ፀጋዝአብ ለምለም ተስፋይ የኢኮኖሚክስ መምህርና ጸሓፊ
(ሸክም የበዛበት ትውልድ፡ 2009 እና የምሥራቃዊት ኮከብ፡ 2010 መጻሕፍት አዘጋጅ)
በአለም የሰው ልጅ የረዥም ጊዜ ታሪክ ውስጥ የራሱ የጽሕፈት ቋንቋ – ቋንቋውን በጽሑፍ ማቅረብ የቻለ ሕዝብ ሥልጡን ይባላል፡፡ በዚህም የተነሣ ሀገራችን ቀደምት የሥልጣኔ መነሻና መዳረሻ አሻራ ካላቸው ሀገራት ጎራ እንድትቀላቀል አስችሏታል፡፡ ከብዙ ሃብቶቿና ቅርሶቿ መሐከልም የጽሑፍ ሃብቶቿና ቅርሶቿ በጉልህ ይጠቀሳሉ፡፡
ብዙ በቁጥር የታወቁና በቁጥር ያልተገለጹ ሀብቶች እንደነበሩና እንዳሉን በብዙ ምሁራን የተገለጸ አንዱ የማንነታችን መገለጫና መለያ በመኾኑ ብዙ ከተባለልን የአደባባይ መታያዎቻችን በመለስ ያሉትን ጓዳዊ ማንነቶቻችንን ከድምዳሜ አንጻር ሳይኾን ለተሻለ የውይይት መነሻ ሀሳብ ይኾኑንን ዘንድ በተጠይቃዊ አመክንዮዎች እንመረምራቸው ዘንድ ይህ ጽሑፍ ተዘጋጀ፡፡
ከላይ በመግቢያው ላይ እንደተገለጸው ሀገራችን ቀዳሚ የሥልጣኔ መለኪያ ከኾነው የጽሑፍ ባለቤትነት በመነሣት ራሳችንን ስንገልጽ ቆይተናል፡፡ ሌሎችም እኛን ይገልጹናል፡፡ ኾኖም ብዙ ከተባለለትና ብዙ ሊባልለት ከሚገባው ከዚህ ታላቅ ሀብታችን ባሻገር ያልታዩ መሠረታዊ ሀሳቦች መኖራቸውን ግን ማስተዋል ይገባል፡፡
ለአብነት፡- ለአላስፈላጊ ትርጉምና እሰጣ ገባ በሚዳርገን መልኩ ሳይኾን በቀናነት ሊያወያየን፣ ሊያመካክረንና ሊያማምረን በሚችል መንገድ ነገሩን ስንመረምር – እውነት ነው! የጽሑፍ ሀብትና ቅርሶች ባለቤት ነን፡፡ እውነት ነው! ይህ እውነተኛ የማንነታችን መገለጫ ነው፡፡ እውነት ነው! ይህ ልንኮራበትና ልናስተዋውቀው የሚገባ ታላቅ ቁም ነገር ነው፡፡ ኾኖም ግን በተገቢው መልኩ በስፋትና በጥልቀትም ሊመረመርና ሊጠና የሚገባውም ትልቅ ርዕሰ ጉዳይ ነው፡፡
ዕውነቱ (Truth) ና እውነታው (Reality) እንደተጠበቀ ኾኖ የኢትዮጵያ ሕዝብ እንደሕዝብ የጽሑፍ ባለቤት ቢኾንም ከጽሑፍ ቋንቋን – ለመጻፍ፣ ለማንበብ፣ ለማስተላለፍ፣ ለማሠልጠን – – – ፋይዳ ያለው ታላቅ ሀብት ቢኾንም እንኳንስ ከዘመናት በፊት ዛሬ አብዛኛው የኢትዮጵያ ሕዝብ እንደሕዝብ በብዙ ሚሊዮን የሚቆጠሩ ዜጎች ማንበብና መጻፍ አይችሉም፡፡ የጽሑፍ ባለቤት የኾነ ሕዝብ እንደምን የባለቤትነት ማረጋገጫ የኾነውንና የባለቤትነት ግብ የኾነውን የተጠቃሚነት ትሩፋት ተቋዳሽ ሳይኾን ቀረ? (ልብ እንበል! ሕዝብ እንደሕዝብ)
