የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ በአንድ ወቅት ስለፈጣን የሕዝብ ብዛት ጥያቄ ቀርቦላቸው ነበር፡፡ እርሳቸውም ሲመልሱ የሚወለዱት ሕፃናት እግር ይዘው እንጂ ሆድ ብቻ አይደለም በማለት ብዙዎችን ፈገግ የሚያስኝ መልስ ሰጥተው ነበር፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለጥያቄው ቀጥተኛ መልስ ለመስጠት ፈልገው እንጂ ችግሩ አሳሳቢ መሆኑ ተዘንገቷቸው አይመስልም፡፡ እርሳቸው ይህን ይበሉ እንጂ የሕዝብ ብዛት ብቻውን ሀብት መሆን አይችልም፡፡ የሕዝብ ብዛትን እንደ ሀብት (Resource) መጠቀም የሚቻለው በአገሪቱ ካለው አብዛኛው ሕዝብ የተማረና የሠለጠነ ባለሙያ ሆኖ በምርት ሂደት ላይ ተሰማርቶ አምራችና ሸማች ዜጋ ሲሆን ብቻ ነው፡፡ በአገሪቱ ውስጥ ያለው አብዛኛው ሕዝብ ተገልጋይ ማለት (dependent) ከሆነ ሀብት በመሆን ፋንታ አገልግሎት ፈላጊ ይሆንና በአገሪቱ የምርት ሂደት ላይ ተጽዕኖ ሊያመጣ ይችላል፡፡

የማዕከላዊ ስታትስቲክስ መረጃ በኢትዮጵያ የሕዝብ ብዛት በፍጥነት እየጨመረ መምጣቱን ያሳያል፡፡ እ.ኤ.አ በ1990ዎቹ መጀመሪያ የኢትዮጵያ ሕዝብ ብዛት 48 ሚሊዮን ብቻ ነበር፡፡ በ2013 እ.ኤ.አ 88 ሚሊዮን ሕዝብ እንደሚኖርባት ይገመት ነበር፡፡ በአሁኑ ጊዜ ኢትዮጵያ ብዙ ሕዝብ የሚኖርባት የአሕጉሪቱ አገር ሆናለች፡፡ ባለፉት ሁለት ዐሥርት ዓመታት የኢትዮጵያ ሕዝብ ብዛት በእጥፍ ጨምሯል፡፡ በዚህ ጊዜ ማለትም ከ1990-2013 ባሉት ዓመታት በዓመት 3.6 በመቶ ዕድገት አሳይቷል፡፡

በፍጥነት የሚጨምር የሕዝብ ብዛት በአንድ አገር የኢኮኖሚ ዕድገት ላይ ያለው አሉታዊና አዎንታዊ ጎን ለረጅም ጊዜ አከራካሪ የሆነ ጉዳይ ነው፡፡ የሥነ ሕዝብና የምጣኔ ሀብት ምሁራን በጉዳዩ ዙሪያ የሚያነሱት ሁለት ገዢ ሐሳቦች አሉ፡፡ የመጀመሪያው የሕዝብ ብዛት በፍጥነት መጨመር ለኢኮኖሚ ዕድገት እንቅፋት ሊሆን አእንደሚችል ይጠቅሳሉ፡፡ በተቃራኒ ወገን ያሉት የሕዝብ ብዛት መጨመር ለኢኮኖሚ ዕድገት ጉልህ እመርታ እንዳለው ይጠቁማሉ፡፡ በአሁኑ ወቅት በሥነ ሕዝብና በምጣኔ ሀብት ዙሪያ ማዕከላዊ የክርክር፣ ጭብጥ ሆኖ ብቅ ያለው በሕዝቦች የዕድሜ ደረጃ (መዋቅር) እና በምጣኔ ሀብታዊ ዕድገት መካከል ስላላው ትስስር ነው፡፡

የማኅበረሰብ ሳይንስ ባለሙያዎችና የሥነ ሕዝብ ምሁራን የምርምር ዝንባሌያቸውን ያደረጉት በሕዝቦች የዕድሜ መዋቅር ወይም እርከን (Age structure)፣ የውልድት ምጣኔ (Birth rate) እንዲሁም የሞት ምጣኔ (mortality rate) መቀነስና መጨመር ሊያስከትል የሚችለውን የኢኮኖሚ ዕድገትና ውድቀትን ነው በማለት ኬሊ ጄ የተሰኙ ምሁር፤ “The population debate in historical perspective: Revision Revised (2001)” በተሰኘ ጥናታቸው ይጠቅሳሉ፡፡ የሕዝብ ቁጥር በፍጥነት መጨመር በነፍስ ወከፍ ገቢ ዕድገት ላይ የሚያመጣው አሉታዊ ውጤት አለ፡፡ ነገር ግን ይህን ዓይነቱን አሉታዊ ገጽታ ለመቀነስ እያደገ ከሚመጣው ሕዝብ ብዛት ውስጥ አምራች የሆነውን ኃይል በመጨመር ወደ አዎንታዊ ውጤት መቀየር እንደሚቻል የምጣኔ ሀብት ምሁራን ይጠቁማሉ፡፡ አምራች የሆነውን ኃይል በመጨመርና ምቹ የሥራ ከባቢን በመፍጠር ቁጠባንና ኢንቨስትመንት በማሳደግ የሕዝብ ብዛት ሊያስከትለው የሚችለውን ተግዳሮት ወደ መልካም አጋጣሚ መቀየር ይቻላል እንደባለሙያዎቹ ገለጻ፡፡

