እስኪ በደንብ አስተውሉ፡፡ የኢትዮጵያ አገራችንን ፖለቲካ በደንብ አስቡበት፡፡ ማንም ከሜዳ እየመጣ ትልቅ የሚሆንበት ነው፡፡ በአገር ቤት እንኳን ሕዝቡ የተረዳው ይመስላል፡፡ በእርግጥ ችግር አለ፡፡ ዲያስፖራዎ ግን ለአገርና ሕዝብ አደገኛ ሆኖ ነው የሚታየኝ ለእኔ፡፡ የዲያስፖራውን ፖለቲካ እንደፈለጋቸው የሚዘውሩትና የንግድ ዕቃ ያደረጉት ድርጅቶችና ግለሰቦችን ሳስብ ለመሆኑ ምን ነክቶን ይሆን እላለሁ፡፡ ዛሬ ዲያስፖራውን እንደልባቸው የሚያንከባልሉት የፌስቡክ አክቲቪስት ተብዬዎችና በኢትዮጵያ ሕዝብ እምባና ደም ላይ ኑሮአቸውን የመሠረቱ ድርጅቶችና ሚዲያዎች ናቸው፡፡ እስከዛሬ ብዙ ስንለሳለስ ጭራሽ በቀጥታ የንግድ ዕቃቸው ነው ያደረጉን፡፡ አብዛኛው ሰው ግን ስለተደራጀ ሴራ አካሄድ ብዙ ስለማይገባው ይመስላል በወሬ ለሞሉት ነው የሚገዛው፡፡ በተግባርማ አይኑን ቀና ቢያደርግ እነዚህ በኢትዮጵያዊነትም ሆነ በተለያዩ ሕዝቦች ማንነት ላይ ተመስርተው እየተንቀሳቀሱ ያሉትን ሁሉ ምን ያህል ለኢትዮጵያና ሕዝቦቿ ጠላት ከሆነው የወያኔ ወሮበላ ቡድን ጋር በሕብረት እንደሚሰሩ ይታዘባል፡፡
ወያኔ በግልጽ የሚያስፈሯትን እናውቃቸዋለን፡፡ ከግለሰብ እስከድርጅት፡፡ እነዚህን ግለሰቦችም ይሁን ቡድኖች ወያኔ በቀጥታም በተዘዋዋሪም ለማጥፋት አለ የተባለ እድሏን ሁሉ ትጠቀማለች፡፡ እስኪ አስተውሉ እስክንድር ነጋን፣ ጫልቱ ጥላሁንን እና የመሳሰሉትን ግለሰቦች፡፡ እነዚህ ሰዎች በቃ ግለሰቦች ናቸው የፖለቲካ ድርጅትም የላቸውም፡፡ ግን ወያኔ ምን ያህል እንደተከታተለቻቸው፡፡ በተለይ እስክንድር ሥሙ አንዴ ስለታወቀና አለም ዓቀፉ ትኩረትን ስላገኘ እንጂ ወያኔ ልታጠፋው ከምትፈልገው ሰው አንዱ ነበር፡፡ ግን ለምን? እንደነ እስክንድር ያሉት እውነተኛ ጠላቶቿ እንደሆኑ ስለምውቅ፡፡ እነሱ ጠላት ሆነው ሳይሆን የወያኔ ወሮበሎነት ስለገባቸውና ሕዝብን እውነቱን ያሳውቁብኛል ብላ ስለምታምን ነው፡፡ በፖለቲካው ከመጡትም እነማንን እንዳጠመደች አስተውሉ አንዱአለም አራጌና አንዳንዶችን በተናጥል ከተቀላቀሉት የፖለቲካ ድርጅት እየለቀመች የማጥፋት ዘመቻ ስትሰራ ሙሉው ድርጅቱ አሰጊ የሆነባትን ደግሞ በሙሉ ሰብስባ ማጎሪያ የከተተችበትን ሂደትም አስተውሉ፡፡ ከፖለቲካ ድርጅቶቹ ጋር ችግር የለባትም