May 8, 2018
ከስዩም ተሾመ
ከድብደባ ወደ ማባበል፥ ማታለልና ማስፈራራት
መደበኛ የወንጀል ምርመራ ዘዴ በእውነትና ዕውቀት ላይ የተመሠረተ ነው፡፡ የስቃይ ምርመራ (Torture) ደግሞ በጉልበትና ፍርሃት ላይ የተመሠረተ ኢ-ሰብዓዊ ድርጊት ነው፡፡ በማዕከላዊ እስር ቤት የሚገኙ መርማሪዎች ለብዙ አመታት በተጠርጣሪ እስረኞች ላይ ስቃይና ድብደባ የፈፀሙት ከእውነትና ዕውቀት ይልቅ በጉልበትና ፍርሃት ስለሚያምኑ መሆኑ እርግጥ ነው፡፡
እነዚህ መርማሪዎች የስቃይ ምርመራ እንዳይፈፅሙ ተከልክለዋል፡፡ ነገር ግን፣ የካበቱት የሥራ በጉልበትና ፍርሃት ላይ የተመሠረተ ነው፡፡ የስቃይ ምርመራ ስለተከለከለ መርማሪዎቹ ሳይንሳዊ የምርመራ ዘዴ ተግባራዊ ያደርጋሉ ማለት አይደለም፡፡ ሰዎችን በማሰቃየት የተካኑ ሰዎች በአንድ ግዜ ተነስተው በእውነትና በዕውቀት የሚመሩ ሊሆኑ አይችሉም፡፡ ከዚያ ይልቅ ከድብደባና ማስፈራራት ወደ ማባበልና ማታለል ይሸጋገራሉ፡፡ ይህ በማዕከላዊ በነበረኝ ቆይታ በተግባር የታዘብኩት እውነታ ነው፡፡
የማዕከላዊ መርማሪዎች በዕውቀትና መረጃ ላይ ተመስተው ምርመራ ከማካሄድ ይልቅ ተጠርጣሪ እስረኞችን በዘዴ ማባበልና ማታለል ይጀምራሉ፡፡ ለዚህ ደግሞ የራሳቸውን የፈጠራ ድርሰት በመፃፍ ተጠርጣሪው “በምርመራ የሰጠሁት ቃል ነው” ብሎ እንዲፈርም ያባብሉታል፡፡ በመቀጠል ተጠርጣሪ እስረኛው ፍርድ ቤት ሲቀርብ በማስረጃነት የሚቀርብበትን ቃል “ከፈረምክ በነፃ ትለቀቃለህ” እያሉ በሃሰት ለማታለል ይሞክራሉ፡፡
በመጨረሻ ወደ ትክክለኛ ማንነታቸው በመመለስ በእስረኛው ላይ የስነ-ልቦና ጫና መፍጠርና በግልፅ ማስፈራራት ይጀምራሉ፡፡ ይህ ሁሉ ተጠርጣሪዎች የእነሱ ባልሆነ ቃል ላይ እንዲፈርሙ ለማድረግ ነው፡፡ በህጉ መሠረት፣ ተጠርጣሪ እስረኛው የእሱ ባልሆነ ቃል ላይ መፈረም ይቅርና ከነጭራሹ ቃሉን ያለመስጠት መብት አለው፡፡ ይህን በደል በዛሬው ዕለት የማዕከላዊ መርማሪዎች በመ/አለቃ አይዳ አሌሮ ላይ ፈፅመውታል፡፡
ውቤ እና አይዳ
መ/አለቃ አይዳ አሌሮ በብላቴ ወታደራዊ ማሰልጠኛ የአይር ወለድ (Airborne) አሰልጣኝ ነበረች፡፡ በውትድርና ስልጠና የከፍተኛ ማዕረግ ተመራቂ ናት፡፡ እኔ ማዕከላዊ እያለሁ ውቤ ወርቁ ከተባለ ወጣት ጋር ተይዛ ከመጣች በኋላ ጣውላ ቤት ቁጥር 1 ገባች፡፡ ወደ “09” ወይም “ሸራተን” ከተዘዋወርን በኋላ የጎንደር ተወላጅ የሆነው ውቤ ወርቁ የታሰሩበን ምክንያትና የተፈፀመባቸውን ግፍ አጫውቶኛል፡፡
