ፕ/ሃይሌ ላሬቦ በመገናኛ ብዙሓን እየቀረቡ ስለኢትዮጵያ ታሪክ ገለጻ ሲያደርጉ ኦሮሞን በተመለከተ የተናገሩት ወይም የጻፉት ብዙ የኦሮሞ ምሁራንና አክቲቪስቶች ቁጣቸውን አንዲገልጹ አስገድዷል። በአንጻሩም ሐቅ ተነገረ፤ ኦሮሞዎች/ብሄረተኞች ልክ ልካቸው ተነገራቸው በማለት ድጋፋቸውንና ደስታቸውን የገለጹ አሉ። የመናገር መብት አላቸው ተዉአቸው ብለው የጻፉም አሉ።በዚህ ምክንያት የተነሳው አቧራ እኔም አይን ውስጥ ስለገባ ዝም ማለት አልቻልኩምና የሚከተለውን ጽፌ ለኢትዮ ሚዲያና ለዘሃበሻ ድረ ገት ልኬ አላወጡልኝም። ሰሞኑን ደግሞ በቁቤ ላይ በተጀመረው ዘመቻ መሰል ነገር ውስጥ የፕ/ር ሃይሌ ስም ስላለበት ይህንኑ አስተያየቴን እንደገና መላክ እንዳለብኝ አመንኩ።የጻፍኩትም እኔን እና እኔን ብቻ በመወክል ነው።

አስተያየቴ ፕ/ላሬቦ በኢሳት ጣቢያ ከጋዜጠኛ ወንድምአገኝ ጎሹ ጋር Jan 10, 2017 ባደረጉት ቃለ ምልልስ ላይ ይነሳ እንጂ በተለያዩ መገናኛ ብዙሀን ላይ በለጠፏቸው 2 ጽሁፎች ላይ ያተኩራል። እነኚህም “ምኒልክን ብትወቅሱ ማንነታችሁን ትረሱ” ፤ እና “ከታሪክ መድረክ – ለመሆኑ የብሔር ብሔረሰብ ጭቆና በኢትዮጵያ ነበረ ወይ” የሚሉ ሲሆኑ ጽሁፎቹን 1ኛ እና 2ኛ እያልኩ እጠቅሳቸዋለሁ። ጽሁፎቹም ኢትዮ ሚዲያ ላይ ወጥተዋል።በሌሎች ሚዲያዎች የተናገሩትንም ለማገናዘቢያነት ተጠቅሜአለሁ፡፡በዚህ ጽሁፍ ውስጥ የተጠቀሱ ቀኖች በሙሉ እአአ ናቸው።
በኔ እይታ ቃለ ምልልሱም ሆነ ጽሁፎቹ ኦሮሞን ተናካሽ ናቸው። ይህም የሆነው በሁለት ምክንያት ይመስለኛል። በመጀመሪያ ስለ ኦሮሞ ግልጽ የሆኑ ፋክቶችን ስተዋል፣ተሳድበዋል:: ሁለተኛ ፕ/ሩ ታሪክን የተረኩ ቢሆኑም በአብዛኛው አቀራረባቸው የፕሮፓጋንዲስቶች እንጂ የታሪክ ባለሙያ አይደለም። ፕ/ሩ የሰሩት ቅስቀሳ ነገር ከዚህ በፊት በብዙ ግለሰቦች፤ አክቲቪስቶች፣ጋዜጥኞች ወዘተ ተብሏል፤ በየመጽሔቶች ተጽፏል። ፖለቲከኞች፣ ጓደኛሞች፣ ዘመዳሞች፤ የስራ ባልደረቦች ወዘተ ያለ ብዙ አቧራ ተነጋግረውበታል፥ ተከራክረውበታል። ክርክሮቹ አንዳንዴ ከረር ያሉ ቢሆኑም ፕ/ሩ ስለ ኦሮሞ የሳቱትን አይነት ሰህተትና ስድብ ግን በአደባባይ የተናገረ/የጻፈ ምሁር አላጋጠመኝም።
1 ስለ ኦሮሞ ብዙ የተሳሳቱ መረጃዎችን ተናግረዋል፡ ተሳድበዋልም
“ የወያኔ መንግስት በኣጼ ሚኒሊክ ዙፋን እንደተቀመጠ ቦረና፡ሜጫ፡ቱለማ በመሳሰሉት ስሞች ራሳቸውን ይጠሩ የነበሩትን ብሔረሰቦች የፈጠራ ስም ሰጥቷቸው ኦሮሞ በሚባል በጋራ መጠሪያ ስም እንዲካተቱ አስገድዷቸዋል:: “ (በ2ኛ ጽሁፍ ገጽ 4)
ይህ በስህተት የተሞላ አባባል ቁምነገር ተሰጥቶት መጠቀስ አይገባውም ነበረ:: ነገር ግን የተጻፈው የታሪክ ፕሮፌሰር ነኝ ባሉ ሰው ስለሆነ እና ሙያቸውና ሀሳባቸው በተለያዩ የኢትዮጲያ ሚደያዎች ላይ ስለተስተጋባ ተንቆ የሚታለፍ አይደለም::ፕ/ሩ ስለ ኦሮሞ ሌሎች ብዙ የተሳሳቱ መረጃዎችን ያሰራጩ እና ጎዶሎ ትንታኔዎን የሰጡ ቢሆንም ከሰሯቸው ስህተቶች መካከል ከላይ ባለው ጥቅስ ውስጥ አንጸባርቀው የሚታዩትን የሚከተሉን ውሸቶች ቃል በቃል እናገኛለን፡
- ኦሮሞ የፈጠራ ስም ነው፤
- ኦሮሞ የሚለው ሰም በወያኔ ነው የተሰጠው፤
- ኦሮሞ የሚለው ሰም ወያኔ ስልጣን ሲይዝ የተጀመረ ነው፤
- ቦረና፡ሜጫ፡ቱለማ ወዘተ የሚባሉ ብሔረሰቦች እንጂ ኦሮሞ የሚባል ብሔረሰብ አልነበረም ( ከኢሳት ጋር ባደረጉት ውይይትም ኦሮሞ የሚለውን ስም እልስማማም ብለዋል)፤
- ኦሮሞ የሚለው ስም በግዳጅ ህዝቡ ላይ የተጫነ ነው።
ከስድባቸው መካከል በኢሳት ራዲዮ በጉልህ የተሰማው: “ሁለተኛ ምንድነው ይሄ ጋላ የሚባላው ህዝብ አሁን ኦሮሞ ነው የሚባለው እኔ ግን በቃሉ አልስማማም” ያሉት ዋነኛው ሲሆን፣ በጽሁፎቻቸው ላይ የገዳ ስርዐትን አሳፋሪ ያሉት እና በተደጋጋሚ ስለ ኦሮሞ ዘላንነት/እረኝነት የጻፉት ሌሎቹ ናቸው:: በቅርቡ (ሴፕተምበር 2017) ክአንድነት ሬድዮ ጋር ጋር ባደረጉት ቃለመጠይቅም በአቋማቸው የጸኑ መሆኑን የሚያመለክት ማብራሪያ ሰጠተዋል።
ኦሮሞ አሁን ያለበት ስፍራ መቼ እንደመጣ፤ ከዛ በሁዋላ እስከ ሚኒሊክ አገር ግንባታ ድረስ ከሌሎች የኢትዮጵያ ክፍሎች/ህዝቦች ጋር ስለነበረው መስተጋብር እንዲሁም በሚኒሊክ የተመራው አገር ግንባታ ወቅት የተከሰቱ ድርጊቶችን በሚመለከት የተሟላ ዕውቀት አለኝ ብዬ ስለማላምን ፕ/ሩን አልሞግትም:: ሆኖም የተለያዩ ትርክቶች እንዳሉ እውቃለሁ:: በቂ የሚባል መረጃ በሌለበት ቀርቶ አሁን በአይናችን ፊት እየተፈጸመ ያለውን ክስተት እንኳ በተለያየ መንገድ እየተረዳነው እንዳለን ሳይ ከ100 ኣመት በፊት በተፈጸሙ ክስተቶች ላይ የተለያየ ትርክት ቢኖር አያስገርመኝም:: ነገር ግን ባለንበት ትውልድ ውስጥ የተከናወኑ/ያልተከናወኑ እንደ ስም ፡ቦታ ወዘተ ባሉ ተጭባጭነት /tangible/ ባላቸው ነገሮች ላይ የጎላ ልዩነት ሊኖር አይችልም::
