
ከአክሊሉ ወንድአፈረው ethioandent@bell.net
“ በመጀመሪያ ሶሻሊስቶች ላይ ዘመቱ ፣ እኔ ደግሞ ሶሻሊስት ስላልነበርኩ ምንም አልተናገርኩም። ቀጥለው የሰራተኛ ማህበራት መሪወች ላይ ዘመቱ እኔም የሰራተኛ ማህበር ጋር ግንኑነት ስሌለለኝ ምን አገባኝ ብየ ዝም አልኩ፣ ፡ ቀጥለው ባይሁዳውያን ላይ ዘመቱ ። እኔም አይሁዳዊ ስላይደለሁ አይመለከተኝም በማለት ዝም አልኩ። ቀጥለው ወደ እኔ ዘመቱ። ያን ጊዜ ሁሉም አልቀዋልና ሰለ እኔ መብት የሚናገር ማንም አልነበረም”።
“First they came for the Socialists, and I did not speak out. Because I was not a Socialist. Then they came for the Trade Unionists, and I did not speak outBecause I was not a Trade Unionist. Then they came for the Jews, and I did not speak out. Because I was not a Jew. Then they came for me-and there was no one left to speak for me”.
ቀደም ሲል የግፈኛው ሂትለር ደጋፊ የነበሩና ኻላ ደግሞ ያንን የግፍ አገዛዝ በመቃወማቸው ምክንያት ለእስር የተዳረጉት የሉተራኑን ካህን ማርቲን ኔሞለር “Martin Niemoller (1892-1984)
ይህን ጽሁፍ ለመጻፍ የተነሳሳሁትበት ምክንያት ዛሬ በሀገራችን እየታየ ካለው ፖለቲካዊ ሁኔታ ጋር ተያይዞ በሰብአዊ መብት አንጻር መዘንጋት የሌለበትን መሰረታዊ ጉዳይ አጽንኦት በመስጠት ለሰብአዊ መብት መከበር የምናደርገው ትግል በጽኑ መሰረት ላይ የታነጸ እንዲሆን የበኩሌን ለማበርከት ነው።
ከላይ ከቀረበው ጥቅስ ሊወሰድ የሚገባው ዋናው ቁምነገር፣ አያንዳንዳችን ለሁሉም ሁላችንም ለያንዳንዱ መብት ካልቆምን የሰው መብት በዘላቂነት ሊከበር አይችልም የሚል ነው። የተወሰኑ ግለሰቦች ወይም የህብረተሰብ ክፍሎች መብት ሲነካ ሁላችንም ካላወገዝንና ትክክል አይደለም ካላልን የሁላችንም መብት አደጋ ላይ መሆኑንና እያንዳንዳችን ለሰብአዊ መበት ጥሰት አደጋ የተጋለጥን መሆናችንን መገንዘብ ተገቢ ነው የሚል ነው።
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ሀገራችን ውስጥ እጅግ ብዙ የፖለቲካ እስረኞች ከየታጎሩበት ዘግናኝ እስርቤቶች እየተፈቱ እንደሆነ መመልከት እጅግ አስደሳች ነው። እነዚህ አሁን የተፈቱት የፖለቲካ እስረኞች ሁሉ ከመጀመሪያውም መታሰር አልነበረባቸውም ብየ ባምንም ሰው ከእስር ሲለቀቅ ደግሞ እስየው የሚያሰብልና ፈችዎችንም እንዳመሰግን ያደረገኝ ነው። አንድም የፖለቲካ እስረኛ የለንም ከሚል ስርአት ጉያ ይህ ሁሉ እስረኛ ሲወጣ ማየት ደግሞ እጅግ የሚገርም ታሪካዊ ክስተት ሆኖ አግኝቸዋለሁ።
