ግንቦት 14 ቀን 2010ዓም(22-05-2018)
ለውጥ በማንኛውም ህይወት ባለው ፍጥረት ወይም ተንቀሳቃሽ አካል ላይ የሚከሰት የተፈጥሮ ግዴታ ነው።ለውጥ በውስጣዊ አካላዊ እንቅስቃሴ ፍጭትና ግጭት፣ ወይም በውጭ ተጽእኖና ግፊት የሚከሰት ሲሆን ውጤቱም በውስጣዊ ይዘት፣በቅርጽና በጸባይ(content,form and character)ላይ ይንጸባረቃል።በይዘትና በጸባይ ከነበረው የተለዬና የተሻለ ሲሆን ስር ነቀል(qualitative )፣ የመልክና የመጠን ለውጥ ከሆነ ደግሞ የጥገና(quantitative)ለውጥ ተብሎ ሊመደብ ይችላል።የዚህ ጽሁፍ ዓላማ የሁሉንም የተፈጥሮ ግዴታ የሆነውን የለውጥ ሂደት ለመመርመር ሳይሆን የለውጥን ሁለ እንተናዊነት በማሳዬት በህብረተሰብ ዙሪያ የተከሰተውንና ሊከሰት የሚችለውን የለውጥ ደረጃ ለመቃኘት ነው።
በጊዜ ብዛት ከሚመጣው ተጽእኖና የከባቢ የተፈጥሮ ለውጥ ጋር በተያያዘና በዕድገት ምክንያት፣ የህብረተሰብ አስተሳሰብ፣አመጋገብ፣ግንኙነት፣ንቃተ ህሊና፣ባህል፣ቁመና፣ዕድሜ….ወዘተ ሳይቀር የሚመጡ ለውጦች ይኖራሉ።ከዛሬ ሽህ ዓመት በፊት ቀርቶ ከሁለት ትውልድ በፊት የኖረው የሰው ልጅ ከአሁኑ ዘመን ሰው ወይም ትውልድ ጋር ሲስተያይ በብዙ መልኩ ይለያል።ምንም እንኳን በሰውነት ደረጃ ቢመሳሰልም በአስተሳሰቡና ከላይ በተገለጹት ባህርያት የተለያዬ ነው።በአካላዊ ገጹም ላይ ቢሆን በአመጋገቡና በኑሮው ደረጃ ልዩነት ሳቢያ እንዲሁም ሳይንስ በወለደው በአንዳንድ የቀዶ ጥገና(medical intervention) ህክምናዎች ጣልቃ ገብነት ቅርጹንና መልኩን ሊለውጥ ዕድሜውንም ማርዘም እንደሚችል ከበቂ በላይ ማስረጃዎች አሉ።
የሰው ልጅ የተለያዩ ብልቶችና የአካል ክፍሎች ጥምርና እንቅስቃሴ ውጤት ነው።በህይወት ለመኖር ከትንሽ እስከ ትልቅ ያሉት የሰውነት ክፍሎች የሚያደርጉት ያላቋረጠ እንቅስቃሴ ወሳኝ ነው።የአካላት እንቅስቃሴ መቆም ማለት ሰውዬው ሞተ ማለት ነው።
ህብረተሰብም በውስጡ የያዛቸው አካላት አሉት፤አካላቱ ልዩ ልዩ አስተሳሰብ፣ባህል፣ታሪክ፣ቋንቋ፣እምነት፣የዕድሜ ደረጃ፣ችሎታ…የሚያንጸባርቁ የሰው ልጆች ናቸው።የነሱ የእርስ በርስና የጋራ እንቅስቃሴ፣መቀራረብና መራራቅ፣መተባበርና መጋጨት፣ ለእድገቱና ለውድቀቱ፣ለመኖሩና ላለመኖሩ መንስኤና ወሳኞች ናቸው።እንቅስቃሴ የማያደርግ ህብረተሰብ ለእድገትና ለለውጥ የታደለ አይሆንም።የለውጡን አይነት የሚወስነው ደግሞ አባላቱ የሚመርጡትና የሚጓዙበት መንገድ ወይም የሚከተሉት የፖለቲካ ራዕይ ይሆናል።
