ለብዙ ጊዜ መልዕክቶቹን የምከታተልለት አፈንዲ ሙተቂ ዛሬ በፌስቡኩ የሌንጮ ለታ ጉዳይ በሚል የጻፈውን መልዕክቱን አንብቤ ይሄ ልጅ በረመዳን ምድር ምንነካው ነው ያልኩት፡፡ አፈንዲ ለብዙ ጊዜ ስከታተለው ከዘረኝነትና ከማንነት ጋር ያልተጣበቀ ፍትሀዊና አዝናኝ የሚባ መልዕክቶቹ ነው የማውቀው፡፡ ሰሞኑን ግን ትንሽ አልተመቸኝም፡፡ ስለ አብይ ሲጽፋቸው የነበሩ መልዕክቶቹ ትንሽ  ግር ቢለኝም ግን የተሰማውንና በትክክልም የመሰለውን የሚጽፍ ስለመሰለኝ እንደውም ከጥሩ ጎኑ ነበር ሳየው የነበረው፡፡አንዳንዶቻችን በራሳችን የምናምነበትንና የምናውቀውን ያህል ነውና የምንፈው፡፡ ብዙዎች ግን ለተቀጠሩበት ኣላማ የሚመች ሴራ እንጂ የሚያውቁትን መረጃና እውነቱን አደለም የሚጽፉት፡፡ አፈንዲን በብዙ ነገሩ እረዳዋለሁ፡፡ የምረዳው ደግሞ በእርግጥም ከቃላቶቹ በዘለቀ ብዙ የምንጋራቸው ነገሮች አሉ፡፡ ለብዙዎች የማይገባቸው ማለቴ ነው፡፡ ለብዙ የሚያስተላልፋቸው መልዕክቶች ብዙዎች በከፍተኛ አግራሞት የሚመለከቱት፡፡ እኔ ግን እንደዛ አደለም፡፡ እሱ ተጽኖ ያደረገበት(ለት) አስተዳደጉ እንጂ ራሴ ልሁን ብሎ አደልም ባይ ነኝ፡፡ ገለምሶ አዲጊያለሁ እያለ ምን አልባትም በቀድሞ ሥርዓቶች ትልልቅ ተሳትፎ ከነበራቸው ቤተሰብ ወጥቶና በኖረበት ዘመናትም በራሱ የሚያያቸው ነገሮች ብዙዎች ዛሬ በኦሮሞነት ያጡትን ማንነት እሱ ሳያጣው ማቆየቱ ይመስለኛል ሚስጢሩ፡፡ ሊያስመሰግነው የሚገባው ቢኖር የኖረባቸውን እውነቶች መጠበቁ ነው፡፡

