የሕገ መንግሥት ቅቡልነት (ሔኖክ አክሊሉ)
(የሕግ ባለሙያና ጠበቃ)
***
የሕገ መንግሥት ቅቡልነት አስፈላጊነት
***
ሕገ መንግሥት በአንድ አገር ውስጥ ያሉ ሕጎች ሁሉ የበላይ ሕግ እንደሆነ አሁን እያመፁ ያሉ የኢሕአዴግ ትውልድ ወጣቶች የሲቪክ እና ስነ ዜታ ትምህርት በሚባለው ላይ እየተነገራቸው ነው ያደጉት። በእርግጥም የበታች ሕጎች ሁሉ የመንፈስ አባት እና የሕጋዊነት መሠረት ነው። የመንግሥትም ሆነ የዜጎች ድርጊት ምንም ዓይነት የተቀደሰ ሐሳብ ያለው ቢመስልም የሚመዘንበት እና ተቀባይነት የሚያገኝበት/የሚያጣበት እንደሆነ ይታመናል። ስለሆነም ሕጎች ሲወጡ ከእርሱ ጋር መጣጣማቸውን መፈተሽ አሁን ዓለም ከደረሰችበት ሕገ መንግሥታዊ ስርዓት ዕድገት አንፃር ግዴታ እንደሆነ ሲያሳስብ ካስፈለገም በአንድ ግለሰብ አቤቱታ አቅራቢነት ሕገ መንግሥት ጣሽ የተባለው ሕግም በሚመለከታቸው አካላት ሊሻር ይችላል። እርሱን የተጣላ ሕግም ሆነ ተግባር መግቢያ አይኖረውም። ይህ የቃል ኪዳን ሰነድ ታዲያ መሠረታዊ የሚባሉ አገራዊር ጥያቄዎች ምላሽ ያገኙበታል ተብሎም ይታመናል። ስለሆነም ሕገ መንግሥት ላይ ጣት የሚቀሰር ከሆነ እርሱን ጥላ አድርገው የተሠሩ ነገሮች በሙሉ አደጋ ገጠማቸው ማለት ይሆናል።
እንደሚባለው ሕገ መንግሥት የሕጋዊነት መሠረት ከሆነ፣ እራሱ ‹ሕገ መንግሥቱስ ሕጋዊነቱን ከየት ያመጣዋል?› የሚለው ጥያቄ ቁልፍ ይሆናል። መልሱ በእርግጥ አጭር እና ቀላል ነው። ሉዓላዊ ከሆነው ሕዝብ (We, the People) የሚለው ይሆናል። የሥልጣን ሁሉ መሠረት የሆነው ሕዝብ የፈለገውን ለመትከል፣ ያልፈለገውን ደግሞ ለማድረቅ የሚችል ምንጭ ነው። አንዳንዴ አምባገነን መንግሥታት ይህ ባለቤትነት የእነርሱ እየመሰላቸው ብዙ ጊዜ እየተሸወዱ መጨረሻ ላይ ክፉ ትምህርት የሚማሩበት የታሪክ አጋጣሚዎች በአገራችን ጭምር ብዙ ጊዜ አይተናል።
ብዙዎች እንደሚስማሙት አንድ ሰነድ በዘመነኛው ጉልበተኛ ‹ሕገ መንግሥት አድርጌ ስላዘጋጀሁልህ፣ እንካ ተቀበል› ተብሎ እንደ ዳቦ የሚሰጥ ነገር አይደለም። ባለጊዜ ነኝ ሲል የነበረው ዘመነኛው ጉልበተኛ ክንዱ ሲዝል፣ ሰነዱን መገላመጥ ብሎም ማቃጠል እንደሚከተል እሩቅ ሳንሔድ የባለፉትን ሁለት ስርዓታት ዕጣ ፈንታ ከፕሮፌሰር ባሕሩ ዘውዴ መጽሐፍ ላይ ማንበብ ይቻላል።
