ሙሉጌታ ገዛኸኝ)
gezahegn.mulu@yahoo.com

:ግርማዊነታቸው ቀ.ኃ.ሥ

የዚህ ፅሑፍ መሠረታዊ መነሻ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴን እስከዛሬ ድረስ ከሚወቀሱባቸው አስተዳደራዊ ነክ ግድፈቶች ገሽሽ አድርጎ የማሞካሸት ሽፋን መስጠት አይደለም፡፡ ከወገንተኝነት የፀዳ የታሪክ አተያይ ሚዛናዊነትንና ቅንነትን የጠበቀ ትንተና ላይ መመርኮዝ ነው፡፡ አጼ ኃይለ ሥላሴ የተገኙት ገና ከጎታች አስተሳሰብ ባልተላቀቅንበት አፍሪካ ቢሆንም ተራማጅ አስተሳሰብና የሞራል ልዕልናን የተላበሱ እንደነበሩ ፀሓፍት ይስማሙበታል፡፡ እንደዚህ ረጅም ዘመን ስልጣን ይዞ በፈላጭ ቆራጭነት አገር ያስተዳደሩት መሪ ይቅርና ቤተሰብን በማስተዳደር ረገድ እንኳ ክፉና በጎ መከሰቱ በማናቸውም ሁናቴ ከሁላችንም የተሰወረ ሊሆን አይችልም፡፡ ዛሬም ቢሆን የስልጣን እርካብ ላይ አንዴ ፊጥ ያሉ የአፍሪካ መሪዎችና ፓርቲያቸው ረጅም ዘመናት ቀጥቅጦ መግዛት ብሎም በምርጫ ሲሸነፉ ሕዝባቸውን ማሰቃየትና መግደል ልማድ ሆኖ በቀረበት አህጉር ማን ተወቃሽ ማንስ ወቃሽ ሊሆን ይችላል፡፡ ከዚህ ድባብ ወጣ ስንል ንጉሠ ነገሥቱ ስማቸው የሚታወስበት በሳል ዲፕሎማሲያዊ ችሎታ በዓለማቀፋዊና አህጉራዊ መድረኮች ያስገኙት ስኬት፤ ለአገር አንድነትና ነጻነት  ጠንካራ የውርስ አሻራ ምን እንደነበር መዳሰስ ነው፡፡

ከአምስት ዓመታት የስደት ዘመን በኋላ በድል አድራጊነት ወደ አገራቸው የተመለሱት ንጉሠ ነገሥት ዘ ኢትዮጵያ  በዙፋናቸው ተደላድለው የታሪክ ተወቃሽ ብቻ ለመሆን አልነበረም ፍላጎታቸው፡፡ በጠንካራ ኢትዮጵያዊ ማንነትና አንድነት ዳር ድንበሯ የታፈረ አገርን ማቆየት በጎነት እንጅ፡፡ የወደፊቷን አፍሪካ እጣ ፈንታ ለመወሰን፤ ከአፍሪካ አንድነት መስራች አባቶች ቀድመው ተሰልፈው የመሰረት ድንጋይ ያኖሩ ዘንድ የትውልድ ሃላፊነትን ፍጻሜ ለማድረስ ታሪክ ጠራቸው፡፡ ቀጥሎም የግዙፉ ስብዕናቸው አሻራው በፓን አፍሪካኒዝም እውን ሆነ፡፡