አፈንዲ ኦነግ ሲገድልና ሲያረድ አላየ ይሆናል ቢያንስ ግን ብዙዎች ያዩትን አልፎም ግፉ በእነሱና በቤተሰቦቻቸው የተፈጸመባቸውን አልተፈጸመበችሁም ውሸትነው ማለቱ አፈንዲን ምን ነካው አስብሎኛል፡፡ ኦነግ አላረገውም ማለትም ይችላል ምን አልባት እሱ የሚያውቃቸው የኦነግ አባላት እንዲህ ሲፈጽሙ ካላየና አላማቸውንም አውቃለሁ ከአለ፡፡በበደኖ በአርባጉጉ በመሳሰሉት ግን የተፈጸመው ግፍ እውነት አደለም የውሸት ፕሮፓጋንዳ ነው ማለቱ ነው ምን ነካው ያሰኘኝ፡፡ ወተርንና አረካን እኔ በሰዎች መታረድ ከዚህ በፊት አልሰማኋቸውም፡፡ ብዙ ሌላ ሰው የማያውቀው እውነታ ደግሞ እኔ አውቃለሁ፡፡ አርባጉጉና በደኖንም ከሌሎች የሰማሁት እንጂ እኔ በአይኔ ያየሁት አደለም፡፡ በቅርብ ወያኔ አሰራጨው የተባለውን ፊልምም እኔ አላየሁትም፡፡ ለምንስ አየዋለሁ? የተሰራጨበትን ሴራ ሁሉ እያወቅሁ ታግሼስ እንደገነ በገዳዮች የተቀነባበርን ፊልም ማየት ያመኛል፡፡ የገለመሶዎቹ ኦነጎች ጥሩዎች ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ ኦነግ የተባለው ቡድን ግን በደረሰባቸው ብዙ ቦታዎች አላማ አድርጎ ሲፈጽም የነበረው ሰዎችን በማንነታቸው ማረድ እንደሆነ እናውቃለን፡፡ ወተር ላይ የታረዱት ኦሮሞዎች ናቸው ብሎናል አፈንዲ፡፡ ሊሆን ይችላል፡፡ ኦነግ እሱ አገር እገነጥላታለሁ ብሎ በተነሳበት ኦሮሚያ ብሎ ስም በአውጣለት ክልል ያሉ ብዙ ኦሮሞ ያልሆኑ ዜጎች ላይ ነበር አረመኔያዊ ጥቃቱ መሠረት ያደረገው፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ግን የኦነግን አረመኔያዊ ድርጊት በሚቃወሙ ኦሮሞ ተወላጆች ላይ ተመሳሳይ አረመኔያዊ ድርጊት ነው የፈጸመው፡፡ ወደ አርሲ ሐረርና ባሌ የመሳሰሉት አካባቢ ደግሞ ኦነግ  ኢላማ ያደረገው በአጠቃላይ ክርስቲያን የተባሉትን ነው፡፡ ብዙዎች ክርስቲያን ኦሮሞዎችም ሰለባ ሆነዋል፡፡  ለፕሮፓጋንዳ የተፈጠረ ወሬና ለፕሮፓጋንዳ የተደረገ በሰው ልጅ ላይ የተፈጸመ አረመኔያዊ ድርጊት ፍጹም የተለያዩ ናቸው፡፡ በወያኔው ማሰራጫ ጨምሮ ብዙ ኦነግ ፈጸማቸው የሚባሉ ለአይንና ጆሮ የሚሰቀጥጡ  አረመኔያዊ ድርጊቶች መፈጸማቸውን ግን መካድ አይቻልም፡፡ እንደተባለውም ወያኔ ለፕሮፓጋንዳዋ እንዲመቻት አንድ በእንድ ቀርጻ በአሳየችው ተጨባጭ በምስል የታገዘ መረጃ እንጂ እኮ በደሉ ደረሰብን በአሉ ሰዎች ብቻም ቃለ አደለም ብዙዎች እውነታውን ያወቁት፡፡