እንደማንኛውም የዓለም ህብረተሰብ የኢትዮጵያ ሕዝብም ብዙ የለውጥ ደረጃዎችን አልፎ አሁን ካለበት ደረጃ ላይ ደርሷል።ወደፊትም የሚደርስባቸው የለውጥ ደረጃዎች ይኖራሉ።ህብረተሰብ ድንጋይ አይደለም፤አንድ ቦታ ላይ ተቀምጦ አይቀርም።የኑሮ ግዴታ አለበትና አርፎ አይቀመጥም።ኑሮውን ለማሻሻል ጥረት ያደርጋል። ሕዝብ ለእድገትና ለመሻሻል እንዲሁም ለለውጥ ባለው ፍላጎት፣ ብሎም ጊዜው በወለዳቸው የመገናኛ ዜዴዎች በሚደርሰው መረጃ የሌላው አገርና አካባቢ የሚኖረው ህብረተሰብ የደረሰበትን ዕድገትና ተመክሮ በማጤን በሚያድርበት የውድድር መንፈስ በነበረው ልማድና ወጉ፣ በሚከተለው ማህበራዊ፣ኤኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ አስተሳሰቦቹ ላይ ለውጥ እንዲያመጣ ይገደዳል።ትውልድ የለውጥ ውጤት ብቻም ሳይሆን የለውጥ ፈጣሪ፣ባለቤትና ለተተኪው ትውልድ የሚያወርስ ድልድይ ነው።
የኢትዮጵያ ሕዝብ ያለፈበትን የረጅም ዘመኑን ትተን ከሃምሳ ዓመት ወዲህ የተከሰተውን የለውጥ ደረጃ ብንመለከት በፖለቲካ በኩል ሦሥት ዓይነት ስርአቶችን አልፏል፣ዘውዳዊ፣ወታደራዊና ጎሰኛ ስርዓቶችን አስተናግዷል ።በኤኮኖሚና ማህበራዊ አሰላለፍና አስተሳሰብም በኩል የነዚህን የሦሥቱን ስርዓቶች ርዕዩተዓለም(ፍልስፍና) የሚያንጸባርቅ አስተዳደር ተሸካሚ ሆኗል።እሁንም የመጨረሻውን የጎሰኛ ስርዓት ተሸክሞ በመጓዝ ላይ ነው።በያንዳንዱ ስርዓት ውስጥ በተፈጠረው ውስጣዊና ውጫዊ ተቃርኖ ምክንያት አንዱ ስርዓት ለሌላው እያስረከበ ሄዷል። የአሁኑም ለሚቀጥለው ስርዓት አስክቦ የመሄዱ ነገር የማይካድ ነው፤ጊዜውን ጠብቆ ይመጣል። የሚያፋጥነው ግን ውጫዊና ውስጣዊ ሁኔታ(የቅራኔ ደረጃ ) መብሰልና መድረስ ሲሆን ያንን ተጠቅሞ የሕብረተሰቡ ለለውጥ ያለው ፍላጎትና ቁርጠኝነት ሲጨመርበት ነው።የፖለቲካ ለውጥ ሁል ጊዜ ወደተሻለ ስርዓት የሚያመራ ሳይሆን ወደከፋና ወደባሰ ስርዓትም ሊያመራ ስለሚችልና በተግባርም ስለታዬ የዛን አቅጣጫ አስቀድሞ መዝጋት አስተዋይነት ነው።
ባለፉት ሦስት ስርዓቶች የባለሥልጣኖች መቀያየር ቢከሰትም የሕብረተሰብ ኑሮና እድገት ላይ ያመጣ የስርዓት ለውጥ አልነበረም፤ለውጡ መሰረታዊ ለውጥ ሳይሆን ከስምና ከትንሽ ጥገናዊ ለውጥ በላይ አልሄደም።ስለሆነም የሕዝቡ ኑሮ ያልተሻሻለበት፣መብቱና ነጻነቱ ያልተከበረበት፣አምባገነኖች እየተቀያየሩ የገዙበት የስልጣን ልውውጥ ከመሆን አላለፈም።አንዱ ሌላውን ለመጣል የተጠቀመበት መንገድና ዘዴ፣ሕዝቡን ከዃላው ለማሰለፍ የተጠቀመበት ስልት የተለያዬ ነው፤ያ ግን የሥርዓት ለውጥ ተደርጎ ሊቆጠር አይገባውም።የተፈራረቁት ስርዓቶች በሕዝቡ ፍላጎትና ምርጫ፣የሕዝቡን ኑሮና አስተሳሰብ የቀዬሩ መሰረታዊ ለውጥ ያበሰሩ ሳይሆን በሕዝቡ ላይ የሰቆቃ ስርአት ያሰፈኑ አምባ ገነኖች ናቸው።የአሁኑም በወያኔ መራሹ የኢሕአዴግ ዙሪያ የተከሰተው የግለሰቦች መለዋወጥ ተቋሙ እስካለተቀየረ ድረስ ካለፉት የተለዬና የራቀ ሊሆን አይችልም።