እርግጥ ነው እሳቸውም የታነፁበት ስብዕና መሰረቱ ፈር ቀዳጁ ዳግማዊ  ምኒልክ ቢሆኑም፡፡ ኃይለ ሥላሴ ለአፍሪካ አህጉር ውህደት ብሎም ለመላው ጥቁር ዘር ልዩ ተምሣሌት ናቸው፡፡ በተለይም በካሪቢያን እና በአሜሪካ ተቀስቅሶ የነበረው የኔግሮ ነጻነት ጠቅላላ ትግልና የኒውዮርክ ሐርለም ሬናይዛንስ ንቅናቄ አራማጆች እነ ማርክስ ጋርቬይ፣ ዊልያም ዲቦይዝ፣ ሲልቪስተር ሲልቫ እና ሌሎችም የጥቁር ብሔርተኞች ልዩ አክብሮት መስጠታቸው ተገቢ ነበር ፡፡ የራሥ ተፈሪያን እምነት መፈጠርና የነጻነት መሪ ሆነው መቆጠር ዛሬም ድረስ በጥቁሮች መብት ትግል ረገድ ይንፀባረቃል፡፡ ይህንን የተገነዘበው እውቁ የሬጌ አቀንቃኝ ሮበርት ኔስታል ማርሌ በሀገረ ጃማይካ የራሥ ተፈሪያንን ጎራ ተቀላቅሏል፡፡ እድሜ ልኩንም ኢትዮጵያን የጥቁሮች ተስፋይቱ ምድር፤  አጼ ኃይለ ሥላሴን ደግሞ የነጻነት መሪ ጥቁሩ ፈርጥ አድርጎ ተመስጧል፡፡ ቦብ በህይወቱ መገባደጃ ጊዜያት ገደማ ሲመኛት ወደነበረው የጥቁሮች ገነት ቅዱስ ስፍራ ኢትዮጵያ ብቅ ለማለት እድል አጋጥሞት በዚያውም ብርሐነ ሥላሴ የሚል የክርስትና ስም ቡራኬን ተቀበለ፡፡ የሬጌው ንጉስ ቦብ ማርሌ አድናቂወች በርካታ ኢትዮጵያውያን አሉ፡፡ ከሙዚቀኞች  ድምጻዊ ንዋይ ደበበ ውብ በሆነ ቅላጼው « ኃይለ ሥላሴ ፀሐይ ሐምሌ፤ ስሙ ሲጠራ በቦብ ማርሌ…» ማለቱ የቦብ ማርሌን ጥልቅ ቁርኝት በስንኙ ቋጭቶ ሰድሮታል፡፡ በልዩ የሙዚቃ ተስጥኦው የሚወደደው ወጣቱ ቴዲ አፍሮም የግርማዊነታቸውን ፓንአፍሪካኒስት እሳቤ ግሩም በሆነ ጥዑመ ዜማ እንዲህ ሲል ገልፆታል፡-« እነ ጆሞ ኬንያታ የኖራቸው ትልቅ ቦታ፤ ከተፈሪ መክረው ለካ፤ ተሞከረ ፓን አፍሪካ…» ከተፈሪ መክረው ለካ ይሰመርበት፡፡ ወቼ ጉድ!!! ይበል የሚያሰኝ ነው ቴዲ፡፡

አጼ ኃይለ ሥላሴ ለአፍሪካ ነጻነት ብሎም ለመላው ጥቁር ዘሮች ነጻ ሕዝብ እውቅና መረጋገጥ ፅኑ እምነትና አቋም ነበራቸው፡፡ በአንድ ወቅት በአሜሪካን አገር የጥቁሮች ሰብዓዊ መብት እውቅና በቅጡ ባላገኘበት ያ ዘመን ዋይት ሀውስ ቤተመንግስት ከወቅቱ ፕሬዝዳንት ጆን.ኦፍ ኬነዲ ጋር የክብር ግብዣ የተደረገላቸው ረቀቅ ያለ ዲፕሎማሲ  ችሎታ የተደነቁ የመጀመሪያው ጥቁር አፍሪካዊ መሪ ነበሩ፡፡ ከአገራቸው ጥቅም አስቀድመው የጥቁሮች መብት አያያዝ ሁናቴ ልዩ ትኩረት እንዲስብ ተወያይተዋል፤ ለቀጣዩ የአፍሪካ አህጉራዊ ትስስር ጥንካሬ ዋጋ  እንዲኖረው ለማስቻል ጭምር  እንጅ፡፡ ይህን ፅኑ አቋማቸው ተግባራዊ ውጤት ማስገኘቱ ሊካድ የማይችል ሀቅ ነው፡፡

