በኢሕአዴግ የተመረጡት አዲስ ጠቅላይ ሚኒስትር ብቅ ካሉበት ጊዜ ጀምሮ የውጭ-አገር ዜችን ጨምሮ ከበርካታ ኢትዮጵያውን የተለያዩ አስተያየቶች ተሰንዝረዋል፤ የድጋፍ፣ የተቃውሞና በሁለቱም መኻል ያሉ የፖለቲካ አስተሳሰቦችም ተንሸራሽረዋል።

ከሁሉ በፊት ላለፉት ሃያ-ስምንት ዓመታት ኢትዮጵያን እየገዛ ያለው ሕወሓት-መሩ የኢሕአዴግ መንግሥት የለየለት አምባ-ገነን መሆኑና የኢትዮጵያ ሕዝብም ለመብቶቹ መከበር እየታገለ መሆኑ ከወዲሁ ግልጥ እንዲሆን እፈልጋለሁ። አምባ-ገነንና ጨቋኝ አገዛዞችን ለማስወገድ የሚደረግ ትግል ምትክ በሌለው የዜጎች ሕይዎትና በአገር ንብረት ላይ የሚያስከትለው ውድመት በቀላሉ የሚታይ አይደለም። አምባ-ገነን አገዛዝን የማስወግዱ ትንንቅም እንደየአገሩ ልዩ ሁኔታ በሕዝብ ሰላምና በአገር አንድነት ኪሣራ ሊደመደም እንደሚችል የታወቀ ነው።

እንደሚታወቀው ማንኛውም አምባ-ገነን አገዛዝ ከውስጥ በገዥው ቡድን መኻል በሚፈጠር ልዩነት ወይም በተደራጀ መልክ በሚንቀሳቀስ/ሱ ድርጅት/ድርጅቶች አማካይነት በሚደረግ ትግል ከሥልጣን ሊወገድ ይችላል። መንግሥታዊ ለውጡ በውጭ ኃይል ቀጥተኛ ጣልቃ-ገብነትም ሊፈጸም ይችላል። በአንዱ ይሁን በሌላው አማካይነት የሚመጣው ለውጥ የሚወስደው ጊዜ፣ በአገር ላይ የሚያስከትለው መዘዝ ወይም የሚያስከፍለው ኪሣራም ሆነ በውጤቱ ዘለቄታዊነት ላይ ወሣኝ ሚና የሚኖረው ከምንም በላይ በሕዝብ ዘንድ የሚኖረው ተሣትፎና ድጋፍ ይሆናል። ያን የተሣትፎ ይዘት የሚወስነው ደግሞ ሕዝብ እንዲወገድ በሚፈልገው ኃይል ላይ ካለው ጥላቻ በላይ፣ ቢያንስ ባልተናነሰ ደረጃ፣ በለውጡ ዓላማና ለለውጡ በቆመው ክፍል ላይ ያለው አመኔታ ይሆናል።

በአገራችን ልዩ ሁኔታ፣ በተለይም ከአለው ውጥረትና ሁከት የበዛበት የአካባቢያችን ሁኔታና የሕዝብን ሰላምና የአገርን አንድነት ተፈታታኝ የሆነ በቋፍ-ላይ የሚገኝ የውስጥ ይዞታችንን ለሚገነዘብ ማንኛውም ሰው ኢትዮጵያ ውስጥ የሚደረግ ለውጥ በአገር አንድነት ኪሣራ እንዳይሆን ከፍተኛ ጥንቃቄን እንደሚጠይቅና እንዲሁ ‘ ያለው ብቻ ይወገድ ’ በሚል ግብዝ ስሊት ሊታይ እንደማይገባ መገንዘብ ያስፈልጋል። አንዳንድ ወገኖች ‘ ወያኔ ከተወገደ ሁሉም ነገር ቀላል ይሆናል ’ እንደሚሉ የታወቀ ነው። እነዚኽ ወገኖች ያልተረዱት ግን አባባላቸው እንጅ አሁን ባለው የአገራችን ሁኔታ የሚሉትን ተፈጻሚ ለማድረግ የሚጠይቀውም ሆነ የሚያስከትለው መዘዝ ቀላል እንዳልሆነ ነው።

የዶ/ር ዓብይን በጠቅላይ ሚኒስትርነት መመረጥ ተከትሎ የድጋፍና የተቃውሞ ድምፆች በቀጣይነት መስተጋባታቸው ይታወቃል። ተቃውሞ በሚያስተጋቡት በኩል ‘ የዶ / ር ዓብይ ወደ ሥልጣን መምጣት የሕወሓት / ኢሕአዴግ አገዛዝ ከሕዝብ የሚቀርብበትን የፍትኅና የመብት – መከበር ጥያቄና አልፎም ለመሠረታዊ የሥርዓት ለውጥ የሚደረገውን እንቅስቃሴ ድርጅቱ ባለበት የውስጥ ቀውስ – አዘል ችግርና ከሚከተለው መርኆና ከአለው ድርጅታዊ ተፈጥሮ ባኅሪ አኳያ ተገቢውን አዎንታዊ ምላሽ መስጠት ስ ለማይችል እንደምንም ጊዜ ለመግዛትና ዕድሜውን ለማራዘም ሲል የተሸረበ ደባ ነው። ስለሆነም ከእኝኽ ሰው ምንም ዓይነት ለውጥ መጠበቅ የዋህነትና አልፎም የሕዝብን ትግል መክዳት ነው ፣ ይኽ ወያኔ / ኢሕአዴግ የሚባል ድርጅት እስካለ ድረስ ከእሱ የሚመጣ ምንም ዓይነት ለውጥ አይኖርም፣ ወዘተ …
’ የሚል አቋምን የያዘ ትችት ይሰማል። ይኽ የጦፈ ክርክርና ትችት ደግሞ ይበልጡን ጎልቶ የሚሰማው ከኢትዮጵያ ውጭ በሚገኘው የኅብረተሰባችን ክፍል ነው።

 

በአንፃሩ በድጋፍ-ሰጪው ጎራ በኩል ሁለት አዝማሚያዎች ይስተዋላሉ። በአንደኛው ክፍል የሚታየው ‘ አሁን አገራችን ከምትገኝበት አሳሳቢ ሁኔታና እርባና ያለው አማራጭም ካለመኖሩ አንፃር ዶ / ር ዓብይን እንበለ – ማጠየቂያ ሙሉ – በሙሉ መደገፍ ያስፈልጋል ’ ፣ የሚል ነው። በሁለተኛው የድጋፍ ዘርፍ በኩል የሚስተናገደው አስተሳሰብ ደግሞ የተለያዩ ደረጃዎች ቢኖሩትም በአብዛኛው ተቀራራቢ አመለካከትንና የፖለቲካ እምነትን ያቀፈ ሆኖ፣ ለዶ/ር ዓብይ ጅማሮ ያለው የአመለካከት አዎንታዊነትም በባኅሪው ሁኔታ-ገዝ የሆነ ቁጡብ ድጋፍ መስጠትን የሚያስተናግድ ሆኖ ይገኛል። በዚኽ አቋም አራማጆች እምነት ‘ ይኽ ክስተት በቅጡ ከተያዘና እንዳይከስም ከተደረገ በአገሪቱ ላይ ያንዣ በበውን የኅልውና – እጦት አደጋና በሕዝብ ዘንድ ያጠላውን ከፍተኛ የተስፋ መቁረጥ ስሜት በማርገቡ ረገድ ከፍተኛ ሚና አለው። በተጨማሪም የኢትዮጵያ ሕዝብ ለሚያደርገው መሠረታዊ የሥርዓት – ለውጥ ትግል በውዥንብር የተናጠውና መዘዙ – በበዛ የጎሣ – ተኮር መከፋፈል የተበከለውን የአገራችን የወቅቱ ጤና – ቢስ የፖለቲካ ይዞታ ለማስከን የሚኖረው ጠቀሜታና ያም ለብሔራዊ መግባባት ሂደት የሚያደርገው አዎንታዊ አስተዋፅዖ ከፍተ ኛና በቀላሉ የሚታይ አይደለም። ’ ከሚል ግንዛቤ የመነጨ መሆኑ ግልጥ ነው።

