ፕሮፌሰር ታይለር ኮዌን (ዶ/ር) ካስተናገዷቸው በርካታ ጥያቄዎች ውስጥ ስለአገሪቱ የውጭ ምንዛሪ እጥረት፣ ስለ ብድር ዕዳ፣ የውጭ ባንኮች እንዲገቡ የመፍቀድ ጥቅሙና ጉዳቱ፣ ወዘተ ተጠይቀዋል፡፡

በኢኮኖሚስቱ ዕይታ መሠረት ኢትዮጵያ ከሌሎች የአፍሪካ አገሮች ይልቅ ተስፋ የሚጣልባት ሆናለች፡፡ ይኸውም በሌሎች አገሮች ዘንድ አምራች ኢንዱስትሪዎች ሲቀዛቀዙ በኢትዮጵያ ግን እያቆጠቆጡ መገኘታቸው፣ ላለፉት አሥር ዓመታት በአማካይ የአሥር በመቶ ዕድገት እያስመዘገበች የቆየች አገር መሆኗ ብቻም ሳይሆን፣ የአገሪቱ ሰፊ የሰው ሀብት ለወደፊቷ ኢትዮጵያ ትልቅ የለውጥ ተስፋ ያለው በመሆኑ ጭምር ኢትዮጵያ ከተቀረው አፍሪካ ይልቅ የተሻለ መንገድ ላይ የምትገኝ አገር ስለመሆኗ ፕሮፌሰር ታይለር አስረድተዋል፡፡

ይህም ሆኖ አገሪቱ ወሳኝ የሚባሉ ችግሮች ተደቅነውባታል፡፡ በመንግሥት ቁጥጥር ሥር የሚመራው የመገበያያ ገንዘቦች የምንዛሪ ተመን፣ ለአገሪቱ ኢኮኖሚ አንቀሳቃሽ የሚሆኑ የግብይት መድረኮች እንዳይበራከቱ እንቅፋት ይሆናል ይላሉ፡፡ መንግሥት በውጭ ምንዛሪ ተመንና በወለድ ምጣኔ ላይ የሚከተለው አሠራር ገበያ መር መሆን እስካልቻለ ድረስ ለኢትዮጵያ የኢኮኖሚ ዕድገት አጋዥ የሆኑ ገበያዎችን የማስፋፋት እንቅስቃሴዎች እንደሚገቱ ጠቅሰዋል፡፡

ይኼንን ሲያብራሩም፣ በመንግሥት ለወለድ የሚቀመጠው ምጣኔ ገበያው ከሚሰጠው መጠን ይልቅ ከ30 እስከ 33 በመቶ ቅናሽ ያለበት በመሆኑ የገበያውን መዛባት ያስከትላል፡፡ ይህ በሆነበት ወቅት ደግሞ የውጭ ምንዛሪ እጥረቱን መፍታት ከባድ እንደሚሆን አሳስበዋል፡፡ ምንም እንኳ የሚያስከትላቸው ከባድ ጫናዎች ቢኖሩም፣ እነዚህ ጫናዎች ለአጭር ጊዜ ብቻ የሚቆዩ በመሆናቸው መንግሥት የምንዛሪ ተመን ላይ የሚያስቀምጠውን ምጣኔ እንዲያነሳ ጠይቀዋል፡፡ የወለድ ምጣኔውን ማንሳት ቢያንስ ለሁለትና ሦስት ዓመታት መንግሥትን ችግር ውስጥ ቢከተው ነው ያሉት የኢኮኖሚክስ ምሁሩ፣ ይህ ዕርምጃ ግን ለኢኮኖሚው የረዥም ጊዜ ዕፎይታ እንደሚያስገኝ ይሞግታሉ፡፡

በቴክኖሎጂ መስክ የኢትዮጵያ አዝማሚያ ብዙም የሚባልለት ባለመሆኑ፣ ይህም ትኩረት ይሻል ብለዋል፡፡ በቴክኖሎጂ መስክ ከፍተኛ የሰው ኃይል ማሰማራት ስላለው ጠቀሜታ በመተንተን ሐሳባቸውን አካፍለዋል፡፡ ከዚሁ በተጨማሪም የግብርናው ዘርፍ ከፍተኛ ምርት ሰጪ እንዲሆን የማድረግ ሥራ መንግሥትን እንደሚጠብቀውም አክለዋል፡፡

የውጭ ባንኮች እንዲገቡ ቢፈቀድ የአገሪቱ የውጭ ምንዛሪ እጥረት ይቀረፍ እንደሆነ ለተጠየቁት ሲመልሱ፣ አይቀረፍም የሚል ፈርጣማ ምላሽ ሰጥተዋል፡፡ ለዚህ ምላሻቸው ማብራሪያቸው አሁንም አገሪቱ የምትከተለው የተዛባ የምንዛሪ ተመንና የወለድ ዋጋ አቅርቦትና ፍላጎትን መሠረት ያደረገ ባለመሆኑ የውጭ ባንኮች ቢገቡም የውጭ ምንዛሪ እጥረቱ ሊፈታ አይችልም የሚል መከራከሪያ ያዘለ ምላሽ አቅርበዋል፡፡ የውጭ ባንኮች ቢገቡ፣ አስተማማኝነቱ የተረጋገጠ የፋይናንስ ሥርዓት ይዘው እንደሚመጡ እንደሚጠበቅ፣ ልዩ ልዩ የፋይናንስ አገልግሎቶችና ምርቶችም እንደሚመጡ፣ የውጭዎቹ አዎንታዊ ተፅዕኖ የአገር ውስጥ ባንኮችንም ተጠቃሚ እንደሚያደርጋቸው ይገልጻሉ፡፡ ይሁንና ብር ከውጭ ገንዘቦች አኳያ የተሰጠው የመገበያያ ዋጋ እስካልተስተካከለ ድረስ አገሪቱ የካፒታል መዛባት ውስጥ እንደምትዋልል ይጠበቃል፡፡

መንግሥት የአገሪቱ ባንኮች ያላቸው አቅም፣ የካፒታል መጠንና የቴክኖሎጂ ብቃት ከውጭ ተፎካካሪዎች ጋር የሚያወዳድራቸው አይደለም በሚል ምክንያት የውጭ ባንኮች እንዳይመጡ መከልከሉ ይታወቃል፡፡ ይህ ግን የአገሪቱ ኢኮኖሚ ዕድገትና መስፋፋት በጊዜ ሒደት አንዱ ባንክ በሌላው እንዲጠቃለል የሚያስገድድበት ጊዜ ሩቅ እንደማይሆንም ሳይጠቅሱ አላለፉም፡፡ በዚህ ሒደት ትንንሾቹ ባንኮች እየከሰሙ ትልልቅ ባንኮች እንደሚወለዱ ይጠበቃል፡፡

በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ ላይ የተከማቸው የውጭ ብድር አገሪቱ ኢኮኖሚያዊ ዕድገት የሚገዳደርበት ደረጃ ላይ ይገኛል፡፡ ይኸውም እንደተለመደው ማደጉን እየገታ፣ ለልማት ይውል የነበረው ገንዘብ ለዕዳ ክፍያ እየዋለ የኢኮኖሚውን የሙቀት መጠን እያቀዛቀዘው እንደሚሄድ ሥጋት አጭሯል፡፡ በአንድ ወቅት ቻይናም በከፍተኛ የዕዳ መጠን ተዘፍቃ እንደነበር ያስታወሱት ፕሮፌሰር ኮዌን፣ ኢትዮጵያ ያለባት የዕዳ መጠን የኢኮኖሚ ዕድገቷን የሚፈታተነው ከሆነ አሸንፎት ካቀዛቀዘው ከባድ ሁኔታዎች እንደሚፈጠሩ አሳስበው ይህም ሆኖ የአገሪቱ የወደፊት ዕድል ጨለምተኝነት እንደማይታበት ይናገራሉ፡፡