ወያኔ፡፡ ዋናው ነገር የፖለቲካ ድርጅቱ የእሷን አላማ ማስፈጸሙ ላይ ነው፡፡ የአንዳንዶቹ የፖለቲካ ድርጅቶች አላማ ተቃዋሚ በመምሰል እውነተኛ ተቃዋሚ ግለሰቦችን በአማልነት በማሳተፍ ለወያኔ መረጃ የሚሆንን ማቀበል ነው፡፡ በእኔ እምነት የእነ ኢንጂነር ይልቃሉ ሰማያዊ ፓርቲ ለዚህ ጥሩ ምሳሌ ነው፡፡ ብዙዎች እነ ይልቃል እውነተኛ መስለዋቸው በተቃዋሚነት አብረው ሲሰለፉ አጅሬው እነሱን ለወያኔ ማጋለጥ እንደሆነ ሥራው የገባቸው አይመስልም፡፡ እንደነ አቶ በቀለ ገርባን የመሳሰሉትን ደግሞ ድርጅቱ ራሱ የምርም ተቃዋሚ ስለሆነ በጅምላ አመራሩን ማሰርና ማጥፋት ለወያኔ አማራጭ የሌለው እድሏ ነበር፡፡ ከአሰረችም በኋላ እንዴት ጥርስ እንደነከሰችባቸው በአይናችን ያየንው እውነት ነው፡፡ እነዚህና የመሳሱሉት ከእስር ለመለቀቅ ብቸኛ አማራጭ የነበረው የሕዝብ ጉልበት ብቻ ነበር፡፡ ፍትህ በፍጹም የማይታሰብ ነበር፡፡ እንግዲህ ብዙዎቹ የታወቁትና እድል የቀናቸው ከእነሱ ጋር ዛሬ ተለቀዋል፡፡ አሁንም ግን ብዙዎች መከራቸው በእስር ቤት እንደቀጠለ ነው፡፡ እነዚህ ናቸው በግልጽ ወያኔን የሚያስበረግጓት፡፡
በሌላ በኩል ወያኔ ተቃዋሚዎቿ ለማስመሰል በብዙ ግለሰቦችና ድርጅቶች የምትሰራው ድራማ ለብዙዎች አይገባቸውም፡፡ በተለይ ይች እስከ ሶስት ወር ባሉ ጊዜያት ውስጥ ታሰሩ ተብለው የሚፈቱትን ስናይ ድራማው ያስቃል፡፡ እነዚህ ግለሰቦች በአብዛኛው ክፉኛ ተቃዋሚ የሚመስሉ ናቸው፡፡ ብዙ ጊዜ ግን የሚያስተላልፉት መልዕክት ውስጥ እንድ ወያኔን የሚጠቅም ነገር ሰንቅረው ነው፡፡ ይህን የማይረዳ አዳሜ ግን እነሱን እየተከተለ እስከማምለክ የሚመስል ደጋፊያቸው ሆኖ ከዋናው ትግል ትኩረቱ እንዲጠፋ ይደረጋል፡፡ ልደቱ አያሌውን ብዙዎች በዚህ አይነት ድራማ ተሳታፊነቱ ይጠቅሱታል፡፡ ልደቱ ታዋቂ ስለሆነና የሆኑ ቦታዎችም ሲነገጫገጭ የተነቃበት ስለሆነ ይሆናል፡፡ ብዙዎች ፍጹም ሳይነቃባቸው የወያኔን አግልግሎታቸውን እንደቀጠሉ ነው፡፡
