“ቋንቋ ሀገራዊ ስሜትን ለመፍጠር ያለው ችሎታ ሀገርን ለመበተንም ጥቅም ላይ ሊውል ይችላል”
***
(፩)
ግርማ ጌታሁን (ዶ/ር)
****
ዶ/ር ግርማ ጌታሁን፣ በብዙዎች ዘንድ የሚታወቁት “የጐጃም ትውልድ በሙሉ ከአባይ እስከ አባይ” በሚል ርዕስ በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ፕሬስ ታትሞ በቀረበው መጽሐፋቸው ነው፡፡ በቅርቡ ደግሞ “የ-ግይጌ ማከያ መዝገበ-ቃላት” በሚል ርዕስ የተዋጣለት ሥራቸውን ሰጥተውናል፡፡ ቀደም ሲል በብሬቲሽ አካዳሚ አማካይነት የታተመውን መጽሐፋቸውን ጨምሮ ሌሎች የታተሙ እና በሕትመት ዝግጅት ላይ የሚገኙ በርከት ያሉ ሥራዎችም አሏቸው፡፡ ባልደረባችን መብራቱ በላቸው በሥራዎቻቸውና በሕይወታቸው ዙሪያ አወያይቷቸዋል፡፡
…………………………..
ስለልጅነትና የትምህርት ጊዜህ ብታጫውተኝ፤ ከቋንቋና ከቃላት ጋር የነበረህን ቀረቤታ ጨምረህ፡፡
………………………….
ዶ/ር ግርማ፡- የተወለድኩት ዐዲስ አበባ ነው፤ ዐሣማ ግቢ/ይልማ በድሉ ዘይት ፋብሪካ እሚባል መንደር ውስጥ፣ በመሳለሚያ እና በራስ ኀይሉ ሜዳ (አኹን አበበ ቢቂላ ስታዲየም) መካከል። የተማርኩት ደግሞ (እስከ 10ኛ ክፍል) መድኀኔዓለም ትምህርት ቤት ነው። በልጅነቴ የዐማርኛ መጻሕፍት አነብብ ነበር። ግን ለቋንቋ እና ቃላት ከሌሎች ልጆች የተለየ ቀረቤታ አልነበረኝም። ግጥም አንብቦ በቃል መያዝ (በተለይ የከበደ ሚካኤልን) እወድድ ነበር፤ የዐማርኛ ቅኔ መፍታትም። ሰዋስው ግን የሚከብደኝ እና የሚያስለቸኝ ትምህርት እንደነበር አልረሳም። ታዲያ ይህ ኹሉ ከሌሎች ልጆች የተለየ የቋንቋ ቀረቤታ እንዳልነበረኝ አመልካች ነው።
በርግጥ ከዐብሮ-አደግ እኩዮቼ ትንሽ ለየት ያለ ጥረት አደርግ ነበር፤ እንግሊዝኛ ለማወቅ የታላቆቼን መማሪያ መጻሕፍት እጠቀም ነበርና። የማላውቃቸውን ቃላት ፍቺዎች ለመረዳት ብዙ ጊዜ አጠፋ እንደነበር ይታወሰኛል። ብዙ ጊዜ ለማላውቀው ቃል የተሰጠው መፍቻ ሌሎች የማላውቃቸው ቃላት ይኖሩታል። የመጀመሪያውን ቃል ፍቺ ለመረዳት የኋላኛዎቹን አስቀድሞ ማወቅ ግድ ነበር። ግን ለዚህ የሚበጅ ትዕግሥት ነበረኝ። ያኔ የቃላት ኀይል እና ሚና፣ ውበት እና አማላይነት ሀዲም አእምሮዬ (subconscious mind) ውስጥ ሥር ሰድደው ይኾን?
