“Paulos Gragne” የተባለ ወዳጄ “ያልገባኝ ይፈታ ዘመቻ!” በማለት በፌስቡክ ገፁ ላይ አንድ ፅሁፍ ለጥፎ አነበብኩ፡፡ወዳጄ በፅሁፉ ያነሳው ጥያቄ “እነ አንዳርጋቸው [ፅጌ] ጉዳይ ግን ወደ ጫካ ተመልሰህ ውጋኝ ነው ወይስ እርቅ ፈጽመው ነው የሚፈቱት?” የሚል ነው፡፡ በእርግጥ ብዙዎች እንደ እሱ ጥያቄውን በይፋ ባይጠይቁትም ሃሳቡ በውስጣቸው ሊመላለስ እንደሚችል መገመት ይቻላል፡፡ የፅሁፉን ጭብጥ በግልፅ ለመረዳት የሚከተለውን ቀንጭበን ወስደናል፦
“ሰዎች ጠ/ሚ አብይ ለምን አንዳርጋቸውን አይፈታም በማለት ሲተቹ አያለው፡፡ አንዳርጋቸው ጽጌ የግንቦት ሰባት አንዱ መስራች ነው፡፡ ትግሉን አምኖ ጫካ የገባ ነው፡፡ ጫካ የገባ ደግሞ የህይወት መጸአትነትንም ለመክፈል ነው። ስለዚህ አንዳርጋቸው ጽጌ ልክ እንደ ተራ ሰው ተለቆ ወደ ዜግነት ሀገሩ እንዲመለስ ነው ወይስ ከግንቦት 7 ጋር ተደራድረው ነው? …ሌንጮ ለታ ጫካ ገብቶ ቢያዝ ከሌላው ወታደር ተለይቶ ‘ይለቀቅ’ [ሊባል] ነው? …ነገ ጥዋት ዶ/ር ብራሃኑ [ነጋ] ታፍኖ ከተወሰደ “ይፈታ” ዘመቻ [ሊጀመር] ነው? እነዚህ ሰዎች አገር ውስጥ ካሉት ተቃዋሚዎችና ጋዜጠኞች የተለዪ ናቸው? የሀገር ውስጦቹ ሥራቸውን ወይም ድምጻቸውን ማሰማታቸውን ይቀጥላሉ። እነ አንዳርጋቸውስ በምን መልኩ ይቀጥላሉ?”
ከላይ በተገለፀው መሠረት ፀሃፊው “አንዳርጋቸው ፅጌ ይፈታ” ወይም “Free_Andargachew_Tsige” የሚለው ዘመቻ ፋይዳን አልተረዳም፡፡ እንደ እሱ አገላለፅ፣ በስልጣን ላይ ያለውን መንግስት ከስልጣን ለማስወገድ ግንቦት7 የተባለ አማፂ ድርጅት አቋቁሞ የትጥቅ ትግል የጀመረ ግለሰብን “ይፈታ” ብሎ መጠየቅ አግባብ አይደለም፡፡ ለዚህ ደግሞ ፀሃፊው ከአንዳርጋቸው ፅጌ በተጨማሪ የግንቦት7 መስራችና መሪ ዶ/ር ብርሃኑ ነጋ እና የቀድሞ የኦነግ መሪ ሌንጮ ለታን እንደ ማሳያ ጠቅሷል፡፡ ስለዚህ ዶ/ር ብርሃኑ እና ሌንጮ ለታ እንደ አንደርጋቸው ፅጌ በተመሣሣይ ታፍነው ቢያዙና እነሱ እንዲፈቱ ዘመቻ ቢካሄድ እንደ ጳውሎስ (Paulos) ላሉ ሰዎች አይገባቸውም፡፡