በውጭ ሆነው የወያኔን አላማ የሚያሳኩ ደግሞ አሸባሪ የሚል ሥም ተሰጥቷቸው በየጊዜው ሕዝብ እነሱን ከመከተል እንዳይዘናጋ ወያኔ የሆነ ወሬ ስለእነዚሁ ትለቃለች፡፡ በዚህ አንጻር በእኔ እይታ የአርበኞች ግንቦት 7 የተባለው ቡድን አንዱ ነው፡፡ ስለ ግንቦት7 የራሱን ቀንደኛ ደጋፊዎች ሳይቀር ለማናገርና ምን አልባት የእኔ እይታ ስህተት ከአለበት በሚል ከሌሎች መረጃ ለማግኘት ሞክሪያለሁ፡፡ ሁሉም ይደግፋል እንጂ እኔ ከማውቀው የተለየ ስለግንቦት 7 የሚያውቀው የለም፡፡ ኧረ ይሄ ቡድን ችግር ሳይኖርበት አይቀርም ከአልኩ የለበትም ብሎ የሚያስረዳኝ ሳይሆን የሚቆጣ ነው ሁሉም፡፡ መቼም አዚም ከአልሆነ አይናችን የሚያየውን እውነት መካድ አይቻልም፡፡ አብዛኛው ግን ግ7 በተግባር የት ጋር ነው ያለው የሚለውን መካድ ስለማይችል ይሄ ጥያቄ ሲነሳበት የሚሰጠው መልስ ወያኔ እንዲህ ቀን ከሌሊት አሸባሪ እያለ የሚወነጅለው ስለሚፈራው ነው ብሎ ነው የግ7ን ትክክለኛነት የሚደመድመው፡፡ ወያኔ ለምን አብዝታ ስለግንቦት7 ማውራት ፈለገች የሚለውን ብዙ ሰው ለማስተዋል ራሱ ፍላጎት ያለው አይመስልም፡፡ የቡድኑ አመራሮችም ይሄንኑ የወያኔን በየጊዜው ስለቡድኑ የምታወራውን ፕሮፓጋንዳ ለትክክለኛ ተቃዋሚነቱ እንደዋነኛ ምስክር አድርገው ነው የሚጠቅሱት፡፡ እንዲህ በአለ ድራማ ነው ብዙው ሕዝብ አእምሮው የሚሸወደው፡፡ ግ7 ወያኔን ምን ያህል እየጠቀማት እንደሆነ ማስተዋል እንዳይመጣ በወያኔም በቡድኑም ከፍጠኛ ጥንቃቄ ነው የሚደረግ የሚመስለው፡፡ ግ7 ወያኔን በሁለት በኩል እየጠቀማት ነው፡፡ አንደኛ አገር ቤት እየታገላት ያለውን ሕዝብ በግ7 ሥም አሸባሪ እያለች ለማፈን፡፡ ሁለተኛ በውጭ ዲያስፖራውን ግ7ን ዋነኛ ተቃዋሚዋ በማስመሰል ሕዝቡ ወደትክክለኛ ትግል እንዳያተኩር በማድረግ እግረ መንገድም ዲያስፖራው ግ7 ድጋፍ በመስጠት መጨረሻ ውሸት እንደሆነ ሲያውቅ ተስፋ እንዲቆርጥና ጠንካራ ፖለቲካ ድርጅት ቢነሳ ሕዝቡ ድጋፍ እንዳያደርግ ከእነጭርሱም ከትግሉ እንዲወጣ ነው፡፡ ይህ የእኔ እይታ ነው፡፡ አይደለም የምትል አመክንዮአዊ(ሎጂካል) በሆነ ሁኔታ አስረዱ፡፡
ሌላው ዲያስፖራውን የሚዘውሩ ከፌስቡክ እስከ ትልልቅ የሕዝብ መገናኛ የሆኑ የመረጃ ማሰራጫዎች ናቸው፡፡ ፌስቡኩን ግለሰብ ስለሆነ ለወያኔ አገለገለም ተቃዋሚም ሆነ እኩል ነው፡፡ አሳዛኙ ግን ትልልቅ ተደራሽነት ያላቸው ሚዲያዎች በኢትዮጵያዊነትና በአንዳንድ ብሔረተኝነት ሥም ለወያኔ መሠረታዊ የሆነው የሆነውን ሚና መጫወታቸው ነው፡፡ በአንድ ወቅት አንድ ጂጂ የተባለችን ግለሰብ የኦሮሞ ሕዝብ አይንና ጆሮ ነኝ የሚል አንድ ሚዲያ በክብር እንግድነት በአንድ ስብሰባ ላይ የጋበዘበትን ሂደት ጠቁሜ ነበር፡፡ ይሄው ሚዲያም በዛን ወቅት ለወያኔ ትልቅ ውለታ የሚሆን የለንደኑንና የአትላንታውን ስብሰባ በዋናነት አቀናበሪ ነበር፡፡ መቼም መገለባበጥ ሥልታቸው ስለሆነ አሁን ላይ ይሄ ሚዲያ የአገር ጉዳይ ዋና አሳሳቢ አጀንዳዬ ነው ብሎ ደግሞ ተነስቷል፡፡
ከዚሁ ከሚዲያው ጎራ ሌላው የኢትዮጵያ አይንና ጆሮ ነኝ በቀጥታ ከኢትዮጵያ ወያኔ በላከችለት ሰላይ ነው እየታገዘና አቅጣጫ እየተሰጠው ሥራውን የሚሰራው፡፡ የወያኔው ባለስልጣን ኤርምያስ ለገሰ በዋናነት የፖለቲካ ተንታኝ የሆነበትን ኢሳትን ማለቴ ነው፡፡ ስለዚህ ሰው ብዙ ጊዜ ተናገሬአለሁ፡፡ ምንም ሰው ሊገባው አልቻለም፡፡ እኔ ይሄን ሰው ለማዳመጥ ትግስቱም የለኝም፡፡ እንደምንም በትላንትናው እለት ያው ግ7 እያለ ራሱን የሚጠራው ሌላው የሕቡዕ የወያኔ ተዋናይ ገንዘብ ማሰባሰብ ላይ ሲናገር ለመስማት ሞከርኩ፡፡ ግ7ን ሮል ሞዴላችሁ ነው አለን፡፡ ይባነንብኛል ብሎ ቢጠረጥር ጥሩ ነበር፡፡ ቀጠለም ዛሬ ላይ ኢትዮጵያ ውስጥ ሕዝቡ በይፋ እኔ ግንቦት 7 ነኝ ይላል አለን፡፡ ከ3 ዓመት በፊት ባሕር ዳር ላይ ሕዝብ ግ7 እውነት መስሎት እኔ ግ7 ነኝ ማለቱን ትዝ ይለኛል፡፡ ከዚያ ወዲህ ግን ግ7ን ሕዝብ ማን እንደሆነ ጠንቅቆ ተረድቶታል፡፡ እንኳን ግ7 ነኝ ብሎ ሊል ግ7 የሚባል ሥም ሲሰማ ደሙ እንደሚፈላ እናውቃለን፡፡ የኢሳቱ ኤርሚያስ ስለትግራይ ሆን ብሎ ብዙ ሕዝብን ከሕዝብ የሚያጋጩ የውሸት መረጃዎችን ለማስተላለፍ መድረኩን በመጠቀም ቀጠለ፡፡ ትግራይ በየ60 ኪሎሜትሩ ኤርፖርት ተሰርቷል፣ ልዩ ትምህርት ቤት ተሰርቷል፣ ልዩ ሆስፒታል ተሰርቷል፡፡ የሆስፒታሉን ልዩነት ሲገልጽ በአገሪቱ ከጥቁር አንበሳ በላቀ ሬሳ የሚመረመርበት ይለናል፡፡ ሬሳ በመመርመር ኢትዮጵያ ውስጥ ዳግማዊ ሚኒሊክ ነው፡፡ እርግጥ ነው ሬሳ ሌላም ቦታ ሊመረመር ይችል ይሆናል፡፡ ግን ሬሳ ለመመርመር ለዚያ የሚያስፈልግ አንድ መሳሪያ እንጂ የሆስፒታልን ልዩ ዘመናዊነትን አያሳይም፡፡ የሆነ ሆኖ ግን እኛ ለሕዝብ ጥቅም በትግራይ ከተሰሩ እንዲህ ያሉ ሕዝባዊ አገልግሎት የሚሰጡ ተቋማት ከመገንባት ጋር ምንም ችግር የለብንም፡፡ ተገንብቶም ከሆነ እሰየው፡፡ ይህን ሁሉ ሲል ግን በትግራይ ስላሉት የወያኔና ደጋፊዎቻቸው ግዙፍ አገር አጥፊ የንግድ ተቋማት ምንም አላለም፡፡ ቢያንስ ኢፈርትንና በሥሩ ያሉትን፡፡ ትግራይ እኮ ከእነዚህ ውጭ የግል የሚባል ሆቴል ከአልሆነ ከእነጭርሱም የሚፈቀድ አይመስልም፡፡ ትምህርት ቤትና ሆስፒታል ነው የታየው፡፡ ይህን በማድረግ ኤርሚያስ የትግራይ ሕዝብ(ትግራይ የሚኖረውን ማለቴ ነው) ልዩ ጥቅም እንዳገኘና ሌላው ሕዝብ ትግራይ የሚኖረውን ሕዝብ በልዩ ጠላትነት እንዲያይ ነው፡፡ ይሄ ደግሞ ወያኔና ደጋፊዎቿ እንቅልፍ አጥተው የሚሸርቡት ሴራ ነው፡፡ የትግራይን ሕዝብ እኛ ከሌለን አለቀልህ እያሉ ቀን ከሌሊት የሚለፈፍፉት እኮ እነሱ ባይኖሩ የትግራይ ሕዝብ እንደሕዝብ እንደሚኖር አጥተውት አደለም፡፡ ግን ትግራይን አጡ ማለት ወያኔ ምሽጓ ፈረሰ ማለት ነው፡፡
ጥቂት ግን በትግራይ ስለሚሰሩ የሕዝብ አገልግሎት ሰጭ ተቋማት ልበል፡፡ አዎ ትክክል ነው በትግራይ ልዩ ትምህርትቤት ተሰርቷል፡፡ መጀመሪያ መቀሌ ኢኒስቲቱት ኦፍ ቴክኖሎጂ ተብሎ ይጠራ ነበር፡፡ አላማውም ትግሬ የሆኑ ተማሪዎችን ብቻ በዛ በማሰልጠን የመረጃ መረብን ለመቆጣጠር በሚል ነው፡፡ ሌሎች ተያያዥ ግንባታዎችም አሉት ለምሳሌ በዛው ትልቅ የቲሹ ካልቸር ላቦራቶሪ ተሰርቷል፡፡ ገነዘቡ ደግሞ አባይ ጸሐይዬ ከሚመራው የስኳር ኮሮፖሬሽን ነው፡፡ ለሸንኮራ አገዳ ልማት ችግኝ አፋጣኝ ለማምረት በሚል፡፡ አስቂኙ ግን መቀሌ ተፈልቶ የሚተከለው ወይ መተሀራ ወይ ሌላ ብዙ ኪሎሜትር ተጉዞ ነው፡፡ ሌላ አንድ የግለሰብ ደግሞ ሞጆ ላይ እንዲሁ ተጀምሮ ነበር፡፡ ግለሰቡ የሕክምና ባለሙያ ሲሆን ከሙያው ጋር ምንም ግንኙነት የለውም፡፡ ይሄም በፈረደበት የስኳር ኮርፖሬሽን ገንዘብ ነው፡፡ እነዚህ ላቦራቶሪዎች ዘላቂነት እንደሌላቸው ይታወቃል ግን ገንዘቡን ለመዝረፍ የተጠቀሙበት ነው፡፡ ሌላው እንድ ነገር ሲሰራ ሰሪዎቹ፣ አስመጪዎቹ ሁሉም የኢፈርት ኩባኒያዎች ናቸው፡፡ ሰሞኑን መቀሌ 8 ቢሊየን ብር ለውሀ አገኘች ተብሎ ወሬ ነበር፡፡ ሊሆን ይችላል፡፡ ለመቀሌ ሕዝብ ግን እንኳን የ8ቢሊየን የ8ሚሊየኑም ፕሮጀክት ተጠናቆ ከተሰጠው ጥሩ ነው፡፡ በትግራይም ሆነ በሌሎች ቦታዎች ግንባታ ሲገነባ ኢፈርትን ለመጥቀም እንጂ የትግራይን ሕዝብ ለመጥቀም