May 23, 2018 – አጠቃላይ
ምሕረት ዘገዬ (mz23602@gmail.com)
ከጠቅላላ ዕውቀት ግብይት ባለፈ ብልኅና አስተዋይ ትግሬዎች ይህን ወረቀት በተለዬ ትኩረት ቢያነቡልኝ ደስ ይለኛል፡፡ ሕወሓት በኢትዮጵያና ሕዝቧ ላይ ያደረሰውንና እያደረሰ ያለውን ተዘርዝሮ የማያልቅ ግፍና በደል የማያውቅ የትግራይ ማኅበረሰብ አባል ይኖራል ተብሎ አይገመትም፡፡ የዚህ ሁሉ ሰቆቃና ዋይታ የዞረ ድምር ምን ሊያከትል እንደሚችል ደግሞ – በአንዳንዶች ግንዛቤ ጥቂት እንደሆኑ ቢነገርም – ቢያንስ ጤናማ አስተሳሰብ አላቸው የሚባሉት የተጠቃሹ ማኅበረሰብ አባላት ሊያውቁት ይገባል፡፡ ማወቅ ብቻም አይደለም፡፡ ከዚያም ባለፈ የበኩላቸውን ጥረት በማድረግ የሁላችንም የምትሆን አዲሲቱን ኢትዮጵያ በመፍጠሩ ሂደት ጉልኅ ሚና ሊጫወቱ ይጠበቅባቸዋል፡፡ የአደባባይ ንግግሮች የተፈለገውን ያህል በቃላት ክሸና ቢያሸበርቁና ስሜትን እንዳያጎፈንኑ ሲባል ከእውነታዎች ሥር ወድቀው ለከንቱ ውዳሤ ማስጌጫነት እንዲውሉ ቢደረግም ሕወሓትን አለትግራይ፣ ትግራይንም አለሕወሓት ማሰብ የሚያዳግት ዘመን ላይ መድረሳችንን መካድ ኅሊናን እንደማሳወር ነው፤ በዚህ ረገድ ብዙ እንደምወቀስ አይጠፋኝም፡፡ ነገር ግን የፈጠጠ ሃቅን ለመሸፈን በመሞከር አጉል ተወዳጅነትን ከማትረፍ ይልቅ እውነቱን ተናግሮ እመሸበት ማደርን እመርጣለሁ፡፡ ስለሆነም ይህን አስጠሊታ ሀገራዊ ምሥል በአፋጣኝ ለመለወጥ ከደጋግና አስተዋይ ተጋሩ ብዙ እንደሚጠበቅ መጠቆም ለክፉ የሚሰጥ ስህተት አይሆንም፡፡ እያለባበሱ ማረስ ምን ጣጣ ሊያስከትል እንደሚችል ገበሬን ሳንጠይቅ በግምትም ልናውቅ እንችላለን፡፡
ጉንዳን ሰውን ሲነክስ አይታችሁ ታውቀላችሁ? እርስዎ ክቡር አንባቢስ በጉንዳን ተነክሰው ያውቃሉ? ወያኔ ማለት ጉንዳን ነው፡፡ በቅርብዎ ጉንዳን ካለ ይህችን ተመሳስሎ (analogy) ይሞክሯት – ብዙም አይጎዱም፡፡
ጉንዳን ከነከሰው ነገር የሚላቀቀው አንገቱ ተቆርጦ ነው፡፡ በምክርም ሆነ በማስጠንቀቂያና በተግሣጽ ወይም በጩኸት ጉንዳን የነከሰውን ነገር አይለቅም፡፡ የሞት የሽረት ጉዳይ ነው፡፡ ሲነክስ እስከ አንገቱ ይሰምጣል መሰለኝ ስትመነጭቁት ጭንቅላቱ ሰውነት ላይ ተጣብቆ ይቀርና ከትከሻው ተጎርዶ ለሁለት ይከፈላል፤ ሕይወቱም በዚያው ያልፋል – ሰውን አቁስሎ፡፡ በተመሳሳይ ሁኔታ ወያኔም ሰቅዞ ከያዛት ኢትዮጵያ የሚላቀቀው ተቆራርጦ እንጂ እንዲሁ አይደለም፡፡