ስለ ማውቀው ሰው ወይም ህዝብ ስም ለመናገር የታሪክ ዲግሪ የሚያስፈልግ አይመስለኝም፡፡በህይወቴ ዘመን እየነኩኝ ስላለፉ ነገሮች መናገር እደፍራለሁ፡፡ ኦሮሞ የሚለው ስም ኦሮሞ በሆኑት ባባቴ ወገኖች፥አማራ በሆኑት በናቴ ወገኖች፥በኦሮሞ ማህበረሰብ በሙሉ፥ ኦሮሞ ባለሆነው ህብረተሰብ በአብዛኛው፥ በኅይለ ስላሴ ዘመን በቋንቋው ስርጭት ያደርግ በነበረው የሐረር ሬድዮ ጣቢያ፥ በደርግ ዘመን በነበሩ መንግስታዊ መስሪያ ቤቶችና መገናኛ ብዙህን በተለይም የኢትዮጲያ ሬድዮ ጣቢያና በሪሳ ጋዜጣ ጥቅም ላይ የዋለ አሁንም እየዋለ ያለ ነው፡፡ እኔ 1983 በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የኢትዮጵያን ታሪክ(Hist 101) የተማርኩበት መማሪያ መጽሐፍ አንድ ርእስ “የኦሮሞ ፍልሰት” የሚል ነበር፡፡ እንግዲህ ቢያንስ በደርግ ጊዜ ኦሮሞ በሌላ ስም አይጠራም፡፡ እርግጥ ነው መሳደብ የፈለጉ ሰዎች በደርግ ዘመንም ቢሆን ጋላ ይሉ ነበር፡፡ ሰዎች ኦሮሞ ሲሉም ሆነ ራሱ ኦሮሞ ስሙን የሚጠቀመው ለሁሉም ጎሳዎች ነበረ፤ ነውም፡፡
ኦሮሞ የሚለው መጠሪያ መቼ ጀምሮ ጥቅም ላይ እንደዋለ አዋቂዎች አስፈላጊ በሆነ ጊዜ በዝርዝር ያቀርቡታል ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ፡፡ እንዲያው ግን ይህ መጠሪያ ቢያንስ ከመቶ አመት በፊት እንደነበረ የጽሁፍ ማስረጃዎን ማቅረብ ይቻላል፡፡ በ1880 የታተመው የ Antonio d’Abbadie መጽሃፍ ርዕስ Sur les Oromo, grande nation africaine… ይላል። በ 1892 የታተመው የViterbo Ettore መጽሃፍ ርዕስ Grammatica e dizionario della lingua oromonica(galla) ይላል። አሩሲዎች ራስ ዳርጌን አሸንፈው በመለሷቸው ጊዜ ከዘፈኗቸው ዘፈኖች ውስጥ ኦሮሞን በማደናነቅ ጠቅሰዋል (E. Cerulli 1922):: ከመቶ ኣመት በፊት መጽሃፍ ቅዱስን ወደ ኦሮሚኛ የተረጎመው ኦኒስሞስ ነሲብ በጻፋቸው መጽሃፎች/ደብዳቤዎች ላይ ኦሮሞ የሚለውን ቃል ተጠቅሟል(E. Cerulli፣1922)። ራሱንም የኦሮሞ አገር ሰው እያለ ያስተዋውቅ እንደነበር ተመዝግቧል(መኩሪያ ቡልቻ፣1995):: በ 1973 የታተመው የ Johannes Launhardt መጽሃፍ ርዕስ Guied to Learning Oromo (galla) Language ይላል።
ከደርግ ስልጣን መያዝ በፊት ኦሮሞን አስመልክቶ የተጻፉት መጽሃፎች ብዙዎቹ በመጽሃፋቸው ርዕስ ላይ ጋላ ቢሉም በውስጥ ገጾቻቸው ላይ ኦሮሞን ይጠቅሳሉ። ለምሳሌ E.C. Foot (1913: 47,78,107)፤ Gaetano Da Padre(1939: 10,39,42 …)፤ Moreno, Matrino Mario (1964, 11,20,16,16 . . .)። በ1973 የተጻፈው የሃይሌ ፊዳ “Hirmaatta dubbii Afaan Oromoo ከደርግ ስልጣን መያዝ በፊት የተጻፈ ሌላው ማስረጃ ነው።
በደርግ ዘመን (ወያኔ ስልጣን ከያዘበት ከ1991 በፊት) የተለያዩ ኢዮጵያውያንና የውጭ ጸሃፊዎች ኦሮሞ የሚለውን መጠሪያ ያውቁ ነበር። ለምሳሌ Edmond Joseph (1988)፣ ባህሩ ዘውዴ (1991)፣ አህመድ ዘካሪያና ሌሎች (1986)፣ Bernd Helen (1981)፣ R Hayward and Mohammed Hassen(1981)፣ Gragg G.B (1982)፣ R. Pankhurst(1976), Hans G Mukarovsky (1991,74)፤ጥላሁን ገምታ (1989)።
አዎ ኦሮሞዎች ራሳቸውን በጎሳቸው የመጥራት ልማድ ነበራቸው፡፡ሆኖም ሁሉም ጎሳዎች አንድ እንደሆ ኑ ያውቃሉ ራሳሸውን ኦሮሞ ይሉም ነበረ፡፡ በጎሳዎች መካከል ያለውን ዝምድና/የዘር ሐረግና ተዋረድ ብዙ ኦሮሞች በቃል ያውቃሉ – ወላጅ ለልጁ ስለሚያስተምር:: የኦሮሞን መነቃቃት በተዳራጀ ሁኔታ ያቀጣጠለው ሜጫና ቱለማ መረዳጃ ማህበር መስራቾችና ደጋፊዎቹ ሁሉንም ጎሳዎች ያካተተ ነበረ፡፡ ከወያኔ ስልጣን መያዝ በጣም ቀደም ሲል የተቋቋመው የኦሮሞ ነጻነት ግንባርም ሁሉን ጎሳዎች አካቶ የኦሮሞን ስም ይዞ የተቋቋመ ነው። ሜጫና ቱለማም ሆነ ኦነግ ጉልበት ባለው መንግስት ሳይሆን በሰዎች ፈቃደኝነት የተቋቋሙ ናቸው፡ጎሳ እንደ ጉዳይም አይታይም ነበር፡፡ ለመሆኑ ቱለማ፣ሜጫ ወዘተ የሚባሉት ጎሳዎች መቼ ነው በየራሳቸው ብሔረሰብ ነን ብለው የጠየቁት እና በግዳጅ ኦሮሞ የተባሉት፡፡ ይህ ስም በግዳጅ የተጫነበትን መመሪያ ደንብ መግለጫ፣ጉባኤ ወይም አዋጅ ወይም ሌላ አሰራር/መሳሪያን የያዘ ዶከመንት ፕ/ር ላሬቦ ያቅርቡ፡፡