አሁን ያለው መንግስታዊ ስርዓት በህወሓት መሪነት የተመሠረተ መሆኑ ይታወቃል፡፡ ኦነግ ደግሞ የሽሽግር መንግስቱን ከመሰረቱት የፖለቲካ ፓርቲዎች ውስጥ አንዱ ነው፡፡ ህወሓት የትግራይ ህዝብ ነፃ አውጪ ግንባር እንደሆነው ሁሉ ኦነግም የኦሮሞ ህዝብ ነፃ አውጪ ግንባር ነው፡፡ በወቅቱ የህወሓት ሊቀመንበር የነበረው አቶ መለስ ዜናዊ እና የኦነግ ሊቀመንበር የነበረው ሌንጮ ለታ በመንግስታዊ ስርዓቱ ምስረታ ሂደት ላይ የበኩላቸውን ሚና ተጫውተዋል፡፡ ሁለቱ መሪዎች የሚወክሉትን የፖለቲካ ቡድን አቋምና አመለካከት አራምደዋል፣ በተግባር እርምጃ ወስደዋል፡፡ በዚህ ምክንያት በህወሓት እና ኦነግ መካከል ግጭት ተፈጠረ፡፡ በወቅቱ ህወሓት የነበረው የሃይል የበላይነት ተጠቅሞ አሸናፊ ሆነ፡፡ ብዛት ያላቸው የኦነግ ወታደሮች በህወሓት ተገደሉ፣ አመራሮቹም ሀገር ጥለው ኮበለሉ፡፡ በዚህ ኦነግ በ1987ቱ ምርጫ እንዳይሳተፍ ተደረገ፡፡ በመጨረሻም ድርጅቱና አመራሮቹ በአሸባሪነት ተፈረጁ፡፡

በተመሣሣይ የግንቦት7 መስራቾች የሆኑት አቶ አንዳርጋቸው ፅጌ እና ዶ/ር ብርሃኑ ነጋ በሀገራችን ፖለቲካ ውስጥ የራሳቸውን አሻራ ያሳረፉ ሰዎች ናቸው፡፡ ዶ/ር ብርሃኑ ነጋ የኢህአፓ አባል ሆኖ የደርግ ስርዓት ከስልጣን ለማውረድ ታግሏል፡፡ ከቀይ-ሽብር ዘመቻ የተረፉት የኢህአፓ አባላትና አመራሮች ትግራይ ውስጥ በህወሓት ጦር ተገድለዋል፡፡ ዶ/ር ብርሃኑ ወደ ውጪ ሀገር በመሰደድ ከዚህ ጭፍጨፋ ከተረፉት የኢህአፓ አባላት አንዱ ነው፡፡ በ1997 ዓ.ም የህወሓት/ኢህአዴግ መንግስት ነፃና ገለልተኛ ምርጫ ለማካሄድ መንቀሳቀስ ሲጀምር ዶ/ር ብርሃኑ የቅንጅት ከፍተኛ አመራር ሆኖ መጣ፡፡ ኢህአዴግ በምርጫው ሲሸነፍ ዶ/ር ብርሃኑ የአዲስ አበባ ከንቲባ ለመሆን የሚያስችለውን ድምፅ አገኘ፡፡ ነገር ግን፣ ኢህአዴግም የድምፅ ኮሮጆ በመገልበጥ ምርጫውን አጭበረበረ፡፡ ይህን የተቃወሙትን እንደ አንዳርጋቸው ፅጌ እና ዶ/ር ብርሃኑ ነጋ ያሉ የቅንጅት መሪዎች ሰብስቦ አሰረ፡፡
በዚህም ህወሓት/ኢህአዴግ የሃሳብና አመለካከት ልዩነትን ለማስተናገድ የሚያስችል ዴሞክራሲያዊ ባህሪ እንደሌለው በተግባር አሳየ፡፡ በወታደራዊ ጉልበት የያዘውን ስልጣን በትጥቅ ትግል ካልሆነ በስተቀር በሰላማዊ መንገድ እንደማይለቅ በተጨባጭ አረጋገጠ፡፡ ይህን የተረዱት የተረዱት ዶ/ር ብርሃኑ እና አንዳርጋቸው ፅጌ ከእስር እንደተፈቱ ግንቦት7ን በመመስረት የትጥግ ጀመሩ፡፡ ይህን መሠረት በማድረግ ደግሞ የህወሓት/ኢህአዴግ መንግስት ድርጅቱንና መሪዎቹን በአሸባሪነት ፈረጀ፡፡