ባለቤትነት ምንድነው? የባለቤትነት መለኪያው ምን ይመስላል? ሕዝባዊ ባለቤትነት የሚባልስ አለ? በምንስ ይገለጻል? የሚሉ ትላልቅ ማዕቀፋዊ ጽንሰ ሀሳቦችን ለጊዜው በጥያቄ እንኳ አስቀምጠን ብናልፍ ለዘመናት የተሻገረ የጽሑፍ ሥልጣኔ ነበረንና አለን ብንልም በአንጻሩ ሕዝብ እንደሕዝብ ለዘመናት የተሻገረ መጻፍና ማንበብ ያለመቻል ማንነት እንዴት ሊኖራቸው ቻለ? አንድ ሰው የቤት ባለቤት ኾነ ማለት ቤቱን የመጠቀም መብት አለው ማለት አይደለምን? ባለቤትነትና ተጠቃሚነት እንዴት ሊነጣጠሉ ይችላሉ? የሚሉ ጥያቄዎች ግን የማይታለፉ ይኾናሉ፡፡
ይህ በንዲህ እንዳለ ጥቂቶች በቤተ መንግሥት፣ በአስተዳደርና በቤተ ዕምነቶች አካባቢ የነበሩ መጻፍና ማንበብ እየቻሉ ብዙዎች ግን ማንበብና መጻፍ ሳይችሉ እጅግ ለረዥም ዘመናት በመቆየታቸው የተቆጨ፣ ያነባና የተንቀሳቀሰ ትውልድ የትኛው ነው? እርግጥ ነው! መሐይምነትና ድንቁርናን በ1960ዎቹ ኹለንተናዊ የሀገራችን እንቅስቃሴዎች ተነሥቷል፡፡ እርግጥ ነው! ይህ ከተነሣ ገና ከግማሽ ክፍለ ዘመን እንኳ እንዳልሞላው እናስተውላለን፡፡ ባለቤት ከኾንበት እስከዚህ እንቅስቃሴ ድረስ የጽሑፍ ኹለንተናዊ ማዕቀፍ ከጥቂቶች ወደ አብዝሃ ሳይተላለፍ እንደምን ሊቆይ ቻለ? የእነዛ ጥቂቶች ማንበብና መጻፍ ተጠቃሚነት ቅናትና ተነሣሽነትስ እንደምን ወደ ታች ሳይወርድ ቀረ?
ሳይወርድስ በጥቂቶች ቻይነትና ተጠቃሚነት እንደምን አብዝሃዎች በባለቤትነት ሊጠሩበት ቻሉ? ጥቂቶችስ ስለምን ከራሳቸው እንዲያልፍ እነሱ ያገኙትን ኹለንተናዊ ተጠቃሚነት ለሌላው ወገናቸው ማስተላለፍ ሳይችሉ ቀሩ? ይህንንስ ወደ አብዝሃ የንቃት ደረጃ ለማስፋት ቻይናውያን እንደሚጠቅሱት ዘመን ተሻጋሪ መምህራቸው ኮንፍሽየስ – እንደህንዳውያን ዘመን ተሻጋሪ መምህራቸው ቡድሃ – ዘመን ተሻጋሪ ኢትዮጵያዊ መምህር መጥቀስ እንደምን አቃተን? ሥልጣኔያችንስ እነዚህ በተጠቀሱበት አውድ የሚጠቀስ አሳቢስ እንደምን ማፍራት ተሳነው?
