May 20, 2018
ከጌታቸው ሽፈራው
ዶክተር አብይ ብዙውን ማስጨብጨብ ቀጥለዋል። መልካም ይሁንላቸው። መደገፍ ሀጥያት አይደለም። አይፈረድምም። ደግሞ ክፉ ክፉውን ብቻ ሲናገሩ የኖሩትን እነ መለስን እንጅ በቅርብ በጎ ሰው ያላየ ሕዝብ ለአብይ ድጋፍ ቢሰጥ አይደንቅም። የአንዳንዶቹ ግን ስሜቱ በዝቷል!

~ነውሩ ግን፣ ገና ጥሩ የሚናገሩት አብይ ስልጣን ላይ ናቸውና ጥያቄም ተቃውሞም አያሰሙ የሚል ሰሞነኛ ወቀሳ ነው። “አዲስ እረኛ ከብት አያስተኛ” እንዲሉ መሆኑ ነው። ሰሞኑን ጥያቄ በተነሳ ቁጥር በውስጥ መስመርም፣ ከስርም በአካልም “ጨለምተኛ፣ ኧረ ተው……” እያሉ የሚወተውቱ ገጥመውኛል።
~በቤናሻንጉል አረመኔያዊ ድርጊት ስለተፈፀመባቸው ሳይቀር ስንጠይቅ “ነውር” የሚመስላቸው አዲስ ደጋፊዎች ተፈጥረዋል። ጥያቄ ማንሳት ኢትዮጵያ ያገኘችውን እድል እንደማጨናገፍ ነው የሚሉም አሉ። ግን ያጋጠመውን መከራ ሲጠየቅ አይፈልጉም!
~ እንደነመለስ ያለ ሰው ሲገዛው በነበረው ሀገር መሰል አቋም ቢይዙ አይፈረድባቸውም። ችግሩ ምንም አይነት ነገር ትንፍሽ ሲበል ከአብይ አንፃር የሚያዩት ወይንም ሁሉም ጭልጥ ያለ ካድሬ እንዲሆንላቸው የሚፈልጉት ነገር ያስተዛዝባል!
~አንዳንዶቹ የአባይ ደጋፊዎች በቃል ደረጃ የሚነገሩትን ሰምተው፣ በተግባር የሚፈፀምን በደል እንዳይነገር/እንዳይጠየቅ ሁሉ የሚፈልጉ ናቸው።
~ኢህአዴግ የሚባለው ኢትዮጵያ ላይ ጉድፍና ቆሻሻ ሲጥል ኖሯል። አሁን አብይ በትንሹም ይህን ቆሻሻ ማንሳት ከጀመሩ መልካም ነው። ነገር ግን ኢህአዴግ የነሰነሰውን ቆሻሻ፣ የኢህአዴግ ሊቀመንበት ዶክተር አብይ አህመድ የማንሳት ግዴታ አለባቸው። እያነሱ ከሆነም “ይህንም አንሳው፣ ይህኛው አልተነሳም……አሁንም ሌላ ጉድፍ እያከላችሁ ነው” ማለት የሚያስብ፣ ቆሻሻን የሚፀየፍ ሰው ተግባር ነው።
~የጀማሪ ደጋፊዎች ችግር የሚመስለኝ ገዥን ሁሌም መለስ በሚባል ጭራቅ ሂሳብ ብቻ ማሰብ ነው። ኢትዮጵያ ንግግርና ትንሽ ተግባር የሚበቃት አድርጎ በትንሹ ማቀድ መሰለኝ ችግራቸው። ኢትዮጵያውያን ሰው የሚገባው ሁሉ ይገባቸዋል ብሎ የሚያስብ ጤነኛ ሰው፣ ዴሞክራሲያዊ ሀገር እንድትሆን እታገላለሁ ወይም ታግያለሁ የሚል “ይህንስ ማን አየብን” ሊል አይገባውም።
~ልጇን ቆሻሻ መጣያ የምትጥል እናት ትኖራለች። በዚች ጨካኝ እናት ሂሳብ እያላትም ልጇን አንድ ጊዜ የምታበላ እናትን “ምሳና ራቱን ስጭው” የሚል ሰው “ጭፍን ነህ” ከተባለ፣ ይህ ፈራጅ ሰው እውር ነው ማለት ነው። በዚህ ምስቅልቅሉ በወጣ ሀገር፣ እነ አብይ ከሚደነቁበት አንዳንድ ነገር፣ ለምሳሌ እስረኛን ጨርሰው ሳይፈቱ፣ ኢህአዴግ የወዘተውን ችግር ሲወሳ “ቋሙ ተቃዋሚ” ከተባለ የአብይ ደጋፊዎች ከድሮዎቹ ካድሬዎችም ብሰዋል ማለት ነው!