ፒራና የምትባል የዓሣ ዝርያ አለች፡፡ ወያኔ እሷንም ይመስላል፡፡ ፒራናዎች አንድ የፈረደበት ሰው ወደ ባህር ገብቶ ቢያገኙ በሴከንዶች ውስጥ ዐፅሙን ያስቀሩታል፡፡ እንደጅብ ተጠራርተው በቅጽበት ውስጥ ይደርሱና በዚያችው ቅጽበት ውስጥ ይረባረቡበታል፡፡ ያ ሰው የሚቀረው ዐፅሙ ብቻ ነው፡፡ ኢትዮጵያም ዐፅሟ ብቻ ገጦ የሚታየው ፒራናው ወያኔ ላለፉት ሃያ ሰባት ዓመታት በመላ ኃይሉ ስለቦጠቦጣት ነው፡፡ ወያኔ እስካለ ኢትዮጵያ ከሞት አትነሣም፡፡
አሁን ግን ሕዝብ በቃኝ ብሏል፡፡ ከዳር እዳርም ተነስቷል፡፡ የወያኔ የከፋፍለህ ግዛም በሉት የጭካኔና ዐረመኔያዊ አገዛዝ ሥልት ከሽፎበታል፤ ከአሁን ወዲያ ያ ዓይነቱ ዘዴ አይሠራም፡፡ አሁን ወያኔ ሕይወት ያለው የሚመስለው በብዙ ምክንያቶች ነው፡፡ ጥቂቶቹን ማየት እንችላለን፡፡
በብሔረሰቦች መካከል የዘራው የጥላቻ መንፈስ አልሠራለትም አንልም፡፡ “የነብር ዐይን ወደ ፍየል፣ የፍየል ዐይን ወደ ቅጠል” እንዲሉ እርስ በርስ በጥላቻ የሚተያዩ ዘውጎች በመበራከታቸው ለወያኔው የአፓርታይድ ዘረኛ ሥርዓት ገላጋይ መስሎ ማሽቃበጥና የተወሰነ ዕረፍት ማግኘት ጠቅመውት ኖረዋል፡፡ አሁን ግን ሕዝብ ነቅቷል፡፡ ውስን ድምባዣሞችና ቅጥረኞች ቢኖሩም በሂደት ጥግ ጥጋቸውን ይይዛሉ፡፡ ለነሱ የሚታዘዘው መቅሰፍት ለወያኔዎች ከሚታዘዘው ቢበልጥ እንጂ እንደማያንስ በዚህ አጋጣሚ “በሦስተኛው ዐይኔ ከሩቅ ያየሁትን” መናገር እፈልጋለሁ፡፡ እንደሂትለር ተዘቅዝቀው ሲሰቀሉ ይታየኛል – ጨካኝ ሆኜ አይደለም፤ የማየውን መናገር ስላለብኝ ነው፡፡
የሀብት ክፍፍሉ የፈጠረው የጥቅም መለያየት ዜጎችን በጥቅም አለያይቷል፡፡ ይህም ወያኔን ጠቅሞት ነበር፡፡ አሁን ግን ይህም አላፊ ነው፡፡ ለምን ቢባል መሠረታዊ የዴሞክራሲና ሰብኣዊ መብቶች እየተጣሱ በመብላትና በመጠጣት ብቻ የኅሊናና የአእምሮ ሰላም ማግኘት እንደማይቻል ሌላው ቀርቶ ሀብታሞችም እየተረዱት መጥተዋልና፡፡
በዚያን ሰሞን ወያኔን የሚውጥ ሕዝባዊ የተቃውሞ እንቅስቀሴን ተከትሎ በራሱ በወያኔ ውስጥ የተከሰተው ማዕበል አንድ የተደበቀ ነገር አውጥቷል፡፡ ያም የተደበቀ ነገር ዶክተር አቢይ የሚባል “የእሳት አደጋ ሠራተኛ” ነው፡፡ ይህ ከየት መጣነቱ ብዙ ያነጋገረ ወጣት ዜጋ ካለፉት ጥቂት ሣምንታት ጀምሮ የሌት ዕንቅልፍና የቀን ዕረፍት ሳያምረው ቆላ ደጋ እየተንከራተተ ነው፡፡ የሚደግፉትም የሚቃወሙትም ቢኖሩም የማይካደው እውነታ ግን ለሀገር