ጠ/ምኒስትር ሃይለማርያም ደሳለኝ በዶር/ኮሎኔል አብይ አህመድ መተካት የዛን ሂደት የተከተለ ነው።አንዳንዶቹ ይህንን የግለሰቦች ለውጥና ተለዋጩ የሚያደርገውን ዲስኩር በመስማት መሰረታዊ ለውጥ እንደመጣ በመቁጠር ከትግሉ ጎራ ለማፈግፈግ ሲዳዳቸው ይታያሉ።አንዳንዶቹም የዶር/ኮሎኔል አብይ አህመድን የዕድሜ ጣራ፣ የትውልድ ቦታና ሃረግ እንዲሁም የሚከተለውን እምነት መነሻ በማድረግ በጭፍኑ የወገናዊነት ድጋፍ ሲሰጡ ይታያል።እንደዚህ አይነት ድጋፍ ደግሞ በእውቀትና አስተሳሰብ ላይ የተመሰረተ ስላልሆነ ዶር አብይን የሚያጠናክረው ሳይሆን ለውድቀቱ የሚጎትተው ገመድ ይሆናል።
የማይካደው ነገር በአቀራረብ ፣በአነጋገርና በአንዳንድ እርምጃዎች አኳያ ዶር/ኮሎኔል አብይ የተለዬ ነው።እሰይ! ፣ይሁን! የሚባሉ ንግግሮችን ተናግሯል፣ወደፊትም ሊናገር ይችላል፤ያለፉት መሪዎች ያላደረጉትን አንዳንድ እርምጃዎችንም ወስዷል።ግን በቂ አይደለም። እርግጥ ነው በውጭ አገር ተሰደው በአንዳንድ ምክንያቶች በእስር ቤት ሲሰቃዩ የነበሩትን ወገኖቻችንን ለማስፈታት ችሏል።ድርጊቱን ማድነቅና መደገፍ ተገቢ ሲሆን አያይዞም ይህንን ውጤት ለማግኘት ያስቻለውን የውል ዝርዝር ማዬትና መጠየቅ ተገቢ ነው።ድርድር ማለት ሰጥቶ መቀበል ነው፤ያ ከሆነ ደግሞ ሳውዲዎችና ሱዳኖች እስረኞችን ሲፈቱ በለውጡ ከአብይ በኩል ምን ተለገሰላቸው?ለሱዳኖቹ የድንበር መሬት መያዛቸውን ተቀበለላቸው?ለሳውዲዎቹ በአገሪቱ ጥቅምና የኤኮኖሚ መስክ የሚሹትን እንዲያገኙ የሚያስችላቸው ዕድል በስምምነት አበሰረላቸው?የሚሉት ሁሉ ሊታሰቡ ይገባል።አብይ ስለጠዬቀ ብቻ የሚሰጡት ችሮታ አይደለም።ከጥቅማቸው ጋር የተያያዘ ስምምነት ውጤት ለመሆኑ ምስክር መቁጠር አስፈላጊ አይሆንም፤የማንኛውም አገር መሪ ለድርድር ሲቀርብ የሚያስቀምጠው ቅድመ ሁኔታ ወይም የጥቅም ጥያቄ ማንሳቱ የማይቀር ነው።
በመሰረቱ ከሁሉም የሚሻለው መፍትሔ በውጭ አገር ለመሰደድ ምክንያት የሆነውን ሥራ አጥነትና ችግር ማሶገድ፣ ኤምባሲዎች በግል የንግድ ሥራ ላይ ከመጠመድ ይልቅ የአገርንና የወገንን ጥቅምና ክብር በሚያረጋግጠው ተግባር ላይ እንዲሰማሩ ማድረግና መቆጣጠር ተገቢ ነው።በውጭ አገር የሚኖረው ኢትዮጵያዊ መብቱ እንዳይደፈር መንከባከብና ጠበቃ መሆን የመንግሥት በተለይም የኤምባሲዎች ሃላፊነት ነው።ከዚህም አይነቱ ቅሌት፣በግፍ ከመሰቃዬትና ከባርነት ኑሮ ያድናል።እስከዛሬ ድረስ እንደሚታዬውና እንደሚታወቀው ከሆነ ግን በዚህ ቦታ ላይ መሾም የዲፕሎማሲን ሥራ ለመሥራት ሳይሆን የመጠቃቀሚያ አንዱ መንገድ ነው።
በሳውዲና በሱዳን የሚኖሩት ወገኖቻችን ባይታሰሩም ይገፉ የነበረው ኑሮ በትልቅ እስር ቤት የመኖር ያህል ነው። በዚህ ዙሪያ ዶር/ኮሎኔል አብይ አህመድ የሠራው ሥራ ሌሎቹ ስላላደረጉት እሱን ልዩ ያደርገዋል፤እርምጃውም መለስተኛ ጥገና ተደርጎ ሊታይ ይችል ይሆናል።ከዚያም በተረፈ ግን እርምጃው፣ ለሥልጣኑ መደላደያ የሚሆን ድጋፍ ከማስገኘቱ በተረፈ ሕዝቡ የሚፈልገውን ዘላቂ ሰላም፣መብትና የአገሩን አንድነት የሚያረጋግጡለት፣ከመፈናቀል ከመገደልና ከመሰደድ የሚያድነው የሥርዓት ለውጥ ተደርጎ መታዬት አይኖርበትም።