አርብ፤ ግንቦት ፲ ፯ ቀን ፳ ፻ ፲ ዓመተ ምህረት ( 5/25/2018 )

( ሆኖም፤ በጉልበት ለያዙት በትረ ሥልጣን እንጂ፤ ለሚጽፉት ታሪክ፤ የእውነታው ባለቤትነት የላቸውም። )

ታሪክ ሲጻፍ፤ የነበረውን መተረኩ፤ በሁለት መንገድ ይኬድበታል። አንደኛው የነበረውን እንዳለ ማቅረብ ነው። ሌላው ደግሞ፤ ላደረጉት ተግባር ማረጋገጫና ማስመከሪያ ለማድረግ፤ የተግባሩን ትክክለኝነት ለማስረገጥ፤ ወደሚፈልጉት አቅጣጫ አንጋዶ ማቅረብ ነው። ይህ ሁለተኛው ሂደት፤ ራስን ለማሞካሸትና ሌሎችን ለማንቋሸሽ፤ ያልነበሩትን ነበሩ፤ የነበሩትን ደግሞ ፈጥሞ አልነበሩም! ማለትን ያስከትላል። አቸናፊዎች ሲጽፉት፤ የሚደረገው፤ ያቸነፉበትን ሁኔታ ሕጋዊነትና ትክክለኝነት ማጎናጸፍ ነው። የቅርቡን ክስተትም ሆነ የሩቁን ታሪክ፤ ለተግባራቸው ማስደገፊያ ከሚሆንበት አንጻር ስለሚከትቡት፤ ለእውነቱ ሳይሆን፤ ለተግባራቸው ትክክለኛነት ነው አምልኮታቸው። ለዚህ ነው የትግሬዎቹ ነፃ አውጪ ግንባር አባላት፤ የትግላቸውን ሂደት፣ ያደረጉትን ግፍና በደል፤ ከርስ በርስ ከመባላት እስከ ዐማራውን ለይቶ በዘሩ መጨረስ ድረስ፤ ምክንያት ለማቅረብና ከሌለ ለመፍጠር፤ የራሳቸውን ምሁራን በታሪካችን ላይ ያዘመቱብን።

ለዚህ ጽሑፌ መነሻ የሆነኝ፤ እኔ ራሴ ስለዋልኩበት የሸረላ ጦርነት፤ በመጽሐፍ አትመው ያወጡትን፤ አንድ ወዳጄ አንብቦ፤ እንዲህ . . . ይባላል፤ ያለኝ ጉዳይ ነው። በርግጥ እኒህ ፀረ-ኢትዮጵያ ትግሬዎች፤ በኢትዮጵያ ሕዝብ ላይ ገዥነታቸው ተቀባይነት እንዲያገኝ፤ ባንድ በኩል ታሪክ ሠሪዎቹ እነሱ፤ ባጠቃላይ የሀገራችን ታሪክ በሙሉ በነሱ የተመራና የነሱ ብቻ ጀግንነት እንደሆነ ማቅረብ ስላለባቸው፤ ታሪክ በአፄ ዮሐንስ እና በትግራይ የበላይነት ይሽከረከርና፤ ከሳቸው በፊት የነበሩት አፄ ቴዎድሮስም ሆኑ ከሳቸው በኋላ የመጡት ዳግማዊ ሚኒሊክ፤ ያለቦታቸው የተገኙ ትክክለኛ ያልሆኑ ንጉሦች ሆነው ቀርበዋል። አልፎም ዐማራና ፀረ-ሕዝብ ተብለው ተፈርጀው፤ በትምህርት ገበታና በፖለቲካ ስሌት ተስለዋል።

