
በአዴን ሲጀምር የአማራን ሕዝብ ለማጥቃት የተደራጀ እንጂ ለአማራ ሕዝብ እንዳልሆን በራሱ በቡድኑ ፕሮገራም ተብለው በተቀመጡ ሰነዶች ማይት ይቻላል፡፡ በተለይ በተለያዩ ክልሎች የሚኖረውን የአማራ ተወላጅ ነፍጠኛ በማለት በአገሪቱ በሙሉ በጠላትነት ሁሉም በእዚህ ሕዝብ ላይ አንድ ሆኖ እንዲቆም ሲሰሩ ከነበሩ ቡድኖች በዓዴን የተባለው በዋናነት ቢጠቀስ ስህተት አደለም፡፡ በወንበዴዎቹ የመጀመሪያ ዓመታት የቀድሞው ኢህዲን ቡድን ዋና የነበረው ታምራት ላይኔ የሚባል ግለሰብ ሊያውም የዋናው የወንበዴው ቡድን ሁለተኛ ሰው በሆነበት ዘመን በሶማሌ ክልል ሄዶ በቀጥታ በዛ የሚኖሩ የአማራውን ተወላጅ ምን ለሶማሌ ሕዝብ ሊሰራ መጣ እዚሀ ድሮ ሲጨቁንህ ነበር አሁን ጊዜው ያንተ ነው በለው የሚል መልዕክት ማስተላለፉ አይረሳም፡፡ ይህ ግለሰብ ብዙ ግፎች በተለያዬ ቦታ የሚኖሩ አማራ ተወላጆች እንዲደርስባቸው ቀዳሚ ቀስቃሽ ነበር፡፡ የበደኖና አርባ ጉጉ እልቂት የዚሁ አማራን ኢላማ ያደረገ ዘመቻ ነበር፡፡ በዛች አገር የመጡ የወንበዴውና ተባባሪዎቹ ሁሉ በአንድነት ኢላማ ያደረጉት አማራ የተባለ ሕዝብ በተለይም ደግሞ በተለያዩ ክልሎች ይኖር የነበረውን ነው፡፡ በአጠቃላይ ይህ ሕዝብ ይህ ሁሉ የጠላትነት ዘመቻ ተከፍቶበት በራሱና አብሯቸው በሚኖራቸው ሕዝብ ድጋፍ ኖረ እንጂ የተሴረው ሴራ ብዙ ነበር፡፡ ወያኔ ከመጀመሪያው በይፋ በአጠቃላይ አማራ የተባልን ሕዝብ በዋና ጠላትነት ፈርጆ የተቋቋመ ቡድን እንደሆነ ግልጽ ነው፡፡ ሰሞኑን የሕዝብ ውይይት በሚል በሻራተን ተዘጋጀ ስብሰባ አንዱ ይሄንኑ የወያኔ የተመሰረተበትን አላማ ሲጠቅስ ሌላዋ ልቧን ሞልታ ይህ ከእውነት የራቀ ነው ስትል ተደምጣለች፡፡ ስለዚህ ስብሰባ ወደኋላ እመጣበታለሁ ግን እውነታውን መወያኔው ማኒፌስቶ ታገኙታላችሁ፡፡
ኦሕዴድ የኦሮሞን ሕዝብ ለወያኔ ባሪያ አድርጎ ለማስገዛት የተቋቋመ ድርጅት እንጂ ለኦሮሞ ሕዝብ አደለም፡፡ የኦሮሞ ሕዝብ ግን እንደ አማራው በልዩ ጠላትነት አልተፈረጀም፡፡ ግን ለአማራው ጠላት እንዲሆን ከፍተኛ ሴራ ሲሰራ ቆይቶ በሁለቱ ሕዝቦች መካከል ብዙ መቃቃር እንዲፈጠር ሆኗል፡፡ ከአማራው በተለየ የኦሮሞን ሕዝብን እንወክላን በሚል ብዙዎች