“ዲሞግራፊክ ዲቨደንድ” እና “ዲሞግራፊክ ትራንዚሽን”
***
“ዲሞግራፊክ ትራንዚሽን” በወሊድ ምጣኔና በሰዎች ህልፈተ ሕይወት መጠን ላይ ተመርኩዞ የሚሰላ የሕዝብ ዕድገት መጠንን የሚያሳይ ጽንሰ ሐሳብ ሲሆን ይህም የወለድ ምጣኔ ከፍ ያለ ሆኖ የሞት መጠን ዝቅ ያለ ሲሆን ከፍተኛ የሕዝብ ዕድገት ምጣኔ እንደሚኖርና የወሊድ ምጣኔና የሕዝብ ሞት መጠን ሁለቱም ዝቅተኛ ወይም ከፍተኛ ሲሆኑ የሕዝብ ዕድገት ምጣኔ ዝቅ እንደሚል የሚገልጽ ሐሳብ መሆኑን ዶ/ር እሸቱ ጉርሙ በአዲስ አበባ የኒቨርስቲ የሥነ ሕዝብ ትምህርት ክፍል መምህር ያስረዳሉ፡፡

የወሊድ ምጣኔ (Fertility rate) ከፍተኛ ሲሆን በርካታ ሕፃናት የሚወለዱ ከመሆናቸው አንጻር አገልግሎት ፈላጊ (dependent population) የሕዝብ መጠን ከፍ ያለ ሆኖ በኢኮኖሚ ዕድገቱ ላይ ጫና የማሳደር ክስተት ይስተዋላል፡፡ በአንጻራዊ መልኩ ደግሞ የወሊድ ምጣኔ ዝቅተኛ ሲሆን የሚወለዱ ሕፃናት ቁጥር አነስተኛ የአገልግሎቱ ፈላጊ (dependent Population) ቁጥር ዝቅተኛ ስለሚሆን ለኢኮኖሚያዊ ዕድገት አስተዋጽዖ የማድረግ ሁኔታን ይፈጥራል፡፡ አገልግሎት ፈላጊ ሲባል በምርቱ ሂደት ላይ ያልተሰማሩትን የኅብረተሰብ ክፍል በተለይም ዕድሜያቸው ከ15 ዓመት በታች በጡረታ ዕድሜ ክልል ማለትም ከ60 ዓመት በላይ የሚገኙትን አረጋውያንን ማለት ነው፡፡ እነዚህ የኅብረተሰብ ክፍሎች በምርት ሂደት ተግባር ላይ ሣይሆን ሕፃናቱ በትምህርት መቅሰም ተግባር ላይ የተሰማሩ በመሆናቸውና አረጋውያንም ደግሞ በጡረታ ዕድሜ ክልል ውስጥ የሚገኙ በመሆናቸው ተገልጋይ እንጂ አምራች ዜጋ ሆነው ለኢኮኖሚ ዕድገት በቀጥታ የሚያበረክቱት አስተዋጽዖ ባለመኖሩ ተገልጋይ ወይም ተረጂ (dependent) ተብለው እንደሚጠቀሱ ዶ/ር እሸቱ ይጠቁማሉ፡፡

የወሊድ ምጣኔና የሞት መጠን መቀነስ ለሕዝብ ዕድገት ዝቅተኛ መሆን አስተዋጽዖ የማበርከታቸውን ያህል የኑሮ ሁኔታ ማደግና የጤንነት አጠባበቅ ሥርዓት መሻሻል ደግሞ የአረጋውያን ዕድሜ እንዲጨምርና በጡረታ ዕድሜ ክልል ያሉ ነዋሪዎች ቁጥር እንዲበረክት ያደርጋል የሚሉት የሥነ ሕዝብ ምሁሩ ይህም ለሕፃናት ዕድገትና ትምህርት ይውል የነበረው በጀት ለአረጋውያን እንክብካቤና የጤንነት አጠባበቅ መሟላት ለሚያስፈልገው ወጪ እንዲመደብ ሊያስገድድ እንደሚችል ይገልጻሉ፡፡

“ዲሞግራፊክ ዲቨደንድ” በአንድ አገር ውስጥ በሕዝብ ዕድገት መጠን ለውጥ ሳቢያ የሚከሰት ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ ያለው ተግባር ሲሆን ይህም የተገልጋዩ/የተረጂው ቁጥር ማለትም የሚወለዱት ሕፃናት ቁጥር ሲቀንስና የአረጋውያን ቁጥር ጨምሮ ቀደም ሲል ለሚወለዱት ልጆች ጤንነትና ትምህርት ይውል የነበረው በጀት ለአረጋውያን እንክብካቤና ክትትል ሲውል በፊት አገሪቱ ካላት በርካታ አምራች ዜጋ ልታገኘው የምትችለው ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ ነው፡፡ ይህም ማለት አብዛኛው የአገሪቱ ሕዝብ ወጣት አምራችና፣ ሸማች ዜጋ ሲሆን ኢኮኖሚውን በስፋት ስለሚያንቀሳቅሰው አገሪቱ ለምርታማነትና ለኢንቨስትመንት አመቺ ሁኔታ ላይ እንድትገኝ ያደርጋታል፡፡ ሆኖም ግን ወጣቱና ሁሉም ዜጋ ሁሉም በቂ ገቢ ሊያስገኝለት በሚችል የሥራ ዘርፍ ላይ መሠማራት ይኖርበታል የሚሉት ዶ/ር እሸቱ ክስተቱ ጤናማ የተማረ ንቁና ቀልጣፋ አምራች ወጣቶችን በብዛትና በጥራት ወደ ሥራው ማሰማራት እንደሚያስችል ይናገራሉ፡፡