የንጉሠ ነገሥቱ አለም ዓቀፋዊ የዲፕሎማሲያዊ ተጋድሎ ምን ይመስል ነበር? ብለን ስንጠይቅ የታሪክ ተመራማሪው ፕሮፌሰር ቴዎዶር ቬዝታል እንዲህ ገልፆታል፡፡ «…ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ በጄኔቭ ለመንግሥታቱ ማሕበር ሊግ ኦፍ ኔሽን ያደረጉት ታሪካዊ ንግግር በወቅቱ አጋር አልባዋ ኢትዮጵያ በብቸኝነት ድምጻቸውን ከፍ አድርገው የተከራከሩት ለአገራቸው ነጻነት እውን መሆን ብቻም ሳይሆን የአፍሪካን እጣ ፋንታ ጭምር ነበር፡፡» የተጫዎቱትን አህጉር ዓቀፍ ዲፕሎማሲያዊ ሚና  ከግምት ውስጥ በማስገባት ከእርሳቸው ቀጥሎ አገሪቱን እያስተዳደሩ የመጡ መሪዎች  የንጉሠ ነገሥቱን ጠንካራ ውርስ ዋጋ እንዲሰጡና በእርሳቸው የታሪክ አለም ዓቀፍ ጎዳና ለመራመድ ግድ ብሏቸዋል፡፡ ያለዚያማ የአሁኖቹ መሪዎች በአፍሪካም ሆነ በመላው ዓለም መድረክ ምን ይዘው፤ በምንስ መሰረት ይቅረቡ የቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴን አርቆ አሳቢና ፈር ቀዳጅነት፤ አገር የገነቡበትን ብልሀት ጠንቅቀው ካልጨበጡ በስተቀር ልቃቂቱ እንደጠፋበት ድር በከንቱ እንደሚባዝኑ የተገነዘቡት ይመስላል፡፡

ሌላው ሳይጠቀስ መታለፍ የሌለበት ጉዳይ በዚሁ የአፍሪካ አህጉር በደቡብ አፍሪካ ተንሰራፍቶ የነበረው የአፓርታይድ ወይም የዘር መድልኦ አገዛዝ  እና በቅኝ ገዛት ቀንበር ስር ለማቀቁት የፀረ-ኮሎኒያሊዝም ትግል ስኬት ብርታት ሆኗቸዋል፡፡ ቅኝ ግዛት እንዲያከትም ለፀረ-አፓርታይድ ትግሉ ያበረከቱት ዓይነተኛ ድጋፍ ሲሆን በተለይም ከአፍሪካ ናሽናል ኮንግሬስ (በምህፃረ ቃል ኤ.ኤን.ሲ) ቀንደኛ መሪዎች በተለይም ኔልሰን ማንዴላ በፖለቲካዊና ወታደራዊ ትጥቅ ትግል ስልጠና እንዲያገኝ መርዳታቸው መላው አፍሪካ በቅኝ ግዛት በሰባ ወይም ሰማንያ ዓመታት ብቻ እንዲቀጭ ያደረጉት ጥረት የአፍሪካ አባት እስከመባል የበቁ ስለመሆናቸው የምዕራቡ ዓለም ፀሓፍትም ይህንኑ ሀቅ አልሸሸጉም፡፡ በሚገባ ተመዝግቦም ይገኛል፡፡

ባረጀውና ባፈጀው የፊውዳላዊ ሥርዓት ወግ ያደጉት አጼ ኃይለ ሥላሴ እንዴትስ የተራማጅነት ስብዕና ሊላበሱ ተቻላቸው የሚል አድናቆት ሲያቀዳጁዋቸው በዓለም መድረክ ፊት በመሪነት ግርማ ሞገስ ያሳዩት ብቃት መሆኑ የተደመሙ ነጮችም በሰፊው ዘግበውታል፡፡

