት 10 ቀን 2003 ዓ.ም አዲስ አበባ ሜጋ ህንፃ ላይ የሚገኘው የወይዘሮ አዜብ መስፍን ቢሮ በመሄድ ስድስት መነኮሳት ጉዳዩን አሳውቀናል። ምንም መልስ አላገኘንበትም፤ በወቅቱ የሆነ የውጭ አገራት መሪዎች የሚሳተፉበት ስብሰባ እየተዘጋጀ ስለሆነ ባለቤታቸውንም ማግኘት እንደማንችል ተነግሮን ተመለስን።
ግን በየጊዜው ነገሩ እያስቸገረንና እየገፋ ሲመጣ 2004 ዓ.ም ጥር 16 ቀን ያዘጋጀነውን ደብዳቤ ይዘን ጠቅላይ ማኒስትሩ ቢሮ ተገኘን። በጊዜው ያነጋገረን ፀሃፊው ሲሆን የመለሰልን መልስ “ለእናንተ ምትክ ቦታ ይሰጣችኋል እንጂ የሚለማ ከሆነ መቃወም አትችሉም” ማመልከት ያለባችሁም ለክልሉ እንጂ ወደ እኛ ጋር መምጣት አልነበረባችሁም የሚል ነበር። እኛም በምላሹ አዝነን ወደ ገዳማችን ተመልሰናል።
ይህ ጉዳይ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን በመሆኑ ለአቡነ ጳውሎስ ግልባጭ ደብዳቤውን ይዘን ስንመጣ ልዩ ፅ/ ቤት እንደደረሰን መግባት አልቻልንም። መግባት ስላልቻልን ያንን ደብዳቤ ለልዩ ፅ/ ቤት አስረከብን ተመልሰናል። ከዛ በኋላ ነገሩ እየተጋጋለ ሲሄድ፣ እነ አሜሪካ ድምፅ የአማርኛው ፕሮግራም አጠቃላይ ዝርዝር ሂደቱን ሲያስተላለፉ ፣የዋልድባ ጉዳይ በህዝበ ክርስትያኑ ዘንድ ተደማጭነት አገኘ። ትኩረቱ ወደ ቤተ ክህነቱ ሲዞርና ህዝቡና ቤተክህነት ሲጋጩ በመንግስት አካላት እነዚህ መጥተው የነበሩ መነኮሳት እንዲመጡ ተባለ… በጊዜው ለእኔ ነው ስልክ የተደወለው።
“እንድትመጡ የአይሮፕላን ትኬትም ተቆርጦላችኋል” አሉኝ፤ “አይ አሁንማ ልትገሉን ካልሆነ በቀር በተደጋጋሚ ቢሮአችሁ ድረስ መጥተን መልስ አልሰጣችሁንም፤ ያኔ መልስ ሳትሰጡን አሁን ምን ተገኘና ኑ ትሉናላችሁ? ከፈለጋችሁ ከታረሰው ቦታ ድረስ ኑና አነጋግሩን” የሚል መልስ ሰጠኋቸው።
በኋላ የጠቅላይ ቤተክህነት ስራ አሰኪያጅ ተስፋዬ ውብሸት የተባለና ሌሎች ሁለት የቤተ ክህነት ሰዎች፣ የሽሬና የመቀሌ ባለስልጣናት፣ ተሰብስበው መጡ። መጀመሪያ ላይ የአዲስ አበባ አገረ ስብከት ምክትል ስራ አስኪያጅ ሽሬ ላይ ሰብስበውን ነበር በዚያ አልተስማማንም፤ እኛም የታረሰው ቦታ ላይ ሄደን ካልተነጋገርን በቀር አንወያይም አልናቸው። እነሱ ደግሞ “ማይፀብሪ” ላይ እንነነጋገር አሉ፤ “ማይፀብሪ ክልላችን አይደለም፣ ሶስቱ ገዳም የሚሰበሰቡት አድርቃይ ላይ ስለሆነ እዛ ተነጋገረን ወደ ታረሰው መሬት እንሂድ፤ እኛ ሶስት አራት መነኩሴዎች ብቻ በዚህ ጉዳይ ላይ መወሰን አንችልም በሶስቱ ገዳማት ያሉ መነኮሳትንም ማነጋገር አለብን አልናቸው።
በዚህ መሰረት መጋቢት 5 ቀን “አባ ነፃ” የተባለውንና በግድቡና ስኳር ልማቱ ፕሮጀክት አማካይነት ይነሳል የተባለው ቦታ ላይ ሄደን ተሰበሰብን። መስማማት አልቻልንም ስንወዛገብ ዋልን፤ ቦታው አይነካም የሚል አቋም በመያዛችን ሊቀጳጳሱም ሆኑ የመጡት የመንግስት ባስልጣናት ሄዱ፤ ግን ወደ መጡበት ሳይመለሱ ወዲያውኑ ፌዴራል ፖሊሶች ልከው በገዳሙ ውስጥ ቤታችንን አስፈተሹ። የትልልቅ መነኮሳት በአት (መኖሪያ) እየተገለበጠ ተበረበረ። በጊዜው እኔንም ይዘው ለመሄድ ፈልገው ነበር፤ ግን በአካባቢው ሊያገኙኝ አልቻሉም። አመጣጣቸውን ስላወቅኩ ወደ በረሃው ገብቼ ተሰወርኩ።
ግዮን፡- አባ ገብረስላሴ እርስዎስ ከመጀመሪያው የዋልድባ ገዳም ውዝግብ አንስቶ የነበሮት ተሳትፎ ምን ይመስል ነበር?
