May 6, 2018
- የምልአተ ጉባኤው ስብሰባ ነገ ይጠናቀቃል፤ ከቀትር በኋላ መግለጫ ይሰጣል
በዴር ኤል ሡልጣን ገዳም ካሉን ሁለት አብያተ መቅደስ መካከል፣ ጣሪያው ተነድሎ አገልግሎት ያቆመውን የቅዱስ ሚካኤል ቤተ መቅደስ እድሳት፣ ከጥቂት ሳምንታት በኋላ ለማከናወን የሚያስችል የተስፋ ቃል ከእስራኤሉ ፕሬዝዳንት ማግኘታቸውን ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ አቡነ ማትያስ ተናገሩ፡፡
ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ፣ በዚህ ሳምንት ኢትዮጵያን ከጎበኙት የእስራኤሉ ፕሬዝዳንት ጋራ፣ ረቡዕ ሚያዝያ 24 ቀን ቀትር ላይ በመንበረ ፓትርያርኩ አጭር ቆይታ ያደረጉ ሲኾን፣ ንጉሥ ሰሎሞን ለኢትዮጵያዊቷ ንግሥት ሳባ የሰጣት ዴር ኤል ሡልጣን ገዳም ቤተ መቅደስ እድሳት ጉዳይ የውይይቱ ዋነኛ ትኩረት እንደነበር ተገልጿል፡፡
በጣሪያው ላይ ከደረሰበት የመሸንቆር ጉዳት ጋራ በተያያዘ ላለፉት 8 ወራት ታሽጎና መተላለፊያው ተዘግቶ የቆየውን የቅዱስ ሚካኤል ቤተ መቅደስ ለማደስ የሚያስችል የተስፋ ቃል ከፕሬዝዳንቱ መስማታቸውን ለቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ የተናገሩት ቅዱስነታቸው፣ “ከጥቂት ሳምንታት በኋላ ማደስ ትችላላችሁ፤ የሚል ተስፋ ሰጥተውናል፤” ብለዋል፡፡ ከጉብኝታቸው መልስ ፈቃዳቸውን እንዳስታወቁን፣ እድሳቱን ለማከናወን ከገዳሙና ከሚመለከተው የመንግሥት አካል ጋራ የተቀናጀ እንቅስቃሴ እንደሚደረግ አስታውቀዋል፡፡
በምልአተ ጉባኤው አጀንዳ ተ.ቁ(9)፣ የኢየሩሳሌም ጉዳይ በሚል የተያዘ ቢኖርም፣ ከዚሁ የርእሰ መንበሩ ለስለስ ያለ አጭር ገለጻ በቀር በስፋት የተደረገ ውይይት አለመኖሩን የስብሰባው ምንጮች ጠቁመዋል፡፡ የኢየሩሳሌም ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ዕንባቆም በምልአተ ጉባኤው ላይ አለመገኘት፣ ከፕሬዝዳንቱ ጉብኝትና ከሰጡት የተስፋ ቃል ጋራ ተያይዞ ጉዳዩ በስፋት እንዳይነሣ ምክንያት ሳይኾን እንዳልቀረ ተገምቷል፡፡
እድሳቱ በራሳችን ወጪ የሚከናወንና ጉዳዩ በሚለዋወጠው የአካባቢው ፖሊቲካ የሚወሰን በመኾኑ ራሱን የቻለ አካል በአፋጣኝ ተዋቅሮ ተገቢው እንቅስቃሴ ሊደረግ እንደሚገባ አስተያየት ሰጭዎች አሳስበዋል፡፡
በሌላ በኩል፣ የጥድፊያ ስሜት ታይቶበታል የተባለውና ጊዜ ወስደው ሊያወያዩ የሚገቡ ዐበይት የቤተ ክርስቲያን ጉዳዮች በአግባቡ እንዳልተነሡበት የተተቸው የዘንድሮው የርክበ ካህናት ቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ፣ ካለፈው ረቡዕ ጀምሮ ሲያካሒድ የቆየውን መደበኛ ስብሰባ፣ ነገ ሰኞ፣ ሚያዝያ 29 ቀን 2010 ዓ.ም. ከቀትር በኋላ 9፡00 ላይ ለብዙኃን መገናኛ በሚሰጠው መግለጫ እንደሚያጠናቅቅ ታውቋል፡፡