ታስቦም አደለም፡፡ እግረ መንገድ ግን የትግራይን ሕዝብ ልማት እያለማንልህ ነው ለማለት ይጠቅማል፡፡ የመቀሌው ኢኒስቲቱዩት ኦፍ ቴክኖሎጂ አሁን በመቀሌ ዩኒቨርሲቲ ሥር የገባ መሠለኝ፡፡ አሁንም ትግሬ ብቻ ይሁን ሌሎችም እንዲማሩ መፈቀድ አለመፈቀዱን አላውቅም፡፡ የመጀመሪያ አላማው ግን ከላይ በነገርኳችሁ ነው፡፡ ኤርፖርት የተባለው መቀሌና(ኩሃ) አክሱም፣ ምን አልባት አድግራት፡፡ አማራ ክልልም እኮ ባሕርዳር፣ ጎንደር፣ ላሊበላ ከትግራዩ በማይበልጥ ርቀት አለ፡፡ የአሰራር ልዩነት ሊኖር ይችላል፡፡ ያም ሆነ ይህ የሕዝብ አገልግሎት ሰጭ ተቋማት አደሉም የእኛ ችግር፡፡ ትግራይ የሚኖረው ትግሬ እንደሁ ኖሮው ያው ሌላ ቦታ የምናየውን ነው፡፡ ይልቅ ከትግራይ የወጡ ትግሬዎች አብዛኞቹ ምን አልባትም ከጥቂቶች በቀር በአንድም ይሁን በሌላ በወያኔ ተጠቃሚ ናቸው፡፡
በመጨረሻም ዶ/ር አብይን ልምከር፡፡ ሽርሽሩ በቃህ፡፡ በአፋጣኝ በተግባር ሕዝቡ እየጠበቀ ያሉትን ጉዳዮች ፈጽም፡፡ ብዙዎች ከወያኑ ጋር ሆነው የተናገርከው እንዳይፈጸም እያሴሩ እንደሆነ ይግባሕ፡፡ የሕዝብን ጎልበት ተጠቀም፡፡ አትለሳለስ፡፡ በአስቸኳይ ወሮበሎች እንደልባቸው ለመሆን ያወጡትን አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አንሳ፡፡ በሮበሎች ኮማንድ ፖስት ሥር አገሪቱን ሰጥተህ አገር እየመራሁ ነኝ ብለህ አታስብ፡፡ ከዛ በማከታተል ሌሎች የወሮበሎች የሽብር አዋጆችን አንሳ፡፡ ቀጥሎ ሕገ መንግስቱን፡፡ አስችኳይ ጊዜ አዋጁን ከማንሳት ጎን ለጎን በግፍ የታሰሩ የሕዝብ ልጆችን ሁሉ አስለቅቅ፡፡ በመከላከያው ውስጥ ያሉ ትግሬ ያልሆኑ ሰራዊቶችን ተጠቀም፡፡ ሕዝብን ተጠቅም፡፡ ወያኔን እድል አትስጥ፡፡ ትንሽ ከቆየህ እንደ አቶ ኃ/ማሪያም ከመሆን አታመልጥም፡፡ ፍጠን! በየቦታው ሥራህ እንዳይታይ ብዙ ትግል የሚያደርጉትን ወያኔ አሰማረታብሀለች፡፡ ከላይ የጠቀስኩት የወያኔው ሰላይ ኤርሚያስ ምሳሌ ነው፡፡ አሁን ላይ ሕዝብ ድጋፉን አልነፈገህም፡፡ መዘግየትህ ግን የሕዝብን ድጋፍ ያሳጣል፡፡ ወሮበሎቹም የፈለጉት ይሄንኑ ነው፡፡
እግዚአብሔር ይረዳናል ሁላችንም ኢትዮጵያውያን ለኢትዮጵያና ሕዝቦቿ ዘብ እንቁም!
ልዑል እግዚአብሔር ኢትዮጵያንና ሕዝቦቿን ይታደግ! አሜን!