አስቀድሜ እንደተናገርኩት የኢትዮጵያውያን በሰሜን አሜሪካ የፍን ነጻ አሥተዳደር (ESFNA) ቦርድ (ባለአደራ) አባላት ወያኔ እንደለመደው አስቀድሞ ዶላር እረጭቶና በጥቅማጥቅም ደልሎ አግባብቷቸው ኖሮ የዐቢይን የጋብዙኝ?” ጥያቄ በተመለከተ ባደረጉት ስብሰባ የመተዳደሪያ ደንባቸውን በመተላለፍ የዐቢይን ጥያቄ ተቀብለው እንዲገኝ ወስነዋል፡፡ በዚህም የክህደት ውሳኔያቸው ዐቢይ/ወያኔ

1. በዳያስፖራ (በሀገረ ግዩራን) ያሉ ኢትዮጵያውያን ሰላማዊ ሰልፍ እየወጡና በሌሎችም መንገዶች በየጊዜው በወያኔ ላይ ተቃውሞ ሲያሰሙ የቆዩ እንደመሆናቸው መጠን ይሄም ጉዳይ ግዩራን ኢትዮጵያውያን ባሉባቸው ሀገራት መንግሥታት ዘንድ በሚገባ የሚታወቅ ጉዳይ በመሆኑና በዚህም ምክንያት በወያኔ እና በእነኝህ መንግሥታት መሀከል የግንኙነት መሻከር ስለተፈጠረ ዐቢይ በዚህ በዓል ላይ በክብር እንግድነት ተገኞቶ ለእነኝህ ሀገራት መንግሥታትና ባጠቃላይ ለዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ አገዛዙ ከሕዝቡ ጋር ሰላም ያወረደ፣ የተስማማ፣ ፍቅር የመሠረተ መስሎ በመቅረብ ከመንግሥታት ጋር የገጠመውን የጎንኙነት መሻከር ቀርፎ ግንኙነቱን ወደነበረበት ቦታ ለመመለስ እንዲችል፡፡

2. ዳያስፖራውን (ግዩራኑን) አግባብቶ ደልሎ ከወያኔ ጎን እንዲሰለፍ፣ አንድነቱን ለመከፋፈል፣ በዳያስፖራው ያለውን ተቃውሞ ማምከን ካልተቻለም ለመፈረካከስ እንዲችል ምቹ ሁኔታ ፈጥረውለታል፡፡

በዚህ አግባብ ያልሆነና መተዳደሪያ ደንብን የሻረ የተላለፈ ውሳኔያቸው የሚነሣውን የሕዝብ ተቃውሞ ለመቀነስ በማሰብም ፖለቲከኛን በእንግድነት ለመጋበዝ የመተዳደሪያ ደንባችን አይፈቅድልንም!” በሚል በክብር እንግድነት እንዳይቀርቡ የይጋበዙልን ጥያቄዎችን ውድቅ ሲያደርግ እንዳልቆየ አሁን ከተቃዋሚዎችም አንድ ሰው ተመርጦ እንዲቀርብ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

ይሄንን ጥሪ ተቀብሎ የሚቀርብ ተቃዋሚ ካለ አትጠራጠሩ እሱ ሀገርንና ሕዝብን ክዶ ከዐቢይ/ወያኔ አሥተዳደር ጋር የተሰለፈና ከሐሰተኛው የዐቢይ/ወያኔ የለውጥ አሥተዳደር ጋር ለመሥራት ከጀርባ የተስማማ የሥልጣን ጥመኛ መሆኑን ሕዝብ ጠንቅቀህ እንድታውቅ!!!

እንዲያውም ዘግይቶ የወጣው መረጃ እንደሚጠቁመው ከሆነ ጥያቄውን ዶ/ር ዐቢይ እንዳቀረቡ ተደርጎ የተወራውና የተደረገው የማስመሰል መሆኑን ነው፡፡ ፍላጎቱ የቅጥረኛ የቦርድ (የባለአደራ) አባላት መሆኑን ነው አፈትልኮ የወጣው መረጃ ያረጋገጠው፡፡

በሰሜን አሜሪካ የምትኖሩ ኢትዮጵያውያን ሆይ! የቦርድ (የባለአደራ) አሥተዳደሩ የሰጣቹህትን የአደራ ኃላፊነት በልቶ ለወያኔ ሸጦናልና ከዚህ በኋላ የሰጣቹሃቸውን ኃላፊነት ሽራቹህ በማሰናበት ታማኝ ጽኑ እና ትጉ የሕዝብ ልጆችን በምትካቸው ትሾሙ ወይም ታስቀምጡ ዘንድ እንድትንቀሳቀሱ ትጠየቃላቹህ???

ይህ የስፖርት ፌዴሬሽን (የፍን ነጻ አሥተዳደር) ተጠሪነቱ ለሕዝብ እንጅ ለማንም አይደለም፡፡ ይሄም ማለት ባለቤትነቱ ወይም ንብረትነቱ የሕዝብ እንጅ የግለሰቦች ወይም የሌላ አይደለም፡፡ ስለሆነም ሕዝቡ የፈለገውን የማድረግ መብት አለው፡፡ መሻርና ማሰናበት የፈለገውን ከሃዲ የቦርድ (የባለአደራ) አባል የመሻርና የማሰናበት ሙሉ መብት አለው፡፡ በመሆኑም እነኝህ ከሃዲ የባለአደራ አባላት እራሳቸውን ለወያኔ ቀጥረው ወደፊት ሌላ በርካታ ጉዳቶችንና አደጋዎችን ሳያደርሱብህ በፊት ፈጥነህ እርምጃውን ትወስድ ዘንድ በታላቅ አክብሮት ትጠየቃለህ???

በተጨማሪም የዐቢይ መገኘት እርግጥ ሆኖ እዚያ ቦታ ላይ ከተገኘ ቅጥረኛው ዐቢይ በዚያ መድረክ ላይ ቆሞ ጨርሶ ስለማያውቀውና እንዳይሆን አድርጎ ከባድ ጉዳትና ስብራት ሲያደርስበት ስለኖረው ኢትዮጵያዊነትና አንድነት ለፍፎ ሕዝብን እንዲያታልል እንዲያጃጅልና ሲጨንቀው የኢትዮጵያዊነት ጭምብል ላጠለቀው ወያኔ ሕዝብ ድጋፍ እንዲሰጥ ለመስበክ ዕድል ላለመስጠት በጩኸትና በተቃውሞ ታውኩት ዘንድ እራሳቹህን አዘጋጁ!!!

ድል ለኢትዮጵያ ሕዝብ!!! ኢትዮጵያ ለዘለዓለም ትኑር!!!

ሠዓሊ አምሳሉ ገ/ኪዳን አርጋው

amsalugkidan@gmail.com