በጌዲዮ ዞን የብሄር ግጭት ዳግመኛ አገርሽቷል።

ሁኔታው እጅግ አሳሳቢ ደረጃ ደርሷል

የይድረሱልን ጥሪም ለመላው ኢትዮጵያውያን አስተላልፈዋል።

ዛሬ ግንቦት 16 2010 ዓ.ም በድረሰን መረጃ በጌዲዮ ዞን በዲላ ከተማ በተፈጠረ የብሄር ግጭት የአንድ ሰው ህይወት ማለፉን ያመልክታል በአሁኑ ስዓትም ከፍተኛ ውጥረት ነግሷል።

ከአንድ ዓመት በፍፊት በ2008 መስከረም ወር በ26-27 የደህዴን ካድሬዎች የጌዲዎ ዞን አመራሮች የፖሊስ ሃላፊዎችና አንዳንድ የአካባቢው ነውጠኛ ወጣቶች የሌላ ብሄረሰብ ተወላጆች ከዲላ ይውጡልን በሚል ሰበብ በፈፀሙት አሰቃቂ ጭፍጨፋ ከ125 በላይ መኖሪያ ቤቶችና የንግድ ተቋማት በቃጠሎ ወድመው ከ 50 በላይ ከሌላ አካባቢ የመጡ በጌዲዮ ዞን የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ንብረታቸው ወድሞና ተዘርፎ በአሰቃቂ ሁኔታ መጨፍጨፋቸው ይታወሳል፡

በዚህ ዘግናኝ ጭፍጨፋ የተሳተፉ የዞኑ ሃላፊዎች እና ካድሬዎች የጌዲዮ ብሄረሰብ የፖሊስ አባላት እና ሌሎችም ወጣቶች በቁጥጥር ስር ውለው የነበረ ሲሆን ምንም እንኳን የጥቃቱ ሰለባዎች የቪዲዮ የፎቶግራፍና የሰነድ ማስረጃ እንዲሁም የሰው ምስክር ለአቃቢ ህግ አቅርበው የነበረ ቢሆንም እነዚህ ወንጀለኞች የማዕረግና የስልጣን እድገት ተሰጧቸው ከአንድ ወር በፊት ያልፍርድ በነፃ መለቀቃቸው ታውቋል።

በዚህ የልብ ልብ የተሰማቸው እነዚህ ባለስልጣናትና ግለሰቦች የአካባቢውን ወጣቶች በማስተባበር ለሎች ብሄረሰቦች ከአካባቢያችን ለቀው ይውጡ በሚል ተመሳሳይ የጭፍጨፋ እንቅስቃሴ ጀምረዋል። በአካባቢውና በዲላ ከተማ የሚኖሩት እነኝህ ወገኖቻችን ይህንን ጥቃት የሚያስቆምላቸው አካልበመጥፋቱና በፍትህ ስርዓቱ ላይ ያላቸው እምነት በመሸርሸሩ በዚህ ሰሞን በንፍስ ወከፍ መሳሪያዎች እራሳቸውን ለመከላከል ቢሰባሰቡም ሙከራቸው ባለመሳካቱ ሱቆቻቸውን እንዲዘጉ በዛሬ ዕለት መገደዳቸውን ለማወቅ ተችሏል።

ይህ በንዲህ እንዳለ ነብሳቸውን ለማዳን በፈጠሩት ግብግብ የአካባቢው ተወላጅ የሆነ ወጣት በስለት ተወግቶ ህይወቱ ማለፉን ምNጫችን አረጋግጦልናል። የጌዲዮ ተወላጆች የሟቹን አስከሬን ገዳዮችን ሳንበቀል እና ከአካባቢው ሳናስወጣቸው የቀብር ስነ ስርዓት አንፈፅምም በማለት በከፍተኛ ሁኔታ ጦር መሳሪያዎችንና ነዳጅን መሰል ተቀጣጣይ መሳሪያዎችን በመያዝ በመንቀሳቀስ ላይ ሲሆኑ በዛሬው ዕለት ወደ ስፍራው የደረሱት የመከላከያ ሰራዊት አባላት የሞተር ሳይክሎች እንዳይንቀሳቀሱ ከማድረግ የዘለለ እርምጃ አለመውሰዳቸው ታውቋል። የጥቃቱ ሰለባዎች አዲሱ የዶ/ር አብይ መንግስት በአፋጣኝ እንዲደርስላቸውና የኢትዮጵያ ህዝብ ይህንን የተጋረጠባቸውን ከባድ አደጋ ለማስቆም ድምፅ እንዲሆንላቸው  ገልፀዋል።