አባ ገብረስላሴ፡- ያው ጉዳዩን አባታችን አባ ገብረየሱስ ገልፀውታል። ገዳሙ ወክሏቸው ሲወጡ ሲወርዱ የነበሩት እሳቸው ናቸው። ግን ማህበሩ በሚሰበሰብበትና ቃለጉባኤ በሚያደርጉበት ሰአት ሁላችንም መኮሳት አብረን እንሰበሰብ ነበር። 2004 ዓ.ም ላይ ገዳሙን ለልማት ልናውለው ነው ለእናንተ ካሳ እንስጣችሁ ብለው በመጡበት ወቅት 500 የምንሆን መነኮሳት ከመንግስት ባለስልጣናትና ከሀገረ ስብከቱ ሰዎች ጋር ተሰብስብናል።
ዙሪያችንን በመከላከያ ሰራዊት አጥረውና ከበው ነበር ያነጋገሩን፤ “ይሄ ገዳም ከመድሃኒአለም የተቀበልነው አደራ ነው፤ ስለዚህ የአደራ እቃ አይበላም፤እኛ ሳንሞት ወይም ሳንሰየፍ ይሄ ቦታ ለልማት ሊውል አይችልም። ሃጥያት አይሻገርብሽ እህል አይብቀልብሽ ብሎ ክርስቶስ በራሱ በቃሉ የተናገረበት፤ ከኢትዮጵያ ህዝብ ባሻገር የአለም ህዝብ የሚድንበት ቦታ ነው” ብለን መነኮሳቱ ተናገርን።
ቦታዎቹ በአራቱ አፍላጋት የተከበቡ ናቸው። በተከዜ፣በዛሬማ፣ በማይዞንና በኢንሲያ የተከበቡ ቦታዎች ናቸው። “ይህች የእኔ ጫንቃ ናት፤ ይህችን ቦታ የሚነካ፣ የሚያርስ ሰው እንደ አርዮስ እንደ ይሁዳ ነው” ብሎ ተናግሯል መድሃኒአለም እየሱስ ክርስቶስ። ስለዚህ እኛም ከእምነትም ከታሪክም አኳያ በህይወት እያለን ቦታው ለልማት አይውልም የሚል አቃም በመያዛችን ስብሰባው ተበተነ። ደን መመንጠር፣ የግድብ ስራ ጀመረ።
አፅመ ቅዱሳንን በግሬደር እየቆፈሩ እየወጡ ወደ ውሃው መስደድን ተያያዙት። በጊዜው ይሄ ነገር እንዴት ነው? በማለታችን ችግሮች ተፈጥረዋል። ገዳሙ ውስጥ ህወሃት የሚባል ድርጅት ያስቀመጣቸው መነኮሳት አሉ። ድሮ በሰለላ ይግቡ አይግቡ አላውቅም፤ አሁን ግን የሚሰሩት ለተባለው ድርጅት ነው። አናሳርስም ካሳም አንቀበልም ያለውን መነኮሳት ሰላዮቹ እየጠቆሙ በሚልሻ ሲያስደበድቡ ብዙ መነኮሳት ገዳሙን ትተው ወጥተዋል። በዚህ የተነሳ በጊዜው ወንድማችን አባገብረየሱስን በጣም በከፍተኛ ሁኔታ ያፈላልጓቸው ነበር።
በዚህ ችግር የተነሳ ግማሹ መነኮሰት ገዳሙን ለቆ ሲሄድ ግማሹ ደግሞ ፀሎት ያዘ፤ ያኔ መከላከያ መጥቶ ፀሎቱን አስቁሟል። ፀሎት እንዳይፀለይ፣ ምህላ እንዳይደረግ ከለከለ “በዚህ በዚህ ጉዳይ ላይ ፀሎት እየተደረገ ነው” እያሉ መረጃ የሚያቀብሉና መነኮሳት በወታደሮች እንዲደበደቡ የሚያደርጉት እነዛ የስርአቱ ሰላይ የሆኑት መነኮሳት ናቸው።
እነዚህ ሁለት ሰላዮች አባ ገብረህይወት መስፍንና አባ ሰላማ የተባሉ መነኩሴዎች ናቸው። እኛ አባቶቻችንን ያስተማሩን እኛም የምናስተምረው ስለ ሰላም፣ ስለፍቅር፣ ሰለአንድነት ነው፤ ሰው አብሮ እንዲበላ፣ እንዲፋቀር፣ ኢትዮጵያዊነት ትልቅ ዋጋ እንዳለው ነው የምንሰብከው። ይሄ የእኛ ብቻ ሳይሆን የቤተክርስትያንም አምነት ነው። ግን ያለው ሁኔታ ወደ ዘረኝነት ተገልብጧል። ከ2004 ዓ.ም ጀምሮ እስካሁን ድረስ በመከራ ነው ያለው።
ግዮን፡- እናንተ ከታሰራችሁ በኋላ እስካሁን ድረስ ያለው የዋልድባ ገዳም በምን ሁኔታ ላይ ነው ያለው መቼም እዛ ካሉ መነኮሳት ጋር በቂ የመረጃ ልውውጥ ታደርጋላችሁ ብለን ተስፋ እናደርጋለን?