ተነስተዋል፡፡ ከመጀመሪያው የነበረው ኦነግን ጨምሮ ሌሎች በርከት ያሉም ትልልቅ መሆን የቻሉ ነበሩ፡፡ ኦነግ በዋናነት አላማ ብሎ የተነሳው ኦሮሞን ከኢትዮጵያዊነት ማምከን ነው፡፡ ይህ አላማ ትግራይን ለመገንጠል ከተነሳው የወያኔው ቡድን ጋር በጣም ስለተጣጣመ ከመጀመሪያውም ወያኔና ኦነግ በዚህ ልዩ ዝምድና መስርተው ነው ወደ መሀል አገር የመጡት፡፡ ወያኔ ትግራይን ለማስገንጠል አማራን ቢቻል ማጥፋት ከአልሆነ ማዳከም አንዱ አላማዋ ሲሆን ኢትዮጵያን ማፈራረስ ግን ግድ እንደሚል ታውቃለች፡፡ ለዚህ ደግሞ ሕዝቦችን በማጋጨት ሕልሟን እውን ለማድረግ መዋቅር ዘርግታ ብዙ ሞክራለች፡፡ ሁለት ወፍ በአንድ ድንጋይ እንዲሉ በተለይ ደግሞ አማራንና ኦሮሞን ማጋጨት ኢትዮጵያን ከማፈራረስ በተጨማሪ ሁለቱን ሕዝቦች ማዳከምና ማሳነስ እንደሚቻል አቅዳ በቀዳሚነት ስትጠቀምበት ቆይታለች፡፡ አማራው በሁሉም ስለሚጠቃና በዓዴን የተባለው ቡድን የወያኔ ቁልፍ ሰዎች ሥር ስለዋለ እንደልብ በዚህ ሕዝብ ላይ ግፍ ለመስራት አስችሏታል፡፡ የኦሮሞ ግን ብዙም በቀጥታ ስላልተመቸ ድራማዊ አካሄድ መሄድ ነበረባት፡፡ ይሄ ደግሞ የኦሮሞ ነን በሚሉ ቡድኖች ነበር፡፡ ኦነግ ዋነኛ በኦሮሞ ላይ ሲፈጸሙ ለኖሩ ግፎች መሪ ተዋናይ ነበር፡፡ በኦሮሞ ላይ ብቻ ሳይሆን ወያኔ በአገሪቱ ለዘረጋችው የሕዝብ እርስ በእርስ የማስተላለቅ ሴራ የወያኔ ቀኝ እጅ በመሆን ነው የሰራው፡፡ ኦሮሞን ከኢትዮጵያዊነት ማስወጣትና በአገሪቱ ምንም ድርሻ የሌለው በማድረግ መሠረቱን ማጣፋትና በማባዘን እንደልብ ግፍ ለማድረስ ማመቻቸት ተቀዳሚው የኦነግና ወያኔ ጥምር ሴራ ነበር፡፡ በብዙ መልኩ ተሳክቶላቸው ብዙወ የመባል ኦሮሞን በገዛ አገሩ አገር አልባ የባዘነ ሊያደርጉት ተችሏቸዋል፡፡ በቀጣይ ወያኔ የተጠቀመችው ይሄን ሕዝብ የኢትዮጵ ጠላት፣ ኦነግ፣ አሸባሪ እያለች አረመኔያዊ ግፍ በሕዝቡ ላይ መፈጸም ነበር፡፡ በግፍ ደረጃ ሲታይ የኦሮሞው ሕዝብ ከአማራው የአነሰ አይመስለኝም፡፡ ብዙዎች በኦነግነት ሥም ከቤታቸው ወጥተው የት እንደገቡ እንኳን ሳይታወቅ ቀርተዋል፡፡ በየእስርቤቱ በሕየወት መቆየት ከቻሉትና በይፋ ተገድለው ዘመድ ከአወቃቸው በላይ ብዙዎች የት እንደገቡ አይታወቅም፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ይህን ሕዝብ እንደ አማራው ሁሉ በሌሎች ጎረቤት ሕዝቦቹ በልዩ ሁኔታ በጠላትነት እንዲታይ ማድረግ ሌላው የወያኔ ሴራ ነበር፡፡ በአለፉት 27 ዓመታት ከኦሮሞ ሕዝብ ጋር ያልተጋጨ ኦሮሚያን የሚያዋስን ክልል ምን አልባት የአማራ ክልል ሳይሆን አይቀርም፡፡ ልብ በሉ አማራን በነፍጠኝነት ሥም በሁሉም ሕዝቦች እንዲጠላ፣ ኦሮሞን ደግሞ በኦነግነት ሥም እንዲሁ በሁሉም ሕዝቦች እንዲጠላ ነው የተደረገው፡፡ ወያኔ እንዳቀደችውም ሁለቱ የአገሪቱ ትልልቅ ሕዝቦች እርስ በእርስ እንደጠላት ከመተያየታቸው በተጨማሪ በሁሉም ሌሎች ሕዝቦች በጠላትነት እንዲታዩ ነበር የተደረገው፡፡ ብዙዎች የኦነግና ወያኔን ሴራ ሳይረዱ ከኢትዮጵያዊነታቸው ተሰደው ባዶ ኦሮሞነትን ሲያጸንፉ ኖሩ፡፡ የወያኔንና ኦነግ አገርን ለማፈራረስ የቃዱትን ሕልም ለማሳካት ብዙዎች ፈጠኑ፡፡ በመጨረሻ ግን ከሁሉም ሕዝብ በላይ ኢትዮጵያ ለኦሮሞ እንደምታስፈልገው የሚያሳይ ገሀዳዊ እውነት ተከሰተ፡፡ ኦሮሞ በኦሮሞነቱ ኦሮሚያ ከምትባለው ጠባብ ቦታ ውጭ መኖር አትችልም አዋጅ ታወጀበት፡፡ ይህም ብቻ አደለም ቀጥሎ በየአቅጣጫው ያሉ ሌሎች በጠላትነት ሊነሱበት እንደሚችል ፍንትው ያለ ማረጋገጫ ሆነ፡፡ አብዲ ኢሌ ኦሮሞ በሶማሌ ክልል ብቻ ሳይሆን ከባቢሌ እስከ ሞያሌ ያሉ ከሶማሌ ጋር የሚያዋስኑ የኦሮሚያ ቦታዎችን ከኦሮሞ ማጽዳት አላማ አድርጎ ተነሳ፡፡ ይህ እንደሚሆን እኔን ጭመሮ ብዙዎች ቀድመን ስንናገር ብዙዎች አፊዘውብናል፡፡
ኢሕአዴግ በቀጥታ በወያኔ የሚመራ የወያኔ ተወካይ የሆኑት እንደ እኔ ኦህዴድና ደህዴን እንዲሁም በቀጥታ በዋነኞቹ የወያኔ ሴራ አቀናባሪ በሚመራው በኣዴን ስብስብ 27 ዓመት በኢትዮጵያ ምድር የውንብድና መዋቅር ዘርግቶ የሠራ የወያኔ አገር አቀፍ መዋቅር ነው፡፡ በአጭሩ ኢሕአዴግ የኢትዮጵያና ሕዝቦቿ ቀንደኛ ጣላት ነው፡፡ እንግዲህ ከእዚህ የኢትዮጵያ ጠላት ከሆነ በድንና ከንዑስ ቡድኖቹ የወጡ ግን ውስጣቸው በቁጭት ሲያር የኖሩ ግለሰቦች ናቸው ዛሬ የአገሪቱን የጨለመ ተሰፋ ወደ ብርሀን እየመለሱ ያሉት፡፡ ደጉና ለማ እንዲሁም አብይና አጋሮቻቸው ሁሉ፡፡ ዛሬ ላይ እነዚህ በግለሰብ ደረጃ አደለም፡፡ ምን አልባትም ብዙዎች የኢትዮጵያ ጠላት የሆነውን ኢሕዴግ ከውስጥ ገብተው መሠረቱን እየናዱት እንደሆነ እንገነዘባለን፡፡ ይሁንና አሁን እንዲጠነቀቁ የምንፈልጋቸው ጉዳዮች አሉ፡፡ ለአብይ ከዚህ በፊት አስተያየቴን ሰጥቻለሁ፡፡ አብይ የኢትዮጵያ ጠ/ሚኒስቴር እንጂ የኢህአዴግ ሊቀመንበርነትህን ማንም እንደማይፈልገው መገንዘብ ይኖርብሀል፡፡ ከዚያ በላይ ግን በኢትዮጵያ ጠ/ሚኒስትርነት ቦታ ሆነህ የአንድን ቡድን ሊያውም የኢትዮጵያ ቀንደኛ ጠላት የሆነን ቡድን ለማስተዋወቅ መሞከር ሕገወጥነት እንደሆነ ልትረዳ ይገባል፡፡ የኢትዮጵያ ጠ/ሚኒስቴርነት ቦታ የኢትዮጵያ መንግስት መዋቅር እንጂ የአንድ ቡድን መዋቅር አደለም፡፡ ይሄ የወንበዴዎች አስተሳሰብ ነው፡፡ የወንበዴ አስተሳሰብ ወርሰህ ጠ/ሚኒስቴርነትህን የኢሕአዴግን ቡድን ለማስተዋወቅ መጠቀም አትችልም፡፡ ይህን አሁንም እነግርሀለሁ፡፡ ወደፊት ኢህአዴግን ወክለህ በምትወዳደረብት ወይም በምትገኝበት ቦታ ብቻ ነው እንደ ኢህአዴግ ሊቀመንበርነት መናገርም ሆን መወከል የምትችለው፡፡ ያኔ በጠ/ሚኒስቴርነትህ ሳይሆን በኢህአዴግ ሊቀመንበርነትህ ብቻ፡፡ ይህ አሰራር ለክልል መንግስታትም ሊሠራ ይገባዋል፡፡ ሲጀምር የክልሎቹ ቡድኖች ሁሉ ከሥያሜአቸው ጀምሮ መንግስት ሆነው በክልሎቹ መቀጠል የሚችሉ አይመስለኝም፡፡ እንበልና በአዴን ሥሙ ተግርኛ ቢሆንም አማራን እንጂ የክልሉን ሕዝብ አይወክልም፡፡ አማራ ውስጥ ብዙ ከአማራ ውጭ ሕዝብ አለ፡፡ ኦሕዴድ እንደዛው ነው፡፡ ኢትዮጵያዊነት ከታሰበ አንዱ መሠረታዊ ሊሆን የሚገባው የዘር ማንነትን መሠረት የአደረገ የፖለቲካ ቡድን በሕግ ሳይቀር ማገድ ነው፡፡ ኦሕዴድ ኦሮሞን እንጂ በኦሮሚያ የሚኖረውን ሕዝብ አይወክልም፡፡ ይህ በድርጅት ደረጃ ብቻም ሳይሆን በግልጽ በአሰራርና በአስተሳሰብም ከፉኛ ተንሰራፍቶ በብዙ ሕዝቦች ላይ በደል እየተፈጸመ ነው፡፡