በርግጠኛነት መናገር የምችለው ግን ለዐማርኛ ቋንቋ እና ሥነጽሑፍ ልዩ ፍላጎት ያደረብኝ ከየካቲቱ አብዮት ጋር ዴሞክራሲያ፣ አብዮት እና ጎሕ መጽሔት ብቅ ሲሉ ነበር። ያኔ በስውር የሚሰራጩ የጥናት የተቃውሞ ጽሑፎች በረከቱ፤ እንደ “ሰቈቃወ ገባር” ያሉ በቴፕ የተቀረጹ የተቃውሞ ግጥሞችም ነበሩ። የፖለቲካ፣ የምጣኔ-ሀብት፣ የፍልስፍና፣ ወዘተ. ጽንሰ-ሐሳቦችን የሚፈቱ ቃላት ተፈጠሩ። ለነዚህ ቃላት አፈጣጠር ደግሞ የግእዝ ርባና ፍንትው ብሎ ታየ። በለጋ አእምሮዬ ውስጥ በደምሳሳው ይሰቡኝ የነበሩ ከንካኝ ነገሮች – የድኾች እና ድኩማን ጕስቍልና፣ የፍትሕ ዕጦት፣ ወዘተ. – ድንገት እኒህን ዐዳዲስ ቃላት በሚጠቀሙ የተቃውሞ ጽሑፎች ቅጥ እና ኁባሬ (form and coherence) አግኝተው የሥርዐተ-ማኅበር ለውጥ አስፈላጊነት ግንዛቤዬን አዳበሩልኝ። ልቤ ወደ ቋንቋ እና ሥነ-ጽሑፍ ያዘነበለው ያኔ ነው።
……………………………………..
የ-ግይጌ ማከያ መዝገበ-ቃላት ብለህ የሰየምከውን መዝገበ-ቃላት ለማዘጋጀት ምን አነሳሳህ? ፍላጎቱ እንዴት ሊያድርብህ ቻለ?
………………………………………..
ዶ/ር ግርማ፡- ይህ በማከያው መግቢያ ላይ ከሞላ-ጐደል ተመልሷል። ለማከያው ጥንስስ በመኾን ያገለገለ አንድ የቃላት ክምችት ነበረኝ። “የጐጃም ታሪከ-ነገሥት” በመባል የሚታወቀውን የአለቃ ተክለ-ኢየሱስ ዋቅጅራ ጽሑፍ ወደ እንግሊዝኛ በምተረጕምበት ጊዜ ከነፍቺዎቻቸው የመዘገብኳቸው ነበሩ። ብዙዎቹ በዕጥር-ምጥን (concise) መዛግብተ-ቃላት ውስጥ አይገኙም። ከሚገኙትም ጥቂት የማይባሉት በዘወትር ፍቺዎቻቸው ብቻ የተሰጡ ነበሩ። ስብስቡ እያደገ ሲመጣ በመዝገበ-ቃላት ምድን (discipline) ተዘጋጅቶ በማከያ መዝገበ-ቃላት ቢታተም ብዙ ባለሙያዎችን፣ ልሂቅ ተማሪዎችንን እና መምህራንን ሊጠቅም እንደሚችል ዐሰብኩ። አጋጣሚው ቃላቱን በነአለቃ ኪዳነ-ወልድ የሆሄ ጥንቀቃ እድብ ለማቅረብም መልካም እንደሚኾን ታየኝ። ያነሣሡኝ ሐሳቦች እኒህ ነበሩ።
………………………………………
ከዚህ ቀደም በአማርኛ ቋንቋ የተዘጋጁ የተለያዩ መዝገበ ቃላት እንዳሉ ይታወቃል፡፡ ለመሆኑ አንተ ያዘጋጀህው መዝገበ-ቃላት ምን የተለየ ነገር የዟል ማለት ይቻላል? ምን አዲስ ነገር ጨምሯል? አስፈላጊነቱንስ እንዴት ትገልጸዋለህ?
………………………………………..
