ግምገማ
የኢትዮጵያ ፖለቲካ- በስምምነት ላይ የተመሰረተ ባህላዊ አንድነት እና ሌሎች ጉዳዮች ደራሲ፣ ገለታው ዘለቀ
የገጽ ብዛት ፣ 288
አሳታሚ፣ ሬድ ሲ ፕሬስ፣ ኒው ጀርሲ 2018
ገምጋሚ መዝገቡ ምትኬ
የደራሲ ገለታው ብዕር የሚደፈር በማይመስለው የተወሳሰበ የሀገራችን ችግር ጉዳይ ዘልቆ በመግባት የዚህ ግምገማ መነሻ የሆነውን እጅግ ጠቃሚ የሆነ አመጽሐፍ ማፍራት ችሏል – “የኢትዮጵያ ፖለቲካ-በስምምነት ላይ የተመሰረተ ባህላዊ አንድነትና ሌሎች ጉዳዮች” የሚል። ጠቅለል ብሎ ሲታይ፣ የመጽሀፉ ይዘት ከግማሽ ምዕተ-ዓመት በፊት ገደማ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች አካባቢ የተነሳ የብሄር ጥያቄ አዝግሞ የወለዳቸው የብሄር ፖለቲካና የብሄር ፈደሬሽን ያስከተሉትን ውስብስብ ችግሮች የዳሰሰ እና ደራሲው የችግሮቹ መፍቻ ቁልፍ ነው ብሎ ያቀረበውን አዲስ የመፍትሄ ሀሳብ የሚመለክት ነው።
ደራሲው እደረሰበት መደምደሚያ (መፍትሄ ሃሳብ) ላይ ለመድረስ በቂ ጥናትና ምርምር አድርጓል። መረጃዎችን አሰባስቦ አጠናቅሯል። ሀገሪቱ የተከተለችው ማህበራዊና ፖለቲካዊ ስርዓት የፈጠራቸውን አያሌ ችግሮች በመቀራረም ተንትኗል። ውጤት– የሀሳብ ፍሰቱ ሳይዛባ በአያሌ ርዕሶች አደራጅቶና ደረጃውን ጠብቆ በጻፈው መጽሐፍ ኅትመት ስራውን አጠናቋል። ይህን ሁሉ ለማከናወን የጠየቀው ጊዜ ረዥምና አድካሚ ሊሆን እንደሚችል ቢገመትም፣ በከንቱ የባከነ ጊዜና ይተደከመ ድካም ባለመሆኑ ውጤቱ የሚክስና የሚያረካ ነው። ደራሲ ገለታው!! ጥረትህ በስምምነት ላይ የተመሰረተ ባህላዊ አንድነት የተሰኜ አዲስ ንድፈ-ሀሳብ ያስገኜልህ በመሆኑ እንኳን ደስ አለህ። በመጽሀፍህ የጀርባ ሽፋን “በስምምነት ላይ የተመሰርተ ባህላዊ አንድነት ንድፈ-ሃሳብ መሀንዲስ” ተብለሃል። ይህን ስያሜ እኔም እጋራለሁ-በትክክል ተገልጸህበታልና።
መጽሐፉ በ፲ ምእራፎች(ርእሶች)፣ በበርካታ ንኡሳን ርዕሶች፣ በአያሌ ሰሌዳዎች፣ በመዋቅሮች፣ በግርጌ ማስታወሻዎች፣ በአባሪ፣ እና በቅሱም (ኢንዴክስ) መደራጀቱ ለማንበብ ምቹ፣ የመረጃ ምንጮችን ለማግኜት ቀላል፣ በቅሱም ላይ የተመለከቱ ስሞችንና ጽንሰ-ሀሳቦችን ለመሻት አመች አድርጎታል።uu
የመጽሀፉ ይዘት በዋቢ መጽሀፍት፣ በግርጌ ማስታወሻዎች፣ በስታስቲክስ መረጃዎች፣ በመጀመሪያና ሁለተኛ የመረጃ ምንጮች የተደገፈ ነው። ደራሲው ህዝቡ ውስጥ በኖረበት ወቅት ዓይቶ የተረዳውንና የሀገሪቱን ህገ-መንግሥትንም ጭምር በማጣቀስ የተጻፈ ነው። ይህም ስለሆነ፣ መጽሐፉ የአሳማኝነትና የተቀባይነት ፈተናን በቀላሉ አልፏል ብየ አምናለሁ።
