እኔ አብይ አህመድ እስካሁን የሄደባቸውን ሂደቶች  በአብዛኛው ወድጄለታለሁ፡፡ ከልቡም ነው የሚል እምነት አለኝ፡፡ ግን ወሳኝና ቅር የሚያሰኙኝ ነገሮች አሁንም አሉ፡፡ አብይ በግሉ ጥሩ ቢሆንም ግን አሁንም በኢትዮጵያ መንግስታዊ መዋቅርና ወሳኚና አፋጣኝ ለውጥ የሚሹ ጉዳዮችን ለውጥ ማድረግ ያላስቻለው አንድ ነገር አለ ከሚል ነው፡፡ ድጋፌም እስካሁን በግሉ በኢትዮጵያዊነት ስላለው እምነቱና ዜጎችን ከእስር ማስለቀቅና በነጻነት በአገራቸው በልበ ሙሉነት እንዲንቀሳቀሱ የሚያበረታታቸው ጥረቱ ነው፡፡ እንግዲህ በዚህ ሁለት ወር በአልሞላ ጊዜ ውስጥ ብዙ እንዲህ ያሉ ተግባራትን አከናውኗል፡፡ ግፋበት በአጭር ጊዜ ውስጥ ኢትዮጵያዊ ዜጋ በተሰደደበትም አገር ይሁን በአገሩ ያለወንጀሉ የሚሰቃይበት ጊዜ ያከትማል የሚል እምነት አለኝ፡፡ በእኔ ብቻም ሳይሆን በበርካታ ዜጎች  እምነት ግን አሁንም አብይ ማድረግ አለበት ብዬ የጠበኳቸው እስካሁንም ያልተደረጉ በርካታ ጉዳዮች አሉ፡፡ እንግዲህ አብይ ይህን ማድረግ ያላስቻለው ነገርም ከአለ ለሕዝብ ይፋ ሊያደርግ ይገባዋል ከዚህ በኋላ፡፡ እስካሁን እኔ በግሌ አብይ እየሰራ ያለውን እያመሰገንኩ መደረግ የሚገባውን በምክር መልክ ሳስተላልፍ ቆይቻለሁ፡፡ አሁንም እቀጥላለሁ፡፡ አብይ እነዚህ እያነሳናቸው ያለወንውን መሠረታዊ ጥያቄዎች ይመልሳል ወይም ያላስቻለው ነገርም ከአለ በይፋ ለሕዝብ ግልጽ ያደርጋል የሚል እምነት አለኝ፡፡ ግን ጊዜ እያለፈ ሲሄድ አደጋው ከሁሉም በፊት ፊት ለፊት በአለው በራሱ በአብይ ላይ ሊሆን ይችላልና የጊዜውን ጉዳይ ቢያስብበት የሚል አሁንም ማሳሰብ እወዳለሁ፡፡

ለመሆኑ እንዲህ የሚያንገበግቡን አብይ በአስቸኳይ እርምጃ ሊወስድባቸው ይገባሉ የምንላቸው ጉዳዮች ምንድናቸው? እስካሁን እንግዲህ ገና ነው በሚል መታገስም ስላለብን ነው፡፡ ግን ከዚህም በፊት መሆን የሚችሉም ነበሩ፡፡

Customer Management Software
AI-Based Lead Scoring, Integrated Phone, Email Management And More.

