
በነዚህ የማያቋርጡ የመስራት እና የመታሰር ሂደት ውስጥ አብረን የነበርነው እስክንድር ነጋ ወደ አሜሪካ ሲመጣ፤ እኔም ከአትላንታ ተነስቼ ወደ ዋሺንግተን ዲሲ በረራ አደረኩ… እስክንድርን ይዞ የሚመጣው አውሮፕላን የአሜሪካን ምድር እስክሚነካ ድረስ በሃሳብ ወደ ኋላ መመለስ የግድ ነው… እናም ልጅነታችንን፣ ወጣትነታችንን የወሰደውን የነጻ-ፕሬስ ትግል በትዝታ እያሰብኩ፤ ይሄንን ማስታወሻ ጻፍኩ።
አገር ለቅቄ ከመውጣቴ ጥቂት አመታት ቀደም ብሎ ከእስክንድር ጋር በተከታታይ የምንገናኝበት አጋጣሚዎች ተፈጠሩ። ፒያሳ እና አራት ኪሎ ሁልግዜም፤ በፖሊስ እና በደህንነት ቀለበት ውስጥ ናት። በአንጻሩ ደቡብ አዲስ አበባ ደግሞ ሰላማዊ ቀጣና በመሆኗ፤ የቄራ ሰፈርን ዝምታ ወደደው። ያን ሰሞን ፖሊስ እና ደህንነት እስክንድርን ለመያዝ አሰሳ ሲያደርጉ፤ እኛ ከአንዱ የሰፈራችን ሆቴል ውስጥ ስለአገራችን የወደፊት እጣ ፈንታ እያወራን ነበር። ጨዋታችን እየደራ ሲመጣ፤ የአገራችንን ጉዳይ ጨርሰን፤ ስለራሳችን የወደፊት እጣ ፈንታ መወያየት ጀመርን።
“ከዚህ በኋላ ከያዙኝ በቀጥታ ይገድሉኛል!” እየሳቀ ነው ይሄን የሚለኝ – እስክንድር።
የሚሰጠኝን መልስ እያወኩትም ቢሆን፤ ደጋግሜ መጠየቅ የምወደውን ጥያቄ እጠይቀዋለሁ። “እንደሚገድሉህ በምን አወክ?” እለዋለሁ።
“ይሄንን ትጠራጠራለህ እንዴ?” ይልና ለመጨረሻ ግዜ በማዕከላዊ እስር ቤት ያጋጠመውን ድብደባ ያስታውሰናል። በጣም የሚገመው ያንን ድብደባ በምሬት ሳይሆን፤ እየሳቀ ነው የሚያጫውተን።
“ይገርማል እኮ። ማዕከላዊ ውስጥ ቁጥር ሰባት ላይ ያለውን እስር ቤት ታውቀው የለ? እዚያ አንዲት ብርድ ልብስ ሰጥተውኝ አገር ሰላም ብዬ ተኝቼ እያለሁ፤ የእስር ቤቱ በር ሲከፈትና ቀዝቃዛ ንፋስ ወደክፍሉ ውስጥ ሲገባ በእንቅልፍ ልቤ ይሰማኛል። ከዚያ እንደስሙኒ ዳቦ በተኛሁበት ብርድ-ልብስ ጥቅልል አድርገው ይዘውኝ ወጡ። በደንብ የነቃሁት በብርድ ልብሱ ውስጥ የወጣው እግሬን ሃይለኛ ብርድ ሲመታው ነው። እኔ ደሞ አልጋ ውስጥ ያለሁ መስሎኝ…” እያለና ሁኔታውን እያስታወሰ፤ መናገር እስከሚያቅተው ድረስ ደጋግሞ ይስቃል። ባለቤቱ ሰርካለም… ጨዋታውም ሳቁም እያሳቃት፤ በቁጠባ የምትስቀውን ሳቅ ታመጣውና እስክንድርን በሳቅ ታጅበዋለች። እኔም ከብርድ ልብሱ ወጥተው የተንጠለጠሉ እግሮቹን፤ ብርድ ሲመታቸው ከእንቅልፉ መባነኑን እያሰብኩ ፈገግ ማለቴ አልቀረም።