ለማ፣ ገዱ፣ አብይና አጋሮቻቸው ሕዝብን ከአላችሁ እንወክላለን ከምትሉት ሊያውም የወንበዴዎች ሴራ ማስፈጸሚያ ቡድን አስተሳሰብ ውጡ ለማ የኦሮሚያ ፕሬዘደንት እንጂ የኦሮሞ ኦሕዴድን የሚወክል ሆኖ በኦሮሚያ ሊያስተዳደር አይችልም፡፡ ገዱም እንደዛው፣ ሁላችሁም ያላችሁበት ሥልጣን የመንግስት መዋቅራዊ ሥልጣን እንጂ የአንድ ቡድን ሥልጣን አድርጋችሁ እያሰባችሁ ሕዝብን ልትመሩ አትችሉም፡፡ ሰሞኑን በዳኖ የአማራ ተወላጆችን መፈናቀል አስመስልክቶ አቶ አዲሱ አረጋ የሰጡት መረጃ ጠቃሚነቱ እንዳለ ሆኖ በመጨረሻ ግን የኦሮሚያ መንግስት ሳይሆን የኦህዴድ ቡድን መረጃ እንደሆነ ሳነብ አሁንም ችግር እንዳለ እረዳለሁ፡፡ ከዚህ አስተሳሰብ ውጡ፡፡ ይህ ወንጅል ነው፡፡ ቡድን መንግስት ሊሆን አይችልም፡፡ አገር የሚተዳደረው በመንግስት እንጂ በቡድን አደልም፡፡ በዚህ ላይ ሁላችሁም የአላችሁበት ቡድን ዋናውን ጨምሮ የውንብድና አስተሳሰብ የተንሰራፋበት ነው፡፡
ሌላው ለሕዝብ እንሰራለን ከአላችሁ ነገሮችን ከመሠረቱ የጸዱ አድርጉ ሰሞኑን እየሆነ ያለው ውዥንብር ብዙ ነው፡፡ ሴረኞች አጋጣሚወን ለራሳቸው ሊጠቀሙበት እንደሚጥሩ እንረዳለን፡፡ እየሆነ ያለው ነገር አንዳንዶች በውሸት ነገሮችን ለራሳቸው እንደሚጠቀሙት ብቻ ሳይሆን በትክክል በደል እየደረሰባቸው ያሉ ዜጎች እንዳሉ እንረዳለን፡፡ ይህ ችግር እየተፈጠረ ያለው ዛሬም ቢሆን ሙሉ ማንነትን መሠረት ያደረገ ጥቃት ከኦሮሚያ አልጠፋም፡፡ ይህን ለማክሰም ደግሞ መንግስታዊ መዋቅሩ እንጂ ድርጅታዊ መዋቅሩ አደልም ሊሰራ የሚገባው፡፡ በዳኖ ማንነትን መሠረት ያደረገ ትቃት አልነበረም ተብሏል፡፡ መልካም፡፡ግን ለምን ከዳኖ አዲሳባ እስከሚደርስ ጉዳዩን መፍትሄ መስጠት አልተቻለም? እንደተባለው ውዥንብሩን ለግል ጥቅም በሕገወጥነት ሊጠቀሙ የሚጥሩ ቢኖሩም በትክክልም በደል የደረሰባቸው ግለሰቦች እንዳሉ አንረዳለን፡፡ ሆኖም ጉዳዩ ወደ ሕዝብ የደረሰበት ሂደት ሴራዊ አካሂድ አለው የሚል እምነት አለኝ፡፡ ለመሆኑ ይህ ጉዳይ መጀመሪያ ሊቀርብ የሚገባው ለሚዲያ ነው ወይስ መፍትሄ ይሰጣሉ ለሚባሉ የመንግስት መዋቅሮች? የኦሮሚያ መንግስት ፕሬዘደንት ይህን ጉዳይ ማወቅ የሚገባው በራሱ መዋቅር ነው ወይስ ከፌስቡክና ከሌሎች መገናኛ ሚዲያዎች? በየትኛውም መዋቅር ያለ የመንግስት ሰንሰለት በትክክል እየሰራና እያልሰራ መሆኑ ከቀበሌ ጀምሮ እላይ ድረስ ግልጽ ሊሆን ይገባል፡፡ ሥልጣንም ሆን ሌሎች አገልግሎታዊ የመንግስት አሰራሮችም ከማንነት ወጥተው ሁሉንም ያሳተፉ እንዲሆን