ሰዎችን ከሲኖ ትራክ የገለበጠው አሽከርካሪ አልተያዘም

(BBC አማርኛ እንደዘገበው)

በፎገራ ሰዎችን የገለበጠው ሲኖትራክ

በፎገራ ወረዳ በሚገኘው የክርስቶስ ሰምራ ገዳም በየአመቱ ግንቦት አስራ ሁለት የክርስቶስ ሰምራ በዓል በድምቀት ይከበራል።

በዘንድሮው ክብረ በዓል አንድ የሲኖ ትራክ አሽከርካሪ በዓሉን ለመታደም ሄደው ወደ ቀያቸው ለመመለስ መኪናው ላይ የተሳፈሩ በርካታ ሰዎችን ሜዳ ላይ መገልበጡ ብዙዎችን በማህበራዊ ሚዲያ እያነጋገረ ይገኛል።

ሰዎች እንደ አሸዋና ጠጠር የመገልበጣቸው ጉዳይ የግርምት፣ የትዝብትና ቀልድ አዘል አስተያየትም አስተናግዷል።

በቀን ስራ የሚተዳደረው ጌታሰው የማታ የክርስቶስ ሰምራ ክብረ በዓል ላይ ከተገኙት አማኞች አንዱ ነው።

ባለፉት ዓመታት እንደነበረው ስለታቸውን ለማድረስ ሲሉ ለአማኞች ነፃ የመጓጓዣ አገልግሎት የሚሰጡ ሰዎች ከተገኙ እሰየው፤ ካልሆነ ግን አማኞች ተሰባስበው ወደ በዓሉ ስፍራ የሚወስዳቸው መኪና ይኮናተራሉ። ካልሆነም በእግር ይጓዛሉ።

“ወደ አካባቢው ለመድረስ መደበኛ መጓጓዣ የለም” የሚለው ጌታሰው በግምት አምስት ሰዓት ይፈጃል ያለውን መንገድ በተደጋጋሚ በእግሩ ተጉዟል።

ጌታሰው የዘንድሮውን በዓል የተካፈለው ከወረታ ከተማ ነፃ የመጓጓዣ አገልግሎት አግኝቶ ነበር።

መሄድ ብቻ ሳይሆን መመለስም አለና በዓሉ እንደተጠናቀቀ ወደ ቤታቸው ለመመለስ ከሌሎች አማኞች ጋር ሲኖ ትራክ ተሳፈሩ። ከተሳፋሪዎቹ መካከል ሴቶችና ህፃናትም ይገኙበታል።

ብዙዎቹ አሽከርካሪው የጫናቸው ስለቱን ለማድረስ እንደሆነ በማመን ጉዞ ይጀምራሉ። ብዙም ሳይርቁ ግን ገዳሙ አቅራቢያ የሚገኝ ሜዳ ላይ መኪናው ቆመ።

አሽከርካሪው ተሳፋሪዎች በሙሉ ሰላሳ ብር እንዲከፍሉ ይጠይቃል። ተሳፋሪዎቹ በበኩላቸው “በነፃ ነው የተሳፈርነው አንከፍልም” ሲሉ ይመልሱለታል።

የተሳፋሪዎቹ እምቢታ ያስቆጣው አሽከርካሪም “ካልሆነ እገለብጣችኋለሁ” ሲል ማስፈራራት ይጀምራል።

ነገሩ ያላማራቸው ተሳፋሪዎቹ “እንዳትገለብጠን፤ ከመኪናው እንወርዳለን ሲሉ” መጯጯህ ይጀምራሉ። የተወሰኑ ሰዎች ከመኪናው መዝለል ይጀምራሉ።

አሽከርካሪው ግን በድንገት አሸዋና ድንጋይ እንደሚገለብጠው ሰዎቹን ሜዳው ላይ ይዘረግፋቸዋል። ከመገልበጡ በፊት ከመኪናው የዘለሉ ሰዎች ቢኖሩም አብዛኞቹ ሰዎች ተገልብጠው መሬት ላይ በመውደቃቸው ጉዳት አጋጥሟቸዋል።

ጌታሰው እንደሚለው መኪናው የስለት ስለመሰላቸው ገንዘብ ለመክፈል ካለመፍቀዳቸው በላይ ገንዘብም አልነበራቸውም።

አሽከርካሪው በመኪናው ሙሉ የነበሩትን ሰዎች ሲገለብጥም ጉዳት ደርሶበታል።

በአማራ ክልል ለግዜው ቦተው ባልታዎቀ ስፍራ በተመሳሳይ መልኩ ሲኖ ትራክ ሰዎችን እንደ አሽዋ በመገልበጥ ጉዳት ሲያደርስባቸው የሚያሳይ ፎቶ

“ቀኝ እጄ አይሰራም። መንጋጋዬም ታሟል። የቁስለት መርፌ ሰጥተውኛል። ስራ መስራትም አልቻልኩም” ሲል ያለበትን ሁኔታ ይገልጻል።

በአሁን ወቅት ህክምና እየተከታተለ ሲሆን አሽከርካሪው ለፍርድ እንዲቀርብ በወረታ ከተማ ቀበሌ 4 ፖሊስ ጽህፈት ቤት አመልክቷል።

የአይን እማኙ እንደሚናገረው አሽከርካሪው የመኪናውን መገልበጫ እስከ መጨረሻው ከፍ አድርጎ ሰዎቹን አራግፏል።

ላለመውደቅ በመገልበጫው ጫፍ የተንጠላጠሉ ሰዎች ነበሩ። አንዳንዶቹ ደግሞ ከመኪናው ዘለው ወርደዋል።

በፎገራ ወረዳ የወረታ ከተማ አስተዳደር የሕዝብ ግንኙነትና ሚዲያ ባለሙያ አቶ ሀይሌ ብርሀኔ እንደሚሉት አሽከርካሪውና ተሳፋሪዎቹ ሂሳብ ክፈሉ በሚል እሰጣ ገባ ውስጥ ከገቡ በኋላ ነበር አሽከርካሪው ሰዎቹን የገለበጣቸው።

“ሰዎቹን ለማስፈራራት የተጠቀመበት መንገድ ነው። እድለኛ ሆነው ነው እንጂ እንዳደረገው ነገር ሰው ሊጎዳ ይችል ነበር” ይላሉ።

“የተወሰኑ ሰዎች ከመኪናው ዘለው ወርደዋል። የከፋ ጉዳት አልደረሰም። የፎገራ ወረዳ ፖሊስ ሰዎቹንና የመኪናውን ታርጋ ቁጥር እያጣራ ነው” ብለዋል።

መኪናው አሸዋ የሚጫንበት እንደሆነና አሽከርካሪውን በቁጥጥር ስር ለማዋል ሂደት ላይ መሆናቸውንም አክለዋል።

የፎገራ ወረዳ ፖሊስ ፅህፈት ቤትን ስለጉዳዩ ለመጠየቅ ያደረግነው ሙከራ አልተሳካም።