
በአሁኑ ወቅት በአንድ ፓርቲ ተፅዕኖ ሥር እንደወደቀ በይፋ የታመነበትን የፌዴራልና የክልል የመንግሥታት ግንኙነት ከፓርቲና ከግለሰቦች ተፅዕኖ በማላቀቅ፣ ተቋማዊ መሠረትና ሕጋዊ ሥርዓት እንዲኖረው ለማድረግ የተረቀቀ የፖሊሲ ማዕቀፍ እንዲፀድቅ ለፓርላማ ተላከ፡፡
‹‹የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ የመንግሥታት ግንኙነት የፖሊሲ ማዕቀፍ›› የሚል መጠሪያ የተሰጠውን ይህንን የፖሊሲ ማዕቀፍ ያረቀቁት፣ የፌዴሬሽን ምክር ቤትና የፌዴራል አርብቶ አደርና ልማት ጉዳዮች ሚኒስቴር ናቸው፡፡ የፖሊሲ ማዕቀፉ ለሚኒስትሮች ምክር ቤት ቀርቦ ሰፊ ውይይት ከተደረገበት በኋላ እንዲፀድቅና ማስፈጸሚያ ሕግ እንዲወጣለት ተወስኗል፡፡
ይህ የፖሊሲ ማዕቀፍ ፀድቆ ማስፈጸሚያ ሕግ ሲወጣለት ተግባራዊ የሚደረገው በአገር አቀፍ ደረጃ በመሆኑ፣ ፌዴሬሽኑን የመሠረቱት ክልሎች ወይም ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች የተወከሉበት የፌዴሬሽን ምክር ቤት የፖሊሲ ማዕቀፉን በማፅደቅ ለሕግ አውጪው ፓርላማ እንዲመራው የሚኒስትሮች ምክር ቤት በወሰነው መሠረት፣ የፌዴሬሽን ምክር ቤት ሰኞ ሚያዝያ 22 ቀን 2010 ዓ.ም. ተወያይቶ ውሳኔውን አሳልፏል፡፡
ባለፈው ሳምንት መጀመርያ በጉዳዩ ላይ የወሰነው የፌዴሬሽን ምክር ቤት የፖሊሲ ማዕቀፉ ወቅታዊና አንገብጋቢ መሆኑን በማጤን ይሁንታውን የሰጠ ሲሆን፣ ፖሊሲው በፍጥነት ፀድቆና አዋጅ ተዘጋጅቶለት ወደ ሥራ እንዲገባ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መርቶታል፡፡
የፖሊሲ ማዕቀፉ በፌዴራልና በክልል መንግሥታት እንዲሁም በክልል መንግሥታት መካከል የሚደረግ የመንግሥታት ግንኙነት፣ በሕግና በተቋማዊ ሥርዓት እንዲመራ ለማድረግ የታለመ ነው፡፡
ኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ሥርዓት መንግሥት መሥርታ ተግባራዊ ማድረግ ከጀመረች ከሁለት አሥርት ዓመታት በላይ ብታስቆጥርም፣ እንደ ሌሎች ፌዴራላዊ ሥርዓት የሚከተሉ አገሮች የፌዴሬሽኑ አካል በሆኑ መንግሥታት መካከል ያለውን ግንኙነት ለመምራት የሚያስችል ዝርዝር የሕግ ድንጋጌ እስካሁን አለመኖሩ፣ የፖሊሲ ማዕቀፉን አስፈላጊ ያደረገው ምክንያት መሆኑ ተጠቅሷል፡፡
ሕገ መንግሥታዊ ዋስትና ያለው የሥልጣን ክፍፍል ተደርጎ የመንግሥታት ኃላፊነት በሕገ መንግሥቱ ዕውቅና ቢያገኝም፣ መንግሥታት የእርስ በርስ ግንኙነት ማድረግ የሚችሉበት ዝርዝር ሕግ በሕገ መንግሥቱ፣ እንዲሁም በሌሎች ሕጎች አለመቀመጡን ለፌዴሬሽን ምክር ቤት የቀረበው የፖሊሲ ማዕቀፉ ማፅደቂያ የውሳኔ ሐሳብ ያትታል፡፡
የክልሎችን የወሰን ለውጥ የተመለከተ ጥያቄ የተነሳ እንደሆነ በሚመለከታቸው ክልሎች ስምምነት እንደሚፈጸም፣ ክልሎቹ መስማማት ካልቻሉ የፌዴሬሽን ምክር ቤት የሕዝቦችን አሠፋፈርና ፍላጎት መሠረት በማድረግ እንደሚወስን የሚገልጸውን የሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 48፣ ለፌዴራል ወይም ለክልል መንግሥት ተለይተው ባልተሰጡ ታክስና ግብር የመጣል ሥልጣንን የሚመለከተውን አንቀጽ 99፣ እንዲሁም ክልሎችና የፌዴራሉ መንግሥት ታክስና ግብር በሚጥሉበት ወቅት ታክስና ግብሩ ከምንጩ ጋር የተያያዘና በአግባቡ ተጠንቶ የተወሰነና መልካም ግንኙነታቸውን የማይጎዳ መሆን እንዳለበት በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 100 ላይ የተደነገጉ መርሆዎችና ድንጋጌዎች የሚፈጸሙበት፣ የመንግሥታት ግንኙነት የሚመራበት ዝርዝር ሕግ እስካሁን አለመኖሩን የውሳኔ ሐሳቡ ለአብነት ያወሳል፡፡