የተወሰነ መረጋጋትንና ለራሱም የማይናቅ ሕዝባዊ ከበሬታን ማግኘቱ ነው፡፡ ለውጥን በቀላሉ መቀበል ለሚቸግረን ሰዎች የወጣቱ ፖለቲከኛ እንቅስቃሴ እምብዝም ሊገባን ባይችልም ወያኔን ግን ከጉድ እንዳወጣው መገመት አይከብድም፡፡ የዚህ ጠ/ሚኒስትር ወደ ጫፍ መውጣት በርካታ ታሳቢ ውድመቶችን አስቀርቷል ወይም በቅድመ ሁኔታዎች የተቀነበበ መዘግየትን ፈጥሯል፡፡ ወያኔ እንደስከዛሬው ዳግም አንሰራራለሁ ብላ ከሆነ “ቅዠት ነው!” በሏት፡፡
“ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ” በሚል የቁልምጫ ስም የሚጠራውና በታላላቅ ዓለም አቀፍ የስለላ ድርጅቶች የሚመራው ፀረ-ኢትዮጵያ ኃይል የሚሰጠው ሁለንተናዊ ድጋፍ ለወያኔ የጀርባ አጥንት መሆኑ አይካድም፡፡ ይህም ድጋፍ ሀገራዊ የኃይል ሚዛኑን እያዬ መደብዘዙና ወዳጋደለው ማዘንበሉ የሚጠበቅ ነው፡፡ የትኛውም ወገን ምንም ያህል ኃይለኛ ቢሆን ከደካማና ከሟች ጋር ተያይዞ ቢያንስ መወቀስን አይፈልግምና ወያኔዎች በመጨረሻው ራቁታቸውንና ብቻቸውን መቅረታቸው አይቀርም፡፡ ይህም ለውድቀታቸው መፋጠን አቢይ ምክንያት ይሆናል ብንል አንሳሳትም፡፡
ዜጎች ፈዘዋል፡፡ ብዙዎች በማይቀበሉት የድግምትና ትብታብ አፍዝ አደንግዝም ይሁን የሚያዩትንና የሚደርስባቸውን ስቃይና እንግልት በማመንና ባለማመን መሀል ሆነው ግራ በመጋባት ብዙ ኢትዮጵያውያን በስማም እንደተባለበት ሰይጣን አይሰሙም፤ አይለሙም፡፡ ይህ ሀገራዊ ፍዘት ለወያኔዎች መቦረቅ እንደዋና ምክንያት ነበር፡፡ ከአሁን በኋላ ግን ይህ ክስተት ታሪክ ይሆናል፡፡ ዜጎች ነቅተዋል፡፡ “አንተ ያመጣኸውን አንተው መልሰው” ከሚለው ጎጂና ኢ-ሃይማታዊ ብሂል ተላቀው ራሳቸውን ነፃ ለማውጣት የተዘጋጁ ወጣቶች በመላ ሀገራችን ዘመኑ የሚዋውን የታሪክ ፍርድ በመጣባበቅ ላይ ናቸው፡፡ የድርሻቸውንም ለመወጣት ተመጣጣኝ ዝግጅቶች እየተደረጉ እንደሆነ በውስጣዊው ዐይናችን እያየን ነው፡፡ ፈጣሪ ሲታከልበት “ፊተኞች ኋለኞች፤ ኋለኞችም ፊተኞች” የሚሆኑበት የማይቀር ክስተት እውን ይሆናል፡፡