አሁንም በዘመነ አብይ ሕዝብ እዬተገደለ፣እየተፈናቀለ፣እየተሰደደና እየታሰረ ነው።ወደ ሳውዲና ሌሎች አረብ አገሮች እየተሰደደ የሚሄደውን ወጣት አላገደውም። አሁንም ሕዝብ እየተፈናቀለ ነው።በተለይም አማራው በየትኛውም አቅጣጫ የጥቃት ዘመቻ እየተካሄደበት ነው።ታዲያ ያንን ጥቃት ለማስቆም ዶር አብይና እመራዋለሁ የሚለው መንግሥት ስልጣንና ብቃት የለውም ማለት ነው? ወይንስ አያውቅም ማለት ነው?ወይንስ እንዲካሄድ በመንግሥት ፈቃድና ትእዛዝ የሚከናወን መንግሥታዊ ሴራ ነው?
ዶር /ኮሎኔል አብይ ስለሰላም፣አንድነትና አብሮነት የሚያወራው ወሬ ለአማራው ህብረተሰብ አይሰራም ማለት ይሆን? ፣ንብረቱ ይዘረፋል፣ቤቱ ይቃጠላል፣ ከኖረበት ቀዬው እየተፈናቀለ ለስደት ተጋልጧል።የ14 ዓመት ህጻን ልጅ ሳይቀር ብልቱን እየተቆረጠ ዓይኑ እየተመነቀለ ኢሰብአዊ ድርጊት እየተፈጸመበት ዝምታው ለምን ይሆን?ዶር/ኮሎኖል አብይ በሳውዲ አረብያ መጠዬቅ የነበረበትን ህመምተኛ ልጅ ሆስፒታል ሄዶ ሲጠይቅና ወላጅ እናቱን ሲያጽናና፣በገዛ አገሩ ላይ በደልና ግፍ የተፈጸመበትን ህጻን ለምን እረሳው?አማራ በመሆኑ ይሆን? የአማራውን ጩኸትና ሰቆቃ የሚያዳምጥ የመንግሥት ጆሮ የለም ማለት ይሆን? የሚያዳምጠው ከጠፋ እራሱን ለመከላከል እርምጃ ቢወስድ የሚፈረድበት አይሆንም።ሕግ ያላስከበረውን መብት ሃይል ያስከብረዋልና! ለሁሉም የሚበጀው ግን ከጎሰኝነት አስተሳሰብ አገራዊ አስተሳሰብ እንዲሰፍን ማድረጉ ነው።
የኢትዮጵያ ሕዝብ ሲያደርግ የነበረውና አሁንም የሚያደርገው ትግል ለአገሩ አንድነት፣ሰላምና እድገት ለሚረዳው ለስር ነቀል የስርዓት ለውጥ እንጂ ለግለሰብ የሥልጣን ቅብብሎሽና ለጥገና ለውጥ አይደለም።አሁን እየታዬ ያለው ለውጥ ምናልባትም የአንዱ ጎሳ(ህወሃት)ተወግዶ በሌላ ጎሳ (ኦሕዴድ)የመለወጥ ውጤት ሊሆን ይችላል፤አዝማሚያውም ያንን ይመስላል። ያም ቢሆን አልጋ ባልጋ ይሆናል ማለት አይደለም፤ በነዚህ ሁለት ጎሳዎች መካከል የሞት የሽረት ትግል ሊካሄድ ይችል ይሆናል።ውስጥ ለውስጥም እንደሚካሄድ መረጃዎች እዬወጡ ነው።ግን ትንቅንቃቸው በሥልጣን ዙሪያ እንጂ በስርዓት ልዩነት ዙሪያ አይደለም።ሁለቱም በኢሕአዴግ የጎሳ ማኒፌስቶ የሚመሩ የአንድ ድርጅት አባላት ናቸውና!ነገሩ ሌባ ሲሰርቅ ይስማማል ሲከፋፈል ይጣላል አይነት ነው።
አሁንም ከላይ ተቀምጦ ስርዓቱን በጉልበት የሚያሽከረክረው የወያኔ ቡድን ነው፤የስልጣን ቦታው አልተነካም።የጦር ሃይሉ፣የደህንነቱ፣የውጭ ጉዳይ፣የፖሊሱ…ያገሪቱ የኤኮኖሚና አስተዳደር ቁልፍ ቦታዎች በሱ መዳፍ ስር ናቸው።አሳልፎ የሚሰጣቸው አይደሉም።አሳልፎ መስጠት ማለት በራሱ ላይ መፍረድ ነው።በቅርቡ የወያኔ ቀንደኛ መስራችና ባለስልጣን የሆነው አባይ ጸሃዬ የተባለው ወንጀለኛ በአንዳንዶቹ የመንግስት ተቋማት ላይ ለውጥ ይደረግ ተብሎ ሲጠየቅ ያለውን ማስታወስ ጠቃሚ ነው። የሚጠየቀው ለውጥ ሊሆን የሚችለው ስሞት ብቻ ነው”On my dead body” ነበር ያለው።