ደራሲው በመጽሐፉ ውስጥ የተጠቀመባቸው ቃላት በጥንቃቄ የተመረጡ፣ የተቆጠቡ፣ አሻሚነት የሌለባቸው ናቸው። ቃላቱ የገነቧቸው ዓረፍተ ነገሮችም እንዲሁ ጥርት ያለ ሀሳብን በመግለጽም ሆነ መልእክትን በማስተላለፍ ረገድ ደረጃውን የጠበቀ አድርጎታል። የመጽሐፉ ይዘት አዳዲስ ሀሳቦችንና መረጃዎችን ያካተተ በመሆኑ የአንባቢን አዲስ መረጃና ሀሳብ የማግኘት ጉጉት እየጨመረና እየመለሰ እንደተዋጣለት ልብወለድ ዓይነት የመሳብ አቅም አለው ብየ አምናለሁ። አንድን ሀሳብ ከቀላል ወደዉስብስብ ደረጃ እያሸጋገረ ያደረገው የሃሳብ ማዳበር ሥራው አንባቢያን በቀላሉ ሃሳቡን እንዲረዱለት የሚያደርግ ነው ብየ አስባለሁ። ታሪካዊ ፋይዳ በሚያሻበት ወቅት ወደኋላ ሄዶ ከወቅቱ ጋር የማዛመድ ወይም የማነጻጸር አቅሙም ብርቱ ነው። ህገመንግሥትን ተከትሎ ባቀረበው ትንታኔ፣ ድንጋጌዎቹ ያቀፏቸውን ንጥረ-ሀሳቦች (ኢለመንትስ) ጭምር በትኖ ማስረዳትን ችሎበታል (ምሳሌ ገጽ 134-139)። ዳታዎችን ተጠቅሞ በመተንተን ሊደርስ እሚፈልገው መደምደሚያ የመድረስ ብቃቱን አሳይቷል።
ደራሲው የጻፈውን መጽሐፍ ዓላማ በሚመለከት ራሱ የገለጸው፣ “ያለፈውን መንቀፍ፣ የአሁኑን መክሰስ ሳይሆን የተሻለ መንገድ ለማሳየት” (ገጽ 43) ነው በሚል ነው። ይህም የጭብጦችን ብልቶች ግራና ቀኝ በማየት፣ እየተመራመረና እያነጻጸረ
ወደትክክለኛ ድምዳሜ ለመድረስ የሚያስችል የትንታኔ አጻጻፍ ስልትን ለመከተል ያለውን ፍላጎትና ያደረገውን ጥረት አመልካች ነው።
መጽሃፉን የጻፈበትን ምክንያት ሲያስረዳም፣ የብሄር ፖለቲካ እና የብሄር ፌደሬሽን ”ለሃገራችን መጻኢ ዕድል አይሆኑም፣ ምንም እንኳን ህወሃት በወታደር ጠርንፎ ቢይዘውም አንድነታችን ተናግቷል፣ ማህበራዊ ሃብታችን (ሶሻል ካፒታል) ፈርሷል። ስለዚህ ለወደፊቷ ኢትዮጵያ ማህበራዊ ፖለቲካ አማራጭ ሃሳብ” ለማምጣት “ችግርን ማንሳቱ ብቻውን መፍትሄ አልሆን ስላለ መፍትሄ በማፈላለጉ በኩል እንደ ዜጋ” በማበርከት የዜግነቴን ላደርስ ነው ብሏል። ቀጥሎም በመጽሐፉ ውስጥ የተካተተው “የማህበራዊ ፖለቲካ ቲየሪ (ንድፈ-ሃሳብ) ለሃገራችን ውስብስብ ችግር መፍቻ አማራጭ አሳብ ይሆናል ብየ” (ገጽ 88) ስለማምን ነው በማለት አስረድቷል።
በመጽሐፉ ላይ የተገለጸውን መረጃ ትክክለኛነት ለማረጋገጥ ይህ ገምጋሚ የተቻለውን ያህል ለማመሳከር ሞክሯል፣ ከተለያዩ የመረጃ ምንጮች ቀደም ሲል አግኝቶት ከነበረው ግንዛቤ ጋርም አጣጥሟል። ደራሲው እንዳለው አግባብ ያልሆነ ውቅስና ክስ አለ ብየ አላምንም። አግባብ የሆነ ትችት መደረጉ ግን እንዲህ የመስለን መጽሐፍ ለሚጽፍ ሰው የሚታለፍ አይሆንም። እጅግ ውስብስብ ችግሮች መኖራቸው የማይካድ ሀቅ ነውና የችግሮች መተንተን ለሚወለደው መፍትሄ ግድ የሚል ነውና – ይህ የምክንያትና ውጤት ግንኙነት ህግ ነው። ዛሬ በደረስንበት ታሪካዊ ወቅት ችግሮች ተደብቀው እንዲኖሩ የሚፈልጉ ወገኖች ቢኖሩም፣ መደበቅ እማይቻልበት ደረጃና ዘመን ላይ እንገኛለን። እነሱም የግድ በገሃድ አምነው የሚቀበሉት ሀቅ እየሆነ መጥቷል።