የመጀመሪያው ጉዳይ አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ተብሎ በሕዝብ ላይ የታወጀው ሕዝብን በወሮበላ ወታደራዊ እዝ ሥር ያኖረ ከጅምሩም በፓርላማ የወደቀ ግን በሕገወጦች ሥራላይ የዋለው አሸባሪ ወሮበሎችን እንደልባቸው እንዲሆኑ ያረገው አዋጅ ነው፡፡ ይሄ አዋጅ አብይ ከተሾመበት ሳምንት ጀምሮ እስከአሁን ሊነሳ የሚችል ነበር፡፡ እስካሁንም አልተነሳም ምን አልባትም ይህ አዋጅ አሁን ላይ ወንጀለኞች እየተጠቀሙበት ነው የሚል ጽኑ እምነት አለኝ፡፡ የዳንጎቴ ሥራአስኪያጅና የድርጅቱ ሠራተኞች መገደል በዋናነት በሕገ ወጡ አዋጅ የመግደል ነጻነት የተሰጠው የወሮበላው ቡደን ሴራ ነው የሚል እምነት አለኝ፡፡ ከዛም በላይ ዛሬም በየቦታው ማንነትን መሠረት ያደረጉ ጥቃቶች እየደረሱ ያሉት የዚሁ ሕገ ወጥ አዋጂ አስፈጻሚ የሆነው ኮማንድ ፖስት (የወሮበሎቹ) ሰንሰለታዊ ሴራ ነው የሚል እምነት አለኝ፡፡ አሁንም ይህ ሕገ ወጥ አዋጅ በአስቸኳይ እንዲነሳ ማድረግ ከአብይ የምንጠበቀው ነው፡፡ በዚህ አንድ ወር ውስጥ መነሳት አለበት ብዬ አምናለሁ፡፡ ይህን ማድርግ ከአልቻለ አብይ ማድረግ ያልቻለበትን እውነት ለሕዝብ ማሳወቅ አለበት ባይ ነኝ፡፡

ከዚህ ሕገ ወጥ አዋጅ በተጨማሪ ሕዝብን ለመዝረፍ፣ ለማሰር፣ ለማሰቃየትና ለመግደል የወጡ ሌሎች በርካታ አዋጆችም አሉ፡፡ እነዚህም በፍጥነት ሊወገዱ ከሚገባቸው ነው፡፡ የሽብር፣ መረጃ፣ የሲቪል ማሕበራት አዋጅ በሚል ሌሎች በሕዝብ ላይ ግፍን ለመፈፀም ወጥተው እስካሁንም እየተሰራባቸው ያሉ አዋጆች እስካልተነሱ ድረስ ለውጥ እያደረግን ነው ማለት አይታሰብም፡፡ እነዚህ አዋጆች መነሳት ብቻም ሳይሆን በእነዚህ አዋጆች ምክነያት የደረሰውን ግፍና ሰቆቃ ለታሪክ የሚያስታውስ ልዩ ሰነድ አብሮ ተዘጋጅቶ ዳግም በኢትዮጵያ ምድር ይህ ላይሆን መሀላ ሆኖ እንዲቀመጥ እላለሁ፡፡

ሌላው ወናው ሕገ መንግስት ተብሎ በአገርና ሕዝብ ላይ እጅግ የከፋ ሴራን ለመፈጸም የሚያስችሉ አንቀፆች በማር ተለውሰው የታጨቁበት ሰነድ ነው፡፡ ይህ ሰነድ ሕዝብን ከሕዝብ ለመለያየት፣ አገርን ለማፈራረስ፣ የማያባራ እርስ በእርስ እልቂት እንዲፈጠርና ለወያኔና አጋሮቻቸው በቀጥታ ዕድሜ ታስቦ የተዘጋጀ ሰነድ ነው፡፡ አንዳንድ አንቀጾችም አንድን ግለሰብ ታስበው ነው፡፡ ለምሳሌ የጠ/ሚኒስቴሩን ሥልጣን ጊዜ ገደብ ብታዩት በቀጥታ ለመለስ ታስቦ ነው፡፡ አንቀጽ ሰላሳ ዘጠኝ ፊት ለፊት ስለሆን እንደውም ችግር የለውም፡፡ ከዛ ይልቅ የከፉ ሕዝብን ከሕዝብ ለማጨራረስ ሆን ተብለው የገቡ አንቀጾች አሉ፡፡ ለምሳሌ አንጽ አርባ አምስት፡፡ ባንዲራንና የአዲስ አበባን ከኦሮሚያ ጋራ የሚኖረውን ግንኙነት  የሚጠቅሱት አንቀጾች  አደገኛ  ከሚባሉ ሴራዎች ውስጥ ናቸው፡፡ ከጅምሮ ይህ ሕገመንግስት ያለ ኢትዮጵያ ሕዝብ ተሳትፎና ፍቃደ በመለስ(ለገስ) ዜናዊናና ሌንጮ(ዩሐንስ) ለታ ጥምር ሴራ የተዘጋጀ ሰነድ ሆኖ የኢትዮጵያ ሕዝቦች ተስማምተውና ፈቅደው ይላል፡፡  ይህ ሰነድ በቀጣይም ዋነኛ የኢትዮጵያውያን የሥቃይና ሞት አዋጅ ሆኖ እስካሁን ሰራ፡፡ ሕገ መንግስቱን ለመናድ በሚል የሀሰት ክስ ብዙ ዜጎቻችን አልቀዋል፡፡ ይህ ሕገ መንግስት የኢትዮጵያን ሕዝብ እንዲያልቁ ያደረገ ሰነድ ነውና በፍጹም ከኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊነት ጋር ሊቀጥል እንደማይችል አብይ ተረድቶ በአስቸኳይ የኢትዮጵያና ሕዝቦቿ ሕገመንግስት ሊያዘጋጅ ይገባዋል፡፡ ህገ መንግስቱ የአፈጻጸም እንጂ ሰነዱ ችግር የለበትም ለምትሉ መጀመሪያ አንበብቡት፡፡ ከዚያ የሴራው ሁሉ ምንጭ ሕገመንግስት ተብሎ እነመለስ ያዘጋጁት ሰነድ እንደሆነ ትረዳላችሁ፡፡ ሕገ መንግስት ማዘጋጀት ከላይ አንደጠቀስኳቸው አዋጆችን ማንሳት ስለማይቀል ጊዜ ይወስዳል፡፡ ይህም ቢሆን በስድስት ወር ውስጥ ተዘጋጅቶ ቢያንስ ለሕዝብ ውይይት መቅረብ ይችላል፡፡ ለዛ ግን አሁኑኑ ሂደቱ ሊጀምር እንደሚገባውና ይሄንኑ ለሕዝብ ማሳወቅ ከሚቻሉ ጉዳዮች አንዱ ነው፡፡