ይህ ክስተት በዘመናት መካከል ለጥቂት ጊዜ ብቻ በተለይም አጋጣሚው ሲፈጠር ሊኖር የሚችለው ከ30-40 ዓመታት ብቻ ሲሆን አገራት ጥንቃቄ በተመላበት ዕቅድ ተመርተው በተለይም የሥነ ሕዝብና የኢኮኖሚ ዕድገት ሁኔታው ሊጣጣም በሚችል መልኩ ካልመሩት ክስተቱ ሳይጠቅም ሊያልፍ ይችላል፡፡ በዚህ ረገድ ደቡብ ኮርያ፣ ታይላንድ፣ ቻይና፣ ሲንጋፖርና ሌሎች የመካከለኛው ምሥራቅ አገራት በሰፊው ተጠቃሚ መሆናቸውን የጠቆሙት ዶክተር እሸቱ እንደ ብራዚል፣ ሜክሲኮ ያሉ የላቲን አሜሪካ አገራት በ“ዲሞግራፊክ ትራንዚሽን” ውስጥ ቢያልፉም ከዲሞግራፊክ ዲቪደንድ እምብዛም ተጠቃሚ ሊሆኑ አለመቻላቸውን ይናገራሉ፡፡ ምክንያቱም በአገራቱ የታየው ዲሞግራፊክ ትራንዚሽን በበቂ ሁኔታ ለዲሞግራፊክ ዲቨደንድ አመቺ ባለመሆኑ የአጋጣሚው ተጠቃሚ ሳይሆኑ ጊዜው አልፎባቸዋል፡፡ “ዲሞግራፊክ ቦነስ” ከዚሁ ጋር ተያይዞ የሚነሳ ሐሳብ መሆኑን የጠቀሱት ዶ/ር እሸቱ በሕዝብ ዕድገት ምጣኔ ለውጥ ሳቢያ በአንድ አገር ኢኮኖሚያዊ ዕድገት ላይ የሚታይ ፈጣንና ጠንካራ ለውጥ በመሆኑ አገራት ወጣትና አምራች ዜጎችን በስፋት በማቀፍ የሚያስመዘግቡትን ፈጣን የኢኮኖሚ ዕድገት የሚያመላክት መሆኑንም አስታውሰዋል፡፡

ትክክለኛና የተቀናጀ የሥነ ሕዝብና የኢኮኖሚ ዕድገት ፖሊሲ ከሌለ የአምራችነት የዕድሜ ደረጃ ድርሻን ብቻ ማሳደግ የዲሞግራፊ ዲቪደንድ ተጠቃሚነትን ለማግኘት የሚያበቃ ዋስትና ሊሆን አይችልም የሚሉት የዘርፉ ምሁራን እንዲያውም ለወጣቱ ምቹ ሁኔታ ካልተፈጠረ ሥራ አጥነት ይባባሳል፣ ወንጀል ይበራከታል፣ የፖለቲካ አለመረጋጋትም በመፍጠር አገራቱን ወዳልተፈለገ አቅጣጫ ሊወስዳቸው ይችላል በማለት ስጋታቸውን ይገልጻሉ፡፡

ዶ/ር እሸቱም ይህንን ሐሳብ ይጋራሉ፡፡ ፈጣን የሕዝብ ዕድገት (Rapid Population Growth Rate) በአንድ አገር ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ዕድገት (Socio economic development) ላይ ብርቱ አሉታዊ ተጽዕኖ ሊያሳድር ይችላል፡፡ ፈጣን የሕዝብ ዕድገት ምጣኔ የሚኖረው በርካታ ሕፃናት ሲወለዱና በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ በአጠቃላይ በአገሪቱ የሕዝብ ቁጥር ላይ የሚጨመረው ተቀላቢና አገልግሎት ፈላጊ ብዛት በርካታ ሲሆን ነው፡፡ ይህ ደግሞ እናቶች ወደ ምርት ተግባር ሳይሆን ሕፃናቱን ወደመንከባከብ እንዲያዘነብሉ የሕክምና ተቋማት የነፍሰጡር እናቶችንና የሕፃናቱን ጤንነት እንዲንከባከቡ ትምህርት ቤቶች ደግሞ በየዓመቱ ወደ ትምህርት ተቋም ለሚገቡ አዳዲስ ተማሪዎች የመማሪያ ቦታና መምህራን እንዲያዘጋጁ ገበሬዎች ደግሞ ለተጨማሪ ሕፃናት ቀለብ እንዲያመርቱ ስለሚያደርግ አብዛኛውን የአገሪቱ ምጣኔ ሀብት ለፍጆታ እንዲውል ያስገድደዋል፡፡ በዚህም ምክንያት ለኢንቨስትመንት የሚውለውን የአገሪቱ ሀብት ውስን ይሆንና የልማት ተግባራት በብዛትና በፍጥነት እንዳያከናውኑ ያደርጋል በማለት የችግሩን አሳሳቢነት በጥልቀት ይፈትሻሉ፡፡

ፈጣን የኢኮኖሚ ዕድገት ያስመዘገቡ አገሮች ማለትም እንደ ኮርያ፣ ታይዋን፣ ቻይናና የመሳሰሉት አገራት የኢኮኖሚ ዕድገት ከመጀመራቸው በፊት የወሊድ መጠኑን የመቀነስ እርምጃ ወስደዋል፡፡ በዚህ ምክንያት በየዓመቱ የሚወለዱ የልጆች መጠን ለመቀነስ በመቻላቸው ለፍጆታ (Consumption) ማለትም ለጤና አገልግሎት ለትምህርትና ለመኖሪያ ቤቶች ለቀለብ የሚውለውን ወጪ በመቀነስ ያንን ሀብት ለኢንቨስትመንት ለማዋል የላቀ የቴክኖሎጂ የኢንዱስትሪ ሽግግር ለማከናወን መቻላቸውን ዶ/ር እሸቱ ያስረዳሉ፡፡