ከሰላሳና ሀምሳ አመታት በሓላ ነጻነት በተረጋገጠባጥ ኢትዮጵያ ውስጥ ዜጎች ያለፉት ሁለት ወራት ሁኔታን በታሪክ መነጽር ሲመረምሩ ያሁኑን ትውልድ የፖለቲካ መሪወቹንና የመብት ታጋዮቹን በታላቅ ግርምት ይመለከታሉ ብየ አገምታለሁ።
በተከታታይ ከተፈቱት ብዙ ወገኖቻችን ውስጥ በአሁኑ ዙር ደግሞ የግንቦት ሰባት አመራር አባል የነበረው አንዳርጋቸው ጽጌ መኖሩ ታላቅ እርምጃ ነው። ይህ ደግሞ ምናልባትም ብሄራዊ መግባባትን እውን ለማድረግ በሚደገረው የወቅቱ ጥረት በተለይም መተማመንን በመፍጠር በኩል አንድ እርምጃ ወደፊት ሊወስደን የሚችል ሊሆን የሚችልበት ሁኔታ ይታየኛል፡፤ እስካሁን እስረኞች ሁሉ እንዲፈቱ ትግል ላደረጉና ለተሟገቱ በተለይም ደግሞ ስቃዩን ተሸክመው ለኖሩ ለእያንዳንዱ እስረኛ ቤተሰቦች ወገንና ዘመዶቻቸው ያለኝ አክብሮት እጅግ ትልቅ ነው። የሁላችሁም ደስታ ደስታየ ነው፣ እንኳን ደስ አላችሁም እላለሁ።
ጠቅላይ ሚኒስቴር አብይም በዚህ አንጻር እስካሁን ያደረጉት እጅግ የሚያሰወድሳቸው ተግባር ነው። በመሆኑም እኔም አመሰግናለሁ እላለሁ።
ይህን ካልኩ ዘንዳ ጠቅላይ ሚኒስቴር አብይንም ሆነ ሌሎች ለውጥ አራማጅ ሀይሎች፣ አክቲቪስቶችና በተቃወዋሚነት የተሰለፉትን የፖለቲካ ሰዎች ማሳሰብ የምፈልገው ሌላ ቁም ነገር የሰብአዊ መብት ትግል ላንዱ ተደርጎ ለሌላው ችላ የሚባል እንዳልሆነ፣ በሀገራችን ሁኔታም አንድም የፖለቲካ እስረኛ በእስር እሰካለ ወይም መዳረሻው እስካልታወቀ ድረስ አሁንም የሰብአዊ መብት ረገጣው የመቀጠሉ ማረጋገጫ እንደሆነ ብቻ ሳይሆን የሁሉም መብት አደጋ ውስጥ መሆኑን ነው።
እንዱን ለማስፈተት ላንቃችን አስኪሰነጠቅ እየጮህን ወይም የባእዳን እርዳታ እንዳይቋረጥ በመፍራት ስለ ለሌላው ሲነሳ ደግሞ ፊታችንን የምናዞር ከሆነ በውነትም ትግላችን የሰብአዊ መብት ትግል፣ ጉዟችንም የሁሉንም ኢትዮጵያዊ መሰረታዊ መብት በእኩልነት ለማስከበር ሳይሆን ለወዳጆቻችን በቁጠባ የምንሰጠው ስጦታ ወይም እንደ እስር ቤት ቀለብ ስንፈልግ የምንሰጠው ሳንፈልግ የምንከለክለው ሸቀጥ ወይም መሳሪያ አድርገን አይተነዋል ማለት ነው። ስለ መብት መከበር ያለን አመለካከትም ከመሰረታዊ እምነት የመነጨ አይደለም ወደሚለው መደምደሚያ የሚወስድ ይሆናል።
የአቶ አንዳርጋቸውን መታሰር በጊዜው እንደተቃወምኩትና የመፈታቱም ዜና እንዳስደሰተኝ ሁሉ፣ የስብአዊ መብትም ሆነ የፖለቲካ ለውጥ መለኪያና ያአንድን ግለሰብ መፈታት አድርጎ መውሰድ ደግሞ ብዙም ጥልቀት የሌለው የትም የማያንቀሳቅስ እይታ እንደሆነ መገንዘብ ተገቢ ነው።
መብት መረገጥ የተጀመረው ከአንዳርጋቸው መታሰር ጀምሮ አይደለም፣ መብት ተከበረ የሚባለውም አንዳርጋቸው ስለተፈታ ብቻ አይደለም፡፡ስለዚህም ከዚህ ክስተት አልፎ በድፍረተ ልንመለከተው የሚገባን እጅግ ብዙ ጉዳይ አለ።