ለእኔ ወያኔና ኦነግ መቼም ቢሆን ተለያይተው አያውቁም፡፡ ማስተዋል ከቻልን እኮ እየተደረገ ያለው ድራማ ነው፡፡ ልብ በሉ በቀርብ ከስንት ዘመን በኋላ ማለቴ ነው ወያኔ ኦነግ ፈጸመው ብላ ያወጣችው ቪዲዮ (እኔ ሙሉውን አላየሁትም ግን አቀራረጹን አይቸለሁ) አኬልዳማ በትክክል ታስቦ በሰው ለጅ ላይ ያለርህራሄ በመፈጸም የተዘጋጀ ወደፊት ለልዩ ሴራ የተቀመጠ በጊዜውም ወያኔ ይጠቅመኛለ በአለው ጊዜ ያወጣው እንጂ እንደው ድርጊቱን እንዴት እንደሆነ ለመመርመር ፖሊሶች ወይም ወንጀል መርማሪዎች እንሚያያይዙት መረጃ አደለም፡፡ አዎ ዋናው ሴራ ነዳፊው ወያኔ ነበር ግን ኦነግ በዋና ተዋናይነት በገዳይነት የተሳተፈ መሪ ተዋናይ ነበር፡፡ ይህ ግን እንደሌላው ፊልም ሳይሆን በትክክል በሰው ልጅ ላይ አረመኔያዊ ድርጊት እየፈጸሙ የተነሳ ፊልም ነው፡፡ አፈንዲ የቱንም ያህል እሱ የሚያውቃቸው ኦነጎ ነን ያሉት ግለሰቦች ወይም ቡድን ምንም በደል እንዳልፈጸሙ ከሆነ የሚያውቀውም የታየውንና የተሰማውን ገሀዳዊ እውነት ግን ውሸት ነው ፕሮፓጋንዳ ነው ማለቱ እጅግ አሳዛኝ ነው፡፡ ኦነግ አልፈጸመውም ማለት ይችላል የሚያውቀውን መረጃ ያህል፡፡ ሰዎች ታረዱ የተባለው ውሸት ነው ማለት ግን  አፈንዲን መርቅኖ ነው  ሲነቃ መሳሳቱን ይረዳዋል ማለት ከብዶኛል፡፡

ኦነግን እኔ የማውቀው የወያኔ የቀኝ እጅ ሆኖ ሲሰራ የኖረ እስከአሁንም በብዙ ኦሮሞዎች ዘንድ ያለተነቃበት የኢትዮጵያ ጠላት እንደሆነ ነው፡፡ በዚህ እነዚህ ሁለት አረመኔ ቡድኖች ብዙ ጊዜ እርስ በእርስ ሲተሳሰቡ አይተናል፡፡ በሺዎች የሚቆጠር የኦሮሞ ልጅ በአልገባው ነገር ከኦነግ ጋር ተሳተፍክ ተብሎ የት እንደደረሰ እንኳን ሳይታወቅ ይሄው ዛሬ ላይ አለን፡፡ ከዚያም በኋላ ኦነግ ነግ እየተባለ ያለቀና ብዙ መከራን የተቀበለ ዜጋችን ቤቱ ይቁጠረው፡፡ ሌንጮ ለታን ጨምሮ የኦነግ ዋነኛ መሪዎች ግን ወደሚመቻቸው አገር በአውሮፕላን በቦሌ በኩል እንደተሸኙ አንረሳውም፡፡ ያም ብቻ አደልም ሌንጮ ለታ ለሁለተኛ ጊዜ አንድ ኦነግ ነህ ተብሎ የታሰረ ጓደኛቸውን ለማስለቀቅ በቀጥታ ከሚኖሩበት አገር አዲስ አበባ ገብተው በሶስት ቀን አስፈትተው መመለሳቸውን እናስታውሳለን፡፡ ይህን ያህል ምንም የማናስብ መሆን አልፈልግም፡፡ ዛሬ በእድሜም በትክክልም ሕሊናቸው ወቅሶአቸው በፊት ያደረኩት ልክ አደለም ብለው ለራሳቸው ንሰሀ ገብተው ከሆነ እኔ ችግር የለብኝም፡፡ እንኳን ሌንጮ ንስሀ ገብቷል ከተባለ ዋና የሴራው ነዳፊዎችም ሊያውም አሁንም በማን አለብኝነት እየኖሩ ነው፡፡ ዛሬም ድረስ ይሄው በሴራቸው ቀጠለዋል፡፡ በሠሩት ልክ ዋጋ እንዲቀበሉ የተቆረጠችው ቀን እስክትደርስ አይታወቃቸውምና፡፡ የፈርዖንና የኖህ ዘመን ሰዎችን ያስታውሱናል፡፡