አንዳንድ የቀድሞ ታሪክ ጸሐፊዎች/ሰዎች የበርበራ ጋላ፣ የዲንቃ ጋላ፣የቱለማ ጋላ፣የሜጫ ጋላ ወዘተ እያሉ መጻፋቸው ጋላ የሚለው ስም በወቅቱ ከኦሮሞ ውጪ ያሉትንም ይጨምራል ያስብል እንደሆነ እንጂ ቱለማ፣ሜጫ ወዘተ ራሳቸውን የቻሉ ብሄረሰቦች ናቸው የሚያስብል ድምዳሜ ላይ የግድ አያደርስም። ኦሮሞን የማያውቅ በዚህ ጉዳይ ሊታለል ይችላል፡፡ ከኦሮሞ ውጪ ያሉ ሰዎች በወቅቱ ሌሎችን ሁሉ በጅምላ ጋላ ብለው ቢጠሩ ይህ የራሳቸው መረዳት እንጂ የኦሮሞ አይደለም::
በቀደሙት መንግስታት ኦሮሞን በጎሳ፣በክፍለ ሀገር በሃማኖት ለመከፋፈል የተደረገበትን ጫና ተቋቁሞ ዛሬ ኦሮሞ በአንድነት ቆሟል:: ለማንም በማይሰወር ትዕይንት ከወለጋ ጫፍ እስክ ሀረርጌ ጫፍ፣ከሰላሌ እስከ ሞያሌ ድረስ ኦሮሞ ፖለቲካዊ፣ ማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ፍላጎቱን በአንድ ድምጽ እያሰማ ይገኛል፡፡ይህም ሁኔታ አንድነቱን ከቀድሞ በበለጠ በደም የተሳሰረ አድርጎ ታል:: በውጭ አገር ተሰዶ ያለውም ኦሮሞ በተመሳሳይ ጎሳ ሳይለየው ሁሉም በኦሮሞ ስም በአለም መሪዎች ፊት እንደቀረበ ገሃድ ነው፡፡ የኦሮሞ አክቲቪስቶች፣ የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች/አባላት፣ በተለያዩ የአሜሪካ፣ካናዳ፣አውሮጳ፣ አረብ አገሮች፣ አፍሪካ አገሮች ያሉት ኮሚኒቲዎች በሙሉ በኦሮሞ ስም እንጂ በጎሳቸው ስም አይደለም የተደራጁት፡፡ በአገር ውስጥ ያሉት ወያኔ አስገድዳ ኦሮሞ እንዲሆኑ አደረገቻቸው ብንል እንኳ በውጭ ያሉትንስ ማን አስገደዳቸወ? ነገሩ እንዲያውም በተቃራኒው ነው፦ አገር ቤት ያሉት በሞት፣ በድብደባና በእስራት ፊት ሆነው ነው ስለ ኦሮሞ የሚናገሩት፤ በውጭ ያሉት ደግሞ ኦሮሞ አይደለንም፡ ሜጫ ነን፣ ቱለማ ነን፣ ከረዩ ነን ለማለት ከልካይ በሌለበት ስርዐት ውስጥ እያሉ ነገር ግን ስለ አንድነታቸው ድምጻቸውን ከፍ አድርገው የሚያሰሙት።
ብዙ ሰዎች ከየዋህነት ወይም ካለማወቅ የተነሳ የኢህአዲግን አደረጃጀትና ከወያኔ ስልጣን መያዝ ጋር የተጀመረውን በቋንቋ ላይ የተመሰረተ የክልል አወቃቀር በማየት የብሄር ፖለቲካ ያኔ የተጀመረ እና በወያኔ አስገዳጅነት የተጀመረ አድርገው ይቆጥራሉ፡፡ አዎ ወያኔ ብሄርን የኢትዮጵያን ፖለቲካ ማዕከል እንዲሆን ከፍተኛውን ድርሻ ይወስዳል። ኦሮሞ የሚለውን መጠሪያም ሆነ የሌሎች ብሄሮችን ስም ግን ወያኔ ነው በግዳጅ የሰጣቸው የሚሉ ግን አልሰማሁም።
ኦሮሞ ከአንድ ምንጅላት አይወለድም(በኢሳት ቲቪ)፣ ህዝቡ በባህልም ሆነ በቋንቋና ዝርያ በፍጹም አይገናኝም (1ኛ ጽሁፍ ገጽ 31 ) ይላሉ ፕ/ር ላሬቦ:: ህዝቡ አንድ ነን ብሎ በጋራ ቋንቋው እየተግባባ እያለ አይ አንድ አይደለህም የሚለው “ከባለቤቱ ያወቀ ቡዳ ነው” ያስብላል። እሬቻን በቢሾፍቱ ለማክበር የሚሰበሰበው ህዘብ የጎሳ ስብጥር ብቻ አንድነቱን የሚናገር ህያው ምስክር ነው:: በወለጋ፣ሸዋ፣ ሃረርጌ፣ወሎ፡ቦረና፣ባሌ፡አርሲ ወዘተ የሰዎች፣የቦታዎ እና የንዑስ ጎሳዎች ስም መወራረስና መደራረብ ከህዝቡ መያያዝ የተነሳ ነው። አይደለም እንጂ ቢሆንስ? አንድ ህዝብ የጋራ ማንነት ለመያዝ የግድ ከአንድ ምንዝላት መወለድ አለበት? ከአንድ አባት ተወልደው በጊዜ ሂደት የተለያዩ ህዝቦች የሆኑ የሉም እንዴ?ፕ/ር ላሬቦ በመጽሃፍ ቅዱስ አያምኑም እንጂ የሰው ልጆች ሁላችን ከአንድ አባት ከአዳም ነው የመጣን። አብረሃም ከቤተሠቡና ከዘሩ ተለይቶ ከወጣ በኋላ ለሌላ (ለአይሁድ) ነገድ መሰረት ሆነ፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ ያለን ደግሞ የቀረበ ዝምድና እንደሚኖረን እገምታለሁ።
