በእኛ ደካማነት እምዬ ኢትዮጵያን በድፍረት አናኑራት!
ግንቦት ፩ ቀን ፪ሺህ፲ ሎንዶን
የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዝብ ልጆች ሆይ፦
በጥንት ዘመን ጦርነት ላይ አንዱ ወገን ሰንደቅ ዐላማውን ካስማረከ ድል ኾነ! ማለት ነበር። ስለዚህም ላለማስማረክ የሚደረገው ጦርነት አጨራራሽ ነበር። ባለንበት አሳፋሪና አሰቃቂ ዘመን በጠላት መሣሪያነት ወገን መስለው አገር የያዙት በመጀመሪያ የዘመቱት በሰንደቅ ዐላማችን ላይ እንደነበር ዕድሜ የፈቀደላችሁ ታስታውሳላችሁ።
ም/ቤት ተብዬው ውስጥ እንኳን ከነሻለቃ አድማሴ ጋር የተደረገውን ትግል የምታስታውሱ አትጠፉም፤፡ የአባታችን የቢትወደድ/ሱልጣን አሊ ሚራህ “ሰንደቅ ዐላማችንን እንኳን ሰዉ ግመሎቻችን ያውቁታል!” የጠላትን ክርክር “ ግባ-ተመሬት!” ወረወረው። ግን ባልሞት ባይ ተጋዳይነት “ የሰይጣን ምልክት “ ያለበት ላይ የሱዳን መተተኛ ሰረዞች ጨምሮበት እንደተገደልን እንደቆሰልን እንደተዋረድን አለን ለ ፳፯ የሃዘን ዓመታት::
የሱዳኑን መተተኛ ነገር እንዴት ዐወቅህ? የሚል ተገቢ ጥያቄ ሊነሳ ይችላል። አጭሩ መልስ “ በአጋጣሚ!” ነው። አንድ ቀን አውቶቡስ ውስጥ ከአንዲት ያገር ልጅ መሰል ጋር አብረን ተቀምጠን “ ሰላም ! ሰላም ! ስንባባል ንግግራችን ከዚያ ሊያልፍ ባለመቻሉ ተሳሳቅንና “ኢትዮጵያዊት መስለሽኝ!” “ እኔም ሱዳናዊ መስለኸኝ ተባብለን – ‘አንድ ነን!’ በመባባል ተስማምተን ቀጠልን። ከዚያ – “ መለስን ትወድደዋለህ” አለችኝ። እኔም ለምን “ጠየቅሽኝ?” ስላት ዘከዘከችው። ዩኒቨርሲቲ በነበረችበት ጊዜ ብዙ ነገር ቃል ገብቶ እንደዋሸ፡ ነገረችኝ። “ምን-ምን?” ስላት ሊሰጣቸው ቃል የገባውን የለም መሬቱን ዝርዝር ዘከዘክችና እንዲያውም “ አባቴ እጅግ ዝነኛ ዐዋቂ ነው። በሰንደቅ ዐላማችሁ ላይ መስመሮቹን የጨመረለት እሱ ነው። “ ስትል የኹለታችንም መውረጃ ደርሶ፦ እንደአጋጣሚ ኹለታችንም ባለቀጠሮዎች ስለነበርን እኔ አድራሻዬን ( ካርድ) ሰጥቼአት እንድንገናኝ ተስማምተን ተለያየን።
በጨዋነት ደወለች፦ ግን ልንገናኝ እንደማንችል በሃዘን ድምጽ ነገረችኝ። ምክንያቱን ስጠይቃት “ አንተ አክራሪ አገር ወዳድ ነህ ብለው ዳግመኛ እንዳላነጋግርህ አዘዙኝ። አኹን የማነጋግርህ ስለአከበርሁህ ትእዛዝ አፍርሼ ነው።” ብላ ዘጋች። ይህን ኹሉ የማዘበዝበው ክብራችንን ለማስመለስ ቀላል ስለኾነ ወገንን ለማንቃት ነው። ይህን አስማት ጥለን/አስጥለን ታሪካዊቷን ሰንደቅ ዐላማችንን ለአገር-ለወገን ለማስረከብ ነው።
የማድረግም ግዴታ የእኛ የልጆችዋ ነው !!!