አባ ገብረየሱስ፡- በነገራችን ላይ የህወሃትና የዋልድባ ገዳም ፀብ ከ1972 ዓ.ም ጀምሮ እስከ አሁን የዘለቀ ነው። በርግጥ በጊዜው እኔ የገዳሙ አባል ባልሆንም የቀደሙ አባቶች እንደነገሩኝና ሁሉም የአካባቢው ምዕመን እንደሚያውቀው፤ አሁን ሜይዴይ የሚል ትምህርት ቤት ያሰየሙበትን ቦታ አካባቢ “አባ ነፃ” አካባቢ ያለ፣ የዘሪማ ወንዝ (ሊገደብ የተፈለገው) አካባቢን በፊትም ይመኙት ነበር።
ህወሃቶች በትግል ላይ እያሉ በ1973 ዓ.ም “እኛን የሚረዳን አካል ስለሌለ አትከልት እየተከልን እንመገብ” በሚል ሰበብ ቦታውን እንወስዳለን በማለት ገዳሙን ያነጋግራሉ። ማህበረ መነኮሳቱ ደግሞ ይሄ ቅዱስ ቦታ ነው አንሰጣችሁም ይሏቸዋል። የሚገርማችሁ ያንን ቦታ ኢህአፓ የተባለው ድርጅት አስቀድሞ ፈለጎት ነበር። ቦታው እንደተባለው ለአትክልት ይመቻል፤ ግን ኢህአፓም አልተሳካለትም” በጊዜው እምቢ የተባሉት ህወሃቶች “ለአንድ ሳምንት ጊዜ ሰጥተናችኋል ቦታውን ስለምንፈልገው እንደወስደዋለን፤ አስተካክሉ” ብለው ሄዱ። የመነኮሳቱ ማህበር “እግዚአብሄር ያውቃል” የሚል መልስ ነው የሰጣቸው።
ታጋዮቹ ሲሄዱ መነኮሳቱ ለአንድ ሳምንት ሱባኤ ያዙ። በሰባተኛው ቀን “አዳባስ” በተባለው ቦታ ላይ ደርግ መጥቶ እዛ ቦታ ላይ የነበረውን የህወሃት ሰራዊት ጨፈጨፈው። በዛው እነሱም ከአካባቢው ጠፉ፣ነገሩም በረደ። ገዳሙን መንካት ሌላ ችግር እንደሚያመጣ የገባቸው ይመስለኛል።
በ1980 ዓ.ም በድጋሚ ህወሃቶች መጡና የገዳሙን ቦታ እንወስዳለን፣ መንገድም ጥርጊያ እንሰራለን በሚል እንቅስቃሴ ጀመሩ። ምልክቱ እስካሁን ድረስ አለ፤ በሰአቱ ያንን ነገር ሲያደርጉ ዘንዶና ነጭ እባብ ታጋዮችን እየገደለ ድራሻቸውን አጠፋቸው፤ አባይ ወልዱና አንዳንድ ሰዎች ከዛ የተረፉ ሰዎች ናቸው። በህወሃቶች በኩል ይሄን እንደቂም ይዘውት ኖረዋል። ያኔ ሊያለሙበት ይዘውት የመጡትን ዶማና አካፋ፣ መመንጠሪያ፣ ትልልቅ ጎላ ብረት ድስት ጥለው ሄደዋል።
እሱን እስከ አሁን ድረስ የአካባቢው ገበሬ እየተጠቀመበት ነው የሚገኘው። የዋልድባን ቅዱስ ቦታ መንካቱ ለህወሃት ሌላም ጣጣ አምጥቶበታል። ማርገፅ ጊዮርጊስ የሚባል ቦታ ላይ ጎድጓዳ ዋሻ ውስጥ ተቀምጠው ከነበሩት ታጋዮች ውስጥ በግንቦት ወር ላይ ከዚህ መጣ ያልተባለ ድንገተኛ ጎርፍ የተወሰኑትን ከእነ ሙሉ እቃቸው ጥርግርግ አድርጎ ይዟቸው ጠፍቷል። ይሄንን ህወሃቶች ጠንቅቀው ያውቁታል። ዛሬ ግድብ እንገድባለን፣ ልማት እናካሂዳለን እያሉ ያሉት ያንን ቂም ለመወጣት ነው፤ ከዚህ ሌላ የዋልድባ ገዳም ሰፊ ነው ወርቅ አለ፣ የከበረ ማዕድን አለ፣ ጥጥ፣ ሰሊጥ ማምረት የሚያስችል ቦታ ነው፤ እነሱ ያንን በብቸኝነትይዘው ማልማት ይፈልጋሉ። ግድቡ ሰበብ ነው። በተጨማሪ ሽፍቶች መጥተው ይገባሉ የሚል ፍራቻ ስላላቸው ገዳሙን ማጥፋት ይፈልጋሉ። ከምንም በላይ ደግሞ “ገዳሙ ኢትጵያዊነት የሚንፀባረቅበት ቦታ ነው፤ ህብረ ብሄር ነው፤ ከየትኛውም ቦታ የመጣ ሰው ይገባል፤ ኢትዮጵያዊነትን ለማጥፋት መጀመሪያ ደግሞ የዋልድባን ገዳም ማጥፋት አለብን” የሚል ነው የስርአቱ አላማ። በገዳሙ ስለ አገር ፍቅር፣ ስለኢትዮጵያ ፍቅር፣ ሰለምና አንድነት በደንብ አንፀን ነው የምንሸኘው፤ ይሄ ነገር ለስርአቱ አይመችም። አማራን ለማጥፋት የግድ ቤተክርስቲያንን ማጥፋት ያስፈልጋል ብለው ስለሚያምኑ መጀመሪያ ዋልድባን ማጥቃት ጀመሩ ማለት ነው።
ስለዚህ የዋልድባና የህወሃት ችግር አርባ አመት ሆኖታል ማለት ነው። 40 አመት ሙሉ የተያዘ ቂም ነው፤ አሁን አዲስ የሚመስለው ችግሩ ፈጦ ስለወጣና ከህዝቡ ዘንድ ስለደረሰ ነው፤ አሁንም ይሄ ጉዳይ አልተፈታም አለማለሁ በሚል ሰበብ ይህ ቅዱስ ቦታ እየታረሰ፣ አፅመ ቅዱሳን ከአፈር ጋር ወደ ወንዝ እየተጣሉ ነው፤ ይሄ ይቁም ነው እኛ የምንለው።
ግዮን፡- በጊዜው እርስዎ ዋናው የመነኩሴዎቹ አመፅ አስተባባሪ ኖት ተብለው ሲፈለጉና ክትትል ሲደረግብዎት ቆይተው፤ ከአንድ አመት በፊት ነበር የተያዙት እንዴትና በእነማን ነበር የተያዙት?
