በመጀመሪያ ቃል ነበር! ….ውይይትም፣ክርክርም፣መጽሓፍም ፣ ግጥምም ፣ድርሰትም፣ዜማና ሙዚቃ፣ራዲዮና ቴሌቭዥን፣ ጋዜጣም፣ፊልምም ሥዕልም …መሠረታቸው ቃል ነው፡፡ መናገር ደግሞ አምላክ በተፈጥሮ ለሰው ልጆች ሁሉ የሰጠው መብቱ ነው፡፡
እንደ 21 ኛው ክፍለ ዘመን ለአይዲሎጂ – ለርዕዮተ ዓለም አመቺ ያልሆነ ዘመን የለም፡፡ ይህ ደግሞ ጥሩ ነው፡፡አሁን በየአለበት ርዕዮተ-ዓለሞች ተከታዮች አጥተው ደርቀው ሞተዋል፡፡አንዳንዶቹ የሞቶቱም ፣ ብዙዎቹ እንደሚገምቱት፣ የበርሊን ግንብ የፈረሰበት ቀን አይደለም፡፡ከዚያ ቀደም ብሎ ነው፡፡ በትክክል ለመናገር ዮሴፍ ስታሊን ሞቶ የተቀበረበት ቀን ነው፡፡አሸናፊ ሁነው የወጡት አመለካከቶች ደግሞ ሁለት ናቸው፡- ዲሞክራሲና እና ቅዱስ ጳውሎስ- በትክክል እንደ አለው- እምነት፣ተስፋ እና እንዲሁም ፍቅር ናቸው፡፡ ከሁሉም የሚበልጠው ደግሞ – የእሱን ቃል እንደገና ለመናገር „ጥላቻ „ ሳይሆን ፍቅር ነው፡፡በጥላቻ ላይ የተመሠረተ ፖለቲካ ለማራመድ ብዙ ጥረት ተደርጎ እሱም ከሽፎአል፡፡
ግን ደግሞ አንድ ሌላ አስቸጋሪ ነገር አለ፡፡ እሱም፡- እንኳን የሰው ልጆችን እነዚያን በስለት እና በጥይት ጥዋት ማታ ሊተናነቁ የሚፈላለጉትን ሰይጣኖችን እና አጋንንቶችን አንድ አድርጎ የሚያስማማቸው ነገር እሱ ምንድነው! ከጥያቄዎች ሁሉ ትልቁ ጥያቄ ደግሞ ይህ ነው!! ምንድነው አገሪቱን ኢትዮጵያን፣በዚያውም ሕዝቡን መልሶ አንድ የሚያደርግ ነገር፡፡
መናገር እንዲያውም እንቁ ነው….
ይህ ጥያቄ የተነሳው ከብዙ መቶ አመታት በፊት ነው፡፡ በጥቂት ፈላስፋዎች ዘንድ ተመልሶ ጥያቄው እንደገና የተወረወረው የዛሬ ሁለት መቶ አመት ገደማ ነው፡፡ እንደ አመጣጡ ከተለያዩ ፈላስፋዎች ለጥያቄውም መልስ የተሰጠው ደግሞ እንደዚሁ በተለያዩ ጊዜያት ነው፡፡ ጥያቄው አሁንም በዚህ በያዝነው ዘመን እንደገና እንደ አዲስ ነገር ተነስቶአል፡፡
ትውልዱ ይህን ነገር በየጊዜው አንስቶ ከአልመረመረው ትርጉሙ ይረሳና የክርክር አርዕስት ይሆናል፡፡ ይህ ደግሞ እጅግ በጣም ጥሩ አጋጣሚ ነው!
ነጻነት ምንድነው! ዲሞክራሲስ የሚባለው ነገር ለእኛ ለኢትዮጵያኖች ዛሬ ምናችን ነው!
ነጻነት እና ዲሞክራሲ፣…የሰበአዊና የዲሞክራቲክ መብቶች መከበር፣….የዲሞክራሲ አየር መተንፈስ፣ የዕለታዊ ጋዜጣዎች ብዛት የራዲዮና የቴለቭዥን ጣቢያዎች ጋጋታ፣…በመቶና በሁለት መቶ የሚቆጠሩ መጽሔቶችና በሚሊዮን የሚቆጠሩ መጻሕፍቶች .. እነዚህ ሁሉ ለአንድ ኢትዮጵያዊ ምንድናቸው!