እ.ኤ.አ በጥቅምት ወር 1954 ዓ.ም ይፋ ጉብኝት ወደ እንግሊዟ ሎንዶን ከተማ ያቀኑት ንጉሠ ነገሥት  በወቅቱ የእንግሊዝ ልዑላን ቤተሰቦች፤ ንግሥቲቱ እና የኤድንብራው መስፍን በቪክቶሪያ አየር ማረፊያ የእንኳን ደህና መጡ ደማቅና ልዩ የክብር አቀባበል ተደርጎላቸዋል፡፡ ጎዳናዎችም ባልተለመደ ሁናቴ ስፍር ቁጥር በሌለው ሰው ተጨናንቀው ተስተውለዋል፡፡ ንግስቲቷ ዳግማዊት ኤልሳቤጥ ባደረጉት ንግግር እንዲህም ብለው ነበር፡፡ «ጃንሆይ ከጥንታዊና ሉዓላዊቷ…..መንግሥት ኢትዮጵያ እንኳን ደህና መጡ፡፡ ከእኛም ቤተክርስትያን ጋር ጠንካራ የሆነ መልካም ግንኙነት አላችሁ፡፡ ከሁለተኛው ዓለም አውዳሚ ጦርነት መገባደጃ የራሷን ነጻነትና ሉዓላዊነት ያስከበረች ብቸኛ አገር…» በማለት ንግግራቸውን ቀጠሉ፡፡ አጼ ኃይለ ሥላሴም በጉብኝታቸው የንግስቲቱን እናት ሰላምታ ለመለዋወጥ ከሎንዶን ከተማ ዌስት ሚኒስትር ምክር ቤት ተነስተው ወደ ክላሬንስ እና ዲግናቶሪስ መኖሪያ ቤኪንግሐም ቤተመንግስት አመሩ፡፡

በዚያው ዘመንም በአሜሪካ የሚታተመው ዝነኛው ታይም መጽሔት በፊትለፊት ገፁ ላይ አጼ ኃይለ ሥላሴን የምዕተ ዓመቱ ታላቅ ሰው በሚል አስተዋውቋቸዋል፡፡

የአገርን ዳር ድንበር አስከብረው የኖሩትን ንጉሠ ነገሥት ተገቢውን ክብር እንኳ ሳይሰጥ በሊቀ መንበሩ መንግሥቱ ኃይለ ማሪያም አማካኝነት ያወረደውና ያዋረደው ደርግ የስልጣን እርካብ ከተቆናጠጠ በኋላ እብሪተኛው የሶማሊያ መሪ ሠይድ ባሬ የቃጣብንን ወረራ እስከ አዋሽ ድረስ ዘለቆ ተቆጣጠረ፡፡ ይህንን ለመመከት የደርግ ጊዜያዊ ወታደራዊ አስተዳደር ምን ያህል አጣብቂኝ ውስጥ ገብቶ ማጣፊያው አጥሮት ላይ ታች ይል እንደነበር ማስታወስ በቂ ይመስለኛል፡፡ የአስተዳደር ጥበብ ከጉልበት ባሻገር  ወሳኝ መሆኑንም ከነአካቴው ግምት ውስጥ ያለማስገባት አላዋቂነት ነው፡፡ የአጼ ኃይለ ሥላሴን ውድቀት ምቹ አጋጣሚ ሲጠባበቅ የነበረው ጎረቤት የሶማሊያ ሪፐብሊክ ሠርግና ምላሽ ሆነለት፡፡ ለአፍታም ሳይቆይ ወረራውን ተገበረው፡፡

ንጉሠ ነገሥቱ በብልሀት የሉዓላዊት አገር ዳር ድንበርን እንዴት እንዳስከበሩ ከግብዞቹ ደርጎች በተሻለ ወራሪ ሀይላትም ጠንቅቀው ያውቁ ነበር፡፡ ደርጎች አገር ማስተዳደር ማለት አገር የተቋቋመበትን ዋልታ መሰረት ማወቅ መሆኑን በቅጡ ያልተገነዘቡና ብስለት ያልነበራቸው የደርግ መስራቾች ከበታችነት ስሜት ከመነጬ አስተሳሰብ የፀዱ አልነበሩም፡፡ የተጠናወታቸው አባዜ ያልተላቀቁ የደርጉ አባላትየወርሃዊ ምንዳ ማነስ ጥያቄ አጀንዳ  ያልዘለለ ሲሆን ስልጣን ከሰፊው ሕዝብ አብዮት ነጥቀው አገሪቱን በአስቸጋሪ ሁናቴ ህልውናዋን አደጋ ላይ ጣሉት፡፡ እስከ ዛሬ ድረስም በርካታ ፖለቲካዊ ውጥንቅጥ ውስጥ ተገባ፡፡ እንግዲህ የወታደራዊው ደርግ ጁንታ ውርስ  የአገር አንድነት በወታደራዊ ሀይል ብቻ የሚፈታ መስሎት በተሳሳተ ግልብ ርዕዮተ ዓለም አካሄድ ለዘመናት ፀንቶ የኖውን አገራዊ አንድነት ከመናድ አፋፍ አድርሶት በመጨረሻም አምባገነኑ መንግስቱ ኃይለማርያም በግርግር እጁ የገባውን ስልጣን ጥሎ እብስ ለማለት ተገደደ፡፡