አባ ገብረየሱስ፡- በወቅቱ እኔ የማህበረ መነኮሳቱ አደራና ውክልና ስለነበረብኝ በአቋሜ ገፋሁበት ፤በመጨረሻም ስብሰባ ላይ ከመንግስት ሃላፊዎች ጋር ስንነጋገር “ይሄ ቦታ የታረስ ብለን አንወስንም ብትገሉም ስጋችንን፣ ብትገርፉም ስጋችንን ነው፤ ግን ምንም አይነት ለውጥ አይኖርም፤ ይኸው ሜዳው ይኸው ፈረሱ” በሚል ነው የተለያየነው። ያኔ ያሳመፀውና መነኮሳቱ አይሆንም እንዲሉ ያደረገብን እሱ ነው፤ ደጀ ሰላም ለሚባለው ድረገፅ፣ለቪኦኤ፣ ለፍትህ ጋዜጣና ለሌሎች አካሎች መረጃ እያሰራጩ ነው በሚል እኔን ማሳደድ ጀመሩ። በወቅቱ እኔን ፈልጎ ለያዘ ሁሉ ውለታ እንደሚከፍሉ ተናገሩ፤ መንገዶች ሁሉ ተዘጉ። መኪናዎች ሁሉ ይፈተሹ ነበር። የተያዝነው 2009 ዓ.ም ታህሳስ 28 ቀን ነው። በግንቦት 7 አባልነት ተጠርጥራችኋል በሚል ነው፤ ሲይዙን የፍርድ ቤት ወረቀት አላሳዩንም፤ ቁጭ ባልንበት ነው የከበቡን፣ እንደ ደረሱ አንድ ቃል ሳያወሩ ዱላ ነው የጀመሩት። ወደ 40 የሚጠጉ ወታደሮች ናቸው፤ ከባድ መሳሪያ በመኪና ላይ ጭነው በታጠቀ ሰራዊት ነው የወረሩን።
*ፍፁም ርህራሄ በጎደለው ሁኔታ ያለማቋረጥ ከባድ ድብደባ ፈፀሙብን፤ እኔም ራሴን ሳትኩ እንደ ሬሳ ጭነው አምጥተው ነው ማዕከላዊ ወንጀል ምራመር ያስገቡኝ። ብዙ ጎድተውኛል፣ የሚገርማችሁ ነገር ሂዱ አትሄዱም የሚል ጥያቄና መልስ እንኳ የለም። የህወሃት ወታደሮች ናቸው እንደደረሱ ያለማቋረጥ ደበደቡን። ደህንነቶቹ ዩ.ኤን የሚል ታርጋ የለጠፈች መኪና ውስጥ ቁጭ ብለው ነበር፤ በተለይ አንደኛው የደህንነት አባል በጣም መቶኛል፤ የተወሰኑት ራቅ ብለው ይመለከታሉ።
ቆቤን አውልቀው ወረወሩት፤ በቪዲየ ይቀርፁኝ ነበር። ራቁቴን አድርገው ቀርፀውኛል፤ ሌላ የቅንብር ነገር መስራት ፈልገው ነበር መሰለኝ፤ ግን ይሄን ሁሉ የሚያደርጉት እየደበደቡኝ ነው፤ መጨረሻ ላይ ራሴን ስቼ ስወድቅ መኪና ውስጥ ከተው ወደ ማዕከላዊ አመጡኝ።
ግዮን፡- አባ ገብረስላሴም ያኔ በቦታው አብረው ሆነው የተያዙት፤ እንዴት ነበር የአያያዝ ሁኔታው?
አባ ገብረስላሴ፡- ከባድ መሳሪያዎች የጫኑ ከ40 ያላነሱ ወታደሮች ናቸው መጥተው የያዙኝ። ደብድበውኛል በጣም አሰቃይተውኛል። የሰው ልጅ ላይ ሊፈፀም በማይገባ መልኩ “የት ነው ያለሁበት ቦታ” ስል ማዕከላዊ መሆኑ በሰው ነው የተነገረኝ እንጂ እንዴት ወደ አዲስ አበባ እንዳመጡኝ እንኳ አላውቅም፤ በዱላ ብዛት ራሴን ስቼ ነበር። ማዕከላዊ ከመጣን በኋላም ቢሆን ተመሳሳይና የከፋ ነገር ነው የገጠመን። ከምሽቱ ሁለት ሰአት ሲሆን እኔንም አባንም ያወጡንና ሌሊቱን ሙሉ እየገረፉ አሳድረውን ሊነጋጋ ሲል ይመልሱናል።
ግዮን፡- ሲገርፏችሁ ምን ነበር የሚሏችሁ?
አባ ገብረስላሴ፡- ከአርበኞች ግንቦት ሰባት ጋር ትገናኛላችሁ፣ ከትልልቅ ባለስልጣናት ከአነ አቶ ገዱ አንዳርጋቸው ጋር ትገናኛላችሁ፤ እያሉ ነው በየቀኑ ለወራት ያለማቋረጥ ማታ ማታ እየጠሩ የሚገርፉን፤ የሚደበድቡን። ስቃይና መከራው ከባድ ነው፤ አሁን ሰውነቴን ገልጨ አላሳያችሁም እንጂ ሰውነቴ ሸቶ ሰው ለመቅረብ ይሳቀቅ ነበር ለምፁ አሁንም ገላዬ ላይ አለ። መንታ አለንጋ አለ፣ የኤሌክትሪክ ሽቦ አለ፤ በእዛ ነው ያለ ርህራሔ ራቁታችንን አድርገው የሚገርፉን።
የ21ኛው ክፍለ ዘመን ፋሽስቶች ናቸው። በእንዲህ ያለ ሁኔታ የተሰቃየነው እኛ ብቻ አይደለንም። ብዙ የኦሮሞና የአማራ ተወላጆች በማዕከላዊ ከባድ ግርፋትና ድብደባ ተፈፅሞባቸዋል። ዘሬ እየተጠቀሰ “አንተ አህያ” እየተባልኩ ነው የሚገርፉኝ፤ ያቺ ሰአት የጣዕረ ሞትና የስቃይ ሰአት ናት። ከህዝብ ጋር ዳግም እንገናኛለን፣ ከእናንተም ጋር ቁጭ ብዬ እንዲህ አወራለሁ ብዬ አላሰብኩም ነበር። ግን እውነተኛው አምላክ ይሄን አድርጓል፡ እኔንም አባንም “እነዚህ መነኩሴ አይደሉም” እያሉ እየተቀባበሉ ነው የሚቀጠቅጡን። ህክምና ቤት አዝለው ሲወስዱን እዛ ያሉትም ሰዎች ተመሳሳይ የህወሃት ሰዎች ናቸው “ለምን ትደበደባላችሁ፤ ለምን የምታውቁትን አትናገሩም” ነው የሚሉን፤ ከሚሉት ነገር ጋር ፈፅሞ ግንኙነት እንደሌለን ብንናገርም አያምኑንም፤ ማዕከላዊ ውስጥ ያሉት የህወሃት ሰዎች ከእነሱ ውጭ የሆነውን አማራውን፣ ኦሮሞውን ሰበብ እየፈለጉ ለማጥፋት የተነሱ ናቸው። የእኛ ጥያቄ በግልፅ ይታወቃል፤ያሰረን ሕወሐት ቢሆንም እንደ እግዚአብሔር ፍቃድ የተፈታነው በህዝብ ግፊትና መሰዋዕትነት ነው።
በጣም በሚያስነውር መልኩ ብዙ ግፍ በሁለታችን ላይ ተፈፅሞብናል። ራቁታችንን ምንም ልብስ ሳንለብስ ሐፍረተ ስጋችን እየታየ ሁሉ ነው የገረፉን። ዋልድባ ቅዱስ ቦታ ነው፤ ህዝበ ክርስትያኑ የሚድንበት የእምነት ቦታ እንዴትና ለምን ይታረሳል በማለታችን ብቻ።
ግዮን፡- ፍርድ ቤት የቀረባችሁት ከስንት ጊዜ በኋላ ነው? ማዕከላዊስ ምን ያህል ጊዜ ታሰራችሁ?