ያ ብቻ አይደለም። ሕጋዊ የሆነ የኢትዮጵያ ገዥ ለመሆን፤ የግድ የራሳቸውን ኢትዮጵያ መጠፍጠፍ ነበረባቸው። ያንን ነው ያደረጉት። እስከዛሬ የነበረውን ሁሉ የዐማራ ነው፤ ትክክል አይደለም ብለው ፈረጁ። ስህተት አለና እናስተካክል ከተባለ፤ ስህተቱን አስተካክሎ በነበረው ኢትዮጵያዊነት መጓዝ፤ ሊመጣ ነው። ያን አድርገው ቢሄዱ፤ እነሱ የጥቅሉ አንድ አካል እንጂ፤ ብቸኛ የበላይ አካል ሊሆኑ አይችሉም። ስለዚህ የግድ የአጀንዳው ባለቤት ቀራጭና ተቆጣጣሪ መሆን የማይችሉበት ሀቅ ሊገዛቸው ሆነ። እናም የነበረው በሙሉ ትክክል አይደለም! ተብሎ ተፈረጀ። እኛ አዲስ ኢትዮጵያ ልንፈጥር የምንችለው፤ አዲስ የኅብረተሰብ አሰላለፍ ስንፈጥር ነው! የሚል ውሳኔ ላይ ደረሱ። እናማ ኢትዮጵያ የኢትዮጵያዊያን ሳትሆን፤ የብሔሮችና ብሔረሰቦች ሀገር ናት! አሉ። ይህ እንግዲህ፤ የነበረውን ኢትዮጵያዊነት በሙሉ ሰርዞ፤ ብሔርና ብሔረሰቦችን ማዕከል ያደረገ የፖለቲካ ስሌት ወደ መድረኩ አቀረበ። ለዚህ ሁሉ በቀዳሚነት እንቅፋት የሚሆንባችው ኢትዮጵያዊ ነኝ የሚለው ዐማራው ስለሆነ፤ ዐማራውን ለይቶ ማጥቃት፤ ቀድሞም ዓላማቸው ነበር፤ ቀጥለው ግን፤ በመላ ኢትዮጵያ፤ እነሱ በሚያዙዋቸው ተባባሪዎቻቸው ሁሉ መመሪያ ሆነ። በነገራችን ላይ አሁንም ዐማራውን ማጥቃቱ እንደቀጠለ ነው።

ይህ ስሌታቸው፤ የነበረውን ታሪክ መለወጥ ፈቀደላቸው። ሀገሪቱ የብሔሮችና ብሔረሰቦች ከሆነች፤ የነዚህን የቀድሞ ታሪክ መፍጠርና ያንን የሀገራችን ታሪክ ብለው ማቅረብ አለባቸው። ያ ካልሆነ፤ የነበረው የሀገራችን ሀቅ፤ በየሂደታቸው ብልት ሥር ሁሉ ብቅ እያለ፤ ሕጋዊ ሰውነታቸውን ይሸረሽረዋል። ለዚህ ነው፤ የቀድሞ ነገሥታት ዐማራ ተብለው መብጠልጠል የተያዙት!