ሌላው እስካሁን አብይ እያደረጋቸው ያሉ ሹም ሽሮች ሕዝብ ከጠበቃቸው እጅግ በአልተጠበቀ መልኩ ነው፡፡ በጡረታ ተሰናበቱ የተባሉት እንዳሉ ሆነው በተለያዩ ቦታዎች አብይ እየሾማቸው ያለው ጭራሽ ኽዝብ ከጠበቀው በተቃራኒ ነው፡፡ ለሕዝብ መከራና ሥቃይ መሪ ተዋናይ ናቸው የተባሉ ግለሰቦችን አሁንም በከፍተኛ ሥልጣን ሾሞ እናየዋለን፡፡ አብይ አዋሳ ላይ ሕዝብን በሰበሰበ ጊዜ አንድ ሽማግሌ የአብይን ሹም ሽር በማረ አንደበታቸው ገልጸውታል፡፡ ሕዝብ በዚህ ጉዳይ እጅግ ግራ መጋባት ብቻም ሳይሆን አብይ አሁንም ለወያኔ እየሰራ ነው የሚለውን ጥርጣሬ እንዲያቆይ አስገድዶታል፡፡ ሰሞኑን የሰጣቸው ሹመቶች ደግሞ ጭራሽ ሕዝብን በብዙ ወደ ኋላ እንዲበረግግ ሳያደርግ አይቀርም፡፡ አብይ የመጀመሪያውን ካቢኔ ሹመት በሰጠበት ወቅት እኔ በራሴ እጅግ ቅር ከመሰኘቴ የተነሳ ብዙ የጠበኩት ነገር ስለወረደብኝ የራሴን ሂስ ሰጥቻለሁ፡፡ ከዛም በላይ ነው ለማስጠንቀቅ የሞከርኩት፡፡ አብይን ግን በቀጣይነት በአሉታዊ ጎኑ ማንሳት ለኢትዮጵያ ጠላቶች የተመቸ መስሎ ስለታየኝ እየሰራ ያለውን እያደነቀሁ ማድረግ ያለበትን እያሳሰብሁ መቀጠሉን መርጫለሁ፡፡