አባ ገብረየሱስ፡- በማዕከላዊ አምስት ወር በእስርና በስቃይ ቆይተናል። እንደ ተያዝን በአራተኛው ቀን ጊዜ ቀጠሮ ፍርድ ቤት አቀረቡን። ዳኛው 28 ቀን ሰጠ፣ ድብደባው የተጠናከረው ከዛ በኋላ ነው። በዛ መልኩ ዝም ብለን በቀጠሮ እየተመላለስን አምስት ወር ከ13 ቀን ሳይቤሪያና ሸራተን በሚባሉት ማሰሪያ ቦታዎች ነው የቆየነው። ለተወሰኑ ጊዜ ምርመራ የጨረሱ እስረኞች ወደ ሚታሰሩበት መልሰውን ነበር።እንደገና ደግሞ ከዛ አውጥተው መልሰው ጨለማ ቤት አሰሩን። ከፍርድ ቤት ቀጠሮ ውጪ ብዙ ቀናት እዛው ማዕከላዊ እስር ቤት እንድንቀመጥ ተደርገናል።
ሰኔ 13 ቀን 2009 ዓም በመደበኛ ፍርድ ቤት ክስ ተመስርቶብን በ14 ወደ ሊንጦ እንድንወርድ ተደረገ። ቂሊንጦ ዞን ሶስት አስገብተው አሰሩን። መጀመሪያ እዛው እንዳለን መረጃ (ሰላይ) ላኩብን።እሱ ከእኛ ጋር መተኛት ጀመረ። ሰውዬው ሙስሊም ነው፤ እኛ ሰውዬውን ባናውቀውም የሚያውቁት ሰዎች ሲናገሩ ሸዋሮቢት፣ ዝዋይ እየተዘዋወረ የሚሰልል ነው። ይህ ሰው መሪጌታ ጌትዬ መኮንን ተብሎ ወደእኛ መጣ፤ በኋላ ሰላይ እንደሆነ አወቅን፤ ለነገሩ ራሱም ይናገራል። ሁለት ወር አካባቢ አንድ ላይ ከታሰርን በኋላ አባ ገብረስላሴን ስድስተኛ ቤት እኔን ሰባተኛ ቤት አስገቡን።
ተለያይተን ከታሰርን በኋላ ታራሚውን እያሳመፁ ነው፣ ምክር እየሰጡ የአርበኞች ግንቦት ሰባት አላማን እየሰበኩ ነው በሚል ፊታቸውን ወደእኛ አዞሩ። እኔን ወደ ዞን ሁለት አባን ደግሞ ወደ ዞን አምስት ወሰዷቸው። እሳቸውን እዛ ወስደው ክፉኛ ደበደቧቸው፤ እኔ ዞን ሁለት ስደርስ የስኳር ፕሮጀክቱን ዲዛይን የሰራው ኪሮስ የተባለና አታክልቲ የተባለው መሃንዲሶች በሙስና ታስረው እዛ አገኘኋቸው። “ገዳማችንን ልታጠፉ፣ ልታወድሙ ነበር፤ ነገር ግን ይኸው እኛም እናንተም አብረን ነው ያለነው” በሚል ትንሽ ውዝግብ ተፈጠረ። በጊዜው ችግር ፈጣሪ የነበሩት ሰዎች እነሱ ስለነበሩና ስለምንተዋወቅ ነው የተናገርኩት። በዚህ ምክንያት እኛ ደስ ስላልናቸው ፖሊሶችም የእነሱ ደጋፊ ስለሆኑ መልሰው ዞን አምስት አስገቡኝ፤ ሁለት ወር ከ19 ቀን እዞ ቦታ ነው የቆየሁት።
ግዮን፡- አባ ገብረስላሴ እርስዎ ቂሊንጦ በጣም እንደ ተሰቃዩ ፣ከባድ ድብደባ እንደተፈፀመብዎ ነው የሰማነውና እስኪ ድርጊቱን ቢያስታውሱን?
አባ ገብረ ሰላሴ፡- በማዕከላዊ ታስሬ በነበርኩበት ብዙ ከተሰቃየሁ በመሃል ከዛ አውጥተው አዲስ አበባ ፖሊስ ይዘውኝ ሄደው ነበር፤ አዲስ አበባ ፖሊስ ቆብህንና ልብስህን ካላወለቅክ አትገባም አሉኝ። “ይሄ ልብስ አባቶች ያለበሱኝ፣መከራ ቢመጣም ልቀበልበት፣ ሞት ቢመጣም ልቀበልበት እንጂ ሐይማኖት ማለት ስንፈልግ የምናወልቀው ስንፈልግ የምንለብሰው አይደለም” የሚል መልስ ሰጠኋቸው “ጳጳሱም ቢሆን ፓትሪያሪኩም ቢመጣ አውልቆ ነው የሚገባው፤ ስለ እዚህ እናንተ የታዘዛችሁትን ፈፅሙ” በሚል ወታደሮቹ ረጅም ሰአት አውልቅ በሚል ሲደበድቡኝ አብረውኝ ወደ ፖሊስ ጣብያው የሄዱ ወደ 40 የሚጠጉ ታሳሪዎች “ለምን እንዲህ ታደርጋላችሁ” ብለው ሲያምፁና ጥያቄ ሲያቀርቡ ወደ ማዕከላዊ መለሱኝ።