በቅድሚያ ዶ/ር ዓብይ ወደ-ሥልጣን የመጡት፡-  አገራችን ከፍተኛ አለመረጋጋት በሰፈነበትና ከመቸውም ጊዜ በላይ የኢትዮጵያን አንድነትና ሰላም በማይሹ ባዕዳን ኃይሎች የመከበብ ድባብ ውስጥ በምትገኝበት፣  የሕወሓት-መሩ ኢሕአዴግ የሕዝብን የመብት ጥያቄ በጥሬ-ጉልበት ለማፈን የሚከተለውን የጥፋት ሂደት የኢትዮጵያ ሕዝብ፣ በተለይም ወጣቱ ትውልድ፣ ለመብቶቹ መከበር ለሚያቀርባቸው ጥያቄዎች ከአገዛዙ አዎንታዊ ምላሽ ቀርቶ የመደመጥ ዕድል እንኳን እንደማያገኝ በመረዳቱ፣ ተስፋ-መቁረጥ በወለደው ቁርጠኝነት አሜን ብሎ ላለመገዛት ወስኖና እራሱን ከፍርሃት አላቅቆ ከአገዛዙ የአፈና መዋቅሮች ጨካኝ ታጣቂ መንጋ ጋር ለመፋለም ቆርጦ መስዋዕትነት ለመክፈል ወደ-ኋላ እንደማይል በተግባር እያረጋገጠ ባለበት፣  ቀውስን በቀውስ ከማባዛት አባዜ ጥንውት መላቀቅ ያቃተው አፄ-በጉልበቱ የሕወሓት አመራር እራሱ የሚመራውን መንግሥትና አገር ወደ ‘ሕገ-መንግሥታዊ’ የቀውስ አፋፍ እየጎተተው በነበረበት፣  በአኳያው ባለው ውጥንቅጡ-የወጣ የኃይሎች አሠላለፍ ምክንያት አንድም እንቅስቃሴው አገርአቀፍ ቅንብር የጎደለው፣ በአብዛኛው አካባቢ-ተኮር ይዘትን የተከተለ በመሆኑና ያም የእርስ-በርስ መጠፋፋትን የማስከተል ባኅሪ ስለሚኖረው በአገርና በሕዝብ አንድነት ላይ የሚያመጣው አደጋ ሁሉንም ከፍተኛ ሥጋት ላይ በጣለበት፤  ኢትዮጵያችን የሕዝብን የለውጥ ትግል ለአዎንታዊ ውጤት የሚያበቃ ተኣማኒነት ያለው ሁነኛ አገር-አቀፍ ድርጅት በሌለበት ዙሪያ-ጥምጥም ፈታኝ ሁኔታ ውስጥ በምትገኝበት፣ እና  እነዚህም ተደማምረው ኢትዮጵያ አገራዊ የኅልውና-እጦትን ለሚያስከትልና ዜጎችን ለእርስበርስ-ትርምስ ለሚዳርግ አደጋ ተጋልጣ፣ ሕዝብ ከፍተኛ ጭንቅት ላይ በነበረበት እጅግ አሳሳቢና አስቸጋሪ ወቅት ላይ በወደቀችበት፣ ወዘተ…
በመሆኑ በገዥው ክፍል የተከሰተው የአመራር ለውጥና የተካሄደበት መንገድ አነጋጋሪና ትኩረትን የሳበ ቢሆን ሊያስገርም አይችልም፤ የሚጠበቅም ነው።

ከዚኽ አጠቃላይ የውጥረት ሁኔታ እኳያ ሲታይ የዶ/ር ዓብይን ወደ-ሥልጣን መምጣት ተከትሎ የሚሰነዘሩ የተለያዩ ደረጃዎች ያሏቸው የተቃውሞም ይሁን የድጋፍ አስተሳሰቦች መንሸራሸራቸው አዲስ ሊሆን አይገባም። አነጋጋሪውና ምላሹን ዘርፈ-ብዙ ያደረገው ግን ኢትዮጵያችን በምትገኝበት በዚኽ እጅግ አሳሳቢ ወቅት በኢሕአዴግ አመራር መኻል ለውጥ የመደረጉን ክስተት በነጠላው በማየት አይደለም። የለውጡ ውጤት ብዙ ባልተጠበቀበት መልክ በመቋጨቱ ብቻም አይደለም። ጉዳዩ ልዩ ትኩረትን የሳበውና በኢትዮጵያውያን ዘንድ ተስፋንም ጨለምተኝነትንም ያዘሉ አስተሳሰቦች የመንሸራሸራቸው መንስዔ ሕዝብ ተስፋውን እያሟጠጠ ባለበትና ለባሰ የችግር-አዙሪት የመዳረግ ስጋቱ በአየለበት ጊዜ፤ በሕወሓት-መሩ ኢሕአዴግ ሃያ-ስምንት የአገዛዝ ዓመታት ውስጥ ታይቶም-ተሰምቶም በማያውቅ መንገድ ኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊነትን ከፍ የሚያደርግ አስተሳሰብን የሚያንጸባርቁ፣ ስለ እኩልነት አፋቸውን ሞልተው በግልጥ የሚናግሩ፣ ለሕዝብ አክብሮትና ከሕዝብ የሚቀርቡ ጥያቄዎችን ለማስተናገድ በጎ-ፈቃድ እንዳላቸው የሚገልጡ ወጣት ፖለቲከኛ ድንገት በሚባል ደረጃ ብቅ በማለታቸው ጭምር ነው።

የጠቅላይ-ሚኒስትርነቱን ኃላፊነት የተረከቡት ግለ-ሰብ ሁኔታዎችን በተለይም ኢትዮጵያንና ኢትጵያዊነትን በተመለከተ ያንፀባረቁት አዎንታዊ አስተሳሰብ፣ የችግሮችን መኖር ያለማመንታት ማመንና በመፍትኄው ረገድም አቀራረባቸው በተለመደው የኢሕአዴግአዊ የ‘እኔ-አውቅልሃለሁ’ የእብሪት መንፈስና የመልእክታቸውም ትኩረት በልዩነት ላይ ያጠነጠነ ሣይሆን የአንድነትን ስሜት በተላበሰ መልክ አብረን ተባብረን ‘ተደምረን’ በመረባረብ ሊሆን እንደሚገባ መሆኑ ለበርካቶች ውስጣዊ እርካታን የሰጠና በአገሪቱ ቀጣይነት ላይ የነበራቸውን ከፍተኛ ስጋት ያረገበላቸው፣ የመነመነ ተስፋቸውን በመጠኑም ቢሆን ያደሰላቸው እንደሆነ የብዙዎች እምነት ነው።

በዜጎች ዘንድ በአንድ በኩል የተስፋ በሌላ በኩል የጨለምተኝነት ድባብ በሰፈነበት ሁኔታ ሥልጣን የያዙት ዶ/ር ዓብይ ለጊዜአዊ የፖለቲካ ፍጆታ ይሁን በሃቀኛ-መንፈስ ለኢትዮጵያ ሕዝብ መልካም ለማድረግ በማሰብ በንግግር ያስደመጧቸውን አሳቦች በተግባር ለመፈጸም በጎ-ፈቃዱ ብቻ ሣይሆን ቁርጠኝነቱና ሃሞቱ ሊኖራቸው ቢችልም የሚገጥሟቸው ፈተናዎች ቀላል እንዳልሆኑ ያንኑ ያኽል ግልጥ ነው። ከልባቸው አምነውበት ለኢትዮጵያ ሕዝብ በጎ ለማድረግ በማሰብ ቀርቶ እንዲያው ድንገት ለጊዚያዊ የፖለቲካ ፍጆታ ሲሉ አጉል ተስፋ ሰጥተውም እንኳን ቢሆን የሚገጥሟቸውን ፈተናዎች መወጣቱ ከባድ እንደሚሆን አጠራጣሪ አይደለም። የተሰጠው ተስፋ ለአጭር-ጊዜ የፖለቲካ ጠቀሜታ ታስቦ ከሆነ ደግሞ ችግሮቹ የበለጠ እየተወሳሰቡ እንደሚሄዱና በሕዝብ ዘንድ የሚኖረው ምላሽም የከፋ እንደሚሆን፣ በድርጅታቸውም ሆነ በግለሰብ ደረጃም በራሣቸው ላይ የሚከተለው ኪሣራ ቀላል እንደማይሆን ሳይታለም-የተፈታ ጉዳይ ነው። ሰበቡም ለአገር እንደሚተርፍ ግልጥ ነው።