በሌላ በኩል ደግሞ የተለያየ ማንነት የነበራቸው ወደ አንድነት ሊመጡ እንደሚችሉ አምናለሁ፡፡ በኢትዮጵያ ውስጥ እንኳ ሙሉ በሙሉ ወይም በከፊል የተዋዋጡ ነገዶች እንዳሉ ፕ/ሩ ራሳቸው አንዳንድ ምሳሌዎች አንስተው ተናግረዋል፡፡ ተወለድኩበት ያሉት ከምባታ ከተለያዩ አባቶች የመጣ ነው ካሉ ለከምባታ ማንነት ከአንድ ምንጅላት መወለድ መሰረት አይደለም ማለት ነው – ከምባታ የሚባል ብሄረሰብ የለም ካላሉ በስተቀር:: ደግሞስ ሁለት ወይም ከዛ በላይ ማህበረሰቦች በጊዜ ሂደት ተቀራርበው ብዙ የምንጋራቸው ነገሮች አሉን ብለው ወደ ተመሳሳይ ማንነት ላይ ቢደርሱ ማነው ድሮ አንድ ለመሆናችሁ ማስረጃ አምጡ የሚላቸው? አንድ የነበሩ ቢለያዩ፥ ተለያይተው የነበሩ አንድ ማንነት ቢይዙ ታሪክ መዝግቦትና እውቅና ሰጥቶት ይተነትነዋል እንጂ ዘመቻ አይከፍተበትም። ቢቻል ቢቻል ከሌሎች ጋር አንድነትን ተጋርቶ የነበረበትን ታሪክ ብናሳውቅ ወይም ዛሬም ካሉት ሌሎች የኢትዮጵያ ነገዶች/ዘሮች ጋር ያለው መመሳሰልን ለሁሉም ወገን ብናሰተምር፡ ማንነት እየሰፋ እየተዋሃደ ሊሄድ ይችላል። ኮንሶ ከኦሮሞ ጋር ለመተዳደር መጠየቁን የሰማነው ዜና አንድ ምሳሌ ነው። ህዝቦች አውቀውና ፈቅደው ተፈጥሯዊ በሆነ አካሄድ ወደ አንድ ስነልቦና ቢመጡ መልካም ይሆናል። ዛሬ ላይ ያለው ሁኔታ ኦሮሞዎች የራሳቸውን ማነነት በግልጽ የለዩበት ነው። ማንም በዚህ ሊከፋ አይገባውም፡፡ ለመከፋፈል መሞከር፣አለመከባበር፣ ስድብ ፖላራይዝ ያደርጋል እንጂ ሰፋ ወዳለ ማንነት አያደርስም::
በዚህ ሰዓት ሜጫ፣ ቱለማ ወዘተ እንጂ ኦሮሞ የለም ማለት ለምን አስፈለገ? ለኢትዮጵያ አንድነት ሲባል? ከፕ/ር ላሬቦ ቀደም ሲል ብዙ በጣም ብዙ ስዎች ተመሳሳይ ዘመቻ አድርገዋል:: ግን አልተሳካም;: የኦሮሞ ናሽናሊዝም እየተስፋፋ ሄደ እንጂ አልጠፋም፡፡ ማንም ሰው በክብር ከኖር የዘሩን ጉዳይ እምብዛም ትኩረት አይሰጠውም:: አለመታደል ሆኖ ይህ አልሆነም:: ብሄረተኝነትን/ ዘረኝነትን ኦሮሞ አልጀመረውም፣ እንዲያውም ሰለባ ሆነ እንጂ:: በሚኒሊክ የተደረገው አገር ግንባታ ኦሮሞን በጉልበት ከቀላቀለ በኋላ ሌሎችን በላዮ ላይ ባይሾም፣ መሬቱን ወስዶ ለስርዓቱ አገልጋዮች በመሰጠት ገባር ባያደርገው፣ ቋንቋውና ባህሉ እኩል ለእኩል ክብር ቢያገኝ፡ የሱም ማነነት ኢትዮጵያን ዲፋይን/define/ ቢያደርግ የዛሬዋ ኢትዮጵያ ነዋሪዎች ዘራቸው ተጨማሪ ማንነት እንጂ የፖለቲካ መዘውር አይሆንም ነበረ::
አሁንም በኦሮሞ አንድነት ፊት መቆም ለኢትዮጵያ አንድነት ሊበጅ አይችልም:: ለዘመናት የተጠማውን ቋንቋውንና ባህሉን በመጠቀም ሀሴት ያደርግ፣ ራሱን በራሱ ያስተዳድር፣ በኢትዮጵያ ውስጥ ተገቢውን ማለትም በቁመቱ ልክ ስፍራ ያግኝ። በመግባባትና በመተሳሰብ ላይ ከተደረገ ይህ መሆኑ ማንንም አይጎዳም። ሌሎች ህዝቦች ማንነቱን አውቀው ለመብቱ መከበር ሲተባባሩት ኦሮሞም ለሌሎች እጁን ይዘረጋል። በመሬት ላይ መጎራበታችን፣ በብዙ ቤተሰብ ደረጃ በጋብቻ መተሳሰራችን፣ በጉርብትና፣ በት/ት ቤት በስፖርት፣ በንግድ ወዘተ አማካይነት ጓደኛ መሆናችን፡ በየእምነት ቤታችን አብረን ማምለካችን እና ሊሎችም ግኑኝነቶታችን ለአንድነታችን ማስቀጠያ መሰረቶች ወይም ገመዶች አድርገን ልንጠቀመባቸው እንችላለን:: ማስገደጃ ሊሆኑ ግን አይችሉም:: ጎን ለጎን እውነተኛ ዲሞክራሲና ፍትሃዊ የሃብት ክፍፍልን የሚተገብር ስርዐት ማስፈን ነው ለኢትዮጵያ አንድነት የሚበጃት:: መከባበር መቻልም ሩቅ ያስጉዘናል። አሁም ምንም መከባበር የለም ማለቴ አይደለም፤ እንዲያውም የአሁኑ ትውልድ ብዙ የተራመደ ይመስለኛል፡፡ የጎንደሮች “የኦሮሞ ደም ደማችን ነው” ማለት ለመከባበር/ለመተሳሰብ ትልቅ እርምጃ ነው።
መከባበርን ከሚያጠፉ ነገሮች አንዱ ስድብ ነው:: መቼም እስክ ሃይለ ስላሴ ዘመነ መንግስት ማብቂያ ድረስ የነበሩ ኦሮሞች ስድብንና ንቀትን ጠግበው አልፈዋል:፡ በደርግ ጊዜ ብዙ መሻሻል የታየ ይመስልኛል፤ ቅሪቱ ቢኖርም:: በተለይ ጋላ የሚለው መጠሪያ ሞቶ የተቀበረ መስሎ ነበር:: ፕ/ሩ ዛሬ ይህን ቃል ከመቃብር ቆፍረው ለአዲሱ ትውልድ ለማስተዋወቅ ለምን ፈለጉ? አንድ የታሪክ ባለሙያ ስለ ስሞቹ አመጣጥና ተወራራሽነት ለተማሪዎቹ በዝርዝር ቢያስተምር አግባነት አለው። ለህዝብ በሚዲያ ሲያቀርብ ግን የአሁን ስሙን ብቻ ይጠቀማል፤ አስፈላጊ ሆኖ የቀድሞ ስሙን ከጠቀሰ አብሮ የቀድሞ ሰሙን አጠቃቀም ቢናገር ትክክል ይሆናል;; ፕ/ሩ “ይህ ጋላ የሚባል . . .” በማለት የገለጻቸው መግቢያ አድርገው መጀመራቸው ከአጠቃላይ ንግግራቸው ይዘት ጋር ተደምሮ ተሳዳቢ ያሰኛቸዋል፡፡ በ2ኛው ጽሁፍ ገጽ4 ላይ በአንድ አንቀጽ ውስጥ “አሁን ኦሮሞ ድሮ ጋላ” ይባል እንደነበረ 2 ጊዜ በተከታታይ መጥቀሳቸው በእውነት ሰለ ኦሮሞ የማያውቅ ኢትዮጵያዊ አንባቢ ስላለ ደጋግሞ በመናገር ግልጽ እንዲሆን ፈልገው ነው? ፕ/ሩ ስለ ኦሮሞ እረኝነትም የተናገሩትም እንዲሁ ነው። ችግሩ ያለው ቃሉ ላይ አይደለም – አጠቃቀማቸው እንጂ። ከኢሳት ቃለምልልስ በኋላ ፕ/ር ላሬቦ በተለያዩ ራድዮኖች ስለ እረኛ ትርጉም በመስጠት ሲዳክሩ ሰምቼ አሳዝነውኛል፡፡ እረኛ በራሱ መጥፎ ቃል አይደለም፤ ቃሉ የሚውለው በዛ ስራ ላይ ለተሰማራ ሰው ነው። ነገር ግን እረኝነት በብዙ ማህበረሶቦች ዘንድ እንደ ዝቅተኛ ሰራ ስለሚቆጠር ሰዎች ሌሎችን ዝቅ አድርጎ ለማሳየት ሲሉ እረኛ እንደሚሉ እናውቃለን። ሀዝብ ሙሉ በሙሉ በእረኝነት ላይ አይሰማራም ። በውስጡ ቢያንስ ቢያንስ የአስተዳደር ሃላፊዎች፣ ዳኞች፡ የጦር መሪዎች፣የሃይማኖት መሪዎች፣ የእጅ ባለሙያዎች፣ብዙ ከብቶች ያላቸው ባለሃበቶች አሉባቸው። አብዛኛው ህዝብ የሚተዳደረው በከብት ማርባት እንደነበረ ለመግለጽ አርብቶ አደር ህዝብ ሊባል ይችላል:: ግን ህዝብ እረኛ አይባልም:: ፕ/ር ላሬቦ በ 2ኛ ጽሁፋቸው ላይ በገጽ 5_6 ላይ በሁለት ተከታታይ አንቀጾች ውሰጥ “እረኛ ህዘብ”፣ “ዘላኖቹ፣የእረኝነት ኑሮአቸውን” በማለት ደጋግመው ሰለ ኦሮሞ ገለጻ ያደረጉት ለኢትዮጵያዊ አድማጭ ስለ ኦሮሞ የማያውቀውን መረጃ ለመስጠት አይደለም። በነኚሁ አንቀጾች ውስጥ የኦሮሞን አረመኔነት መተረካቸው ለደረስኩበት ድምዳሜ ምክንያት ሆኖኛል። አንዳንድ መጠሪያዎች እንደ ስድብ እንደሚቆጠሩ ፕ/ሩ ራሳቸው ያውቃሉ። ግሪኮች ኢትዮጵያን “ጥቁር ህዝብ” እንደሚሉ፤ ይህ ማለት ደግሞ ኒግሮ ማለት እንደሆነና እሱም እንደስድብ እንደሚቆጠር ለኢሳት ተናግረዋል።
ለመሆኑ አንድ ህዝብ ራሱን ስሜ ይሄ ነው ካለ አይ አይደለም ለማለት በምድር ላይ ስልጣን ያለው ማነው? እንኳን ቀድሞ የነበረ ስሙን ቀርቶ ወዶ አዲስ ቢያወጣ ወይም ሌላ የነበረን ስም ቢወርስ አልቀበልም ማለት ይቻላል? አንድን ህዝብ እሱ ራሱን የሚጠራበትን አውቀው በስሙ የሚጠሩትን እንዳከበሩት ይቆጥራል፤ ስሙን የማያውቁትን ወይም የረሱትን ግዴለሽ ይላል፤ በሌላ ስም የሚጠሩትን ቅር ይሰኝባቸዋል፤ እንደ ስድብ በሚቆጥረው ስም የሚጠሩትን ግን እንደሚጠሉት ሊቆጥር ይችላል፡፡
ሌላው የፕ/ር ላሬቦ ስድብ የኦሮሞ ህዝብ እንደ ቅርሱ የሚቆጥረውን የገዳን ሰርዓት “አሳፋሪ” (1ኛ ጽሁፍ ገጽ 33)፡ ”ገዳና ግድያ በቃላት ይለያዩ እንጂ ትርጉማቸው እንድ ነው:: እጅና መዳብ ናቸው ”(1ኛ ጽሁፍ ገጽ 33) ማለታቸው ነው፡፡ ለመሆኑ ማስረጃቸው ምን ይሆን? እንደሳቸው ሳይሆን የገዳ ተቋም በዮኒስኮ ተመዘገቦ የአለም ቅርስ ሆኗል። ፕ/ር ላሬቦ ስለ ኦሮሞ ስም፣ባህልና ስነልቦና በቂ እውቀት የላቸውም። ፕ/ሩ ከመረጃ ርቀው ይሆን ወይስ ጥላቻ አእምሮአቸውን ጋርዶታል?
ከላይ እንደገለጽኩት ፕ/ሩ ሲፈልጉ ኦሮሞ የፈጠራ ሰም ነው፣ አልስማማም ይላሉ:: ሲፈልጉ ጋላ ማለት ኦሮሞ ሰለመሆኑ ያከራከራል ይላሉ (1 ኛ ጽሁፍ ገጽ 30):: በሌላ በኩል ራሳቸው ኦሮሞን እና ጋላን እያቀያየሩ ይጠቀማሉ። በ 1ኛ ጽሁፍ ገጽ 4 ላይ “. . . ያደረሱትን ጥፋት ባይናቸው ያዩት፥ . . . ጋላ ፈጽመ ከሚሉት ግፍና ጭካኔ የተነሳ ድርጊታቸውን አገሪቷን ለመቅጣት . . . የተላክ . . . ብለው ገልጸውታል” ብለው የጻፉት ፕ/ር ይህንኑ ሃሳብ በ2ኛ ጽሁፍ ገጽ 34 ላይ ደግሞ ” . . ካቶሊኮች፤ ኦሮሞዎችን አምላክ ኢትዮጵያውያንን . . ሊበቀል የላከው . .” በማለት ጽፈዋል:: ከኢሳት ጋር ባደረጉት ውይይት “ አልስማማም” ያሉትን ”ኦሮሞ” የሚለውን ሰያሜ በዛው ቃል መጠይቅ ውስጥ እና በጽሁፎቻቸው ውስጥ ሲጠቀሙ ያለምም በቂ ማብራሪያ ነው፡፡
ፕ/ላሬቦ ስለ ኢትዮጵያ እንደማያስተምሩ ከECADF ሬድዮ ጋር ካደረጉት ቃለ ምልልስ መረዳት ይቻላል። ያ ማለት ስለ ኦሮሞም አላሰተማሩም። ስለ ኦሮሞ ያደረጉት ጥናትም የለም፤ ስለ ጨለንቆ ይቅርና፡፡ ታዲያ ፕ/ር ላሬቦ ለምንድን ነው ዶ/ር ነጋሶ ጊዳዳ በታሪክ ተመረቁ እንጂ ታሪክ አላስተማሩም ያጠኑትም ስለ ወለጋ እንጂ ሰለ ጨለንቆ አካባቢ አይደለም፤ ስለዚህ ስለጨለንቆ አያውቁም፤ የተናገሩትም ስህተት ነው በማለት ይቅርታ ይደረግላቸው በማለት ለኢሳት ጋዜጠኛ የተናገሩት? ስለ ኦሮሞ ለመናገር ወለጋ ላይ ጥናት ያደረጉት ግን ኮሌጅ ውስጥ ያላስተማሩት ዶ/ር ነጋሶ ጊዳዳ ወይስ ምንም ጥናት ያላደረጉት፣ ምንም ያላስተማሩት ፕ/ር ላሬቦ የተሻለ ብቃት አላቸው? ለመሆኑስ ማነው ይቅርታ አድራጊው? ፕ/ር ላሬቦንስ ማን አማላጅነት ጠራቸው? የፕ/ር ላሬቦን መለኪያ ተጠቅሜ ራሳቸው ስለ ኦሮሞ ስላላጠኑ እና/ወይም ስላላስተማሩ ሁሉን አውቃለሁ ማለቱን አቁመው፤ ጥናት አድርገው ወይም አስተምረው ብቃት እስኪያዳብሩ ድረስ ስለ ኦሮሞ እንደ ታሪክ ባለ ሙያ ሆነው ከመናገር መቆጠብ አለባቸው እላለሁ::