እየሳቀ ጨዋታውን ይቀጥላል… “ከዚያ በኋላ አንድ ክፍል ውስጥ አስገብተው ደበደቡኝ። ብዙ እግሮችና ብዙ መዳፎች በላዬ ላይ ያረፉ ይመስለኛል። እንዴት እንደሚያዩኝ አላውቅም… በጨለማ ውስጥ ሆዴን፣ ፊቴን የተገኘው ቦታ ላይ ሁሉ ነው የሚመቱኝ።” እስክንድር ይሄን ሁሉ ታሪክ እየሳቀ ይነግረንና የመጨረሻውን ድርጊታቸውን ሲነግረን ግን ትክዝ ይላል። የሚጽፍበት… ቀኝ እጁን ለመስበር ያደረጉትን ትግል ሲያስበው ሳቁ ሁሉ ይጠፋል። ግራ እጁን ያነሳና ቀኝ እጁን ደገፍ ያደርገዋል። እጁን ከጥቅም ውጪ ለማድረግ የደረሰበትን ድብደባ ተርኮ ሲጨርስ፤ እናም ከዚህ በኋላ እንደገና እዚያ እስር ቤት ከተወሰደ፤ ሞት እንጂ ምንም እንደማይጠብቀው በርግጠኝነት ያወራናል።
እኔ ቡናዬን፣ እስክንድር የሚወደውን ሻይ ፉት እያለ፤ ሰርካለም የሁለታችንን ጨዋታ በጣፋጭ ሚሪንዳ እያወራረደች በሰከነ መንፈስ እያዳመጠች፤ ምንም ሆነ ምን ግን እስክንድር የሚያቀርበውን ሃሳብ በአብላጫ ድምጽ በመደገፍ ጨዋታችን ይቀጥላል። እንዲህ የአገራችንን ነገር አውርተን አውርተን መፍትሄ ስናጣለት… “እንግዲያው አንድ ነገር ማድረግ አለብን!” እለዋለሁ፤ በእጃችን ላይ ያሉትን አማራጮች በመደርደር። “አንደኛው አማራጭ ያለውን እስር እና አፈና ተቋቁመን መቀጠል ይኖርብናል፤ ወይም ደግሞ ይህን አገር ለቀን መውጣት አለብን፤ ወይም ደግሞ የሚታገሉ ወጣቶችን ተቀላቅለን ጠመንጃ ማንሳት አለብን።” እለውና እንኳንስ መተኮስ የጠመንጃውን ክብደት እያሰብኩ፤ አጭር ትንታኔ ስሰጥ፤ እስክንድር በጥሞና ይሰማና መፍትሄው የዲሞክራሲ መስፈን መሆኑን ደጋግሞ ይገልጽልኛል።
“መፍትሄው ዲሞክራሲያዊ ስርአት እንዲፈጠር ማድረግ ነው።” ይልና ፖለቲካዊ ትንታኔ ያክልበታል።
እነዚያን አድካሚ እና ደስ የሚሉ ቀናት በዚህ አይነት እናሳልፍና፤ ቅዳሜና እሁድ ሲመጣ እንለያያለን። እነሱም ፒያሳና አራት ኪሎን መናፈቃቸው አልቀረም። ይህ የልቦና መሻት ግን እስክንድርን ሌላ ዋጋ ሊያስከፍለው ሆነ። በመታሰርና ባለመታሰር ቆይተው፤ እስክንድር እንደገና የሚታሰርበት ቀን ደረሰ።
ነገሩ ካለፈ በኋላ… እስክንድር እና ሰርካለም እንደተለመደው ያለፈውን ነገር እየሳቁ አጫወቱኝ።
ፖሊስ እና ደህንነት ያልነበረበት የኛ ሰፈር ጭር ያለ ነው። በቃ ይሄ የኛ ሰፈር ጸጥታ ሰለቻቸው። ዝምታው ሊበላቸው ሲደርስ…