መ/አ አይዳ የውትድርና ሥራዋን በመልቀቅ በጎንደር ከተማ የራሷን ቢዝነስ (ቡና ቤት) ለማቋቋም ጥረት እያደረገች ነበር፡፡ አቶ ውቤ ደግሞ በሁመራ ከተማ የራሱን ቡና ቤት ለመክፈት እየተንቀሳቀሰ ነበር፡፡ የራሳቸውን ቢዝነስ ለመክፈት ዕቀድ ያላቸው ሁለቱ ግለሰቦች የሁለቱም ወዳጅ በነበረ ግለሰብ አማካኝነት ይገናኙና በአጋርነት (Partnership) የራሳቸውን ቡና ቤት በሁመራ ከተማ ለመክፈት ይስማማሉ፡፡ በመጋቢት ወር መጀመሪያ ሁመራ ከሚገኝ አንድ ሆቴል ቁርስ እየበሉ ሳሉ በደህንነት ሰዎች ይታፈናሉ፡፡ በመጀመሪያ ከሁመራ ወደ መቀለ ከዚያ ደግሞ ወደ አዲስ አበባ በመውሰድ ከላይ እንደጠቀስኩት በማዕላዊ ይታሰራሉ፡፡ በመጨረሻም ከእኛ ጋራ ወደ “ሶስተኛ” የተዘዋወሩ ሲሆን አሁንም ድረስ በእስር ላይ ይገኛሉ፡፡
ውቤ ወርቁ በሁመራ ከተማ ከተያዘ በኋላ በደህንነት ሰዎች ኢ-ሰብዓዊ የሆነ ግፍና በደል ተፈፅሞበታል፡፡ በራሱ አንደበት እንደ ነገረኝ፣ ደህንነቶቹ ልብሱን በማስወለቅ ፎቶ አንስተውታል፡፡ “ይህንን ፎቶ ለወዳጅ ዘመዶችህ በመላክ መሳቂያ-መሳለቂያ እናደርግሃለን!” በማለት ዝተውበታል፡፡ ከዚያ በተጨማሪ በአሰቃቂ ሁኔታ ተደብድቧል፡፡ በመ/አ አይዳ አሌሮ ላየ ተመሣሣይ በደልና ኢሰብዓዊ ድርጊት ሊፈፅሙባት እንደሚችሉ መገመት ይቻላል፡፡
በመ/አ አይዳ እና ውቤ ወርቁ ላይ የሚፈፀመው ግፍ በዚህ ብቻ አላበቃም፡፡ አሁንም የማዕከላዊ መርማሪዎች ራሳቸው በፃፉት የፈጠራ ድርሰት ላይ “ቃላችን’ ብላችሁ ፈርሙ!” በማለት ተጠርጣሪዎቹን በመጀመሪያ ማባበል፣ ቀጥሎ ማታለል፣ አሁን ደግሞ ጭራሽ ማስፈራራት ላይ ናቸው፡፡ ለምሳሌ መ/አ አይዳ አሌሮ በተደጋጋሚ በነፃ ትፈቺያለሽ ብለው ለማባበልና ለማታለል ጥረት አድርገው ሳይሳካላቸው ቀርቷል፡፡ በዛሬው ዕለት ደግሞ ከአንዴም ሁለቴ ወደ መርማሪው ቢሮ በመጥራት “ይህን ‘ቃሌ ነው’ ብለሽ ካልፈረምሽ በፀረ-ሽብር ህጉ ተከስሰሽ 25 አመት ትከናነቢያለሽ” በማለት አስፈራርተዋታል፡፡ በመሆኑም በራሷ ላይ ማስረጃ ሆኖ በሚቀርብ የፈጠራ ድርሰት ላይ በግድ እንድትፈርም ማስፈራራያና የስነ-ልቦና ጫና እየተደረገባት ይገኛል፡፡