እዛ እንደ ደረስኩ ኮማንደር መብራህቱና ኮማንደር ሐዱሽ የሚባሉ ተቀብለው ጨለማ ቤት አስገብተው ዘግናኝ በሆነ ሁኔታ ሲደበድቡኝ አምሽተው ወደ አባ ገብረየሰሱስ መለሱኝ። እሳቸውንም ምርመራ አለብዎት ብለው ወስደው ሲያሰቃይዋቸው ውለው ከመለሷቸው በኋላ እየታሹ ነው ያገኘኋቸው። ወደ ቂሊንጦ ስንወርድ የገጠመን አንድ አይነት ነው፤እዛም ፈላጭ ቆራጮቹ የህወሃት ሰዎች ናቸው። ኦህዴድ ይሁን ደኢህዴን ወይም ብአዴን ቅፅል ነው እንጂ ምንም ስልጣን የላቸውም፤ አድራጊ ፈጣሪዎቹ ህወሃቶች ናቸው። ዘረኝነት ላይ የተመረኮዘ ጥቃት የሚፈፅሙት፣ ሰው የሚደበድቡትና የሚያሰቃዩት እነሱ ናቸው። በጣም በሚያስገርም ሁኔታ ሰው የሚደበድበው፣ አካሉ የሚጎድለውና ቂሊንጦ ነው። ዞን አራት፣ ዞን አምስት የተባለ ጨለማ ቤት ውስጥ የሚፈፀመው በደል ከባድ ነው።
እኛ ገና ቂሊንጦ ስንደርስ “ግሞ የመነኩሴ አሸባሪ “እያሉ እየሰደቡ፣ እያንጓጠጡ ነው ያስገቡን። ለሁለት ወር ያህል እንግዳ መቀበያ የሚባል ክፍል ነው ያስቀመጡን። ሌሎች እስረኞች ክፍል አንገባም፤ አምስት ስድስት ሰው ነው በደንብ የሚከታተለን። ከዛ በኋላ “ስብከት እየሰበካችሁ ነው፣ አድማ እያሳደማችሁ” ነው በሚል ወንድሜ አባ ገብረየሱስን ወደ ዞን ሁለት ወሰዷቸው፤ “ለምን ትወስዷቸዋላችሁ? እናንተ እኮ አስቀምጡ ነው የተባላችሁት እንጂ ለምን ሰው ታሰቃያለችሁ” ብዬ ጥያቄ ሳቀርብ እኔን ወደ ዞን አምስት ወሰዱኝ።
ህዳር 27 ቀን 2010 ዓ.ም ቀጠሮ አለህ በሚል አወጡኝ፤ ተፈሪ የሚባል ፖሊስ ነው እስረኛ የሚለብሰውን ዩኒፎርም በእጁ ይዞ “ልብስህን አውልቅና ይሄን ልበስ” አለኝ በጊዜው ከእሱ ሌላ አራት ዱላ የያዙ ወታደሮች ቆመዋል፤ የሚያናግረኝ በስርአጽ እንኳ ሳይሆን መሬት ለመሬት እየጎተተ ነበር፤ “ካላወለቅክ እንገልሃለን ብለውኛል” ገብረ እግዚአብሄር የሚባል የደህንነት ሃላፊ ቆሞ ነው ይሄን ሁሉ የሚያዘው፤ እምቢ ስላቸው መሬት ለመሬት እየጎተቱ፣ እየደበደቡ ተጫወቱብኝ።
ያቺ ቀን የማትረሳ የህይወት ቀኔ ናት። የጭንቀት፣ የሃዘንና የመከራ ቀኔ፤ ልቤን ሁሉ ተመትቼ ለብዙ ቀን ሲያስለኝና ደም ሲያስተፋኝ የቆየሁበት። የመነኩሴ ልብስህን አውልቅ ብለው ነው ለማመን በሚከብድ ሁኔታ ሰውን ማሰቃየት ምን የሚሉት ነው? በጊዜው የነበረውን ሁኔታ ብዙ ሰው ተመልክቶ ስለ ነበር ዞን፤ ሁለት ውስጥ ያሉ ወደ ሶስት የሚሆኑ የእነሱ አባል የሆኑ ሰዎች ሁሉ “ለምን በሐይማኖታችን ትገባላችሁ?” የሚል ጥያቄ አንስተው ነበር።
በሰአቱ እጄ በካቴና ቢታሰርም መስቀል ይዤ ነበር። ሲያስደበድበኝ የነበረው ገብረእግዚአብሄር የሚባለው የደህንነቱ ሰው “ማነው መስቀሉን የሰጠህ?” አለኝ፤ እኔም “መስቀሉን የሰጠኝ ታላቁ ንጉስ ኢየሱስ ክርስቶስ ነው” ስለው ከቦታው ተነስቶ ሄደ። ከጠዋቱ አንድ ሰአት ተኩል እስከ ረፋዱ አራት ሰአት ድረስ “ልብስህን አውልቀህ የታሳሪዎች ዩኒፎርም ልበስ፣ አለበለዚያ ትሞታለህ እንጂ አንተውህም” እያሉ መሬት ለመሬት እየጎተቱ ያለማቋረጥ ሲደበድቡኝ ሲያሰቃዩኝ ነው ያረፈዱት። በዚህ የተነሳ ሰላሳ ሁለት ቀን በጨለማ ቤት ካሰሩኝ በኋላ ወደ ሌላ ዞን አስገቡኝ፤ አባ ገብረየሱስን ደግሞ ወደ ዞን አምስት ወሰዷቸው።
እዛም በቀን አምስትና ስድስት ጊዜ እየጠሩ ያስፈራሩን፣ ይዝቱብን ነበር። “መጀመሪያ ጥይቷ የምትተኮሰው እናንተ ላይ ነው” እያሉ ያስፈራሩን ነበር፤ ምንድነው የምትፈልጉት ስንላቸው መልስ አይሰጡንም፤ ስለዋልድባ ስናነሳ ነው ፊታቸው የሚለዋወጠው፤ ስለ ገዳማችን ካነሳን አንድ ነገር ሳይፈጠር እኛም ሳንሰቃይ ያደርንበት ጊዜ የለም። ቂሊንጦ በዚህ መልክ ነው እስከ መጨረሻው ድረስ የቆየነው።
ግዮን፡- ለወራት ለሰው ልጅ ከሚሸከመው በላይ የሆነ ከባድ በደል ሲፈፀምባችሁ ፍርድ ቤት ብቻ ነበር የመናገር እድል ያገኛችሁት፤ እዛ የነበረው አካሄድ በራሱ ህዝበ ክርስትያኑን ያሳዘነ ነበር፤ በዚህ ዙሪያ የነበራችሁ ስሜት ምን ነበር?
