ከአርባ አመታት በፊት በውጭ አገር የሚገኙ ኢትዮጵያውያውያን፤ የመጀመሪያ ጠቅላላ ስብሰባቸውን ቦሰተን ከተማ ላይ ሲያደርጉ ቀዳማዊ ኃይለ ስላሴ፤ የስብሰባውን አላማ አድንቀው ለተማሪዎቹ ደብዳቤ ልከውላቸው ነበር (ሙሉውን ደብዳቤ ከዚህ በፊት ለህትመት አብቅተነዋል)። በወቅቱ የነበሩት የተማሪዎቹ መሪዎች ግን፤ የቀዳማዊ ኃይለስላሴን መንግስት የሚቃወሙ በመሆናቸው፤ ይህንን የንጉሠ ነገሥቱን አክብሮት የተሞላበት ደብዳቤ ለመላው ተማሪ ሳያስነብቡ ቀሩ። ይልቁንም የወቅቱ ተማሪዎች ንጉሠ ነገሥታቸውን ንቀው እና ጠልተው፤ ስብስባቸውን እያጠናከሩ ሄደው እራሳቸውን ወደ ፖለቲካ ድርጅት ቀየሩ። ኢህአፓ እና መኢሶን የዚያ ትውልድ የተማሪዎች ንቅናቄ ውልዶች ናቸው። መጨረሻቸውም እርስ በርስ መገዳደል እና መጨራረስ መሆኑን ታሪክ ይነግረናል። ምናልባት የቀዳማዊ ኃይለስላሴን መልዕክት በጥላቻ ከማየት ይልቅ፤ ትንሽም ቢሆን ቅንጣት ያህል ስፍራ ሰጥተው ቢሆን ኖሮ እርስ በርስ ከመጨራረስ ይልቅ ኢትዮጵያን ዛሬ ከደረሰችበት በላይ በእጥፍ ሊያሳድጓት ይችሉ ነበር። …አሁን ሌላ ዘመን ላይ ነን። የዶ/ር አብይ አህመድ የፍቃድ ደብዳቤ ለአባላቱ እንዳይደርስ ተደርጎ አልተደበቀም። ለአባላቱ ይፋ ሆኖ ግልጽ ውይይት እና ውሳኔ ይሰጥበታል። ውሳኔው ምንም ሆነ ምን የሳቸው ደጋፊዎች ብቻ ሳይሆኑ፤ እራሳቸው ዶ/ር አብይም ጭምር ውሳኔውን በኩርፊያ ሳይሆን በጸጋ ለመቀበል መዘጋጀት አለባቸው። ይህ ሲሆን… በሃሳብ ሳንለያይ ነገን በተስፋ ማየት እንጀምራለን።

ዶ/ር አብይ አህመድ ለፌዴሬሽኑ ያቀረቡት ጥያቄ እና ድምጸ ውሳኔው!

ዳዊት ከበደ ወየሳ

ዶ/ር አብይ አህመድ በመጪው የጁላይ ወር፤ ዳላስ ቴክሳስ በሚደረገው የሰሜን አሜሪካ የስፖርት ፌዴሬሽን ላይ ለመገኘት ጥያቄ አቅርበዋል። ዶ/ር አብይ እንደማንኛውም ሰው መገኘት የሚችሉ ቢሆንም፤ በደብዳቤያቸው ላይ ያቀረቡት ሃሳብ ግን… በዝግጅቱ ላይ ተገኝተው ንግግር ለማድረግ እንዲፈቀድላቸው ነው። ዶ/ር አብይ አህመድ በደብዳቤያቸው ላይ፤ የሰሜን አሜሪካ የስፖርት ፌዴሬሽን በየአመቱ ለሚያደርገው ዝግጅት ያላቸውን አድናቆት አልሸሸጉም፤ ኢትዮጵያውያንን በኢትዮያዊነት መንፈስ ለረዥም አመታት በአንድነት በማሰባሰቡ ለፌዴሬሽኑ አክብሮታቸውን በትህትና ገልጸዋል። እሳቸውም በእንዲህ አይነቱ ዝግጅት ላይ፤ በተለይም አርብ ጁላይ 6 ቀን በሚከበረው የ”ኢትዮጵያ ቀን” ላይ በመገኘት፤ የኢትዮጵያዊነት ስሜትን የሚያነቃቃ ንግግር ለማድረግ ነው ጥያቄ ያቀረቡት። ይህ ጥያቄ ሰፋ እና ሞቅ ያለ ውይይት አስከትሏል።