መልሱ አጭር ነው፡፡ ስለ የኑሮ ሁኔታችን ጥሩ ሥዕል እና በቂ መልስ የሚሰጡም እጹብ ድንቅ ነገሮች ናቸው፡፡ ይህም ሲባል እንዲያው ለቀልድ አይደለም፡፡ በዓይን የሚታዩ በእጅ የሚዳሰሱ ተጨባጭ ነገሮች ናቸው፡፡ጥያቄው አሉ ወይስ የሉም ነው፡፡
„…ዲሞክራሲና ነጻነት ምንድናቸው!“ የሚለውን ጥያቄን ለአንድ አውሮፓዊ ብንወርውርለት፣ ከእሱ አፍ የምንሰማቸው መልሶች ከአፍሪካዊው ወንድማችን አስተያየት ይለያል፡፡አረቦችን ብንጠይቃቸው እነሱ የሚሰጡን መልሶች፣እጅግ ያስደንቅን ይሆናል፡፡ስለ ነጻነት ምንም የማያውቀው የቻይናው ተወላጅ ደግሞ የሚሰነዝራቸው አስተያየቶች፣ምናልባት ያስደንግጠን ወይም „…ደስ የሰኘን“ ይሆናል ፡፡ ሰሜን ኮሪያን ግን እንደ አለ እንርሳት! ኪዩባንም ለጊዜው እዚያው እንተዋት፡፡
አንድ የጠለቀ ዕውቀት ያለውን አስተማሪ ግን ብንጠይቅ እሱ ከሰበሰበው ጥበቡ ለማካፈል፣ብዙ ቦታ-እርግጠኛ ነኝ- ይወስደናል፡፡ ይህ ሰው ረጋ ብሎ ስለ ፈረንሣይና ስለ አሜሪካን አብዮት ያነሳልን ይሆናል፡፡ ስለ ሮማውያን ሕጎች፣ስለ እንግሊዞች ማግና ካርታም፣ስለ ዝነኛው ግሎሪየስ አብዮት ቆየት ብሎም ሳይተቅስ አያልፍም፡፡ጊዜ ከአለን ደግሞ – አንድ በአንድ ተጉዞ ስለ ጥንታዊ ግሪኮችም ዲሞክረሲ፣ አብሮ አያይዞም -በቀላሉ ዲሞክራሲን እንድንረዳው ያጫውተን ይሆናል፡፡
ግን ስለ „ዲሞክራሲ“ በኢትዮጵያ ሲነሳ ዘለው አሁን በያዝነው 21ኛው ክፍለ -ዘመን ስለ „…አብዮታዊ ዲሞክራሲ“ የሚተነትኑልን ሰዎች ጥቂት አይደሉም፡፡ ስለ „አዲሱ ዲሞክራሲ“ እና ስለ ሌላው ማንነቱ ስለማይታወቀው ስለ አንድ„…ልማታዊ ዲሞክራሲ…“ ስለ ሚባለውም ነገር፣ ማብራሪያ ለመስጠት ዝግጁ የሆኑ ስዎች እጅግ ብዙ ናቸው፡፡
ዲሞክራሲ ምንድነው! ነጻነትስ!
ለአንዳንዱ የአገሪቱ ሊህቃን „…ዲሞክራሲ“ ማለት – በእነሱ እምነት- ሌላ ነገር ሳይሆን„…ብሔራዊ ዲሞክራሲ…“ ነው፡፡ለሌላው ሳይጨነቅ ጉዳዩ “ …ሶሻል ዲሞክረሲ ..“ ነው፡፡ እንደገና ለሌሎቹ ዲሞክራሲ“ የአታላዮች ጨዋታ“ ነው፡፡ይህም ሲባል፣ያንን ሲሉ እና ያልሆነበ ቦታ ትንተና ሲያቀርቡ ብዙ ጊዜ ተሰምቶአል፡፡ ሴሚናርም ዲስኩሩም እዚያም እዚህም – እንደ ትልቅ ቁም ነገር፣ ሲሰጥበት ከርሞአል፡፡
ሌሎች ደግሞ -ለማስረዳት- እሩቅ ቦታ ሄደወ እውነተኛ „ዲሞክራሲ ለሁሉም“ የሚመጣው „…በኮሙኒስት ሥርዓት ሥር ብቻ ነው..“ የሚለውን የማሳመኛ መንገድ ሲመርጡልን፣ እነሱንም በ20ኛው ክፍለ ዘመን አዳምጠናል፡፡ ነገሩ አይቀርም ጠብቁ! ይመጣላችኋል ለማለት ነው፡፡
ሕይወት ግን አጭር ናት!