፩ኛ፦ መሲሃቸው ሟቹ “ ሕዝቡ ከፈለገ ሊያደርገው ይችላል።” ያለውን በአባሪነት አቅርቤአለሁ
፪ኛ፦ ሕዝቡ መፈለጉን ማሳያው በሕብረት ሰንደቅ ዐላማውን ይዞ ወጥቶ እምዬ ምኒልክ ከአድዋ በድልአድራጊነት በጀግና ሠራዊታቸው ታጅበው መዲናቸው የገቡበትን ግንቦት ፲፭ን በነቂስ ወጥቶ ሲያከብር ነው። ሼሁና ቄሱ ይህን የሰይጣን ሥራ አውግዘው ይቀሰቅሳሉ ባይባሉም፦ አንዳንዶች መውጣታቸው አይቀርም። ይህን ለማስተባበር ፕሬዚዳንት ኬነዲ ከ፳ ዓመታት በፊት አፍሪካን ሲጎበኙ መዲናችንን የመጀመሪያ ለማድረግ የጨረሱትን ዕቅድ ያስለወጠው የኢትዮጵያ ልጆች በስደትም ታሪክ በመሥራት በዓለም ላይ ( አውሮፓ – አሜሪካ – እስያ – አፍሪካ – ኦስትሬሊያ ደቡብ አሜሪካ ..).በአንድ ቆመን ፕሬዜዳንቱን አስቀረናቸው። ያኔ መገናኚያችን ስልክ ብቻ ነበር።
ታዲያ አኹን እንዲህ በተምበሸበሽንበት ጊዜ ዘላለማዊ ክብራችንን ማስመለስ ያቅተናል?! አባት-እናት አርበኞቻችን አድዋን በባለመተቱ ሲያከብሩ ያለቅስን እንጠፋለን? አኹን ግን “የክቱ የአዲስ አበባው አንበሳ “ብቅ ይበለና” ከቄሮዎችና ከፋኖዎች እንዲሁም ከዘርማ እህት ወንድሞቹ ጋር ኾኖ እናት አባቶቹን አክስት አጎቶቹን አጅቦ ክብራችንን ባያስመስልስ የእምዬን አዋጅ ያስታውስ። እንዲያውም ዛሬ ልደታ ነች ለካ!! “ ወስልቶ የቀረውን አልምረውም።ማርያምን ለዚህ አማላጅ የለኝም!” ስለዚህ ታሪክ አይምርህም።ኅሊናህም ዕድሜ ልክህን አያሳርፍህም። ሀፍረትን ለብሰህ ዕድሜህን ኹሉ ትገፋለህና!! ምርጫህን ዕወቅ! የታሪክ ግዴታህን ተወጣ!
የፖለቲካና ሕዝባዊ ድርጅቶች ቀስቅሱ፦ ሕዝባዊ መገናኝያ ድርጅቶች ለአገር ለወገን ክብር ከወትሮአችሁ የበለጠ እንደምትቀሰቅሱ አልጠራተርም።
በቀጣዩ እሁድ በ፲’፱ “ ለአባይ እሮጣለሁ!” የምትሉት ኹሉ በታሪካዊቷ ሰንደቅ ዐላማችሁ ደምቃችሁ “ ለእናት ኢትዮጵያ እሮጣለሁ!” በሉ። ከከለከሏችሁ ወደቤታችሁ። ግን እንደማይከለክሏችሁ፦ እኔም እናንተም እናውቃለን።
ኢትዮጵያችንን አምላኳ ይጠብቃታል! ልጆችዋም ግዴታችንን እንወጣለን !!!
ጥላሁን ገሠሠ ፤- ኢ ኢ ኢ ት ዮ ጵ ያያያ! የኛ መመኪያ ሲል።
እኛስ ዛሬ የኢትዮጵያችን መመኪያ እንኾናልን ? ! ? !
ጠ. ሚኒስትር ሆይ፦ ይህ “ብርቱና ቀናኢ ሕዝብ” እንዲሁም ሃይማኖተኛ! ቃል እንዲከበርለት ይወድዳል። ለኅሊናና ለቃል ሳይኾን ታሪኩን ለማክበር በወጣው ሕዝብ ላይ
ለኢ-ሕጋዊውና ጸረ ታሪክ አዋጅ በመገዛት፦ ከምካከሉ አንድ እንኳን ቢጎዳ የሚያስከትለውን መገንዘብ ዐዋቂነት ነው። የመጀመሪያውን ግልጽ ደብዳቤየን መመልከቱም ደግ ነው።
ኮማንደር አሰፋ ሠይፉ