ደራሲው የማእከላዊ ስታቲስትክስ ኤጀንሲ ያጠናቀራቸውን መረጃዎች በተለያዩ የመጽሐፉ ክፍሎች በምንጭነት ተጠቅሞባቸዋል። (ለምሳሌ የቤንሻንጉል-ጉሙዝ ህዝቦች ጥንቅር ገጽ 138፣ የሃረሪ ክልል ነዋሪዎች ጥንቅር (ገጽ 135 – 137)። በመሆኑም፣ ይህ ገምጋሚ ባመሳከራቸው መረጃዎች መጠን የመጽሐፉ ይዘት ትክክለኛና አስተማማኝ፣ ታሪካዊ ጠቀሜታው ከፍተኛ፣ ሀገሪቱ ለገጠማት ችግር መፍቻ ቁልፍ ሀሳቦች የተሰነዘሩበት በመሆኑ እያንዳንዱ ቤተሰብ፣ የችግሮቹ ፈጣሪዎች ጭምር፣ መጽሐፉን በየቤቱ ሊያኖረው፣ አንብቦ ላላነበበ በማስተላለፍ ጠቃሚ ሀሳቦችን እንዲሰራጩ፣ እንዲሰርጹ፣ እንዲዳብሩ ሊያደርግ ይገባል ብየ አምናለሁ።
በቃላት ተከሽፎ ለአንባቢ ዓይን ወይም ለአድማጭ ጆሮ ከመድረሱ በፊት፣ ማንኛውም ሀሳብ ባሳቢው ጠባብ የአእምሮ ክልል ውስጥ ተወስኖ ይጠነሰሳል፣ ይውጠነጠናል፣ ይብላላል። ይህ ለሰው ልጅ ከአምላኩ ከተሰጡት በረከቶች መካከል አንዱ ሲሆን፣ እንደየሰው ተፈጥሯዊ ባህርይ በጎንና አልሚ ሀሳብን ከመጥፎና የጥፋት ሀሳብ በመለየት መርጦ የመቀበልና የመተግበር፣ ወይም ሃሳቡን ለሶስተኛ ወገን የማስተላለፍ ችሎታንም አጎናጽፎታል። በደራሲ ገለታው መጽሐፍ ውስጥ የሰፈሩ ሀሳቦች፣ የሀሳብ መገለጫ የሆኑ ቃላትና ዓረፍተ-ነገሮች ሁሉ በዚህ ሂደት ያለፉ በመሆናቸው የሱን ስብዕና እና ተፈጥሯዊ ባህርይ አመልካቾችም ናቸው። እሱ የተላበሳቸውን ማህበራዊ እሴቶች፣ የቆመላቸውን በጎ ዓላማዎች፣ የሱን ማንነትና ምንነትም ይገልጻሉ። ይህን ለመረዳት ሩቅ መሄድ ሳያስፈልግ፣ ደራሲው ራሱ የመጽሐፉን መታሰቢያነት ለነማ እና ለምን ዓላማ ከሰጠበት በመጀመሪያው ገጽ ላይ ከተመለከተው ምንባብ መመልከቱ በቂ ነው። እንዲህ ይላል፦
በ2008 ክፉ ቀን በረሃብ ምክንያት ህይወታቸውን ላጡ ህጻናትና በረሃብ ለተጎዱ ሁሉ ይህ መጽሐፍ መታሰቢያ ይሁንልኝ። ይህ የከፋ ችግር በቀጥታ ከመልካም አስተዳደር እጦት ጋር የተያያዘ ነው። ረሃብን ለማጥፋትና መልካም አስተዳደርን፣ ዲሞክራሲን ለማስፈን ሲታገሉ ለታሰሩ፣ ለሞቱ ጋዜጠኞች፣ የፖለቲካ መሪዎችና አክቲቪስቶች ሁሉ ይህ መጽሐፍ ማስታወሻየ ነው።
ደራሲ ገለታው ለምስጋና እና ለአድናቆት ቅድሚያውን የሰጠው ለፍትህ፣ ለነፃነትና ለዲሞክራሲ ቁርጠኛ ታጋዮች ነው። ምክንያቱን ገልጿል፤ እነዚህ “ለተጨቆኑ የቆሙ ናቸውና። ይህች ምድር እንዲህ ያሉ ጀግኖችና ርህሩሆች እስካሏት ድረስ ከእንግዲህ አልሰጋም” በማለት።
******* ******** ***********
የገምጋሚው ትኩረት፦ የብሔር ፈደራሊዝም አነሳስና አሁን ያለበት ሁኔታ