ኢኮኖሚውን፣ የመንግሥትና የግል መሥሪያ ቤቶችን፣ ወጭ ገቢ ንግዱን፣ የሸቀጥ ምርቱንና ሸቀጡን ራሱን፣ ላኪና አስመጭነቱን፣ ፖሊሲውንና ፖሊሱን፣ መከላከያውን፣ ደኅንነቱን፣ አየር መንገዱን፣ ቴሌውን፣ መብራት ኃይሉን፣ ኮንዶሚኒዩሙን፣ ሚዲያውን፣ ሪል እስቴቱን፣ ህንፃና መንገድ ግንባታውን፣ ፋብሪካውን፣ ቀበሌውን፣ ወረዳውን፣ ክፍለ ከተማውን፣ ማዘጋጃውን፣ መሬት ዕደላውንና መሬት ቅሚያውን(መሬት አስተዳደሩን)፣ ኢንዱስትሪውን፣ ትምህርቱን፣ የመሬት ውስጥና የመሬት ላይ ማዕድኑን፣ ውኃ እያሸጉ መሸጡን፣ የሠራተኛ ቅጥሩንና ስንብቱን፣ መልከ ጥፉም ቢሆን ህገ መንግሥቱን፣ ደንቡንና መመሪያውን፣ ዐዋጁን፣ ፓርላማውን፣ ቤተ መንግሥቱን፣ የሚኒስትር መሥሪያ ቤቱንና ሚኒስትሮችን፣ ሚኒስትር ዴኤታዎችን፣ የሀገር ሀብት ንብረቱን – ጓዳ ጎድጓዳውን፣ የመረጃ ቋቱን፣ የመረጃ መረቡን፣ ዲፕሎማሲውን፣ ወዘተ….. የተቆጣጠረው ሕወሓት እንደመሆኑ ሥልጣኑን በሚታሰበው ፍጥነት ወደ ኢትዮጵያዊ ኃይል በውድም ይሁን በግድ ለማዘዋወር ጊዜ መፍጀቱ የሚጠበቅ ነው፡፡ ይህ ለዓመታት ሥር ድረስ ዘልቆ ሀገሪቱን በየፈርጁ የማነቅ ወያኔያዊ ድርጊት ሕወሓትን ከነሰንኮፉ በቀላሉ ነቅሎ የመጣል ሂደቱን አስቸጋሪ እንደሚያደርገውና ጥበብና አስተዋይነት እንደሚያስፈልገው መገንዘብ ይገባል፡፡ የኢትዮጵ ችር እንደግግር በረዶ ለዘመናት ሲቆለል እንደመክረሙ በወራትና በሣምንታት ውስጥ እንደጤዛ የሚረግፍ አይደለም፡፡ እናስተውል!!
በደጅም ሆነ በቤት ያለው የኢትዮጵያ ሕዝብ እምነት የሚጥልበትና በፍቅርና በውዴታ እየተጠጋው ለእውነተኛ ነፃነት የሚያበቃ የፖለቲካ ኃይል እንዳይኖር ወያኔዎች በርትተው ሲሠሩ ከመቆየታቸውም ባሻገር ተቃዋሚ ነን ባዮቹ ራሳቸውም በረባ ባልረባው እየተጣሉ ሲናከሱና ሲዘራጠጡ በህልም እልም ዓለም ከመኖር ባለፈ የሕዝብ ተስፋ ሊሆኑ አልተቻላቸውም፡፡ ብዛታቸውም ቢሆን በብጥቅጣቂ የግል ፍላጎቶች ላይ እየተመሠረተ ለመቁጠር አስቸጋሪ እስኪሆኑ ተበራክተዋል፡፡ በቁጥጥር ሥር ያልዋለና ወደ ጥቅም ያልተለወጠ ብዛትና ልዩነት ደግሞ ዛሬ አልመች ብሎ በነገር ጅራፍ ቢያተጋትግ ነገ በጥይት አረር ማለባለቡ አይቀርምና ይህ የፖለቲከኞቻችን መብዛት በራሱ ከራስ ምታቶቻችን መካከል ዋናው ሆኗል፡፡ ለወያኔ ዕድሜ መራዘምም የበኩሉን አስተዋፅዖ ማድረጉ የታመነ ነው፡፡ ተቃዋሚዎች የሕዝብ አለኝታ ይሆኑ ዘንድ ከባላንጣነት ነባር አዙሪት ወጥተው በጋራ ወደሚያሰባስቧቸው ነጥቦች እንዲያመሩ፣ በኅብረት በመታገልም ሥልጣን ከሕዝብ እንዲገኝ የሚቻልበትን ሥርዓት እንዲፈጥሩ በዚህ አጋጣሚ እናሳስባቸዋለን፡፡
