አብይ አህመድና ኡሁሩ ኬንያታ Image copyright FACEBOOK/UHURU KENYATTA

ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ በኬንያ ጉብኝታቸው ኬንያን ከኢትዮጵያ የሚያገናኘውን የባቡር መስመር ለመጨረስ እንደተስማሙ ተገልጿል።

ከኬንያዋ ኢሶዮሎ ከተማ በሞያሌ እስከ አዲስ አበባ የሚዘልቀውን እንዲሁም ናይሮቢን ከአዲስ አበባ የሚያገናኝ መስመር እንደሆነ ፕሬዚዳንት ኡሁሩ ኬንያታ በፌስቡክ ገፃቸው ላይ አስፍረዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ዓለም አቀፍ ጉብኝታቸውን በጂቡቲ፣ ሱዳን ትናንት ደግሞ በናይሮቢ ኬንያ የቀጠሉ ሲሆን ከፕሬዚዳንት ኡሁሩ ኬንያታ ጋር የሁለቱን ሀገራት ግንኙነት ለማጠናከር እንደመከሩ በኢትዮጵያ የኬንያ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ አስታውቀዋል።

አምባሳደሩ እንደገለፁት በፖለቲካው፣ ኢኮኖሚያዊ እና ማህበራዊ ጉዳዮች ትስስራቸው የሚጠነክርበትን ሁኔታም ነቅሰዋል።

”የሁለቱ ሃገራት መሪዎች በደህንነት እና ጸጥታ ጉዳዮች ላይ አብሮ ለመስራትም በከፍተኛ ደረጃ ተስማምተዋል” ብለዋል።

ኬንያ እና ኢትዮጵያን በኤሌክትሪክ ሃይል ለማገናኘት የተጀመረውን ትልቅ ፕሮጀክት ለማጠናቀቅ ሁለቱም መሪዎች ፍላጎት እንዳላቸው አምባሳደሩ ገልፀው “ይህንንም ወደ ስራ ለመተርጎም ከስምምነት ላይ ደርሰዋል።” ብለዋል።

በተለይም ሁለቱ ሀገራት የሚያገናኘውን መንገድ መጠናከር ኢኮኖሚያዊ ጥቅሙ የትየለሌ እንደሆነ ገልፀዋል።

”ሞያሌን የአካባቢያችን ዱባይ ማድረግ የሁለቱ ሃገራት ፍላጎት ነው” ብለዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ከኢትዮጵያ ጋር ከፍተኛ ኢኮኖሚያዊ እና ፖለቲካዊ ትስስር አላቸው የሚባሉ ሃገራት ያደረጓቸው እና እያደረጓቸው ያሉት ጉብኝቶች ፋይዳቸው ከፍተኛ እንደሆነ ተንታኞች ይገልፃሉ።

የምጣኔ ሃብት ባለሙያው ዶክተር አሰፋ አድማሴ ሶስቱ አገራት በተለያየ መንገድ ከኢትዮጵያ ጋር ያላቸው ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ቁርኝት ከፍተኛ በመሆኑ የጠቅላይ ሚኒስትሩ ጉብኝት ትልቅ ትርጉም ያለው ነው ብለው ያምናሉ።

ኢትዮጵያ በምስራቅ አፍሪካ ጠንካራ ኢኮኖሚ ካላቸው አገራት ተጠቃሽ ከሆነችው ኬንያ ጋር የሚኖራት ግንኙነት ወሳኝ እንደሆነ የሚያስረዱት ዶክተር አሰፋ ኢትዮጵያና ኬንያ ረዥም ድንበር መጋራታቸውን እና ግንኙነታቸውም ሰላማዊ ሆኖ መዝለቁን ይጠቅሳሉ።

በተጨማሪም በሁለቱ አገራት መካከል ያለው የንግድ እንቅስቃሴ ውስን ቢሆንም በህዝቦቻቸው መካከል የሚደረገው ንግድ ግን ቦታ የሚሰጠው እንደሆነ የሚገልፁት ዶክተር አሰፋ ግንኙነቱንም ማጠናከር አስፈላጊ ነው ብለው ያምናሉ።

“ኢትዮጵያ የወደብ አማራጮች እየፈለገች እንደሆነ ይታወቃል። በዚህ ረገድ በኢትዮጵያ፣ በደቡብ ሱዳንና ኬንያ መካከል የተፈረመው የላሙ የንግድ በር ፕሮጀክትን ማንሳት ይቻላል” በማለት በብዙ መልኩ ኬንያ ከኢኮኖሚም ሆነ ከፖለቲካ አንፃር የኢትዮጵያ ወሳኝ ጎረቤት እንደሆነች ይናገራሉ።

ዶክተር አነ
FACEBOOK/ UHURU KENYATTA

ከህዳሴው ግድብ ፕሮጀክት አጋርነት አንፃር ደግሞ የሱዳን ጉርብትናም ወሳኝ እንደሆነ የሚናገሩት ዶክተር አሰፋ ጅቡቲም በኢትዮጵያ ኢኮኖሚ የጎላ ድርሻ አላት ብለው ያምናሉ።

“በጥቅሉ የኢትዮጵያ ፖለቲካዊም ሆነ ኢኮኖሚያዊ እጣ ፋንታ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በአለም አቀፍ ጉብኝታቸው በቀዳሚነት ከጎበኟቸው አገራት ጋር የተሳሰረ ነው” ይላሉ።

በተመሳሳይ ጠቅላይ ሚንስትሩ ከበለጸጉት ምዕራባውያን አገራት ቅድሚያ ሰጥተው የጎረቤት አገራት መጎብኘታቸው የአፍሪካ ቀንድ ፖለቲካን እንደተረዱት ያሳያል የሚሉት ደግሞ የምስራቅ አፍሪካ የፖለቲካ ተንታኝ የሆኑት ዶክተር ብርሃኑ ሌንጂሶ ናቸው።

”በጠቅላይ ሚንስትሩ ጉብኘት የተደረገባቸው እኚህ አገራት ስትራቴጂካዊ ጥቅማቸው ላቅ ያሉ ናቸው” ይላሉ።

በኬንያ እና በሱዳን የተደረጉት ጉብኝቶች ሊያስገኟቸው ከየሚችሉት ፖለቲካዊ እና ኢኮኖሚያዊ ጥቅሞች ባሻገር ከጠቅላይ ሚንስትሩ ጉብኘት በኋላ ኢትዮጵያውያን እስረኞች መፈታት ትልቅ ትርጉም የሚሰጠው እንደሆነም ዶክተር ብርሃኑ ይገልፃሉ።

“ስኬታማ ሊባል የሚችለው ይህ የጠቅላይ ሚንስትሩ ጉብኘት በጎረቤት አገራት ብቻ ሳይሆን በአገር ውስጥ ፖለቲካ አመራራቸው ውስጥም ተቀባይነት ሊያስገኝላቸው ይችላል” ይላሉ።

Source     -BBC/AMHARIC