“ፒያሳ አልናፈቀሽም?” ማለቱ አልቀረም።
“ኧረ ናፍቆኛል”
“እንሂዳ”
“እሺ እንሂድ!” ይባባላሉ በድፍረት። እናም ይሄን ተባብለው ሲያበቁ፤ ሰላማዊ ሰፈራችንን ለቀው ወደ ፒያሳ አቀኑ። በመንገዳቸው ላይ በወቅቱ ተወዳጅ ስለነበረው የአካፑልኮ ተከታታይ ፊልም እያወሩ፤ አሁን የት ሄደው እንደሚያዩት እየተነጋገሩ፤ ፖሊስ እና ደህንነቶች እንዳያዩዋቸው ተጠንቅቀው… በማዘጋጃ ቤቱ የግንብ አጥር ጥላ ጥላውን… ወደ ጊዮርጊስ ለመሄድ አቀበቱን እንደጀመሩ፤ ከፊት ለፊታቸው ሲቪል የለበሱ ሁለት ሰዎች፤ ወደነሱ አቅጣጫ ሲመጡ አዩዋቸው። እነዚያ ሁለት ሰዎች የማዕከላዊ ፖሊስ ጣቢያ አሳሪዎች… ፀሃዬ እና ተወልደ የሚባሉ የህወሃት አባላት ናቸው። “የፈሩት ይደርሳል” ሆነ ነገሩ።
ሰርካለም ቶሎ ብላ በለበሰችው አንገል-ልብስ ፊቷን በከፊል ሸፈነች። እስክንድር ፊቱ መሸፈን ባይችልም፤ ግንባሩን አኮሳትሮ መልኩን ቀየረ ወይም ለመቀየር ሞከረ። ሁለቱ የህወሃት ደህንነቶች፤ እንደአመጣጣቸው እስክንድር እና ሰርካለምን አልፈዋቸው ሄዱ። በሰርካለም እና በእስክንድር ፊት ላይ የደስታ ስሜት ተነበበ። ሆኖም 2 እና 3 እርምጃ ከተለያዩ በኋላ፤ ከደህንነቶቹ አንደኛው፤ “እስክንድር!” ብሎ ተጣራ።
ጥሪውን ሰምተው ዝም ብለው ቢሄዱ ጥሩ ነበር። እስክንድር ግን ማስመሰልን አያውቅበትም። “እስክድር!” ብሎ ፀዬ ሲጠራው፤ ድንገት ዞር አለ። ወዲያውኑ ተወልደ የሚባለው እጁን ወደ ሽጉጡ ሲሰድ ጸሃዬ ደግሞ፤ እጁን ወደ ስልኩ ላከ።
“አንተን አልበር እንዴ ስፈልግክ የነበረው” አለና… ወደ ማዕከላዊ ደወለ። በስልክ የተጠራው የማዕከላዊ ፖሊስ መኪና ሲክለፈለፍ መጣ። ከኋላ ክፍት የሆነ ፒክ አፕ መኪና እነሱ ጋር ሲደርስ ቆመ። ይሄን ግዜ ሰርካለም “እንዲህማ ዝም ብላቹህ አትወስዱትም!” ብላ አሻፈረኝ አለች።
“እንዲታሰር ተብሎ፤ እሱን ስንፈልገው ነበር” አላት ጸሃዬ። ተወልደ የሚባለው ፊቱ የማይፈታው ደህንነት ግን፤ ለሹፌር ትዕዛዝ እየሰጠው ነው።
ሰርካለም በቀላሉ የምትረታ አልሆነችም። “የት እንደምትወስዱት ስለማላውቅ፤ ከዚህ ቦታ ንቅንቅ አንልም!” በማለት እስክንድርን ጭምቅ አድርጋ ያዘችው።
“የት እንደምንወስደው ማየት ከፈለግሽ አብረሽው መምጣት ችያለሽ!” አላትና… በፒክ-አፕ መኪና ላይ ተጭነው ወደ ማዕከላዊ ፖሊስ ጣቢያ ተወሰዱ። እዚያም ዋናው በር ላይ ሲደርሱ፤ “ይኸው እዚህ ነው ይዘነው የመጣነው! አሁን መሄድ ትችያለሽ!” አሏት።
