6 May 2018

ውድነህ ዘነበ

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አቶ ድሪባ ኩማ በ40/60 ቤቶች ፕሮግራም እየተገነቡ የሚገኙ 17‚737 ቤቶች በሚቀጥለው ሰኔ 30 ቀን 2010 .. እንደሚጠናቀቁ ቢገልጹም፣ ዋጋቸው እየናረ ለሚገኘው የግንባታ ማጠናቀቂያ ዕቃዎች ዋጋ በጀት ባለመኖሩ ዕቅዱ የሚሠራ አለመሆኑን ምንጮች ገለጹ፡፡

ከንቲባ ድሪባ ከሳምንት በፊት ለከተማው ምክር ቤት ባቀረቡት የ2010 .. የዘጠኝ ወራት ሥራ አፈጻጸም ሪፖርት፣ በ40/60 ፕሮግራም ከሚገነቡት 38‚240 ቤቶች ውስጥ 17‚737 ቤቶች በበጀት ዓመቱ መጨረሻ ሙሉ ለሙሉ እንደሚጠናቀቁ ገልጸው ነበር፡፡

ነገር ግን ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የቁጠባ ቤቶች ልማት ኢንተርፕራይዝ የተገኘው መረጃ እንደሚያመለክተው፣ የተጠቀሱትን ቤቶች በበጀት ዓመቱ መጨረሻ ለማጠናቀቅ ዕቅድ ቢያዝም፣ ብር ከዶላር ጋር ያለው ምጣኔ በ15 በመቶ እንዲቀንስ ከተደረገ ወዲህ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየናረ የመጣው የግንባታ ማጠናቀቂያ ዕቃዎች ዋጋ ምክንያት ዕቅዱ ሊሳካ አይችልም፡፡

‹‹የበጀት ዓመቱ ሊጠናቀቅ የቀሩት ሁለት ወራት ያህል ነው፡፡ እነዚህን ቤቶች ለማጠናቀቅ በርካታ የሰው ኃይል ብናሰማራም፣ ለግንባታ ማጠናቀቂያ ዕቃዎች ዋጋ የሚውል በጀት ባለመኖሩ ዕቅዱ ይሳካል ብዬ አላምንም፤›› ሲሉ ስማቸውን መግለጽ ያልፈለጉ የኢንተርፕራይዙ የሥራ ኃላፊ ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡

የኤሌክትሪክ ዕቃዎች፣ ፓይፖችና የመሳሰሉት የግንባታ ማጠናቀቂያ ዕቃዎች ዋጋ መጨመር፣ ግንባታው በተስተጓጎለ ቁጥር የሥራ ማስኬጃ ወጪዎች መጨመራቸው ኢንተርፕራይዙን አቅም አሳጥተውታል ብለዋል፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በአሁኑ ወቅት በ20/80 ፕሮግራም 94‚114 ቤቶች፣ በ40/60 ቤቶች ደግሞ 38‚240 ቤቶች በአጠቃላይ 132‚354 ቤቶች እየገነባ ነው፡፡

በዘጠኝ ወራት የሥራ አፈጻጸም ሪፖርቱ 17‚737 የሚሆኑ የ40/60 ቤቶች የግንባታ አፈጻጸም 73 በመቶ የደረሰ መሆኑ ቢገለጽም፣ ለአስተዳደሩ ፈተና የሆነው ቀሪውን ለማጠናቀቅ የግንባታ ዕቃዎች ዋጋ ንረት ነው፡፡

2008 .. የተጀመሩት 20‚503 የሚሆኑ የ40/60 ቤቶች የግንባታ አፈጻጸም 50 በመቶ ላይ የሚገኝ መሆኑን፣ በበጀት ዓመቱ 80 በመቶ ለማድረስ ዕቅድ መያዙን ከንቲባው በሪፖርታቸው ገልጸዋል፡፡

ከዚህ በተጨማሪ በ20/80 ቤቶች ፕሮግራም በፓኬጅ ሁለት የሚገነቡት 52‚693 ቤቶች የግንባታ አማካይ አፈጻጸም 75.5 በመቶ እንደሆነ፣ በፓኬጅ ሦስት እየተገነቡ የሚገኙት 41‚421 ቤቶች አማካይ አፈጻጸም ደግሞ 52 በመቶ መድረሱን ከንቲባው ጠቁመዋል፡፡ በበጀት ዓመቱ ለሁለቱም ፕሮግራሞች 20 ቢሊዮን ብር መመደቡን መዘገባችን ይታወሳል፡፡

ሪፖርተር