እሱ ብቻ ሳይሆን የቀሩትም የወያኔ መሪዎችና ተባባሪ የጎሳ ድርጅት አጋሮቻቸው የተለዬ እምነትና አቋም የላቸውም። የኢትዮጵያን አንድነት የሚያረጋግጥና የሕዝቡን የበላይነት፣የጎሳን ፖለቲካና የክልልን ግምብ የሚንድ፣መሠረታዊ ለውጥ የሚያመጣ አገር ወዳድ ሃይል ስልጣኑን ከሚይዝ ሞታቸውን ይመርጣሉ።የሕዝቡን ጥያቄ ሊፈታና ሊወክለው የሚችል ሃይል መጣ ማለት እነሱ ላለፉት 28 ዓመታት ለሰሩት ወንጀልና ለፈጸሙት ግፍ፣ዘረፋና ያገር ክህደት በሕግ የሚጠይቅ መንግሥት ተፈጠረ ማለት ነው።የዶር/ኮሎኔል አብይ አማካሪዎች የዚሁ ሥርዓት ባለቤቶች የሆኑትና ሕዝብ አንቅሮ የተፋቸው የወያኔ መስራቾች አባይ ጸሃዬ፣በረከት ስምኦን፣ስዩም መስፍን፣አርከበ እቁባይ፣ስብሃት ነጋና የቀሩትም ናቸው።ታዲያ በነዚህ ምክር ከሚመራ ሰው ለውጥ መጠበቅ ከእባብ እንቁላል እርግብ ይፈለፈላል ማለት አይሆንምን?
የዶር. አህመድ በጠቅላይ ሚኒስትርነት ተሾመ ማለት የስርዓት ለውጥ መጣ ማለት አይደለም።በቀና እንዬው ከተባለ ምናልባት ወደዚያ ሊያመራ የሚችል ዕድል ሊፈጥር ይችል ይሆናል።ያንን ግን የሚወስነው የሕዝቡ ቀጣይ ትግልና የዶር. አብይ ከኢሕአዴግ ውስጥ ወጥቶ ለመታገል የሚያደርገው ቁርጠኝነት ነው።ያንን እስካላደረገ ድረስ ለስርዓት ለውጥ ቆሟል ማለት አይቻልም።አንዳንዶቹ አብይን ከፈርኦን ቤት ካደገውና ከድቶ እስራኤላውያንን ለነጻነት ከመራው ከሙሴ ጋር ያስተያዩታል።አብይ ግን ኢሕአዴግን ከድቶ የኢትዮጵያን ሕዝብ ነጻ ለማውጣት የተነሳ አይደለም።እዛው ውስጥ ሆኖ ያው ስርዓት እንዳይፈርስ የሚጥር ሰው ነው። ስለሆነም ትግሉ ሊቆም አይገባውም።በዚህ መለስተኛ ለውጥ ተራው ቀርቶ ሌሎቹም በተቃዋሚው ጎራ የተሰለፉት ድርጅቶች ሳይቀሩ በመደገፍና በመጠራጠር ውዥንብር ዓለም ውስጥ ገብተዋል።የራሳቸውን ራዕይ በተግባር ለመግለጽ ከመወሰን ይልቅ ከሚታገሉት ጎራ የሚፈልጉትን የሚያገኙ እየመሰላቸው በመደገፍና በመቃወም ጠርዝ ላይ ተንሳፈው ይገኛሉ።አንዳንዶቹም ተቃዋሚ ነን ባዮች ሃቁን ባለመረዳት ሳይሆን ምናልባት የሥልጣኑ ተቋዳሽ እንሆናለን በሚል ቀቢጠ ተስፋ ለመሞዳሞድ እየዳዳቸው ነው።ምኞታቸው ቢሳካ ከፓርላማ የተወሰነ ወንበር በላይ የሚደርሳቸው የሥልጣን ባለቤትነት አይኖራቸውም።የተቃዋሚው ጎራ በተለይም በአሜሪካ የሚኖሩት ኢትዮጵያዊያን ማሰብ ያለባቸው ለዶር አብይ በሚሰጡት ድጋፍ ምክንያት ለብዙ ጊዜ ሲታገሉለት የቆዬውና አሁን በተግባር ሊገለጽ ጠርዝ ላይ የደረሰው የአሜሪካኖቹ HR 128 እና በእንጥልጥል ላይ ያለው SR 168 የተባሉት ሕጎች የውሃ ሽታ ሊሆኑ እንደሚችሉ ነው።ምክንያቱም ለውጥ መጥቷል ብለው እራሳቸው መስክር በመሆን ሕጉ እንዳያልፍ ከሚጥሩት ከወያኔ/ኢሕአዴግ ደጋፊዎች ጎን ተሰልፈዋልና ነው።