እስክንድር ዞር አለና ሰርኪን ያበረታታት ጀመር። “አይዞሽ ምንም አልሆንም! እፈታለሁ!” አላት። እንዲህ እያላት ወደማዕከላዊ ግቢ ገባ። ሰርኪ ብቻዋን ውጪ ቀረች። ከዚህ በኋላ ሁኔታውን ለሌሎች ጋዜጠኞች ማሳወቅ ያስፈልጋል። ጠበቃ እና ዋስ ማዘጋጀትም ሌላ ሃላፊነት ነው። መደረግ የሚገባው ነገር በሙሉ ተደረገ።
እንዲህ እንደዋዛ ያወራሁትን የእስር ታሪክ በምሬት ሳይሆን በሳቅ አጅበውት፤ እስክንድር እና ሰርካለም ሲያጫውቱኝ ሁሌም ከልቤ እስቅ ነበር። ይሄም አለፈና ሌላ ቀን ተተካ።
እኔ ከአገር ቤት ከወጣሁ በኋላ፤ የነጻው ፕሬስ አዲስ ምዕራፍ ላይ ደረሰ። በተለይም የ1997 ምርጫ እና የነጻው ፕሬስ ሚና ፈጽሞ የሚለያዩ አልነበሩም። በዚያን ግዜ እስክንድር እና ሰርካለም እንደአሳታሚም፣ እንደጋዜጠኛም ብዙ መቶ ሺህ ጋዜጦችን ያትሙ ጀመር። ከምኒልክ መጽሄት ጀምሮ አስኳል እስከሚባለው ጋዜጣ ድረስ፤ እያንዳንዱ ህትመታቸው በኢትዮጵያ የፕሬስ ታሪክ ውስጥ ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ በመቶ ሺዎች ኮፒ ይታተም ጀመር።
እንግዲህ በምርጫው ሰሞን የነበረውን ግርግር እዚህ ላይ አምጥተን ማስታወስ የለብንም። ነገር ግን ከዚያ ግርግር ጋር በተያያዘ እስክንድር እና ሰርካለም፤ ከብዙ የነጻው ፕሬስ ጋዜጠኞች እና የፖለቲካ ድርጅት መሪዎች ጋር ለእስር ተዳረጉ። ሰርካለም በእስር ላይ እያለች ከብዙ ወራት በኋላ ነው እርጉዝ መሆኗን ያወቀችው። እናም በእስር ቤት ሳለች፤ ወንድ ልጅ ተገላገለች፤ ስሙም “ናፍቆት” ተባለ።
ከሁለት አመታት በኋላ ጋዜጠኞች እና የፖለቲካ ድርጅት መሪዎች ከእስር ሲፈቱ ደስ አለን። ሆኖም ነጻው-ፕሬስ ዳግም እንዳያንሰራራ ተደርጎ ተመታ። ብዙዎች የፕሬስ ፈቃዳቸውን ተነጠቁ። የተቀሩትም በማተሚያ ቤቶች ተጽዕኖ ዳግም የህትመት ውጤቶች እንዳይታዩ፤ ገዢው መንግስት ያላሰለሰ የአፈና ስራውን ቀጠለበት። ይህ የፕሬስ አፈና ግን ሌላ መንገድ ከፈተ። ጋዜጠኞች በማህበራዊ ገጾች አማካኝነት ሃሳባቸውን በአንድ ለሊት ለብዙ ሺዎች ለማዳረስ ቻሉ። ይህ ሁኔታ ህወሃትን አስደገጠው፤ በጽሁፍ መችን ማሸነፍ አቅቶት፤ ኢህአዴግን ፍርሃት አብረከረከው። እናም የፕሬስ አዋጁንም በመተው፤ ጋዜጠኞች ሃሳባቸውን በመግለጻቸውና የህዝብን ድምጽ በምናሰማታቸው “አሸባሪ” ተብሎ እስከ 18 አመት የሚያስፈርድ አዲስ ህግ አወጡ።
