6 May 2018

ብሩክ አብዱ

በደቡብ ክልል በካፋ ዞን ጊምቦ ወረዳ ጎጀብ አካባቢ ሐሙስ ሚያዚያ 24 ቀን 2010 .. በተቀሰቀሰ ግጭት፣ መጠኑ ከፍተኛ የሆነ በርካታ ንብረት መውደሙን የሪፖርተር ምንጮች አስታወቁ፡፡

የግጭቱ መነሻ የሆነው ጉዳይ በጎጀብ አካባቢ የሚኖሩ ወጣቶች፣ የጎጀብ እርሻ ልማት ይዞታ ተከፋፍሎ ይሰጠን በማለት ለጠየቁት ጥያቄ ምላሽ ሳይገኝ በመቆየቱ እንደሆነ ለማወቅ ተችሏል፡፡ ይሁን እንጂ በእርሻ ልማቱ ላይ ያለው ሰብልና ሌሎች ተንቀሳቃሽ ንብረቶችን ለማንሳት ጊዜ ይወስዳል በመባላቸው፣ በእርሻ ልማቱ ላይ ጥቃት መፈጸማቸው ታውቋል፡፡

በዚህም የተነሳ የእርሻ ልማቱ በእሳት ከመቃጠሉም በላይ ሦስት እህል የያዙ መጋዘኖች፣ ሦስት ትራክተሮች፣ አንድ ኮምባይነር፣ ወፍጮ ቤትና የእርሻ ልማቱ ሰነዶች ሙሉ በሙሉ መውደማቸው ተጠቁሟል፡፡

ሚያዚያ 24 ቀን 2010 .. ከንጋቱ 1200 ሰዓት ጀምሮ እስከ ቀኑ 1000 ሰዓት ድረስ ከጅማ ወደ ካፋ ዞን የሚወስደው መንገድ ተዘግቶ የነበረ ሲሆን፣ በፀጥታ ኃይሎች ጣልቃ ገብነት መንገዱ ሊከፈት እንደቻለም ታውቋል፡፡

ተቃውሞ ሲያሰሙ ከነበሩ ወጣቶች አንዱ በጥይት ተመትቶ እንደቆሰለም ለማወቅ ተችሏል፡፡

በግጭቱ ተሳታፊ ናቸው የተባሉ ከ50 በላይ ግለሰቦችም በቁጥጥር ሥር መዋላቸው ተሰምቷል፡፡

በመጋዘኖቹ ውስጥ የነበሩ ሌሎች ንብረቶችም መውደማቸውና መጥፋታቸውም ታውቋል፡፡

በቅርቡ የመከላከያ ሚኒስትር በመሆን የተሾሙትና የኮማንድ ፖስቱ ሴክሬታርያት ዋና ጸሐፊ አቶ ሞቱማ መቃሳ፣ ስላጋጠመው ግጭት መረጃ ስለሌላቸው ማብራሪያ መስጠት እንደማይችሉ ሪፖርተር ላቀረበላቸው ጥያቄ ምላሽ ሰጥተዋል፡፡