ወደመጽሀፉ ይዘት በመግባት ከተነሱት በርካታ ነጥቦች መካከል ቀጥሎ ያሉትን አንዳንዶቹን ላካፍላችሁ፣ በተለይ የብሄር ፖለቲካንና የብሄር ፈደራሊዝምን በሚመለከት። በሀገራችን የብሄር ፖለቲካ ስለወለደው የብሄር ፌደሬሽን ጉዳይ ደራሲ ገለታው በመጽሐፉ ሰፊ ቦታ ስጥቷል። የደራሲ ገለታው መጽሐፍ የብሄር ፓለቲካ አስተሳሰብ እንዴት እንደተነሳና እያደገ እንደመጣ ተርኳል። እንዲህም ይላል። “በአንድ የፖለቲካ ስልጣን ስር መቆየታችን፣ በአምባገነንና በፊውዳል ስርአት ስር መቆየታችን ብቻ አንድ ነን ሊያሰኘን እንዴት ይችላል? ከሁሉ በላይ የየራሳችን ታሪክ፣ ባህልና ቋንቋ መልክዓምድር ያለን”
ስለሆነ ይህን አንድነት የሚባል ነገር እንደገና እንመልከተው (ገጽ 109) የሚሉ ወገኖች በአስራ ዘጠኝ ስልሳዎቹ መነሳታቸውን ያወሳል። ቀጥሎም በአንድ በኩል “መለያየታችንን ሳንፈራ ይህን ህብር መልካችንን ይዘን አብረን ለመኖር እንደገና ኪዳን አጽንተን ያለፈውን ችግር አስተካክለን መኖር ይጠበቅብናል” የሚሉና፣ በሌላ በኩል የተለያየ ባህል ያለውን ቡድን እንዳመሉ ለማስተዳደር የሚበጀው ራስን በራስ ማስተዳደር ነው የሚሉ ወገኖች መነሳታቸውን ይዘክራል። የኋለኛው አስተሳሰብ ምስለትን ( አሲሚሊሽን) ለመቀነስ የብሄር ፈደራሊዝም እውን መሆን እንዳለበትና የብሄር የፖለቲካ ድርጅት ማቋቋምን የሚጠይቅ ስለሆነ ቅርበቱ ከፈደሬሽን ይልቅ ኮንፈደሬሽን መሆኑን ደራሲው ይከራከራል። (ገጽ 110)
የብሄር ፈደራሊዝምና የብሄር ፖለቲካ ከኢትዮጵያ ውጭ ምን መልክ እንዳለው ደራሲው እያነጻጻረ አሳይቷል። በመጽሐፉ ገጽ 48 ላይ የብሄር ፖለቲካ “በአንዳንድ አገራት ለምሳሌ ህንድና ኔፖል እንዲሁም በተወሰነ ደረጃ ኢንዶኒዣ የሚታይ ሲሆን፣ በብሄር ፖለቲካ ውስጥ ደፍሮና ጠልቆ የገባ እንደኢትዮጵያ የለም። ኢትዮጵያ ከሌሎች አገራት በተለየ መንገድ በጥልቀት የብሄርን ፖለቲካ የምታራምድ አገር ናት። የብሄር ፖለቲካዊ ማንነት እስከመገንጠል የሚሄድባት አገር በዚህች ፕላኔት ላይ ኢትዮጵያ ናት።” ብሏል። በቋንቋ ላይ የተመሰረተ ፈደሬሽንን የተቀበሉ በጣት የሚቆጠሩ ጥቂት አገሮች ቢኖሩም፣ የብሄር ፖለቲካን በህግ ከልክለዋል-ወንጀል አድርገዋል። ዓለም የብሄር ፖለቲካን ከሰፈሯ አርቃ በማስወገድ በምትኩ በርዕዮት እና የላቀ አማራጭ ሀሳብ ይዞ በመገኘት ተቀባይነት መገኘት ላይ ባተኮረበት በአሁኑ ወቅት ኢትዮጵያ የሙጥኝ ብላ መቀጠሏ ያተረፈችውን በርካታ ችግሮች በተለይ በመጽሀፉ ገጽ 51-87 በሰፊው ዘርዝሯል። “የብሄር ፖለቲካና የብሄር ፈደራሊዝም አገር አፍራሽ ነው” በማለትም ደምድሟል፣ ምክንያቶቹንም አስረድቷል።
በኢትዮጵያ የብሄር ፓለቲካ አራማጆች በለስ ቀንቷቸው ስልጣን ላይ ከወጡ በኋላ የሆነውን ደራሲ ገለታው እንዲህ ሲል ገልጾታል። ኢትዮጵያ ትቅደም የሚለው መፈክር ቀን ጨለመበት። “ያች እናት አገር ኢትዮጵያ ልኳ ያልሆነ የብሔር ጥብቆ ለብሳ በአደባባይ ብሔር ብሔር ዝፈኝ ስትባል አላምርባት አለ። ልኳ ያልሆነ ይህን የብሔር ፖለቲካ ለብሳ በግድ ዘፈን ጀመረች ብሄር ብሄር ብሄር። ዘፈኑ አልመች ያላት ለብሄር ክብር ላለመስጠት ሳይሆን፣ ውድድር ውስጥ መግባት የሌለባቸው ብሄራዊ ማንነትና ጎሳዊ ማንነት ፉክክር ስለያዙ ኢትዮጵያዊነትን እየጎዳው ስለሄደ ነው” ይላል(ገጽ 31)። ቀጥሎም “በግድ በሆነ አንድነት ተፈጥራለች የተባለችውን ኢትዮጵያ ለማስተካከል ኢንጂነሪንግ አስፈለገ….