ይህ ህግ ተግባራዊ ከመሆኑ በፊት እስክንድር ወላጅ አባቱን አጣ። አቶ ነጋ የኢትዮጵያ ህግ ባለሙያዎች ፕሬዘዳንት ሆነው አገራቸውን አገልግለዋል። ወላጅ እናቱ ድሮ ከነፕሮፌሰር አስራት ወልደየስ ጋር ቤሩት ሄደው የነርሲንግ ህክምና ያጠኑ፤ ከመጀመሪያዎቹ ዘመናዊ ሃኪሞች አንዷ ነበሩ። ወ/ሮ በላይነሽ የዛሬ ሰባት አመት አረፉ። … እስክንድርን ብቻ ሳይሆን ሌሎች ጋዜጠኞችን ጭምር ያበረታቱን የነበሩት እናቱ ወ/ሮ በላይነሽ፤ ፍርድ ቤት ቀርበው በነእስክንድር ላይ የፖለቲካ ውሳኔ ሲሰጥ፤ “በህግ አምላክ!” እያሉ፤ ዳኞቹ በሚገባቸው መልክ አንገታቸው ድረስ በድፍረት የሚናገሩ ናቸው።
እስክንድር ሲታሰር… ከአራት ኪሎ ተነስተው ወደ ፒያሳ ሲመጡ መጀመሪያ የሚያገኙት የኔን ቢሮ ስለሆነ፤ የመታሰሩን መርዶ መጀመሪያ ለኔ ነው የሚነግሩኝ። ከዚያም ጠንከር አድርገው፤ “እስክንድር ወንድም የለውም። ወንድሞቹ እናንተ ናቹህ። ዝም እንዳትሉ!” ይሉናል።
በ’ርግጥም አንድ ጋዜጠኛ ሲታሰር ሌላኛው ዝም ብሎ አያውቅም። በመንግስት ደረጃ በአንድ ግዜ ሊታፈን የማይችል፤ የጎሬላ ፕሬስ የሚሉት አይነት የትግል ስልት ይዘን፤ አንዱ ሲታሰር ሌላው እየተተካ፤ አንዱ ህትመት ሲዘጋ ሌላ እየተከፈተ… እራሳችንን በማያቋርጥ ፍልሚያ ውስጥ ከተትነው። ብዙዎቻችን ከአገር ከወጣን በኋላ፤ ለፕሬስ ነጻነት የሚደረገው የትግል መንፈስ ደስ የሚያሰኘንን ያህል፤ የሚከፈለው መስዋዕትነት ግን ከእጥፍ በላይ መበርታቱን ስናይ፤ በእሳት ውስጥ ለተፈተኑት እስክንድር ነጋ እና ሌሎች ጋዜጠኞቻችን ልባችን መሰበሩ አልቀረም… አክብሮታችን ግን ዛሬም ድረስ እንዳለ ነው።
ወጋችንን እናጠቃለው። እስክንድር ነጋ ለመጨረሻ ግዜ “አሸባሪ” ተብሎ ከመታሰሩ በፊት፤ ለሚወዳቸው እናቱ ጸሎት እና ተስካር ሊያደርግላቸው እየተዘጋጀ ነበር። ይህ በህግ ሽፋን የፖለቲካ ውሳኔ የተሰጠበት ችሎት፤ የእስክንድር እና የሰርካለም ንብረቶችን እንዲወረስ ያደረገ ነው። መኪናቸው፣ ባለ አንድ ፎቅ ቤታቸው፤ የቢሮ ውስጥ ንብረታቸው፣ አንድሺህ ካሬ ሜትር ካርታ ያለው የእናቱ መሬት… እነዚህ ሁሉ እንዲወረሱ ትዕዛዝ ሲሰጥ፤ እስክንድር ነጋ በፍርድ ቤት እንዲህ አለ። “አንድ ቀን ፍትህ በኢትዮጵያ ውስጥ ሲረጋገጥ፤ ልጄ ናፍቆት እስክንድር… ነገ አድጎ የቤተሰቡን ንብረት ያስመልሳል።” ነበር ያላቸው።