አባ ገብረየሱስ፡- በአሁን ሰአት ያለው ፍርድ ቤት የዳኝነት፣የአቃቤ ህግና የጠበቃ ሙያ በተቢው መንገድ የሚታይበት ቦታ አይደለም። እኛ ፍርድ ቤት ሲባል እውነት የሚፈረድበት፣ ንፁህ ሰው ነፃነቱ የሚረጋገጥበት ትልቅ ቦታ ነበር የሚመስለን፤ ግን አይደለም። በእኛ ጉዳይ እንዳየነው ስልክ ተደውሎ እንዲህ አድርግ እንዲህ በል እየተባለ ዳኛ የሚታዘዝበት ቦታ ነው። በራሱ አዕምሮ የሚሰራ ዳኛ አላየንም ፤እውነቱ ፈጦ እያለ የምንባለው ግን ሌላ ነው… እኔ አሁን ስያዝ ምንም አልተገኘብኝም፣ በኋላም እንደዛው። ግን ማዕከላዊ የእኔ ያልሆነ ነገር አቀረበ… ተው የእኔ አይደለም ብዬው ነበር። ለምሳሌ ሞባይል፤ የሌላ ሰው ሞባይል የእኔ አድርገው የማዕከላዊ ሰዎች አቅርበዋል። የእኔ አይደለም የእኔ ከሆነ ባለሙያዎች ስላሉ በእነሱ ይመርመር ብያለሁ። እኔም ሆንኩ አባታችን ዳዊትና ድርሳነ ሚካኤል ይዘን ነው የተገኘነው።
እኛ እየተከራከርን ያለነው በዋልድባ ጉዳይ ነው።አሁንም ወደፊትም ይሄንን አቋማችንን እንገፋበታለን። አባገብረየሱስም ሆነ አባ ገብረ ሰላሴ የምንከራከረው ገዳሙ እየታረሰ ነው፣ ቅርሶች እየተዘረፉ ነው በሚል ነው፤ ይሄን መግለፅ አስካለብን ድረስ እንናገራለን። መቼም ወደኋላ አንልም፤ እኛ እንዴት አሸባሪ ሰው ገዳይ እንባላለን?..ማንን ለማዳን ነው ሰው የምንገድለው? ብለን ለፍርድ ቤት ስንናገር “አይ ይሄንን በፅሁፍ አቅርቡ፤ ቀጠሮ እዚህ ቀን ሰጥተናል” የሚል መልስ ካልሆነ በቀር አቃቢ ህግን ለምን እንዲህ አደረግክ? ለዚህ በትክክል ማስረጃ አለህ ወይ? ብለው ዳኞች አይጠይቁም።
ብዙ ጊዜ ሰምታችሁት ይሆናል የሃሰት ምስክር የሚባለውን ነገር፤ የሃሰት ምስክር ፋብሪካው ማዕከላዊ ነው፤ አራት ጓደኞች አስሮ ሁለቱን ምስክር አድርጎ ያቀርባል። በእኛ ላይ አልመሰከሩም እንጂ እኛ የማናውቃቸው ግን ከእኛ ክስ ያሉ ሰዎች፤ ማዕከላዊ በፅሁፍ ይሄ እገሌ ላይ የምትመሰክሩት ይሄ ደግሞ እገሌ ላይ እየተባሉ ስልጠና እየተሰጣቸው ተቀምጠዋል። እኛ ደግሞ የምትሉት አሸባሪ አይደለንም። እንዴት አብረውን እስር ቤት የነበሩ ሰዎች ምስክር ይሆናሉ ብለናል።
በቂሊንጦ ካየነው መሃል በእሳት ቃጠሎው የተነሳ ሟች ብለው “እሱ እንዲህ አድርጎ፣ይሄን ሰርቶ” በሚል አግዝፈው ከሰውታል። ግን ሞተ የተባለው ሰውዬ በህይወት አለ፤ አይገለፅ ስለተባለ እንጂ። ሌላው 18ኛ ወንጀል ችሎት በሙስና ጉዳይ ሁለት ፋይሎች አሉ፤ በሁለቱ የተለያዩ ነገሮች ፈጠው ቁልጭ ብለው ታይተዋል። አብረው የታሰሩ ሰዎች ከመሃል የተወሰኑትን አወጡና በሚፈልጉት ሌሎች ታሳሪዎች ላይ ምስክር መሆን ይችላሉ በሚል እንዲመሰክሩ ተፈቀደ። እነ አብዮት ተስፋዬ፣ አበበብርሃኔ የሚባሉ በሙስና የተያዙ ግለሰቦች ናቸው። በሌላ በኩል እነ ጌታቸው የሚባሉ ተከሳሾች ላይ ከእነሱ ጋር አብረው ከታሰሩት መሃል የተወሰኑት ምስክር አድርገው መረጡ። እንዴት እነዚህ ሊመሰክሩብን ይችላሉ በሚል አቃቤ ህጉን ሲሞግቱ እነዛው ዳኞች “አብረው የታሰሩ ሰዎች ሊመሰክሩ አይችሉም” ሲሉ በየኑ። አያችሁ ሁለት ዳኝነት፤ በአንድ ጉዳይ። የፍትህ ስርአቱ ችግር አለበት። እኛም ስንገላታና ስንሰቃይ የነበረው በፍትህ እጦት ነው።
በተለይ ዘርአይ ወልደሰንበት የሚባል ዳኛ አለ፤ ይሄ ሰው የህወሃት ሰው ነው። በተለያዩ ድረ ገፆች ሲፅፍ፣ ስርአቱን ሲያሞካሽ የነበረ ነው። ወደ አቃቤ ህግነት ቦታ ሲመጣ የአፋር ብሄር ነኝ በሚል የመጣ ነው፤ ከአቃቤ ህግ አልፎ ወደ ዳኝነት ገባ። አቃቤ ህግ ከሆነ በኋላ ጠበቃ ሆነ፣ ከጥብቅና ተመልሶ ወደ ፍርድ ቤት ገባና ዳኛ ሆነ። ሆን ተብሎ ጎንደርን ለማጥቃትና ለመምታት ስለተፈለገ የእኛ ጉዳይ የሚታይበት ችሎት ላይ ተቀመጠ።