የመንግሥታት ግንኙነት በሕግ እንዲመራ ሕገ መንግሥቱ በተጠቀሱትና በሌሎች አንቀጾች የሕግ መሠረት ቢጥልም፣ ላለፉት ዓመታት ተግባራዊ ሲደረግ የቆየው መደበኛ ከሆነው የግንኙነት አግባብ ይልቅ በገዥው ፓርቲ መስመር ላይ ተንጠልጥሎ እንደሆነ የውሳኔ ሐሳቡ ይገልጻል፡፡
በፓርቲ መስመር ሲደረግ የቆየው ግንኙነት በጋራ ጉዳዮች ላይ ለመወሰን የተቻለ ቢሆንም፣ የግንኙነት ሥርዓቱ በሕግ የተደገፈና ተቋማዊ እንዳይሆን ከማድረጉ በተጨማሪ፣ በዚህ መንገድ ለመቀጠል መሞከር የማይቻልና መጨረሻውም አገርን ሊበትን እንደሚችል ይጠቁማል፡፡
‹‹አሁን ባለንበት ሁኔታ በተለያዩ ደረጃ ያሉ የመንግሥት እርከኖችን የሚመሩት የፖለቲካ ፓርቲዎች ተመሳሳይ ወይም አጋር በመሆናቸው፣ የመንግሥታት ግንኙነቱ ቢሰምርም የአውራ ፓርቲ የበላይነት ቀስ በቀስ ሊቀየርና የተለያዩ ፓርቲዎች በተለያየ የሥልጣን እርከን የሚይዙበት ዕድል ቢፈጠር፣ የመንግሥታቱ ብሎም የፓርቲዎቹ ግንኙነት ሰላማዊና የሰመረ ላይሆን ይችላል፡፡ ይህ ደግሞ ለሥርዓቱ ህልውና እንቅፋት ሊሆን ይችላል፤›› በማለት የውሳኔ ሐሳቡ ያትታል፡፡
የሚኒስትሮች ምክር ቤት ያፀደቀውን የፖሊሲ ማዕቀፍ በፓርላማ እንዲፀድቅና አዋጅ ተዘጋጅቶለት ወደ ትግበራ እንዲገባ የፌዴሬሽን ምክር ቤትም ይሁንታውን ሰጥቶታል፡፡ ይህ የፖሊሲ ማዕቀፍ በመሠረታዊነት ሦስት ዓላማዎችን ዕውን ለማድረግ ያለመ ሲሆን፣ እነዚህም በፌዴራልና በክልል መንግሥታትና በክልል መንግሥታት መካከል የጋራ ጉዳዮችን በተመለከተ ተቋማዊ የምክክርና የትብብር ማዕቀፍ እንዲኖር ማድረግ፣ በተጠቀሱት መንግሥታት መካከል የሚከሰቱ አለመግባባቶችና ግጭቶች የሚፈቱበትን ተቋማዊ ሥርዓት መዘርጋትና ማጠናከር፣ እንዲሁም የግንኙነት ሥርዓቱን አፈጻጸም ለመከታተል የሚያስችሉ አደረጃጀቶችን፣ አሠራሮችንና መርሆዎችን መፍጠርና ማቋቋም ናቸው፡፡
ሕጋዊ ዕውቅና ኖሯቸው ከሚፈጠሩ የመንግሥታት ግንኙነት ተቋማዊ አደረጃጀቶችና አሠራሮች መካከል ዋና ዋናዎቹ አገር አቀፍ የሕግ አውጪዎች የጋራ መድረክ፣ አገር አቀፍ የሕግ አስፈጻሚዎች የጋራ መድረክ፣ አገር አቀፍ የዳኝነት አካላት ግንኙነት መድረክ ይገኙበታል፡፡
የመንግሥታት ግንኙነቱ ጠንካራና ቀጣይነት ያለው እንዲሆን ለማድረግም በአገር አቀፍ ደረጃ ግንኙነቱን የሚያስተባብር፣ ሙያዊና ቴክኒካዊ ሥራዎችን በመምራት ማዕከል ሆኖ የሚያገለግል ጽሕፈት ቤት በፌዴራልና በክልል መንግሥታት በጋራ እንዲቋቋም ማድረግ፣ ሌላው በፖሊሲ ማዕቀፉ የተካተተ አደረጃጀት ነው፡፡
የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በመጪዎቹ ጥቂት ሳምንታት የፖሊሲ ማዕቀፉን እንደሚመለከት፣ ከባለድርሻ አካላት ጋር ሰፋ ያለ ውይይት እንደሚያደርግ ለማወቅ ተችሏል፡፡