የአገር ኢኮኖሚን ኢንቨስት በማድረግ ልማትን ለማከናወን የሚረዳ ምቹ ሁኔታ ከሌለ ኢንቨስትመንትን ለማካሄድ የግድ ወደ ብድርና እርዳታ ጥያቄ መገባት ይኖርበታል፡፡ ይህም በተለያዩ መስኮች ወደፊት መከፈሉ ስለማይቀር ምንም እንኳን የኢኮኖሚ ዕድገት ቢኖርም በሕዝቡ አኗኗር ላይ ለውጥ ለማምጣት ረጅም ጊዜ የሚወስድ ይሆናል የሚሉት ዶ/ር እሸቱ ፈጣን የሕዝብ ብዛት የሚያስከትለውን ተያያዥ ችግሮች ይዳስሳሉ፡፡

የኢትዮጵያ የሕዝብ ብዛት ከተፈጥሮ ሀብት እና ምጣኔ ሀብት ዕድገት ጋር ይተሳሰራል፡፡ ከዓመታት በፊት በአገሪቱ 48 ከመቶ የነበረው የደን ሽፋን እጅግ በከፍተኛ ሁኔታ ተመናምኗል፡፡ ይህም የሕዝቡ ብዛት በተፈጥሮ ሀብት ላይ ያመጣው ጫና በመሆኑ ምጣኔ ሀብቱን እንደሚጎዳው ይታወቃል፡፡ ሕዝብ በየጊዜው የሚጨምር ከሆነ የተፈጥሮ ሀብት መጎዳቱ አይቀርም፡፡ በሕዝብ ብዛት የተነሣ የተፈጥሮ ሀብትን ለመቀራመት የሚደረግ ሩጫ የተፈጥሮ ሀብቱን አደጋ ውስጥ ሊከተው እንደሚችል የአካባቢ ጥበቃ ባለሙያዎች ያስረዳሉ፡፡

ባለፉት ዐሥርት ዓመታት ኢትዮጵያ ከፍተኛ የሆነ የአካባቢ ጥበቃ መዛባት ገጥሟታል፡፡ ለዚህም በዋናነት እንደ ምክንያት የሚጠቀሰው በሕዝብ ብዛት የተነሣ የሚከሰተው ችግር ነው፡፡ ከሥነ ምሕዳር መዛባት ጋር በተያያዘ የመሬት ለምነትና በቂ ምርት የመስጠት አቅም መቀነስ ዋነኛው ነው፡፡ በርካታ የኢትዮጵያ ሕዝብ በገጠር የሚኖርና የኢኮኖሚ መሠረቱም ግብርና በመሆኑ መሬቱ በተደጋጋሚ በመታረሱ ምርታማነቱ አደጋ ላይ ወድቋል፡፡ የሕዝብ ብዛቱ በየጊዜው በፍጥነት በመጨመሩ (2.6-3) የተለያዩ ዛፎችና ተክሎች ለማገዶነት እና ለሌሎችም ግብዓቶች በመዋላቸው የአገሪቱ የደን ሽፋን ከ40 በመቶ ወደ 4 በመቶ አዘቅዝቋል፡፡

ዛፎችን ለተለያዩ ግብዓቶች መቁረጥና የመመንጠር መጠኑም በዓመት ወደ መቶ ሺሕ ሄክታር ደርሷል፡፡ የደኖች መመናመን የአፈሩን ንጥረ ነገር በጎርፍ እንዲታጠብ በማድረግ አፈሩ ለምነቱን እንዲያጣና ምርታማነቱ እንዲቀንስ እያደረገ መሆኑን ካርላ ቤደሊ እና ሌሎች “Population growth and environment in Ethiopia (2001)” በተሰኘ ጥናታቸው የችግሩን አሳሳቢነት ለመጠቆም ሞክረዋል፡፡

የሕዝብ ብዛት፣ የምግብ ዋስትና እና የተፈጥሮ ሀብት
***

በኢትዮጵያ በተደጋጋሚ ከተከሰተው ድርቅ በተጨማሪ በከፍተኛ ፍጥነት የሚያድገው የሕዝብ ቁጥርና የአካባቢ መራቆት ችግር ላለፉት ሦስት ዐሥርት ዓመታት ኢትዮጵያ ላጋጠማት አስከፊ የምግብ እጥረት ዋነኛ ምክንያት ነው፡፡ ከ1960ዎቹ ጀምሮ አገሪቱ እያደገ ከመጣው ሕዝቧ ጋር ራሷን በምግብ የመቻል ፈተናን ለማለፍ እንዳልቻለች ምሁራኑ ከላይ በተጠቀሰው ጥናታቸው አካተውታል፡፡

ፈጣን የሕዝብ ዕድገት በማኅበረ ኢኮኖሚያዊ ለውጥ ላይ ብቻ ሳይሆን በተፈጥሮ ሀብት አጠቃቀም በምግብ ዋስትና መረጋገጥ በአካባቢ ደኖችና የእርሻ ይዞታዎች ላይ ብርቱ ተጽዕኖ ያሳድራል፡፡ ለምሳሌ እያንዳንዱ ዜጋ በልቶ ማደር ስላለበት ዛፎች በብዛት ተቆርጠው የሰብል ማሣ እንዲበረክት፣ የግጦሽ መሬቱ እንዲመነምን የምግብ ዋስትና እንዲንኮታኮትና ታዳሽ ያልሆኑ የኃይል ምንጮች እንዲነጥፉ ሊያደርግ ይችላል፡፡ ፈጣን የሕዝብ ዕድገት በዚህ ረገድ የሚኖረውን አሉታዊ ተጽዕኖ ለመቋቋም በቴክኖሎጂ የታገዘ ልማት ማካሄድ ተገቢ ቢሆንም አብዛኛው የአገሪቱ ሀብት ሕፃናትን ለመንከባከብና ለማስተማር መዋል ስላለበት የመዋዕለ ንዋይ እጥረት ለኢንቨስትመንትና ለቴክኖሎጂ ሽግግር የሚረዳ፤ የማኅበረሰብና ኢኮኖሚያዊ ዕድገት ተግባራት በስፋት እንዳይከናወኑ ስለሚያደርግ በርካታ የሕዝብ ቁጥር ያላት አገር በተለይም አብዛኛው ተገልጋይ (dependent) ከሆነ የተፈጥሮ ሀብት ከማሟጠጥ፣ አካባቢ ከመራቆት፣ የምግብ ዋስትና መረጋገጥ በጥያቄ ምልክት ውስጥ እንዲገባ ያደርጋል በማለት ፈጣን የሕዝብ ቁጥር መጨመር ሊያስከትል የሚችለውን ተያያዥ ችግር ዶ/ር እሸቱ በስጋት ያዩታል፡፡