ከዚሀ ጋር ተያይዞ – “የቀደሙ አባቶቻችን ያልጻፉበት ርዕሰ ጉዳይ የለም!” እንላለን፡፡ ከመንፈሳዊ መጻሕፍት አንሥቶ እስከ ፍልስፍና፤ ከሥነ ተፈጥሮ እስከ ህክምናዊ ጥበቦች፤ ከአስተዳደር እስከ ታሪክ፤ ከሥነ ጥበብ እስከ ተግባር፤ ከኪነ ጥበብ እስከ ግኝቶች የተሻገረ፤ ከአለም እስከ ዓለማት ለማየት የሚያስችል፤ ከግለሰብ እስከ የዓለም ኹኔታ፤ ከሚታየው ብቻ ሳይኾን ስለማይታዩ ረቂቅ ነገሮች፤ ካለፉ ነገሮች እስከ የሚመጡና ሊከሰቱ ስለሚችሉ ነገሮች፤ ከራስ ባሻገር የሌሎችን ተርጉሞ እስከ ማቅረብ ድረስ የደረሰ፤ ከንጽጸር እስከ አጣጥሞ እስከ ማስቀመጥ የደረሱ ብዙ እልፍ አላፍ ጽሑፎች ተጽፈዋል፡፡ እንዲያውም ይህ ሀብታችንና ቅርሳችን በተለያዩ መንገዶች ተዘርፏል:: በመዘረፍ ላይም ይገኛልም – እንላለን፡፡
አባቶቻችንና እናቶቻችን ስለብዙ ነገር ጽፈዋል፡፡ አስቀምጠዋልም ብለን ትንሹም – ትልቁም ያነሣል፡፡ እውነት ነው! ከዚህ በአደባባይ ከሚገለጸው ነገር የተለየ እውነት ሊኖር የሚችልበት እድል ጠባብ ነው፡፡ ነገር ግን ወደ ጓዳ ስንገባ ብዙ ጥያቄዎች እንዲነሡ ያደርጋል፡፡
“ስለፍልስፍና የተጻፉ ብዙ መጻሕፍቶች አሉን እንላለን፡፡” ከዚያ ፍልስፍናውን ከዕሳቤ፣ ከአስተምህሮትና ከአኗኗር ዘይቤ አንጻር ለይታችሁ አስቀምጡ ስንባል ብዙዎች መልስ የለንም፡፡ እስኪ በአለም እንደሚታወቁት ፈላስፋዎችና ፍልስፍናዎች ስም ጠቅሳችሁ፤ ዘመን አጣቅሳችሁ፤ ዕሳቤ አነጻጽራችሁ፤ አስተምህሮት አበጀታችሁ፤ አሳዩን ስንባል ብዙዎች መልስ የለንም፡፡
ሃብቱና ቅርሱ እንዳለን – ብዙ እንላለን፡፡ መኖሩን ሌላው በሚገባው መልኩ ግለጹ ስንባል መልስ የለንም፡፡ ሃብቱን፡- አንድ ቻይናዊ፣ ጀርመናዊ፣ ካናዳዊ፣ ሩሲያዊ፣ የመናዊ፣ ህንዳዊ፣ ሱዳናዊ፣ ሜክሲኳዊ አልያም ቬተናማዊ በሚገባው መልኩ ማስቀመጥ አልቻልንም፡፡ የጽሑፍ ቋንቋ ባለቤት ነን እንዳልነው – አንድ ሰው ብድግ አድርጎ አንሥቶ በቀላሉ ሊረዳው በሚችል ተሰንዶ የተዘጋጀ የኛ ፍልስፍና የምንለው የለንም፡፡
ለአብነት፡- የሕንዳውያንን ፍልስፍና አልያም የቻይናውያን ፍልስፍና ዘመኑ በሚረዳው መንገድ በማስቀመጣቸው ያለማንም እርዳታ በቀላሉ ከጽሑፍ ሀብታቸው አንብበን በመረዳት እነሱ ፍልስፍናቸው ይህ ነው! እንዲህ ያምናሉ! ይህን የሚያደርጉት ከዚህ የተነሣ ነው! ይህን ዕሳቤና አስተምህሮት ያራመደው እከሌ ነው! ከእከሌ በዚህ ይመሳሰላል – በዚህ ደሞ ይለያል! ከዚህ ዘመን እሰከዚህ ዘመን ድረስ! ማለት በምንችልበት ደረጃ እናገኛለን፡፡ እኛ ግን አለን እንላለን – በዚህ ደረጃ ግን ብዙዎች መግለጽ አልቻልንም፡፡ አንችልም፡፡
በተመሳሳይ በሌሎች ሀብቶቻችን ላይም በተወሰነ መልኩ በመንፈሳዊ ዕሳቤዎችና አስተምህሮቶቻችን ላይ በአንጻራዊ (Relatively) መልኩ ይሻል እንደኾነ እንጂ ከዚህ የተለየ እንዳልኾነ ኹለንተናዊ ታሪካችንም ኾነ አኗኗራችን ዐቢይ ምስክር ነው፡፡
ይህም እንኳ ኾኖ ሳለ እስካሁን ድረስ ይህ በመኾኑ እንቅልፍ የሚያጣ፣ ትርጉም ባለው መንገድ የሚያነባ፣ ቀን ከለሊት በእንባና በቁጭት የሚሰራ ትውልድ እስከ ዛሬ አለመፈጠሩ ምክንያቱ ምን ይኾን? ሀብት አለኝ! ቅርስ አለኝ! ብሎ እልፍ አላፍ እየዘረዘሩ – ዘመኑን በዋጀ መንገድ ማንም በትጋት ሊረዳውና ሊገነዘበው በሚችል መንገድ አለመቀመጡ ምክንያቱ ምን ይኾን?