አስራ ስምንት አመት በተፈረደበት እለት፤ ባለቤቱ ሰርካለም ፋሲል በስፍራው ነበረች። በፍርድ ቤቱ ውሳኔ መሰረት፤ እስክንድር በጦር መሳሪያ ታጅቦ ወደ ወህኒ ሲወሰድ፤ ሰርካለም ድምጿን ከፍ አድርጋ፤ “እስክንድር ጀግና ነህ! አስራ ስምንት አመት ቁጥር ነው። እስክንድር እጠብቅሃለሁ! እስክንድር አንተ ጀግና ነህ!” ነበር ያለችው።
ሁሉም ነገር አለፈ።ሰርካለም እና እስክንድር ከአምነስቲ ኢንተርናሽናል በተጨማሪ የበርካታ ፕሬስ ማህበራትን ቀዳሚ ሽልማት አግኝተዋል። በኢትዮጵያ የሚደርስባቸው ወከባ ግን የሚያቆም አልሆነም። በመሆኑም ከአመታት በፊት ሰርካለም እና ናፍቆት ወደ አሜሪካ መጥተው፤ ኑሯቸውን በቨርጂንያ አደረጉ። በአገራችን በመጣው ለውጥ ምክንያት እስክንድር እና ሌሎች የህሊና እስረኞች ከእስር ሲፈቱ፤ እስክንድር ነጋም ከቃሊቲ እስር ቤት ተፈታ። አሁን ደግሞ ከ27 አመታት በፊት፤ ተማሪ ሆኖ ወደኖረባት ዋሺንግተን ሜትሮ ዳግም ሊመለስ ነው። እያንዳንዷ ደቂቃ እውነት የማይመስለውን እውነት ይዛልን በመምጣት ላይ ናት። የወንድም ያህል አብረን ያደግን ጓደኝናዬ እስክንድር ነጋን ከ18 አመታት በኋላ ዳግም ላየው ነው። ከምንም በላይ ግን ሰርካለም እና ናፍቆት ይህን ጀግና ይናፍቁታል። በውጭ አገር የሚገኙ ኢትዮጵያውያንም እስክንድር ነጋን ሊያገኙት ይፈልጋሉ።
እስክንድር ነጋ እና ሌሎች የነጻ-ፕሬስ ጋዜጠኞች ሃሳብን በነጻነት ስለመግለጽ መብት ያደረጉት ትግል፤ በታሪካችን ውስጥ ትልቅ ስፍራ ይሰጠዋል። በሞት ከተለዩን ጋዜጠኞች በቀር… እስክንድር ነጋ ጥቁር ጥላ ባጠላበት ነጻነት ውስጥ፤ እየወደቀና እየተነሳ እዚህ ደርሷል። ይህ የጨለማ ውስጥ ጉዞ እስከሚያበቃ ድረስ፤ በኢትዮጵያ ውስጥ ሃሳብን በነጻነት የመግለጽ መብት መከበሩ እስከሚረጋገጥ ድረስ፤ ስለፕሬስ ነጻነት የሚደረገው ትግል መቆሚያ ያለው አይመስልም። የኢትዮጵያ አምላክ ለታላቁ እስክንድር ብርታትን ይስጥልን።
እስክንድር ነጋ ይዞ የሚመጣው አውሮፕላን ወደ አሜሪካ እየተጓዘ ነው። እኛም እስክንድር ነጋን በናፍቆት ከናፍቆት ጋር እየጠበቅነው ነው። “በአሜሪካ የምትገኙ ኢትዮጵያውያን፤ እናንተ ለእውነት እና ለፍትህ የቆማቹህ፤ እናንተ ለወገናቹህ ድምጽ ሆናቹህ የጮሃችሁለት ሁሉ፤ እንኳን ደስ አላቹህ! ጀግናቹህ መጥቷል እና በደስታ እና በእልልታ ተቀበሉት!”