የተፈጥሮ ሀብትን በአግባቡ ለመጠቀም የአካባቢ መራቆትን ለመከላከልና የምግብ ዋስትናን በበቂ ሁኔታ ለማረጋገጥ ሰከን ያለ የሕዝብ ዕድገት ምጣኔ ያስፈልጋል የሚሉት ደ/ር እሸቱ ይህ ማለት በአንድ አገር ውስጥ በየዓመቱ በወሊድ ምክንያት የሚጨምረው የሕዝብ ብዛት ከኢኮኖሚያዊ ዕድገቱ ጋር የተመጣጠነ በተለይም ኢኮኖሚያዊ ዕድገቱን የሚያግዝ ከሆነ የተፈጥሮ ሀብት ከመመናመን ይልቅ ይበልጥ ሊለሙ፣ የአካባቢ ሁኔታ ከመራቆት ይልቅ ይበልጥ በደን ሊሸፈኑና፣ የምግብ ዋስትናን ሊረጋገጥ ይችላል፡፡

የሕዝብ ብዛት የተፈጥሮ ሀብት ያራቁታል የሚለውን ሐሳብ በተቃራኒው የሚያዩት አሉ፡፡ ከእነዚህ አንዱ ዶ/ር ወልዳይ አምኃ ናቸው፡፡ የሚወለደው ሰው ሁሉ ሆድ ብቻ ይዞ አይመጣም፤ የሚሠሩ እጆችና የሚያስብ አእምሮ ጨምሮ ይመጣል የሚለውን የጠቅላይ ሚኒስትሩን ሐሳብ ይጋራሉ፡፡ ስለዚህ ሕዝብ ቁጥሩ ቢጨምርም የተሻለ አሠራርና ፈጠራ ሊያመጣም እንደሚችል መረዳት ይገባል የሚል ሐሳብ አላቸው፡፡ የሰው ሀብት ልማት ላይ እንዲሁም ምጣኔ ሀብት ማሳደግ ላይ ትኩረት ከተደረገ ሕዝብ ብዛት በራሱ መንገድ ቁጥጥር ስለሚደረግበት ስጋት ሊሆን አይችልም በማለት ያስረዳሉ፡፡

ሕዝብ ሲበዛ መሠረተ ልማት ከማሟላት አኳያ ችግር በመፍጠር ውጫዊና ውስጣዊ ስደት እንዲባባስ በማድረግ ሥራ አጥነትን በማስፋፋት እንዲሁም በምጣኔ ሀብቱ ላይ የጥገኞችን ቁጥር ያበዛዋል፡፡ ከፖለቲካ አኳያም አለመረጋጋትና ሁከት ሊቀስቀስ ይችላል፡፡ ስለዚህ ፈጣን የሕዝብ ዕድገት ከፈጣን ምጣኔ ሀብት ዕድገት ጋር ተዋሕዶ ካልሄደ አደጋው የከፋ እንደሚሆንና በአገር ላይ ከፍተኛ የሆነ ስጋት ሊፈጥር እንደሚችል የዘርፉ ምሁራን ይጠቁሙና፤ ይህንን ለማስታረቅ በጠንካራ የሥነ ሕዝብና የኢኮኖሚ ፖሊስ የታገዘ የተቀናጀ አሠራር በአገር ደረጃ ሊሠራ እንደሚገባ ያስገነዝባሉ፡፡

ኢትዮጵያ ከፍተኛ የወሊድ መጠንን በመቀነስ በተለይ ወጣት ሴቶችን በትምህርት በማብቃት የወሊድ ቁጥርን ለመቀነስ ያስችላል፡፡ ወጣት ሴቶች እየተማሩ በሄዱ ቁጥር ካልተማሩት በተሻለ የቤተሰብ ምጣኔን እንደሚገነዘቡ ይታወቃል፡፡ በተጨማሪም የትምህርት ተደራሽነትንና ጥራትን፣ ግብርናውን የማዘመን አሠራርን መሠረት ልማት ዝርጋታውን፣ አካባቢ ጥበቃን፣ ጾታዊ እኩልነትን አካቶ ቤተሰብ ምጣኔን ላይ በመሥራት ይህንንም በጠንካራ የሥነ ሕዝብ ፖሊሲ በመደገፍ ፈጣን የሕዝብ ዕድገት ሊያመጣ የሚችለውን የወሊድ መጠን መቀነስ እንደሚቻል የዓለም ባንክ በ2011 ያወጣው ጥናት ይጠቁማል፡፡