ዶ/ር ግርማ፡- የኔ ማከያ እንጂ ወጥ እና ሙሉ መዝገበ-ቃላት አይደለም። በተጨማሪ ማከያው ልሳነ-ክልኤ እንጂ ልሳነ-ዋሕድ አይደለም፤ የዐማርኛ ቃላትን በእንግሊዝኛ ስለሚፈታ። ስለዚህ ቃላቱንም መፍቻውንም በዐማርኛ ከሚሰጥ ልሳነ-ዋሕድ መዝገበ-ቃላት በጣም ይለያል።
ጥያቄውን ትንሽ ቀየር አድርጎ ማከያውን ከብጤዎቹ ስለሚለየው ነገር ጥቂት ማለት ይበጅ ይኾናል። ዐማርኛ ቃላትን በእንግሊዝኛ ከሚፈቱ መዛግብተ-ቃላት ጋር ሲነጻጻር ማከያው ለየት የሚያደርጉ ገጽታዎች አሉት። አንደኛው ተካታቾቹን ቃላት በቅድሚያ በሥርውቃላዊ ሆሄ ጥንቀቃ ማቅረቡ ነው፤ (በጽሑፍ እና በንግግር የሚታዩበትን/የሚደመጡበትን ቅርጽ ሳይዘነጋ)። እንዲያ በማድረጉ ድምፀ-ሞክሼ ሆሄያት ያላቸውን ልዩ ርባና – የፍቺ እና የታሪክ ልዩነቶችን የማጕላት መጠነኛ ርባና – አለው። ሠባ እና ሰባ፣ አባይ እና ዐባይ፣ ወዘተ. ውስጥ ያሉ ድምፀ-ሞክሼ ሆሄያት በዐማርኛ ድምፆቻቸው ስለተመሳሰሉ በግድየለሽነት እየተተካኩ መጻፋቸው ካለማወቅ የተነሣ አጕል ልማድ ነው። በዚህ ረገድ ማከያው ግንዛቤ ለመፍጠር በትንሹም ቢኾን ሊረዳ ይችላል።
ማከያው በዘመናዊ ዐማርኛ ውስጥ የተረሱ ቃላትን በማካተት ከአንባቢ ጋር ያስተዋውቃል። እንደ ቅርምዝ፣ በለዲ፣ አባደ ያሉት ቃላት በውሰት የምንጠቀምባቸውን crimson, rose/pink, alienate በቅጡ የሚገልጹ ናቸው። “ሳይቸግር ጤፍ ብድር” እንዳይተረትብን የቃላት ጥሪታችንን እንድናዳብር የሚያበረታታ ይመስለኛል።
ማከያውን ከብጤዎች ለየት ከሚያደርጉ ገጽታዎች አንዱ ከእላዴ ቃላት ምድን ወጣ ብሎ መድበሉን አማላይ እና መዜንው የሚያደርጉ የቦታ ስያሜዎችን (ላፍቶ፣ መካኒሳ፣ ቡሬ)፣ በዘፈን እና የልጆች ግጥሞች ውስጥ የሚደመጡ እንግዳ ቃላትን (ለምሳሌ ቊልቢጥ፣ ጭንብር ቦቃ)፣ ወዘተ. ፍቺዎች የሚያመላክቱ መጠነኛ ቃላት ማካተቱ ነው።
በቃላት አፈታት ረገድም የፍቺ መቀራረብ እና መራራቅን ሊያሳይ የሚረዳ አደረጃጀት አለው። ፍቺዎችን በሚገልጿቸው ስሜቶች እያቧደነ በቍጥር፣ በሆሄያት እና በንኡስ ቍጥሮች ይደረድራል። በዚህ ዐይነት የሚፈታቸውን ቃላትም እስከተቻለ የተሟላ ፍቺ እንዲኖራቸው ይሞክራል፤ ከታተሙ እና ካልታተሙ የጽሑፍ ምንጮች አገባባዊ ምሳሌ እየሰጠ።
………………………………
በኢሕአፓ የፖለቲካ እንቅስቃሴ ውስጥ ተሳትፎ እንደነበረህ ለመረዳት ችያለሁ፡፡ በዚያ ወቅት ይወጡ የነበሩ መጣጥፎች ላይ ቃላት ታርም እንደነበርም ተባራሪ ወሬ ሰምቻለሁ፡፡ እስኪ ከሥነ ጽሑፍና ከቋንቋ አኳያ የነበረህን አስተዋጽዖ ጨምረህ፣ በወቅቱ ስለነበረህ ተሳትፎ ግለጽልኝ፡፡
……………………………..