አፈንዲ ሰሞኑን የሆነ ስሜት ውስጥ እንዳትሆን እሰገለሁ፡፡ በዚህ ደረጃ ባይሆንም አንዳንደ ሌሎች የታዘብኩት ጉዳዮችም አሉና፡፡ አንተው የምትረዳው ስለመሰለኝ እነሱን በመጥቀስ ማሳበቅ አልፈልግም፡፡ ምን ሆነህ ነው ወንድሜ? በነገራችን ላይ አቋምህን ልጋፋ አልወድም፡፡ እኔ ኦነግን ቀንደኛ የኢትዮጵያ ጠላት እንደሆነ አምናለሁ ከወያኔ ቀጥሎ ማለቴ ነው፡፡ ኦነግን አንተ በተቃራኒው መልካም አድርገህ መሳልህ የሚያጣላን አይመስለኝም፡፡ የአመንክበትና እስከምታውቀው ድረስ ከሆነ ማለት ነው፡፡ ከዚህ ውጭ በሆነ እውነታውን ደብቆ አይኔን ግንባር ያረገው ብሎ ለሆነ ሴራ ከሚወጡ ሀሳቦች በቀር ሰው ሁሉ በተረዳውና ከልብ በአመነበት ሁሉ ቢሆን እወዳለሁ፡፡ እየተቸገርን ያለንው ራሳቸውን ለጥቅም ባርነት አስገዝተው ጥቅምም ባያገኙ በሆነ የጥላቻ መንፈስ እውነቱን ገልብጠው መርዝ በሚነዙ ነው፡፡ ይመስለኛል አንተ ሙስሊምም ብትሆን ስለክርስትና ታውቃለህ ምን አልባትም መጻፈቅዱሱንም ታነባለህ፡፡ እኔ ብዙ ስለሙስሊም አውቃለሁ፡፡ ስለአገሬ እስልምና ማለቴ ነው፡፡ የአረቡን እስልምና ማለቴ አደልም፡፡ ብዙዎቻችን አስተዳደጋችን ለአንዳነዶች አግራሞትን በሚያጭር ሁኔታም ነው፡፡ ይህን ላቆየውና በእኛ የክርስቶስ ሐዋሪያ የሆነው ጳውሎስ ቀድሞ ክርስቶስን ተቃዋሚ ነበር፡፡ ይህ ሰው በትክክልም የሚያምነበትን ነበር የሚያደርገው፡፡ የሚቃወመውም ከልቡ ነበር፡፡ የአይሁድ ካህናት ግን ክርስቶስን የተቃወሙት ሳያውቁ ቀርተው ሳይሆን በመሆናቸው ተከታዮቻችንን ሁሉ ያጠፋብናል በሚልና የራሳቸው ሴራ እንዳይጋለጥባቸው ነበር፡፡ ጳውሎስ ግን እንደዚያ ከልቡ ስለተቃወመ በክርስቶስ ተመረጠ፡፡ የጳውሎስ ችግር እስነትን አለመረዳት ላይ እንጂ መዋሸት ወይም ሴራ ላይ አልነበረምና፡፡ በአመንበት መቆም ለሕሊናችን ነጽህና ከመርዳቱም በላይ እውነቱ ሲገለጥልንም እውነትን የመካድ ልምምድ አባዜ ስለሌለን ሳንቸገር እውነትን እንዋህዳታለን፡፡ በውዴታቸው የአወቁትን እውነት የሚክዱ ከምንም የከፉ ናቸው፡፡ ለማንኛውም አፈንዲ ሰው አልታረደም የውሸት ፕሮፓጋንዳ ነው ማለት የሚያስችልህ የአመንክበት እውነት እደሌለህ አይገባኝም፡፡ ምን አልባት ምን ለማለት ፈልገህ ይህን እንዳልክ አልገባኝ እንደሆነ እንጂ፡፡ ያ ደግሞ  ከሆነ ታብራራልናለህ ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ፡፡

አመሰግናለሁ!

ልዑል እግዚአብሔር ኢትዮጵያንና ልጆቿን ይባርክ! አሜን!

ሰርፀ ደስታ