May 26, 2018
(ዘ-ሐበሻ) 35ኛው የኢትዮጵያውያን የስፖርትና የባህል ፌስቲቫል በቴክሳስ ግዛት ዳላስ ከተማ ከጁላይ አንድ እስከ ጁላይ 7 ቀን 2018 ይደረጋል:: በዚህ ታሪካዊው ዝግጅት ላይ በቅርቡ የጠቅላይ ሚኒስተርነቱን ቦታ የያዙት ዶ/ር ዓብይ አህመድ በ እንግድነት ለመገኘት ጥያቄ ማቅረባቸውን የቅርብ ምንጮች ለዘ-ሐበሻ አረጋግጠዋል::
ሰበር ዜናውን በቪዲዮ ለማየት እዚህ ይጫኑ
በተጨማሪም ዶ/ር ዓብይ አህመድ በአውሮፓው የኢትዮጵያ ስፖርት ፌዴሬሽንም ተመሳሳይ ጥያቄ ማቅረባቸውም ታውቋል::
ዶ/ር ዓብይ አህመድ በዳላሱ የኢትዮጵያ ስፖርት ፌስቲቫል ላይ በተለይም አርብ ቀን በሚከበረው የኢትዮጵያ ቀን ላይ በመገኘት ንግግር ለማድረግ ጥያቄ ያቀረቡ ሲሆን ፌዴሬሽኑ ውሳኔ ለመስጠት የፊታችን ሰኞ አስቸኳይ ስብሰባ እንደጠራ ምንጮቻችን ገልጸውልናል::
ፌዴሬሽኑ ከወዲሁ በኢትዮጵያ ያለው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ እንዲነሳና እስረኞች እንዲለቀቁ ቅድመ ሁኔታ ማስቀመጡን የሚገልጹት እነዚሁ ምንጮች የፊታችን ሰኞ የጠቅላይ ሚኒስተሩን ጥያቄ ይቀበለው አይቀበለው ይወሰንበታል ተብሏል::
የዘንድሮው የኢትዮጵያ ስፖርትና የባህል ፌስቲቫል የክብር እንግዳ ጋዜጠኛና የሰብ አዊ መብት ተሟጋች ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ መሆኑ ይታወቃል::
በተመሳሳይ ዶ/ር ዓብይ አህመድ በጀርመን ስቱትጋርት ከተማ በሚደረገው የኢትዮጵያውያን የባህልና የስፖርት ፌስቲቫል ላይም ጥያቄ ያቀረቡ ሲሆን የአውሮፓው ፌዴሬሽን ጠቅላይ ሚኒስትሩ ያቀረቡትን ጥያቄ የሚወስነው የአሜሪካውን ፌዴሬሽን ውሳኔ ካወቀ በኋላ እንደሆነ ታውቋል:: እንደ ምንጮቻችን ዘገባ የአሜሪካው ፌዴሬሽን የዶ/ር ዓብይን ጥያቄ ከተቀበለው የአውሮፓውም ይቀበለዋል::
የአሜሪካው ፌዴሬሽን ከዚህ ቀደም ፕሮፌሰር አስራትን ጨምሮ ብርቱክን ሚደቅሳን የክብር እንግዳ አድርጎ መጋበዙ አይዘነጋም:: የብርቱካን ሚደቅሳ ጉዳይም ፌዴሬሽኑን ለሁለት ከፍሎት እንደነበር ይታወሳል::