ዶ/ር ግርማ፡- በ-ኢሕአፓ መራሹ የፖለቲካ እንቅስቃሴ ከብጤዎቼ የላቀ ወይም የጐላ ተሳትፎ አልነበረኝም። በዚያን ዘመን የኹለተኛ ደረጃ ትምህርቴን እንኳ ያላጠናቀቅኹ ለጋ ወጣት ነበርኩ። እንኳን በነዮሐንስ ብርሃኔ እና ጸጋዬ ደብተራው የሚቀርቡ ጽሑፎችን ላርም፣ እነርሱ የሚጽፉትን እንብቤ በቅጡ ለማኰት የሚያስችል እውቀት አልነበረኝም። የሰማኸው “ዋርካ በሌለበት እምቦጮን አድባር የሚያደርጉ” ሰዎች የሚሉትን ነው። መሠረት የለውም።
በርግጥ እንዳቅሚቲ አጽፍ ነበር፤ በወጣት ማኅበር ሥነጽሑፍ ክበብ በምሳተፍ ጊዜ። ለወጣት ሊጉም ቀስቃሽ ጽሑፎች፣ ግጥሞች እና መዝሙሮች አዘጋጅ ነበር። ያኔ ያወቁትን ማሳወቅ (ዕውቀቱ ቍንጽል እና ግልብ ቢኾንም) የወጣቱ “አብዮታዊ ግዴታ” ነበር። አንዳንድ ግጥሞቼን በቃል አጥንተው የያዙ ወጣቶችም አጋጥመውኛል። ግን የኔ ግጥሞች እና ዐጫጭር ልቦለድ-ቀመስ ጽሑፎች ለጎሕ መጽሔት ኅትመት የሚበቁ አልነበሩም።
………………………………..
ቋንቋ ላንተ ምንድን ነው?
……………………………….
ዶ/ር ግርማ፡- በዚህ ጥያቄ ላይ ዐጭር እና የተሟላ መልስ መስጠት አልችልም። እንዲያ ብዬ ከመተው ግን የዋህ እና ደምላላ (general) መልስ ለመስጠት እሞክራለኹ። ቋንቋ ለኔ ታላቅ የመግባቢያ መሣሪያ ነው። በርሱ የሚግባቡ ሰዎችን በሐሳብ፣ በባህል፣ በምናብ፣ በመንፈስ ያስተሳስራል። ዘወትር በሚጠቀሙበት (እንደ አፍ መፍቻ ቋንቋ በሚናገሩት) ሰዎች መኻል ሀገራዊ ስሜት ይፈጥራል። እንዲያ በመኾኑም ኃያል ነው። በደንብ ዐውቆ ለሚጠቀምበት ሰው ቋንቋ ትልቅ ሥልጣን ያጐናጽፋል፤ ሐሳብን/ስሜትን እንደልብ የመግለጽ ሥልጣን፤ ውዥንብርን በማጥራት፣ የግጭት መንሥኤ እና መፍትሔን በማመላከት ሌሎችን የማሳመን ወይም የማግባባት ሥልጣን። ሐሳብን/ስሜትን/ምናብን በቅጡ መግለጽ የሚችል ሰው ደግሞ አለመቻል ከሚያስከትለው ባሕሪያዊ እና ሥነ-አእምሯዊ ችግሮች ራሱን ይጠብቃል። የቋንቋ ክሂል ሐሳብን ከማደራጀት ችሎታ ጋር ተመጋጋቢ ይመስለኛል።
ቋንቋ፣ ለኃያልነት ምንጭ በኾነ ባሕሪው የተነሣ፣ ምቹ የፖለቲካ መሣሪያም ይኾናል። ሀገራዊ ስሜትን ለመፍጠር ያለው ችሎታ ሀገርን ለመበተንም ጥቅም ላይ ሊውል ይችላል። ለዚህ ይመስለኛል ለብሔረተኞች፣ በተለይም ለዘውግ ብሔረተኞች ምቹ እና ተመራጭ መሣሪያ የሚኾነው። እንደ ኢትዮጵያ ባሉ ልሳነ-ብዙ እና ዘውገይር (multiethnic) ሀገራት፣ በተለይ የዜጎች ሰብአዊ እና ዴምክራሲያዊ መብቶች በማይከበሩባቸው ሀገራት፣ ቋንቋ ለዘውጌ ብሔረተኛ እንቅስቃሴ ዐይነተኛ መሣሪያ መኾኑን ዘወትር እናያለን።
……………………………..