ባለቤትነት ያለተጠቃሚነትስ ምን ፋይዳ አለው? የጽሑፍ ቋንቋ ባለቤትነት በራሱ መሣሪያ (means) እንጂ በራሱ ግብ (Goal) እንዴት ሊኾን ይችላል? መጻፍም ኾነ ማጻፍስ ቢኾን እንደምን መሣሪያ (means) እንጂ በራሱ ግብ (Goal) እንዴት ሊኾን ይችላል?
ለምሳሌ፡- እጅግ በርካታ ዘመናትን ያስቆጠሩ በርካታ መንፈሳዊ መጻሕፍቶች አሉን፡፡ የነዚህ መጻሕፍቶች ዓላማ ከትልቁ የሰው ልጅ ከተፈጠረበት ዓላማና ሊኖርበት ከሚገባ ዓላማ በታች እንጂ ፈጽሞ በላይ ሊኾን አይችልም፡፡ ስለኾነም የተጻፉት ለሰው ልጅ የሕይወት ሂደት ኹለንተናዊ ተጠቃሚነት መሣሪያ (means) ይኾን ዘንድ ግድ የሚል ይኾናል፡፡
በመኾኑም እነዚህ መጻሕፍቶች ከጥቂቶች ወደ አብዝሃ አለመተላለፋቸው – በጥቂቶች መሪነትና አንባቢነት ወደ አብዝሃ የሚወርድና የሚዳረስ የተጠቃሚነት መገለጫ ቢኖራቸውም የጥቂቶችን ያክል አብዝሃዎች ቢያውቋቸው ይበልጥ የመጻሕፍቶቹ ዓላማ ከቀደመው ይልቅ ይበልጥ የተሳካ ያደርገዋል፡፡ ካልኾነ ክስረት መኾኑ አይቀሬ ነው፡፡
ክስረቱም ሊገኝ የሚችለውን ኹለንተናዊ የመጽሐፉን ጠቀሜታ ካለማግኘት በዘለለ በማግኘት ሊገኙ የሚችሉ ኹለንተናዊ የተሳሳሪነት (Multidimesional Interconnected) ውጤቶችና ኹለንተናዊ የርቢ መስተጋብሮችንም (Multidimesional Relationships) የሚያሳጣ መኾኑን በንድፈ ሀሳብም ኾነ በተግባር ደረጃ መረዳት እጅግ ቀላል ነው፡፡
በዚህ መንገድ እኛ ኢትዮጵያውያን ብዙ እጅግ በጣም ብዙ ቃላት ከሚገልጹት በላይ ብዙ ኹለንተናዊ ነገሮችን አጥተናል፡፡ በማጣት ላይም እንገኛለን፡፡ ያለፈውን እንኳ ብንተው ዛሬ ይህ ማጣት እንዴት ብሔራዊና ሕዝባዊ ቁጭትና መነሣሣትን ሳይፈጥርብን ቀረ? ለዘመናት እንደነበርነው ዛሬም አለን አይደል?
ሥልጡን ነበርን እንላለን እንጂ ሥልጡን ነን አንልም፤ ታሪክ ተሰርቷል እንጂ ታሪክ እንሰራለን አንልም፤ አለን እንጂ ያለንን ዘመኑን በዋጀ መልኩ መግለጽ አልቻልንም፤ ያለንን እንኳ እንዲህ እናምናለን! ለዚህ እንታመናለን! ፍልስፍናችን ይህ ነው! የዚህ መገለጫው ዕሳቤና አስተምህሮታችንም ይህን ይመስላል! ብለን ከኹለንተናዊ አኗኗራችን ጋር አስተሳስረን መግለጽ አልቻልንም፡፡
በአደባባይ እንዳለን ማንነት ጓዳችን የዛ ማንነት ተጠቃሚ እንደምን መኾን አልቻለም? ዕውን በዚህ ዐውድ መሠልጠናችን ከወዴት አለ? ይህስ ሳይኖር እንደምን የሥልጡንነት ባሕሪያትና ጠባያት ሊኖሩን ይችላሉ? ፈጣሪ ሀገራችን ነጻ ፍቃድን የኹሉ ነገር ማዕከል ወደ ሚያደርግ የዕሳቤ ሂደት ትገባ ዘንድ ይርዳን!
ቸር እንሰንብት!