በውጭ ኢንቨስትመንት ረገድ፣ ኢትዮጵያ በከባድ የገጽታ ድርቅ ስትመታ መቆየቷን ገልጸው ልሂቃኑና ጉምቱዎቹ የአሜሪካ ኢኮኖሚስቶች ሳይቀር በኢትዮጵያ እየታየ ስላለው መልካም ነገር፣ እየተከናወነ ስላለው ጉዳይ ብዙም ዕውቀቱ እንደሌላቸው ጠቅሰዋል፡፡ በየወቅቱ በስዊዘርላንዷ ዳቮስ ከተማ እየተገናኙ የሚመክሩት የዓለም ጠበብቶቹ ኢትዮጵያን እንዲያውቋት ለማድረግና አገሪቱም ከውጭ ኢንቨስትመንት በብዛት ተጠቃሚ እንድትሆን የሚያግዙ የሕዝብ ግንኙነት ሥራዎች እንደሚያስፈልጓት ፕሮፌሰር ኮዌን ይመክራሉ፡፡ የሕዝብ ግንኙነት ዘመቻውን ራሷ አገሪቱ በቀጥታ የምታከናውነው ከሚሆን ይልቅ፣ ለአገሪቱ ቅኑዓን የሆኑ ጸሐፍት ስለአገሪቱ ገጽታ እንዲያስተጋቡ ማድረግ እንደሚበጅ መክረዋል፡፡

አዲስ አበባ እንደ ህንድና ናይጄሪያ ከተሞች መጨናነቅ እንደጀመረች ማየታቸውን የገለጹት ፕሮፌሰር ኮዌን፣ የከተማይቱ ገጽታ የህንድ ከተሞች ከ25 ዓመታት በፊት ያለፉበት ሁኔታ እንደሚያስታውስ ዘክረዋል፡፡ በመሆኑም በከተማይቱ የሚታየው የመኪና ጭስ የሰዎችን ጤና የሚፈታተንበት ደረጃ ላይ እየደረሰ ስለመሆኑ አመላካች እንደሆነ፣ የትራፊክ መጨናነቁም ለከተማ ገጽታ አስቸጋሪ እንደሚሆን አሳስበው፣ ይህ በቶሎ መለወጥ ካልቻለ ከተማዋ ከማትወጣበት አስቀያሚ ሁኔታ ውስጥ እንደምትወድቅ ገልጸዋል፡፡

ስለ ዓለም ባንክ፣ የዓለም የገንዘብ ድርጅትና የዓለም የንግድ ድርጅት ወቅታዊ ጉዳይ ሕዝብ ዘመም አቀንቃኝነት ወይም ፖፑሊስት አራማጆች በምዕራቡ ዓለም ከመምጣታቸው አኳያ ለወደፊቱ ኢትዮጵያ ምን ይጠብቃታል? ምንስ ልትጠቀም ትችላለች? ለሚለው ጥያቄም ምላሽ ሰጥተዋል፡፡

‹‹ፀረ የዓለም ባንክ አቋም እንዳለው ሰው አትመልከቱኝ እንጂ የዓለም ባንክ ባይኖር እንኳ ኢትዮጵያ ምንም የምታጣው ነገር የለም፤›› ያሉት ፕሮፌሰሩ፣ እነዚህ ተቋማት የነበራቸውን አስፈላጊነት በአሁኑ ወቅት እንዳጡት፣ ምናልባትም በቀውስ ውስጥ የሚገኙ እንደ አርጀንቲና ያሉ ጥቂት አገሮች አሁንም ድረስ የዓለም ባንክ አሊያም የዓለም የገንዘብ ድርጅት ትልቅ ጠቀሜታ ሊሰጧቸው እንደሚችሉ አብራርተዋል፡፡ ‹‹የዓለም የገንዘብ ድርጅት ቀውስ ላይ አተኩሮ የሚሠራ ተቋም ነው፡፡ ከእሱ ጋር አለመሥራት ግን አሳዛኝ ክስተት አይሆንም፤›› ብለውታል፡፡