አቀራረባቸው የፕሮፓጋንዲስቶች እንጂ የታሪክ ባለሙያ አይደለም
ታሪክን በታሪክነት እንደ ባለሞያ የምናወራ ከሆነ ያለፉትንም ሆነ ያሉትን የታሪክ ተዋናኞች ደግፈንም ነቅፈንም ሳይሆን በወቅቱ የነበሩ ክስተቶችን ከወገንትኝነት በጸዳ መልኩ ማቅረብ፤ በማስረጃ ማስደገፍ፤ ምክንያቶችንም መተንተን መሆን አለበት ይመስለኛል። አስፈላጊ በሚሆን ጊዜ ሌሎች የታሪክ ባለሙያዎች ወይም ሰዎች የጻፉት ታሪክ መረጃው ወይም ትንታኔው ትክክል ካልሆነ አሁንም ከወገንተኝነት በጸዳ ሁኔታ በመረጃ ላይ ተመስርቶ ማስተካከያውን ማቅረብ የታሪክ ባለሙያ ተግባር ዋናው ይመስለኛል። የታሪክ ባለሙያ አቀራረቡም ሆን አስተምሮው በተቻለ መጠን ከፖለቲካ ወገንተኝነት የራቀ መሆን ይገባዋል። ፕ/ሩ ራሳቸው ለኢሳት ሲናገሩ እንደሰማሁት “ታሪክን የፖለቲካ ገረድ ማድረግ አይገባም”። ለፖለቲከኛ ደጋፊ ይገኛል፤ ተቃዋሚም ያፈራል። የታሪክ ባለሙያ የሚያስፈልገው ደጋፊም፤ ተቃዋሚም ሳይሆን በሁሉም ዘንድ መታመንንና መከበርን ነው።
በቅስቀሳ/በፖለቲካ ስራ ላይ ያሉ ሰዎች/ቡድኖች ታሪክን መነሻ አደርገው (በቅንንነትም በማጣመምም) ያለፉ ክስተቶችን ሊያንቆለጳጵሱ፤ እንዲቀጥል ሊያበረታቱ፤ ሊተቹ፡ ሊቀለብሱ የሚያስችሉ ሃሳቦችን/opinion፤ ፕሮግራሞችንና ቅስቀሳዎችን ቢያወጡ እንደስራችው ልንወስድ እንችላለን። ሃሳባቸው በህዝብ ዘንድ ሊሰርጽ ይችላል ወይም ተቀባይነት ላያገኝ ይችላል። የታሪክ ባለሙያ ግን በገለልተኛ ስፍራ ቆሞ ሙያው የሚፈቅድለትን ስነምግባር ተከትሎ ታሪክን ይናገራል – የፖለቲካ ሂደትን ለማፋጥንም ለመቀልበስም ዓላማ አድርጎ ሳይነሳ።
አሜሪካን ሂስቶሪያን ማህበርና የአውሮፓ የታሪክ አስትማሪዎች ማህበር በየራሳቸው ባወጡት የስነምግባር ደንብ ውስጥ ጥቂቶቹ እንዲህ ይላሉ፦
- የታሪክ ባለሙያ የሕብረተሰቡ አካል እንደመሆኑ መጠን ከቤተሰቡና ከአካባቢው የወረሳቸው ልክ ያልሆኑ ግምቶች/ባያዝ/ ሊኖሩት ስለሚችሉ እነኚህ እንዳይጫኑት ጥረት ማድረግ አለበት፤
- ሌሎች የታሪክ ባለሙያዎች/ሰዎችን ስራ ማክበር ይገባዋል ምክንያቱም በአንድ ባለፈ ጉዳይ ላይ መረጃው ተመሳሳይ ሆኖ እያለ እንኳ የተለያየ ዓይነት ግንዛቤ ሊያዝ የሚቻል ስለሆነ፤ የተለያየ መረጃም ሊኖር ይችላል፤
- አጨቃጫቂ ወይም ስሜት ነኪ/ቀስቃሽ ትርክቶችን/ጉዳዮችን በሃላፊነት/በጥንቃቄ መያዝ ይገባዋል። ፍርደ-ገምድል የነበሩ/የሆኑ ትርክቶችን ወደ መልከ-ብዙ ትርክትነት በማምጣት በሕብረተሰቡ ውስጥ ነጻ ውይይት እንዲፈጠር ያበረታታል፤
- በራስ እይታ ላይ የተመሰረቱ አስተያየቶችን አለመስጠትና እንዲሁም በአድማጩ ዘንድ እንደ ሰድብ/መጥፎ/የሚቆጠሩ ቃላቶችን ከመጠቀም መራቅ፤
- ራቅ ባለ ዘመን የተፈጸሙ( በቅርብ የተፈጸሙን ጨምሮ) ክስተቶችን አስመልክቶ ከአንድ በላይ እውነት ሊኖር እንደሚችል መገንዘብ፤ የታሪክ ባለሙያ የራሱን ዕይታ ይኖረዋል፤ ነገር ግን የሱም ሆነ የሌሎች ዕይታ በወቅቱ ከነበረው ሁኔታ እንጻር እንደሚታዩ ማወቅ ይገባዋል፤
- በስራው ላይ ትችት/ክሪትስዝም/ እንደሚኖር አውቆ ይዘጋጃል፤
- የታሪክ ባለሙያ ታሪክን በግል በባለቤትነት/ሞኖፖሊ/ ሊይዝ አይችልም። ታሪክ ራሱ በሰዎች ማንነትና ሕይወት ውስጥ ሰንጥቆ የሚያልፍ በመሆኑ ሁሉም ሰው ባለድርሻ ነውና፤
- በተከፋፈሉ/ፉክክር ላይ ባሉ የህብረተሰብ ክፍሎች መካከል ዘላቂ መግባባት እንዲመጣ ያበረታታል።
እነኚህን የስነምግባር መርሆዎች አብዛኞቹን ፕ/ር ላሬቦ በየሚዲያዎቹ ሲገልጹ ሰመቻለሁ። ሆኖም ራሳቸው በግልጽ ጥሰዋቸዋል። ከዚህ አንጻር በፕ/ሩ ያዘንኩባቸው ጉዳዮች ከብዙ በጥቂቱ የሚከተሉት ናቸው፦
- ፕ/ሩ አብዝተው ወገንተኝነት አሳይተዋል
ያለፉት 40-50 አመታት የኢትዮጲያ ፖለቲካ ማእክላዊ ጉዳይ የኢትዮጲያ አመሰራረት እና የብሔር-ብሔረሰቦች አያያዝ መሆኑና በተለይም የአጼ ሚኒሊክ ድርሻ በተለያዩ ወገኖች የተለያየ ትርጉም እንደሚሰጠው እየታወቀ ፕ/ሩ አጼ ሚኒሊክን ከአለም ተወዳዳሪ የሌላቸው መሪ አድርገው አቅርበዋል (1ኛ ጽሁፍ ገጽ 4)፡ ኢትዮጲያውያን በሙሉ ተከፍሎ የማያልቅ ውለታ አለባቸው (1ኛ ጽሁፍ ገጽ 2) በማለት በጣም አግንነዋቸዋል::