የአንድ አገር ማኅበረ ኢኮኖሚያዊ ዕድገት የሚለካው በአገሪቱ ሕዝቦች ላይ በሚያመጣው የአኗኗር ሁኔታ (Quality of Life) ለውጥ መሆን እንዳለበት መታወቅ ይኖርበታል፡፡ ኢኮኖሚያዊ ዕድገት (Economic Growth) በሕዝብ አኗኗር ሁኔታ ላይ ሊከሰት ይችላል፡፡ ለምሳሌ አንድ የዓለም አቀፍ ኩባንያ (Multinational Corporation) በአንድ አገር ውስጥ ኢንቨስትመንት ካካሄደ በአገሪቱ ውስጥ የሚመረተውን ምርትና የሚሰጡትን አገልግሎቶች (Goods and services produced in a country during the year) በከፍተኛ መጠን ሊያሳድግ እንደሚችል የሥነ ሕዝብ ምሑሩ ዶ/ር እሸቱ ያስገነዝባሉ፡፡ ይህም እንደ ኢኮኖሚ ዕድገት መለኪያ የሚወሰደውን (Per capita income) ሊያሳድገው ይችላል፡፡ ነገር ግን ከምርቱ ሂደቱ የተገኘው ትርፍና ኢንቨስትመንት የዋለው ዋናው ገንዘብ ወደ መጣበት አገር እየተመለሰ የሚሄድ ከሆነ፤ አገሪቱ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ዕድገት (Socio-economic transformation) በማሳየት ረገድ ቀርፋፋ ልትሆን እንደምትችልና የአንድ አገር የሕዝብ ዕድገት ምጣኔና የምጣኔ ሀብት እድገት የተመጣጠነ መሆን እንደሚኖርበት ያስረዳሉ፡፡

የተመጣጠነ የምጣኔ ሀብት የሕዝብ ዕድገት ማለት በአገሪቱ ውስጥ የሚኖረው ማኅበረ ኢኮኖሚያዊ ዕድገት በሕዝቦች አኗኗር ላይ መሠረታዊ ለውጥ በሚያመጣ ሁኔታ የተቃኘ ሲሆን ነው፡፡ ይህም ማለት አንድ ሕፃን ሲወለድ በቅድሚያ የምግብና የጤንነት አገልግሎት በበቂ ሁኔታ ማግኘት ይኖርበታል፡፡ ከፍ እያለ ሲሄድም የትምህርት አገልግሎት ይፈልጋል፡፡ ቀጥሎም ለራሱና ለሚመሠርተው ሕዝብ ቀለብና ተዛማጅ ወጪዎች መሸፈኛ በቂ ክፍያ የሚያገኝበት ሥራ ያስፈልገዋል፡፡ ከዚያም የመኖሪያ ቤትና ወደ ሥራ ሄዶ የሚመላለስበት የትርንስፖርት አገልግሎትና መንገድ ይፈልጋል፡፡ የተሟላ ኑሮ ለመኖር ደግሞ ሌሎች ተዛማች አግልግሎቶች በበቂ ሁኔታ መቅረብ ይኖርባቸዋል፡፡ ይህንን ሁኔታ የተጣጣመ ለማድረግ ለ1% ሕዝብ ዕድገት 3% የኢኮኖሚ ዕድገት እንደሚያስፈልግ በዚህ ዘርፍ የተሰሩ ጥናቶች ያስረዳሉ፡፡

ይህም ማለት ለምሳሌ አንድ አገር የሕዝብ ምጣኔ በ2.5% በየዓመቱ ቢያድግ ይህቺ አገር መሠረታዊ የሕዝቦችዋን ፍላጎት ለመሟላት ቢያንስ ቢያንስ ኢኮኖሚያዊ በ7.5% በየዓመቱ ማደግና የዚህ ዕድገት ተጠቃሚዎችም ሕዝቦቿ መሆን እንዳለባቸው ይነገራል፡፡ በዚህ ረገድ የተሸለ ማኅበረ ኢኮኖሚ ዕድገትና የተሻሻለ የአኗኗር ሂደት ለማምጣት በቅድሚያ የሕዝብ እድገት ምጣኔን መቀነስ ዋነኛ አማራጭ ተደርጎ መወሰዱን የሚናገሩት ዶ/ር እሸቱ እንደ ጃፓን ያሉ አገራት የተሻሻለ ዕድገት ማስመዝገብ የቻሉት የሕዝብ እድገት መጠናቸውን ወደ 1 ፐርሰንት በማውረድና ኢኮኖሚያቸውን ደግሞ 10 ፐርሰንት በላይ በማድረስ መሆኑን ታሪክ ይነግረናል፡፡ ይህ ሁኔታ ደግሞ ጃፓን የራሷን ኢኮኖሚ በሰፊው በአገሪቷ ላይ ኢንቨስት ለማድረግ መቻሏንና የኢንቨስትመንቱ ተጠቃሚ እንድትሆን አድርጓታል ይላሉ፡፡

ልማትን ለማካሄድ በቅድሚያ የሚቆጠብ ኢኮኖሚያዊ የአመራረት ሥርዓት ሊኖርና የሚቆጠበ ገንዘብም ተመልሶ በኢንቨስትመንት መልክ በሰፊው ወደ ሥራ የሚገባበት ሁኔታ መመቻቸት ይኖርበታል፡፡ በአንዳንድ አገሮች በውጪ ዕርዳታ በብድርና በውጪ ካፒታል ፍሰቶች በመከናወን ላይ የሚገኙት የልማት እንቅስቃሴዎች ለኢኮኖሚው ማደግ የሚያበረክቱት አስተዋጽዖ ቀላል ባይሆንም ብድሩ ሊከፈልና ወደ አገር ውስጥ የገባው የካፒታል መጠን ተመልሶ ወደ መጣበት አገር ሲመለስ የሕዝቡን ኑሮ ለማሻሻልና መሠረታዊ ለውጥ ለማምጣት ረዘም ያለ ጊዜ መውሰዱ የግዴታ ይሆናል፡፡