የብሄር ፈደራሊዝም ዲዛይን ተሰራ።” በዚህም መሰረት ህገመንግስት አንቀጽ 47 ተቀረጸለት። በዘጠኝ ክልሎች (፩/ የትግራይ ክልል፣ ፪/ የአፋር ክልል፣ ፫/ የአማራ ክልል፣ ፬/ የኦሮሚያ ክልል፣ ፭/ የሶማሊያ ክልል፣ ፮/ የቤንሻንጉል-ጉሙዝ ክልል፣ ፯/ የደቡብ ብሄር ብሄረሰቦችና ህዝቦች ክልል፣ ፰/ የጋምቤላ ክልል፣ ፱/ የሃረሪ ህዝብ ክልል) የተዋቀረ የብሄር ፈደሬሽን በኢትዮጵያ ተመሰረተ (ገጽ 32)።
በኢትዮጵያ ህገመንግሥት አንቀጽ 46(2) መሰረት ክልሎች የሚፈጠሩት የህዝብን አሰፋፈር፣ ቋንቋ፣ ማንነትና ፈቃድ ላይ በመመስረት መሆኑን ገልጾ፣ የብሄር ፈደሬሽን በኢትዮጵያ የተተረጎመው ግን መርህን መሰረት አድርጎ፣ ዲሞራሲያዊና ፍትሀዊነትን ተከትሎ ሳይሆን በዘፈቀደና አንዳንድ ቡድኖችን ያላግባበ ጠቅሞ ሌሎችን በሚጎዳ ሁኔታ መሆኑን ደራሲው አሳይቷል። በዚህ ረገድ የደቡብ ብሄር፣ ብሄረሰብ እና ህዝቦች፣ የሀረሪ ህዝብ ክልል እና የቤንሻንጉል-ጉሙዝ ክልል የተጠቀሱ ናቸው።
የደቡብ ብሄር፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች 56 ብሄርና ብሄረሰቦችን ያቀፈ የህብረብሄር ክልል እንደመሆኑ እንደሌሎች ክልሎች ቋንቋንና ማንነትን መሰረት በማድረግ የተቋቋመ አይደለም። አልተፈቀደላቸውም እንጅ ከመካከላቸው የክልል እና የዞን አስተዳደር መብት የጠየቁ አሉበት።
የሃረሪ ክልል አፈጣጠር በምን ላይ ተመስርቶ እንደሆነ ግልጽ አይደለም፣ ህገመንግሥቱን የተከተለም አይደለም ይላል ደራሲው። ሀረሪ ከቃሊቲ ክፍለ ከተማ የምታንስ፣ 183,344 የተለያዩ ብሄር/ብሄረሰቦች ህዝቦች የሚኖሩባት ጥንታዊት ከተማ ናት። ደራሲው ባጠናቀረው ዳታ መሰረት ከነዋሪዎቹ መካከል 56.41% ኦሮሞዎች፣ 22.77% አማሮች፣ 4.34% ጉራጌዎች፣ 8.65% ሀረሪዎች፣ 1.53% ትግሬዎች እና 1.25% አርጎባዎች ናቸው። በዚህ መርህ አልባ አደረጃጀት መሰረት ከነዋሪው ህዝብ መካከል ከ9% (15,859) በታች የሆኑት ሀረሪዎች መንግስት መስርተው 91% የሚሆኑ የሌሎች ብሄር/ብሄረስቦች ህዝቦችን ይገዛሉ። አናሳዎች ብዙሃኑን። ከዲሞክራሲም ሆነ ከመርህ ወይም ከህገመንግስት ጋር የማይጣጣም አሰራርና አደረጃጀት።