ያም ሆነ ይህ የኢትዮጵያ ነፃነት በቅርብ መምጣት የሚያጠያይቅ አይደለም፡፡ “የጭንቅላት ሥጋ መብሰሉ ለማይቀር እንጨት ይፈጃል” ይባላል፡፡ አንድ ነገር መሆኑ ባይቀርም በአንድ ወይ በሌላ ምክንያት ሊዘገይ ይችላል፡፡ መምጣቱ የማይቀር ነገር መዘግየቱ ያልተጠበቀ ወይም ቢጠበቅም ድንበሩን የጣሰ ችግር ሊያስከትል የመቻሉ ጠማማ ዕድል ከፍተኛ ነው፡፡ የመምጣት መሄድን ትርጉም የሚያውቅ ሰው ሂያጅና መጪን በአግባቡ ይቀበላል፤ ይሸኛልም፡፡ አለበለዚያ ችግሮች ይከሰቱና “ምነው ባልተፈጠርኩ!” ማለት ይከተላል፡፡ ያኔ ጸጸትና ቁጭት ዋጋ የላቸውም፡፡ መጥኖ መደቆስ ቀድሞ ነውና…
የአስተዋይ ተጋሩ አስፈላጊነት እዚህ ላይ ነው፡፡ አንድ ውኃ ውስጥ እየሰመጠ ያለ ሰው የሚያድነው መስሎት የውኃውን ዐረፋ ወይም የሚንሣፈፍ ገለባ እንደሚጨብጥ ሁሉ ሕወሓትም ከታሪካዊ ውድቀቱና ግብኣተ መሬቱ የሚተርፍ እየመሰለው በአሁኑ ሰዓት የቀቢፀ ተስፋ ተግባራቱን በኅቡዕና በግልጽ እያከናወነ ይገኛል፡፡ ጥቂት ነገሮችን እንይ፡፡
ዶ/ር አቢይን ከመነሻው እንዳይመረጥ ለማድረግ ብዙ ጣረ፤ ግን አልተሳካም፡፡ ምናልባት የኢትዮጵያ ጠባቂ አምላክ አልፈቀደለትምና የሆነው ሁሉ ሆኖ የሆነውና እየሆነ ያለው እንዲሁም ወደስተፊት ሊሆን ያለው ሊሆን ግድ ሆነ፡፡ እንጂ አንዱን የሰው ከብት በሌላ የሰው በክት ተክቶ እንደጥንት እንደጧቱ ዕቃ ዕቃ ጨዋታውን ሊቀጥል ነበር፡፡ ሁልጊዜ ብልጥነት የለም፡፡ እንደ እውነቱ ከሆነ የኛ ጠባይ ለሰውም ለእግዜሩም አስቸጋሪ ስለሆነ እንጂ ይህን ያህል መሰቃየትም አይገባንም ነበር፡፡ ኢትዮጵያ ከፀረ-አማራው ማይሙ ሽፈራው ሽጉጤ የበለጠና እንዲያውም እርሱን መሰል የሰው ጎደሎዎችን ከእንደገና ጠፍጥፈው የተሻ ስብዕና ያላቸው ሰዎች እንዲሆኑ ማድረግ የሚችሉ የተማሩ ዜጎች እንዳሏት እየተረዳን ነው – ወላድ በድባብ ትሂድ፡፡ ወያኔ የመረጠልንን ፀረ-አማራውን ሽፈራው ሽጉጤንና የፈጣሪ በጎ ፈቃድ ተጨምሮበት እንደተሾመልን በበኩሌ አምኜ የተቀበልኩትን አቢይ አህመድን በዐይነ ኅሊናችሁ አስቡና ፍርዱን ራሳችሁ ስጡ፡፡ ለማንኛውም ሰው እንዳናገኝ ወያኔዎች ከፍተኛ ጥረት ቢያደርም አልተቻላቸውምና ከሸፈባቸው፡፡ ያለው አይቀርምና ብዙ ደክመው እስካሁን የዚህን ልጅ ግስጋሴ ሊያቆሙ አልቻሉም፡፡ ከላይ ከታዘዘ የሥሩ ምንም እንደማያመጣ በእግረ መንገድ እየተማርን ነው፡፡ ሊገድሉትና ሊያስገድሉትም እንደሞከሩ ሰማን፡፡ ያንንም በፈጣሪ እገዛ አመለጠ – ዶክተሩ፡፡ የብዙዎቻችንን ተስፋ እውን እንዲያደርግ አሁንና ወደፊትም ፈጣሪ ይርዳው፡፡