ማድረግ ሌላው ሊታሰብበት የሚገባ ነው፡፡ ማግለል የሚጀምረው ከዚህ ነው፡፡ ዛሬ ብዙ አልደግመውም ግን የየክልሎቹ ህገ መንግስት ተብዬ ሰነድ በግልጽ ሌሎችን መብት እንደሌላቸው እንደደነገገ ዛሬም ላስታውስ እወዳለሁ፡፡ ከዚህ በኋላ ዛሬ ለሕዝብ ቆመናል ከአላችሁ ማንነትን መሠረት ያደረግን ጥቃትንም ይሁን ማንኛውንም መብት የሚነካ አሰራር በክልላችሁ እዳይደገም በማድረግ ቀዳሚነቱን ድርሻ ተወጡ፡፡ ይ ምክሬ ነው
ሰሞኑን ሌላ የሰማሁት የሕዝብ መወያያ መድረክ ተብሎ በሻራተን አዲስ የተደረግን ውይይት ነው፡፡ አብይ ሆይ እንዲህ ያለ የሚያምታታ ውይይት ቢቀርብን ነው የሚሻለው፡፡ አንዱ አማራ ነገር መሰለኝ ተነስቶ እምዬ ሚኒሊክ አለ፡፡ ብቻ ታሪኩን በውል ከማስጨበጥ ይልቅ ቋትኝ ቋጥኝ በሚያህሉ ቃላቶች አጅቦ ተሰብሳቢውን ለማስበርገግ ሞከረ፡፡ ቀጠለና አንዱ የታሪክ ጉዳይ ከአነሳን ወደማንፈልገው ጭቅጭጭቅ ነው የሚከትን የሥርዓት ችግር ነበረ አሁንም አለ ሲል ደመደመ፡፡ ይሄው ተናጋሪ ግን ስለሕገመንግስቱ ሴራዎች አንዳንድ ነጥቦችን አቅርቦ ተናገረ፡፡ ቀጥላ አንድ ሴት ከጂማ ዩኒቨርሲቲ ነኝ ያለች ሕገመንግስቱ የአለበት የአፈጻጸም ችግር ነው ብላ ደመደመች፡፡ የፌደራል ሥርዓቱንም ደገፈች፡፡ እሷው የኦሮሞ ከሱማሌ መፈናቀልን ምርር ብላ ተናገረች፡፡ እያለ ሌላው ቀጠለ፡፡ ዝም ብሎ ለሰማቸው እሺ ምንድነው ሊያወሩ የፈለጉት ከማለት ውጭ ይሄ ነው የሚለው እንድም መፍትሔ አያገኝም፡፡ እስኪ ከጠቀስኳቸው ከሴቷ ልነሳና ጥቂት ልበል፡፡ የጂማዋ ዩኒቨርሲቲ መምህርት የኦሮሞዎች ከሱማሌ መፈናቀል ምክነያቱ ምን ነበር ተብላ ብትጠየቅ የፌደራል ሥርዓቱ የአፈጻጸም ችግር ነው ከማለት አትመለስም፡፡ እሷ ኦሮሞ ስለሆነች የድመት አይን ምን ያያል ቢሉት አይጥ እንደተባለው ነው እይታዋ፡፡ ያሳዝናል፡፡ እሺ የአማራዎችስ ከበደኖ ጀምሮ፣ ከጉራ ፈርዳ፣ ከቤኒሻንጉል ይሄው ዛሬ ደግሞ ከዳኖ ብትባል ይሄ ትክክል ነው ከማለት የማትመለስ አይነት እይታ ውስጥ ነች፡፡ የዩኒቨርሲቲ መምህሯ፡፡ የታሪክ ጉዳይ አናንሳ ባዩ ተናጋሪ ከሕገመንግስቱ ጠቅሶ ያነሳቸውን ጉዳዮች በጣም ወድጄለት ግን የታሪክን ጉዳይ አናንሳ የምትለዋ መሸፋፈኛ ተናጋሪውን መሠረት