የውጭ አገር በተለይም የአውሮፓ የፖለቲካ ተንታኞችና የመንግሥታት ተቋማትም የዶር/ኮሎኔል አብይን ሥልጣን ላይ መውጣት እንደ ትልቅ ለውጥ በማናፋት ላይ ናቸው።በእነሱ እምነት ለአፍሪካ ሕዝብ በእውቀትና በፍልስፍና ላይ የተመሰረተ የፖለቲካ ስርዓት ተገቢ ነው ብለው አያምኑም፤ሕዝቡም ለዚያ ብቃት አለው አይሉም።በዚሁ የንቀት አመለካከታቸው የአገራችንን የፖለቲካ መስመርና ስርዓት ከጎሳ በላይ የተሻገረና ሊሻገርም እንደማይችል አድርገው ይቆጥሩታል።ሥልጣኑ በጎሳ ተራ የሚወራረድ መሆን እንዳለበት ያምናሉ።በቀደሙት ስርዓቶች አማራው የበላይ ነበር ፣አሁን ላለፉት 28 ዓመታት የትግሬው ጎሳ ባለተረኛ ሆኗል፣አሁን ደግሞ የኦሮሞው ጎሳ ተራ መሆን አለበት ከሚለው አስተሳሰብ ተነስተው የሕዝቡን ትግል በማኮሰስ የተሳሳተ ትንታኔና የማይመጥነውን መልስ በመስጠት ላይ ናቸው። ለአለፉት ዓመታት ኦፒዲኦ ለተባለው ድርጅት አባላት ድጋፍና ስልጠና በመስጠት ያጠናከሩ አገሮች እንዳሉ በተጨባጭ የተያዘ መረጃ አለ።አንዱም እኔ የምኖርበት አገር ሆላንድ ነው።ጥቅማቸውን የሚያጡበት ሁኔታ እያደገ ስለመጣ ያንን በመረዳት ብዙ የንዋይ ተፋሰስ ያደረጉበትና ለወደፊቱም ዘረፋ አመቺ ነው ብለው የሚተማመኑበት የኦሮሞ ክልል የተባለው ያገራችን ክፍል በመሆኑ የኦፒዲኦው ዶር አብይ ሥልጣኑን እንዲይዝ ምክርና ድጋፍ ከመስጠት ወደዃላ እንደማይሉ በብዙ መልኩ የሚታመን ነው።የኦሮሞውን የበላይነት ለማግዘፍ ከየቦታው እየተጠራሩ የሚገቡትን የኦነግና መሰል የኦሮሞ ድርጅት አባላት እንቅስቃሴም መገንዘቡ አገራችን ከአንዱ የጎሳ የበላይነት ወደሌላው ጎሳ የበላይነት እያመራች መሆኑን ዓይናችንን እንጨፍን ካልልን በስተቀር ሁኔታው ያረጋግጥልናል።
ግራም ነፈሰ ቀኝ ኢትዮጵያ ውስጥ የተካሄደውና በመካሄድም ላይ ያለው ሕዝባዊ ትግል ወያኔና ግብረአበሮቹ እንደሚፈልጉት የሚያዙበት ሁኔታ እንዲቀጥል የሚፈቅድላቸው አይደለም ። ዶር.አብይ የሚናገረውን ኢትዮጵያዊነትን የሚያጎላ ንግግር እንዲናገር ያስገደደውም ያው የሕዝቡ ትግል ነው።እንደ ሟቹ መለስና እንደ ሃይለማርያም ደሳለኝ እየተቆጡና እየተሳደቡ ሊገዙ የሚችሉበት ጊዜ አክትሟል።ለመሆኑ ሥልጣኑን እስከከተረከበበት ጊዜ ድረስ ኢትዮጵያዊነትን ከመናገር ያገደው ምን ነበር?ለምን ላለፉት 28 ዓመታት ድምጹን አላሰማም?የፓርላማ አባል በመሆኑስ አሁን ስለህዝቡ ጥቅምና መብት የሚናገረውን ቃል ተንፍሶ ያውቃል?ነገሩ ዶሮን ሲያታልሏት …ነው።የኢትዮጵያን ስም ደጋግሞ በንግግሩ አወሳ የሚለውም ምክንያት ለድጋፍ በቂ አይሆንም።የሚመራው ድርጅት እኮ የኢትዮጵያ ሕዝብ አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ግንባር የሚል ነው እንጂ የሌላ አገር ግንባር ነኝ አላለም።ታዲያ አብይ ኢትዮጵያ ስላለ እንዴት ብርቅና አዲስ ነገር ይሆንብናል?