ከአሁን በኋላ አቢይን በአካላዊ ጉዳት ማስወገድ የህልም ያህል ነው፤ አይቻልም ማለት ግን አይደለም፡፡ ህልምነቱን ወያኔዎች በሚገባ ይረዳሉ፡፡ የሚያስከትለውን ጦስ አማካሪዎቻቸውም ይነግሯቸዋልና ወደዚያ ዓይነቱ ቅሌት አይገቡም ወይም ቢያንስ የሚገቡ አይመስለኝም፡፡ ሌላውና የቀራቸው ብቸኛ ካርድ እርሱን በህዝቡ ዘንድ ማስጠላትና “የቀደመው ጊዜ ይሻለን ነበር” ወደሚል አቅጣጫ ሕዝቡን ማስኬድ ነው፡፡ ይህን ለማድረግ ደግሞ የተለያዩ ዕቅዶችን ነድፈው እየተንቀሳቀሱ ነው፡፡ የተወሰኑትን አሁን ማየት እንችላለን፡፡
አማራን በኦሮሞና በሌሎች ዘውጎች በተለይም በጋምቤላና በቤንሻጉል ጉሙዝ እንዲገደል፣ ሁሉንም ሕዝብ እኩል ማገልገል በሚገባው የሀገር መከላከያ ሠራዊት በታገዘ የትግራይ ሚሊሽያ አማካይነት ከመኖሪያው እንዲፈናቀል ማድረግ በአሁኑ “የሰላምና የመረጋጋት ወርቃማ ጊዜ ውስጥ” ሥራየ ብለው ተያይዘውታል፡፡ ኦሮሞ አማራን አሳደደ፤ ገደለ፤ ከመኖሪያውም አፈናቀለ፡፡ ጥሩ፡፡ ኦሮሞ በብዛቱ ከአማራም የሚበልጥ በመሆኑ ምንም ዓይነት አፀፋ ከአማራ ቢመጣ ይቋቋመዋል፡፡ ጉሙዙስ? ጋምቤላውስ? ይህን ሥሌት እዩልኝ፡፡ ይህ የማን ሥራ እንደሆነ እንግዲህ ተመልከቱ፡፡ በመሠረቱ የጋምቤላም ሆነ የቤንሻጉል ሕዝብ በምንም ዓይነት መንገድ በራሱ ተነሳሽነት አማራን አይገድልም፤ አያስወጣምም፤ እውቱን ለመናር ድፍረቱም ይራዋል ብዬ አላስብም – ተከባብረው ከመኖራቸውም በተጨማሪ የሚያገዳድላቸው የተለዬ ምክንያት በተለይ ሰሞኑን የለም፡፡ ይህ ነገር የሆነው የሚሆነውም በወያኔ ቀጥተኛ ትዕዛዝና በጎሣዎቹ እበላ ባይ ጥቂት ካድሬዎች አስፈጻሚነት ነው፡፡ “ሀገሪቱ ካለሕወሓት ሰላም የላትም” በሚል እሳቤ ዓለም አቀፋዊ ድጋፍ ለማግኘትና ሕዝቡንም እንደተለመደው በማስፈራራትና በማስበርገግ የግፍ አገዛዛቸውን ለመቀጠል ሕወሓት ሆን ብሎ የሚያደርገው እንጂ ከሌላ ከማንም ወገን ይህ ነገር አልመጣም፡፡ ስለዚህ ጎሣዎችን ከጎሣዎች ማጋጨት፣ እዚህና እዚያ የሽብር ጥቃቶችን መፈጸም፣ ቦምብ ማፈንዳት፣ ሰዎችን አለአበሳቸው ማሰር፣ ሁከትና አምባጓሮ መፍጠር፣ የድንበር ግጭቶችን ማስነሳት፣ ወዘተ. ወያኔ እስኪወድቅ የሚቀጥለባቸው ዕኩይ ተግባራት ናቸውና መንቃት ይገባል፡፡ እነሱ በቆፈሩት ጉድጓድ ሁሉ እየዘለልን ከገባን ከፈርዖናዊ አገዛዛቸው ነፃ መውጣት አንችልም፡፡ ወጥመዶቻቸውን እንወቅ፤ ከዚያም እንጠንቀቅ፡፡