ሕገ መንግሥት ነዋሪነት ወይም ዘለቄታዊነት ያለው የሕዝቦች ስምምነት ስለሆነ ጉልበት እንዲገባበት አይፈልግም። ይህ ከጉልበት ነጻ የሆነ ሒደት በማርቀቁም ሆነ ማፅደቁ ወቅት እንዲሁም በአተገባበሩ ጊዜ ሁሉ ሊከበር ይገባዋል። ከሕገ መንግሥት በመለስ ያሉ ሕጎችን ለማስፈፀም ኀይል እንደ ሁኔታው አስፈላጊ ሊሆን እንደሚችል ይታመናል።
አንድን ሕገ መንግሥት፣ ሕገ መንግሥት የሚያደርገው ዋናው ቁልፍ ነገር በሕዝብ ያለው ቅቡልነት (legitimacy) እንደሆነ የዘርፉ ጥናቶች ያሳያሉ። ቅቡልነት የዜጎችን ክብር እና ስምምነት ያገኘ ሥልጣንን የሚያመለክት ነው። ይህ ደግሞ የኅሊና እና የነፍስ ነገር እንጂ የስጋ ጉዳይ አይደለም። ትክክል ነው፤ ተገቢ ነው ብሎ በኅሊና መቀበል በስምምነት የሚመጣ እንጂ በዱላ የሚፈጠር አይደለም። ጉዳዩ ከመጀመሪያው የአዕምሮ እንጂ የስጋ አይደለምና።
በተለይ ከዚህ ጋር በተጣጣመ መልኩ ዕውቁ የፌዴራሊዝም እና የሕገ መንግሥት ተመራማሪ ዳንኤል አላዛር የሚከተለውን በሚያምር ቋንቋ ገልጾታል፣ “ሕገ መንግሥታዊ ቅቡልነት በአንድ ስርዓት አስገዳጅነት የሚገኝ ይሁንታ ሳይሆን በፈቃደኝነት የሚገኝ ነው። ዘላቂነት እና እውነተኛ ትርጉም ያለው ሕገ መንግሥት እንዲሆን ቅቡልነት ያለጥርጥር አስፈላጊ ይሆናል።”
ሕገ መንግሥታዊ ቅቡልነት የተለያየ መልክ እንዳለው እነዚሁ የዘርፉ ባለሙያዎች ያስረዳሉ። የመጀመሪያው ሕጋዊነትን የሚመለከት ነው። ይህ ዓይነቱ ቅቡልነት ሕገ መንግሥቱ ተረቅቆ የፀደቀበትን ሒደት የሚዳስስ ይሆናል። ‹ሕዝብ በመረጣቸው ተወካዮቹ ወይም እራሱ በሕዝበ ውሳኔ የሚያፀድቅበት ሒደት ዴሞክራሲያዊ ነበር?› የሚለውን በአብዛኛው የሚመለከት ነው። ይህን ጥያቄ በአዎንታዊ ከመለሰ ሕጋዊ ቅቡልነት ተገኝቷል ብሎ አፍን ሞልቶ በድፍረት መናገር ይቻላል። ይሄ ግን በራሱ ብዙ የማያስኬደን እና ገኛ ረጅም መንገድ እንደሚቀረን ከማመን የሚጋርደን ሊሆን አይገባም፤ ምክንያቱም አንድ ተግባር ሕጋዊ ነው ስለተባለ ብቻ ሕዝብ ይቀበለዋል ማለት አይደለም። እንደዚሁም ሕጋዊ አይደለም ማለት ሕዝባዊ ተቀባይነት የለውም ማለት አይደለም። ሁለቱ የሚገናኙበት እና የሚለያዩበት በርካታ አጋጣሚዎች ይኖራሉ።
በብዙ የሕገ መንግሥት ባለሙያዎች የሚጠቀሰው ወሳኙ ኅሊናዊ ቅቡልነት ነው። ይህ በሕጋዊነት እንደ ምርጫን በመሰሉ ስርዓታት ብቻ የሚፈጠር ሳይሆን በዜጎች እምነት ማግኘትን የሚያመለክት ወሳኝ ነጥብ ነው። ይህን ለማግኘት ጊዜ መጠየቁ እንዳለ ሆኖ ዜጎች ትክክል/ተገቢ ነው የሚል እውነተኛ የውስጥ እምነት ሲኖራቸው የሚፈጠር ቅቡልነት እንደሆነ ተደርጎ ይቆጠራል። ወደ እዚህ የላቀ ደረጃ ለመድረስ ደግሞ የማኅበረሰብን የሞራል፣ ማኅበራዊ፣ ሃይማኖታዊ እና ሌሎች እሴቶችን ማካተት ይጠይቃል። በአጠቃላይ ፍርዱ የዜጎች የኅሊና ጉዳይ ይሆናል እንደ ማለት ነው።