አዲሱ መሪ ባለ-ሁለት-ጎን-ስለትን ከመጨበጥ ያልተለየ ሁኔታ ውስጥ መሆናቸው ግልጥ ነው። ያም በአንድ በኩል የችግሮቻችንን ውስብስብነት አቅልሎ በማየት ለውጥ በሚፈልገው ታጋይ ሕዝብ፣ በተለይ ግን ጅማሮውን ከማደናቀፍ የፖለቲካ ትርፍ ለማግኘት ከሚከጅሉ አንዳንድ ድርጅቶች፣ እንደ ኅብረተሰብ ከባኅል አብዮት ያልተናነሰ መሠረታዊ የአስተሳሰብ-ለውጥ የሚያስፈልቸውና ሂደትና ጊዜን የሚጠይቁትን ጨምሮ ለሁሉም ጥያቄዎች ቅጽበታዊ ምላሽ በሚፈልጉ ወገኖች፤ በሌላ በኩል እነሱ ሙሉ-በሙሉ በማይቆጣጠሩት ለውጥ ጊዚያዊ ጥቅሞቻቸው እንዳይነኩባቸው ከሚፈልጉና ከሚሰጉ ስግብግቦችና እስካሁን ለሠሩት ወንጀል ተጠያቂነትን ከሚፈሩ ክፍሎች በኩል የሚገጥማቸው አይቀሬ የመሰናክል ገመድ-ጉተታ ይሆናል።

ዶ/ር ዓብይ የሚገጥሟቸው ፈተናዎች ከሁሉም አቅጣጫዎች የሚመጡ ሲሆኑ፣ በአብዛኛው በንግግር ያስደመጧቸውን በጎ-አሳቦችና የሰጧቸውን ተስፋ-ሰጪ ቃሎች ሕዝብ በጉጉት በሚጠብቀው ደረጃና ባልተራዘመ የጊዜ-ገደብ ውስጥ በተግባር መፈጸም መቻል-አለመቻላቸው ላይ ያረፈ ይሆናል ማለት ይቻላል።
አንደኛው በተለይ ለለውጥ ከሚታገለው ጎራ መኻል ያለ-አንዳች ማጠየቂያ ሙሉ ድጋፍንና ትብብርን ለመስጠት ከሚሹ ወገኖች በኩል ይሆናል። እነኝኽ ወገኖች ካላቸው ቅን አመለካከትና የተጋነነ ሙሉ ተስፋ የተነሣ ያለ ምንም ዓይነት የሁኔታ-ገደብ ለዶ/ር ዓብይ የሚሰጥ ድጋፍ ከሌሎች፣ በተለይም በአራተኛው ረድፍ፣ በኩል ሊገጥማቸው የሚችለውን እክልና እንቅፋት አቅልሎ ያዬ ወይም በተገቢ ያላገናዘበ ስለሚሆን፣ አንድም በደፈናው የሚሰጥ ድጋፍ የሕዝብ ጥያቄዎች ቸል እንዲባሉና በይደር እንዲያዙ የማድረግ ሚና ስለሚኖረው ሕዝብ የሚያድርገው ትግል ላይ ምናልባት ግለቱን እንጅ ይዘቱን ሣይለቅ እንዳይቀጥል የተወሰነ አሉታዊ አስተዋፅዖ ሊኖረው ይችላል። ያ ደግሞ የዶ/ር ዓብይ አካሄድ ለማይጥማቸውና ምክንያት እየፈጠሩ እንቅፋት ለሚሆኑ፣ በተለይ በሕወሓት አመራር ውስጥ ያሉ አክራሪዎች የሚከተሏቸውን መሠሪ የመሰናክል እርምጃዎች እንዲገፉበት መልካም ሰበብ ይፈጥርላቸዋል።

ሁለተኛው ፈተና የሚሰነዘረው የተቃውሞ ድምጽ ከሚያሰማውና በዶ/ር ዓብይ ጅምር አካሄድ ላይ አሉታዊነት የሚኖረው ምንም-ይሁን-ምን ‘ እሣት ካየው ምን – ለየው ነውና በዚኽ ሥርዓት ሥር ሲያገለግሉ ከኖሩ ይኽ ሰው ምንም ዓ ይነት ለውጥ መጠበቅ ስህተት ስለሆነ አማራጩ አንዳችም ድጋፍ አለማድረግ ብቻ ሣይሆን እንዲያውም ፋታ ሳይሰጡ ከሥርዓቱ ጋር ማስወገድ ብቻ ነው ’ የሚል አቋም ካላቸው ክፍሎች ይሆናል። የዚኽ አመለካከት ባለቤቶችና አቋም አራማጆች በሚገፉት ያላሰለሰ ዘመቻ በጋራ መቆም በሚገባው ለውጥ-ፈላጊ ክፍል መኻል እስካሁን የቆየውን ቅጡ በውል-ያልለዬ ልዩነት ይበልጥ ስለሚያሰፋ በሕዝብ ዘንድ ውዥንብር መፍጠሩ አይቀርም፤ ሕዝብ በአማራጩ ኃይል ላይ ያለውን ተስፋም ያመነምናል። ያ ደግሞ አገዛዙ ሣይነካ እንዲቀጥል የሚፈልገው የገዥው አክራሪ ክንፍ ጉዳዩን ገልብጦ ‘ ይኽውና በ ተቃዋሚው ወገን የተሰለፉት ኃይሎች ባላቸው ግትር አ ቋ ም ሁሉንም እነሱ በፈለጉት ካልሆነ በስተቀር በአገር ጉዳይ አብረን ለመሥራት በቀና – መንፈስ ያቀረብነውን ጥሪና በጎ ፈቃድ መቀበል ያቃ ታቸ ው ፣ ትኩረታቸውና ጥረ ታ ቸው ሁሉ ንደምንም ሥልጣን ለመያዝ እንጅ አገራችን ያለችበት የቀውስ ሁኔታ የማያሳስባቸው፣ ለአገራዊ – መግባባት ደንታ – ቢስና ለሰላማዊ ለውጥ ኃላፊነት ለመውሰድ የተዘጋ ጁ አይደ ሉ ም ’ የሚል የቅጥጥብ ዘመቻ ለማድረግ ይረዳዋል። በዚኽም የፖለቲካውን የመወያያ ነጥብ (አጀንዳ) ለመቀማት ቢያንስ ውዥንብር ለመንዛት በመጠኑ ይጠቀምበታል። በለውጥ-ፈላጊው ክፍል የሚኖር የአንድነት እጦት ዶ/ር ዓብይ ለሕዝብ በይፋ የገቡትን ቃል ተፈጻሚ እንዲያደርጉ የሚደረገውን ምክንያታዊና ሥርዓት ያለው ግፊት የማኮሰስ ሚና ይኖረዋል።

በእርግጥ መርኅን የተከተለ ተቃውሞ ተገቢ ነው። መርኅ ግን አንደኛ፣ ምን-ጊዜም ቢሆን ጊዚያዊ የሆነ ስልታዊ አካሄድ ለተያዘው የፖለቲካ ልዕለ-ግብ የሚረዳ መሥመርን ሊተካ ወይም ሊቀይር አይገባውም። ሁለተኛ፣ የትግል አቋም በመፈክር ብቻ የሚገለጥ ሣይሆን የታመነበትን ዓላማ እውን ለማድረግ መርኆን የተከተለ ልዕለ-ግብ-አስጨባጭ መሥመርን መከተልና ያንንም ለፍጻሜ የሚያበቃ ጥሬ ምኞት ሣይሆን ድርጅታዊ ብቃትን ይጠይቃል። የማይቀየር መተክላዊ አቋም እንጂ የግድ ያንን መተክላዊ አቋም ተግባራዊ ለማድረግ የምንከተለው የትግል ስልት አይደለም። ምክንያቱም የትግል ስልት ከነባራዊ ሁኔታዎች መቀያየር ጋር ሊለዋወጥ ስለሚችል ነው። በአንድ ወቅት የፖለቲካ ግብን ለመጨበጥ የጥቅ-ትግል መሥመርን መከተል የግድ ይሆናል። ሆኖም፣ በትጥቅ-ትግል እንዲወገድ የሚፈለገው ኃይል በአስገዳጅ ሁኔታዎች ምክንያት ያንኑ የፖለቲካ ግብ እውን ማድረግ የሚቻልበት ሁኔታ፣ ለምሣሌ መሥፈርቶችን ባሟላ መልኩ የምርጫ ፖለቲካ ተሣትፎን የሚፈቅድ ከሆነ፣ ያንን መከተል ምትክ በሌለው የሕዝብ ሕይዎትና በአገር ንብረት ላይ የሚያስከትለውን ኪሣራ ማስወገድ ያስችላል ማለት ነው።