በአማርኛ ቋንቋ ከሚነሱ አከራካሪ ነጥቦች አንዱ ድምፀ-ሞክሼ ፊደላትና ድምፀ-ሞክሼ ቃላት በዋናነት ተጠቃሽ ናቸው፡፡ በዚህ ላይ ያንተ አቋም ምንድን ነው? ለምን? ብታብራራልኝ::
……………………………
ዶ/ር ግርማ፡- የዐማርኛ ሥርዐተ-ጽሕፈት በዐዋጅ ወይም ልማድ ባዳበረው እድብ የጸና መደበኛ አጻጻፍ የለውም፤ ኹሉም ሰው እንዳሻው የሚጽፍበትን ልማድ መደበኛ ካላልነው በቀር። ለዚህ ኢመደበኛ ሥርዐተ-ጽሕፈት አንዱ ምክንያት በቋንቋው ፊደል ውስጥ ያሉ ድምፀ-ሞክሼ ሆሄያት ናቸው። ጽሑፉን በንግግር እንደሚደመጠው የመጻፍ ልማድ ደግሞ ሌላ ምክንያት ነው። ተጨማሪ ምክንያቶችም ይኖራሉ። እነዚህ ኹለቱ ግን ዐበይት ይመስሉኛል።
ዐማርኛ ድምፀ-ሞክሼ ሆሄያት ያሉት ከሌሎች ሴማዊ ቋንቋዎች ጋር የተዛመደ ስለኾነ፣ መሠረታዊ የቃላት ሀብቱንም ከነርሱ ስለሚዋረስ፣ ለጽሕፈቱ ደግሞ የግእዝ ፊደልን በማከያ ሆሄያት አምልቶ ስለሚጠቀም ነው። አፋዊ ቋንቋው በኺደት አንዳንድ ድምፆችን ስላጣ ጥንት የተለያየ ድምፅ ወካይ የነበሩ አንዳንድ ሆሄያቱ ዛሬ አንድ ድምፅ የሚወክሉ ድምፀ-ሞክሼ ኾነዋል። የሆሄያቱ ጥንታዊ ሙያ ግን (ማለትም ፍቺ-ዐዛይ መኾናቸው) አልተለወጠም። ሀ እና ሐ የዐማርኛ ድምፃቸው ይመሳሰል እንጂ ፍቺ-ዐዛይ ሙያቸው ይለያያል፤ ቢያንስ ሴማዊ ለኾኑ ቃላት። ስለሚለያይም ‹ምሁር› እና ‹ምሑር› ብለን ስንጽፍ ቃላቱ በ”ሁ” እና “ሑ” የተነሣ የፍቺ ልይዩነትን ሲያስከትሉ እናያለን። ምሁር በዕውቀት ብልጹግ መኾንን ሲገልጽ፣ ምሑር ደግሞ ይቅርታ/ስርየት ማግኘትን ይገልጻል። የ<ሐ> ልዩ ድምፅ ባልጠፋበት ትግርኛ ለምሳሌ ይህ ልዩነት ግልጽ ነው። በግእዝም እንዲሁ። ዐማርኛን ብቻ ለሚያውቅ ወይም በተናጠል ለሚያስብ ሰው ይህ የሆሄያቱ ጥንታዊ የድምፅ ልይዩነት – የፍቺ-ዐዛይነት እየቅላዊ ሚናቸው – ዐይታየውም። ስለማይታየውም ሆሄያትን እንግደፍ/እንቀንስ የሚል ሐሳብ በቀላሉ ይማርከዋል።
ድምፀ-ሞክሼ ሆሄያት ያሏቸውን የፍቺ-ዐዛይነት ሙያ አጥንተን እነርሱን ባግባቡ መጠቀም በዐማርኛ ሥርዐተ-ጽሕፈት ውስጥ የሚታየውን ኢመደበኛነት በከፊል ማሰወገድ ያስችለናል። በጽሑፍ የሚቀርቡ ሐሳቦችን በእቅጩ ለመግለጽ ይረዳናል። ቋንቋው ከሌሎች ሴማዊ ቋንቋዎች ጋር ያለውን ዝምድና ለማየት/ለማሳየት ያበቃናል።