እንግዲህ ከላይ ያነሳኋቸው ጉዳዮች አብይ እርምጃ ሊወስድባቸውና በተግባር በአገር ላይ ለውጥ ለማምጣት መቁረጡን በማሳየት ዜጎችን ሁሉ በአንድነት ሊያሳትፍበት የሚችልበት ከዜጎች ሁሉ ጋር የመተማመኛ ተግባራቶቹ ናቸው ብዬ በጽኑ አምናለሁ፡፡  አብይ የኢትዮጵያን ሕዝብ ለማሸበር የወጡትን አዋጆች እያሰበባቸው ብንል እነኳን ያደረጋቸውንና እያደረጋቸው ያለውን ሹምሽሮች ስናይ አብይ ምን አስቦ ነው ከማለት አልፈን ከፍተኛ ጥርጣሬ ውስጥ አልፎም በአብይ ተስፋ መቁረጥን እያስከተሉ ያሉ ጉዳዮች ናቸው፡፡ አብይ መቼም በየሔደበት ስለዜጎች ደህንነትና ኢትዮጵያዊነት ለየሕዝቦች አንድነት መናገሩ ለተንኮል ነው ለማለት ይከብዳል፡፡ ግን ተንኮል አለበት ብለው ለሚያስቡ መሠረተ ቢስ ናችሁ ለማለት አያስደፍርም፡፡

እንግዲህ ይህ ሁሉ በአለበትና ዜጎች እንደ መተማመኛ የሚጠይቋቸውንም እንዳቸውንም  ሳያደርግ በኖርዝ አሜሪካና አውሮፓ ኢትዮጵያውያን በሚያዘጋጁዋቸው የስፖት ፌስቲቫሎች ልገኝ ብሎ ጥያቄ ማቅረቡን ሰማን፡፡ እንደእውነቱ አኔም መጀመሪያ ከጥሩ ጎኑ አይቼው ጥያቄውን መቀበል እንጂ ማቅማማትም አያስፈልግም ከሚሉት ነበር፡፡ በዚህ ሁኔታ ዛሬ የአብይን ጉዳይ ከሚጠራጠሩት ሊሆን ይችላል የአብይ የአሜሪካ ስፖርት ፌስቲቫል ላይ ለመገኘት ጥያቄ ማቅረቡን  ከSR 168 ጋር አያይዞ አንዱ በፌስ ቡኩ የጠቆመውን ሳይ አብይ ሆይ  በSR 168 አትምጣብኝ አልኩ፡፡ ይህ የኢትዮጵያውያን የሕልውናቸው ማረጋገጫ ጉዳይ ነውና፡፡ ስለዚህ እኔም አዘጋጆቹን ጥሪውን ለመቀበል ጠበቅ ያለ ቅድመ ሁኔታ መጠይቅ እንዳለባቸው ተሰማኝ፡፡ እንደውም ይግርባችሁ ለማለት አወዳለሁ! ዛሬም የኢትዮጵያ ሕዝብ ጠላቶች እየተሾሙ በአሉበት ነባራዊ ሁኔታና በአሜሪካም ሆነ በሌሎች መንግስታት በኢትዮጵያ ሕዝብ ላይ በደልን እየፈፀሙ ያሉትን ለሕግ እንዲቀርቡ ድጋፋቸውን እየጠየቅን በአለንበት ሁኔታ  አብይ በነዚህ ፌስቲቫሎች ለመገኘት ጥያቄ ያቀረበበት ጉዳይ ከመጠራጠርም በላይ አንድ ሴራ አለው ብሎ ለመደምደም ጥቂት የጎደለው ነው፡፡ ስለዚህ አብይን በSR 168 አትምጣብን እላለሁ፡፡ በዚህ ጉዳይ ማንም ኢትዮጵያዊ ነኝ የሚል ሊያቅማማ አያስፈልግም፡፡ አብይ ይህን አስቦ ላይሆን ይችላል፡፡ ግን ከዚህ ጀርባ ቢያንስ አብይን ሊጠቀሙ የሰቡ ሴረኞች መኖራቸው ብዙም አያጠራጥርም፡፡ በዚህ አጋጣሚ እኔም ያላስተዋልኩትን እንዳስተውል ያደረገኝ  የፌስቡኩን ተጠራጣሪ አመሰግናለሁ፡፡ አዎ እንደ እርግብ የቧህ እንደ እባብ ብልህ ሁኑ ነው የተባለውና! ድንቅ እይታ ነው፡፡

አመሰግናለሁ

ልዑል አምላክ እግዚአብሔር ኢትዮጵያንና ሕዝቦቿን ከሴረኞች ይጠብቅ! አሜን!

ሰርፀ ደስታ