ዞሮ-ዞሮ፣ ማንኛውም አገራዊ ፖለቲካን በተመለከተ የሚደረግ ተቃውሞ ዓላማው መሠረታዊ እምነትን (መተክልን) ያላደራደረ፣ አካሄዱ ግን ሁኔታ-ገዝ ሊሆን ይገባል። ዓላማው አገራዊና ሕዝባዊ ባኅሪ ያለው ድርጅት ደግሞ ነገሮችን ከግል ወይም ከጠባብ የቡድን ጥቅም በላይ አድርጎ ማየትን የግድ ይላል። ደፈናዊ ተቃውሞ ወይም ወገዛ በነጠላው የትግል ስልትም ሆነ ግብ-አስጨጭ መሥመር (ስትራተጂ) ሆኖ ሊወሰድ አይችልም። በኢትዮጵያ የፖለቲካ እንቅስሴ ሂደት ውስጥ ከፍተኛ መስዋዕትነት የከፈሉና ሙሉ ሕይዎታቸውን ለቆሙበት ዓላማ የሰጡ አባላት ካሏቸው ድርጅቶች ጀምሮ በቅርብ እስከተደራጁት ድረስ ያሉ ኃይሎች አገራቸው ከተደቀኑባት አደጋዎች ተላቅቃ ሕዝባቸው ሰላምን እንዲያገኝና መብቶቹ የሚከበሩበት ሥርዓት ባለቤት እንዲሆን የሚቻላቸውን በማድረግ ላይ መሆናቸው የታወቀ ነው። በተያዘው የስንጥር አካሄድ ግን አንዳቸውም የቆሙበትን ዓላማ ለግ ለማብቃት ቀርቶ በመሬት ላይ ያለውን ሁኔታ ሊቀይር የሚችል ይኽ ነው የሚባል ጫና-አሣዳሪ አቅምና ይዞታ ላይ አለመሆቸው የማይታበል አሣፋሪ ሃቅ ነው።

ስለሆነም፣ ዶ/ር ዓብይ የተናገሩትን በተግባር ቢተረጉሙ ጥቅሙ ለሁሉም ስለሚሆን፣ የሕወሓትን አክራሪ ቡድንም ሆነ ተመሣሣይ አቋም ያላቸውንና ፀረ-አንድነት ኃይሎችንና ባዕዳንን ብቻ ሊጠቅም ከሚችል ደፈናዊ ተቃውሞ ከማቀንቀንና ጥሬ ወገዛ ላይ ከመረባረብ ይልቅ በቃላቸው ለመያዝ የሚያስችል ከመቸውም ጊዜ ይበልጥ በተቀነባበረ መልክ አስገዳጅነት ያለው ጫና-አሳዳሪ አዎንታዊ እንቅስቃሴ ማድረጉ የተሻለ ይሆናል።
ኢትዮጵያውያን ቆም-ብለን መጠየቅ የሚኖርብን አሁን ካለው የአገሪቱ ሁኔታና ስብጥርጥሩ-ከወጣ የኃይል-አሠላለፍ አኳያ ከዶ/ር ዓብይ ጅማሮ መደናቀፍ ተጠቃሚው ማን ነው? በቁጥር ብዛትና በዓላማ ጥራትም ይሁን በቁርጠኝነት ረገድ የማይታሙ ድርጅቶች እጥረት አለ ማለት አይቻልም። ይሁንናም በጎ-ምኞትንና የያዝነውን ዓላማ ትክክለኛነት በሌጣው ከማስተጋባት ውጪ በተግባር ሊታይና ሊገለጥ የሚችል አገርን የሚታደግ አቅምና ይዞታ ያለው ድርጅት የትኛው ነው? አሉታዊ መልሱን ሁላችንም እናውቀዋለን።

ሦስተኛው የዶ/ር ዓብይ ቀጥተኛ ያልሆነ ፈተና የሚቀርበው ከእስካሁኑ አቀራረባቸው ተስፋ ካገኙና የሚናግሩትን ተፈጻሚ እንዲያደርጉ ማበረታታትና ይኽ አቅጣጫ ሳይቀለበስ የሚቻለውን ሁሉ ማድረግ ያስፈልጋል የሚል እምነት ካላቸው ወገኖች በኩል ይሆናል። ይኸኛው ክፍል ከላይ ሲታይ ከመጀመሪያው ምድብ ጋር የሚቀራረብ ይመስላል። ሆኖም መሠረታዊ ልዩነታቸው ይኸኛው ድጋፍ ማድረግ ያስፈልጋል ሲል ልቅ-ድጋፍ ሣይሆን ሁኔታ-ገዝ ቁጡብ ድጋፍ የሚል ነው። ማለትም፣ የዶ/ር ዓብይን አጀማመር በመሠረቱ መደገፍና ድጋፉ ግን ደፈናዊ ሣይሆን ሕዝብ ለሚታገልላቸው የመብት ጥያቄዎች አጥጋቢ ምላሽ መስጠት እንዲቻልና አገራዊ አንድነትም በአስተማማኝ እንዲከበር መሟላት ያለባቸውን መርኅ-ተኮር አሳማኝ-ምክንያዊ ማጠየቂያዎች በማስቀመጥ ነው። ሁኔታ-ገዝ-ቁጡብ-ድጋፍ አራማጅ በሆነው በዚኽ ክፍል እምነት አገሪቱን ወደ-ሰከነ-ሽግግር የሚወስድ ሂደት እውን እንዲሆን ከርቀት በመተቸት ፋንታ የዶ/ር ዓብይ አገራዊ አስተሳሰብና የአንድነት ቅኝት እንዳይቀለበስ በተቻለመጠን ሁሉም የበኩሉን አዎንታዊ ሚና ለመጫዎት ፍላጎትና በጎ-ፈቃድ በማሳየት ብቻ ሳይቆጠብ ለተገባራዊነቱ የዜግነት ግዴታውን ለመወጣት መዘጋጀትና እንደየ-አቅሙ አስተዋፅዖ ማድረግ ያስፈልጋል።

ይኽ ክፍል ለመሠረታዊ የሥርዓት-ለውጥ የሚደረገውን የሕዝብ ትግል በተቻለ መጠን መወገድ የሚችሉ ቀውሶችን አስወግዶ በአንፃራዊ አነስተኛ ኪሣራ እውን እንዲሆን ትኩረቱን በለውጡ ሂደት ላይ ያደረገ እምነትን የያዘ ነው ማለት ይቻላል። እንደሚታወቀው በለየላቸው የአምባ-ገነን አገዛዞች ሥር ያለ ሕዝብ በላዩ-ላይ የተጫነበትን አገዛዝ ለማስወገድ የሚያደርገው ትግል ፈርጀ-ብዙና መጠነሠፊ በመሆኑ፣ የሰውና የንብረት ውድመትን እንደሚጠይቅ ተደጋግሞ የታዬ ሃቅ ነው። (ከውስጥ በሚደረግ ወታደራዊ መፈንቅለ-መንግሥት የሚመጣ ለውጥ በአገር አንድነት ላይ ያሉ ስጋቶችን የማስቀረት ዕድሉ የተሻለ ሊሆን ቢችልም፣ የሕዝብን ዴሞክራሲያዊ መብቶች የመጨፍለቅ ባኅሪው የታወቀ ነው።) አምባ-ገነን የአገዛዝ ሥርዓትን ማስወገድ የትግል ልዕለ-ግብ ተደርጎ የሚወሰድ እንቅስቃሴ፣ በተለይም ደም-አፋሳሽ ኃይል መጠቀምን የሚጠይቅ ሲሆን ውጤቱ የሕዝብን ሰላምና መረጋጋት የሚያደፈርስ፣ በልዩ-ልዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች መኻል በቀላሉ የማይሽሩ ችግሮችን በማትረፍና እንዲሁም የአገር አንድነትን እስከማጣት የሚያደርሱ ዋጋን ሊያስከፍሉ መቻላቸው ይታወቃል። በተለይም እንደ ሕወሓት ዓይነት አገርን ለራሣቸው ጊዚያዊ ጥቅም በሚያስገዙና ጥቅማቸው ከሚቀር አገር ብትፈርስ ምርጫቸው እንደሆነ በሚያምኑ ጥቂት አክራሪዎች የሚመራ አገዛዝን ለመለወጥ (ለማስወገድ) የሚደረግ ትግል የቅርቡን ሣይሆን የሩቁን፣ የድርጅት ወይም የቡድን ጊዚያዊ የፖለቲካ ትርፍ ሣይሆን የአገርንና የሕዝብን ዘለቄታዊ ጥቅም ልዕለ-ግቡ ባደረገ የሰከነ አካሄድና ይዞታ ካልተመራ ውጤቱ የባሰ ውስብስብ ቀውስ ሊሆን የመቻል ዕድሉን ማጤን ያስፈልጋል።