ለምሳሌ በፖለቲካ እስረኞች አንጻር ገና ኢህአዴግና አጋፋሪወቹ ወደ አዲስ አባባ ሲጓዙ ጀምሮ ህወሀት መራሹ ቡድን አፍኖ የት እንዳደረሳቸው የማይታወቁትን የኢህአፓ ታላላቅ መሪዎች እነ ጸጋየ ገብረመድህንን፣ ይስሃቅ ደብረጽዮንን፣ አመሀ ስጦታውን በለጠን፤ እንዲሁም ከጥቂት አመታት በዃላ ከአዲስ አባባ አፍነው የወሰዷቸውን እነ ለማን ፣ አበራሽ በርታን፣ ሙሉ አምባውን፣ ከባህር ዳር፣ ከአርባ ምንጭ፣ አፍነው የወሰዷቸውን፤ እነ ደምሴ ተስፋየን ከሱዳን መንግስት ጋር በመተባበር አፍነው ወደ ኢትዮጵያ መልሰው ያሰሯቸውን፣ ወዘተ አሁኑኑ እንዲፈቱ ወይም መዳረሻቸውን እንዲያሳውቁ ሁላችንም ልንጠይቅ ይገባል። ከዚህ ማፈግፈግ የመብት ታጋይነቱንና ለሰብአዊ መብት መከበር ቆርጦ መቆምን በጥያቄ ውስጥ ያሰገባል። በሰብአዊ መብት ሚዛን ሁሉም ነጻ ሳይወጣ ማንም ነጻ እንዳልሆነ አሳሪዎችና ታሳሪዎች በየጊዜው ቦታ ከሚለዋወጡባት ከሀገራችን ፖለቲከኞች ታሪክ መማር ይገባናል።
ኣእምሮአችንንም አይናችነነም ባግባቡ ከከፈትነው ደግሞ የሉተራኑን ካህን ማርቲን ኔሞለር “Martin Niemoller ትርክት እጅግ ሰፊ ትምህርት ሊሰጠን ይችላል። ።
በዚህ ጽሁፍ ስለኢህአፓ አባላት የምናገረው ብዙወች “የሰብአዊ መብት ተሟጋቾችና አክትቪስቶች” ስማቸውን እንኳ ማንሳት ስለተሳናቸው ይህንን ዝምታ መስበር አለበት ብየ እንጂ ሌሎችም እጅግ ብዙወች በየጉድጓጉ እየተሰቃዩ እንደሆነ እገነዘባለሁ።
በትግል አንጻር ቢታይም እነዚህ ያህአፓ ታጋዮች ጨርቄን ማቄን ሳይሉ ለኢትዮጵያ ህዝብ እኩልነት እና ሙሉ መብት ሲታገሉ የኖሩ ብርቅየ ኢትዮጵያውያን እንጂ ሌላ አይደሉም ።፣ ከሰብአዊ ርህራሄ አንጻር ቢታይም እነርሱም አባት እናት፣ ወንድም እህት፣ አክስት አጎት ባለቤትና ልጅ ወዘተ አላቸው። ከፖለቲካ አንጻርም እነርሱም የፖለቲካ አጋሮች የትግል ጓዶችም አሏቸው።
ስለዚህም የነርሱን መዳረሻ አለማሳወቅ ወይም አለመፍታት ታላቅ ግፍ ነው። ለብሄራዊ እርቅም ትልቅ እንቅፋት ነው። ጥፋት አለባቸው ከተባለ ደግሞ ለፍርድ አቅርቦ መሞገት ነው። ከዚህ ውጭ ግን 24 አመት እና 27 አመት አፍኖ መኖር ወይም መዳረሻቸውን አለማሳወቅ ምንም ማብራሪያ ሊቀርብበት የማይችል በምንም መመዘና ቀባይነት የሌለው ተግባር ነው። በሀገራችን ታሪክ ከነዚህ ሰወች በላይ ታስሮ የሚያውቅ ግለሰብ መኖሩም አጠራጣሪ ነው።
የሁሉም ሰው ልጅ ህይወት እኩል ዋጋ አለውና ዶክተር አብይም እነዚህን የስርአቱ ተጠቂዎች ወይ መፍታት ወይ ሞተውም ከሆነ የማሳወቅ የሞራልም፣ የፖለቲካም ሀላፊነት አለባቸው።
የሰብአዊ መብት ተሟጋቾች፣ የተለያዩ ሚዲያወች፤ ሌሎች አክቲቪስቶችና ተቃዋሚወችም በሀገራችን ውስጥ የመብት መከበርን የሚለኩበትን ሚዛን በጥንቃቄ ሊፈትሹት ይገባል። በሰብአዊ መብት አንጻር ልጅና የእንጀራ ልጅ የሚባል ነገር የለም። በሰብአዊ መብት አንጻር የኛ ሰው እና የነርሱ ሰው የሚባል የለም። የሁሉም መብት ካልተከበረ ይዋል ይደር እንጂ የማንም መብት ሊከበር አይችልም።ስለዚህም ሁሉም የኢህአፓ አባላት ባስቸኳይ ይፈቱ ወይም መዳረሻቸው ይገለጽ ብለን እንነሳ።
ሜይ 28፣2018