„የቡርጃ ዲሞክራሲ..“ ተብሎም በምላሰኛ ካድሬዎች „የምዕራቡ ሥርዓት“ – የተረሳውን እንደገና ለማስታወስ- ተጥላልቶ በእነሱ ዘንድ ውድቅ ተደርጎአል፡፡እሱንም ዝም ብለን ተቀብለን እንደ አልሰማን አሳልፈነዋል፡፡
በደንብ ሳንመረምረውና በሥነ – ሥርዓቱ አጣጥመንም አንዱንም „…ትምህርት“ ሳንውጠው ደግሞ አንደኛው ዘሎ “…የእኔን ሓሳብ ብቻ ተቀበል ባትቀበል ዋ! ባሩድ ታሸታለህ…“ ብሎ አሸብሮአል፡፡ እነዚህን ሁሉ „ትንተናዎች“ በላይ በላዩ በሕዝቡ ላይ ሲለቀቁ ደግሞ እንደ ተለመደው ሰው ሁሉ አንገቱን ደፍቶ እንደ አመጣጡ ሰምቶ እንደ አልሰማ ዝም ብሎ ተቀብሎታል፡፡
በአንድ ዘመን አንዱ ወገን ተነስቶ „…ዲሞክረሲ በገደብ…“ እያለ እንደ ፈለገውና እንደ አመቸው፣ፎክሮና ቀለሙን አፍሶ ሰውን ግራ አጋብቶል፡፡ „…ዲሞክራሲ አለገደብ „ ተብሎም መልስ ተሰጥቶበታል፡፡እሱንም „…ጊዜ ያመጣውን ጊዜ ይወስደዋል“ በሚለው ፍልስፍና ጸጥ ለጥ ብሎ ሰው ሁሉ ዛሬ ያለንበት ሁኔታ ውስጥ ገብተናል፡፡
„…የጭቁን ሕዝብ ዲሞክራሲ …“ የሚሉ ሰዎች በአገሪቱ ብቅ ብለዋል፡፡ከዚያም ከእነአካቴው „…የላብ አደሩና የገበሬው አምባገነን መንግሥት „ የሚባል ትልቅ ነገር አለ ተብሎ በአገሪቱ አስተሳሰቡ እንዲነግሥ ተደርጎአል፡፡ይህንንም በዘመኑ የነበሩት ድርጅቶች በበተኑት ፕሮግራማቸውም ላይ „ጥሩ አድርገው“ – ታሪክ ነውና- ስለ አስቀምጡት መመልከቱ አይከፋም፡፡
ከዚህ ሁሉ የውዥብር ዘመን በኋላ ደግሞ አሁን አንድ የቆየና የሰነበተ አንድ „ትልቅ“ ፍልስፍና – እነሱ እንደሚሉት እንደ „….አዲስ ትምህርት“ በአገሪቱ ላይ ለቀዋል፡፡ „…ከሌሎቹ ሕዝቦች በፊት“ አንዳዶቹ እንደአሉት „ኢትዮጵያ ውስጥ ከጥንት ጀምሮ የተዘረጋ አንድ ልዩ ዲሞክራሲ“ አለ፡፡እሱም- እንደተሰማው- „….የገ!ዳ ሥርዓትና የገ!ዳ ዲሞክራሲ!! ነው፡፡“ እሱን የሚያዋጣ ስለሆነ „ እንከተለው „ የሚሉ አመለካከቶች እዚያም እዚህም ብቅ ብቅ ማለት ጀምረዋል፡፡
ለመሆኑ ገ!ዳ! …ምንድነው!
የገዳ ዲሞክራሲስ ምን ይመስላል! ሁለቱ ሥርዓቶች „ …ሰበአዊና ዲሞክረሲ መብቶች የተጠበቁበትና የተከበሩበት የዲሞክረሲ ሥርዓት“ እና „ የገ!ዳ ዲሞክራሲ„ የእነዚህ ፣ የሁለቱ ሥርዓቶች አንድነትና ልዩነታቸው ምንድነው!