ማወደሱ ይሁን መሳደቡን ምን አመጣው። አጼ ሚኒሊክን የወቅሱትን ወይም ከፕ/ር ላሬቦ የተለየ ሀሳብ ያላቸውን ሁሉ ቅሌታም (1ኛ ጽሁፍ ገጽ 16)፤ ጥሬ ሰው (1ኛ ጽሁፍ ገጽ 22) ፤ እውነትን ለመቀበል ዝግጁ ያልሆኑ(1ኛ ጽሁፍ ገጽ 6)፤ የጎሳ ጽንፈኞች ((1ኛ ጽሁፍ ገጽ 23)፤ የፖለቲካ ጮሌዎች(1ኛ ጽሁፍ ገጽ 24) ብሎ ቃል በቃል መሳድብ የምን ዓይነት ሙያ ሰራ እንደሆነ እላውቅም ። እንደ አንድ ዜጋ የወደዱትን ማግነን ያልፈለጉትን መቀመቅ መክተት መብታቸው ነው- እንደ ታሪክ ባለሞያ ግን አንድ እውነት ብቻ ነው ያለው፤ ያንን ያልተቀበለን ቅሌታም ነው ማለት ከስነ ምግባር ውጪ ነው፡ ታሪክን የፖለቲካ ገረድ ማድረግ ነው።።
ለኢሳት የጨለንቆ ጦርነት 30 ደቂቃ በማይሞላ ጊዜ ውስጥ በሚኒሊክ ጦር አሽናፊነት መጠናቀቁን ሲተርኩ ልክ በቦታው እንደነበረ ስው “… ከመቅጽበት ዓይን በሚደንቅ ፍጥነት ደርሶ. . . (1ኛ ጽሁፍ ገጽ 41) በማለት እንደ ጋዜጠኛ ዘግበዋል፤ ከኢሳት ጋዜጠኛ ጋርም አድናቆትን በሚያሳብቅ ሁነታ ሲሳሳቁበት ስምቻለሁ። ሚኒሊክም ሆነ ሚኒሊክ የወጉት ወገን (ኦሮሞም ይሁን አደሬ) ኢትዮጲያዊ እስከሆኑ ድረስ አንዱን ጀግና ሌላውን መሳቂያ ማድረግ ለዚህ ትውልድ አይመችም። ጉዳዩ የታሪካችን አንድ አካል ነው፤ ይጠና፣ ከስሜት በጸዳ ሁነታ ይዘገብ።
በብዙ ስፍራ ኦሮሞ አደረሰ ያሉትን ውድመት በስፋትና ስሜት ቀስቃሽ በሆነ ሁኔታ ዘርዝረዋል (1ኛ ጽሁፍ ገጽ 33-34)፡በኦሮሞ ላይ ስለደረሰው እካላዊም ሆነ ሞራላዊ ጉዳት ለመናገር አልፈለጉም፤ እንዲያው በደፈናው ሚኒሊክ ሰው ናቸውና ስህተት አያጡም በማለት አቃለው አልፈዋል (1ኛ ጽሁፍ ገጽ 8):: በተቃራኒው ኦሮሞ በሚኒሊክ ተጠቃሚ መሆኑን ደግመው ደጋግመው ይናገራሉ። ከECADF ፎረም ላይም ኦሮሞዎች ያደረሱት በደል ናላን የሚያዞር ነው፤ ገና ተዘርዝሮም አላለቀም ካሉ በኋላ እንዲያውም እሳችው ስለ ኦሮሞ በቅርቡ ሌላ መጣጥፍ እንደሚያወጡ ተናግረዋል፡፡ እኔ እንዲህ እላለሁ: የፈለጉትን ብለው ይጻፉ፤ የሚሉት ሁሉ የታሪክ ባለሙያ እንደተናገረው ሳይሆን እንደማንኛም ተራ ሰው አባባል/አቋም ይቆጠራል:: እስካሁን ባለኝ መረጃ ፕ/ሩ ስለ ኦሮሞ ቋንቋና ባህል አያውቁም፤ ስለዚህ ምንም ነገር በስልጣን መናገር አይችሉም። ፕ/ር ላሬቦ ከሆነልዎት በሚቀጥለው ፕሮፓጋንዳዎ ስድብን አስውግደው ይጻፉ::
2 ፕ/ላሬቦ እሳቸውን ሁሉን አዋቂና እውነተኛ አድርገው አቅርበዋል:: ከሳቸው ሃሳብ ጋር የማይስማማ ስድብና ዘላፋ ይቀምሳል፡ ስም ይወጣለታል:: ለምሳሌ በ1ኛ ጽሁፍ ላይ ብቻ የሚከተሉን እንመልከት፦
ገጽ 6 “ በየቡናቤቱና በየመሸታ ቤቱ ከመሰሎቻቸው የሚወራው ወሬና ልቦለድ “
“ስለ አጼ ሚኒሊክ ጥሩነት ሊቀበሉ ዝግጁ አይደሉም እውነት ነጻ እንዳታወጣቸው ይሸሿቷል፡፡
ገጽ 7 “ ይህንን ዐይነት ክብረ ቢስነት በኤርትራዊያን ምሁራን . . .”
ገጽ 16 “ በእሬትና በስኳር . . . መካከል ያለውን ልዩነት መናገር የማይችሉ ቅሌታም . . .”
ገጽ 17 “ ይህም ኢትዮጲያውያን በንግግር እንጂ በተግባር የሚረቡ እንዳልሆኑ . . . “
ገጽ 22 “ ጥሬ ሰው ብቻ ነው ያጼ ሚኒሊክን. . . “
ገጽ 23 “ አንዳንድ የጎሳ ጽንፈኞች . . . “
ገጽ 24 “ ከአፍንጫቸውና ከሆዳቸው ባሻገር አልፈው ማሰብ የማይችሉ ባላባቶችን . . . “
ገጽ 24 “ አንዳንድ የፖለቲካ ጮሌዎች . . . “
ገጽ 28 “ እንዲህ ዓይነት . . . ችሎታ ያጣ፣ ቅሌታምና ግፈኛ መሪ . . . “ (ግራኝ መሃመድን)
ገጽ 30 “ ባሁኑ ወቅት በሰፊው የተሰራጨውን ተረት ከማስተጋባት በስተቀር ጥልቀትና ቁምነገርኝነት የለውም “ (አቶ አበራ ቶላ የጸፉትን መጽሃፍ)
ገጽ 31 “ፍሬ ነገሬ . . . ዘውገኞች ስለዚህ ህብረተሰብ የሚሰብኩት ስብከት ልበወለድ አንጃ ግራንጃ “
ገጽ 32 “ማንም በሠለጠነው በዛሬው ዘመን ልብ ያለው ሰው . . . ጭንቅላቱን መመርመር . . . በዚህ የማይስማማ ካለ እሱራሱ የአእምሮ ችግር እንዳለው ይቆጠራል “ (ስለ ገዳ ሉባ )
ገጽ 34 “ ስለዚህ ዛሬ . . . የኔ ዘር ንጹህ ነው ሊል አይችልም፡፡ የሚል ካለ ወይ ውሸታም . . .የሚናገረውን የማያውቅ . . . ”
ገጽ 36 “ እንግዲህ. . .ቅሌታም ብቻ ነው ልቦ ወለድን. . . (የአኖሌ ጭፍጨፋ ተካሂዷል የሚሉትን እና/ወይም ተስፋዮ ገ/አብን)
ገጽ 38 “ በ አሩሲ . . . አጥጋቢ . . . በፈጠራና በስብከት “
ገጽ 40 “እኔ በተፈጥሮዮ ከፈረንጅ ስር ቱስ ቱስ . . . “ (ዶ/ር ነጋሶ ጊዳዳን)
ገጽ 46 “ በጥራዝ ነጠቁና እቤተ ክርስቲያን እንደገባችውሻ . . .”