ከዚህ በመነሳት ደራሲው የሚያነሳቸው ጥያቄዎች አሉ “አገው ሃረሪን ሲያስብ ምን ይሰማዋል? ሲዳማ ከሶስት ሚሊዮን ህዝብ በላይ እያለው፣ ክልል መሆን እፈልጋለሁ እያለ ሲከለከል ምን ይሰማዋል? ኮንሶዎች ዞን መሆን እንሻለን ሲሉ ለምን ይከለከላሉ? ዞን ቀርቶ የራሳቸውን መንግስት ማቆም ይችላሉ ተብሎ የለም እንዴ? … እስከመገንጠል መሄድ መብታቸው” መሆኑ በህገመንግስት ተረጋግጦ የለ እንዴ? የሚል። “ፈደራሊዝሙ እልፍ ጥያቄዎችን የሚያስነሳና የማይመልስ ነው።” ብሎ ደምድሟል።(ገጽ 137 )
የቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል ጉዳይም ከችግር ያልተላቀቀ መሆኑን ደራሲው አመላክቷል። የክልሉ ህገመንግስት አንቀጽ 2 “በክልሉ ውስጥ የሚኖሩ ሌሎች ህዝቦች የሚታወቁ ቢሆንም የክልሉ ባለቤት ብሄር፣ ብሄረሰቦች በርታ፣ ጉሙዝ፣ ሽንሻ፣ ማኦና ኮሞ ናቸው” በማለት ክልሉን በዋናነት ለበርታ፣ ለጉሙዝ፣ ለሽናሻ፣ማኦና ኮሞ ብቻ ሰጥቷል። ነዋሪዉን ባለቤት በሆኑና ባልሆኑ መካከል ልዩነት ፈጥሮ በርካታ ዉስብስብ ችግሮችን ማስከተሉን ለማሳየት ደራሲው ሰፊ ትንተና አድርጎበታል። (ፍትሀዊ ያልሆነው ይህ አደረጃጀትና የአንድን አገር ህዝቦች የክልሉ ባለቤቶችና ባለቤቶች አድርጎ መፍጠር ዛሬ ባለቤት አይደሉም የተባሉትን ለጥቃት፣ ለስደትና ለእንግልት ዳርጎ ይገኛል።)
ደራሲው ይህ የብሄር ፈደራሊዝም በሀገሪቱ በርካታ ችግሮችን ማስከተሉን፤ ለምሳሌ በተለያዩ ስፍራዎች በድንበር ነክ ግጭቶች ሳቢያ የአንድ አገር ልጆች መተላለቃቸውን፣ ህዝብ ለአካል ጉዳትና ስደት መዳረጉን፣ ንብረት መውደሙን፣ በየአካባቢው ያልተመለሱ የአስተዳደር ችግር ጥያቄዎች መበራከታቸውን፣ በሀገሪቱ ብሄራዊ አንድነት ላይ የአደጋ ስጋት እንዲያንዣብብ ምክንያት መሆኑን ገልጧል። ደራሲው ህብረብሄር ባለበት አገር ብዙሃንነት (ዳይቨርሲቲ) በትክክል ሊስተናገድ የሚችለው በዲሞክራሲ እንጅ በብሄር ፖለቲካ አለመሆኑን አመልክቶ፣ የብሄር ፖለቲካ ባለበት ሰላም ይወርዳል ማለት ዘበት መሆኑን ጠቁሟል። (ገጽ 209)
ሀገሪቱ እንዲህ በመሳሰሉ ውስብስብ ችግሮች ውስጥ ካለች መፍትሄው ምንድነው? ለሚለው ጥያቄ የደራሲው መልስ “ያለን የባህልና የቋንቋ ልዩነት ያሳለፍነው ታሪክም ቢሆን ተደማምረው የሚገነጣጥሉን ሳይሆኑ ወደ አዲስ ኪዳን የሚመሩን ናቸው:: ለምን ወደአዲስ ኪዳን አንገባም?” ገጽ 111። በስምምነት ላይ የተመሰረተ ባህላዊ አንድነት እንመስርት። እንዴት? ያለፈውን ከመውቀስ የተሻለ ቤት እንስራ! ለዚህ ደግሞ ያለፈውን ባህላዊ ትውስታዎቻችንን ሜዳ ላይ ሳንጥል፣ አገሪቱ ያሳለፈቻቸውን አኩሪ ታሪክ ሳናዋርድ፣ በአንድ በኩል ያለፈውን ታሪክ የሚንከባከብና ባህሎቻችንን የሚጠብቅ አንድ ራሱን የቻለ የባህል መንግስት እንመሰርት፣ በሌላ በኩል ልማትን ለማፋጠን የሚችል ዲሞክራሲን የሚያመጣ የፖለቲካ መዋቅር ያለው መንግሥትም እንፍጠር። ይህንንም በሚገባ በህገመንግስት ስራውን ለይተን እንኑር። ስያሜውን በስምምነት ላይ የተመሰረተ ባህላዊ አንድነት (ስባአ) እንበልና አንድ ታሪካዊ ጎዳና ውስጥ እንግባ። እኛ ቡድኖች በባህላዊና በብሄራዊ ማንነታችን መካክል ውድድር ሳንፈጥር ሁለቱንም አክብረን እንኑር። ከሁሉ በላይ ኑ እና ኪዳን እንግባ – አዲስ ኪዳን። ያለንን መንፈሳዊና ቁሳዊ ባህሎች አዋጥተን ምርጥ ቤት እንስራ። ኢትዮጵያን እንደገና አንጸን ውብ አርገን እንስራት። ኑ
