May 21, 2018
መግቢያ
በህብረተሰብ ታሪክ ውስጥ ስለ ሰብዓዊ መብቶች የመከበር አስፈላጊነት በግልጽ መወራትና መጻፍ የተጀመረው በቅርብ ጊዜ ይሁን እንጂ፣ የሰው ልጅ በተፈጥሮው ጭቆናን የማይቀበል ግን ደግሞ በአቅም ማነስ ብቻ ለጉልበታሙ ይገዛ ነበር እንጂ፣ እንደ ሰው ማንም ከማን እንደማይበልጥና በተፈጥሮም ከአካልና የአዕምሮ ብስለት መበላለጥ ሌላ፣ ሰው በሰውነቱ እኩል እንደሆነ ሁሉም ያምናል። ለምሳሌ በተለምዶ የሴት ልጅ እንደ ወንዶች ቀስትና ደጋን ይዛ ወጥታና አድና ቤተሰቡን መመገብ አትችልም ተብሎ በወንዶች ስለተወሰነባቸውና ውሎአቸው ቤት ውስጥ መዋል፣ ልጆችን መንከባከብና ለቤተሰቡ ምግብ ማብሰል ስለሆነ፣ በማህበረሰቡ ውስጥ ከሚደረገው ማንኛውም ውይይትና ውሳኔ ተገልለው ኖረዋል። ይህ ሰው ሰራሽ የሆነ የሥራ ክፍፍል፣ በመብት ደረጃ ወንዶችን የበላይ አድርጎ ያስቀመጠና ለዘመናት በሥራ ላይ የዋለ ስለሆነ፣ ወንዶች ከሴቶች የበለጠ መብት ቢኖራቸው “ተፈጥሮያዊ” ነው ብለን እስከማመን አድርሶን ነበር። ከሴቶች የነጻነት ትግል በኋላ ግን፣ ዛሬ በብዙ አገራት ሴቶች በህብረተሰቡ ውስጥ የመሪነትን ቦታ ወስደው ከወንዶች በበለጠ እንጂ ባላነሰ መልኩ ተልዕኮያቸውን እየፈጸሙ መገኘታቸው፣ ለዘመናት ሰፍኖ የነበረው የሴቶችን የበታችነት ያራመደው አስተሳሰብ፣ ለመጨቆን ሆን ተብሎ በወንዶች የተጠነሰሰ እንጂ ተፈጥሮ ወንድንም ሴትንም እንደማያበላልጥና ወንዶች ከሴቶች የበለጠ ሰብዓዊ መብት እንደሌላቸው አስመስክሯል።