አህጉራዊው የአፍሪካ አንድነት ድርጅት ወደ አፍሪካ ህብረትነት ከተቀየረ ማግስት መስራች አባቶችን በተለይም የጋናው መሪ ክዋሚ ንክሩማህ ሐውልት እንዲቆምላቸውና እንዲዘከሩ ሲደረግ አጼ ኃይለ ሥላሴን ማስቀረት ማለት ከአንዳች እኩይ ጥላቻ የመነጨ ካልሆነ በስተቀር ሌላ ምን ሊሆን ይችላል፡፡ ይህንን እውነተኛ የታሪክ ፀሓፍትም ሆኑ ቀጣዩ ትውልድ ይፈርዱታል፡፡ በታሪክ ሽሚያ ጡዘት የሰከሩት የአሁኖቹ መሪዎች ለንጉሠ ነገሥቱ ዘመን የማይሽረው ጠንካራ ኢትዮጵያዊ አንድነትና አፍሪካዊ ማንነት መሰረት መጣል አስተዋፅዖ ክብር መንፈጋቸው ትዝብት ላይ የሚጥላቸው ለመሆኑ ፈፅሞ አያጠራጥርም፡፡ በአንድ አጋጣሚ በቶጎ ዋና ከተማ ሎሜ በተካሄደው የአፍሪካ አንድነት ድርጅት(አ.አ.ድ) ላይ የቀድሞው የሊቢያ ጁማሀሪያ ሶሻሊስት ሪፐብሊክ መሪ ሙአመር ጋዳፊ የአህጉራዊው ድርጅት ዋና መቀመጫ በአዲስ አበባ ሆኖ መቀጠል አይችልም የሚል የሰላ ሙግት ባነሱበት ወቅት ጮሌው ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ጋዳፊን የረታበት መላ ታዲያ ብልጭ ያለው የንጉሠ ነገሥት ኃይለ ሥላሴን ጉልህ ሚና ታሪክ ያስከነዳ ማስረጃ አጣቅሶ ማቅረቡ ብቻ እንደሚያዋጣ ጠንቅቆ ስለተገነዘበ የነበረው እድል የታሪክ ተወቃሽ ላለመሆን በእሳቸው መጀን ተማፅኖ ሽንጠ ገትር እሰጥ አገባ ሲነገታገት ተስተውሏል፡፡ እንግዲህ ከዚህ የከፋ አህጉራዊና ሌላም ተግዳሮት አጋጥሞ ቢሆን ኖሮ ደግሞ በርካታ እውነታን ማጣቀስ የማይቀር መሆኑን ፍንትው ያደረገ አጋጣሚ ነበር፡፡

በመጨረሻም የዚህ ፅሑፉ ማሳረግያ ይሆን ዘንድ አጼ ኃይለ ሥላሴ የዳግማዊ ምኒልክ ሐውልት ሲመረቅ ያደረጉት ንግግር እዚያው በሐውልቱ ላይ ተቀርፆ ይገኛል፡፡ እንዲህም ይላል፡- «ከትልቅ ወይም ከትንሽ መወለድ ቁምነገር አይደለም፡፡ ራስን ለትልቅ ታሪክ መውለድ እንጅ፡፡» ፍላጎት ያለው ማናቸውም ግለሰብ ጠጋ ብሎ ፅሁፉን በቅርበት መመልከት ይችላል፡፡ ለዛሬው በዚህ እንደምድም፡፡ ቸር ይግጠመን!!!