የፈረሰውን ቅጥር እናድስ። ወደአዲስ ኪዳን እንሻገር።” ገጽ 114-117 በማለት የመጽሐፉ ርእስ የሆነውን አዲስ ንድፈ-ሀሳብ አስተዋውቋል።
አዲሱ ኪዳን ገጽ 125
ደራሲው ስለአዲሱ ንድፈሀሳብ ሲያብራራ እንዲህ ይላል። በስምምነት ላይ የተመሰረተ ባህላዊ አንድነት ማለት ቡድኖች ሁሉ ያላቸውን ቁሳዊና መንፈሳዊ ባህሎች ሁሉ ለኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊነት መሰዋትና መልሰው የመንከባከብ ሃላፊነትን መውሰድ፣ ወደአዲስ ኪዳን መሻገር እና የተባበረችውን ኢትዮጵያን መገንባት ማለት ነው። በስምምነት ላይ የተመሰረተ ባህላዊ አንድነት ስንል አንዱ ጉዳይ በስምምነት ላይ የሚለው ጉዳይ ነው። ወደስምምነት የሚወስደን ጎዳናው ምንድን ነው? የሚልም ይነሳል። ይሄ ከባድ ጉዳይ አይደለም። ለሀገር የሚያስቡ ወገኖች ሲነሱ ወደመግባባት ልንገባ እንችላለን። ብሄራዊ እርቅን፣ ብሄራዊ መግባባትን፣ የሽግግር መንግስትን፣ ወይም ፍትሃዊ ዲሞክራሲያዊ ምርጫም ከተደረገ በዚያ መንግስት በኩል ወደዚህ ስምምነት መግባት እንችላለን። ዋናው በስምምነቱ ይዘቶች ላይ መስማማቱ ነው።….ባህላዊ አንድነት ስንል ቡድኖች ያላቸውን ሀብት፣ ቋንቋ፣ ታሪክ፣ ቁሳዊና መንፈሳዊ እሴቶች በማዋጣት ለኢትዮጵያዊነት በመሰዋት አንድነትን ማሳየትና የአንድነትን ሰንሰ ሃሳብ በዚህ መሰረት ላይ ማቆም ማለት ነው። (ገጽ 115)
አዲሱ የሀገር አስተዳደር ቅርጽ (የፈደራል መንግስት)
ደራሲው ስለፈደሬሽን በመጽሐፉ ዉስጥ ሰፊ ሽፋን ሰጥቷል። የመጽሃፉ ቅሱም(ኢንዴክስ) እንደሚያመለክተው ከሌሎች ነጥቦች የበለጠ ተደጋግሞ የተነሳ ጉዳይ መሆኑን ያሳያል። በተለይ በአብዛኛው በአሃዳዊነት እና ቀጥሎም በብዙ ችግሮች ተተብትቦ ዛሬ በመተግበር ላይ ባለ የብሄር ፈደሬሽን ስር ለኖረ ህዝብ ስለፈደሬሽንና ኮንፈደሬሽን ትክክለኛ ምንነት መጻፉ
ተገቢ ነው። ደራሲው ከብሄር ፈደራሊዝም ወደ ሳይንሳዊ ፈደራሊዝም እንሸጋገር በሚል በነደፈው አዲስ የሀገር አስተዳደር ቅርጽ ላይ የፈደራል አስተዳደርን አመልክቷል-የፈደራል መንግስትና የባህል ፈደራሽን በሚል።
የባህል አስተዳደር-ቡድኖች ሁሉ የባህል ተወካዮቻቸውን አዋጥተው የሚመሰርቱት የባህል አርበኞች ቤት ነው። ይህ ቤት ወደታች ይደራጅና የቡድኖችን ባህልና ቋንቋ ሲንከባከብ ይኖራል። ተጨባጭ የሆኑና ያልሆኑ ባህሎችን መንከባከብ፣ የሰላምና እርቅ ጉዳዮችን ይሰራል፣ ብሄራዊ ሙዚየሞችን ይንከባከባል፣ የኬር ቴከር ሀልስፊነትን ይወስድዳል፣ አስፈላጊ ከሆነም የምርጫ አስፈጻሚ ይሆናል። የፍትህ አካሉ በሁለቱ አስተዳደሮች የጋራፎ ተሳትፎ የሚቆም ነጻ ተቋም ይሆናል።