~አብይ ከህወሓት ጋር ትግል ላይ ናቸው አይደሉም የሚለው የሚስማሙበትም የማይስማሙበትም አሉ። ከሆነም እንደ ታክቲክ የሚደግፋቸው ይኖራል። የሚቃወም ይኖራል። ጥያቄውን የሚቀጥል አለ!
~ከምንም በላይ ፍትሕና ዴሞክራሲን እፈልጋለሁ የሚል ሁሉ ጠያቂ መሆን አለበት። አይደለም የኢህአዴጉ ቀርቶ በሕዝብ ድምፅ፣ በነፃ ምርጫ የተመረጠውንም ልጓም ሊሆን የሚችለው ጠያቂ ሕዝብ ነው!
ለምሳሌ እኔ!
~አብይን ከመለስ ጋር አላወዳድርም። በተቃራኒው መለስ ክፉ ስለተናገረ፣ አብይ መልካም ስለተናገረ ህዝብ የሚፈልገው የመሪ ጣራም አላደርጋቸውም። በሊቀመንበርነት የሚመሩት ኢህአዴግ የጣለውን ቆሻሻ ለቅሞ ይዘልቁታል ብየ አላምንም። እንደሚሉት በጎ ከሆኑ እንኳ ቆሻሻውን የመልቀም ግዴታ አለባቸው!
~እኔ ካድሬ አይደለሁም። ጠያቂ ነኝ። ለሚጠይቅ ሰው መነሻው ህዝብ እንጅ ግለሰብ አይደለም። የሕዝብ ፍላጎት 100 ፐርሰንት አይሳካም። ጠያቂ ግን የሕዝብ ፍላጎት 99 በመቶ ቢሟላም አንዷንም መጠየቅ አለበት። 30 በመቶ ደርሶ መቶ እንዲሞላ መጠየቅ አለበት። ቢያንስ 50 ይደርሳልና!
~በመለስ ዘመን ግድያን የተቃወመ፣ አብይ ስለመጡ ግድያን ወደጎን አይቶ ካለፈ ይህ ሰው ተግባሩን አልተቃወመም። ለምሳሌ እኔ ጠያቂ ነኝ። አብይን እጠይቃለሁ፣ መለስ ተመልሶ ቢመጣ እቃወመዋለሁ፣ እጠይቀዋለሁ፣ ኮ/ል መንግስቱን ቢመለስ እቃወመዋለሁ። ሌላው ቀርቶ አጤ ምኒልክ ቢመለስ፣ አጤ ቴዎድሮስ ቢመለስ… …ቢመለስ የቀረ የህዝብ ጥያቄን እጠይቀዋለሁ!
~ለሕዝብ መከራ የሚያምነውን ጌታ ሳይቀር የሚያማርር፣ እነ አብይ መልካም ተናገሩ፣ ከእነ መለስ የሚለያቸውን አንዳንድ ነገር እዛው እነ መለስ ሊቀመንበር የነበሩበት ፓርቲ ሊቀመንበር ሆነው ሰሩ ብሎ “ምንም አትናገር” የሚል ካለ ጤንነቱ ያጠራጥራል። የኢህአዴግን ሊቀመንበር ከጌታም በላይ ጌታ አድርጎ የተቀበለ ጋር መከራከር ይከብዳል!
~ኢህአዴግን እቃወማለሁ! የኢህአዴግ ሊቀመንበር ዶክተር አብይንም ለታክቲክ ጥሩ አደረጉ፣ ደግ አደረጉ ተብሎ ይደገፉ ይሆናል። ዞሮ ዞሮ ግን የኢህአዴግ ሊቀመንበር ናቸው። ሊጠየቁ ግዴታ አለባቸው! የማንሳት አቅም ካላቸው፣ ኢህአዴግ የጣለውን ቆሻሻ ሁሉ የማንሳት ግዴታ አለባቸው። ሲያነሱ “ይህንም ……” ሊባል ይገባል! ጉድፍ ሲበትኑ ደግሞ ተቃውሞ ይጠብቃቸዋል። ይህ ሕዝብን መነሻ ካደረግን ነው! ቀድመን ካመንናቸው አመንናቸው ነው! በፖለቲካ ሳያዩ ያመኑ አያተርፉም! አይተርፉምም!