የኑሮ ውድቱን ታዘቡ፡፡ አቢይ ሥልጣን ከያዘ ወዲህ ከሞላ ጎደል የሁሉም ነገሮች ዋጋ ከዕጥፍ በማይተናነስ ጨምሯል፡፡ አንዲት ዕንቁላል እንኳን ባቅሟ ከብር 2.50 ወደ ብር 5 አድጋለች – እኔ በተወለድኩበት ዓመት በአንድ ብር አንድ መቶ ዕንቁላል ይሸመት እንደነበር “አስታውሳለሁ”፤ መቶ ኪሎ ጤፍ ደግሞ በ25 ብር ብቻ! ሊያውም ተወዶ – ምን ዓይነት የተረት ተረት ዘመን ላይ ደረስን ግን ወገኖቼ? በአጭሩ አሁን ገበያው እሳት ሆኗል፡፡ ሰው ሁሉ ደግሞ ነቅቷል፡፡ ይህም ደስ ይላል፡፡ ሻጥር እንደሆነ ሕዝቡ ገብቶታል፡፡ ሰበቡ የዶላር ምንዛሬ ይባል እንጂ አዲሱን ጠ/ሚኒስትር ለማሳጣትና ሕዝብ “የዱሮው ይሻለኛል!” እንዲል በወያኔና ግብረ አበሮቹ ሆን ተብሎ አሻጥር እየተሠራ እንደሆነ ሁሉም ተገንዝቦታል፡፡ በአንድ ሣምንት ውስጥ የሁሉም ነገር ዋጋ እንዲህ ማሻቀቡ አለነገር እንዳልሆነ ማንም ይረዳል፡፡ ንግዱም ሆነ አገልግሎቱ በአብዛኛው በወያኔና ደጋፊዎቹ በመያዙ ጃዝ ሲባሉ የሚታዘዙ ተፅዕኖ ፈጣሪ ሰዎች ከየሴክተሩ ሞልተዋል – ከየንግድና የኢኮኖሚ እንቅስቃሴው ማለቴ ነው፡፡ ስለዚህ ላልተወሰነ ጊዜ መጎዳታችን አይቀርም፡፡ ቢሆንም እንደ ቀደመው የሙሤ ዘመን ሰዎች በቀላሉ ለችግር ሳንረታ የቋሚ ነፃነታችን ደወል እስኪደወል መጽናት አለብን፡፡ አቢይም በእውነት የኛ ከሆነ ጊዜ ባለውሉ ይነግረናል፡፡ በብሂሉ “ሽልም ከሆነ ይገፋል፤ ቂጣም ከሆነ ይጠፋል” እንዲሉ ነውና ለዚህ ጠ/ሚኒስትር የተወሰነ ጊዜ መስጠቱ፣ በማስተዋል እየተራመዱና ነገሮችን በብልኃት እየመረመሩ ማገዙም ጥሩ ነው፡፡ ይህ ልጅ እንዲህ ያለ ዕረፍት የሚማስነው የግል ዕዳ ኖሮበት ሣይሆን ለሀገርና ለሕዝብ ብሎ መሆኑን እንረዳ፡፡
ልዩ ማስታወሻ
ይህን ጽሑፍ ትናንት ነበር የላክሁት፡፡ ግን ለአንድም ድረገፅ አልደረሰም፡፡ በላክሁ በጥቂት ደቂቃዎች ውስጥ የሚለጥፉ ድረገፆችም አላወጡትም፡፡ ምክንያቱም አልደረሳቸውም፡፡ ኢሜይሌን ስፈትሽ ለማንም እንዳልደረሰ ተረዳሁ፡፡ “ታግዷል” የሚል መልእክትም አገኘሁ፡፡ ይህ ለኔ የጠቆመኝ ነገር መላላክም እንዳልተቻለ ነው፡፡ ስለዚህ ይቺን አጭር ማስታወሻ ለጠ/ሚ አቢይ መጻፍ ፈለግሁ፡፡ መልእክቴ የታገደበት መልእክት ቀጥሎ ያለውን ይመስላል – አንድ ምሣሌ ነው፡፡
Message blocked
Your message to emadebo@gmail.com has been blocked. See technical details below for more information.