የሌለው የራስን ፍላጎት አንጸባራቂ ያስመስለዋል፡፡ ታሪክ የሌለው አገርና ህዝብ ልፍስፍስ ነው፡፡ ታሪክ የዜጎች ልበሙሉነት መሠረት ነው፡፡ ታሪክ ሳይኖረው አለም ላይ ትልቅ የሆነ አገር አላየነም፡፡ ወጣቶቹ እነ አሜሪካ ሳይቀሩ መሠረታቸው ታሪክ ላይ ነው፡፡ የታሪክም ትምህርት በእነዚህ አገሮች ግዴታ እንጂ አማራጭም አደለም፡፡ በመልዕክቱ ግን ሻል ይላል፡፡ እምዬ ሚኒሊክ ባዩ ደግሞ የዩኒቨርሲቲዋ አይነት ነው፡፡ እሷ ኦሮሞ ነበረች ይሄ ደግሞ አማራ ነው፡፡ በቃ ለዚህ ሰው ደግሞ ወደ አንድ ሚሊየን የተጠጋው ተፈናቃይ ኦሮሞ አይታየውም፡፡ ታሪክም አነሳ የጥል ሀውልት ይፍረስ ከማለት ውጭ ተጨባጭ እውነታን መናገር አልቻለም፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝብ እምዬ ያላቸውን ሚኒሊክን እንዴት ትነቅፋላችሁ አይነት ነው፡፡ እኔ በሚኒሊክ ላይ ያለኝን አቋም ብዙዎች ታዎቃላችሁ፡፡ በዚህ አይነት ግን ሚኒሊክን ማወደስ አልፈልግም፡፡ በአጠቃላይ የዛን ውይይት ሂደት ስትመለከቱት በህዝባዊ ውይይት ሥም ውዥንብር መፍጠር ነው፡፡
በዚሁ ሳምንት አብይ ሳውዲአረቢያን ጎብኝቶ ከተመለሰ በኋላ ለወጣቶች ያደረገው ንግግር ጥሩ ከሚባሉ ነው፡፡ እይታውንም ቁጭቱንም ወድጄዋለሁ፡፡ በተለይም የተጓዘበትን አላማ ያነሳበትን፡፡ ምን ትፈልጋላችሁ ሲሉን ዜጎቻችንን ፍቱልን አልናቸው፡፡ እኛ ዜጎቻችንን ስናከብር እነሱ ያልጠየቅንውን ጨምረው ሰጡን፡፡ ይህ ጉዳይ ትልልቅ ግንዛቤ ነው፡፡ አዎ ዜጎች በመሪዎቻቸው ሲከበሩ በሄዱበት ሁሉ ይከበራሉ፡፡ በኃይለስላሴ ጊዜ ለትምህርት የተላኩ ኢትዮጵያውያን በሄዱበት ሁሉ ትልቅ ክብር እንደነበራቸው ይነገራል፡፡ ዛሬ ኢትዮጵያውያን ከባርነትም በታች ዕቃ ሆነዋል፡፡ በተለይ አረቡ አገር፡፡ እነዚህ ዜጎች የሚፈለጉት ዶላር ለማምጣት ኤክስፖርት የተደረጉ ዕቃዎች እንጂ እነዜጋ ይቅርና እንደሰውም አደልም፡፡ ከዚሁ ጋር በተያያዘ አብይ ስለሳውዲ አረቢያ እቅድ አድንቆ ሲያወራ ሰምቻለሁ፡፡ ለእኔ ብዙ አያስደንቀኝም፡፡ ለእኛ ሳውዲ አረቢያም ጥሩ ምሳሌ አደለችም፡፡ እኛ ምሳሌ ማድረግ ከአለብን የሩቅ ምስራቅና(ቻይና፣ ኮሪያ፣ ጃፓን) ህንድን ነው፡፡ በተፈጥሮ የጭንቅላት