ይኽ ማለት ከወዲሁ ዙሪያውን የዳሰሰና ለሁሉም ምናልባታዊ ሁኔታዎች ሙሉ ቅድመ-ዝግጅት ማድረግ የግድ ያስፈልጋል ማለት እንጅ የባሰ ሊከተል ይችላል ከሚል ስጋት በመነሣት አማራጩ ዝም ብሎ መገዛት ነው የሚል እንዳልሆነ በተገቢ ግልጥ ይሁን።

ለዚኽም ነው ላለፉት በርካታ ዓመታት በአገራችን የተከሰተውን ዙሪያ-ጥምጥም ችግር በተሰበጣጠረና ብኩን በሆነ የኃይል አሠላለፍ የአገር አንድነትን አስከብሮ፣ የፍትኅና የእኩልነት ሕዝባዊ ሥርዓት እውን ማድረግ አጉል ምኞት ስለሚሆን ከሁሉ በፊት አሣፋሪ የሆነውን የሁነኛ ብሔራዊ-አማራጭ-ኃይል ክፍተት መሙላት ያስፈልጋል የሚል አሳቤን በአክብሮት ሳቀርብ የቆየሁት፤ አባል የሆንኩበት ድርጅትም ይኽንኑ አስተሳሰብ ተግባራዊ ለማድረግ ያልተቋረጠ ጥረት ሲያደርግ የቆየው። ያ ዓይነት ሕዝብ አመኔታውን የሚቸረው አገር-አቀፍ አማራጭ ኃይል ቢኖር ኖሮ በአሁኑ ጊዜ በአገዛዙ ውስጥ የተፈጠረውን ሽግሽግ-ወለድ ክስተት ተከትሎ የሚታየውን አዲስ የፖለቲካ ቅኝት አገራዊ ኃላፊነትን በተላበሰ መንፈስ በአግባቡ በማስተናገድ ሕዝብ ለዳግም ቅልበሳ ሣይዳረግና አንድነቱ ሳይደፈርስ ለአዎንታዊ ውጤት በማብቃቱ ረገድ ከፍተኛ ሚና ሊኖረው በቻለ ነበር። በአሁኑ ጊዜ የተከሰተው ዋነኛ ባለቤት የሌለው የ ‘ እንደግፍ፣ አንደግፍ ’ ብትን አስተሳሰብ ውስጥም ባልተገባ ነበር።

ዶ/ር ዓብይ የሚገጥማቸው አራተኛውና ትልቁ እንቅፋት
‘ በአፍ ደጋፊ – በተግባር – አደናቃፊ ’ ከሆነው ክፍል ይሆናል። ይኽ ክፍል ከዶ/ር ዓብይ ኋላ በመሆን በአዛዥ-ናዛዥነት እራሱን የእዝል/የጀርባመንግሥት አድርጎ ለመቀጠል የሚከጅል የሕወሓት ክንፍ ነው። ይኽም በዋናነት ከሕወሓት አመራር ውስጥ ሥልጣንን የሙጥኝ በማለት ከአገርና ከሕዝብ ዘለቄታዊ ጥቅም ይልቅ በትግራይ ሕዝብ ስም ለግል ዝና ከሚጨነቁ ግብዞችና ሃብት ማካበትን ሥራዬ-ብለው ከያዙ የለየላቸው ስግብግቦች በኩል የሚቃጣ ይሆናል። ለዚኽ እኩይ ዓላማም በአፋቸው የሚደግፉ በመምሰል በተግባር ግን በተለይ ለትግራይ ሕዝብና ለሕወሓት አባላት የዶ/ር ዓብይን ኢትዮጵያዊ ቅኝትና ሕዝባዊ አቀራረብ በማጣመም ‘ በትግራይ ሕዝብ መስዋዕትነት የተገኘውን ድል አሣልፎ ለመስጠት የተወጠነ ፀረ ትግ ራዋይ እንቅስቃሴ ’ እንደሆነ አድርገው በማቅረብ፣ ለሌሎች ደግሞ እነሱ ሆን ብለው ያስቀመጧቸውና የተግባር ሰው ሣይሆኑ ባዶ-ተስፋ እየመገቡ የተነሣባቸውን የሕዝብ እንቅስቃሴ ለማብረድና ለእነሱ መልሶ መጠናከር ጊዜ እየገዙላቸው እንደሆነ አድርገው በማቅረብ ጅምሩን በእንጭጩ ለማጨናገፍ የማይፈነቅሉት ድንጋይ አይኖርም። በተለመደ መሠሪ ሥራዎቻቸውም ሕዝብ በዶ/ር ዓብይ ላይ ጥርጣሬ እንዲያድርበትና ተስፋ እንዲቆርጥ፣ የሰጧቸውን ተስፋዎችና የገቧቸውን ቃሎችም እንዳልጠበቁ ለማሳየት እንዲረዳቸው በማስላት ዜችን ከማሰርና ከማንገላታት፣ ንብረት ከመዝረፍና ተመሣሣይ ሕገ-ወጥ እርምጃዎችን ከመውሰድ አይቆጠቡም።

በተጨማሪም ጠቅላይ ሚኒስትሩ የኢሕአዴግ ‘ሕገ-መንግሥት’ የሚሰጣቸውን ሥልጣን፣ በተለይም በጦር-ኃይሉና በደኅንነቱ መዋቅሮች ላይ ያላቸውን ሥልጣን፣ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ለመንፈግ ይሞክራሉ። ሆኖም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ድፍረቱ ካላቸው፣ ይኖራቸዋል የሚል እምነት አለኝ፣ ያው ‘ሕገ-መንግሥት’ በተለይም አንቀጽ 72 እና 74 ንዑስ አንቀጽ 1 እና 13ን በመጠቀም፣ እንዲሁም በተለይ መከላከያ ኃይሉ በአንቀጽ 87 ንዑስ አንቀጽ 4 እና 5 መሠረት እንዲገዛ በማድረግ የሚሰነዘርን ትንኮሳና መተናኮል አስቀድመው ማስወገድ ይችላሉ። አልፎም አክራሪው አደናቃፊ ጉጅሌ ድንገት በምክር-ቤቱ ውስጥ ያሉ ደጋፊዎቹን በመጠቀም አላሠራቸው ካለ፣ አንቅጽ 60 ንዑስ አንቀጽ 1 እና 2ን በመጠቀም ምክር-ቤቱን መበተንና አዲስ ምርጫ እንዲዘጋጅ ማድረግ ይችላሉ። ለዚኽ ደግሞ በአንቀጽ 54 ንዑስ አንቀጽ 7 መሠረት ሕዝብን በማሳመንና የምክር-ቤቱ አባላትም በንዑስ አንቀጽ 4 ላይ ያለባቸውን ተጠያቂነት በማስገንዘብ የምክር-ቤቱን መበተን ተፈጻሚ ማድረግ ይችላሉ። ለዚኽ ሁሉ ግን ጠንካራ የሕዝብ ድጋፍ ላይለያቸውና ለአገርና ለሕዝብ ዘለቄታዊ ጥቅሞች ቅድሚያ በሚሰጡና ሁኔታዎች ለትግላቸው አመች እንዲሆኑ በሚፈልጉ ኃይሎች በኩል ሲሆን ሁኔታ-ገዝ ድጋፍ መስጠት ቢያንስ አደናቃፊ አለመሆንን ይጠይቃል።

በአፍ – ደጋፊ፣ በተግባር አደናቃፊ የሆኑት የሕወሓት መሪዎች ከእብሪታዊ መታበይና ከ‘ሁሉምይገባኛል’ የተዛባ አመለካከት መላቀቅ ቢችሉና ጊዜ ወስደው በጥሞና ቢያስቡበት፣ በዶ/ር ዓብይ የተያዘው አዲስ የፖለቲካ ቅኝት ከማንም በላይ እነሱን የሚታደግ መሆኑን በተገነዘቡ ነበር። የሕዝብ ቁጣ በተባባሰ መልክ ቀጥሎ ከሥልጣን ቢወገዱ ከማንም በላይ ሁሉንም የሚያጡትም ሆነ ለሚከሰተው አይቀሬ ትርምስና የአገር አንድነትን አደጋ ላይ በመጣል በታሪክ ተጠያቂ የሚሆኑት እነሱ መሆናቸውን ሊረዱ ይገባል። ይኽን ጅማሮ በበጎም ባይሆን ችግሮችን በሰላም ለማስተናገድ የሚያስችል መራር መድኃኒት አድርገው ቢወስዱት ቢያንስ በታሪክ ተጠያቂነትን ከእነሱ አልፎ ለልጅ-ልጆቻቸው ያለማውረስ ዕድል ይሰጣቸዋል።