ፖለቲካዊ አስተዳደር መንግስት- በህዝብ ተወካዮች የሚመሰረት አስተዳደር ነው። (ገጽ 127- ሰንጠረዥ)
እንከኖች
የጎላ እንከን ፈልጌ ማግኘት አልቻልኩም፤ ስለአልታየኝ ወይም የስራው ጥራት ክፍተትን ስለአልፈጠረ ሊሆን ይችላል። ዐቢይ እንከን ሲጠፋ ጊዜ የሚከተሉትን ማንሳት ፈለግሁ።
1) ደራሲው በቀረጸው አዲሱ የአስተዳደር ቅርጽ፣ የፍትህ አካሉ በሁለቱ አስተዳደሮች የጋራ ተሳትፎ የሚቆም ነፃ አካል መሆኑ ተገልጿል። አዲስ አደረጃጀት ይመስላል። በተለይ ከአደረጃጀትና ከምርጫ መርህና አፈጻጸም አንጻር እንዴት ሊሰራ እንደሚችል በሚያሳይ መልክ ሃሳቡ የበለጠ ዘርዘርና ሰፋ ብሎ ቢወጣ።
2) እንዲሁም በባህል ፈደሬሽንና በፈደራል መንግሥቱ መካከል ሊኖር ስለሚችለው የጎንዮሽ ግንኙነት ቢዳብር። ሀሳቡ አዲስ እንደመሆኑ አንባቢ የራሱን ግምት ከሚወስድ ይልቅ የሀሳቡ አመንጭ ጥናት ያደረገበት ስለሆነ ደራሲው ይበልጥ ቢያዳብረው መልካም ይመስለኛል።
3) በቅሱም ውስጥ ማርቲን ሉተር የሚለው ስም በታሪክ ውስጥ ታላቅ ስፍራ ያላቸውን ሰዎች የሚያጣቅስ ነው። በመጽሀፉ ውስጥ የሁለቱም ስራ በተለያየ ቦታ የተጠቀሰ ስለሆነ፣ ማርቲን ሉተር ኪንግ እና ጀርመናዊው የፕሮተስታንት መስራች የሆነው ማርቲን ሉተር ተለይተው የየራሳቸው ማጣቃሻ ገጽ ቢኖራቸው መልካም ነው ብየ አስባለሁ።
መደምደሚያ
ይህ መጽሀፍ እጅግ ጠቃሚና አስተማሪ ነው። እኔ በጣም ወድጀዋለሁ። መነበብ፣ መጠናት ያለበት ነው። ከያዘቸው ቁም ነገሮች አንጻር በማናቸውም ጊዜ በመረጃ ምንጭነት ሊያገለግል ስለሚችል በጥንቃቄ በቤትም ሊቀመጥ የሚገባ ነው ብየ አምናለሁ። በተለይ ደራሲው ያስተዋወቀው በስምምነት ላይ የተመሰረተ ባህላዊ አንድነት-ስባአ (Conventional Cultural Unity) የተሰኘው አዲስ ንድፈ-ሀሳብ በስፋት ሊታወቅ፣ ውይይት ሊደረግበት፣ ሊዳብርና ሀገሪቱ ዛሬ በብሄር ፖለቲካ ችግር ተተብትባ በመንታ መንገድ ላይ ቆማ መፍትሄ በምትሻበት ጊዜ መፍትሄ አፈላላጊዎች ሊጠቀሙበት፣ ሊመረምሩት የሚገባ ጉዳይ ነው።
የኢትዮጵያዊነት መንፈስ ተዳክሞ አገር በክልል የብሄር/ብሄረሰብ ፓለቲካ እየተናጠች ባለበችበትና ግጭት በበዛበት፣ ባልተለመደ ሁኔታ ለአንድ ኢትዮጵያዊ ከብሄር ክልሉ ወጥቶ ሌላው ክልል መሄድም ሆነ መኖር የባእድነት ስሜት በፈጠረበት፣ መጠራጠርና አለመተማመን ሰፍኖ የአንድ አገር ህዝብ አንድነት በላላበት፣ እንዲሁም ፍቅርና ሰላም በታጣበት በአሁኑ ወቅት ከብሄርተኝነት ይልቅ ብሄራዊነት እንደ አንዱ ዓይነተኛና ዋነኛ መፍትሄ ሆኖ የተንጸባረቀበት የደራሲ ገለታው መጽሐፍ እጅግ ጠቃሚ ሆኖ ያገለግላል ብየ አምናለሁ።
አመሰግናለሁ።