ስለዚህ በኦነግ/ግንቦት7 እና ህወሓት/ኢህአዴግ መካከል ያለው መሠረታዊ ልዩነት በታሪክ አጋጣሚ የተፈጠረ የሃይል (የጉልበት) የበላይነት ነው፡፡ የህወሓቱ መለስ ዜናዊ የሀገር መሪ፣ የኦነጉ ሌንጮ ለታ ደግሞ አሸባሪ የተባሉት በዚህ ምክንያት ነው፡፡ ዶ/ር ብርሃኑ ነጋ ከንቲባነት ወደ የትጥቅ ትግል መሪነት የተቀየረው በህወሓት/ኢህአዴግ ጭቆና ምክንያት ነው፡፡ አንዳርጋቸው ፅጌ የረቀቁ የፖለቲካና ፍልስፍና መፅሃፍ ከመፃፍ ይልቅ በዱር ጫካ የተንከራተተው በኢትዮጲያ ህዝብ ላይ የተጫነውን የጭቆና ቀንበር ለመጣል ነው፡፡ ስለዚህ የኦነግ እና ግንቦት7 አባላትና አመራሮች በአሸባሪነት የተፈረጁት የህዝብን መብትና እኩልነት ለማረጋገጥ በመንቀሳቀሳቸው ብቻ ነው፡፡
ኦነግና ግንቦት7 በአሸባሪ ድርጅት የተፈረጁበት የፀረ-ሽብርተኝነት አዋጅ በተግባር ዜጎችን የሚያሸብር ነው፡፡ አዋጁ የፀደቀበት መሠረታዊ ዓላማ የሚታወቀው በፀረ-ሽብር ህጉ በተከሰሱ ሰዎች ማንነት ነው፡፡ በፀረ-ሽብር ህጉ የተከሰሱት እነማን ናቸው? እንደሚታወቀው የዚህ ህግ ሰለባ የሆኑት፤ ጋዜጠኞች፣ የፖለቲካ መሪዎችና አባላት፣ የመብት ተሟጋቾች፣ የሃይማኖት መሪዎች፣… በአጠቃላይ የዜጎች መብትና እኩልነት እንዲከበር በአንድም ሆነ በሌላ መልኩ የጠየቁ የህዝብ ልጆች ናቸው፡፡ በአሸባሪነት የተፈረጁት እንደ ኦነግና ግንቦት7 ያሉ ድርጅቶች በፀረ-ሽብር አዋጁ ከተከሰሱት ጋዜጠኞች፣ የፖለቲካ መሪዎችና አባላት፣ የመብት ተሟጋቾች፣ የሃይማኖት መሪዎች፣… ተለይተው አይታዩም፡፡ በአጠቃላይ በፀረ-ሽብር ህጉ የተፈረጁ ድርጅቶችም ሆኑ የተፈረደባቸው ሰዎች የዜጎችን መብትና ነፃነት ለማስከበር ባመኑበት መንገድ የተጏዙ የነፃነት ታጋዮች ናቸው፡፡
ከላይ በተገለፀው መሠረት ሌንጮ ለታ፣ መለስ ዜናዊ፣ ዶ/ር ብርሃኑ ነጋ እና አንዳርጋቸው ፅጌ የአንድ ዘመን ትውልድ ናቸው፡፡ ሁሉም በየፊናቸው የፖለቲካ ድርጅት መሪዎች ናቸው፡፡ በሌንጮ ለታ የሚመራው ኦነግ በ1987ቱ ምርጫ ለመሳተፍ ዝግጅት እያደረገ ሳለ በህወሓት/ኢህአዴግ በተፈፀመበት ሸርና አሻጥር ከምርጫው ራሱን እንዲያገል ተደርጏል፡፡ በተመሣሣይ በ1997ቱ ምርጫ በህወሓት/ኢህአዴግ በፈፀመው የምርጫ ማጭበርበር ምክንያት ቅንጅት ለአንድነትና ለዴሞክራሲ ፓርቲ ውጤቱን ውድቅ እንዲደርግ አስገድዶታል፡፡ ስለዚህ የኦነግ እና ቅንጅት/ግንቦት7 መሪዎች በሀገራችን ነፃና ገለልተኛ የሆነ ዴሞክራሲያዊ ምርጫ ለማድረግ፣ የህዝብ ድምፅና የህግ የበላይነት እንዲከበር ጥረት አድርገዋል፡፡