ችግር ያለብን አይመስለኝም፡፡ ችግሩ አራሙቻ በቀለበት እንጂ፡፡ ከ50 ዓመት ጀምሮ የተነሳው አስተሳሰብ ብዙ ዓመት ወደ ኋላ መለሰን፡፡ አብይን አሁን የሚለውን እንዲያስብ ያስቻለው የ60ዎቹ ትውልድ አለመሆኑ እንጂ ከ60ዎቹ ትውልድ አንዱ ቢሆን ዛሬ እያሰበው ያለው የማይረባ በሆነበት ነበር፡፡ አብይ ለራስህ አስበው፡፡ አሁንም ቢሆን ጨለምተኛው የ60ዎቹ ትውልድ አስተሳሰብ እስካልተላቀቅን ብዙ ፈተና አለ፡፡ ግን እየወጣንው መሠለኝ እድሜም ከ60ዎቹ ትውልድ ኢትዮጵያን ነጻ እያደረጋት ይመስላል፡፡
በመጨረሻም ሁሉንም ኢትዮጵያዊ እላለሁ ወሬዎችን ማራገብ ሳይሆን አንድ መስመር ላይ እንሰለፍ፡፡ ችግሮች ሊከሰቱ ይችላሉ፡፡ 27 ዓመት የተገነባ የጥላቻና የውንብድና አሰራር በአንድ ጊዜ አይወገድም፡፡ በዚህ ላይ የተገኘውን ክፍትት ሁሉ በመጠቀም አሁን እየመጣ ያለው ተስፋ ፍጹም እውነት እንዳልሆን ለማስመሰልና በውዥንበር ወደነበረበት ለመመለስ ሴረኞች እንቅልፍ አጥተው እይሰሩ ነው፡፡ ከሕዝብ ጎን የቆማችሁ መሪዎች ምንም አይነት ክፍተት ማለመስጠት ሥሩ፡፡ ችግርም ከአለ በራሳችሁ አንደበት ሳትደብቁ ለሕዝብ ቀድማችሁ ይፋ አድርጉ፡፡ ለሌሎች የሴራ መጠቀሚያነት ከመዋሉ በፊት ጥርት ያለውን ለሕዝብ አሳውቁ፡፡ አብይ መንግስታዊ አካሄድ ሂድ የዜጎችን ደህንነት መጠበቅ ተቀዳሚ ሥራህ ይሁን፡፡ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ እስካልተነሳ ይህን ማድረግ እንደማይቻል ግን እወቅ፡፡ በአስቸኳ ጊዜ አዋጅ ሥም መንግስታዊ መዋቅሩን በወሮበሎች አስይዞ የዜጎችን ደህንነት መጠበቅ አይቻለም፡፡ ቢያንስ በዳንጎቴ ሰራተኞች ላይ የደረሰውን አይነት ጥቃት ማስቀረት በተቻለ ነበር፡፡ በኦሮሚያ እንደበፊቱም ባይሆን አሁንም ዘረኝነት አለ፡፡ በአማራ እያተስፋፋ ያለ ነው የሚመስለው፡፡ ኦሮሞ ብዙ ኢትዮጵያዊነቱን ጥሎ ነው የተጎዳው፡፡ አማራን እስከዛሬ ጉልበትና ተስፋ ሆኖ ያኖረው ኢትዮጵያዊነቱ ነበር፡፡ ከቅርብ ጊዜ በኋላ ከአማራም ብዙዎች ከኢትዮጵያዊነት ፉርጎ ወርደዋል፡፡ በዚህ ጉዳይ ሌላ ጊዜ፡፡ ለዛሬ እንደውም አበዛሁ፡፡
እግዚአብሔር ኢትዮጵያንና ሕዝቦቿን ይጠብቅ! አሜን!
ሰርፀ ደስታ