LEARN MORE

ጠ/ሚ አቢይ ሆይ! እንቅስቃሴህ ጥሩ ነው፡፡ ግን ብዙ የታሰረ ነገር በሀገርህ ውስጥ አለና በዚያም ላይ በርታ፡፡ የጽፍም ሆነ የንግግር ግንኙነታችን ታስሯል፤ እነ አንዳርጋቸው ጽጌን ጨምሮ ብዙ ዜጎቻችን አለአበሳቸው ታስረዋል፤ ሆዳችን ነፃ ተለቆ ኅሊናችን ተቀፍድዶ ታስሯል፤ ኑሯችን በወያኔ የንግድና የፖለቲካ ባለሟሎች ተጠፍንጎ ታስሯል፤ ዕውቀት ግንዛቤያችን ተኮድኩዷል፤ አእምሯችን ጫጭቷል፤ የሶማሊያ ዘላንና የዐረብ ገበሬ በየበረሃው እንደልቡ የሚጠቀምበት ኢንተርኔት እንኳን ሳይለቀቅልን አንተ የምትታማበት “የሽርሸር መንግሥት”ም በቃላት ደረጃ እያማለለን ባለበት ሁኔታ አንዳንዶች “ውስጡን ለቄስ” ቢሉ አንተ የምትሰጠው መልስ እንዳያጥርህ እሰጋልሃለሁ፡፡ ስለዚህ ከውጪ መጀመርህ መልካም ሆኖ በአፋጣኝ ወደ ውስጥ ገብተህ ብዙ ነገሮችን ማስተካከል ካልጀመርክ ይህችን ሀገር ወዳልተጠበቀ ቀውስ በመምራቱ ረገድ የበኩልህን ድርሻ እያበረከትህ እንደሆነ ላስገነዝብህ እወዳለሁ፡፡ “ለዐይን ይበጃል ያሉት ኩል ዐይን አጠፋ” እንደሚባለው እንዳይሆንብንም እፈራለሁ፡፡ ወያኔዎችን ያወቅሃቸው አልመሰለኝም፡፡ ቀን ቀን ስትገነባው የምትውለውን ሁሉ ማታ ማታና ሌሊት ሌሊት ሲያፈርሱ የሚውሉ የእፉኝት ልጆች ናቸውና በሁለት ወር ውስጥ የሠራሃትን ትንሽ ታሪክህን ሳትቀር እንዳያጠፉብህ ተጠንቀቅ፡፡ አለበለዚያም አለመቻልህን አሳውቀህ ዘወር በል፡፡ አሁንና እስካሁን በምታደርገው ነገር ሁሉ ግን አድናቂህና አዛኝህም ነኝ፤ ለተቀማጭ ሰማይ ቅርብ መሆኑን ደግሞ አሣምሬ አውቃለሁ፡፡ አለመቻልን ማወቅም የጥበብ አካል መሆኑን እረዳለሁ፡፡ አለመቻል ስልህ ደግሞ ከዐውሬ ጋር የመታገልን አለመቻል እንጂ በጥበብ ሀገርን መምራት ስላለመቻል አለመቻል ማለቴ አይደለም፡፡ ከአክብሮት ጋር፡፡ በሌላ አድራሻ ደግሞ ልሞክር እስኪ፡፡