ምንም እንኳን አንድ ግለሰብ የፈለገውን ሥርዓት ለማስፈን ችሎታና መብት እንደሌለው የታወቀ ቢሆንም ፣የዶር. አብይን መመረጥ እንደ በጎ ካዬነውና ከተቀበልነው ከሱም በኩል የሚጠበቅበት አገር ነክ ጥያቄዎችን የመመለስ ግዴታ አለበት።በጆሯችን የሰማናቸውን የሚጥሙ ቃላቶች በተግባር ሊያሳዬን ይገባዋል።ማለትና ማድረግ የተለያዩ ናቸውና!። ጨው ለራስህ ስትል ጣፍጥ አለበለዚያ ድንጋይ ነው ብለው ይወረዉሩሃል እንዳይሆን ሊያስብበት ይገባል።ማወቅ ያለበት ምንም እንኳን ሕዝብ ባይመርጠውም በአገር ስም የጠ/ሚኒስትርነቱን ቦታ ከያዘበት እለት ጀምሮ የሁሉም ኢትዮጵያዊ ጠ/ሚኒስትር እንጂ የአንድ ጎሳ ድርጅት መሪና ተወካይ እንዳልሆነ ነው።የሚወስዳቸው እርምጃና የሚከተለው መርህ አገርንና ሁሉንም ኢትዮጵያዊ የሚጠቅም እንጂ የአንድ ወይንም የተባበሩትን የጎሳ ድርጅት ስብስብ የሆነውን ኢሕአዴግን ለማገልገልና ህልውናውን ለማስጠበቅ መሆን የለበትም።ሀይልና መከታ አድርጎ መቁጠርና መተማመንም ያለበት የኢሕአዴግን የመጨቆኛ መሳሪያዎች ሳይሆን በኢትዮጵያ ሕዝብ ሊሆን ይገባል። ተስፋ የጣለበትን ሕዝብ ከዃላው ለማሰለፍ የሚከተሉትን ቢፈጽም ይረዳዋል፣መልካምም ይሆናል።
እውነተኛ ለውጥም ተከስቷል ብሎ ለማለትና በዶር/ኮሎኔል አብይ ላይ እምነት ለመጣል የሚከተሉት የተግባር ፈተናዎች ወሳኞች ናቸው።
1 ጊዜያዊ አዋጁን ባስቸዃይ ማንሳት
2 የታወቁትን ግለሰቦች በመፍታት ብቻ ሳይቆም በግፍ የታሰሩ ዜጎችን ካለምንም ቅድመ ሁኔታ መፍታት፣ወደፊቱም ማንኛውም ዜጋ በመቃወሙ ብቻ እንዳይታሰርም ማረጋገጥ።
3 የአጋዚና የመከላከያ ሃይሉ ወደ ጦር ሰፈሩ እንዲገባ ማድረግ፣ ከአገር ድንበር ማስከበር ተግባር ውጭ በሕዝብ ላይ አመጽ እንዳይፈጽም ማገድ፣በፈጸሙት ላይ ሕጋዊ እርምጃ መውሰድ
4 ስለፍቅር፣ሰላምና አንድነት የሚሰብከውን ሰበካ በተግባር ለመግለጽ በሱ ድርጅት ፈቃድና ድጋፍ በአማራውና በኦሮሞው ማህበረሰብ መካከል የጥላቻና የበቀል ምልክት የሆነውን የአኖሌን ሃውልት ስህተተኛነት ገልጾ እንዲፈርስ ማድረግ ፣
5 ከየቦታው የተፈናቀሉት ወደ ቀድሞ ቦታቸው እንዲመለሱና ለወደመባቸው ንብረትና የስነልቦና ስብራት ካሳ እንዲሰጣቸው ማድረግ።ያፈናቀሉና በደል ባደረሱት ላይ ሕጋዊ እርምጃ መውሰድ።ወደ ፊትም ማንኛውም ዜጋ በፈለገበት ቦታ የመኖርና የመስራት ፣ሃብት የማፍራት መብት እንዳለው በሕግ ማረጋገጥ