እስካሁን በሥልጣን ላይ በቆዩበት ጊዜ ሁሉ የሠሯቸው መልካም ነገሮች ሊኖሩ ቢችሉም እንኳ፣ በእነሱ ላይ ያለው ተቃውሞ ከቀጠለ ግን ሲታወስ የሚኖርው መጥፎ ሥራቸው ብቻ ይሆናል። የጉጅሌው አባላት ጨርሶ መርሳት የሌለባቸው ሁለት ተያያዥ ጉዳዮችን ነው። አንደኛ፣ ጭቆናና ግፍ የመረረውን ሕዝብ እስከወዲያኛው በጥሬ-ጉልበት መግዛት እንደማይቻልና ምናልባት ይዋል-ይደር እንጂ ምን-ጊዜም አቸናፊው ሕዝብ እንደሆነ፤ ሁለተኛ፣ ያለ-ውዴታው ጥሬ-ጉልበትን በመጠቀም በግድ የተያዘ ሕዝብ መብቶቹን ለማስከበር የሚያደርገው ፍልሚያ ያላስፈላጊና ቢያንስ ሊደርስ የማይገባው የሰው ሕይዎትን ያጠፋል፣ ውድመትን ያስከትላል። ችግሮች በሰላም ሣይሆን በኃይል እንዲፈቱ ከተደረገ ለእልቂቱና ለውድመቱ ሁሉ ተጠያቂዎቹ ተቸናፊ በሚሆነው መንግሥት ሥር ቁልፍ የኃላፊነት ቦታ የያዙት ስለሚሆኑ በእነሱና በተባባሪዎቻቸው ላይ የሚኖረው አፀፋ እጅግ የከፋ ይሆናል

ጉዳዩን ይበልጥ የሚያካርረውና አፀፋውን አስከፊም አፀያፊም የሚያደርገው ደግሞ አስጠያቂው ወንጀል በአንድ የተወሰነ የአገሪቱ ማኅበረሰብ (በትግራይ ሕዝብ) ስም በሚንቀሳቀስ ድርጅት፣ ያውም አገራዊ ሥልጣን በያዘበት ሃያ-ስምንት ረጅም ዓመታት ለዘለቀ ጊዜ መሆኑ ነው። የሕወሓት አመራር አባላት ለተጠናወታቸው እብሪት ምንጩ አንድም በመንግሥቱ ኃይለ-ማርያም አገዛዝ የተንገፈገፈው የኢትዮጵያ ሕዝብ በሩን ከፍቶ ከስንቅ ማቅረብና መንገድ ከመምራት እስከ መዋጋት ድረስ ባደረገው ተጋድሎ ደርግን ማስወገድ መቻሉን ጠቅላላ የኢትዮጵያን ሕዝብ እንዳንበረከኩ ከመቁጠር፤ እንዲሁም የፈለጉትን ሲያደርጉ ሕዝብ በትእግሥት መመልከቱን እንደ ፍርሃት ከመቁጠር ግብዝ መታበይ መሆኑ አጠራጣሪ አይደለም።

ሕዝብ የሚደግፈውና በብሔራዊ-መግባባት የአገር አንድነትን፣ ፍትኅንና የዜጎች እኩልነትን የሚያረጋግጥ ሥርዓት የማስገኘት ዕድል የሚኖረውን የለውጥ ጅማሮ ለማደናቀፍ መከጀል ሲበዛ ጤናቢስነት ይሆናል።
አምስተኛ የመሰናክል ጥረት የሚመጣው ልዩ-ልዩ ጥቅማ-ጥቅም ይቀርብናል ብለው ከሚያስቡ አካባቢ ይሆናል። ከዚኽ በኩል የሚገጥማቸው በተለይ የአገሪቱ የውጭ-ምንዛሬ እጥረትን ለማባባስ የሚደረግ ጥረት ቢሆንም ለመቋቋም አንፃራዊ ቅለት ይኖረዋል።

የማደናቀፉ ሙከራ ግን በአገር ውስጥ ካሉ ክፍሎች ብቻ የሚሰነዘር አይሆንም። ስድስተኛው የመሰናክል ጥረት የአገራችንን አንድነትና ሰላም ከማይፈልጉና ጥንካሬዋን በስጋት ከሚመለከቱ በቅርብም በሩቅም ካሉ ባዕዳን በኩል ይሆናል። በአገር ውስጥ የሚደረገውን ሕዝባዊ የተቃውሞ እንቅስቃሴ የውስጥ አንድነትን ያናጋል ከሚል አጉል ተስፋ እንዲፋፋም የሚችሉትን መሠሪ መተናኮል ሲያደርጉና ውጤቱንም በጉጉት አንጋጥጠው ሲጠብቁ ከነበሩ፣ የመገነጠል ጥያቄ ያነገቡ ቡድኖችንም ሲረዱ ከነበሩ ግብፅን ከመሣሰሉ አገሮችና ሸዓብያን ከመሰሉ የእነሱ ጉዳይ አስፈጻሚዎች በኩል የዶ/ር ዓብይን አካሄድ ለማደናቀፍ መውተፍተፋቸው የሚጠበቅ ነው። ከነዚኽ ኃይሎች የሚሰነዘረው አደናቃፊ ሙከራ ቀጥተኛ ሣይሆን የመገንጠል ጥያቄ ይሁን አክራሪ ዝንባሌን ያነገቡ እንዲሁም በልዩ-ልዩ ምክንያቶች በተመቃውሞ ዘርፍ የቆሙ ቡድኖችን በመርዳትና በማደፋፈር የሚደረጉ ሁከት-ፈጣሪ እንቅስቃሴዎችና በተለይ በልማት ተቋማት ላይ ያነጣጠሩ እርምጃዎች ሊሆኑ ይችላሉ። ዜጎች በግልም ሆነ በቡድን በአገሪቱ የፖለቲካ ሕይዎት በሰላም ተሣታፊ ለመሆን  ኔታዎችከተመቻቹላቸውና መብታቸው ከተከበረ፣ የባዕዳን መሣሪያ የሚሆኑበት ምክንያት አይኖርም። መብቶች በተከበሩበት ሁኔታ በልዩ-ልዩ ምክንያቶች የአገርን አንድነት ለመፈታተን የሚሞክሩ ቡድኖች ሙሉበሙሉ ሊኖሩ አይችሉም ባይባልም፣ ችግሩን መቋቋም ከባድ አይሆንም።

 

‘ሽህ-ሠሪ፣ አሥር-ሽህ አነዋሪ’ እንደሚባለው፣ መቸም ትችት፣ በተለይም አገራዊና ሕዝባዊ ኃላፊነት ለማይሰማውና ለሚሰነዘሩ አስተያየቶችና ትችቶች የተጠያቂነት መንፈስ ለሚጎድለው ሰው ቀላል ሊመስል ይችላል። ዶ/ር ዓብይ ድርጅታቸው ኢሕአዴግ ለጠቅላይ ሚስትርነት ከመረጣቸው ጀምሮ በግለሰብም በድርጅት ደረጃ የተለያዩ አስተያየቶችና አቋሞች ተሰንዝረዋል። በተለይ በተቃውሞ ከተሰጡት አስተያየቶችና ከተወሰዱት አቋሞች ውስጥ፣ ከሞላ-ጎደል ከሁሉም ማለት ይቻላል፣ አብዛኞቹ ቅድመ-ዶ/ር ዓብይ፣ ከዶ/ር ዓብይ መመረጥ ወዲኽ እና ዶ/ር ዓብይ ለሕዝብ የሰጧቸውን ተስፋ-አጫሪ አስተሳሰቦችን በተግባር ላይ ማዋል ቢችሉ ወይም በግልባጩ ቢሰናከሉ በአገር አንድነትና በሕዝብ የመብቶች-መከበር ጥያቄ ላይ የሚኖረው አንደምታ፤ እንዲሁም ጅማሮው በስኬት ወይም በመደናቀፍ ቢቋጭ ወደፊት በአገራችን ሊከሰቱና ሊኖሩ በሚችሉ ኩኔቶችና ሁኔታዎች ላይ የነበራቸውን፣ ያላቸውንና ሊኖራቸው የሚችለውን ጫና-አሣዳሪ አስተዋጽዖ በተመለከተ በግልጥ የተቀመጠ ምልከታ አላየሁም። በእኔ እምነት ምን-ጊዜም ቢሆን ለማንኛውም ጊዚያዊ ክስተትም ይሁን አጠቃላይ ሁኔታ በነጠላው የቆመና የተራቆተ ድጋፍም ሆነ ደፈናዊ ተቃውሞ ውጤቱ አሉታዊ ነው።