እንደሚታወቀው የሰሜን አሜሪካ ስፖርት ፌዴሬሽን እንደዚህ አይነት ሃይለኝ ክርክር ውስጥ የገባው፤ ከጥቂት አመታት በፊት በአትላንታው ዝግጅት ላይ፤ “ብርቱካን ሚዴቅሳ በክብር እንግድነት ትገኝ ወይስ አትገኝ?” በሚለው ሃሳብ ላይ ነው። በወቅቱ ፌዴሬሽኑ ለሁለት እስከመከፈል የደረሰው የአብላጫውን ውሳኔ ከመቀበል ይልቅ፤ “እኔ ያልኩት ካልሆነ…” የሚል ማገንገን በመበርከቱ ነው። ያን ግዜ የፌዴሬሽኑ አባላት በጋራ ለወሰኑት ውሳኔ ተገዥ የሆኑት ክፍሎች አሸናፊ ሆነው ዛሬም ድረስ ዘልቀው፤ 35ኛ አመታችንን እንድናከብር ምክንያት ሆነውናል። አሁንም የዶ/ር አብይን መገኘት አስመልክቶ ውሳኔ ለመስጠት አስቸኳይ ስብሰባ ተጠርቷል። ውሳኔው “እሺ” ወይም “እምቢ” ሊሆን ይችላል። ዋናው ቁምነገር ውሳኔው ምንም ሆነ ምን፤ ሁላችንም ለውሳኔው ተገዥ ለመሆን እራሳችንን ማዘጋጀታችን ላይ ነው።

አሁን ያለንበትን ሁኔታ መሰረት አድርገን ለግዜው ሃሳቦችን ለሶስት ከፍለን ማየት የግድ ነው። አንደኛው ወገን የዶ/ር አብይ አህመድን ጥያቄ የሚቀበል ነው። ሁለተኛው ወገን የዚያ ተቃራኒ ሲሆን፤ ሶስተኛው አካል ደግሞ የአስታራቂነት ሚና የሚጫወተው ክፍል ነው። እኛም የራሳችንን ውሳኔ ከመስጠታችን በፊት እነዚህም ሶስት ክፍሎች በአንክሮ እንመልከታቸው።

1ኛ – የዶ/ር አብይ አህመድን መገኘት የሚደግፉት ክፍሎች የሚከተሉትን ሃሳቦች ይሰነዝራሉ።

1-1/ “እንኳንስ ዶ/ር አብይ ጥያቄ አቅርቦልን ቀርቶ፤ እኛው ራሳችን ጠይቀነውም ቢሆን እንዲገኝ ማድረግ ነበረብን። ስለዚህ መገኘት አለበት።” ይላሉ።

1-2/ “አሁን ባለው ሁኔታ ዶ/ር አብይን ለማየት እና ለማግኘት የሚፈልገው ኢትዮያዊ ቁጥር በርካታ ነው። ስለሆነም በእለቱ መገኘቱ ለፌዴሬሽኑ ጥቅም እንጂ ጉዳት ስለሌው ቢገኝ ይመረጣል።” የሚሉ ወገኖችም አሉ።

1-3/ “በደብዳቤው ላይ እንደተገለጸው፤ ዶ/ር አብይ የሚገኘው ኢትዮጵያዊነትን ለመስበክ ከሆነ በእለቱ መጋበዙ ምንም ክፋት የለውም።” በማለት የሚከራከሩም አሉ።

2ኛ –  የዶ/ር አብይ አህመድን መገኘት የማይደግፉት ደግሞ ይህንን ይላሉ።

2-1/ “ፌዴሬሽኑ በእለቱ ዋና ተናጋሪ አድርጎ የሰየመው፤ ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋን ነው። በዚህ ላይ ሌላ ተደራቢ ሰው አድርገን መጋበዝ ትክክል አይደለም። ስለዚህ ሌላ ተናጋሪ መጋበዝ አግባብ አይደለም።” ብለዋል።

2-2/ “ምንም ሆነ ምን ዶ/ር አብይ በዚህ ዝግጅት ላይ፤ የሚያስተላልፈው የፖለቲካ መልዕክት ስለሆነ  መገኘት  የለበትም።” የሚሉም አሉ።

2-3/  “ሲጀመር በዚህ አጭር ግዜ ውስጥ እንዲገኝ ጥያቄ መቅረቡ አግባብ አይደለም። ሲቀጥል ደግሞ ዶ/ር አብይ እስካሁን ሲናገር ከነበረው የተለየ ነገር አይናገርም። አመጣጡ የፖለቲካ ትርፍ ለማግኘት ስለሆነ፤ ተቀባይነት ሊኖረው አይገባም።” በማለት የዶ/ር አብይ አህመድን መገኘት አይቀበሉትም።

3ኛ – ከላይ የተገለጹትን ሁለት የተለያዩ ወገኖች ለማቀራረብ የሚጥሩ 3ኛ ወገኖች ደግሞ ይሄንን ይላሉ።

3-1/ ዶ/ር አብይ በፌዴሬሽኑ ዝግጅት ላይ የሚገኝ ከሆነ፤ ተመጣጣኝ የሆነ ግብረ መልስ የሚሰጡ እንደታማኝ በየነ አይነት ሰዎችም ተገኝተው ንግግር ማድረግ አለባቸው።

3-2/ ዶ/ር አብይ በፌዴሬሽኑ የመክፈቻ ወይም የመዝጊያ ዝግጅት ላይ መገኘት ይችላል። በኢትዮጵያ ቀን ላይ ተገኝቶ ንግግር ማድረጉ ግን ተቀባይነት የለውም።