ለዚህም ነው በአንዳንድ አገሮች የሚታየው የኢኮኖሚ ዕድገት ሥር ነቀል የሆነ የኑሮ ሁኔታ ለውጥ በሕዝቡ ዘንድ ሳያሳይ የሚቀረውና ኅብረተሰቡ ከዕድገቱ ተጠቃሚ የማንሆነው የሚል ጥያቄ እንዲያቀርቡ የሚያደርገው፡፡ ስለዚህም ፈጣን የሕዝብ ዕድገት መጠንን መቀነስ አገራት በራሳቸው ኢኮኖሚ እንደተማመኑ መሠረታዊ የኑሮ ለውጥ (Quality of Life) እንዲያመጡና አገራዊ ሀብት በቅድሚያ ለቁጠባ በቀጣይነትም ለሰፊ ኢንቨስትመንት እንዲመጣ ያደርጋል፡፡ ይህም የተፈጥሮ ሀብት በአግባቡ ጥቅም ላይ እንዲውል የምግብ ዋስትና እንዲረጋገጥና የአካባቢ ልማት እንዲፋጠን የሚረዳ በመሆኑ አገራቱ የሕዝቡ ዕድገት መጠን ከማኅበረሰባዊ ኢኮኖሚያዊ ዕድገት ጋር ተጣጥሞ እንዲሄድ ብርቱ ጥረት ማድረግ እንደሚጠበቅባቸው ዶ/ር እሸቱ ይመክራሉ፡፡

የውልደትና የሞት ምጣኔ
***

የሕዝብ ብዛትን የሚወስኑ ሦስት ነገሮች አሉ፡፡ ውልደት፣ሞትና ስደት ናቸው፡፡ ከእነዚህ ውስጥ በኢትዮጵያ ለሕዝብ ብዛት መጨመር የሚጠቀሱት የውልደትና የሞት ምጣኔ ሲሆኑ፤ የስደት ምጣኔ ብዙም ግምት ውስጥ የማይገባ መሆኑን ከበደ ተስፋዬ “Theoretical consideration of Demographic variable in development programs (1994)” በተሰኘ ጥናታቸው ይጠቅሳሉ፡፡ አያይዘውም የውልደት ምጣኔው ከ1970-1990 ከፍተኛ ሲሆን፤ ከዚያ በኋላ ባሉ ዓመታት ግን መቀነሱን ይገልጻሉ፡፡ የ2000 የኢትዮጵያ የሥነ ሕዝብና ጤና ጥናት መረጃ እንደሚያሳየው የውልደት ምጣኔው አንዲት ሴት ስድስት ልጆች ትወልድ ነበር፡፡ ባለፈው ዐሥር ዓመት ምጣኔው ወደ ግማሽ ልጅ መቀነስ ተችሏል፡፡ ይህም ቢሆን አሁንም ከፍተኛው የወሊድ ምጣኔ እንደሆነ ከበደ ተስፋዬ ከላይ በተጠቀሰው ጥናታቸው ያስረዳሉ፡፡ በቅርቡ የማዕከላዊ እስታቲክስ ኤጀንሲ የ2008 ዓ.ም. የሥነ ሕዝብ ጤና ጥናት ውጤትን ይፋ አድርጓል፡፡ በጥናቱ ከተካተቱት ዋነኛው የሥነ ሕዝብና የጤና ጥናት ውጤቶች መካከል በፈረንጆች 2000 ላይ 5.5 ልጅ በአማካይ የነበረው የአንዲት ኢትዮጵያዊ እናት የውልደት መጠን አሁን በጥናቱ ወደ 4.6 ልጅ በአማካይ መውረዱ ታውቋል፡፡ ይህም የሆነበት ምክንያት በእናቶች ጤናና በቤተሰብ ምጣኔ ላይ በተሠራው ውጤታማ ሥራ መሆኑ ተጠቅሷል፡፡

የሕዝብ ብዛት በራሱ ሀብት መሆኑን የሚጠቅሱት አካላት ሰፊ የገበያ አማራጭና ገበያ የመሳብ እምቅ ሀብት መሆኑንም ጨምረው ያስረዳሉ፡፡ አገሪቱ ከ30 ዓመታት በታች በርካታ ሕዝብ ስለሚኖሩባት ወጣቱም ለልማቱ ጠቃሚ ስለሚሆን የሕዝብ ብዛቱ በራሱ ስጋት እንደማይሆን ይሁን እንጂ ቁጥጥር ሊደረግበት እንደሚገባ ይጠቁማሉ፡፡ የሕዝብ ብዛትንና የምጣኔ ሀብት ዕድገት እንዲሁም ከተፈጥሮ ሀብት ጋር ያለውን ዝምድና በማጣጣም የሕዝብ ብዛት ስጋት ከመሆኑ አስቀድሞ ሌሎች አማራጮችን መጠቀም እንደሚቻል ይከራከራሉ፡፡

የኢትዮጵያ ማይክሮ ፋይናንስ ተቋም ዳይሬክተር ዶ/ር ወልዳይ አምኃ የሕዝብ ብዛት ሥጋትም ነው፤ ሥጋትም አይደለም የሚል መከራከሪያ አላቸው፡፡ የሕዝብ ብዛት ስጋት ቢሆን ኖሮ ቻይና ትጠፋ ነበር፤ ነገር ግን ሕዝቧን ከሞላ ጎደል ለመመገብ፤ የሥራ ዕድልም ለማስፋፋትና ወጣቶቿን በሥራ ለማሳተፍ ችላለች፡፡ ስለዚህ ሕዝብ ኃይል ነው፡፡ ኢትዮጵያ በምሥራቅ አፍሪካ ጠንካራ ኢኮኖሚ እየገነባችና እየፈጠረች ያለች አገር ናት፡፡ ነገር ግን አሁን ባለው ሁኔታ ኢኮኖሚው በሚፈለገው ደረጃ ባለመድረሱ የሥነ ሕዝብ ፖሊሲው ላይ ትኩረት ተደርጎ ሊሠራ እንደሚገባ ዶ/ር ወልዳይ ያስረዳሉ፡፡ ይህ ካልሆነ ግን ሥራ አጥነቱ በተስፋፋበትና በተለይ በከተሞች በምግብ ራስን መቻል ባልተቻለበት ሁኔታ ሕዝቡም አምራች ኃይል ሳይሆን ቁጥሩ ብቻ ካደገ አገሪቱ አስቸጋሪ ፈተና ውስጥ እንደምትወድቅ ዶ/ር ወልዳይ ያስረዳሉ፡፡