አንዳንድ ወገኖች በዶ/ር ዓብይ ላይ ላላቸው ጨለምተኛ አስተሰብ በምክንያትነት የሚያቀርቡት መከራከሪያ የሚገርም ሆኖ አገኘዋለሁ። አንዳንዶች ‘ ይኽ ሰው አሁንም ድርጅቴ ኢሕአዴግ ነው፣ የምሠራውም በድርጅቴ መመሪያ ነው፣ ሕገ – መንግሥቱ እንዲነካ አይፈልግም፣ ኢሕአዴግ በሥልጣን ላይ እንዲቀጥል ይፈልጋል፣ ወዘተ .. .’ ይላሉ። አዎን፣ ሁሉም ትክክል ነው። ጥያቄው ግን የተባለው ለውጥ እኮ ኢሕአዴግን ያስወገደ አብዮት አይደለም፤ ዶ/ር አብይንም የመረጣቸው ድርጅታቸው ኢሕአዴግ እንጅ ሕዝብ ወይም ተቃዋሚው አለመሆኑን፣ የሚመሩትም በኢሕአዴግ ሕገ-መንግሥት፣ ተጠሪነታቸውም ለዚሁ መሆኑን ያፈጠጠ ሃቅ ማን ይክዳል። ዶ/ር ዓብይ የማንም ተቃዋሚ ድርጅት አባልም፣ ወኪልም እንዳልሆኑና በሕዝብ ግፊት ምክንያት በኢሕአዴግ ውስጥ በተደረገ ሽግሽግ-ወለድ ሂደት ወደ-ሥልጣን የመጡ መሆናቸው ሊዘነጋ አይገባም። በለውጥ-ፈላጊው በኩል ከምንገኝ ወገኖች የሚቀነቀን ያ ዓይነት አስተሳሰብ መሠረቱ ዶ/ር ዓብይ እኛ ታግለን ማምጣት ያለብንን ለውጥ ለምን አላስገኙም የሚል እሳቤን ያዘለ ከመሆን አያልፍልም። ያ ደግሞ በተለያዩ መሥመሮች ሲጓዙ ከቆዩ ተቀናቃኝ ክፍሎች፣ ቢያንስ በመጀመሪያ ደረጃ ወይም በጋራ ድርድር ከሚደረስ የጋራ ግንዛቤ ላይ ተመሥርቶ በሚነደፍ የጋራ ትልም ካልሆነ በስተቀር፣ ሊደረግ የሚችል አይደለም።

ቁም-ነገሩ ያለው በገሃድ ከሚታይና ከማይካድ ሃቅ ላይ ሣይሆን፣ የዶ/ር ዓብይ ጅማሮ ለአገርና ለሕዝብ ይጠቅማል ወይስ አይጠቅምም? ለምንፈልገው የሥርዓት ለውጥ እውን መሆን ይረዳል ወይስ አይረዳም? ይኸ በሕዝብ ትግል ከውስጥ የተጀመረ አዲስ አቅጣጫ የአገርን አንድነት አስከብሮና ሕዝብ በመፃዒዕድሉ ላይ ያለውን ከፍተኛ ስጋት በማስወገዱ ረገድ ያለውን አስተዋፅዖ እውቅና መስጠትና በተለያዩ አሉታዊ ኃይሎች እንዳይቀለበስ የሚቻለውን ሁሉ ማድረጉ ለመሠረታዊ የሥርዓት ለውጥ የሚደረገውን ትግል የተሻለ መልክ ለማስያዝ ይረዳል ወይስ አይረዳም? ምኞት ሣይሆን በተጨባጭ ተግባራዊ የሚሆን አሳማኝ አማራጩስ ምን ነበር? ለሚሉት ጥያቄዎች ከምናገኛቸው ሃቀኛ መልሶች ላይ ነው። እዚኽ ላይ ብዥታ የፈጠረና ግልጥ መሆን ያለበት ጉዳይ አለ። የዶ/ር ዓብይን አስተሳሰብ፣ አቋምና ተግባር የምንመዝነው አገዛዙ የሚከተላቸውን መርኆዎችና ተግባሮች በተቃወምነውና እንዲለወጥም ለአገሪቱ ይበጃል የሚለውን ዓላማ እንግበን በምንታገለው ወገን በኩል ባለነው ሚዛን ሣይሆን፣ ከዚያው ከሥርዓቱ ውስጥ ያለ አንድ መሪ ከሚያንፀባርቀውና ከሚያደርገው በመነሣት እንደሆነና፣ ያም ለቆምንለት አገራዊና ሕዝባዊ ዓላማ ልዕለ-ግብ ከሚኖረው አስተጋብዖ አኳያ ሊሆን ይገባል።

ከዶ/ር ዓብይ ወደ ሥልጣን መምጣት ጉዳይ በተያያዘ ሣልጠቅስ የማላልፈው አቶ ኃይለ-ማርያም ደሣለኝን በተመለከተ ይሆናል። አንዳንድ ሰዎች ዕድሜ-ልካቸውን ከሠሩት ሥራ ይልቅ ከራሣቸው በላይ ለሆነ ሕዝባዊና አገራዊ ዓላማ እራሣቸውን አሳልፎ በመስጠት በሚከፍሉት የሕይዎት መስዋዕትነት ወይም በሚወስዱት ያልታሰበና ያልተጠበቀ ደፋርና ቁርጠኛ እርምጃ ይወደሳሉ፣ ይወሳሉ፣ ይከበራሉ። በዚኽ መንፈስ በበኩሌ አቶ ኃይለ-ማርያም ደሣለኝ ከተሰጣቸው ሥልጣን-አልባ የጠቅላይ ሚኒትር ኃላፊነት ለመልቀቅ በወሰዱት ደፋር እርምጃ አክብሬአቸዋለሁ። ውሣኔአቸውም ለዶ/ር ዓብይ ወደ ሥልጣን መምጣት አስተዋፅዖ እንዳደገረ ይነገራል። በተለይ የዶ/ር ዓብይ ጅማሮ አዎንታዊ የለውጥ ሂደትን የሚከተል ከሆነ፣ አቶ ኃይለ-ማርያም በአገሪቱ የወደፊት ዕጣ-ፈንታ ላይ በበጎ የሚመዘገብ የታሪክ አሻራ እንደተው እቆጥረዋለሁ።

እንዲሁም አቶ ለማ መገርሳና አቶ ገዱ አንዳርጋቸው ቀደም-ሲል ባራመዱት ቋንቋን መሠረት ያደረገ የፖለቲካ ቅኝትና በተከከተሉት አደረጃጀት ለሕወሓት አገዛዝ ምርኩዝ ሆነው አገልግለዋል የሚል ነቀፌታ ሲሰነዘር መቆየቱ ቢታወቅም፣ የሕወሓትን ሕዝብ-ከፋፋይና መሠሪ አካሄድ ማስቆምና ሕዝብን መታደግ የሚቻለው ዞሮ-ዞሮ የትም የማያደርሰውን መከፋፋል ትቶ ኢትዮጵያዊ አንድነትን ማቀፍ እንደሚሻል በወሰዱት ምሣሌአዊ እርምጃ ኢትዮጵያን ከጥፋት የማዳን አስተዋፅዖ አድርገዋልና ከበሬታ ችሬአቸዋለሁ። ለዚኽ ሁሉ የአንድነት መንፈስ መንሠራራት ፈር-ቀዳጅ የሆነው የሐምሌው ታሪካዊ የጎንደር ትዕይንተ-ሕዝብ ምን-ጊዜም በታሪክ ሲወሳ የሚኖር እንደሆነ አልጠራጠርም። በአምቦና በሌሎች አካባቢዎች ያሉ ወጣቶች ያደረጉት ተጋድሎ ለዚኽ ሕዝባዊ ነውጥ አለመክሰም ያደረገው ታሪካዊ አስተዋፅዖም ሊረሣ አይችልም።

በመንፈሰ-ጠንካራነታቸው ለቆሙበት የዜጎች መብት መከበርና ለሙያ ነፃነት በእስር ለተንገላቱና በከፈሉት ስቃይ ኢትዮጵያዊ ወኔንና ኩራትን ከፍ ላደረጉ ጋዜጠኞች፣ አምደኞችና ጦማሪዎች፣ እንዲሁም የፖለቲካ ድርጅት መሪዎች አሁን ለታየው የለውጥ ክስተትም ሆነ ወደፊት ለፍሬ ለሚበቃው ሕዝባዊ ትግል ባደረጉት መሰል-የሌለው ድርሻ ሊኮሩ ይገባቸዋል፣ በበኩሌ አክብሮቴና አድናቆቴ አይለያቸውም እላለሁ።