እንደገና ደግሞ አሁን በቅርቡ „…አብዮታዊ ዲሞክረሲ እየተሸረሸረ ነው!….አብዮታዊ ዲሞክረሲን ማዳን ማለት ኢትዮጵያን ማዳን ማለት ነው…“ የሚል ጥሪም በኢትዮጵያ ውስጥ ተበትኖአል፡፡ ለመሆኑ „….አብዮታዊ ዲሞክረሲ“ ምንድነው! ኢትዮጵያን „ማዳንና“ ጸሓፊዎቹ የሚሉትን„…አብዮታዊ ዲሞክራሲን“ ምን ያገናኛቸዋል! ለመሆኑ „…አብዮታዊ ዲሞክራሲ“ ሕዝቡ የሚያምንበት „ሃይማኖት ነው“ ወይስ ማንም ሰው የማያውቀው አዲስ ልዩ „ርዕዮተ -ዓለም“ ነው ! ሁለቱ „ሥርዓቶችስ“ እንዴት አድርገው ነው „…የዜጎቻቸውን መብት“ የሚያስከብሩት! …አስክብረውም እነሱ የሚንቀሳቀሱት!
ለመሆኑ „…ገ!ዳ! እና አብዮታዊ – ልማታዊ ዲሞክረሲ“ ምንድናቸው!…እነሱስ ስለ „ፕሬስ ነጻነት“ ምን ይላሉ!…ስለ „ሴቶች መብትስ“ ምን ያጫውታሉ! …ስለ „ነጻ-ምርጫስ በአንድ አገር ውስጥ“ ምን ያስተምራሉ ! ስለ „ፓርላማ ዲሞክራሲስ ያላቸው አቋም“ ምን ይመስላል!
ለእነዚህና ከዚህ ጋር ተያይዘው ለሚነሱት ጥያቄዎች ሁሉ፣ አንባቢው መልሱን የሚያገኘው ከጽሑፉ አናት፣ ከመጀመሪያው ገጽ ላይ ሳይሆን፣መልሱ ያለው ከጽሑፉ የመጨረሻ ገጽ ላይ ነው፡፡እኔም ይህቺን „ዲሞክራሲ“ የምትባለውን ነገር ከብዙ በጥቂቱ፣ምን እንደሆነች በአጭሩ ለማብራራት ጥረት አደርጋለሁ፡፡ ነገሩ „…እንደ ሻሪያ ሕግና እንደ ወንጀለኛ መቅጫ ሕግ ዓይነት ነው ! አንደኛው ከሌላው ጋር በምንም ዓይነት አብሮ አይሄድም፡፡
„ልዩነታቸውና አንድነታቸው“ የገ!ዳ! ዲሞክረሲ እና….እኔ የማነሳው ዲሞክራሲ፣ወይም አሁን „አደጋ“ ላይ ወድቆአል የሚባልለት„…አብዮታዊ ዲሞክረሲ“ በደንብ ለያይተን፣ ሰንጥቀን ብልት አውጥተን ከአላየናቸው „ግራ“ የሚያጋባ ነው፡፡ከዲሞክራሲ ጋር አብረው ስማቸው ተጠቅሶ በድንገት ስለተነሳ ዕውነትም „..ግራ ያጋባል“ !!!
የኢትዮጵያ ትራጀዲ-እዚህ ላይ ግልጽ እንሁን- መድረኩ ላይ እስከ አሁን ድረስ ብቅ ብሎ የቆዩበት ምክንያትም በአንድ ምክንያት ነው፡፡ „ …አንዴ እንደ ቧልት፣አንዴ ጊዜ ደግሞ“ እንደሚባለው „ በፌዝ መልክ፣ሌላ ጊዜ ደስ ሲለው ይኸው ነገር ተመልሶ “…በለቅሶ እና በሓዘን መልክ“ ተፈራርቀው ኢትዮጵያን የመቱዋት – በዚሁ መሠረታዊ በሆነ „በዲሞክረሲ ጥያቄ „ ዙሪያ ግልጽ የሆነ አመለካከት በአገሪቱ ምሁራን ዘንድ በአለመኖሩ ነው፡፡
በዕውነትም ትልቁ ችግራችን ይህ ነው!