እኛ፣ የወልቃይት ኮሚቴ፣ የባህር ዳር ታሳሪዎች በአጠቃላይ በአማራ ክልል ያለን አብዛኛው ሰዎች በ4ኛ ወንጀል ችሎት ነው ጉዳያችን እንዲታይ የተደረገው። ሌላው በኦሮምያ ያለውና ጠንካራ የተባለው የእነ በቀለ ገርባ ፋይልም እንዲሁ። ይሄንን ጉዳይ ማየት ያለበት የእነሱ ሰው ስለሆነና ሌላው እየሸረሸረ እንደሚፈልጉት ስላላደረጉላቸው ይሄ ሰውዬ በችሎቱ ላይ ዳኛ ሆኖ እንዲቀመጥ ተደረገ።
በፍርድ ሂደቱ የእኛም ሆነ የወልቃይት ተከሳሾች ማስረጃ ሊገኝብን ስላልቻለና ፍትሃዊ ዳኝነት መስጠት ስላልቻለ ወደእሰጣ ገባና ተራ ስድብ ተገባ። ሠላማዊ ሂደቱ ቀርቶ ባለበት ሁኔታ የ32 እስረኞች ክስ ተቋረጠ። እኛና አንድ ነጋ ዘላለም የሚባል ልጅ ቀረን። ክርክራችን እኛ አላቋረጥንም፤ በተለይ የምንኩስና ልብሳችንን እናቃጥለዋለን እንገላችኋለን እየተባልን ስለቆየን በተደጋጋሚ ለፍርድ ቤቱ አቤት ስንል፤ ያኔ ምን እንደታየው አናውቅም “የሃይማኖት ልብሳቸውን መልበስ እንዳይከለከሉ” የሚል ትዕዛዝ ሰጠ። ያ ትዕዛዝ ለእኛ አይደለም። ትዕዛዙ ለቤተክርስትያን ነው፤ እንደዛ በመወኑ እኛ ደስ ብሎናል፤ ግን ሰጠም አልሰጠም እኛ አላወለቅንም፤ አናወልቅም። በህይወት እያለን እንደማይሆን እነሱም ያወቁታል፤ ይሄ የእምነት ጉዳይ ነውና እኛ ብናወልቀው ውርደቱ ከራሳችን አልፎ ለቤተክርስትያን ነው፤ ነገር ግን በአቋማችን ፀንተን መቆየታችን ለቤተ ክርስትያንም ለህዝበ ክርስትያኑም የሚያኮራ ፍርድ ተሰጥቷል ፤በዚህ የተከበረችው ቤተክርስትያን ናት፡
ግዮን፡- አባ ገብረስላሴ የሚጨምሩት አለ?
አባ ገብረስላሴ፡- ፍርድ ቤት ዳኛ ማለት ከህዝብም፣ ከመንግስትም ሳይሆን በገለልተኝነት ከእውነት ፊት መቆም ያለበት ነው ብዬ አምናለሁ። ከፖለቲካው ነፃ መሆን አለበት። ነገር ግን እኛ ያየነው ፈፅሞ የተለየ ነው፤ በሽብር ስም ሆን ተብሎ አማራና ኦሮሞን እንዲበቀሉ የተቀመጡ ሰዎች አሉ፤ አንዱ አቶ ዘርአይ ወ/ሰንበት ነው። በነገራችን ላይ ኢትዮጵያ ውስጥ ሽብር የለም። በዚህች አገር ላይ እያሸበሩ፣ እየደበደቡና እያሰቃዩ ያሉት እነሱ ናቸው። ሌላ አይደለም፤ ይሄ ዳኛ በወልቃይት ጉዳይ 4 ገፅ ዝርዝር የያዘ ክስ ቀርቦበታል።
“አማራ አህያ፤ ምን ታረጋላችሁ?” እያለ ሁሌ ይሳደበል። ስለዚህ “አንተ ዘረኛ ነህ፣ ዳኝነት ማለት ከፖለቲካ የፀዳ ነው፣ አንተ ግን ህወሃት ነህ፣ ልትዳኘን አትችልም” ብለን ስናቀርብ እየተሳደበና እያንጓጠጠ እስካሁን ድረሰ አለ። የሚገርማችሁ አቃቤ ህግ የእከሌ የእከሌ ክሳቸው ተቋርጧል በሚልበት ቀን አይመጣም፤ ችሎት ላይ አይገኝም። በነገራችን ላይ እኛ አሁን ለእናንተ የምንገልፀው ያየነውንና ያገጠመንን የሰዎችን ድርጊት እንጂ የምንሰብከው የምንኖረውም ስለፍቅርና አንድነት ነው። ሁሉንም የሰው ልጅ በፍቅርና በአክብሮት ነው የምናየው፤ ወደፊትም ከዚሀ ሃሳብ አንወጣም። ግን እንደ ህወሃት አስከፊ ድርጊት የሚፈፅሙትን ሰዎች እንጠላለን ስራቸው አሰቃቂ ነው፤ ከድሮ ጀምሮ ቂም ያለባቸው ነው የሚመስሉት።
ፍርድ ቤት ላይ ወሳኙ ከኋላ ነው ያለው እንጂ ዳኞች ለህሊናቸው ብለው የሚፈርዱበት፣ የሚወስኑት ነገር የላቸውም። አድርጉ የተባሉትን ነው የሚያደርጉት። ዳኛ የለም፤ ፍትህ የለም፤ በአሁን ሰአት ኢትዮጵያዊ መሆን በራሱ በጣም አስቸጋሪ ነው። በቂሊንጦና በቃሊቲ ያሉ እስረኞች አብዛኛዎቹ አሁንም ፍትህ አላገኙም። ኑ እየተባሉ እየተጠሩ እየተደበደቡ፣ እየተሰቃዩ ያሉ በርካታ ናቸው። ከአንድ አመት እስከ አምስት አመት ድረስ ምንም ወንጀል የሌለባቸው፤ ግን በፍትህ እጦትና በፈላጊያቸው አካል ያለ በቂ ምክንያት እንዲቀመጡ የተደረጉ አሉ።
ግዮን፡- በቅርቡ ዶ/ር አብይ አህመድ ጠ/ ሚኒሰቴር ሆነው ተመርጠዋል፤ከተፈታችሁ በኋላ እሳቸውን ለማነጋገር አላሰባችሁም?… ለእዚህና ሌሎች ጥያቄዎች መነኮሳቱ የሰጡትን ምላሽ በቀጣይ ዕትም ይዘን እንቀርባለን።