በኢትዮጵያ ከግብርና ወደ ኢንዱስትሪ የሚደረገው ሽግግር አዝጋሚ ነው፡፡ ዶ/ር ወልዳይም በዚህ ይስማማሉ፡፡ ወደ ኢንዱስትሪ በሚደረገው ሽግግር አገሪቱ ተኝታ ነበር፡፡ አሁን ጅምሮች አሉ፡፡ ለውጡ በአንድ ጊዜ የሚመጣ አይደለም፡፡ የግል ባለሀብቱ ወደ ማንፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪው በሚፈለገው መጠን ሊገባ አልቻለም፡፡ መንግሥት ይህንን ዘርፍ በተለያዩ ማበረታቻዎች በማገዝ ድጋፍ በማድረግ አብሮ መሥራት አለበት፡፡ የግሉን ክፍለ ኢኮኖሚ ማመን ያስፈልጋል፡፡ መተማመን ሲኖሮ ነው ውጤታማ መሆን ብሎም በፍጥነት እያደገ ለመጣው ወጣት ኃይል የሥራ ዕድል መፍጠር የሚቻለው በማለት ዶ/ር ወልዳይ በፍጥነት እያደገ ላለው የሕዝብ ቁጥር ኢንዱስትሪው የሚከፍተውን የሥራ ዕድል ይጠቁማሉ፡፡

ባለፈው ዓመት በኦሮሚያ እና በአማራ ክልሎች የታየው የሕዝብ እምቢተኝነት በተለይም የወጣቶች ተቃውሞ መንግሥትንም፣ አገርንም፣ ሕዝብንም ብዙ ዋጋ አስከፍሏል፡፡ መንግሥት ችግሮችን በማፈን አድበስብሶ የመሄድ አቅጣጫ ሲከተል መቆየቱ ለተባባሰ እምቢተኛነቱ በር ከፋች ሆኗል፡፡ ችግሮችን ቀድሞ በማየትና መፍትሔ ከመስጠት ይልቅ የማዳፈን እርምጃ የሚከተለው ገዢው መንግሥት እንደ ፈሊጥ የያዘው “ተሐድሶና ጥልቅ ተሐድሶ” የሚል ትችት በተደጋጋሚ ይነሣበታል፡፡ ለኢኮኖሚው ዕድገትና ሁሉን ዐቀፍ አካታች ለሆነ ልማት ፖለቲካዊ መግባባቶች ወሳኝ ድርሻ እንዳላቸው ዶ/ር ወልዳይ አስታውሰው ባለፈው ዓመት የተከሰተውንም ችግር መመርመር የሚያስፈልገው ከምንጩ መሆን እንዳለበት ይናገራሉ፡፡

የኢኮኖሚ ዕድገቱ ሁሉንም የኅብረተሰብ ክፍል አካቷል? በየጊዜው ቁጥሩ እየጨመረ ላለው ለወጣቱ የሥራ ዕድል ለመፍጠር አስችሏል? ኢንቨስትመንትን በበቂ ሁኔታ ለመሳብ ተችሏል? የሚሉት መሠረታዊ ጉዳዮች መልስ ሊያገኙ እንደሚገባም ጠቁመዋል፡፡ ስለዚህ ያለፈው ችግር መንግሥትን በፖለቲካዊም ሆነ በኢኮኖሚያዊ አካሄዱ ላይ ቆም ብሎ እንዲያስብ ሊያደርገው እንደሚችል ዶ/ር ወልዳይ አምኃ አስረድተዋል፡፡

በኢትዮጵያ ፈጣን የሕዝብ ዕድገት በኢኮኖሚ ዕድገቱ ላይ የራሱ የሆነ ጫና መፍጠሩ ቢታወቅም ለኢኮኖሚ ዕድገት መቀጨጭ ብቸኛ ምክንያት አይደለም፡፡ ሌሎች ምክንያቶች ማለትም የማይክሮ ኢኮኖሚ ሁኔታው፣ የተቋማት ተጠያቂነት እና ግልጽነት፣ የቴክኖሎጂ ፖሊስና የአቅም ግንባታ መጠናከር ግምት ውስጥ መግባት እንደሚኖርባቸው ካሣሁን ዓለሙ “Impact of population Growth on the Ethiopian economic performance (2014፣ 44)” በተሰኘው ጥናታቸው ገልጸውታል፡፡

በኢትዮጵያ ፈጣን የሕዝብ ዕድገት በኢኮኖሚ ዕድገቱ ላይ የራሱ የሆነ ጫና መፍጠሩ ቢታወቅም ለኢኮኖሚ ዕድገት መቀጨጭ ብቸኛ ምክንያት አይደለም፡፡ ሌሎች ምክንያቶች ማለትም የማይክሮ ኢኮኖሚ ሁኔታው፣ የተቋማት ተጠያቂነት እና ግልጽነት፣ የቴክኖሎጂ ፖሊስና የአቅም ግንባታ መጠናከር ግምት ውስጥ መግባት እንደሚኖርባቸው ካሣሁን ዓለሙ “Impact of population Growth on the Ethiopian economic performance (2014፣ 44)” በተሰኘው ጥናታቸው ገልጸውታል፡፡