በተቃራኒው የህወሓት/ኢህአዴግ መንግስት የህዝብ ድምፅ አጭበርብሯል፣ ይህን የተቃወሙ ዜጎችንና የፖለቲካ መሪዎችን ለእስራት፣ ሞትና ስደት ዳርጏል፡፡ በዚህ መሠረት በሰላማዊ የፖለቲካ ትግል ዴሞክራሲያዊ ስርዓት መገንባት፣ በዚህም የዜጎችን መብትና እኩልነት ማስከበር እንደማይቻል በግልፅ አረጋግጧል፡፡ በመሆኑም የፖለቲካ ለውጥ የሚመጣው በህዝባዊ አመፅና በትጥቅ ትግል አማካኝነት ብቻ እንደሆነ አሳይቷል፡፡ ነገር ግን፣ ህወሓት/ኢህአዴግ ምርጫና አማራጭ አሳጥቶ ወደ ትጥቅ ትግል እንዲመለስ ያደረገውን ኦነግ፣ እንዲሁም የትጥቅ ትግል እንዲጀምር ያደረገውን ግንቦት7 በአሸባሪነት ፈረጀ፡፡
በመሠረቱ ህወሓት/ኢህአዴግ የህዝብን ድምፅ ባያጭበረብር ወይም የህግ የበላይነትን ቢያረጋግጥ ኖሮ ኦነግና ግንቦት7 የትጥቅ ትግል አይጀምሩም ነበር፡፡ ይህንንም ኦነግ በሽግግር መንግስቱ በመሳተፍ፣ የግንቦት7 መሪዎች ደግሞ በ1997ቱ ምርጫ በተግባር አሳይተዋል፡፡ ሰላማዊ የፖለቲካ መስመርን ትተው የትጥቅ ትግል የጀመሩበት መሠረታዊ ምክንያት የህወሓት/ኢህአዴግ አምባገነንነትና አጭበርባሪነት ነው፡፡ የትግላቸው ዓላማ ይህን አምባገነንና አጭበርባሪ መንግስት ከስልጣን በማስወገድ የዜጎችን መብትና እኩልነት ማረጋገጥ ነው፡፡ ስለዚህ እነዚህ የፖለቲካ ቡድኖች የትጥቅ ትግል የጀመሩት ህወሓት/ኢህአዴግ በፈፀመው ስህተት፣ የትግላቸው የመጨረሻ ውጤትም ይህን ስህተት ማስተካከል ነው፡፡ በአጠቃላይ ከምክንያት-ውጤት ተያያዥነት አንፃር የኦነግና ግንቦት7 ትግል ትክክል ነው፡፡
የፀረ-ሽብር አዋጁ መሠረታዊ ዓላማ ከላይ በተጠቀሰው ትክክለኛ የትግል መስመር የተሰማሩ የፖለቲካ ቡድኖችንና ግለሰቦችን በአሸባሪነት ለመፈረጅ፣ ለማሰርና ለማሰቃየት ነው፡፡ በመሆኑም የአዋጁ ፋይዳ ዜጎች የህወሓት/ኢህአዴግን የተሳሳተ መስመርን በግድ እንዲቀበሉ፣ የኦነግና ግንቦት7 ትክክለኛ መስመርን በፍቃዳቸው እንዳይቀበሉ ለማድረግ ነው፡፡ ለዚህ ደግሞ የፀረ-ሽብር ህጉ ተከሳሾችን መመልከት