ሁሉም የማኅበረሰብ ግንኙነቶች በአገሪቱ የሠፈነውን ጎሣዊ-ልዩነት ላይ ያተኮረው የፖለቲካ ቅኝትን መከተል ዘይቤ በሆነባት ኢትዮጵያችን፣ ስለ ኢትዮጵያ ታላቅነትና በክቡር መስዋዕትነታቸው አገራቸውንና ወገናቸውን ስላስከበሩ የአገር ባለውለታ አርበኞቻችንን አዲሱ ትውልድ እንዲያውቃቸው፣ እንዳይረሱና ታሪክ ሲዘክራቸው እንዲኖር በኪነታዊ ሙያቸው የኢትዮጵያዊነት መንፈስ አንገቱን ቀና እንዲያደርግ ያስቻሉ ወገኖች ሊመሰገኑና ሊበረታቱ ይገባል።

አቶ መለስ ዜናዊና አቶ ኃይለማርያም ደሣለኝ
የብሔር፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች በኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር፤ ዶ/ር ነጋሶ ጊዳዳ፣ መቶ-አለቃ ግርማ ወ/ጊዮርጊስና ዶ/ር ሙላቱ ተሾመ እንዲሁ የብሔር፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች በኢትዮጵያ ፕሬዝደንት እንደነበሩ ነው ሣያቸው የነበረው። ዶ/ር ዓብይ አሕመድ በአሁኑ ጊዜ ከሚያንፀባርቁት የአንድነትና የኢትዮጵያዊነት ቅኝት አኳያ ግን በሕወሓት-መሩ የኢሕአዴግ መንግሥት የሃያ-ስምንት ዓመታት የአገዛዝ ዘመን ውስጥ የመጀመሪያው የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር የመሆን ዕድል አላቸው የሚል ግምት አለኝ።

በመጨረሻም፣ ዶ/ር ዓብይ አሕመድ ከሁሉም አቅጣጫዎች በሚወረወሩ ጊዚያዊ የፖለቲካ ውዥንብሮች ከመንገዳቸው ሣይወጡ በጀመሩት የኢትዮጵያዊነትና የአንድነት የፖለቲካ ቅኝት ወደ-ኋላ ሣይሉ እንዲቀጥሉበትና በአንዲት አገር ሕዝብ መኻል ቋንቋን መሠረት ያደረገ ከፋፋይ የልዩነት አጥር ጨርሶ እንዲነቃቀል፣ ኢትዮጵያዊያን ካለፈ የጋራ ታሪካቸው በላይ የማይነጣጠል የወደፊት ዕጣ-ፈንታቸው ይበልጥ የተሳሰረ በመሆኑ በጋራ ቆመው አገራቸው ከመቸውም ጊዜ የበለጠ አንድነቷ የተከበረ፣ ፍትኅ፣ እውነተኛ የዜጎች እኩልነትና የሕግ የበላይነት የሠፈኑባት እንድትሆን ሁላችንም ከተቃውሞ ሥነ-ልቦና በመላቀቅ በምንችለው ደረጃና አቅም የሚጠበቅብንን አስተዋፅዖ ካደረግን የጋራ የሆነችውን አገራችንን ልንታደግ እንችላለን። ለዶ/ር ዓብይ ጅማሮ የሚደረግ ሁኔታ-ገዝ ማበረታታት በተባበረ፣ በተጠናከረናመርኅን በተከተለ ሁኔታ ከተደረገ ለማክሸፍ የተሠለፉት ኩምሽሽ እንዲሉ፣ እሣቸውም ቃላቸውን እንዳያጥፉ ለማስገደድ ያስችላል።

ይኽንን በማድረግ የሚፈለገውንና የምንጠብቀውን ውጤት በምንፈልገው ደረጃና መጠን ማግኘት ቢያቅተን እንኳን፣ ቢያንስ ቢያንስ ለቀጣዩ ትግል የተሻለ ይዞታ ላይ እንደሚያደርሰን አምናለሁ።

ከጥቂት ዓመታት በፊት “ ለውጥ በኢትዮጵያ፤ ድኅረ – ሕወሓት / ኢሕአዴግ – ምን ዓይነት ሽግግር፣
እንዴት ?” (*1) በሚል ርእስ ባቀርብኩት ረዘም-ያለ ጽሑፍ ላይ ኢትዮጵያ አገራዊ አንድነቷ ተጠብቆ የፍትኅና የእኩልነት ሕዝባዊ ሥርዓት እውን እንዲሆን በቅድሚያ በአገራችን ላይ የሠፈነውን ሕዝብን እርስ-በርሱ የሚያናክስ ከፋፋይ የፖለቲካዊ-ጎሠኝነት ቅኝትና እሱንም የተከተለ የአደረጃጀት ዘይቤ በኢትዮጵያዊ የአንድነት ቅኝት መቀየርና ለዚኽም በዚሁ አሣፋሪና ወደ-ኋላ ያዬ የውዥንብር ፖለቲካ የተናጠውን ፖለቲካችንን ማስከን የሚችል የአደራ መንግሥት እንደሚያስፈልግ ጠቅሸ ነበር።

ዶ/ር ዓብይ በጀመሩት መሥመር ቢቀጥሉና እንዳይቀለበስ ርብርብ ቢደረግ ያንን ሚና ሊጫዎቱና ቀጣዩ ምርጫ ዓለም-አቀፍ መሥፈርቶችን ባሟላ መልኩ ነፃ፣ ፍትኃዊና ርቱዓዊ እንዲሆን ሁኔታዎችን ሊያመቻቹ ይችላሉ የሚል እምነት አለኝ። ያንን ማድረግ ከቻልን ደግሞ ኢትዮጵያችንን ከአሥር ዓመታት ባልበለጠ ጊዜ ውስጥ አንድነቷና ሰላሟ የተጠበቀ፣ ሰው-ሠራሽ ረሃብና ችግር የተወገዱባት፣ ዜጎቿ ባመቻቸው መንገድ ሁሉ ጥለዋት ለአዋራጅ ስደት የማይዳረጉባትና ውጭውን አንጋጥጠው በመመለከት ፈንታ የወጡት ወደ አገራቸው ለመመለስ በጉጉት የሚናፍቋትና ተመልሰው የሚኖሩባት፣ የፖለቲካ እስር-ቤቶች ተረት የሚሆኑባት፣ የበለፀገችና ለቀሩት የአፍሪቃ አገሮች ዳግም ጥሩ ምሣሌና አርኣያ እንደምትሆን አልጠራጠርም።

ኢትዮጵያውያን እራሣችንን እንደ-አንዲት-አገር-ዜጎች በማየት በጋራ ከቆምን፣ የአምባ-ገነን አገዛዞችን አዙሪት ለመስበርና ሁሉም አትራፊና-ተጠቃሚ የሚሆንበት ፍትኃዊ ሥርዓት ባለቤት መሆን እንችላለን። ይኽንን ለማድረግ ግን ከተቃውሞ ሥነ-ልቦና መላቀቅና ኢትዮጵያችን የሁሉም ዜጎቿ፤ የአሳሪውም፣ የታሳሪውም፤ የአሰዳጁም የተሰዳጁም፣ የድሃውም፣ የሃብታሙም፣ የአቸናፊውም፣ የተቸናፊውም መሆኑን መቀበል፤ በልዩ-ልዩ መንግሥታትም ሆነ፣ ድርጅቶች፣ ቡድኖች ወይም ግለሰቦች የተሠሩ መልካምም ሆኑ መጥፎ ድርጊቶች፤ የጋራ ታሪካችን አካል መሆናቸውን እምነን መቀበልና መጥፎው እንዳይደገም ትምህርት ሆኖን፣ ጥሩውን በኩራት ተንከባክበን ግን የበለጠ ለመሥራት ቆርጠን መነሣት ያስፈልጋል እላለሁ።

‘አንድ ስንሆን እንጠነክራለን፣ ስንከፋፈል እንወድቃለን’ እንደሚባለው፣ እንድነት፣ ከአንድነትም በእኩልነት ላይ የተመሠረተ አንድነት፣ ጠቀሜታው አጠያያቂ አይደለም። በመሆኑም፣ በልዩነት ላይ በማተኮርና በመከፋፈል እራስን ለጥቃት ላለማጋለጥና ለጥቂት አምባ-ገነኖች አገዛዝ መደላድል ላለመሆን አንድነታችን ይጠንክር።

ኢትዮጵያዊነት አቸናፊ መንፈስ ነው! አምላክ ኢትዮጵያን ይባርክ!! አንድነቷን ይጠብቅ!!! በነፃነቷ ታፍራና ተከብራ ትኑር!!!