በርግጥ የዐማርኛ ሥርዐተ-ጽሕፈት መደበኛነትን በቅንስ ፊደል ማጽናት ይቻላል፤ ከድምፀ-ሞክሼ ሆሄያቱ አንዳንድ ብቻ አስቀርቶ ሌሎቹን በመግደፍ። ይህ ምርጫ ግን ከላይ የጠቀስኳቸውን የሥርውቃላዊ ሆሄ ጥንቀቃ (orthography) ጥቅሞች የሚያሳጣ ነው። በታሪክ፣ በርቅቀት (sophistiation) እና በውበት የላቀን ፊደል ትቶ የተራቈተ ፊደልን መምረጥ ነው። ቅንሱ ፊደል የመማር ማስተማር ኺደትን ያቀልላል፣ መሃይምነትን ለማጥፋት የሚደረግ ጥረትን ያቀላጥፋል የሚሉ ማመካኛዎች ግን በኔ አተያይ እምብዛ አሳማኝ አይደሉም።
እንዲያም ብዬ ግን ቅንሱ ፊደል ይዘት-ጠበቅ ኾኖ ሥራ ላይ እስከዋለ፣ ደግሞም የምልኡ ፊደል ተኪ እስካልኾነ በዐማርኛ ሥርዐተ-ጽሕፈት ውስጥ ግልጋሎት ሊኖረው እንደሚችል ዐስባለኹ። ለምሳሌ ወግ-ለቀቅ (informal) ጽሑፎችን ለማቅረብ ተመራጭ ፊደል ሊኾን ይችላል። መንግሥታዊ ሰነዶች፣ የሕግ፣ የፍልስፍና፣ የትምህርት፣ ወዘተ. ጽሑፎች በምልኡ ፊደል ሆሄ ጠንቅቅው መጻፋቸው ደንብ ከኾነ፣ ጓደኛሞች የሚለዋወጧቸው ደብዳቤዎች፣ ወዘተ. ደግሞ በቅንሱ ፊደል ይዘት-ጠብቀው ቢጻፉ ጕዳት ያለው አይመስለኝም። ወገኛም ወግ-ለቀቅም ጽሑፎች መደበኛ ኾነው (ሆሄ ጠንቅቀው) እስከተጻፉ ችግር የሚኖር አይመስለኝም። እንዲያውም ሦስተኛ ሥርዐተ-ጽሕፈትም ማከል ይቻላል፤ በዐማርኛ ሌጣ ሆሄያት (ግእዝ በሚባሉት) ብቻ የሚጻፍ። እንዲህ ዐይነቱ ደግሞ በተንቀሳቃሽ ስልክ ለሚላክ ዐጭር ጽሑፍ መጻፊያ ምቹ ሳይኾን አይቀርም።
ቅንሱን ፊደል ብቻ ብንጠቀም መደበኛ የጽሕፈት ሥርዐት በገዛራሱ (automatically) አይፈጠርም። ለምሳሌ በምልኡ ፊደል “ሥርዐት” ብለን የምንጽፈውን ቃል በቅንሱ ፊደል “ስራት፣ ስርአት፣ ስርኣት” ብለን እንደ አባባላችን ልንጽፈው እንችላለን። በሌላ አነጋገር ሠ እና ዐ ግዱፍ የኾኑበቱ ቅንሱም ፊደል ቢኾን ብሂል-መር አጻጻፍን እስከተከተለ መደበኛነት አያገኝም። ችግሩ የድምፀ-ሞክሼ ሆሄያትን አጠቃቀም አለማወቅ ብቻ አይደለም፤ ከብሂል-መር አጻጻፍም አለመላቀቅ እንጂ። ሥርውቃላዊ አጻጻፍ አስፈላጊነቱ ለድምፀ-ሞክሼ ሆሄያት መለያ ብቻ እንደኾነ ማሰብ ስሕተት ነው። ‹አረገ›፣ ‹ግርግዳ›፣ … የሚሉት ብሂል-መር አጻጻፎች ‹አደረገ›፣ ‹ግድግዳ›፣ … በሚሉ አጻጻፎች ሊታረሙ የሚችሉት የቃላቱን ዐምዶች ወይም ሥሮች በማወቅ ነው።
ለማጠቃለል አንድ መደበኛ ሥርዐተ-ጽሕፈት ለዐማርኛ ሥነ-ጽሑፍ እድገት አስፈላጊ ነው እላለኹ። ለቋንቋው ሥነ-ጽሑፍ ግን ከአንድ በላይ መደበኛ ሥርዐተ-ጽሕፈት መኖሩ ችግር አይመስለኝም። ችግር የሚኾነው ቋንቋውን ፍጹም አምልቶ እና አስውቦ ሊያቀርብ የሚችለውን ጥንታዊ ፊደል ጥሎ በዘበናይ ቅንስ ፊደል መጻፍ እና ከኹሉም ይልቅ የሚጠቀሙበትን ፊደል ደንብ ሳይጠብቁ መጠቀም ነው።