ገጽ 46 “ . . . የአሽሟጣቾቻውን ከንቱነት ብኩንነት”
3 ፕ/ር ላሬቦ ለትችት ዝግጁ አይደሉም፣
በማህበራዊ መገናኛ የለቀቋቸ ጽሁፎች (በ1ኛውም በ2ኛውም) ላይ አስተያየት ለመስጠት የሚያስችል አድራሻ አላስቀመጡም፡፡ ኢሜላቸውን አግኝተው አስተያየት የሰጡአቸውን ሰዎች እንዴት ኢሜይሌን አገኙት ብለዋል፣ የታሪክ ባለሙያ አይደሉም በማለት ወርፈዋቸዋል (1ኛ ጽሁፍ ገጽ 7)።;
4 ፕ/ላሬቦ የፖለቲካ አክቲቪስት ናቸው
በ1ኛ ጽሁፍ ገጽ 7 ላይ እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ ተቃውሞውን እንዲያሰማ ጥሪ አቅርበዋል:: ከዐውደ ንባቡ (አንቀጹ) እንደምረዳው ተቃውሞው እርሳቸውን በሚተቹት ላይ እንዲደረግ የፈለጉ ይመስላል፣ በሌላ በኩል የታሪክ ባለሙያ ሳይሆኑ ስለ ታሪክ የሚጽፉ/የሚናገሩትን ሊሆን ይችላል::
አንድ የታሪክ ባለሙያ የሚያስፈልገው መታመን መቻል እና ከዛ ጋር ተያይዞ የሚመጣ መከበር/መደመጥ እንጂ ድጋፍ አይደለም:: እሳቸውም የሚያውቁትን ብቻ ያስተምሩ -ማናቸውም ጉዳይ በሌላ መልኩ ሊታይ እንደሚችል ሳይዘነጉና ያንንም እውቅና እየሰጡ:: ለመሆኑ በአንድ ቀደም ሲል በተፈጸመ ክስተት ላይ ሁለት ኢትዮጵያውያን የተለያየ ግንዛቤ ቢይዙ እርስ በእርስ መቀዋመም አለባቸው እንዴ? የታሪክ ባለሙያ ስነ ምግባር የሚጠይቀው ከመቀዋመም ይልቅ አንዱ የአንዱን አቋም ለመረዳት እንዲችል ማበረታታና የተፈጸሙ ድርጊቶች በተፈጸሙበት ዘመን ከነበረው ሁኔታ አንጻር ሊታዩ እንደሚገባ ማስተማር ነው;;
ከዚህ ጋር ተያይዞ የምለው፡ ታሪክ የሚነገረው ስለ ድሮ የማናውቀውን ለማሳወቅ ወይም የረሳነውን ለማስታወስ ነው እንጂ ለማዝናናት አይመስለኝም:: ምናልባት በጣም ሩቅ ዘመን የሆነው ታሪክ ለምሳሌ የንግስት ሳባ ታሪክ አይነት በየትኛውም መልኩ ቢነገር አድማጩን ሊያስደስት/ሊያዝናና ይችላል:: ነገር ግን አከራካሪ የሆነው የቅርብ ጊዜ የኢትዮጵያ ታሪክ ሲተረክ ማንንም ለማስደሰት መሆን አይገባም፡፡ ተጎድቻለሁ በሚልበት ጉዳይ ላይ እንድትደሰትበት ጽፌልሃለሁ (1ኛ ጽሁፍ ገጽ 4) ማለት ማሾፍ ነው፡፡ በርግጥ ፕ/ሩ ሊያስደስቱ የፈለጉት ወገን አለ – እሱም ድጋፉንና ደስታውን ገልጿል:: ፕ/ሩ ፖላራይዝ አደረጉን እንጂ ከአቋማችን የጣት ያህል አላንቀሳቀሱንም።
ሰሞኑን ደግሞ ከአንድነት ሬድዮ ጋራ ባደረጉት ቃለመጠይቅ ኦነግን በመተቸት ፖለቲካ ስራ ውስጥ በቀጥታ ገብተዋል። እሱም ቢሆን የድርጅቱን መስራቾቾ የግል ስብእና ለማዋረድ ሞክሩ እንጂ ፍሬ ያለው ነገር አልተናገሩም። ፕ/ር ሃይሌ ላሬቦ በተማሪዎቻቸው፣ በመምህራንና በሃላፊዎቻቸው ተረጋግጦ በፍርድ ቤት ጭምር የጸደቀው ሃሳብን በአግባ ቡ ያለማደራጀትና በግልጽ ያለማቅረብ፣ የሚያስተምሩት ትምህር ይዘተ የተዘበራረቀ መሆን ድክመታቸው ይሆን እንዴ እንዲህ የታሪክ ባለሙያ፣ ፓለቲከኛ፣ አክቲቪስት፣ ተሳዳቢ የሚያደርጋቸው።
5 ፕ/ሩ ራሳቸውን (የታሪክ ባለሙያዎች) ብቻ የታሪክ ትምህርት ባለቤት አድርገው ያያሉ
በ1ኛው ጽሁፍ ገጽ 7 ላይ እንዲህ ብለው ጽፈዋል “ በጣም የገረመኝ ነገር ቢኖር ሙያቸውና እውቀታቸውን በምንም መልኩ ከታሪክ ትምህርት የማይገናኝ ሁኖ ሳለ በታሪክ ውስጥ ገብተው ሊፈተፍጉና ሊያስተምሩኝ ይሞክራሉ:: ለነዚህ ዐይነቱ ታሪክ ማለት ማንም አፈ ጮሌ ገብቶ የሚፈተፍትበት የጥናት ዘርፍ ይመስላቸዋል”። እርግጥ ነው የታሪክ ዲግሪ ያለው ባለሙያ ለመረጃ የተሻለ ቅርበት አለው፣መረጃዎችንም ለመተንተን የተሻለ የትምህርት ዝግጅት አለው:: ሆኖም ታሪክ የሚፈጸመው በግለሰቦችና በህዝብ ነው፣ እያንዳንዱም ሰው በታሪክ ይነካል፣ ስለሚያውቀውም ይናገራል:: ይህን ማወቅ የታሪክ ባለሙያ አንዱ ስነምግባር ነው::
- ፕ/ር ላሬቦ ሌሎች ባለሙያዎችን ይነቅፋሉ
የውጭ አገር ጸሃፊዎችን
የውጭ አገር ጸሃፊዎችን ያጥላሉ (1ኛ ጽሁፍ ገጽ 27)፤ ሲመቻቸው ደግሞ የውጭ አገር ጸሃፊዎን ምስክር አድርገው ያቀርባሉ (1ኛ ጽሁፍ ገጽ 20)።
የውጭ አገር ጸሃፊዎችን ከማይቀበሉበት ምክንያ ት አንዱ ለራሳቸው ጥቅም ነው የሚጽፉት በማለት ነው (1ኛ ጽሁፍ ገጽ 14):: ከECADF ሬድዮ ጋር ካደረጉት ቃለ ምልልስ መረዳት እንደሚቻለው ፕ/ር ላሬቦም የታሪክ ትምህርትን የመረጡት ከስራ ማግኘት አንጻር እንጂ እንግሊዝ አገር የሄዱት ፍልስፍና ፍካሬ መለከት ለማጥናት ነበረ;;
የአገር ውስጥ ጸሃፊዎችን (ራሳቸውን ይጨምር ይሆን?)
1 ኛ ጽሁፍ ገጽ 27 “ የውጭ ሊቃውንት . . . ሌላ ለየት ያለ የራሳቸው ሀሳብ ማመንጨት ችሎታ ያጡት ብዙ የኢትዮጵያ የታሪክ ምሁራን . . “
1ኛ ጽሁፍገጽ 24 “ አብዛኞች የአገራችን ታሪክ ምሁራን የውጭ አገር ምሁራን በመከተል የተሳሳተ አመለካከታቸውን . . .”
2ኛ ጽሁፍ ገጽ 6 “. . . የኢትዮጵያ ምሁራን ታሪክን የፖለቲካ ደንገጡር እንዳደረጓትን ምንስ ያህል የባዕዳን ቃል አስተጋቢዎች . . . “
ዶ/ር ላፒሶን (2ኛ ጽሁፍ ገጽ 11)” ፤ ዶ/ ር ነጋሶን(1ኛ ጽሁፍ ገጽ 40)፡ ዶ/ር አሰፋ ጃለታን(1ኛ ጽሁፍ ገጽ 7) ስም በመጥራት አንቋሸዋል፡፡
አበቃሁ
Damessa2013@gmail.com