ለተነሱት ነጥቦች ጥሩ ማሳያ ተደርጎ የሚጠቀሰው እ.ኤ.አ. በ1946 የፀደቀው የጃፓን ሕገ መንግሥት ነው። ይህ አገር በሁለተኛው የዓለም ጦርነት በአሜሪካኖች እጅ ሽንፈትን ተከናንቦ በቁጥጥራቸው ሥር ውሎ ነበር። አሜርካኖችም ጃፓንን ማስወጣት፣ ማስገባት እንደ ጀመሩ አሁን የሚተዳደሩበትን ዴሞክራሲያዊ የሚባል ሕገ መንግሥት በበላይነት አስረቅቀው ሥራ ላይ እንዲውል አስደርገዋል። ለዚህም ሥራቸው ባለውለታቸውም ናቸው። የጃፓን ሕዝብም ሕገ መንግሥቱ በወራሪው የአሜሪካኖች አባትነት የተሠራ መሆኑን ቢያውቅም ባህሉን ጠብቆ ጥቅሙን የሚያስጠብቅ መሆኑን ስለተረዳ እጃቸውን ስሞ፣ ከክፉ ይጠብቀው ብሎ ተቀብሎታል። እንደውም ‹ጃፓኖች ከ70 ዓመት በላይ የሆነ ረጅሙ ያልተሻሻለ ሕገ መንግሥት ያላቸው ብቸኛ አገር ናቸው› እየተባለ ይነገርላቸዋል። በዚህ መሃል ብዙ መንግሥታት እና ጎበዞች መጥተው ሔደዋል። ሕገ መንግሥቱ ግን አልተለወጠም። ታዲያ በዚህ ዓመት ጠቅላይ ሚኒስትሩ የአገራቸውን ወታደራዊ ሁኔታ እራሳቸውን በመከላከል ደረጃ የሚያሻሽል የሕግ ረቂቅ ቻይናን እና ሰሜን ኮሪያን ወደ ጎን እያዩ ለምክር ቤት ቢያቀርቡ ሕገ መንግሥት ተነካ ብሎ ብዙ የሕዝብ ተቃውሞ አስተናገደ። መንግሥቱም ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱ አደጋ ላይ ወደቀ ብሎ ለመቃውሞ በወጣው ሕዝብ ላይ መሣሪያ አላነሳም። ይህ ነው እንግዲህ ሕገ መንግሥት ጠባቂ ሕዝብ ማለት!
አገረ መንግሥታት፣ በተለይም ከጎረቤት አገሮች ጋር የሚያወራርዱት ሒሳብ ያለባቸው አገሮች ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓታቸውን የሚጠብቁ ተቋማትን ሲያቋቁሙ በአብዛኛው ይታያሉ። ለዚህ ፓኪስታንን በምሳሌነት መጥቀስ ይቻላል። ከእነዚህን ምሳሌዎች እንደምንረዳው ሕገ መንግሥታዊ ቅቡልነት የሕዝብን እምነት የሚጠይቅ ነገር ስለሆነ ማንም የሚያፈርሰው፣ ማንም የሚገነባው ሳይሆን የሚጠበቀውም ሆነ የሚፈርሰው በማንም ጉልበተኛ ተላላኪነት ሳይሆን፣ ሕዝብ ራሱ በሕዝብ ፈቃድ ብቻ ነው።