ከጥቂት አመታት በፊት-ለማስታወስ- ሦስት ድርጅቶች በድል አድራጉነት አዲስ አበባን ተቆጣጥረው አንድ ነገር አድርገዋል፡፡ „ነጻነት ወይስ ባርነት“ በሚል ጥሪ ኤርትራ ከኢትጵያ እንድትገነጠል ተደርጎአል፡፡ብዙ ንግግሮች፣ብዙ ጽሑፎች፣ፊልምና ፎቶግራፎችም ወጥተዋል፡፡ ውጤቱ ግን – ተመልካቾች እንደአሉት-ሕዝቡ እንደተመኘው „ ነጻነት“ ሳይሆን ባርነት ነው፡፡በሺህና በአሥር ሺህ መንደራቸውን ለቀው በየጊዜው ለስደት የሚወጡት፣በሽሽት ባሕር ገብተው ሕይወታቸው የሚጠፋው ወጣቶች ቁጥር እንደ ማሥረጃ – ተመልካቾቹ ይጠቅሳሉ፡፡
ልጅ እንዳልካቸው መኮንን ጠቅላይ ሚኒስትር ሲሆኑ ይህ የዲሞክራሲ ጥያቄ ተነስቶአል፡፡በኋላም ልጅ ሚካኤል እምሩ እንደዚሁ ጠቅላይ ሚኒስትር ሲባሉ ጥያቄው ተመልሶ ተወርዉሮአል፡፡እንደገና ደርግ የሚባለው ፍጡር ሥልጣኑን ሲጨብጥ ይኸው ጥያቄ ተነስቶ መልስ ሳያገኝ ተዘሎ ታልፎአል፡፡ከአሥራ ሰባት አመት የወታደር ምንግሥት በኋላ ሕዝባዊ ወያኔ ፣ሻቢያና ኦነግ አዲስ አበባን ሲቆጣጠሩ እንደገና ሁለት አረፍተ ነገሮች ተወርዉረዋል፡- „ነጻነትና ባርነት“ እንዲሁም „አብዮታዊ ዲሞክራሲ“ ተብሎአል፡፡አሁን ደግሞ ይህ እስከ ዛሬ ድረስ መልስ ያላገኘው „የዲሞክራሲ ጥያቄ“ በጠቅላይ ሚኒስትር አቢይ ዘመን ተመልሶ የአጀንዳው አናት ላይ ተቀምጦአል፡፡
ዲሞክራሲ ምንድነው! ነጻነትስ!… ሰበአዊ መብት ለአንድ ኢትዮጵያዊ ምኑ ነው!
ዓይንን ጨርሶ የማይከፍተው ፣የአገሪቱ ምሁራን እሰከ ዛሬ ድረስ ጨብጠውት አንለቀውም ብለው የያዙት „…የፖለቲካ ፍልስፍና እና የፖለቲካ ቲዎሪ „ -የሚሰማ ቢኖር- በሌላ „ግልጽ በሆነ ትምህርት“ ሳይውል ሳያድር በአስቸኳይ መተካት አለበት፡፡
ግን በየትኛው ፍልስፍና ፣ በየትኛው ትክክለኛ ትምህርት!
ለመሆኑ ዲሞክራሲ ምንድነው!! ዲሞክራቲክ ሥርዓትስ የሚባለው ነገር በተጨባጭ ምን ይመስላል!
ይልማ ኃይለ ሚካኤል
በርሊን 2018 ዓ.ም. እ.አ.አ.
ይህ ጽሑፍ ግልጽ ደብዳቤ ነው፡፡
በመጀመሪያ ታስቦ የነበረው ጉዳዩ በቀጥታ ለሚለከታቸው ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ነበር፡፡ ግን ብዙ ደብዳቤ ከሁሉም አቅጣጫ እንደደረሳቸው መገመት ይቻላል፡፡ ከታሪካችን እንደምናውቀው አንድ ጠቅላይ ሚኒስትር ብቻውን ምንም ነገር ሊያደርግ አይችልም፡፡ስለዚህ ይህ „ደብዳቤው“ አንዱን ከአንዱ ሳይለይ ፊደል ለቆጠረው ለአገሪቱ ምሁራን ሁሉ የተጻፈ ነው፡፡ እንደምነውቀው የአገሪቱ ምሁራን በየአለበት በተለያዩ ስሞችና በተለያዩ ፕሮግራሞች፣እርስ በእራሳቸውም በሚቃረኑ ዓላማዎች ሥር ወገን ለይተው እዚያና እዚህ ተሰበጣጥረው ሲታገሉ፣ሲፎካከሩ ይታያል፡፡ እነሱ ናቸው የአገሪቱ ችግር ፈቺ ፡፡ እነሱም ናቸው የአገሪቱ ችግር ሁሉ ፈጣሪ፡፡ የችግሩም አካል እነሱ ናቸው፡፡ስለዚህ ጥያቄው የተነሳው ለሁሉም ነው፡፡ የአውሮፓ ሥልጣኔ -በመጨረሻ ላይ ለማንሳት የተመሠረተው፣ በአንድ ቡድን ዕውቀትና፣በእሱም ትምህርትና ጥበብ ላይ ብቻ አይደለም፡፡ወደፊት እንደምናየው፣በሓሳቦች መፋጨት እና በምርምር ላይ ነው!
ይቀጥላል!