ወደ አሁኑ ታሪክ ስንመለስ፤ ታሪካቸውን ስጽፉ፤ መሪዎቹን የሚቃወመውም አስገደ፤ ገሃዲን ስልጽፍና ሌሎችም የ“ታሪክ ሊቆቻቸው!” የ“ኢትዮጵያን ታሪክ!” ሲጽፉ፤ ትግሬዎችንና ኢትዮጵያዊያንን፤ እኛ ትግሬዎች እና እነሱ ጠላቶቻችን፤ የሚል የተለያዩ ሁለት ክፍሎች አስቀምጠው ነው። እናም ትግሬዎች ሲዋጉ ጀግኖች፤ ሌሎች ደግሞ፤ ኢድህም ሆነ ኢሕአፓ፤ ማለትም ኢትዮጵያዊ ነን የሚሉት፤ ፈሪዎችና ፈርጣጮች ሆነው ተስለዋል። ትግሬዎች የተዋጉት፤ ኢትዮጵያዊያንን ነው። በዚህ ውጊያ ደግሞ፤ ትግሬዎች “ጀግኖች!” ናቸው። ጠላቶቻቸው ኢትዮጵያዊያን ደግሞ “ፈሪዎች!” ናቸው። ትግሬዎቹ አቸናፊ ሆነው የወጡት፤ ቆራጥና ጀግና የወርቅ ልጆች ስለሆኑ ነው። ይህ ነው እንግዲህ ለታሪክ ጸሐፊዎቻቸው መፈንጫ ወለሉ። ይህ ሂደት፤ ለትግራይ ጥቅም ሁሉ ነገር እንዲውል መንገድ ጠረገ። እናም ሁሉ ነገር፤ ከሌሎች የኢትዮጵያ ክልሎች እየተዘረፈ፤ ለትግራይ ሆነ። ከዐማራው ክልል ማንኛውም ሀብት እየተመጠመጠና እየተጋጠ፤ ወደ ትግራይ ተጓዘ። ይህ ደግሞ እንደ አንድ የሀገራችን ክልል ሳይሆን፤ በሀገር ደረጃ በሚመጥን፤ ሁለት የተለያዩ ሀገሮች በሆነ እሳቤ ተካሄደ። የሱዳን መንግሥት መቀሌ ተስተናግዷል። ሌሎችም በሀገር ደረጃ መስተናገድ ያለባቸው ጉዳዮች፤ መቀሌ ተስተናግደዋል። የሀገራችን ወታደራዊ ማዕከል ትግራይ ሆኗል። ደብረዘይት ሳይሆን፤ ትግራይ ነው የአየር ኃይሉ ዋና ክፍል ያለው። የማንኛውም መንግሥታዊ አካል ማዕከልና ባለቤት፤ ንብረትና መሪ ክፍል፤ ትግሬዎችና የትግራይ ክልል ነው። የባቡር ሐዲድ የሚዘረጋው ትግራይን ብቻ ባተኮረ ሁኔታ ነው። ይሄን ሁሉ ከኔ የበለጠ ሀገር ቤት የሚኖረው ኢትዮጵያዊ ታውቁታላችሁ።

በወልቃይት ሸረላ ላይ፤ ከ፴ ፰ ሰላሳ ስምንት ዓመት በፊት የተደረገው ጦርነት እንዲህ ነው። አንድ መቶ ሃምሳ የሆንነው የኢሕአሠ አባላት፤ ከሁለት ሺህ በላይ የሆነውን የትግሬዎች ነፃ አውጪ ግንባር ጦር፤ ለሁለት ቀን ከተዋጋን በኋላ፤ ከኛ አንድም ጓድ ሳይጎድልብን፤ በርግጥ ከኔ ጭምር አስራ ሰባት ቆስለናል፤ አቸንፎ ቦታውን የሚቆጣጠር ሳይኖር፤ ሁለታችንም ወደ ኋላችን አፈገፈግን። በዚህ ሁኔታ የተጠናቀቀን ጦርነት፤ ከነሱ ሰማንያ ዘጠኝ ተጋዳላይ የሸረላ አርሶ አደር፤ አካባቢው በመግማቱ ሰው በመሆን ተቆርቁሮ ቀብሮ፤ ባቸናፊነት ራሳቸውን መሳላቸውን ስረዳ፤ በሕይወት እያለሁ! አይደረግም! ባይ ነኝ። አንድ ሴት መሪያቸው መውደቋንና ታላቅ ጀግና እንደነበረች አሁንም እያከበሯት ነው። መልካም፤ ያን ማመናቸው ራሱ መንገድ ይከፍታል። ራሴ ቆስያለሁ ስል፤ ከኛ በኩል የነበረውን ማመኔ ነው። ለኔ በዚህ ሂሳብ፤ ምን የማይጽፉት ይኖራል! ለነገሩ ከነሱ ድሮም አልጠብቅም! የነሱን መጽሐፍት የሚያነብ ግን፤ ሀቅን ማግኘት አይችልም። ይሄን ልብ ያለው ይረዳ! ይህ የኔ የሀቅ ምስክርነት ነው።