3-3/ ዶ/ር አብይ ስራውን ገና መጀመሩ ነው። ባይሆን እስከሚቀጥለው አመት ድረስ ጠቅላላ ስራውን እንገምግመው። ከዚያም እኛ ራሳችን ልንጋብዘው እንችላለን። የዘንድሮን ግን ይለፈን… በማለት አስታራቂ የሚመስሉ ሃሳቦችን ሰንዝረዋል።

 

እንግዲህ እነዚህ ሃሳብ እና አስተያየቶች በቅርበት ከፌዴሬሽኑ ሰዎች ጋር ስንነጋገር የተሰጡን ሃሳቦች ናቸው። በዛሬው እለት በፌዴሬሽኑ አባላት መካከል የሚደረገው ስብሰባም እነዚህን መሰረታዊ ነጥቦች እንደሚያንሸራሽር ይጠበቃል። የፌዴሬሽኑ ተወካዮች አባሎቻቸውን በማማከር የሚሰጡትን ሃሳብ እና ውሳኔ ይዘው፤ እነሱም ዛሬ ምሽት ድምጻችወን ይሰጣሉ፤ ይህ ውሳኔም የመጨረሻ ይሆናል።

ከኛ የሚጠበቀው ውሳኔው ምንም ሆነ ምን፤ ለውሳኔው አክብሮት መስጠት ይኖርብናል። ዶ/ር አብይ አህመድ በኢትዮጵያ ቀን ላይ እንዲገኙ የሚፈልጉ ሰዎች እንዳሉ ሁሉ፤ ኢህአዴግ ያደረሰባቸው ጉዳት ያላጠገገላቸው ኢትዮጵያውያን ደግሞ የዶ/ር አብይ አህመድን በዚህ አይነቱ ዝግጅት ላይ መገኘትን አይቀበሉትም። ምንም ሆነ ምን ግን የፌዴሬሽኑን ውሳኔ ለመቀበል ራሳችንን እናዘጋጅ። ውሳኔውን ብንቀበለውም ሆነ ባንቀበለው ተቃውሞ እና ድጋፋችንን በሰለጠነ መንገድ መግለጽ ይኖርብናል።

ልብ ይበሉ። በስፖርት ውድድር ጨዋታ ላይ ሁለት ተቃራኒ ቡድኖች ይጋጠማሉ። ፍልሚያው እልህ አስጨራሽ ሊሆን ይችላል። ዳኝነቱም ቢሆን ከበድ ይላል። በመጨረሻ ግን አንደኛው አሸናፊ ሌላኛው ተሸናፊ ይሆንንና የጨዋታው ግዜ ያበቃል። በውድድሩ መጨረሻ ላይ የሁለቱም ቡድን አባላት እጅ ለእጅ ተጨባብጠው፤ አንዳንዴም ማልያ ተቀያይረው በፍቅር እና በሰላም ይለያያሉ። ይህን የተመለከተው የሁለቱ ቡድኖች  ቲፎዞም የተፋላሚዎቹን ፍቅር ተመልክቶ ሽንፈቱን ውጦ ለሚቀጥለው አመት ፍልሚያ፤ ተስፋ ሰንቆ ይለያያል።

አሁን ባለው ሁኔታ የዶ/ር አብይ ጥያቄ ተቀባይነት ካገኘ ፌዴሬሽኑ የደረሰህበትን ድምጸ ውሳኔ፤ ለህዝቡ ባስቸኳይ ይፋ ማድረግ አለበት። ይህ ከሆነ የዶ/ር አብይ አህመድ ተቃዋሚዎች አጋጣሚውን በመጠቀም በትልቁ ስቴድየም ውስጥ ትልቅ እና የሰለጠነ ተቃውሞ ለማቅረብ ነገሩን ወደ ጥሩ አጋጣሚ መቀየር አለባቸው።

በሌላ በኩል ደግሞ የጠቅላይ ሚንስትሩ ጥያቄ ውድቅ ከሆነ፤ ፌዴሬሽኑ በደብዳቤ የአክብሮት ምላሽ ሊሰጥ ይገባዋል። በዚያው መጠን ዶ/ር አብይም ውሳኔውን አክብረው በመቀበል፤ አዎንታዊ የአጸፋ ምላሽ ሊሰጡ ይገባል። ይህን የተመለከተው ህዝብም በተመሳሳይ መልኩ ሰላም ሊያወርድ ይችላል። ከዚህ ሁሉ ተቃራኒ በመሆን፤ “እኔ ያልኩት ካልሆነ…” የሚል ወገን ካለ ግን ከራሱ ጋር ለአንድ አፍታም ቢሆን ሊመክር ይገባዋል። በጥላቻ ከመለያየት ይልቅ፤ በፍቅር መለያየት እንደሚቻል ነጋሪ እና መካሪ የሚያስፈልገን ግዜ ላይ አይደለንምና… ልብ ያለው ልብ ይበል።