ብቻ በቂ ነው፡፡ በፀረ-ሽብር ህግ ከተከሰሱ ሰዎች ከ3ቱ ውስጥ 2ቱ “የኦነግ ወይም የአርበኞች-ግንቦት7 አባል ናችሁ” ወይም “ድጋፍ ታደርጋላችሁ” የተባሉ ናቸው፡፡ በአጠቃላይ የፀረ-ሽብር አዋጁ ዓላማና ፋይዳ ዜጎች የመብትና እኩልነት ጥያቄ እንዳያነሱ፣ ፍትህና የህግ የበላይነት እንዳይረጋገጥ ማድረግ ነው፡፡
በዚህ አዋጅ መሠረት በአሸባሪነት የተፈረጁ የፖለቲካ ድርጅቶች፣ የተፈረደባቸው አመራሮችና አባላት የሚታገሉት ለህዝብ መብትና እኩልነት፣ ፍትህና የህግ የበላይነት ነው፡፡ እነዚህ ሰዎች የሚታገሉት ለግል ጥቅም እንዳይሆን አብዛኞቹ በራሳቸው የተሻለ ህይወት መኖር የሚችሉ ናቸው፣ “የስልጣን ጥማት” እንዳይባል ከትጥቅ ትግል ይልቅ ህወሓት/ኢህአዴግን በመጠጋት ብቻ የከፍተኛ ስልጣን ባለቤት መሆን ይችላሉ፡፡ ስለዚህ የትግላቸው መነሻና መድረሻ የህዝብ መብትና ነፃነት ነው፡፡ በመሆኑም እነዚህ ታጋዮች ትክክለኛ የህዝብ ልጆች ናቸው፡፡
በህዝብ ላይ ፍርሃትና ሽብር የሚፈጥሩት የመንግስት ወታደሮች እንጂ የኦነግ ወይም የግንቦት7 ታጋዮች አይደሉም፡፡ ስለዚህ “አሸባሪ ድርጅት” ተብሎ መፈረጅ ያለበት ዜጎችን በአደባባይ የሚገድለው የህወሓት/ኢህአዴግ መንግስት እንጂ ይህን ግድያ ለማስቆም የሚታገሉት አይደሉም፡፡ በእነዚህ ሰዎች ሥራና ተግባር የሚሸበረው መንግስት እንጂ ዜጎች አይደሉም፡፡ “አሸባሪ” ተብለው የተፈረጁትና የተፈረደባቸው መንግስትን በማሸበራቸው እንጂ ህዝብ ስለፈራቸው አይደለም፡፡ በመሆኑም ለህወሓት/ኢህአዴግ “አሸባሪ” ሲሆኑ ለእኛ ደግሞ “የአሸባሪዎች አሸባሪ” ናቸው፡፡ የህወሓት/ኢህአዴግ አመራሮችና ደጋፊዎች እንደ አንዳርጋቸው ፅጌ፥ ዶ/ር ብርሃኑ ነጋ፣ ሌንጮ ለታ እና የመሳሰሉ መሪዎችን “አሸባሪዎች” እና “ወንጀለኞች” ቢሏቸውም በህዝብ ዘንድ “ጀግኖች፥ የህዝብ ልጆች” ናቸው፡፡

በዚህ መሠረት “አንዳርጋቸው ፅጌ ይፈታ!” የሚለው ዘመቻ ትርጉምና ፋይዳ ምን እንደሆነ መረዳት ሆነ ማስረዳት ቀላል ነው፡፡ “አንዳርጋቸው ፅጌ ይፈታ!” ሲባል “ጀግናው የህዝብ ልጅ ይፈታ!” ማለት ነው፡፡ የታሰው “ወንጀለኛ” ሳይሆን የአሸባሪዎች አሸባሪ ጀግና ነው፡፡ አንዳርጋቸው አንድ ግለሰብ ሳይሆን የብዙ ሚሊዮኖች መሪ ነው፡፡ ስለዚህ የታሰረው ግለሰብ ሳይሆን ህዝብ ነው!!