6 ቋንቋን መሰረት ያደረገው የክልልን አወቃቀር ማፍረስ፤አቶ ለማ መገርሳ የቀደደውን የጎሳ ማንነት መታወቂያ በአገር አቀፍ ደረጃ መተግበር፤የኢትዮጵያዊነትን መንፈስ ከቃላት ባሻገር የሚዳብርበትን መንገድ መከተል።ላለፉት 28 ዓመታት በሕዝቡ አይምሮ ውስጥ የተተከለውን የጎሰኝነት ቫይረስ ማምከን።አገሪቱን ለመበታተን ታቅዶ የወጣውን የኦነግን፣የሻእብያንና የወያኔን ሕገ መንግስት ሽሮ ሁሉም በተሳተፈበትና በተቀበለው ሕግ መተካት።
7 የዴሞክራሲ መብቶችን እንዲከበሩ ማድረግ፣አፋኝ ሕጎችን መሻር፣የመሰብሰብ፣የመደራጀት፣ በሰልፍም ሆነ በጽሁፍ የመቃወም፣የመደገፍ መብትን ማረጋገጥ
8 ሥልጣናቸውን ተመርኩዘው፣ወይም በጎሳ አባልነታቸው የአገር ሃብትና ንብረት የመዘበሩ፣ስልጣናቸውን ተገን አድርገው ሕዝቡን በሙስና የዘረፉና ያሰቃዩ ወንጀለኞች ላይ ሕጋዊ እርምጃ መውሰድ።ለዚህም የሚረዳ የሕዝቡን ብሶት የሚቀበል (እምባ ጠባቂ)አካል መፍጠር
9 የሽግግር ሁኔታን በመፍጠር ለቀጣዩ ሕዝባዊ ስርዓት መመስረት የሚያስፈልገውን ጎዳና መጥረግና ማመቻቸት
10 ማንኛውም በአገር ውስጥና ከአገር ውጭ ያለ የተቃዋሚ ድርጅት፣ስብስብ እንዲሁም ግለሰብ ካለምንም ገደብና ቅድመ ሁኔታ በአገር ቤት ገብቶ የመታገልና የማታገል መብቱን መቀበል፣ለደህንነቱም ዋስትና መስጠት።
11 የመገናኛና የሚዲያ ዘርፎች ከመንግስት ቁጥጥር ነጻ ሆነው ለሁሉም በእኩልነት እንዲያገለግሉ ማድረግ።
ዶር. አብይ አህመድና የሚመራው መንግሥት ለእነዚህ ጥያቄዎች ተግባራዊ መልስ የሚሰጥ ከሆነ እውነትም ለለውጥ የተነሳ ነው የሚለው ግምት የሚያስተማምን ይሆናል።የኢትዮጵያም ሕዝብ ከጎኑ በመሰለፍ የሚቃጣበትን አደጋ ሊመክትለት ይችላል።ምርጫው የሱ ነው።
የተለዬ ሃሳብና በዶር/ኮሎኔል አብይ አህመድ ላይ ትችት የሚያቀርበውን ወገን እንደ ጸረ ለውጥ ከማዬት ይልቅ የዶለዶመ ቢላዋን ለመሳል እንደሚረዳ ሞረድ ማዬቱ ለትግሉ ይረዳል።የዶር አብይ አካሄድ የለውጥ ጉዞን የሚያበስር ከሆነ ይበልጥ ሃይል እንዲኖረውና አገር አጥፊ ጎሰኞችንና የጎሳ ፖለቲካን የሚያንበረክክ እንዲሆን ይረዳዋል።ከጭፍን ደጋፊ የነቃ ተቃዋሚ ይጠቅማል። ተቀናቃኝና ተሟጋች የሌለበት የፖለቲካ መስክ ፣ ባለቤት እንደሌለው ለቁንጫ እንደተጋለጠ ወና ቤት ይቆጠራል።
አገሬ አዲስ
